እስልምናና የመሲሁ ስቅለት
እስልምናና ክርስትና በመሲሁ ስቅለት ላይ ያላቸው አቋም ፍፁም ሊታረቅ የማይችል ነው፡፡ የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የመጽሐፍ ቅዱስ አንኳር ማጠንጠኛ ቢሆንም ነገር ግን ይህ እውነት በሙስሊሞች ወገን የከረረ ተቃውሞ ሲሰነዘርበት ኖሯል፡፡ የዛሬ 2000 ዓመታት ገደማ የተከሰተው ይህ ክስተት ግን ቀደም ሲል በነበሩ ነቢያት የተተነበየና በዓይን ምስክሮች ዘገባ የበለፀገ ታሪካዊ ክስተት ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የኢሳይያስ 53 ትንቢትና የስቅለቱ ትክክለኛ ጊዜ በግልፅ የተተነበየበትን የዳንኤል 9፡25-26 ትንቢት መጥቀስ እንችላለን፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸውና ብሉይ ኪዳን ደግሞ በአይሁድም እጅ ጭምር ስለሚገኝ ክርስቲያኖች የጨመሯቸው ሐሳቦች ሊሆኑ ከቶ አይችሉም፡፡
አይሁድ “የናዝሬቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱ መሲሁ አለመሆኑን ያረጋግጣል” የሚል አቋም አላቸው፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችና አጠቃላዩ የብሉይ ኪዳን አስተምህሮ መሲሁ የሰው ልጆች ከዘለዓለም ጥፋት ይድኑ ዘንድ ነፍሱን አሳልፎ እንደሚሰጥ በማያሻማ ሁኔታ የሚያሳዩ በመሆናቸው ክርስቲያኖች ከአይሁድ በተፃራሪ የናዝሬቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱ የነዚህ ትንቢቶች ፍፃሜ በመሆኑ መሲሁ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ያምናሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በኖረበት ዘመን አካባቢ የነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት የነበራቸው የታሪክ ጸሐፊያንም ቢሆኑ የመሲሁን መሰቀል በማያሻማ ቃል ዘግበውት አልፈዋል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡-
ሮማዊ ባለ ስልጣን እና ጸሐፌ ታሪክ የነበረው ቆርኖሌዎስ ታሲተስ (56-117 ዓ.ም.) ክርስቶስን እና ክርቲያኖችን በተመለከተ እንደሚከተለው ጽፏል፡-
ይህንን ስም ያስገኘው ክርስቶስ ጢባሪዮስ ቄሣር ንጉሥ በነበረበት ዘመን ወኪል አስተዳዳሪ በነበረው በጳንጢዮስ ጲላጦስ ትእዛዝ ተገድሏል፡፡[1]
ታሲተስ የጻፈው ታሪክ አውዱ የአዕምሮ መታወክ ችግር የነበረበት ንጉሥ ኔሮ የሮም ከተማ እንድትቃጠል ትዕዛዝ የሰጠው ራሱ ሆኖ ሳለ ወንጀሉን በክርስቲያኖች ላይ እንዳላከከ የሚናገር ነው፡፡ ከአጻጻፉ እንደምንረዳው የአረማውያንን አማልክት ባለማምለካቸው የተነሳ ታሲተስ ክርስቲያኖችን በመጥላቱ ምክንያት መጥፎ ስሞችን የሰጣቸው ቢሆንም ነገር ግን ክርስቶስን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የሚያረጋግጡ ነጥቦችን ጠቅሷል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተናገረው ክርስቶስ በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን የይሁዳ ገዢ በነበረው በጳንጢዮስ ጲላጦስ ትዕዛዝ መገደሉ እና ክርስቲያኖች ስያሜያቸውን ከእርሱ ማግኘታቸው የታሪክ እውነታ ነው ማለት ነው፡፡ ታሲተስ ክርስቲያኖችን የሚጠላ ሰው እንደ መሆኑ መጠን ክርስቶስ መሰቀሉን የሚናገረው የክርስቲያኖች እምነት አንደንዶች እንደሚሉት የፈጠራ ታሪክ ቢሆን ኖሮ እነርሱን ከማጋለጥ ይልቅ እነርሱን ሊደግፍ የሚችል ነገር እንደማይጽፍ ግልፅ ነው፡፡ የታሲተስ ምስክርነት የክርስቶስ ስቅለት በወቅቱ በነበሩ ሕዝቦች ዘንድ የታወቀ ታሪካዊ ክስተት ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮሪዮን) በመባል የሚታወቀው የአይሁድ እና የሮም ታሪክ ጸሐፊ በ93-94 ዓ.ም. በጻፋቸው ሁለት መጽሐፍቱ ውስጥ ክርስቶስን ጠቅሶታል፡፡ በአንደኛው ውስጥ እንዲህ በማለት ስለ ይናገራል፡-
“በዚህ ጊዜ ሰው ብሎ እርሱን መጥራት ተገቢ ከሆነ ኢየሱስ የተባለ ጥበበኛ ሰው ነበር፤ የድንቅ ሥራዎች አድራጊ፣ እውነትን በደስታ የሚቀበሉ አይነት ሰዎች መምህርም ነበር፡፡ ከአይሁድ እና ከአሕዛብ ብዙዎችን ወደ ራሱ ሳበ፡፡ እርሱም ክርስቶስ ነበረ፣ እናም ጲላጦስ ከኛው መካከል ታላላቆች የሆኑቱ በሰጡት አስተያየት እንዲሰቀል ፈረደበት፡፡ በሦስተኛው ቀን ሕያው ሆኖ ስለታያቸው መጀመርያ የወደዱት አልከዱትም ነበር፡፡ ይህም መለኮታዊ መልዕክተኞች የሆኑ ነቢያት እነዚህንና ሌሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ስለ እርሱ እንደተናገሩት ነው፡፡ ከእርሱ ስያሜውን ያገኘው ነገደ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ ከምድረ ገፅ አልጠፋም፡፡” [2]
የባቢሎናውያን ታልሙድ የጥንት አይሁዳውያን ህግጋት፣ ትምህርቶች እና ታሪኮች ስብስብ ነው፡፡ የአይሁድን ትምህርት በመደገፍ የኢየሱስን መለኮታዊነት የሚክድ ቢሆንም ነገር ግን ስቅለቱን በተመለከተ የሚሰጠን ጠቃሚ መረጃ አለ፡-
“በፋሲካ ዋዜማ ዬሹዋ (ኢየሱስ) ተሰቀለ፡፡ ከመገደሉ በፊት 40 ቀናት ቀደም ብሎ አዋጅ ነጋሪ በመውጣት ‘አስማትን በመለማመድ እስራኤልን ወደ ክህደት ስለመራ ይወገራል፡፡ እርሱን በመደገፍ የሆነ ነገር መናገር የሚችል ፊት ለፊት ይውጣና ስለ እርሱ ይሟገት’ በማለት ጮኾ ነበር፡፡ እርሱን የሚደግፍ ምንም ነገር ባለመቅረቡ በፋሲካ ዋዜማ ተሰቀለ፡፡” [3]
