በቁርኣን ሚስቶችን መምታት አልተፈቀደምን? የኡስታዝ አቡ ሐይደር ክህደት ሲጋለጥ

በቁርአን ሚስቶችን መምታት አልተፈቀደምን?

የኡስታዝ አቡ ሐይደር ክህደት ሲጋለጥ

ኡስታዝ አቡ ሐይደር እስልምና ሚስቶችን ስለመምታት የሚያስተምረውን አሳፋሪ ትምሕርት ለማብራራት ብዕሩን ካነሳ ሰነባብቷል፡፡ ብዙ ሙስሊም ወገኖችም የእርሱን “ምላሽ” እንደ መጨረሻውና ትክክለኛው ምላሽ በመቁጠር በማሕበራዊ ሚድያዎች ላይ ሲቀባበሉት እየታዘብን ነው፡፡ ሆኖም የኡስታዙ “ምላሽ” እንደ ሌሎቹ እስላማዊ ምላሾች ሁሉ ሃይማኖቱን ከስህተቱ ለማትረፍ የሚበቃ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህንን “ምላሽ” ከቁርአንና ከቀደሙት እስላማዊ ምንጮች አንጻር እንፈትሻለን፤ የኡስታዙንም ጽርፈት እናጋልጣለን፡፡ አቡ ሐይደር እንዲህ በማለት ይጀምራል፡-

ቅዱስ ቁርኣን ሚስቶቻችሁን ግረፉ! በማለት ያዛል፡ ስለሆነም ሴቶች ተበድለዋል የሚለውን ቅጥፈት ነው፡፡ ለዚህ ክሳቸውም ተከታዩን የቁርኣን ክፍል ዋቢ አድርገው አቅርበዋል፡

ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው፤ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡና (ወንዶች) ከገንዘቦቻቸው (ለሴቶች) በመስጠታቸው ነው። መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች (ክብራቸውንና ንብረታቸውን የሚጠብቁ) ናቸው። እነዚያንም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገሥጹዋቸው፤ በመኝታዎችም ተለዩዋቸው፣ (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም። ቢታዘዙዋችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ። አላህ የበላይ ታላቅ ነውና።” (ሱረቱኒሳእ 34)፡፡

በዚህ ቅዱስ አንቀጽ ውስጥ ‹‹(ሳካ ሳታደርጉ) ምቷቸውም›› የሚለውን ኃይለቃል ቆንጥሮ በማውጣት፡ ኢስላም ሴቶችን ግረፉ ይላይ ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ፡፡

ይህ ለኛ የሚያሳየን በኢስላም ጉዳይ ውስጣቸው ምን ያህል እንደተቃጠለና፡ ለኢስላም እንዴት አይነት የከፋ ጥላቻ እንዳላቸው ነው፡፡ እንዴት እንደሆነም በምላሹ ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡

ለዚህ የከፋ አስተሳሰብ ያለን ኢስላማዊ ምላሽ በመጠኑም ቢሆን እንደሚከተለው ይቀርባል፡

ኡስታዙ ሴቶችን መምታት የከፋ አስተሳሰብ መሆኑን መቀበሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም “በኢስላም ጉዳይ ውስጣቸው ምን ያህል እንደተቃጠለ” “ለኢስላም እንዴት ዓይነት የከፋ ጥላቻ እንዳላቸው..” የሚሉት ቃላት ኡስታዙ የሙስሊም አንባቢያኑን አእምሮ አስቀድሞ በመመረዝ ጠያቂዎቹን (እኛን) በመቃወም ስሜት በጥቅሱ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ እንዲለዝብ ለማድረግ የተጠቀመበት ንግግር እንጂ በምሑራዊ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ለማስቀመጥ የሚመጥኑ አይደሉም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን በእስልምና ላይ ጥያቄ ያላቸውን ሰዎች በጠላትነት ሳይፈርጁ በቅንነትና በአክብሮት ምላሽ መስጠት የሚጀምሩበት ቀን ቅርብ አይመስልም፡፡ በእምነቱ የሚተማመንና በቂ ምላሽ እንዳለው የሚያውቅ ሰው “ጥያቄ ለምን ተነሳ” ብሎ አያማርርም፣ አይበሳጭም፣ ጠያቂዎቹን በጠላትነት በመፈረጅ የጥላቻን መርዝ አይረጭም፡፡ ይህ በመልሱ ላይ የማይተማመን ሰው ምልክት ነው፡፡ ኡስታዙ ይቀጥላል፡-

1. ኢስላም በትዳር ዓለም ውስጥ በባልና ሚስት መሀከል መልካም ግኑኝነት እንዲኖር ያዛል፡፡ በተለይ ባሎችን ለየት ባለ መልኩ ሚስቶቻቸውን በመልካም አን ኗኗር እንዲያስቀምጧቸው ይመክራል፡፡

በዚሁ ሱራ ላይ የሚገኘው የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡

እላንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! ሴቶችን ያስገደዳችሁ ሆናችሁ ልትወርሱና ግልፅን መጥፎን ስራ ካልሠሩ በስተቀር ከሰጣችኋቸው ከፊሉን ልትወስዱ፣ ልታጉላሏቸውም ለናንተ አይፈቀድም፤ በመልካምም ተኗኗርሩዋቸው፤ ብትጠሉዋቸውም (ታገሡ) አንዳችን ነገር ልትጠሉ አላህም በርሱ ብዙ ደግ ነገርን ሊያደርግ ይቻላልና።” (ሱረቱኒሳእ 19)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ከምናገኛቸው ቁም ነገሮች መሐከል፡

. ዐረቦች ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መላክ በፊት ያደርጉት እንደነበረው ልማድ፡ ሴትን ልጅ ባሏ ሲሞት ያለ ፈቃዷ እሷን እንደ ንብረት ቆጥሮ መውረስና በግዳጅም ማግባት እንዲሁም ላልፈለገችው ሰው መዳር እጅግ የተወገዘ መሆኑን፡፡

