መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ለማስመሰል በሙስሊም ሰባኪያን ለሚጠቀሱት ጥቅሶች የተሰጠ ማብራርያ
ተከታዩ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ለማስመሰል በሙስሊም ሰባኪያን በማሕበራዊ ሚድያዎች ላይ እየተዘዋወረ የሚገኝ ሲሆን በጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች በተለያዩ እስላማዊ መጻሕፍት ውስጥም በተደጋጋሚ ሲጠቀሱ እንታዘባለን፡፡ አብዛኞቹ ጥቅሶች በጣም በቀላሉ ሊብራሩ የሚችሉ ሲሆን አንዳንዶቹ፣ በተለይም የካቶሊክና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በቀኖናነት ከተቀበሉት መጽሐፈ ሲራክ ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች ትክክለኛ ትርጓሜያቸውን ለማረጋገጥ ኦሪጅናል ግሪኩን ማየት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ መጽሐፈ ሲራክን ጨምሮ ሌሎች የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት በፕሮቴስታንትና በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የቀኖናነት ደረጃ እንደሌላቸው ይታወቃል ነገር ግን ለመንፈሳዊ ትምህርትና በተለይም ከዘመነ ነቢያት እስከ ክርስቶስ መምጫ ድረስ የሚገኙትን ክፍለ ዘመናት ታሪኮች ለማወቅ እንደሚጠቅሙ ስለሚታመንባቸው ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጎን ለጎን በነዚህ ወገኖች ይጠናሉ፡፡ ሙስሊም ወገኖች ብዙ ጊዜ ይህንን የቀኖና ልዩነት እንደ ችግር የሚያነሱ ቢሆንም እነርሱ ራሳቸው “ሐዲስ ቁድሲ” በማለት የሚጠሯቸው የሐዲስ ክፍሎች እንደ ቁርአን ሁሉ የአላህ ቃል ናቸው ወይስ አይደሉም? በሚለው ላይ ስምምነት የላቸውም፡፡ ክርስቲያኖች በነዚህ መጻሕፍት ዙርያ ያላቸውን ልዩነት በዚሁ መንገድ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለማንኛውም ለጥያቄ የቀረቡትን ጥቅሶች በሙሉ እንደሚከተለው እናብራራለን፡-
- “ከደረቅ ሴት ጋር ከምትኖር ከምድር አውሬዎች ከአንበሳዎች ጋር መኖር ይሽላል” (መጽሐፈ ሲራክ 25:16)፤ “ከጠበኛና ከቍጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል” (ምሳሌ 21፡14)
ታድያ ይሄ እውነት አይደለም እንዴ? ጥበብ ከሌላትና ለባሏ ከማትገዛ ሴት ጋር መኖር በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ ቃል ስለ መልካም ሴቶች ሳይሆን ስለ መጥፎ ሴቶች የተነገረ ነው፡፡ ምንም ስህተት የለበትም፡፡
—–
- “ሴት ልጅ ለአባቷ የተሠወረ ቁርጥማት ናት አሷን ማሰብ እንቅልፍ ያሳጣዋል” (መጽሐፈ ሲራክ 42:9 ተጨማሪ ሲራክ 42:14)
ይህም በጣም እውነት ነው፡፡ ሴት ልጅ ሕይወቷ በአደጋ የተከበበ ነው፡፡ ሴት ልጅ የወለደ አባት ሁሌም ስለ ልጁ ደህንነት ይጨነቃል፤ መጥፎ ወንዶች አደጋ እንዳያደርሱባት ይሰጋል፡፡ በመጨረሻም በጋብቻ ምክንያት ጥላው በመሄድ የሌላ ቤተሰብ አባል ትሆናለች፡፡ በጥንት ዘመን ደግሞ ሴት ልጅ ካገባች በኋላ አባቷ ከስም ውጪ የአባትነት መብቱን እስኪያጣ ድረስ ከልጁ ሕይወት ይገለላል፡፡ ይህ ትልቅ የልብ ስብራት ነው፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ ይህንን ሃቅ የሚገልፅ እንጂ ስህተት የለበትም፡፡
—–
- “በሰርግዋ ምሽት ድንግል ያልሆነችዋን ሴት ሁሉ ግደል” (ዘዳግም 22:20-21)