ከላይ ባነበብነው የታልሙድ ዘገባ መሰረት የአይሁድ የቀደመ ሐሳብ ኢየሱስን በሕጋቸው መሰረት በድንጋይ በመውገር መግደል ቢሆንም ነገር ግን እነርሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ኢየሱስ በሮማውያን ልማድ መሰረት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቷል፡፡ ይህም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተተነበየው ነው፡፡ ይህ ዘገባ ኢየሱስ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆኑ ተዓምራትን ማድረጉን እና በአይሁድ ፋሲካ ዋዜማ መሰቀሉን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ አስደናቂ ማስረጃ ነው፡፡
የኢስጦኢኮች ፈላስፋ የነበረው ማራ በር-ሴራፒዮን (ማራ ወልደ ሴራፒዮን) በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ የሚከተለውን ደብዳቤ ለልጁ ጽፎ ነበር፡-
“ሶቅራጥስን በመግደል የአቴንስ ሰዎች ምን አተረፉ? ድርቅና ወረርሽኝ ለሰሩት ወንጀል እንደ መቀጣጫ መጣባቸው፡፡ የሳሞስ ሰዎች ፓይታጎረስን በማቃጠላቸው ምን አተረፉ? በቅጽበት መሬታቸው በአሸዋ ተሸፈነ፡፡ አይሁድ ጥበበኛ ንጉሣቸውን በመግደላቸው ምን አተረፉ? ልክ ከዚያ በኋላ መንግሥታቸው አከተመለት፡፡ አምላክ ለነዚህ ሦስት ሰዎች በትክክለኛ ፍረድ ተበቀለለላቸው፡፡ አቴናውያን በረሃብ ሞቱ፡፡ ሳሞሳውያን በባህር ሰጠሙ፡፡ አይሁድ ተፍረክርከው ከምድራቸው ላይ በመባረር ሙሉ በሙሉ ተበትነው ኖሩ፡፡ ነገር ግን ሶቅራጥስ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ በፕላቶ ትምህርት ኖሯልና፡፡ ፓይታጎረስ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ በሄራ ሐውልት ውስጥ ኖሯልና፡፡ ጥበበኛውም ንጉሥ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ ራሱ ባስተማረው ትምህርት ኖሯልና፡፡” [4]
ምንም እንኳ ክርስቶስን በስም ባይጠቅሰውም ጲላጦስ ፊት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ከተመሰረቱበት ክሶች መካከል ‹ራሱን የአይሁድ ንጉስ አደረገ› የሚለው አንዱ በመሆኑ ይህ ፈላስፋ ጥበበኛ ንጉሥ ብሎ የጠራው እርሱን መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ሮማዊው ጄነራል ታይታስ (ቲቶ) ኢየሩሳሌምን የደመሰሰው እና አይሁድ የተበተኑት በ70 ዓ.ም. (ክርስቶስ ከተሰቀለ ከ37 ዓመታት በኋላ) ነበር፡፡ ማራ ወልደ ሴራፕዮን የኖረው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ይህ የእርሱ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ የሚተርከው የክርቶስ ሕይወት እውነት ስለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡
የሁለተኛው ክፍለ ዘመን የግሪክ ጸሐፌ ታሪክ የነበረው ሉሺያን ኢየሱስን “አዲስ ኃይማኖት ወደ ዓለም በማምጣቱ ምክንያት በምድረ ፓለስታይን የተሰቀለ ሰው” ብሎታል፡፡[5] ፍሌጎን የተሰኘ ሮማዊ ጸሐፊ “ኢየሱስ በሕይወት በነበረ ጊዜ ራሱን መርዳት አልቻለም ነበር ነገር ግን ከሞተ በኋላ በመነሳት የመከራውን ምልክት አሳይቷል፤ እጆቹም እንዴት በሚስማር እንደተቸነከሩ አሳይቷል” ሲል ስለ ትንሣኤው ጽፏል፡፡ በኢየሱስ ዘመን በምድር ላይ ስለወደቀው ጨለማና ስለ ምድር መናወጥ ጽፏል፡፡[6]
ከነዚህ በተጨማሪ ከአዲስ ኪዳን ውጪ የኢየሱስ ሞት ተዘግቦ የምናገኘው በጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች ውስጥ ነው፡፡ የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ የክርስቶስን ሞት ደጋግሞ የጻፈ ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከጽሑፎቹ መካከል በአንዱ ውስጥ “ስለ ኃጢአታችን እስከ ሞት ድረስ መከራን የተቀበለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” በማለት አስፍሯል፡፡ የፖሊካርፕ ወዳጅ የነበረው ኢግናጢዎስ በበኩሉ “በእውነት መከራን ተቀብሎ ከሞተ በኋላ ተነስቷል… ጌታችንን የሰቀሉት ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው ሰዎች ነበሩ” በማለት ጽፏል፡፡[7] የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያን ጸሐፊ የነበረው ዮስጦስ ሰማዕትም ትሪፎ ለተሰኘ አይሁዳዊ በሰጠው ምላሽ በእርሱ ዘመን የነበሩት አይሁድ ኢየሱስን “የተሰቀለ ገሊላዊ” በማለት ይጠሩት እንደነበር ጽፏል፡፡[8]