. ከተሰጣቸው የመህር ገንዘብ ላይ ግልጽ የሆነ ዝሙትን ፈጽመው ካልተገኙ በስተቀር ልትወስዱባቸውና ልታጉሏሏቸው እንደማይገባ

. በመልካም አንዋኗር ልናሮራቸው እንደሚገባና

. እነሱን የምንጠላበት ምክንያቶች ቢከሰቱ እንኳ መታገስ እንደሚገባንና፡ የተወሰነ የምንጠላበት ነገር ቢኖርም አላህ በምትኩ ብዙ የተሻለ ነገርን ሊያደርግልን እንደሚችል እንማራለን፡፡

ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በትምህርታቸው ላይ የትኛውም እምነት ውስጥ ልናገኘው የማንችለውን ነገር እንዲህ በማለት አስተምረውናል፡

ዐብደላህ ኢብኑዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገሩን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡

ከናንተ መሐል በላጭ ማለት ለሚስቱ መልካም የሆነ ሰው ነው፡፡ እኔ ለሚስቶቼ መልካም ሰው በመሆኔ በላጫችሁ ነኝ” (ኢብኑ ማጀህ 1977

ቲርሚዚይ 3895

ሶሒሕ ኢብኑ ሒባን 4177) ዘግበውታል።

2. ክስ ወደ ቀረበበት ጥቅስ ስንመለስ አንቀጹ የሚጀምረው ማለትም ( (ሱረቱኒሳእ 34) መልካም ሚስቶችን በማወደስና በማላቅ እንጂ ‹‹#ግረፏቸው›› በማለት አይደለም፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው፡

”…መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች (ክብራቸውንና ንብረታቸውን የሚጠብቁ) ናቸው…” በማለት ነው፡፡

 ጌታቸውን አላህን የሚታዘዙ፡ ባለቤታቸውን በሐቁ ትእዛዙን የሚጠብቁ፡ እሱ ከነሱ ሲርቅ (ለዳዕዋም ሆነ ለስራ በወጣበት) ደግሞ ብልታቸውንና ንብረታቸውን የሚጠብቁት ‹‹#መልካሞች›› ናቸው አለ እንጂ ‹‹#ግረፏቸው›› አላለም፡፡

ታዲያ ይህን አንቀጽ ለምን መዝለል ተፈለገ?

ነገሩ ልብ ከታወረ አይነስጋ ቢመለከት ምን ይጠቅማል?

አላህም በቃሉ እንዲህ አይደል ያለው፡

 “…እነሆ ዓይኖች አይታወሩም ግን እነዚያ በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ይታወራሉ።” (ሱረቱል ሐጅ 46)፡፡

3. እነዚህን መልካም ሚስቶች ካወደሰ በኋላ ደግሞ እንዲህ ይላል፡– ‹‹እነዚያንም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገሥጹዋቸው፤ በመኝታዎችም ተለዩዋቸው፣ (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም።››፡፡

ኡስታዙ የዘረዘራቸው “መልካም ትምሕርቶች” “ምቷቸው” የሚለውን ቃል ይፍቃሉን? ሴትን ልጅ የመምታትን ፀያፍነት ይቀንሳሉን? ሴቶችን ለመምታት የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ያቀርባሉን? መልሱ አሉታዊ ነው፤ ስለዚህ የኛ ጥያቄ በዙርያው በሚገኙት አናቅፅና በሌሎች እስላማዊ ትምሕርቶች  ላይ እስካልሆነ ድረስ መጥቀስ ለምን ያስፈልገናል? ባለመጥቀሳችንስ ስለምን እንወቀሳለን? እነዚህ የተባሉት ነገሮች ሁሉ መልካም መሆናቸውን የሚክድ ማንም የለም፤ ስለዚህ ጥያቄያችን በእነርሱ ላይ አይደለም፡፡ ኡዝታዙ “ምቷቸው” የምትለዋን ቃል ለማድበስበስ አቧራ እያነሳ ነው፡፡ በማስከተል እንዲህ ይላል፡-

 አሁን አንቀጹ የሚናገረው ስለአመጸኛ ሴቶች› (ሚስቶች) እንደሆነ ያስተውሉ፡፡

 ‹‹ሴቶችን›› ብሎ በጥቅሉ መልካሞቹንም ሌላውንም ለመፈረጅ መሞከር በውስጥ የታመቀ የጥላቻ ስሜትን ከመግለጽ ውጪ ምንም ለባለቤቱ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡

ጥቅሱ ማመፃቸውን የምትፈሩትን” እንጂ “አመፀኞችን” አይልም፡፡ ሴት ልጅ በምንም ነገር ብታኮርፍ ወይም ቅር ብትሰኝ ባል ችግሯን ለመረዳት ጆሮ ሳይሰጥ እርምጃ መውሰድ ይጀምራል፤ በመጨረሻም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ካልተገዛች እስከ መምታት ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ማመጿን ስለተጠራጠረ ብቻ እርምጃዎችን እንዲወስድባት ጥቅሱ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ የሆነው ሆኖ አመፀኛ ሚስቶችንስ ቢሆን መምታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይደለምን? ባል ሚስቱን እንዲመታ የሚያስችል ምንም ዓይነት ጥሩ ምክንያት የለም፡፡ ኡስታዙ ይቀጥላል፡-

እንደዛም ሆኖ የሚገርመው ነገር እነዚህን ‹‹አመጸኛ ሴቶች›› ወደ ትክክለኛው ባሕሪቸው ለመመለስ ቁዱስ ቁርኣን ‹‹ግርፋትን›› መፍትሄ አድርጎ አልወሰደም፡፡

በዚህ አንቀጽ ላይ ብቻ እንኳ ብንመለከተው ሶስት መፍትሄዎችን ነው የጠቆመው፡፡ እነሱም፡

. ‹‹ገሥጹዋቸው››

ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ ኢስላም በተግሳጽ ስለሚያምን ማለት ነው፡፡ ተግሳጽ (መውዒዟህ) ማለት፡ልብ ድረስ ዘልቆ ሊገባ የሚችል፡ ህሊናን የሚኮረኩር ምክርና ንግግር ማለት ነው፡፡

