ሙሐመድ – የማደጎ ልጁን ሚስት የቀማ ነቢይ!

ሙሐመድ – የማደጎ ልጁን ሚስት የቀማ ነቢይ!

የእስልምናው ነቢይ ሙሐመድ ዘይድ ኢብን ሐሪሣህ የተሰኘ ባርያ ነበረው፡፡ ያንንም ባርያ በዓረብ ቅድመ-ኢስላም እንደሚደረገው በማደጎ ሊያሳድገው እንደልጁ ወሰደው፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የልጁ ስም ዘይድ ኢብን ሙሐመድ ተብሎ መጠራት ጀመረ፡፡ በወቅቱ በነበረው የዓረቦች ባሕል መሠረት አንድ በማደጎ የሚያሳድግ አባት በማደጎ የሚያድገውን ልጅ እንደ አብራኩ ክፋይ በማየት ለልጆቹ የሚያርገውን አባታዊ ተግባር ያለማጓደል በማድረግ ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳድገዋል፤ እንደ አባት ወግም ሚስት ያጋባዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አሳዳጊው አባት የአብራኩ ክፋዮች ንበረትም ሆነ ማንኛውም ነገር የሚመለከተውን ያህል የማደጎው ልጅ ጉዳይም ይመለከተዋል፡፡ አንድ አባት ልጁ ሚስት ቢያገባ የልጁን ሚስት እንደ ልጁ ያያታል፡፡ ምክንያቱም የልጁ ሚስት ናትና፡፡ በወቅቱ በነበረው የዓረቦች ባሕል መሠረት ከማደጎው ልጅ ይልቅ ለአብራካቸው ክፋይ የሚያደሉ ወላጆች በማሕበረሰቡ ዘንድ የተወገዙ ይሆኑ ነበር፤ እንደ ክፉ ሰዎችም ይቆጠራሉ፡፡ ይህንን ሰናይ ተግባር ማንም አዕምሮ ያለው ሰው የሚያደንቀውና የሚደግፈው ነው፡፡

ሙሐመድ በዚህ የዓረብ ባሕል መሠረት ልጁን ዘይድን በቁረይሽ መካከል ከተመረጠች ዘይነብ ከምትባል መልከ መልካም ሴት ጋር አጋባው፡፡ ጥሩ ተግባር! ችግሩ የሚፈጠረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ “ነቢዩ” ከዕለታት አንድ ቀን ልጁን ዘይድን ሊጎበኘው ወደቤቱ ይኼዳል፡፡ በሰዓቱም ዘይድ ቤት አልነበረም፡፡ እስላማዊ ምንጮች እንደሚናገሩት ሚስቱም ዘይነብ እርቃኗን (እጅግ ገላጣ በሆነ አለባበስ) ቤቷ ውስጥ ነበረች፡፡ የቤቷ በር ላይ የነበረው ስስ መጋረጃ በንፋስ ተገልጦ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ “ነቢዩ” በር ላይ ቆሞ ዘይነብን ሙሉ አርቃኗን ተመልክቷት በልቡ የተመኛት፡፡ ከዚያም “አላህ እንዳገባት መገለጥን ላከልኝ” በሚል በቁርአን ሱረቱ አል-አሕዛብ 33፡37-40 ላይ ሚገኘውን ተናገረ፡፡ አወይ መለኮታዊ መገለጥ! ይህንን ታሪክ አስመልከቶ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ የሚገኙትን ማስረጃዎች ከቁርአን በመጀመር አብረን እንመለከታለን፡-

