ሙስሊሞች በኢየሱስ ያምናሉ? ክርስቲያኖችም በሙሐመድ ያምናሉ!

ሙስሊሞች በኢየሱስ ያምናሉ? ክርስቲያኖችም በሙሐመድ ያምናሉ!

የሙስሊሞችን ሙግት መሠረተ ቢስነት የሚያስረዳ ምሳሌ

ሙስሊም ወገኖች በኢየሱስ እንደሚያምኑና አንድ ሙስሊም በኢየሱስ ካላመነ ሙስሊም ተብሎ ሊጠራ እንደማይችል ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ዒሳ በዘንባባይቱ ዛፍ ስር የተወለደ፣ ለሙሐመድ መንገድን ለመጥረግ የመጣ፣ ነቢይ ብቻ የነበረ፣ ሙስሊም የነበረ፣ ሐዋርያቱም ሙስሊሞች የነበሩ፣ ሳይሰቀል ወደ ሰማይ ያረገና መስቀልን ለመሰባበር፣ አሳማዎችን ለመግደልና ክርስትናን ለማጥፋት ወደ ምድር ተመልሶ የሚመጣ መሆኑን እንደሚያምኑ ይነግሩናል፡፡ ይህ ትራኬ ስለ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈውና በታሪክ ከታወቀው እውነታ ጋር እንደሚጣረስ ስንነግራቸው  የኢየሱስን ታሪክ ጳውሎስ የተባለ ሰው ስለበረዘው እንጂ እውነቱ በቁርኣን ውስጥ ከተጻፈው የተለየ እንዳልሆነ ይነግሩናል፡፡

ይህ እምነት “ዐፄ ቴዎድሮስ የተባለ አሣ አስጋሪ በጂንካ ምድር ተወልዶ አርባምንጭ ሄዶ በአዞ ተበልቶ ሞተ” ብሎ የዐፄ ቴዎድሮስን ታሪክ የማጣመም ያህል ነው፡፡ የትኛውንም የታሪክ ድርሳን ብናገላብጥ ዐፄ ቴዎድሮስ ጂንካ ውስጥ አልተወለዱም፣ ሥራቸውም አሣ ማስገር አልነበረም፣ ወደ አርባምንጭም አልሄዱም የሞቱትም በአዞ ተበልተው አይደለም፡፡ በዐይን ምስክሮችና በታሪክ መዛግብት ከተረጋገጠው በተጻራሪ እንዲህ ባለ መንገድ ታሪክን ማጣመም የሚቻል ከሆነ ክርስቲያኖች የሙሐመድን ታሪክ ቀጥሎ በተቀመጠመው መንገድ በማጣመም ቢያቀርቡ የሙስሊሞች ምላሽ ምን ይሆን?

በቁርኣን፣ በሐዲሳትና በሲራ ውስጥ የሚገኙት የሙሐመድ ታሪኮች በሙስሊም ሊቃውንት ስለተበረዙ እንጂ ሙሐመድ በወጣትነቱ በሀገረ የመን ወንጌል ተመስክሮለት ክርስቲያን የሆነ፣ በኋላም ወንጌልን በአረብ በተለይም በመካና በመዲና ያስፋፋ፣ የኢየሱስን ሁሉን ቻይነት ያስተማረ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በወዳጆቹ ወደ አረብኛ ያስተረጎመና በክርስቶስ ላይ ስለነበረው እምነት ሰማዕት ሆኖ በፋርስ ወታደሮች አንገቱን የተሰየፈ ፅኑ ክርስቲያን ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ሞት በኋላ ኻሊፋ ነኝ ብሎ የተነሳው ኡሥማን ሙሐመድ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በመቀየር፣ የጻፋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች በሙሉ አንድ ላይ ሰብስቦ በማቃጠል፣ በሙሐመድ ስብከት ያመኑ ክርስቲያኖችን በማሳደድና ከአገር በማባረር ቁርኣን የሚባል አዲስ መጽሐፍና እስልምና የሚባል አዲስ እምነት መሥርቷል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሙሐመድ በሥላሴ የሚያምን ፅኑ ክርስቲያን ነበር፡፡

ትክክለኛ ስሙ እንዲያውም አብድ አል-መሲህ (የመሲሁ ባርያ) የሚል እንጂ “ሙሐመድ” አልነበረም፡፡ “ሙሐመድ” ማለት “የተመሰገነ” ወይም “ምስጋና የተገባው” የሚል ነው፡፡ ከአንዱ አምላክ በስተቀር ምስጋና የተገባው ማን አለ? ይህ በራሱ የሙሐመድ (አብድ አል-መሲህ) ታሪክ ስለመበረዙ አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡

ኡሥማንና ተባባሪዎቹ የዚህን ቅዱስ ሰው ታሪክ ለማጉደፍ ያልፈበረኩት የታሪክ ዓይነት የለም፡፡ ለምሳሌ ያህል “ገብርኤል በተገለጠለት ጊዜ ከምድር ጋር አጣብቆ እንደ ጠቦት ግመል አረፋ አስደፍቆታል” በማለት በሐዲሳትና በሲራ ውስጥ ጽፈዋል፡፡ ይህ ሙሐመድን “ሰይጣን ይዞት ነበር” ለማስባል የተፈበረከ ታሪክ ነው፡፡ ከዚህም አልፈው ድግምት ተሠርቶበት ሚስቶቹ በሌሉበት ቦታ ከሚስቶቹ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈፀመ እንዳለ ይመስለው እንደነበር ጽፈውበታል፡፡ ኡሥማንና ተባባሪዎቹ የሙሐመድን ስም ለማጉደፍ ያልፈበረኩት ታሪክ ምን አለና! ከ9 ዓመት ህፃን ጋር ወሲብ እንደፈፀመ ሁሉ ጽፈውበታል፡፡ ነፍሰ ገዳይና ጨፍጫፊም አስመስለውታል፡፡ የሰው ዐይን በጋለ ብረት ጎልጉሎ የሚያወጣ፣ እጅና እግር የሚቆርጥ በቀለኛና ክፉ ሰው አስመስለው ስለውታል፡፡ ትምሕርቶቹንም ከቀደሙት ነቢያት ትምሕርቶች ጋር እንዲጋጭ አድርገው በርዘውታል፡፡