ጸሐፊው ጥቅሱን በቀጥታ ሳይሆን በራሱ አባባል ነው የጠቀሰው፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ድንግል አለመሆኗን እያወቀች የድንግል ዋጋ ተከፍሎባት በማግባት ባሏ ላይ የማታለል ወንጀል ስለምትፈፅም ሴት እንጂ ስለ ሁሉም ሴቶች አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጪ ስለሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በጣም ጥብቅ ትዕዛዛት አሉት፡፡ በሙሴ ሕግ መሠረት በጋብቻ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ወሲብ ከፈፀሙ ቅጣቱ በድንጋይ ተወግሮ መገደል ነው (ዘዳግም 22፡22)፡፡ ያላገባ ወንድ ካላገባች ወይም ካልታጨች ሴት ጋር ከተኛ ለጥሎሽ የሚከፈለውን ክፍያ ሁሉ ከፍሎ ልጅቱን የማግባት ግዴታ አለበት፡፡ አባቷ ልጁን ለመዳር ፈቃደኛ ካልሆነ ክፍያውን ተቀብሎ ጋብቻውን አለመቀበል ይችላል (ዘዳግም 22፡28-29)፡፡ የታጨች ድንግ የደፈረ ሰው ይገደላል (ዘዳግም 22፡25)፡፡ አንዲት ሴት ድንግል አለመሆኗን እያወቀች የድንግል ማጫ ዋጋ ተከፍሎባት ካገባችና ባሏን ካታለለችው ቅጣቱ በድንጋይ መወገር ነው፡፡ ይህ በአባቷ ቤት ሳለች ዝሙት በመፈፀሟ ምክንያት የሚደርስባት ቅጣት ነው፡፡ አንዲት ሴት ያለ ፈቃዷ ተደፍራ ለዚህ ቅጣት እንዳትዳረግ የሚከላከሉ ሕግጋት መኖራቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል (ዘዳግም 22፡23-29)፡፡ ባሏ በሐሰት ቢከሳት ወላጆቿ ያስቀመጡትን የድንግልና ማረጋገጫ ጨርቅ ለከተማ ሽማግሌዎች በማሳየት ሽማግሌዎች ሰውየው እንዲገረፍ ያደርጉታል፤ የድንግል ማጫ ሁለት እጥፍ ያህል ክፍያ እንዲከፍልም ይገደዳል፡፡ ልጅቱንም የመፍታት መብት አይኖረውም (ዘዳግም 22፡13-21)፡፡
ይህ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የሚደረግ ወሲብ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ኃጢአት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በእስልምናም ቢሆን ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ወሲብ የሚፈፅሙ ሰዎች በድንጋይ ተወግረው ይገደላሉ፡፡
ከላይ የሚገኘው ሕግ በመለኮታዊ አስተዳደር ስር ለነበሩት እስራኤላውያን የተሰጠ እንጂ ሁሉንም ሕዝቦች የተመለከተ አይደለም፡፡
—-
- “ከሴት ቸርነት የወንድ ንፉግነት ይሻላል ውሽማዋንና ባሏን የምታቃና ሴት አፍረት ናት “(መጽሐፈ ሲራክ 42:14)
ከአውዱ እንደሚታየው ጥቅሱ እየተናገረ ያለው ለትዳሯ ስለማትታመን መጥፎ ሴት ነው፡፡ የሚቀርብላትን የወሲብ ጥያቄ ሁሉ የምታስተናግድና ትዳሯን የማታከብር ሴት የወሲብ ጥያቄ የሚያቀርቡላትን ሰዎች እየጠቀመች ሳይሆን እየጎዳች ነው፡፡ ስለዚህ ቸርነቷ የክፋት እንጂ የደግነት አይደለም፡፡ የጥቅሱ ሐሳብ ይህ ነው፡፡
—-
- “ከልብስ ብል ይገኛል፤ኃጢያትም ሁሉ ከሴቶች ይገኛል” (መጽሐፈ ሲራክ 42:13-14)
ይህ የትርጉም ችግር ነው፡፡ ግሪኩ እንዲህ ይነበባል፡-
καὶ ἀπὸ γυναικὸς πονηρία γυναικός. (ካይ አፖ ጉናይኮስ ፖኔሪያ ጉናይኮስ)
የእንግሊዘኛው ትርጉም እንዲህ ይላል፡- “and woman’s spite out of woman.” (Sirach 42:13)፡፡
πονηρία (ፖኔሪያ) ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙ ኃጢአት ሳይሆን መጥፎ ስሜት፣ ክፋት፣ ስቃይ፣ በደል፣ ተንኮል፣ ማለት ነው፡፡ ኃጢአት በግሪክ ἁμαρτίας (ሐማርቲያስ) ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ኃጢአት ሊባሉ ቢችሉም ሴቶችን የኃጢአት ምንጭ በማስመሰል ከሚያቀርበው ትርጉም የተለየ ምልከታ እንዳላቸው ግልፅ ነው፡፡ ጥቅሱ ተብሎ መተርጎም የነበረበረበት “የሴት መጥፎ ስሜት ከሴት ነው” በማለት ነበር፡፡ ይህ ሁሉም ሰው ከውስጡ ለሚወጣው ክፋት ተጠያቂው ራሱ መሆኑን የሚገልፅ ነው፡፡ የወንድም መጥፎ ስሜት ያው ከራሱ ከወንድ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ካየነው ሴቶች አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት አዘውትረው እርስ በርሳቸው መጎዳዳታቸውን ለማመልከትም ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጥቅሱ ያለውን እውነታ የሚገልፅ በመሆኑ ችግር የለበትም፡፡
—-
- “ጥንቱንም ኃጢአት ከሴት ተገኘች፤ ስለ እርሱዋም ሁላችንም እንሞታለን” (መጽሐፈ ሲራክ 25:23)
ይህ ከተከለከለው ዛፍ አስቀድማ የበላችው እናታችን ሔዋን መሆኗን የሚገልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ እውነት ነው፡፡ በእስልምናም ቢሆን አስቀድማ ፍሬውን የበላችው ሔዋን መሆኗ ይታመናል፡፡ አልጠበሪና አል-ቁርጡቢ በሱራ አልበቀራ 2፡35-36 ላይ የሰጡን ማብራርያ መመልከት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የኃጢአት መድኃኒትም የመጣው በሴት በኩል መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
—-
- “ሚስጢርህን እንዳታወጣብህ ለሴት ልብህን አትስጣት” (መጽሐፈ ሲራክ 9:5)
ሲራክ 9፡5 እንደዚያ አይልም፡-“ፈቃዷ እንዳያስትህ ድንግልን አትቈንጥጣት” ነው የሚለው፡፡
ጸሐፊው የጠቀሰው ሐሳብ ቁጥር 2 ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አሁንም የትርጉም መዛባት ይታያል፡፡
ግሪኩ እንዲህ ይላል፡- μὴ δῷς γυναικὶ τὴν ψυχήν σου ἐπιβῆναι αὐτὴν ἐπὶ τὴν ἰσχύν σου. (ሜ ዶስ ጉናይኪ ቴን ፕሱኬን ሶው ኤፒቤናይ አውቴን ኤፒ ቴን ኢስኩን ሶው)
የእንግሊዝኛ ትርጉም እንዲህ አስቀምጦታል፡- “Do not put yourself in a woman’s hands or she may come to dominate you completely.”
ψυχήν σου (ፕሱኬን ሶው) ማለት “ነፍስህን” ወይም “እስትንፋስህን” ማለት ሲሆን ἰσχύν σου (ኢስኩን ሶው) ማለት ደግሞ “ኃይልህን” ማለት ነው፡፡ ጥቅሱ ኃይልን ወይም ሥልጣንን ስለማጣት እንጂ ስለ ምስጢር አይናገርም፤ ስለዚህ ትርጉሙ፡- “ለሴት ሙሉ በሙሉ ነፍስህን አትስጥ ሙሉ በሙሉ ሥልጣንህን እንዳታሳጣህ” የሚል ሐሳብ ነው ያለው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ባል የሚስት ራስ እንጂ ሚስት የባል ራስ አይደለችም፡፡ ጠንካራ ሆኖ ኃላፊነቱን በመወጣት ባል ይህንን ሥልጣኑን ማስጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ደካማና አቋም የለሽ ከሆነ ሚስት በባሏ ላይ በመሰልጠን ይህ የተፈጥሮ ሕግ ይጣሳል፡፡ ስለዚህ ምክሩ መልካም እንጂ መጥፎ አይደለም፡፡
—-
- “ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል” (ምሳ 25፡27)
አሁንም ጥቅሱ ስለ ሁሉም ሴቶች ሳይሆን ስለ መጥፎ ሴቶች ነው የሚናገረው፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ከእውነታ ያፈነገጠ ምንም ነገር የለም፡፡ ከጠበኛ ሴት ጋር መኖር በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ ይህንን የሚክድ ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ መልካም ሴቶች እንዳሉ ሁሉ ለትዳር የማይመቹ ጠበኛ ሴቶችም አሉ፡፡ ወንዶችም እንደዚያው፡፡ ይህንን የታወቀ ሃቅ መግለፅ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ?