ስድብና ዘለፋ ያልታከለበት ማለት ነው፡፡

 ሙጃሂድ ኢብኑ ጀብር (ረሒመሁላህ) የተባሉት ታቢዒ እንደገለጹትም፡– ‹‹አላህን ፍሪና ተመለሺ በሐቄ ታዘዢኝ ይበላት›› ነው ማለት የሚገባው (ተፍሲሩጠበሪይ ሱረቱኒሳእ 34 9343)፡፡

 ወደ አላህ መንገድ ስንጣራ አንዱ አካሄድ በመልካም ግሳጼ መሆኑን ቅዱስ ቁርኣን ሲጠቁመን ‹‹አልመውዒዟህ›› በሚል ቃል ነው የተጠቀመው (ሱረተነሕል 125)፡፡

ስለዚህም አመጸኛዋን ሚስትህን ምከራት፡ ገስጻት ተባልክ እንጂ ግረፋት አልተባልክም፡፡ መልካም፡፡ በዚህ መልኩ ካልተመለሰችና ካልታረመችስ ቀጣዩ እርምጃ ምንድነው?

. ‹‹በመኝታዎችም ተለዩዋቸው››

ይህ ሁለተኛው እርምጃ ነው፡፡ በመኝታ መለየት ሁለት ነገሮችን ያቅፋል፡፡ የመጀመሪያው፡በአንድ ፍራሽ ላይ ሁነህ ግን ጀርባ በመስጠት ማኩረፍህን መግለጽ ሲሆን፡ ሁለተኛው ደግሞ፡ፍራሽ በመለየት ለብቻህ ተኛ የሚለው ነው፡፡ ቤት ለቀህ ግን እንዳትወጣ! ተከልክለሀልና፡፡ ሚስት ባለቤቷ እሷን ጀርባ ሰጥቶ መተኛቱ ወይም ፍራሽ መለየቱ ለሷ ትርጉም አለው፡፡ መለየቱም አያስችላትም፡፡ ስለዚህ ከዚህ አመጸኛ ባሕሪዋ ተጸጽታ ትመለስ ዘንድ የባል ኩርፊያ አጋዥ ነው፡፡ አሁንም ደግማ ከዚህ ባሕሪዋ የማትመለስ ከሆነስ ቀጣዩ እርምጃ ምንድነው?

ጤናማ አስተሳሰብ ያላት ሴት ከዚህ አልፋ አትሄድም፡፡ ከዚህ የምታልፍ ከሆነ ግን መፍትሄው መምታት ሳይሆን መጸለይ፣ በትዕግስትና በፍቅር ደጋግሞ መምከር፣ ካልሆነም በቅርብ ወዳጆችና በሃይማኖት አባቶች ማስመከር እንጂ መምታት ፀያፍ ነው፡፡

. ‹‹(ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም››

የሚለው ነው፡፡ አላዋቂዎች ሆይ! የታለ ግረፏቸው የሚለው? መግረፍ በዐረብኛ ‹‹ጀልድ›› እንጂ ‹‹ደርብ›› አይደለም፡፡

ለነገሩ እናንተ እንደ ገደል ማሚቱ ተጽፎ የተሰጣችሁን ከማስተጋባት ውጪ ዐረብኛውን (አሊፍ ትቁም ትተኛ) የት ታውቁትና!!

ዘለፋው ባንተ ዕድሜ ካለ ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡ የተለያዩ የዐረብኛ መዝገበ ቃላትን ስንመለከት “ደርብ” ቀጥተኛ ትርጉሙ “መምታት” (to beat, strike, to hit) ነው (Hans Wehr Dictionary of Modern Written Arabic, Spoken Language Services, Ithaca, NY, 1976, page 538)፡፡ መምታት ደግሞ ዓይነቶች አሉት፤ (በጥፊ፣ በዱላ፣ በአለንጋ፣ በቦክስ፣ በካልቾ፣ ወዘተ.)፡፡ ይህ ቃል “መምታት” ሲል ሁሉንም ዓይነት መምታትን ያመለክታል፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች “ግረፏቸው” (scourge them) ብለው የተረጎሙት፡፡ አቡ ሐይደር “ግረፏቸው” የሚለው ትክክለኛ ትርጉም አይደለም የሚል ከሆነ መውቀስም መዝለፍም ያለበት ክርስቲያኖችን ሳይሆን ፒክታልን የመሳሰሉትን ሙስሊም ሊቃውንት ነው፡፡ በማስከተል እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

በጣም ከገረመኝ ድፍረታቸው ደግሞ (ሳካ ሳታደርጉ) የሚለው የአማርኛው የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ላይ ጭማሪ ያስገቡት ነው ማለታቸው ነው፡፡

አወቅሽ አወቅሽ ቢሏትየተባለው ተረት ለናንተ ነበር ማለት ነው?

ለማንኛውም ይህ በቅንፍ የገባው ገላጭ ቃል ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐይሂ ወሰለም) ንግግር የተወሰደ ማብራሪያ እንጂ የተርጓሚዎች የግል ሀሳብ አይደለም፡፡

በሐጀቱል ወዳዕ (የመሰናበቻው ሐጅ) ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ካስተላለፉት ሰፊ ትምሕርት ላይ የተወሰደ ነው፡፡

በዚህ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ውስጥ ‹‹ምቷቸው›› ለሚለው ቃል ምን አይነት መምታት? የሚል ጠያቂ ቢመጣ ምላሹ ይህ ይህ ይሆናል፡

 “… እናንተ ሰዎች ሆይ! በሴቶች ጉዳይ አላህ ፍሩ! እናንተ እነሱን በአላህ አደራ ነው የወሰዳችኋቸው፣ ብልቶቻቸውንም በአላህ ቃል (በመልካም ያዙዋቸው በሚለው) ነው ሐላል ያደረጋችሁት፣ እናንተም በነሱ ላይ በቤቶቻችሁ የማትፈልጉትን ሰው እንዳያስገቡ የመከልከል መብት አላችሁ፡፡ እምቢ ብለው ይህን ካደረጉ፡ ህመም የማያስከትልና ያልበረታ ምትን ምቷቸው፡፡ እነሱም በናንተ ላይ ሲሳያቸውን ልትችሉ፣ ልብሳቸውን በአግባቡ ልትሸፍኑ መብት አላቸውና…” (ሙስሊም 1218 አቡ ዳዉድ 1907)፡፡