እነዚህ ሁሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች ባሉበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ ቢናገር ስህተት አይሆንምን? የኢየሱስ ስቅለት በብሉይ ኪዳን የተተነበየ፣ በኢየሱስ በራሱ አስቀድሞ የተነገረ፣ በአዲስ ኪዳን የሐዋርያት ምስክርነት የተዘገበ፣ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች የተመሰከረለት እና በአይሁድ እና በአረማውያን ታሪክ ጸሐፊዎች የተረጋገጠ የታሪክ እውነታ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ከኖሩ ታዋቂ ከሆኑ የታሪክ ተመራማሪዎች መካከል የመሲሁን ስቅለት ያስተባበለ ምሁር አልተገኘም፡፡ ይልቅስ የአንደንድ ምሁራን ጥርጣሬ በስቅለቱ ላይ ሳይሆን በትንሣኤው ላይ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በታሪካዊ መስፈርት መሰረት የአዲስ ኪዳን ዘገባ ተቀባይነት በማጣቱ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች በልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል ለማመን የሚቸገሩ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ነው፡፡ በዓለም ላይ ካለ ከየትኛውም እምነት ይልቅ ክርስትና ለተመሠረተበት መሠረት ታሪካዊ ማስረጃ የማቅረብ ብቃት አለው፡፡ ስለዚህ የክርስቲያኖች እምነት አንዳንዶች እንደሚሉት ጭፍን እምነት ሳይሆን በአሳማኝ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ሙስሊም ወገኖቻችን በብዙ ታሪካዊ ማስረጃዎች የበለፀገውን የመሲሁን ስቅለት በማስተባበል “አልተሰቀለም” በማለት ይሞግታሉ፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ትልቁ ማስረጃ በቁርአን ውስጥ በሱራ አል-ኒሳ 4፡157-158 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ስለ ክርስቶስ አለመሰቀል በቀጥታ እንደሚናገር የሚታመን የቁርአን ብቸኛ ጥቅስ ሲሆን እንዲህ ይነበባል፡-
وَقَوْلِهِمْ إِنَّا قَتَلْنَا الْمَسِيحَ عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ رَسُولَ اللَّهِ وَمَا قَتَلُوهُ وَمَا صَلَبُوهُ وَلَٰكِن شُبِّهَ لَهُمْ ۚ وَإِنَّ الَّذِينَ اخْتَلَفُوا فِيهِ لَفِي شَكٍّ مِّنْهُ ۚ مَا لَهُم بِهِ مِنْ عِلْمٍ إِلَّا اتِّبَاعَ الظَّنِّ ۚ وَمَا قَتَلُوهُ يَقِينًا
“«እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን» በማለታቸውም (ረገምናቸው)፡፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ግን ለእነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዚያም በእርሱ ነገር የተለያዩት ከእርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡”
ሙስሊሞች በሙሉ ልብ የተቀበሉት ይህ ብቸኛ ዘገባ የተገኘው ከታሪካዊ ክስተቱ በጊዜም ሆነ በቦታ እጅግ ከራቀ ከአንድ ሰው ነው፡፡ ይህ ክስተት ከተፈፀመ ከስድስት መቶ አመታት በኋላ የኖረ እና ታሪኩ ከተከሰተበት ቦታ ቢያንስ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ የኖረ የቦታውን መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ እንኳ በወጉ የማያውቀውን ሰው ሀሳብ ያለምንም ማስረጃ እንዴት ልንቀበል እንችላለን? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄያችን ሙስሊም ወገኖቻችን የሚሰጡን ምላሽ “በቃ! ይህ አላህ ለነቢዩ የገለጠለት ቃል ነው! ይህንን ለመቀበል ማስረጃ አያስፈልግም!” የሚል አይነት ብቻ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ጭፍን እምነት ይለዋል ይሄ ነው![9] ሙስሊም ወገኖቻችን ለዚህ ቁርኣናዊ ሀሳብ ድጋፍ የሚሰጥ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን እስከ መሐመድ ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፈ አንድ ታሪካዊ ሰነድ ሊጠቅሱልን ይችሉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ግን ሙስሊሞች ይህንን ማድረግ እንደማይችሉ በሙሉ መተማመን ልንናገር እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የመሲሁን መሰቀል እንጂ አለመሰቀሉን የሚደግፍ ምንም አይነት ጥንታዊ የታሪክ ዘገባ የለምና! ከላይ የተጠቀሰው የቁርአን ጥቅስ በራሱ የተሳሳተ ሀሳብ በውስጡ እንደሚገኝ፣ ምሉዕ እንዳልሆነና ለተለያዩ ትርጓሜዎች የተጋለጠ መሆኑን ሙስሊም ወገኖች ሊያውቁት ይገባል፡፡ ይህንንም ሀቅ እንደሚከተለው እንገልጣለን፡፡
በጥቅሱ መሠረት “እኛ የአላህን መልክተኛ የመርያምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን” ባዮቹ አይሁዶች ናቸው፡፡ ነገር ግን እስኪ ቆም ብለን ይህንን አባባል በአንክሮ እናጢን፡፡ በዚህ ቃል መሠረት አይሁዶች ኢየሱስን የአላህ መልእክተኛና አልመሲህ (ክርስቶስ) ብለው ጠርተውታል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ አይሁዶች ኢየሱስን እንደ አምላክ መልእክተኛና እንደመሲህ ተቀብለውት አያውቁም፡፡ ለአንድ አይሁዳዊ የናዝሬቱ ኢየሱስን “የአምላክ መልእክተኛና መሲህ” ብሎ መጥራት ታላቅ ክህደት ነው፡፡ አይሁዶች ኢየሱስን ለሞት አሳልፈው የሰጡት የአምላክ መልእክተኛና እነርሱን ለማዳን የመጣ መሲህ መሆኑን ባለመቀበላቸው አልነበረምን? ታዲያ እንዴት “የአላህ መልክትኛ አል-መሲህ ኢሳን ገደልን” ብለው ሊናገሩ ቻሉ? ይህ ንግግር ከአይሁድ አንደበት ያልወጣ በዘፈቀደ የተነገረ የተሳሳተ ሀሳብ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አይሁዶች ለሃይማኖታቸው ጥንቁቆች በመሆናቸው እንዲህ አይነት ሀሳብ አይናገሩም፡፡ ሁሉን አዋቂ የሆነው አምላክ አይሁድ ኢየሱስን “መልእክተኛና መሲህ” ብለው እንደማይጠሩት ስለሚያውቅ እንዲህ አይነት መገለጥ አያናግርም፡፡