ቁርኣን፣ ሐዲሳትና የሲራ መጻሕፍት በሙሉ ከኸሊፋው በኋላ የተጻፉ የተበረዙ መጻሕፍት ስለሆኑ አንቀበላቸውም፡፡ በተለይም ደግሞ ኡሥማን ቀደም ሲል የነበሩትን ጽሑፎች ሰብስቦ ማቃጠሉ የሙሐመድን ትክክለኛ ታሪክ ለማጥፋት ያደረገው ሸፍጥ መሆኑ ግልፅ አይደለምን?

ይህ ምሳሌ የሙስሊሞች ሙግት ምን ያክል መሠረተ ቢስ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱ እምነት ከእውነት የራቀና ማስረጃ የሌለው መሆኑን እናውቃለን፡፡ ዳሩ ግን ሙስሊሞች ስለ ኢየሱስ እናምናለን በሚሉት መንገድ ከተኬደ የገዛ እምነታቸው ሐሰትና ፈጠራ መሆኑን ሳያረጋግጡ ከእንዲህ ዓይነቱ አጣብቂኝ የሚወጡበት መንገድ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፡፡

የኢየሱስ መሰቀልና መሞት፣ በዕለቱም የተከሰቱ ተዓምራት (የፀሐይ መጨለምና የምድር መናወጥ) በክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ባልሆኑ የግሪክና የአይሁድ የታሪክ ጸሐፊያንም ጭምር ተዘግበው ይገኛሉ፡፡ በዘመኑ የነበሩት ጸሐፊያን የሰጡትን ምስክርነት በመካድና ክርስቲያኖችን በብረዛ በመወንጀል ምንም ዓይነት ማስረጃና ማረጋገጫ የሌለውን የቁርኣንን የፈጠራ ታሪክ የተቀበሉት ሙስሊም ወገኖች በሙሐመድ ታሪክ ላይ ተመሳሳይ ተግባር ቢፈጸምና እነርሱም በብረዛ ቢወነጀሉ የሚቃወሙበት ሃቀኛ ሚዛንና ግብረ ገባዊ መሠረት የላቸውም፡፡

መልዕክት ለሙስሊም ወገኖች

በአባይ ሚዛን መጠቀማችሁ የቆማችሁበት መሠረት ዐለት ሳይሆን አሸዋ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ለእውነት ግድ የሚላችሁ ከሆነ ክርስትናን በምትመዝኑበት ሚዛን እስልምናንም ለመመዘን ዝግጁዎች መሆን ያስፈልጋችኋል፡፡ ለእውነት እውነተኞች ሁኑ! እውነትን ካገኛችሁ ለመቀበል አታቅማሙ፡፡ እውነት ደግሞ የነፍሳችሁ ቤዛ የሆነው፣ ስለ እናንተ ነፍሱን አሳልፎ የሰጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡  እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐንስ 14፡6)

ከገሃነም ፍርድ ሊያድናችሁ የሚችለው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ማናችንም ብንሆን የዘለዓለም ሕይወት ሊኖረን አይችልም፡፡ ስለዚህ ወደ ነፍሳችሁ ጌታና ወደ ፈጣሪያችሁ ወደ ኢየሱስ ኑ!

መልዕክት ለክርስቲያኖች

ሙስሊም ወገኖች ሙግታቸው ትክክል እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ውጤታማው መንገድ የገዛ ሙግቶቻቸውን በሃይማኖታቸው ላይ መጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል “ሥላሴ የሚል ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥታችሁ አሳዩን” ብለው ሲጠይቁ “ተውሒድ የሚል ቃልና ሦስቱ ክፍሎቹ የተጠቀሱበትን ከቁርኣን አሳዩን” ብሎ መጠየቅ፤ የነቢያትና የሐዋርያትን ምስክርነት በማጣጣል “ኢየሱስ በራሱ አንደበት አምላክ ነኝና አምልኩኝ ያለበትን አሳዩን” ብለው ሲጠይቁ በተመሳሳይ ዒሳ በቁርኣን ውስጥ “እኔ መሲህ ነኝ፣ ከድንግል ነው የተወለድኩት፣ ጌታ አይደለሁም፣ አልሰቀልም” ያለበትን ቦታ እንዲያሳዩን መጠየቅ፣ ወዘተ.፡፡ ሙስሊሞች የታሪክ መዛግብትንና ቅዱሳት መጻሕፍትን በፈለጉበት መንገድ እየተረጎሙና እያጣመሙ፣ እጅግ የከረሩ መስፈርቶችን እየተጠቀሙ የገዛ መጻሕፍታቸውን ግን እንደ አይነኬ በመቁጠር ከምርመራ ነፃ እንዲሆኑ ዕድል መስጠት የለብንም፡፡

————

ለበለጠ መረጃ

I believe in Mohammad Dr. David Wood

“የት እንደተጻፈ አሳዩን” – ሙስሊም ሰባኪያን በቆፈሩት ጉድጓድ ሲወድቁ

እስልምናና የመሲሁ ስቅለት

ሙስሊሞች የኢየሱስን አምላክነት የማይቀበሉበት ድብቅ ምክንያት

መሲሁ ኢየሱስ