ለዚያም አላህ በርሱ ላይ ለለገሰለትና (አንተም ነጻ በማውጣት) በርሱ ላይ ለለገስክለት ሰው (ለዘይድ)፥ አላህ ገላጩ የኾነን ነገር በነፍስህ ውስጥ የምትደብቅና አላህ ልትፈራው ይልቅ የተገባው ሲኾን፣ ሰዎችን የምትፈራ ሆነህ ፦ ሚስትህን ባንተ ዘንድ ያዝ፤ (ከመፍታት) አላህንም ፍራ፤ በምትል ጊዜ፥ (አስታውስ) ዘይድንም ከርሷ ጉዳይን በፈጸመ ጊዜ (1) በምእምናኖች ላይ፣ ልጅ አድርገው ባስጠጉዋቸው (ሰዎች) ሚስቶች፥ ከነሱ ጉዳይን በፈጸሙ ጊዜ (በማግባት) ችግር እንዳይኖርባቸው፥ እርሷን አጋባንህ፤ የአላህም ትእዛዝ ተፈጻሚ ነው። በነቢዩ ላይ አላህ ለርሱ በፈረደው ነገር ምንም ችግር ሊኖርበት አይገባም፤ በነዚያ ከዚያ በፊት ባለፉት (ነቢያት)፥ አላህ የነገረው የአላህን ትእዛዝ የተፈረደ ፍርድ ነው። ለነዚያ የአላህን መልክቶች ለሚያደርሱና ለሚፈሩት፥ ከአላህ በስተቀር አንድንም ለማይፈሩት (ተደነገገ)፤ ተቆጣጣሪም በአላህ በቃ። ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድንም ሰው አባት አይደለም፤ ግን የአላህ መልክተኛና የንቢዮች መደምደሚያ ነው፤ አላህም በነገሩ ሁላ ዐዋቂ ነው። ሱረቱ አል-አሕዛብ 33፡37-40

በዚህ ክፍል በተጻፈው መሠረት አላህ ወደ ብርሃን ሊያወጣ ያለውን እውነት ሙሐመድ በልቡ ደብቆ ነበር፡፡ ይህም ማለት ሙሐመድ የልጁን ሚስት የማግባቱን ጉዳይ ሙሐመድ ቢደብቅም አላህ ወደ ብርሃን አውጥቶታል፡፡ ስለዚህ ፍቺው ገና ሳይፈፀም አላህ ሙሐመድ ባለትዳር በሆነች ሴት በዘይነብ ፍቅር እንዲወድቅ አድርጎታል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ሙሐመድ ዘይነብን ማግባት ስላለበት እንድትፋታ ያደረጋት ራሱ አላህ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ በማጽደቂያነት የቀረበው ዓረቦች የማደጎ ልጆቻቸውን ሚስቶች ከፍቺ በኋላ ማግባት ይችሉ ዘንድ ምሳሌ ለመሆን የሚል አስገራሚ ምክንያት ነው፡፡ ሙስሊም ሰባኪያንም ይህንን የመሐመድን የተኮነነ ተግባር ለማጽደቅ የማደጎ ልጅን ሚስት ማግባት አለመቻልን ትልቅ ማሕበራዊ ችግር በማስመሰል ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን አሳዳጊዎች የማደጎ ልጆቻቸውን ሚስቶች ማግባት በመከልከላቸው ምክንያት ማሕበራዊ ሥርዓቱ የተናጋ ማሕበረሰብ በዓለም ላይ አልታየም፡፡ ሙሐመድ ዘይነብን የተመኛት ባለትዳር በነበረችበት ጊዜ በመሆኑና ስለ ውበቷ ባልተገባ መንገድ በመናገሩ ለትዳሯ መናጋትና ለፍቺ ምክንያት መሆኑ በእስላማዊ ሐዲሳት ውስጥ በግልፅ ተጽፎ ስለሚገኝ “ምሳሌ ለመሆነ ነው” የሚለው ሰበብ አያስኬድም፡፡[1] ይህ ዓይነቱ አመክንዮ ሙሐመድን በግድ ነቢይ ለማሰኘት የተደረገ ከንቱ ጥረት ነው፡፡ አሳማኝ አይደለም፡፡