ይህ ጥቅስ በአብዛኞቹ ሙስሊሞች ዘንድ ዒሳ እንዳልተሰቀለ እንደሚናገር ቢታሰብም ነገር ግን ቃል በቃል “ዒሳ አልተሰቀለም” እንደማይል ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለዚህ ነው አሕመዲያን የመሳሰሉት ሙስሊም ቡድኖች እና ታላላቅ የሱኒ ኢስላም አቃቤ እምነታውያን ሳይቀሩ (ለምሳሌ ያህል አሕመድ ዲዳት፣ ዶ/ር ሻቢር አሊ) ዒሳ በመስቀል ላይ መሰቀሉን ነገር ግን አለመሞቱን የሚያስተምሩት፡፡ ብዙ ሙስሊሞች በተርጓሚዎች በቅንፍ ውስጥ የተጨመሩት ጭማሬ ቃላት በአረብኛው ቁርአን ውስጥ እንደማይገኙ ስለማያውቁ ይህ ጥቅስ ዒሳ አለመሰቀሉን በግልፅ እንደሚናገር ያስባሉ፡፡ እነዚህ ጭማሬ ቃላት ሲወጡ ግን የጥቅሱ አሻሚነት ግልፅ ይሆናል፡-
“እኛ አላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው፤ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ነገር ግን ለነሱተመሰለ፡፡ እነዝያ በሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡”
ጥቅሱ በአረብኛ ሲነበብ ዒሳ አለመሰቀሉንም ሆነ በእርሱ ምትክ ሌላ ሰው መሰቀሉን በፍፁም አይናገርም፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው አይሁድ ዒሳን አለመስቀላቸውንና አለመግደላቸውን ነው፡፡ “አልገደሉትም፣ አልሰቀሉትም” የሚሉት ቃላት “አልተገደለም፣ አልተሰቀለም” ተብለው እንዲተረጎሙ የሚያስገድድ ሰዋሰዋዊም ሆነ አውዳዊ ምክንያት የለም፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው አይሁድ ዒሳን አለመግደላቸውንና አለመስቀላቸውን እንጂ ዒሳ በሌሎች ሰዎች አለመሰቀሉንና አለመገደሉን አይደለም፡፡
አይሁድ ኢየሱስን እንዲሰቀል ለሮማውያን አሳልፈው በመስጠታቸው እንደሰቀሉትና እንደገደሉት ቢነገርም ነገር ግን የስቅለት ሂደቱን የፈፀሙት ሮማውያን ናቸው፡፡ በኢየሱስ ዘመን አይሁድ በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ማንንም የመግደል መብትና ሥልጣን አልነበራቸውም፡፡ በመስቀል ላይ ሰቅሎ መግደልም ልማዳቸው አልነበረም፡፡ በዘመኑ በሰዎች ላይ የሞት ፍርድ የማስፈፀም መብትና ሥልጣን የቅኝ ገዢዎቹ የሮማውያን ነበር፡፡ በስቅላት መቅጣትም የእነርሱ ልማድ ነበር፡፡ ስለዚህ የዘመኑ አይሁድ ኢየሱስን አሳልፈው በመስጠታቸው ለስቅለቱና ለሞቱ ተጠያቂዎች ቢሆኑም ድርጊቱን ቃል በቃል የፈፀሙት ቅኝ ገዢዎቻቸው ሮማውያን እንጂ እነርሱ ባለመሆናቸው በዚህ ረገድ ከታሰበ አይሁድ አልገደሉትም፤ አልሰቀሉትም፡፡ ነገር ግን የታሪክ መዛግብት እንደሚናገሩት ሮማውያን ሰቅለውታል፡፡ ከሙታን ተነስቶም ወደ ሰማይ ሄዷል፡፡
ይህ ጥቅስ በሌላ መንገድም ሊተረጎም ይችላል፡፡ አይሁድ ዒሳን ቃል በቃል ሰቅለውታል፤ ገድለውታል ብንል እንኳ ቁርአን “አልገደሉትም አልሰቀሉትም” በማለት መናገሩ አለመገደሉንና አለመሰቀሉን የማያሳይበት አንድ ግልፅ ምክንያት አለ፡፡ አይሁድ ዒሳን ቢሰቅሉትና ቢገድሉትም ነገር ግን ይህንን ተግባር እንዲፈፅሙ የፈቀደው አላህ በመሆኑ እነርሱ የገደሉትና የሰቀሉት ቢመስላቸውም ነገር ግን በራሳቸው ሥልጣንና ኃይል ያንን ባለመፈፀማቸው አልገደሉትም አልሰቀሉትም፡፡ ይህንን ትርጓሜ ይበልጥ ግልፅ የሚያደርግልን ሐሳብ በቁርአን 8፡17 ላይ ይገኛል፡- “አልገደላችኋቸውም ግን አላህ ገደላቸው፡፡ (ጭብጥን ዐፈር) በወረወርክም ጊዜ አንተ አልወረወርክም፡፡ ግን አላህ ወረወረ (ወደ ዓይኖቻቸው አደረሰው)፡፡”
በዚህ ጥቅስ መሰረት ሙስሊሞች ጠላቶቻቸውን ቢገድሉም ነገር ግን “በአላህ ፈቃድ” ያንን ስላደረጉ እነርሱ አልገደሏቸውም ነገር ግን አላህ ገደላቸው፡፡ ጠላቶቻቸውን ለማሳወር መሐመድ አፈርን በወረወሩ ጊዜ “በአላህ ፈቃድ ስለወረወሩ” እርሳቸው አልወረወሩም ነገር ግን አላህ ወረወረ፡፡ ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው ነገር ቢኖር ሰዎች በአላህ ፈቃድ የሆነ ነገር ቢፈፅሙ ነገሩን እነርሱ እንደፈፀሙት ሳይሆን አላህ እንደፈፀመው እንደሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ በተመሳሳይ መንገድ አይሁድ ዒሳን ቢሰቅሉትና ቢገድሉትም ነገር ግን በአላህ ፈቃድ እንጂ በራሳቸው ፈቃድና ሥልጣን ያንን ስላላደረጉ “አልገደሉትም፣ አልሰቀሉትምም” ስለዚህ በትዕቢት “ገድለነዋል” በማለት መናገራቸው ትክክል አይደለም፡፡ ይህንን ትርጓሜ ከተከታዮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ማነፃፀር ይቻላል፡- የሐዋርያት ሥራ 2፡23-24፣ 3፡18፣ 4፡27-28፣ 1ጴጥሮስ 1፡19-20፣ ራዕይ 13፡8፡፡
በኢየሱስ ፋንታ ሌላ ሰው እንደተሰቀለ የሚያምኑት ሙስሊሞች ሱራ 4፡157 የራሳቸውን ትወራ የሚደግፍ ለማስመሰል ቃላትን በቅንፍ ውስጥ በመጨመር እንደተረጎሙት ሁሉ ከላይ የተቀመጡትን ሁለት ትርጓሜዎች እንዲደግፍ ለማድረግ በሚከተሉት መልኩ መጻፍ ይቻላል፡-
“እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (አይሁድ ዋሽተዋል)፤ አልገደሉትምአልሰቀሉትምም ነገር ግን (ሮማውያን ያደረጉት) ለነሱ ተመሰለ፡፡ እነዝያ በሱ ነገር የተለያዩት (ሙስሊሞች) ከርሱ በመጠራጠርውስጥ ናቸው፡፡ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም (አይሁድ) አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ (ሮማውያን ከገደሉት በኋላ) አላህ ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡”
ወይም፡-
“እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (አይሁድ ተሞኙ)፤ አልገደሉትም አልሰቀሉትምምነገር ግን (አላህ በፈቃዱ ያደረገው) ለነሱ ተመሰለ፡፡ እነዝያ በሱ ነገር የተለያዩት (ሙስሊሞች) ከርሱ በመጠራጠር ውስጥናቸው፡፡ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም (አይሁድ) አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ (በፈቃዱ ከተገደለ በኋላ) አላህ ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡”
እንግዲህ ይህንን አሻሚና ለብዙ ትርጉሞች የተጋለጠ ጥቅስ ነው ሙስሊሞች የመሲሁን ስቅለት ለማስተባበል እንደ ማስረጃ የሚጠቅሱት፡፡
ዒሳ እንደተሰቀለ ነገር ግን በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ እንዳልሞተና ራሱን እንደሳተ የሚናገር ትወራ በአሁኑ ወቅት በተለይም በተማሩት ሙስሊሞች ዘንድ በስፋት ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡ ይህ አስተሳሰብ “ራስን የመሳት ትወራ” (Swoon Theory) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቬንቹሪኒ በተሰኘ ሰው በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የተጀመረ ነው፡፡ ግንባር ቀደም ሙስሊም አቃቤ እምነት የነበሩት ሼኽ አሕመድ ዲዳት[10] እና የዘመናችን ስመጥር ተሟጋች የሆኑት ዶ/ር ሻቢር አሊን[11] የመሳሰሉት ሙስሊሞች ያቀነቅኑታል፡፡ ከእስላማዊ ቡድኖች መካከል የኔሽን ኦፍ ኢስላም (NOI) እና የአሕመዲያ ጎራዎች እንደ እምነት አቋም ይዘውታል፡፡ ይህንን አቋም የሚያራምዱት ሙስሊም አቃቤ እምነታውያንም ሆኑ ቡድኖች ሱራ 4፡157 ላይ የሚገኘውን ቃል ከላይ ባስቀመጥናቸው ሁለት መንገዶች መተርጎማቸው ብዙ የአገራችን ሙስሊሞች የማይገምቱት ሃቅ ነው፡፡ ከላይ የተቀመጡትን ትርጓሜዎች የሚቃወሙ ሙስሊሞች ክርክራቸው ከኛ ጋር ሳይሆን ከገዛ የእምነት ወንድሞቻቸው ጋር ነው የሚሆነው!
ዒሳ ሳይሞት ወደ ሰማይ አርጓል የሚለው ትምህርት በሙስሊሙ ዓለም ውስጥ ለዘመናት ተቀባይነትን አግኝቶ ኖሯል፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች በስቅለቱ ወቅት ስለነበረው ሁኔታና በኢየሱስ ምትክ ተሰቀለ ብለው ስለሚያስቡት ሰው ማንነት በታሪክ አንድ ሆነው አያውቁም፡፡ ከላይ እንዳየነው በምትኩ የተሰቀለው ሰው ማን እንደሆነ ቁርአን በፍፁም አይናገርም፡፡ ስለዚህ ይህንን በተመለከተ ያለው የእስልምና ትምህርት በግምት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሙስሊም ምሁራንን ለክፍፍል ዳርጓል፡፡ አንዳንዶች ከአይሁድ መካከል አንዱ ተሰቅሏል በማለት ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ የተሰቀለው ከሮማውያን ወታደሮች መካከል አንዱ ነው ይላሉ፡፡ ከዒሳ ተከታዮች መካከል አንዱ በፍቃደኝነት መሞት ስለፈለገ አላህ የዒሳን መልክ ሰጥቶት ተሰቀለ የሚሉም አሉ፡፡ ‘‘የበርናባስ ወንጌል’’ በሚል ስም በመካከለኛው ዘመን በአንድ ሙስሊም የተጻፈ መጽሐፍ ደግሞ በምትኩ የሞተው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው ይላል፡፡ ነገር ግን ለነዚህ ሁሉ እስላማዊ መላምቶች ድጋፍ የሚሰጥ አንድ ጥቅስ እንኳ በቁርኣን ውስጥ አይገኝም፡፡ ቁርኣን እንኳንስ በምትኩ ሞተ የተባለውን ሰው ስም ሊጠቅስ ይቅርና ሌላ ሰው ስለመሞቱ እንኳ ፍንጭ አይሰጥም፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅነው “…ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ” በሚለው ሐረግ ውስጥ በቅንፍ የተቀመጠው “የተገደለው ሰው በዒሳ” የሚለው ሀሳብ በተርጓሚዎቹ የተጨመረ እንጂ በአረብኛው ቁርኣን ውስጥ አይገኝም፡፡
በዒሳ ምትክ ሌላ ሰው ተሰቅሏል የሚለው የሙስሊሞች መላምት “Substitution Theory” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህ መላምት ሊያስከትላቸው ከሚችላቸው ጥያቄዎች መካከል የተወሰትን እንደሚከተለው እናነሳለን፡-
- ይህ ሀሳብ ከታሪካዊ ዘገባዎች ጋር ይጋጫል፡፡ በየትኛውም የታሪክ ዘገባ ድጋፍ የለውም፡፡ የታሪክ መዛግብትን በአንድ ሰው “መገለጥ” መሻር ጭፍን እምነት አይሆንምን?
- አላህ ዒሳን ምንም ሳይሆን ዝም ብሎ ወደራሱ መውሰድ ከቻለ በእርሱ ምትክ ሌላ ሰው እንዲገደል ማድረጉ ጥቅሙ ምንድነው?