የአማርኛ ቅዱስ ቁርኣን ተርጓሚዎችም በቅንፍ ውስጥ (ሳካ ሳታደርጉ) የሚለውን ከራሳቸው ሳይሆን የጨመሩት፡ የታላቁን ነቢይ የቁርኣን ማብራሪያ በመውሰድ ነው፡፡

አንድ የማንካካደው ሃቅ አለ፤ በቅንፍ የገባው በአረብኛው ቁርአን ውስጥ የለም! ስለዚህ ተርጓሚዎቹ ከየትም ያምጡት ከየት በአረብኛ ቁርአን ውስጥ የሌለ የሰው ቃል የአላህ ቃል በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ጨምረዋል፡፡ ቁርአን የተብራራና አልፎ ተርፎም ሁሉንም ነገር የሚያብራራ እንደሆነ ይናገር የለምን? ከሰማይ የወረደ በተባለው መጽሐፍ ላይ ውጪያዊ ማብራርያ በማከል ለዚያውም በግርጌ ማስታወሻ ሳይሆን በዋናው ጽሑፍ ውስጥ ቃላትን መጨማመር አንባቢን ማሳሳትና ብረዛ አይሆንምን? “ሁሉንም ነገር የሚያብራራ” የተባለውስ መጽሐፍ ሌላ ማብራርያ መፈለጉ ጥያቄን አይፈጥርምን?

4. አሁንም ‹‹ምቷቸው›› የሚለውን፡በቀበቶና አለንጋ፣ በዱላና በከዘራ ነው የተንሸዋረረ ምልከታን ሰዎች እንዳይነዙ ታላቁ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኝ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ብሎ አብራራው፡

አጣእ ኢብኑ የሳር (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን አገኘሁትና ‹‹ህመምን ያላስከተለና ያልበረታ ምት ምንድነው?›› አልሁት፡፡

እሱም፡– ‹‹በሲዋክና (መፋቂያ) በመሳሰለው መምታት ነው›› አለኝ፡፡ (ተፍሲሩጠበሪይ፡ ሱረቱኒሳእ 34 ቁጥር 9386)፡፡

አሁንስ ምን ይዋጣችሁ፡፡

አያችሁ! የምቱ ዓላማና ግብ አመጸኛዋ ሚስት አደብ እንድትይዝ እንጂ እሷን ለመጉዳት እንዳልሆነ ግልጽ ሆነላችሁ?

የሳዑዲ ዜጋ የሆነችው ራኒያ አል-በዝ በባሏ በደረሰባት ድብደባ ምክንያት 13 አጥንቶቿ ተሰብረዋል፡፡

እርስ በርሱ ከተምታታው የሙስሊም ሊቃውንት ትርጓሜ ውስጥ የሚመቸንን መርጠን መያዝ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱን አስተያየት ወደ መሐመድ ዘመን ወስደን ካልመረመርነው እውነቱን ማወቅ አንችልም፡፡ በየዘመናቱ የኖሩት ሙስሊሞች ይህንን ህሊናን የሚጎረብጥ ተግባር ለማድበስበስ የተለያዩ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ ሆኖም በመሐመድ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ስንመለከት የምንታዘበው ተቃራኒውን ነው፡፡ በመሐመድ ዘመን የነበሩት ሙስሊሞች ህመምን ከማስከተል አልፎ በአካል ላይ ምልክትን የሚያስቀር ምት ሚስቶቻቸውን ሲመቱ ነበር፡-

“ኢክሪማ እንዳወራው፡- ሪፋ ሚስቱን ከፈታ በኋላ አብዱልረህማን አገባት፡፡ ያቺም ሴት አረንጓዴ ልብስ ለብሳ በመምጣት በድብደባ ምክንያት የደረሰባትን አረንጓዴ ምልክት ለአይሻ አሳየቻት፡፡ መተጋገዝ የሴቶች ወግ በመሆኑ የአላህ መልእክተኛ በመጡ ጊዜ አይሻ እንዲህ አለች፡- ‹‹እንደ አማኝ ሴቶች የሚሠቃዩ ሴቶችን አላየሁም፡፡ ይመልከቱ! የሰውነት ቆዳዋ ከልብሷ በላይ አረንጓዴ ሆኗል!›› አብዱልረህማንም ሚስቱ ነቢዩ ዘንድ መሄዷን ሲሰማ ከሌላ ሚስት የወለዳቸውን ሁለቱን ወንድ ልጆቹን ይዞ መጣ፡፡ ሴቲቱም፡- ‹‹በአላህ እምላለሁ! እኔ ምንም አልበደልኩትም ነገር ግን እርሱ መውለድ የማይችል ወንድ ነው›› ከዚያም የልብሷን ጫፍ በመያዝ ‹‹እርሱ ልክ እንደዚህ ለኔ ጥቅመ ቢስ ነው›› በማለት ተናገረች፡፡ አብዱልረህማንም እንዲህ አለ፡- ‹‹በአላህ እምላለሁ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ዋሽታለች፡፡ እኔ በጣም ጠንካራ ነኝ፤ ላረካትም እችላለሁ ነገር ግን እርሷ ታዛዥ አይደለችም፤ ወደ ሪፋ መመለስ ፈልጋለች፡፡›› የአላህ መልእክተኛም እንዲህ አሏት፡- ‹‹ፍላጎትሽ እንደርሱ ከሆነ አብዱልረህማን ካንቺ ጋር ግንኙነት እስኪፈጽም ድረስ ወደ ሪፋ መመለስ እንደማይፈቀድልሽ ማወቅ ያስፈልግሻል፡፡›› ነቢዩም ሁለት ወንድ ልጆችን ከአብዱልረህማን ጋር አይተው ‹‹እነኚህ ልጆችህ ናቸውን?›› ብለው ጠየቁት፡፡ አብዱልረህማንም ‹‹አዎን›› ብሎ መለሰ፡፡ ከዚያም ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹መውለድ አይችልም ነው ያልሽው? በአላህ እምላለሁ ቁራ ከሌላው ቁራ ጋር እንደሚመሳሰል ሁሉ እነዚህም ልጆች ከእርሱ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡››” (Bukhari, vol. 7, No. 715)