ይህ የሙሐመድ ተግባር ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ኢ-ሞራላዊ ከመሆኑም በላይ በዓረቦች ዘንድ ክቡር የነበረውን የማደጎ ልጅ አስተዳደግ ሥርአት አላህ ለሙሐመድ የወሲብ ስሜት ሲል ብቻ አጣጥሎ አራክሶታል፡፡ “ከዚህ በኋላ በገዛ አባቶቻቸው ስም ጥሯቸው እንጂ እንደልጅ አድርጋችሁ አትዩአቸው” ብሏል፡፡ የሚገርመው ነገር ቁጥር 38 ላይ አላህ ባለፉት ነቢያትም ላይ እንዲህ ያለ ነገር ደንግጓል ይለናል፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን በታሪክ ውስጥ ካለፉት ነቢያት የማደጎ ልጁን ሚስት አስፈትቶ ያገባ አንድ ነቢይ ሊጠቅሱልን ይችሉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን፡፡ እንኳንስ ከነቢያት መካከል ይቅርና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ከሚባሉት ጥሩ ሰዎች መካከል አንዱ እንኳ ይህንን ተግባር ስለመፈፀሙ ማስረጃ ማቅረብ ይችሉ ይሆን?

በቀደሙ ነቢያት አስተምሕሮ መሠረት ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ ነው፡፡ ያሕዌ እግዚአብሔር በትዳር የታሰረችን ሴት ስለመመኘትና ፍቺን መፈፀምን በተመለከተ በቀደሙ ነቢያት አማካኝነት ጠንካራ ትእዛዛትና ማስጠንቀቂያዎችን ሰጥቷል፡፡ በእግዚአብሔር ባርያ በሙሴ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ሲል ተጽፏል፡-

የባለንጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባለንጀራህንም ቤት እርሻውንም ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም፣ ከባለንጀራህም ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ፡፡  (ዘዳ. 5፡21)

በነቢዩ በሚልክያስ መጽሐፍም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡-

ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል እግዚአብሔር ቁርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በለቅሶ በኀዘን ትከድናላችሁ፡፡ እናንተም፡- ስለ ምድር ነው? ብላችኋል፡፡ ሚስትህ ባልጀራህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ሆና ሳለች እርሷን አታልለሃልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆ የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፣ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል፡፡ መፋታትን እጠላለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዘህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ፡፡ (ሚል. 2፡13-16)

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነቢያትን ትምሕርት በማጠናከር እንዲህ ሲል ጉዳዩን ወደ ላቀ የሥነ መግባር ደረጃ ወስዶታል፡-

አታመንዝር እንደተባለ ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል፡፡  (ማቴ. 5፡27-28)

እንግዲህ ከላይ ባየናቸው የቀደምት ነቢያት አስተምሕሮ መሠረት ሙሐመድ የዝሙት ኃጢአት ተወቃሽ ነው፡፡ ልብ በሉ፤ ሙግታችን አንድ ነቢይ ኃጢአት ሊሠራ አይችልም የሚል አይደለም፡፡ ዳዊትን የመሳሰሉት ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች አስደንጋጭ ኃጢአቶችን ፈፅመዋል፡፡ ነገር ግን ተግባራቸው ትክክል አለመሆኑን በመቀበል ስለ ኃጢአታቸው ንስሐ በመግባት እግዚአብሔርን ይቅርታ ሲጠይቁ እንጂ ኃጢአታቸውን ለማጽደቅ መገለጥን ሲናገሩ አናገኛቸውም፡፡ ሙሐመድ ግን የማደጎ ልጁን ሚስት በመመኘት ኃጢአት ፈፅሟል፤ የልቡን ምኞት ለማርካት ሲልም ተገቢ ያልሆነ የአድናቆት ንግግር በመናገር ትዳሯን ካናጋ በኋላ አግብቷታል፡፡ ደሩ ግን ኃጢአቱን አምኖ ንስሐ እንደ መግባት አላህ እንደ ፈቀደለት በመናገር የረከሰውን ተግባሩን አጽድቋል፡፡ ይህ ፈጣሪን የኃጢአት ተባባሪና ተዋናይ በማድረግ ክብሩን ማቃለል ነው፡፡

የዚህ ተግባር ሌላው ችግር በጥሩ ግብረ ገብነት ላይ የተመሠረተውን የማደጎ ሥርዓት አላህ በጭፍን ሲያጥላላና ሲያሰቀር መታየቱ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ በማደጎ የሚያድጉ ልጆችን በአሳዳጊያቸው ጠርቶ የልጅነትን መብት እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ በገዛ አባታቸው ስም እንዲጠሩ ሲያስገድድ እናያለን፡-