- በዒሳ ቦታ ሌላ ሰው እንዲሰቀል አላህ ሁኔታዎችን ባያመቻችና የሰውየውን መልክ ከዒሳ መልክ ጋር ባያመሳስል ኖሮ ተሰቅሏል የሚል ትምህርት ባልተስፋፋ ነበር፡፡ ታዲያ አላህ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሕይወት አያሳዝነውምን? ስለምን ይህን ሁሉ የማስመሰል ሥራ በመሥራት ክርስትና እንዲፈጠር አደረገ?
- የዒሳ መልክ የተመሳሰለው ለጠላቶቹ ብቻ ወይንስ ለወዳጆቹም ጭምር? ለሁለቱም ወገኖች ከሆነ አላህ ተከታዮቹ የነበሩትን አማኞች በማታለል ማሳሳት ለምን አስፈለገው? ለጠላቶቹ ብቻ ከሆነ ከወዳጆቹ መካከል አንዱ እንኳ አለመሰቀሉን ስለምን አልዘገበም?
- በዒሳ ምትክ ተሰቀለ የተባለው ሰው በመስቀል ላይ በነበረበት ጊዜ ሲመለከቱ የነበሩ የዓይን ምስክሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ታዲያ እነዚህ ከጠላቶቹ ወገን ያልነበሩ ሰዎች የተሰቀለውን ሰው ሲመለከቱ የሚታያቸው የዒሳ መልክ ወይንስ የሰውዬው መልክ? የዒሳ መልክ ከሆነ ስለ ስቅለቱ ትዕይንት ሊመሰክሩ የሚችሉት ዒሳ መሰቀሉን ነው፡፡ ነገር ግን የተሰቀለው ሌላ ሰው ስለሆነ ምስክርነታቸው ሀሰት ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በማያውቁት ሁኔታ ሀሰትን በመመስከር ተሳስተው ሌሎችንም በምስክርነታቸው እንዲያሳስቱ ያደረገውን ይህንን የማታለል መንገድ ለመጠቀም አላህ ስለምን መረጠ? አላህ ሁሉን ቻይ አይደልምን? ስለምን ለብዙዎች መጥፋት ምክንያት የሆነውን ይህንን መንገድ ተጠቀመ? ማንንም ሳያታልልና ሳያሳስት ዒሳ እንዳይሰቀል ማድረግ አይችልም ነበርን?
- ቁርኣን ሁሉን ነገር ግልፅ ለማድረግ የወረደ ከሆነ ስለምን በዒሳ ቦታ የተሰቀለውን ሰው ማንነት በመጥቀስ እንዲሁም ዒሳ አለመሰቀሉን አሻሚ ባልሆነ ቋንቋ በመናገር ሙስሊሞችን ከመከፋፈል አልታደገም?
- ቁርአን ሁሉን ነገር ግልፅ ለማድረግ የመጣ መጽሐፍ ነው ከተባለ ብዙዎች “የተሳሳቱበትን” ይህንን ትልቅ ጉዳይ ግልፅ ከማድረግ ይልቅ አሻሚ በሆነ ንግግር በማቅረብ እና ያልተሟላ መረጃን በመስጠት እውነተኛ መገለጥ መሆኑን ያመኑትን ሰዎች ሳይቀር ግራ መጋባት እና ክፍፍል ውስጥ ማስገባቱ እንዴት ይታያል? በዚህ ሁኔታ ሁሉን ነገር ግልፅ ለማድረግ መምጣቱንስ መቀበል ተገቢ ነውን? ሁሉን ነገር ግልፅ የሚያደርግ መጽሐፍ መሆኑን መናገሩስ ውሸት አይሆንምን?
- የዒሳ ተልዕኮ ስለ ፈጣሪ እውነተኛውን ነገር ማስተማር ከነበረ፤ በብዙ ተዓምራት የፈጣሪን ክብር ሲገልጥ ከቆየ በኋላ በመጨረሻው ሰዓት “በመስኮት ሾልኮ በመጥፋት” ዓለምን ሁሉ ግራ መጋባት እና ውዥንብር ውስጥ በመክተት፤ ብዙዎች መሞቱን እንዲያምኑ አድርጎ ሀሰተኛ ትምህርት እንዲያስፋፉ ምክንያት መሆኑ ተገቢ ነበርን? ተልዕኮው ዓለምን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዳ ከነበረ ወደ ዓለም መምጣቱ ትክክል ነበርን?
- አንድ ነቢይ ስለ እምነቱ መስዋዕት ሆኖ ለአማኞች የፅናት ተምሳሌት ከመሆንና ሰዎችን ውዥንብር ውስጥ በመክተት በመስኮት ሾልኮ ከመጥፋት የትኛው የተሻለ ነው?
- አላህ ዒሳን የሚወደው ከሆነ ሰማዕት በመሆን ተልዕኮውን ከግብ እንዲያደርስ ከማድረግ ይልቅ በመስኮት አሾልኮ እንዲሰወር በማድረግ ተልዕኮው እንዲከሽፍ ስለምን አደረገ?
- ዒሳ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ካመኑ አላህ ለዒሳ ይህንን ሁሉ ውዥንብር በመፍጠር ለብዙዎች መጥፋት ምክንያት ሆኖ ወደ ሰማይ ከመሄድ እና እንደ ሌሎቹ ነቢያት ሰማዕት በመሆን ተልዕኮውን ከክሽፈት በመታደግ መካከል ቢያስመርጠው የትኛውን የሚመርጥ ይመስልዎታል?
- አላህ የአንዱን የዒሳን ሕይወት ከጊዜያዊ ሞት ለማትረፍ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ወደ ዘለዓለም ጥፋት የሚወስድ ተግባር መፈፀሙ ስለ አላህ የማስላትና የማገናዘብ ችሎታ ምን ይላል?
- ነቢዩ መሐመድ ይህንን “መገለጥ” ይዘው የመጡት ነገሩ ከተከሰተ ከ 600 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች የኢየሱስን መሰቀል በማመን አልፈዋል፡፡ በዚሁም ሳብያ ብዙዎች እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ታዲያ አላህ ይህን ያህል አመታት በመዘግየት “መገለጡን” ከሚልክ ወዲያውኑ በወቅቱ ቢልክ ኖሮ ብዙዎችን ከጥፋት ለማዳን የተሻለ መንገድ አይሆንም ነበርን? ለነዚያ ለጠፉ ህዝቦች ሕይወትስ ተጠያቂው ዒሳ የተሰቀለ በማስመሰል ያታለላቸውና ያሳሳታቸው ራሱ አላህ አይሆንምን?