—-
- “በቤትህ አጠገብ ለውሀ መፍሰሻ አታበጅለት ለሴት የልብህን ሚስጢር አታውጣላት” (መጽሐፈ ሲራክ 25:24)
አሁንም ችግሩ ከትርጉም ነው፡፡ ግሪኩ እንዲህ ይላል፡- μὴ δῷς ὕδατι διέξοδον μηδὲ γυναικὶ πονηρᾷ ἐξουσίαν. (ሜ ዶስ ኡዳቲ ዲዬግዛዶን ሜዴ ጉናይኪ ፖኔራ ኤክሶሲያን)
በእንግሊዘኛው ትርጉም እንዲህ ተብሏል፡- “Do not let water find a leak, nor a spiteful woman give free rein to her tongue.”
ይህም ሲተረጎም “ለውኀ መፍሰሻ ሽንቁር አታብጅለት፤ ለመጥፎ ሴት ምላስም ነፃነት አትስጥ” የሚል ነው፡፡
γυναικὶ πονηρᾷ (ጉናይኪ ፖኔራ) ማለት “መጥፎ ሴት” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ ሁሉንም ሴቶች ሳይሆን በምላሷ በመለፍለፍ ጥፋት የምታስከትልን ሴት የተመለከተ ነው፡፡
—-
- ሴት ልጅ ሚስጥር መጠበቅ አትችልም፡- ”በእቅፍክ ለምትተኛዋ እንኳ ስለ ምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ” (ሚኪያስ7:5)
ይህ ጥቅስ ሴት ልጅ ምስጢር መጠበቅ አትችልም አይደልም፡፡ ነገር ግን የጥቅሱን አውድ ስንመለከት ደግና ምስጢር ጠባቂ ሰው ከምድር ላይ ተመናምኖ የሚታመን ሰው የሚጠፋበት ዘመን እንደሚመጣ የሚናገር ሲሆን በዚያን ጊዜ ሚስት እንኳ እንደማትታመን የሚናገር ነው፡፡ “ሴት ልጅ ሚስጥር መጠበቅ አትችልም” የሚል ሐሳብ የለውም፡፡ ሚስትን ጨምሮ ሰው ሁሉ የማይታመንበት ዘመን እንደሚመጣ የሚናገር ነው፡፡
—-
- ሴት ልጅ ደካማ ናት፡- “እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ” (1ኛ የጴጥሮስ 3:7)
አውዱ እንዲህ ይላል፡- “እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው፡፡” (1ጴጥሮስ 3፡7)፡፡
“ደካማ ፍጥረት” (Weak Vessels) የሚለው ሴቶች በስሜትና በአካል ከወንድ አንፃር ደካሞችና እንክነብካቤ የሚያሻቸው መሆናቸውን እንጂ በመንፈስና በአዕምሮ ደካማ መሆናቸውን አያሳይም፡፡ ወንዶች ሴቶችን ካላከበሩ ጸሎታቸው እግዚአብሔር ዘንድ እንደማይደርስ መነገሩ ሴቶች በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ደረጃና በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ የሚገልፅ ነው፡፡ ይህ ሴት ልጅ ከፊት ካለፈች ጸሎት እንደሚቋረጥ ከሚናገረው እስላማዊ አስተምሕሮ ምንኛ የተለየ ነው!