በዚህ ሐዲስ ውስጥ በተዘገበው መሠረት፡-

  • ሴቲቱ በጋብቻዋ ደስተኛ አልነበረችም ነገር ግን አላመነዘረችም፤ ባሏ ግን “ታዛዥ አይደለችም” በሚል ሰበብ በሰውነቷ ላይ ምልክት እስኪታይ ድረስ ክፉኛ መታት፡፡
  • አይሻ ‹‹እንደ አማኝ ሴቶች የሚሠቃዩ ሴቶችን አላየሁም›› በማለት በመሐመድ ዘመን የነበሩት ሙስሊም ሴቶች ይደርስባቸው የነበረውን ሠቆቃ ገልጻለች፡፡
  • መሐመድ በሴቲቱ ላይ የደረሰው ድብደባ ትክክል አለመሆኑን አልተናገረም፡፡ ይልቅስ ባሏ መውለድ እንደማይችል በመናገሯ ምክንያት ሲገስጻትና ለደብዳቢው ባሏ ሲሟገት እንመለከታለን፡፡ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ድብደባውን ማጽደቅ ነው፡፡

በአንድ ወቅት መሐመድ ሚስቱ አይሻን ደረቷ ላይ እንደመታትና ምቱም ህመምን እንዳስከተለባት በሳሒህ ሙስሊም ሐዲስ ውስጥ ተጽፏል (Sahih Muslim No. 2127)፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ  የመሐመድ ሚስቶች የነበሩት አይሻና ሐፍሳ መሐመድን ገንዘብ እየጠየቁ ያስቸግሩት ነበር፡፡ ዑመር ሚስቱ ተመሳሳይ ጥያቄ በማቅረቧ ምክንያት አንገቷ ላይ በጥፍ እንደመታት ለመሐመድ ሲነግረው መሐመድ እንደሳቀ ተዘግቧል፡፡ ከዚያም የአይሻ አባት አቡበከርና የሐፍሳ አባት ዑመር ሁለቱን ሴቶች አንገቶቻቸው ላይ በጥፊ እንደመቷቸው ተጽፏል፡፡ መሐመድም ድርጊቱን አልተቃወመም (Sahih Muslim No. 3506)፡፡ በሌላ ሐዲስ አቡበከር አይሻን ደረቷ ላይ በክርኑ በመምታት ክፉኛ እንዳሳመማት ተጽፏል (Bukhari volume 8, No. 828)፡፡ በሌላ ዘገባ ደግሞ መሐመድ አንዲት ሴት ማንን ማግባት እንዳለባት ስታማክረው ሙአዊያ ከተባለው ድኻ ወንድ ይልቅ ሁል ጊዜ በትሩን በትከሻው ላይ ይዞ የሚዞረውንና ሚስቶችን በመደብደብ የሚታወቀውን አቡ ጀህም የተባለውን ሰው እንድታገባ መክሯታል (Sahih Muslim, Book 009, Number 3512; Book 009, Number 3526; Book 009, Number 3527)፡፡ ከዚህ ሁሉ የምንገነዘበው መሐመድ ሴቶችን በመምታት ዙርያ ችግር እንደሌለበትና “መምታት” ሲባልም የሚያሳምም አመታት መሆኑን ነው፡፡

መሐመድ ሚስቶችን መምታት እንዴት እንደሆነ ሲያስተምር “ማንም ሰው ባርያን በሚገርፍበት አኳሆን ሚስቱን ከገረፈ በኋላ በቀኑ መጨረሻ አብሯት ግንኙነት መፈፀም የለበትም” በማለት ተናግሯል (Bukhari volume 7, No. 132)፡፡ ይህንን ሐዲስ ባርያዎች በሚገረፉበት መንገድ ሚስቶችን መግረፍ ተገቢ አለመሆኑን እንደሚናገር አድርጎ መገንዘብ ይቻላል፤ ወይንም ደግሞ ባርያዎች በሚገረፉበት መንገድ ሚስትን ገርፎ አብሯት የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም እንዳልተፈቀደ እንደሚናገርም አድርጎ መገንዘብም ይቻላል፡፡ ግልፅነት ይጎድለዋል፡፡ ዳሩ ግን ሚስትን መግረፍን እንደሚያጸድቅ መካድ አይቻልም፡፡

መሐመድ ሚስቶችን መምታትን መፍቀዱ ላይ ምንም ዓይነት ክርክር ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን ልዩነት ያለው “ምን ዓይነት አመታት?” በሚለው ላይ ነው፡፡ የተለያዩ እስላማዊ ምንጮች “ጉዳትን የማያስከትል አመታት” እንደሆነ ይናገራሉ፤ መሐመድም እንደርሱ ብሎ ማስተማሩ ተዘግቧል፡፡ ይህም ቢሆን ምን ማለት እንደሆነ ከስምምነት የተደረሰ አይመስልም፡፡ ነገር ግን “ህመምን ያላስከተለ” የሚለው የሙስሊም ዐቃቤያነ እምነት ትርጓሜ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመሐመድ ዘመን የነበሩት ሙስሊም ወንዶች ሚስቶቻቸው ላይ ምልክት እስኪታይ ድረስ ይመቷቸው ነበር፡፡ በአንድ ሐዲስ መሠረት ሚስቶችን መምታት ከተፈቀደ በኋላ ሙስሊም ሴቶች ተቃውሞ በማሰማት ወደ መሐመድ ቤተሰብ ኼደው አመልክተው እንደነበር ተዘግቧል (Sunan Ibn Majah, No. 1985)፡፡ የተመቱት በመፋቂያ ቢሆን ኖሮ ስሞታ ለማቅረብ ወደ መሐመድ ባልሄዱ ነበር፡፡

