እግዚአብሔር ሚስት አለችውን?
አንዳንድ ሙስሊሞች በትንቢተ ኢሳይያስ 54፡4 ላይ “ፈጣሪሽ ባልሽ ነው” የሚለውን ጥቅስ ከአውዱ በማፋታት “እግዚአብሔር እንዴት ሚስት ሊኖረው ይችላል?” በማለት ሲጠይቁ ይደመጣሉ፡፡ በርግጥ ቁርኣን አውድ አልባ መጽሐፍ በመሆኑ ምክንያት በኡስታዞች ከተጻፉ የፕሮፓጋንዳ መጻሕፍት ላይ የተለቃቀሙ ቁርጥራጭ ጥቅሶችን ከማንበብ የዘለለ ዕውቀት የሌላቸው ሙስሊም ወገኖቻችን መጽሐፍ ቅዱስም ልክ እንደ ቁርኣን አውድ አልባ መጽሐፍ መስሎ ቢታያቸው አያስገርምም፡፡ የጥቅሱን አውድና ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ስንመለከት ስለ ሀገር የሚናገር ቅኔያዊ ንግግር እንጂ ስለ አንዲት ሴት የማይናገር መሆኑን ማየት እንችላለን፡-
…የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ አትቈጥቢ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና። አታፍሪምና አትፍሪ አተዋረጂምና አትደንግጪ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፥ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም። ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል። እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፥ ይላል አምላክሽ። ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፥ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ። ….አንቺ የተቸገርሽ በዐውል ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ። የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ። ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። በጽድቅ ትታነጺያለሽ ከግፍ ራቂ፥ አትፈሪምም፥ ድንጋጤም ወደ አንቺ አትቀርብም። እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ። (ኢሳ. 54፡4-17)
ስለ ስለ ሰማርያና ኢየሩሳሌም የተነገሩትንም ተምሳሌታዊ ንግግሮች በተመሳሳይ መንገድ እግዚአብሔር እንደ ሰው ጋብቻን የፈፀመ በማስመሰል ሲተረጉሙ እንታዘባለን፡-
“የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ። ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።” (ሕዝቅኤል 23፡1-4)
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ነቢዩ የአምልኮተ ጣዖትን ፀያፍነት ለማመልከት በጋብቻ ላይ ማመንዘርን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ ትንቢቱ እንዲህ ባለ አስደንጋጭ መንገድ መቅረቡ አምልኮተ ጣዖት ርክሰት መሆኑን ለማስገንዘብ የታለመ ነው፡፡ በጥቅሱ ውስጥ በሴቶች የተመሰሉት የእስራኤልና የይሁዳ ዋና ከተሞች የነበሩት ሰማርያና ኢየሩሳሌም መሆናቸው በግልፅ ተነግሮ ሳለ ሙስሊም ወገኖቻችን ግን እግዚአብሔር ኦሖላና ኦሖሊባ የተባሉ ሚስቶች እንዳሉት የተነገረ በማስመሰል ሲስቱ ይታያሉ፡፡
በእርግጥ የጋብቻ ሐሳብ አመንጪ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ጋብቻ የተቀደሰና ክቡር መሆኑን ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ጋብቻ በአምላካችን ዘንድ ያለው ቦታ ትልቅ በመሆኑ ምክንያት በእርሱና በእስራኤል መካከል የነበውን ሕብረት በጋብቻ መስሎታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስራኤል “በሚስት” እግዚአብሔር ደግሞ “በባል” የተመሰሉባቸው ብዙ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል የሚገኘው ሕብረት እንዲሁ በጋብቻ ተመስሏል (ኤፌ. 5፡22-33)፡፡ ይህንን ሐሳብ በመውሰድ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ሴቶች መካከል አንዷን አግብቷል ብሎ መናገር አላዋቂነት ከሚለው ቃል በከፋ ሌላ ቃል ሊገለፅ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