- መገለጡን ይዘው የመጡት “ነቢዩ” ሕይወታቸውን ስንመዝን ለነቢይነት የሚያበቃና ምሳሌያዊ የሚሆን ምንም ነገር የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ያህል የ6 ዓመት ህፃን አጭተው በ9 ዓመቷ አብረዋት ተኝተዋል፡፡[12]የማደጎ ልጃቸውን ሚስት እንደተመኟት በአደባባይ ተናግረዋል፤ ስለ ውበቷ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በማውራትም ትዳሯን ካናጉ በኋላ አግብተዋታል፡፡[13] በአንድ ወቅት አስማት ተሰርቶባቸው ሲሰቃዩ ነበር፡፡[14] ሙስሊም ወታደሮች ምርኮኛ ሴቶችን ባሎቻቸው በሕይወት እያሉ እንዲደፍሩ ፈቅደዋል፡፡[15] በቀልና ጥላቻን አስተምረዋል፡፡[16] ታድያ እንዲህ ዓይነት የስነ ምግባር ጉድለት የነበረባቸው ሰው ቅዱሳን ሐዋርያ እንከን አልባ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማሩት ትምህርት እና የመሰከሩት ምስክርነት ስህተት መሆኑን ለመናገር ብቃት አላቸውን? የመሐመድን ምስክርነትስ ከሐዋርያት ምስክርነት በላይ እውነት አድርጎ መቁጠር ምክንያታዊ ነውን?
- አላህ የዒሳን መሰቀል በተመለከተ ዓለምን ሁሉ ማታለሉ ስለ ባሕርዩ ምንን ያመለክታል? ማታለልና ማጭበርበርስ የእውነተኛው አምላክ ባሕርይ ነውን?
ከላይ የቀረቡት ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ እስካልተመለሱ ድረስ ለአንድ ክርስቲያን በኢየሱስ ቦታ ሌላ ሰው ተሰቅሏል ብሎ ማመን እውነትን በሀሰት መለወጥ ነው!
በቁርኣን ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል ተፅፎ እናገኛለን፡- “ዒሳ ሆይ እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፡፡” (3፡55)፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው “ወሳጂህ” የሚለው ቃል በአረቢኛ “ሙተወፊከ” ከሚል ቃል የተተረጎመ ነው፡፡ እውቁ ክርስቲያን ጸሐፊ ጌርሃርድ ኔልስ እንደ አሊ ኢብን አባስ፣ አብዱላህ ኢብን ሙነቢህ፣ ሙአዌህ፣ ኢብን ኢስሃቅ፣ ሳልማህ እና ወሃብ ኢብን ሙነቢህ የመሳሰሉ በርካታ ጥንታዊ ሙስሊም ሊቃውንት ይህንን የቁርኣን ቃል “እንድትሞት አደርጋለሁ” በሚል እንደሚረዱት ይገልፃሉ፡፡[17] ዒሳ ህፃን ሆኖ ሳለ የሚከተለውን ቃል እንደተናገረ ሱራ 19፡33 ላይ እናነባለን፡- “ሰላምም በኔ ላይ ነው በተወለድሁ ቀን በምሞትበትም ቀን ህያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፡፡” ብዙ ሙስሊሞች ኢየሱስ ወደፊት ወደ ምድር ተመልሶ እንደማንኛውም ሰው ይሞታል ከዚያም ይነሳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህንንም ጥቅስ በዚያው መልኩ ይተረጉሙታል፡፡ ነገር ግን የኢየሱስን መሞት የሚያምኑ ሰዎች ይህንን ጥቅስ እንደ አንድ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸው ሀሳብ እዚያው ቁርአን 19፡15 ላይ ይገኛል፡፡ “በተወለደበት ቀንና በሚሞትበትም ቀን ሕያው ሆኖ በሚነሳበትም ቀን ሰላም በሱ ላይ ይሁን”፡፡ ይህ ቃል የተነገረው ለመጥምቁ ዮሐንስ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ መሞቱን ሙስሊሞች ያምናሉ፡፡ ስለዚህ የአንድን የቁርኣን ሀሳብ ትክክለኛ ፍቺ ለመረዳት በሌላ የቁርኣን ጥቅስ ብርሃን ማየት አማራጭ የሌለው መንገድ በመሆኑ እነዚህን ሙሉ በሙሉ የሚመሳስሉ ንግግሮች በአንድ መንገድ መተርጎም ግድ ይላል፡፡
ለኢየሱስ መሞት ድጋፍ የሚሰጥ ሀሳብ በቁርኣን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ውስጥም እናገኛለን፡፡ ሳሂህ አልቡኻሪ ውስጥ እንደተፃፈው አንድ ነቢይ ወገኖቹ ባቆሰሉት ጊዜ “አያውቁምና ህዝቤን ይቅር በላቸው” ብሎ እንደጸለየላቸው መሐመድ መናገራቸውን ኢብን ማሱድ ዘግቧል፡፡[18] በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይህንን ጸሎት እንደጸለየ የተነገረ ሙስሊሞች የሚቀበሉት ነቢይ ማን ነው? መልሱ ሉቃስ 23፡32-48 ላይ ይገኛል፡-
“ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋርይገድሉ ዘንድ ወሰዱ፡፡ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንምበግራ ሰቀሉ፡፡ ኢየሱስም፡– አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ፡፡ ልብሱንም ተከፋፍለው እጣተጣጣሉበት ህዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር፡፡”
ቁርአን በርካታ ቅዱሳን ነቢያት በክፉ አድራጊዎች መገደላቸውን ይናገራል (2፡61፣ 2፡91፣ 321 3፡112 ይመልከቱ)፡፡ ታድያ ሙስሊሞች የኢየሱስን ስቅለት በፅኑ የሚቃወሙት ስለምንድነው? ምናልባት ኢየሱስን የሚያክል ታላቅ ነቢይ በጠላቶቹ እጅ ተዋርዶ ሞተ የሚለው ሐሳብ ለእርሱ ካላቸው አክብሮት አንጻር አልመስል ብሏቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የተሰቀለው ዓለምን ለማዳን በመሆኑ እና ሞትን አሸንፎ በመነሳቱ ምክንያት ስቅለቱ ታላቅ ድል ነው፡፡ ኢየሱስ ሞቶ በዝያው አልቀረም ነገር ግን በሦስተኛው ቀን በመነሳት ጌትነቱን አረጋግጧል! የተርሴሱ ሳውል የኢየሱስን ትንሣኤ በፅኑ ከሚቃወሙ አይሁዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ የጌታንም ደቀመዛሙርት ይገድልና ያስር ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ ሞቶ ቀርቷል ብሎ የሚያስበው የናዝሬቱ ኢየሱስ በደማስቆ ጎዳና ላይ በታላቅ ክብር እና በሚያስፈራ ግርማ ተገለጠለት፡፡ እርሱም ከትንሣኤውን ምስክሮች ጋር አብሮ የትንሣኤውን የምስራች ማወጅ ጀመረ፡፡ በስተሽምግልናውም ኢየሱስን ከመካድ ይልቅ በሮም ከተማ ውስጥ ሰማዕት መሆንን እንደመረጠ በቤተክርስቲያን ታሪክ ተጽፎልናል፡፡ ይህ ሰው በአንድ ወቅት በፊልጵስዩስ ከተማ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ድንቅ መልዕክት ፅፎ ነበር፡-