አላህ ለአንድ ሰው በሆዱ ውስጥ ሁለትን ልቦች አላደረገም፤ ሚስቶቻችሁንም እነዚያን ከነርሱ እንደናቶቻችሁ ጀርባዎች ይኹኑብን የምትሏቸውን እናቶቻችሁ አላደረገም። ልጅ በማድረግ የምታስጠጓቸውንም ልጆቻችሁ አላደረገም፤ ይሃችሁ በአፎቻችሁ የምትሉት ነው፤ አላህም እውነቱን ይናገራል፤ እርሱም ትክክለኛዉን መንገድ ይመራል። ለአባቶቻቸው (በማስጠጋት) ጥሩዋቸው፤ እርሱ አላህ ዘንድ ትክክለኛ ነው፤ አባቶቻቸውንም ባታወቁ፣ በሃይማኖት ወንድሞቻቸሁና ዘመዶቻችሁ ናቸው፤ በርሱ በተሳሳታችሁበትም ነገርም በናንተ ላይ ሐጢያት የለባችሁም፤ ግን ልቦቻችሁ ዐዉቀው በሠሩት ( ሐጢያት አለባችሁ) አላህም መሃሪ አዛኝ ነው። (ሱረቱ አል-አሕዛብ 33፡4-5)

በዚህ ክፍል መሠረት አላህ በሰዎች ሆድ ውስጥ ሁለት ልብ እንዳልፈጠረ ሁሉ ሚስቶቻቸውን እንደ እናታቸው ማየት እንደሌለባቸውና ያስጠጓቸውንም የማደጎ ልጆች እንደራሳቸው ልጆች ማየት እንደሌለባቸው ተነግሯል፡፡ “ያስጠጋችኋቸው ልጆች ‹‹ልጆቻችን ናቸው›› አትበሉ፤ ይህ እናንተ በአፋችሁ የምትሉት ነው እንጂ አላህ ልጆቻችሁ አላደረገም፤ ይህም በመሆኑ በአባቶቻቸው ስም ጥሯቸው” ይላል፡፡ “አባቶቻቸውን ባታውቁ ወንድሞቻችሁ እንጂ ልጆቻችሁ አይሁኑ” ይላል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ከሰማይ እንደ ወረደ ግልጠተ መለኮት ታምኖ ላለፉት አሥራ አራት ክፍለ ዘመናት የሙስሊሙ ዓለም መመርያ የሆነው፡፡ ቅድመ-ኢስላም የነበሩ ዓረቦች እንኳ የነበራቸውን ሰብአዊ በጎነት አምላክ የተባለው አላህ ሳይኖረው ይታያል፡፡ የዓረቦቹን በጎ ባሕርይም ሲያጥላላና ሲያበላሽ ይታያል፡፡ ይህ ቃል እንደ አምላክ ቃል መታመኑ የሚያስገርም ነው፡፡

ይህንን ጥቅስ በተመለከተ ኢብን ከሢር እንዲህ ይላል፡-

<ልጅ በማድረግ የምታስጠጓቸውንም ልጆቻችሁ አላደረገም>

ይህ ክፍል ነፃ የተደረገውን የነቢዩን ባርያ ዘይድ ኢብን ኋሪዝን በተመለከተ የወረደ ነው፡፡ አላህ ክብር ይግባውና፡፡ ነቢዩ ነቢይ ከመሆናቸው በፊት ጉዲፈቻ (በማደጎ) ወስደውት ነበር፡፡ ልጁም ዘይድ ኢብን ሙሐመድ ይባል ነበር፡፡ አላህም በዚህ አጠራርና ሁኔታ ላይ ገደብን ማድረግ ፈለገ፡፡