ኢብን ከሢር የተሰኘው ሙስሊም ሊቅ “ጉዳት የማያደርስ ምት” የሚለውን “አጅና እግራቸውን መስበርን የመሳሰሉ ጉዳቶችን” እንደሆነ ይናገራል (“Tafsir of Ibn Kathir”, Al-Firdous Ltd., London, 2000)፡፡ “እጅና እግራቸውን መስበር”! ስለዚህ ጉዳት ማድረስ ማለት እጅና እግርን መስበርን የመሳሰሉ አካላዊ ጉዳቶችን እንጂ ህመምን አይደለም ማለት ነው፡፡

በመሐመድ ሐዲስ መሠረት ባል ሚስቱን የመምታት ፍፁማዊ መብት አለው፡፡ “ዑመር እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹ባል ሚስቱን ለምን እንደመታት መጠየቅ የለበትም፡፡›” አቡዳውድና ኢብን ማጃህ ዘግበውታል፡፡ (Mishkat Al-Masabih: vol. 2, p. 693)

“በመፋቂያ መምታት” የሚለው ስላቅ እዚህ ጋ አይሠራም፡፡ በማስከተል ኡስታዙ እንዲህ ይለናል፡-

5. ደግሞም ኢስላም የተከበረውን ፊት ከመምታት እንድንቆጠብ ያዘናል፡፡

ተከታዩ ሐዲሥም ይህን ያብራራዋል፡

ሙዓዊያህ ኢብኑ ሐይደቱል ቁሸሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡– “የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንዳችን ባለቤቱ በሱ ላይ ምን ሐቅ አልላት? አልኳቸው፡፡

እሳቸውም፡

 ከምትመገበው ልትመግባት፣

ስትለብስ ልታለብሳት፣

 #ፊቷን ላትመታት፣

በመጥፎ ንግግር ላትናገራት (ካኮረፍካትም) እዛው ቤት ውስጥ ሁነህ እንጂ ላትተዋት›› በማለት መለሱልኝ

(አቡ ዳዉድ 2142)፡፡

ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ሴት ልጅ ሁለንተናዋ ክቡር ነው፡፡ ፊቷንም ይሁን ደረቷን፣ አንገቷንም ይሁን እግሯን መምታት ፀያፍ ተግባር ነው፡፡ እስልምና ሚስቶችን መምታት የሚያስተምር የዓለማችን ብቸኛው ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰባተኛው ክፍለ ዘመን አረብያ ኋላ ቀር ልማድ ነው፡፡ የሰው ልጆች የደረሱበትን የአስተሳሰብ ደረጃ የሚመጥን አይደለም፡፡ ኡስታዙ ይቀጥላል፡-

6. አንቀጹ ይቀጥልና ደግሞ፡

 ‹‹ቢታዘዙዋችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ። አላህ የበላይ ታላቅ ነውና።›› በማለት ይዘጋዋል፡፤ አዎ! ወደ ታዛዥነታቸው ከተመለሱ እነሱን ለመጨቆን አላህ ምንም መንገድን አላበጀም፡፡

የበላይነትን ለማሳየት የምንጥር ከሆነ ደግሞ፡ እርሱ ጌታችን አላህ የበላይና ታላቁ አምላክ መሆኑን ማስታወስ እንደሚገባን መከረን፡፡ ይህ ነው የኢስላም አስተምህሮ!!

ሴትን ልጅ ከመምታት የከፋ ዕብደት ምን ሆነና ነው ኡስታዙ እንዲህ የተደነቀው? “ግደሏቸው” ስላላለ ይሆን? “ምቷቸው” ካለ በኋላ “ከታዘዟችሁ አትጨቁኗቸው” ማለቱ ምን ያስደንቃል? በርግጥ እስልምና ለሴት ልጅ የሰጠውን ዝቅተኛ ቦታ ያስተዋለ ሰው “ግደሏቸው” ባለማለቱ ሊደነቅ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ በዚህ ቦታ ምንም የሚያስደንቅ ነገር የለም፡፡ በማስከተል እንዲህ በማለት ጉዳዩን ወደ ክርስትና ለማዞር ይሞክራል፡-

7. አሁን ተራው የናንተ ነው፡፡

ኢስላም ሴቶችን ግረፉ ይላል በማለት ‹‹ወደ ገደለው እንግባ›› እንዳለው ሰውዬ አንድ ቃልን ብቻ ከውስጥ በመምዘዝ ሃይማኖቱን ጥላሸት ለመቀባት የምትሞክሩት፡ በናንተ ዘንድ እንዲህ አይነት አመጸኛ ሴት ስትኖር ምን መፍትሄ መውሰድ እንዳለባችሁ መጽሐፋችሁ ይነግራችኋልን? በማለት እኛም እንጠይቃችሁ በተራችን፡፡

እስኪ ከሚናገረው መፍትሔ የምታውቁትን አካፍሉን፡፡ እነዚህን ጥቅሶችስ እንዴት ትፈቱታላችሁ፡

ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በውጪ በቤት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 21 9)

ከጠበኛና ከቍጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 21 19)

ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 25 24)

በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 27 15)

ከደረቅ ሴት ጋር ከምትኖር ከምድር አውሬና ከአንበሶች ጋር መኖር ይሻላል” (መጽሐፈ ሲራክ 257)፡፡ (የኦርቶዶክስ መጽሐፍ ቅዱስ)(81 አሃዱ)

ወገኖቻችን! ይሄ ነው መፍትሄው?

ይህን ይዛችሁ ነው የኛን የምትተቹት?