“በክርስቶስ ኢየሱስ ዘንድ የነበረ ይህ አሳብ በናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፡፡ ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ በምስሉም እንደሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፡፡ ለሞትም ይኸውምለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለልክ ከፍከፍ አደረገው፡፡ ከስምም ሁሉ በላይየሆነውን ስምሰጠው፡፡ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታእንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፡፡” ፊል. 2፡5-11
ከትንሣኤው ምስክሮች መካከል አንዱ ለሆነው ለሐዋርያው ዮሐንስ መሲሁ ኢየሱስ በአንድ ወቅት በታላቅ ክብርተገልጦለት እንዲህ ብሎታል፡-
“አትፍራ ፊተኛውና መጨረሻው ህያውም እኔ ነኝ ፡፡ ሞቼም ነበርሁ እነሆ ከዘለዓለም እስከለዘለዓለም ድረስህያው ነኝ፡፡ የሞትና የሲኦል መክፈቻ አለኝ፡፡” ራዕ. 2፡18
ሙስሊም ወገኖች ሆይ! የኢየሱስን ስቅለት በተመለከተ ዛሬ በክርስቲያኖች መካከል ምንም አይነት መለያየት አለመኖሩን እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግልፅ በሆነ ቋንቋ የኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ በመዘገቡ ምክንያት በክርስቲያኖች ዘንድ ምንም አይነት ጥርጣሬና ውዝግብ የለም! የሚከተለው የቁርአን ጥቅስ ከክርስቲያኖች ይልቅ በናንተ መካከል ያለውን ሁኔታ በትክክል የሚገልፅ ስለሆነ ልብ ትሉት ዘንድ ያስፈልጋል፡-
“እነዚያ በሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው ፡፡ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡” 4፡ 158
ሙስሊሞች ሆይ! ከጥርጣሬ ነፃ ለመውጣትና ስለመሲሁ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ወደ ተውራት፣ ወደዘቡርና ወደ ኢንጂል ተመልከቱ፡፡ የሚከተለውንም የቁርኣን ቃል ለመተግበር አትዘግዩ፡-
“ወደ አንተ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ” ቁርአን 10፡94
ማጣቀሻዎች
[1] Josh McDowell, Evidence that Demands a Verdict, New and Revised, 1999, pp. 122-123
[2] Ibid., p. 125
[3] Ibid., pp. 123-124
[4] Ibid., p. 123
[5] Norman L. Geislere, Encyclopedia of Christian Apologetics, 1999, p. 128
[6] Ibid.
[7] Ibid.
[8] Ibid.
[9] ሚስተር አህመድ ዲዳት በ1984 በደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ ክርስቲያን አቃቤ እምነት ከሆኑት ከጆሽ ማክዱዌል ጋር ስለ ክርስቶስ ስቅለት ክርክር በገጠሙበት ወቅት ሱራ 4፡157ን ከጠቀሱ በኋላ እንዲህ ነበር ያሉት፡– “…ሙስሊም ይህንን ስልጣናዊ ንግግር እንደማይሻር የአምላክ ቃል ይቀበላል። በዚህ ሁኔታ ምንም ጥያቄ አይጠይቅም፣ ምንም ማረጋገጫም አይፈልግም! “እነሆ የጌታዬ ቃሎች፣ አመና ሰደቅና (አምናለሁ፣ አረጋግጣለሁ)” ይላል … ሙስሊሙ ግን የሚመልሰው “እነዚህ የሁሉን ቻዩ አምላክ ቃሎች ናቸው! ስለዚህ ምን እንደተፈጸመ አምላክ ያውቃል!” በማለት ነው።” የመክፈቻ ንግግራቸውን የመጀመርያ ደቂቃ እዚህ ያገኛሉ።
[10] Ahmed Deedat: Crucifixion or Crucifiction (ሙሉ ቡክሌት ይመልከቱ፡፡)
[11] ዶ/ር ሻቢር አሊ ክርስቲያን ሊቅ ከሆኑት ከዶ/ር ዊልያም ሌን ክሬግ ጋር ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ማርች 4፣ 2003 በቶሮንቶ ያደረጉትን ክርክር በተከታዩ አድራሻ ይመልከቱ፡-
http://www.youtube.com/watch?v=Qrasny8-pCA
[12] Sahih al-Bukhari, Vol. 5 No. 234; Vol. 7 No. 65
[13] Sahih Muslim, Book 008, No. 3330; The History of al-Tabari: The Victor of Islam;Translated by Michael Fishbein; State University of New York Press, 1997, Vol. VIII, pp. 2-3; በተጨማሪም ሱራ 33፡37-38
[14] Sahih al-Bukhari, Vol. 7, 71:660
[15] Sunan Abu Dawud, 2150; Sahih Muslim, No. 3371; በተጨማሪም ሱራ 23፡1-6፣ 70፡22-30
[16] ሱራ 2፡191-193፣ 8፡12፣ 8፡67፣ 8፡65፣ 9፡5፣ 9፡14፣ 9፡29፣ 9፡73፣ 9፡123፣ 48፡29፣ 58፡22
[17] ጌርሃርድ ኔልስ፣ ለሙስሊሞች ጥያቄዎች የክርስቲያኖች መልሶች፣ የሕይወት በር አገልግሎት፣ ገፅ 146
[18] Bukhari Vol. 4:683