ይህ ክፍል ከኢስላም በፊት የነበረውን በማደጎ የሚያድጉ ልጆች በሚያሳድጋቸው ሰውዬ ስም የሚጠሩበትን ሂደት ለመሻር የመጣ ትዕዛዝ ነው፡፡ ከዚያም አላህ በስጋ አባቶቻቸው ስም እንዲጠሩ አዘዘ፤ ይህም የበለጠ ፍትሐዊና ተገቢ ነበር፡፡ አል-ቡኻሪ እንደዘገበው አብደላህ ኢብን ኡመር እንዳለው ነፃ የሆነው የነቢዩ ባርያ ዘይድ የቁርአኑ ክፍል እስኪወርድ ድረስ ሁል ጊዜ ዘይድ ኢብን ሙሐመድ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡

በዚህም ክፍል አላህ የማደጎ ልጆች ወላጅ አባቶቻቸው የሚታወቁ ከሆነ በወላጃቻቸው ስም እንዲጠሩ ያዛል፡፡ ወላጆቻቸው ያልታወቁ ከሆነ ግን የሃይማኖት ወንድሞች ወይም ነፃ የሆኑ ባሮች ተብለው መጠራት እንዳለባቸው ያስተምራል፡፡ ይህም ትክክለኛው ዘራቸው ስለማይታወቅ ለማስተካከል ነው፡፡[2]

ኢብን ከሢር ስለ ሱረቱ አል-አሕዛብ 33፡40 ሲጽፍ፡-

<ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ መካከል የማንም አባት አይደለም>

ከዚህ ክፍል በኋላ ዘይድ ኢብን ሙሐመድ ብሎ መጥራት የተከለከለ ሆነ፡፡ ምንም እንኳ በማደጎ ቢያሳድገውም አባቱ አልነበረምና፡፡[3]

እንግዲህ ሙሐመድ ለአሳዳጊ አባቶች የልጆቻቸውን ሚስት እንዲያገቡ አርአያ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ምን የሚሉት አርአያነት ነው? አላህ የማደጎ ልጅ ማሳደግን ለመከልከል ፈልጎ ነው? እንዲያ ከሆነ በቀጥታ በትእዛዝ መልክ መገለጡን ማውረድ ሲችል ሙሐመድን የማደጎ ልጁን ሚስት እንዲያገባ ማዘዙ ምን የሚሉት አሠራር ነው? ለምሳሌ ያህል ሙሐመድ ሙስሊም ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንዲመቱ አዟል፡፡ ይህን ትእዛዝ ሲያዝ ሚስቶቹን በመምታት በተግባር እያሳያቸው ነበርን? ካልሆነ ታድያ ሙስሊሞች የማደጎ ልጆቻቸውን ሚስት ማግባት እንደሚችሉ ሕግ ለመስጠት ሙሐመድ የግድ ማግባት የነበረበት ለምንድነው? ይህ ሙሐመድ የገዛ ስሜቱን በአላህ አሳብቦ ከግብ ለማድረስ የፈጠረው የፈጠራ ሰበብ እንጂ የአምላክ ቃል ሊሆን አይችልም፡፡ ሙሐመድ በዘይነብ ፍቅር ከወደቀ በኋላ በሰዎች ለሚደርስበት ትችት መልስ ይሆነው ዘንድ ከአላህ መገለጥ ወረደልኝ ብሎ አታለላቸው፡፡ ከዚያም በመቀጠል ራሱን ከወቀሳ ለማስመለጥ አማኞች ሁሉ የማደጎ ልጆቻቸውን ፈት ሚስቶች ማግባት ተፈቅዶላቸዋል ብሎ መልካሙን ባሕል ውኀ ሲያበላው ይታያል፡፡ ድንቄም ነቢይ!

ከዚህ ታሪክ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሌሎች ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሙሐመድ ዘይነብን እንዲያገባ የአላህ ፈቃድ ከሆነ ለዘይድ ሳያጋባው አስቀድሞ ለራሱ እንዲያገባት አይገልጥለትም ነበርን? “ነቢዩ” ዘይነብን እርቃኗን ካያት በኋላ ነገሩ የተገለባበጠው በምን ምክንያት ነው? የእውነት ለትዳር ፈልጓት ቢሆን ኖሮ ዘይድን ከማጋባቱ በፊት ለራሱ ማግባት ይችል ነበር፤ ነገር ግን ከዘይድ ጋር ካጋባት በኋላ በአጋጣሚ እርቃኗን ሲያይ አላህ ለኔ ፈቅዶልኛል ብሎ አገባት፡፡ ይህ የሚያሳየው ሙሐመድ ወሲባዊ ስሜቱን ለማርካት ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይልና በምክንያታዊነት ሳይሆን በፍትወት ስሜት የሚነዳ ሰው እንደ ነበር ነው፡፡ ህፃን ሚስቱ አይሻ ይህንን ሁኔታ ከታዘበች በኋላ፡- “አምላክህ ስሜትህን ለማርካት ይጣደፋል” በማለት ሙሐመድን በነገር መጎሽመጧ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡[4]

