ዳዊት ሕዝቡን እንዲቆጥር ያነሳሳው ማነው?

ዳዊት ሕዝቡን እንዲቆጥር ያነሳሳው ማነው?

በ2ሳሙኤል 24፡1 መሠረት እግዚአብሔር ነው ነገር ግን በ1ዜና 21፡1 ላይ ሰይጣን እንደሆነ ተገልጿል፤ በዚህም ሳብያ ወደ ሰባ ሺህ ሕዝብ ተቀስፎ መሞቱ ተነግሮናል፡፡

“ደግሞም የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ዳዊትንም፦ ሂድ፥ እስራኤልንና ይሁዳን ቍጠር ብሎ በላያቸው አስነሣው። ንጉሡም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊት አለቆች፦ የሕዝቡን ድምር አውቅ ዘንድ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ተመላለሱ፥ ሕዝቡንም ቍጠሩአቸው አላቸው። ኢዮአብም ንጉሡን፦ የጌታዬ የንጉሡ ዓይን እያየ አምላክህ እግዚአብሔር ዛሬ ካለው ሕዝብ መጠን በላይ መቶ እጥፍ ይጨምርበት፤ ጌታዬ ንጉሡ ግን ይህን ነገር ለምን ይወድዳል? አለው። ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብና በሠራዊቱ አለቆች ላይ አሸነፈ። ኢዮአብና የሠራዊቱ አለቆችም የእስራኤልን ሕዝብ ይቈጥሩ ዘንድ ከንጉሥ ዘንድ ወጡ።” (2ሳሙኤል 24፡1-4)

“ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን አንቀሳቀሰው። ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች፦ ሂዱ፥ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፥ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ አላቸው። ኢዮአብም፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሁሉ የጌታዬ ባሪያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለ ምን ያመጣል? ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ።” (1ዜና 21፡1-4)

ልስ – ሙሉ ታሪኩን ስናነብ ዳዊት በሠራዊቱ ብዛት መመካት ስለ ጀመረ እግዚአብሔር ሊቀጣው እንደፈለገ እናያለን፡፡ የልቡ ትዕቢት ይገለጥ ዘንድና ስለ ትዕቢቱም የሚገባውን ቅጣት ያገኝ ዘንድ ሕዝቡን እንዲቆጥር እግዚአብሔር አነሳሳው፡፡ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ሥልጣን ስላለው ለራሱ ዓላማ ማስፈፀምያ ሰይጣንን ጨምሮ የትኛውንም ፍጥረት መጠቀም ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ዳዊትን ስለ ትዕቢቱ መቅጣት ሲሆን የሰይጣን ዓላማ ደግሞ እስራኤላውያንን ማጥፋት ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ዓላማ ሲያስፈፅም በተለያዩ ስፍራዎች ላይ እናነባለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞቶ ለሰው ልጆች ቤዛ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ዓላማ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰይጣን ክፉ ሰዎችን በማነሳሳት ክርስቶስን እንዲሰቅሉት በማድረግ ሳያውቀው የእግዚአብሔር ዓላማ ግብ እንዲመታ አድርጓል፡፡ ይህ የእግዚአብሔርን ኃይልና ጥበብ የሚያሳይ ሲሆን ሰይጣንን ጨምሮ ማንኛውም ፍጥረት በርሱ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ያረጋግጥልናል፡፡ እዚህ ጋ የተቀሰፈው ሕዝብ ምን አጠፋ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በጥቅሱ ውስጥ የተነገረ ግልጽ ምክንያት ባይኖርም ነገር ግን በአቤሴሎም ዘመን እግዚአብሔር በቀባላቸው ንጉሥ ላይ ስላመጹ ሊሆን ይችላል፤ ወይንም ደግሞ በዳዊት ልብ ውስጥ የነበረው በቁጥር ብዛት የመመካት ነገር በተመሳሳይ ሁኔታ በሕዝቡ ልብ ውስጥም ሊኖር ይችላል፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር የሕዝብ ቆጠራ ሲደረግ ምን ጊዜም ሕዝቡን ከመቅሠፍት የሚጋርድ ቤዛ ይቀርብ ዘንድ እግዚአብሔር በነቢዩ ሙሴ አማካይነት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡-

 “እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ። አልፎ የሚቈጠር ሁሉ ግማሽ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሰጣል፤ የሰቅል ግማሽ ለእግዚአብሔር ያነሣል። ሰቅሉ ሀያ ኦቦሊ ነው። አልፎ የተቈጠረ ሁሉ፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም ከፍ ያለ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታ ይሰጣል። ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የእግዚአብሔርን ስጦታ ስትሰጡ ባለ ጠጋው ከሰቅል ግማሽ አይጨምር፥ ድሀውም አያጕድል።” (ዘጸአት 30:11–15)፡፡

ይህ ቤዛ አለመሰጠቱ ሕዝቡን ለመቅሰፍት አጋልጦት ሊሆን ይችላል የሚል አንድምታም አለ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር በፈጠራት ነፍስ ላይ ሙሉ ሥልጣን ስላለው በማንኛውም ጊዜ ሊወስዳት እንደሚችልና ማንም በዚህ ጉዳይ ጠያቂ ሆኖ ሊቀርብ እንደማይችልም መዘንጋት የለብንም፡፡

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ግጭቶች?

ቁርኣን ግጭቶች