—-
- ሴት ልጅ በድንጋይ ትወገር፡- “የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት” (ኦሪት ዘዳግም 22:21)
ከጋብቻ በፊት ወሲብ የፈፀመችን ሴት እንጂ ዝም ተብሎ ሴትን በድንጋይ ውገራት አልተባለም፡፡ እስልምና ከጋብቻ ውጪ ዝሙት የፈፀመችን ሴት ምን አድርጉ ይላል? ይህ የብሉይ ኪዳን ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በመሆኑ ቴዎክራሲያዊ መንግሥት በሌለበት ሊተገበር አይችልም፡፡ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ሕጉ አይሠራም፡፡ ሙስሊሞች ግን በሸሪኣ ሕግ መሠረት ዛሬም ይህንን ተግባራዊ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡
—-
- ሴት ልጅ በእሳት ትቃጠል፡- “የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች በእሳት ትቃጠል” (ኦሪት ዘሌዋውያን 21:9)
ሙስሊሙ ይህንን ጥቅስ ሲጠቅስ ጤነኛዋን ሴት አቃጥሉ የተባለ በማስመሰል ቢሆንም በግልፅ እንደሚታየው ራሷን በግልሙትና በምታረክስ የካህን ልጅ ላይ የተላለፈ ፍርድ ነው፡፡ ይህም የብሉይ ኪዳን ሕግ እንጂ በአዲስ ኪዳን የሚሠራ አይደለም፡፡
—-
- 50 ብር ካሎት ልጃገረድ(ድንግል) መውሰድ ይችላሉ፡- “ማንኛውም ሰው ድንግልና ያለትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ ወስዶም ቢደርስባት ቢያገኙትም ያ የደረሰባት ሰው አምሳ (50) የብር ስቅል ለብላቴናይቱ አባት ይስጥ፣ አስነውሯታልና ሚስትም ትሁነው በዕድሜ ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም፡፡” (ኦሪት ዘዳግም 22፡28-29)
የጥቅሱ ሐሳብ አንድ ሰው ድንግል የሆነችን ሴት አባብሎ ድንግልናዋን ቢወስድ አምሳ የብር ሰቅል ከከፈለ በኋላ ያግባት የሚል ነው፡፡ ጋብቻውም ሴቷን በማስገደድ ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚደረግ ነው፡፡ አምሳ የብር ሰቅል ማለት 800 ግራም ብር ማለት እንጂ አምሳ የኢትዮጵያ ብር ማለት አይደለም፡፡ ይህ እንኳንስ በዚያ ዘመን ይቅርና በዚህ ዘመን እንኳ በጣም ውድ ክፍያ ነው፡፡
—-
- ሃፍረተ ስጋዋን ለሰውና ለመንግስታት ማሳየት፡- “እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በፊትሽ: እገልጣለሁ ኅፍረተ ሥጋሽንም ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ ርኵሰትንም በላይሽ እጥላለሁ፥ እንቅሻማለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ” (ትንቢተ ናሆም 3:5)
ይህ ጣዖት አምላኪ በመሆን እግዚአብሔር ላይ በደል ስለፈፀመችው የእስራኤል መንግሥት የተነገረ ዘይቤያዊ ንግግር እንጂ ስለ ሴት ልጅ አይደለም፡፡
—-
- ሴትን ልጅ ረግሜኣታለው፡- “እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ ፤ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ” (ትንቢተ ሚልክያስ 2:2)
ጥቅሱ ሴትን ልጅ ረግሜአታለሁ ይላልን? “በረከታችሁንም እረግማታለሁ” ነው የሚለው፡፡ ይህንን ዝርዝር ያዘጋጀው ሰው መሠረታዊ የማንበብ ክህሎት እንኳ ያለው አይመስልም፡፡
- ጋለሞታ ማለት አንዲት ሴት አግብታ የፈታች ወይም ባሏ የሞተባት ሴት ማለት ነው፡- “ጋለሞታ ሴት የተጠላች አዘቅት ናትና” (ምሳሌ 23፣27) “ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት የረከሰች ሴት አያግባ ወይም ከባሏ የተፈታችን ሴት አያግባ” (ኦሪት ዛሌላውያን 21:7)