ውድ ሙስሊሞች!

ቆም ብላችሁ አስቡ፡፡ ሙሐመድ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ አላህ ፈቅዶልኛል በሚል የማታላያ ቃል ለራሱ ሲያመቻች የኖረ ሰው እንጂ እንደ ቀደሙት ነቢያች ለእውነት የኖረ ነቢይ አልነበረም፡፡ የ9 ዓመት ህፃን ማግባት ሲፈልግ “አላህ ገለጠልኝ” አለ፤ የማደጎ ልጁን ሚስት ማግባት ሲፈልግ “አላህ ገለጠልኝ” አለ፤ ለሙስሊሞች አራት ሚስት ብቻ ሲፈቀድላቸው እርሱ ግን አሥራ አንድ ሚስት “አላህ ፈቅዶልኛል” ብሎ የቁርአኑን ሕግ ጥሶ አገባ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሰዎ እንዲገደሉ “አላህ ገልጦኛና፣ ማንም በእኔ ሥልጣን ላይ ጥያቄ ማንሳት አይችልም” አለ፡፡ ኧረ ምኑ ተቆጥሮ ምኑ ያልቃል?

እንዲህ ያለ ሰው ነቢይ ሊባል ይገባዋልን? ነቢይ ከተባለስ ሐሰተኛ ነቢያት ምን ዓይነት ሊሆኑ ነው? እስኪ ሙሐመድ ያልፈፀመውን አንድ ኃጢአት ጥቀሱልን? ነፍሰ ገዳይነት ነውን? ዝሙት ነውን? ዝርፍያ ነውን? ሐሰትን መናገር ነውን? አምልኮተ ጣዖት ነውን? ዘረኝነት ነውን? ሴቶችና ህፃናትን መድፈር ነውን? የገዛ መጻሕፍታችሁ ሙሐመድ እነዚህን ሁሉ ኃጢአቶች ስለመፈፀሙ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ውድ ሙስሊሞች፣ እንዲህ ያለ ነውርና ክፋት ያልተገኘበትን አንድ አዳኝ እንጠቁማችሁ፡፡ ስሙ ኢየሱስ ይባላል! በእብራይስጥ ዬሹዋ መሺያኽ ብለው ይጠሩታል፣ ዓረብ ክርስቲያኖች የሱዋ አል-መሲህ ይሉታል፣ እናንተ ደግሞ አል-መሲህ ዒሳ ትሉታላችሁ፡፡ እርሱ ፍፁም ጻድቅ፣ ንፁህና ኃጢአት የሌለበት መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን ከኃጢአታቸው ለማዳን ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ እንዲህ ይላችኋል፡-

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡28)

ይህ ቅዱስ ጌታ እናንተ በገዛ ሥራችሁ ልታገኙት ያልቻላችሁትን የዘላለምን ሕይወት በነፃ ይሰጣችኋል፡፡ ኃጢአትን ድል የምትነሱበትንም ቅዱሱን መንፈስ ይልክላችኋል፡፡ ዛሬውኑ በስሙ በማመን ከዘላለም ጥፋት ትድኑ ዘንድ ጥሪን እናቀርብላችኋለን!


 

[1] Sahih Muslim, Book 008, Number 3330

[2] Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 7 (Surat An-Nur to Surat Al-Ahzab, Verse 50), abridged First Edition: 2000, pp. 634-637

[3] ዝኒ ከማሁ ገፅ 701

[4] Sahih Al-Bukhari, book 60, Hadith 311


ነቢዩ መሐመድ