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ከእውነታ ያፈነገጠ ምንም ነገር የለም፡፡ ከጠበኛ ሴት ጋር መኖር በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ ይህንን የሚክድ ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ መልካም ሴቶች እንዳሉ ሁሉ ለትዳር የማይመቹ ጠበኛ ሴቶችም አሉ፡፡ ወንዶችም እንደዚያው፡፡ ይህንን የታወቀ ሃቅ መግለፅ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ? ነገር ግን ከቁርአን በተጻራሪ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድም ቦታ ላይ “ሚስቶቻችሁን ምቱ” አይልም፡፡ በትዳር ውስጥ ዱላ በምንም ዓይነት መንገድ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡

እስልምናና ክርስትና በሴቶች መብትና ደረጃ ላይ ያላቸው ልዩነት የሚመነጨው ስለ ሴቶች ተፈጥሮ ካላቸው አስተምሕሮ ነው፡፡ በእስልምና መሠረት ሴቶች በፍጥረታቸው ከወንዶች ያነሱ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በቁርአንና በሐዲሳት ውስጥ በበርካታ መንገዶች ተገልፆ እናገኛለን፡፡ በዚህ ላይ የተሰጠውን ሰፊ ሐተታ ሴቶች በቁርኣን በሐዲስና በመጽሐፍ ቅዱስ በሚል ርዕስ ከተጻፈው ጽሑፍ ያገኛሉ፡፡

በክርስትና መሠረት ወንዶችና ሴቶች እኩል ናቸው፡-

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡” (ገላቲያ 3፡28)፡፡

እኩል በአምሳለ እግዚአብሔር ተፈጥረዋል፡-

“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡፡ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡” (ዘፍጥረት 1፡26-27)፡፡

“የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው፡፡” (ዘርጥረት 5፡1-2)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲወዱና እንዲያከብሩ እንጂ እንዲመቷቸው አያዝም፡-

“ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ፡፡ ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ፡፡ ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ፡፡” (1ቆሮንቶስ 7፡3-5)፡፡

“ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ፡፡ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፡፡ የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ፡፡ ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ፡፡” (ኤፌሶን 5፡25-33)፡፡

“ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው፡፡” (ቆላስይስ 3፡19)፡፡

“እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው፡፡” (1ጴጥሮስ 3፡7)፡፡

“ደካማ ፍጥረት” (Weak Vessels) የሚለው ሴቶች በስሜትና በአካል ከወንድ አንፃር ደካሞችና እንክነብካቤ የሚያሻቸው መሆናቸውን እንጂ በመንፈስና በአዕምሮ ደካማ መሆናቸውን አያሳይም፡፡ ወንዶች ሴቶችን ካላከበሩ ጸሎታቸው እግዚአብሔር ዘንድ እንደማይደርስ መነገሩ ሴቶች በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ደረጃና በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ የሚገልፅ ነው፡፡ ይህ ሴት ልጅ ከፊት ካለፈች ጸሎት እንደሚቋረጥ ከሚናገረው እስላማዊ አስተምሕሮ ምንኛ የተለየ ነው!

“አቡ ዘር እንዳስተላለፈው፡- የአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ብለዋል፡- ከመካከላችሁ አንድ ሰው ለጸሎት በሚቆምበት ሰዓት… ከፊት ለፊቱ የኮርቻ ያህል መጠን ያለው ነገር የማይኖር ከሆነ ጸሎቱ (በፊቱ በሚያልፍ) አህያ፣ ሴት እና ጥቁር ውሻ ይቋረጣል፡፡ እኔም አቡ ዘር ሆይ ጥቁር ውሻን ከቀይ ወይም ከቢጫ የሚለየው ምንድነው? ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እርሱም የወንድሜ ልጅ ሆይ አንተ እንደጠየቅኸኝ ሁሉ እኔም የአላህን መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ጠይቄያቸው ነበር፤ ‹ጥቁር ውሻ ዲያብሎስ ነው› በማለት ነበር የመለሱልኝ፡፡” (Sahih Muslim, Book 004, Number 1032)

በክርስትና የትዳር አጋራችንን አስቀድመን በጥንቃቄ እንድንመርጥ ተነግሮናል (ምሳሌ 31)፡፡ አማኝ ወንዶችና ሴቶች በትዳር ውስጥ ያላቸው ሚናና የሥራ ድርሻ ምን እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ባሎች ሚስቶቻቸውን በፍፁማዊ ፍቅር መውደድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻቸው መታዘዝና ባሎቻቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል (1ቆሮንቶስ 7፡3-5፣ ኤፌሶን 5፡25-33)፡፡ በትዳር ውስጥ ችግር የሚፈጠር ከሆነ “ክፉውን በመልካም ማሸነፍ” በሚለው ክርስቲያናዊ መርህ መሠረት ነገሮችን እናስተካክላለን እንጂ ዱላን እንደ አማራጭ አንወስድም (ሮሜ 12፡21)፡፡ እስልምና የሰይፍ መንገድ በመሆኑ በጦርነትና በድብድብ መፍትሄ እንደሚመጣ ያስተምራል፡፡ ክርስትና ደግሞ የፍቅር መንገድ በመሆኑ በውይይትና አንዳችን የሌላችንን ድካም በመሸከም መፍትሄ እንደሚመጣ ያስተምራል፡፡ ኡስታዙ እንዲህ ሲል ይቋጫል፡-

8. በመጨረሻም ለነዚህ ወገኖች የምናስተላልፈው መልእክት፡

እባክችሁ በዕድሜያችሁ አትቀልዱ! በእሳት አትጫወቱ! የዘላለም ህይወት የሚገኝበትን ጀነትን ከፈለጋችሁ አንድ አምላክ ብቻ ወደሚመለክበት ኢስላም በፈቃደኝነት !