“ጋለሞታ” ማለት ዝሙተኛ ሴት ማለት እንጂ አግብታ የፈታች ወይም ባሏ የሞተባት ማለት አይደለም፡፡ የአማርኛ ቋንቋ እጥረት ያለበት ሰው ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ ስህተት የሚሠራ ሰው ፈፅሞ የለም፡፡ ጥቅሶቹ በእንግሊዘኛ ትርጉሞች “whore” ነው የሚሉት በዕብራይስጥ ደግሞ “ዘና” ይላሉ፡፡ ዕብራይስጥና አረብኛ ስለሚቀራረቡ ዝርዝሩን ያዘጋጀው ሰው አረብኛ የሚችል ከሆነ “ዚና” ከሚለው ቃል ተነስቶ መረዳት ይችላል፡፡ “ዚና” ማለት “በአረብኛ “ዝሙት” ማለት ነው፡፡ ዘሌዋውያን 21፡7 “ጋለሞታ ወይም ከባሏ የተፈታች” በማለት ለሁለት ከፍሎ አስቀምጧል፡፡ የእግዚአብሔር ካህን አገልግሎቱ ላይ እንቅፋት እንዳይገጥመው ማግባት ያለበት ድንግል የሆነችን ሴት እንጂ ከዚህ ቀደም ጋብቻ የፈፀመች መሆን እንደማይገባው ተነግሯል፡፡ ሕጉ የተሰጠው በኢየሩሳሌም መቅደስ ውስጥ ለሚያገለግሉ ጥቂት ካህናት እንጂ ለሕዝቡ ሁሉ የተሰጠ አይደለም፡፡
—-
- ”ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል በክርስቶስ ላይ ተነስተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና” (ጢሞቴዎስ 5:11)
የጥቅሱ አውድ የሚናገረው በቤተክርስቲያን የመበለቶች መዝገብ ላይ ስለሚመዘገቡ ሴቶች ነው፡፡ በዕድሜ ወጣት የሆኑትን በመበለትነት መመዝገብ አያስፈልግም እያለ ነው፤ ምክንያቱም ወጣት ሴቶቹ የማግባት ፍላጎት ሊኖራቸው ስለሚችል ያለ ጋብቻ በመኖር ቤተክርስቲያንን የማገልገል ቃል ኪዳናቸውን ሊያፈርሱ ስለሚችሉ መመዝገብ አያስፈልግም፡፡ ይህ ሴቶቹ ለፈተና እንዳይዳረጉ ከማሰብ አንፃር ነው፡፡ ምንም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡
—-
- ውሻ እና ሴት፡- “ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የጋለሞታይቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና።” (ኦሪት ዘዳግም 23 ፣ 17-18)
ከሴተኛ አዳሪነት የተገኘ ገንዘብና ከውሻ ሽያጭ የተገኘ ገንዘብ በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ በመሆናቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳይመጡ መከልከሉ ምን ያስገርማል? ይህ ሰው በተከታዩ ሐዲስ የተሸማቀቀና እርሱን የሚመስል ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ የገባ መሆን አለበት፡-
“አቡ ዘር እንዳስተላለፈው፡- የአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ብለዋል፡- ከመካከላችሁ አንድ ሰው ለጸሎት በሚቆምበት ሰዓት… ከፊት ለፊቱ የኮርቻ ያህል መጠን ያለው ነገር የማይኖር ከሆነ ጸሎቱ (በፊቱ በሚያልፍ) አህያ፣ ሴት እና ጥቁር ውሻ ይቋረጣል፡፡ እኔም አቡ ዘር ሆይ ጥቁር ውሻን ከቀይ ወይም ከቢጫ የሚለየው ምንድነው? ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እርሱም የወንድሜ ልጅ ሆይ አንተ እንደጠየቅኸኝ ሁሉ እኔም የአላህን መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ጠይቄያቸው ነበር፤ ‹ጥቁር ውሻ ዲያብሎስ ነው› በማለት ነበር የመለሱልኝ፡፡” (Sahih Muslim, Book 004, Number 1032)
ሙስሊም ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ለማስመሰል የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች እነርሱ የሚሉትን ሐሳብ እንደማያስተላልፉ ከላይ በበቂ ሁኔታ አብራርተናል፡፡ አሁን ደግሞ እስልምና ሴቶችን በተመለከተ ምን እንደሚያስተምርና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አቋም ምን እንደሆነ ማየት ያስፈልገናል፡፡ ሴቶች በቁርኣን በሐዲስና በመጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