አላህን ላላመለከ፡ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት ያላመነና በዚሁ ክህደቱ እምቢ ብሎ የሞተ ሰው፡ ጀነት ለርሱ ዝግ ናት፡፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ካልሾለከ በስተቀር ወደ ጀነት አይመለስም፡፡ አላህ ሂዳያ ይስጣችሁ ለኛም ጽናቱን ይለግሰን፡፡ ሰላምም ቀጥታን በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን፡፡

የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደሆነች ቃል ኑ፤ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጐ ላይይዝ ነዉ፤ በላቸዉ። እምቢ ቢሉም እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው” (ሱረቱ አሊዒምራን 64)፡፡

ኡስታዝ አቡ ሀይደር

አይ ኡስታዝ! ሴቶች የወሲብ ሸቀጥ ወደሆኑበት የአላህ ገነት እየጋበዝከን ባልሆነ! እናንተ ገነት በምትሉት ለሴቶች ግን ገሃነም በሆነው የአላህ ገነት ውስጥ ለሙስሊም ወንዶች የስሜት ማርኪያ እንዲሆኑ የተፈጠሩ ሴት ፍጥረታት እንደሚገኙ ቁርአን ይናገራል፡-

78፡30-33 “ለጥንቁቆቹ መዳኛ ስፍራ አልላቸው፡፡ አትክልቶችና ወይኖችም፡፡ እኩያዎች የኾኑ ጡተ ጉቻማዎችም፡፡ የተሞሉ ብርጭቆዎችም፡፡”

44፡51-54 “ጥንቁቆቹ በእርግጥ በጸጥተኛ መኖሪያ ውስጥ ናቸው፡፡ በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡ ፊት ለፊት የተቅጣጩ ኾነው ከስስ ሐርና ከወፍራም ሐር ይለብሳሉ፡፡ (ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ ዓይናማዎች የኾኑን ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን፡፡”

56፡34-36 “ከፍ በተደረጉ ምንጣፎችም (ሴቶችም መካከል)፡፡ እኛ አዲስ ፍጥረት አድርገን (ለእነርሱ) ፈጠርናቸው፡፡ ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎች እኩያዎች (አደረግናቸው)፡፡ ለቀኝ ጓዶች (አዘጋጀናቸው)፡፡”

አንድ ሙስሊም ወንድ በገነት ውስጥ የ100 ወንዶች ጉልበት እንደሚያገኝ ቲርሚዚ መዘገቡን ሚሽካት አል መሳቢህ የተሰኘው የሐዲሳት ስብስብ መጽሐፍ ይጠቅሳል፡፡ (Mishkat Al-Masabih: vol. 3, p. 1200)

መሐመድ እንደተናገረው የገሃነም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሴቶች ናቸው፡-

“ሴቶች ሆይ ምፅዋት ስጡ የገሃነም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሴቶች መሆናቸውን አይቻለሁና፡፡ ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ ለምንድነው?› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ብዙ ጊዜ ትሳደባላችሁ፤ ለባሎቻችሁም ምስጋና ትነፍጋላችሁ፡፡ በዕውቀትና በሃይማኖት ከእናንተ በከፋ ሁኔታ ጎደሎ የሆነ አላየሁም›… ሴቶቹም እንዲህ ብለው ጠየቁ፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ በዕውቀትና በሃይማኖት ጎደሎዎች የሆንነው እንዴት ነው?› እርሱም ‹የሁለት ሴቶች ምስክርነት ከአንድ ወንድ ምስክርነት ጋር እኩል አይደለምን?› በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በአዎንታ መለሱ፡፡ ‹ይህ በዕውቀት ጎደሎዎች መሆናችሁን ያሳያል፡፡ ሴት በወር አበባ ጊዜዋ መጸለይም ሆነ መፆም አለመቻሏ እውነት አይደለምን?› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ሴቶቹም በአዎንታ መለሱ፡፡ ‹ይህ በሃይማኖት ጎደሎ መሆናችሁን ያሳያል› በማለት መለሱላቸው፡፡” (Sahih Al-Bukhari vol.1 no.301 p.181. See also Sahih Muslim vol.2 book 4 no.1982, 1983 p.432)

እንዲህ የሴቶችን ክብር ወደሚያራክስ የጨለማ መንገድ ነው የምትጠሩን? ሌላው ይቅርና በቁርአናችሁ ውስጥ ከማርያም ስም በስተቀር የአንዲት ሴት ስም እንኳ አልተጠቀሰም፡፡ በእስልምናም ውስጥ ሴት ነቢያት አይታወቁም፡፡ ዕድሜ ልካቸውን በጥቁር ጨርቅ ተጀቡነው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ወንዶች እስከ አራት እንዲያገቡና ከዚያም አልፈው ቁባቶችን እንዲይዙ ሲፈቀድላቸው ሴቶች ግን ከወንዱ መልካም ፈቃድ ውጭ ምንም መወሰን እንዳይችሉ በአስጨናቂ ሕግጋት ታጥረዋል (ሱራ 4፡3)፡፡ በወር አበባ ላይ ያለች ሙስሊም ሴት ሰላት መስገድ፣ ፆም መፆምም ሆነ ቁርአንን መንካት አይፈቀድላትም፡፡ ከዚህ በተጻራሪ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሴት ነቢያት በብዛት ተጠቅሰዋል (ዘጸአት 15፡20፣ መሣፍንት 4፡4፣ 1ዜና 34፡22፣ የሐዋርያት ሥራ 21፡9)፡፡ ከሐዋርያት ጋር ሲያገለግሉ የነበሩ ሴት አገልጋዮችም ነበሩ (ሮሜ 16፡1፣ 7)፡፡ የጌታችን ትንሣኤ የመጀመርያዎቹ ምስክሮች ሴቶች ነበሩ (ማቴዎስ 28፡1-9፣ ማርቆስ 16፡1-8፣ ሉቃስ 24፡1-11፣ ዮሐንስ 20፡1-10)፡፡ ሴቶች ለምስክርነት በማይቀርቡበት በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የክርስትና መሠረት የሆነውን የክርስቶስን ትንሣኤ ለመመስከር መመረጣቸው ምንኛ አስደናቂ ነገር ነው!

ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን፤ ከነዚህ እውነታዎች አንፃር ትክክለኛው የአምላክ መንገድ የትኛው ይመስላችኋል? ኡስታዞቻችሁ ስለ እስልምናም ሆነ ስለ ክርስትና የሚነግሯችሁ ነገር እውነት አይደለም፡፡ የክርስቶስ ትምሕርት የሕይወትና የነፃነት ትምሕርት ነው፡፡ የመሐመድ ትምሕርት ግን የሞትና የባርነት ትምሕርት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የልብ ዓይኖቻችሁን በመክፈት የሕይወትና የነፃነት መንገድ ወደ ሆነው፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተመሠረተው ትክክለኛው መንገድ ይመራችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡

ሴቶች በእስልምና