የ2ኛ ጴጥሮስ መልዕክት ነገረ ክርስቶስ፡ ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት ምላሽ

የ2ጴጥሮስ መልዕክት ነገረ ክርስቶስ

ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት ምላሽ

ወንድም ሚናስ


ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት ስለመሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የማያወላዳ ምስክርነት ይሰጣሉ። ከእነዚህ ምስክርነቶች መካከል የተወሰኑቱ በተለያዩ መንገዶች ሊተረጎሙ የሚችሉ በመሆናቸው ከሌሎች ግልፅ ጥቅሶች ጋር በማስደገፍ መመልከት አስፈላጊ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን ችለው በመቆም እጅግ ጠንካራ በሆነ አውድና የቋንቋ አጠቃቀም አምላክነቱን የሚገልጡ ናቸው። ከእነዚህ ጠንካራ ጥቅሶች መካከል አንዱ በሐዋርያው ጴጥሮስ የተጻፈ ነው። ሐዋርያት ከክርስቶስ ጋር አብረው ስለነበሩ ስለማንነቱ ከማንም በላይ ያውቃሉ ስለዚህ የእነርሱ ምስክርነት ለኢየሱስ አምላክነት ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል፦

“የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ስምዖን ጴጥሮስ፤ በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤” — 2ኛ ጴጥሮስ 1፥1 (አዲሱ መ.ት)

Σίμων Πέτρος δοῦλος καὶ ἀπόστολος Ἰησοῦ Χριστοῦ τοῖς ἰσότιμον ἡμῖν λαχοῦσιν πίστιν ἐν δικαιοσύνῃ τοῦ θεοῦ ἡμῶν καὶ σωτῆρος Ἰησοῦ Χριστοῦ.

ቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ ይህንን መልእክት የጻፈላቸው ሰዎች ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ያምኑ ነበር፤ ይህ ለክርስቶስ አምላክነት ግልጽ ማረጋገጫ ነው። ሆኖም የክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ የሐሰት መምህራንና ከእነርሱ ሙግቶችን የሚኮርጁት ሙስሊም ጸሐፊያን 2ጴጥሮስ 1፥1 የመሲሑን አምላክነት አያረጋግጥም ይሉናል። በዚህ ጽሑፍ ከእነኚህ ሙስሊም ጸሐፊያን መካከል የአንዱን እንፈትሻለን። እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

አብዱል፦

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

5፥72 እነዚያ *«አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው»* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ

በግሪክ ኮይኔ የተዘጋጁ የአዲስ ኪዳን እደ-ክታባታት 5800 ገደማ ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ዋና ዋናዎቹ ደግሞ ኮዴክስ ሳይናቲከስ፣ ኮዴክስ ቫቲካነስ፣ ኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ፣ ኮዴክስ ኤፍሬማይ ናቸው። በ 330 ድኅረ-ልደት በተዘጋጀው በኮዴክስ ሳይናቲከስ እና በ 350 ድኅረ-ልደት በተዘጋጀው በኮዴክስ ቫቲካነስ መካከል የቃላት ሆነ የአሳብ ልዩነት አላቸው፥ ፊተኛው ኮዴክስ ሳይናቲከስ ያዘጋጁት ኢየሱስን “ጌታችን” ሲሉት ኃለኛው ኮዴክስ ቫቲካነስ ያዘጋጁት ደግሞ “አምላካችን” ብለውታል፦
2ኛ ጴጥሮስ 1፥1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ *በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ* ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ። ϲυμεων πετροϲ δουλοϲ και αποϲτο λοϲ ιυ χυ τοιϲ ϊϲο τιμον ημιν λαχου ϲιν πιϲτιν ειϲ δι καιοϲυνην του κυ ημων και ϲωτη ροϲ ιυ χυ

እዚህ አንቀጽ ላይ በኮዴክስ ሳይናቲከስ “ኮዩ” κυ ብሎታል፥ “ኮዩ” የሚለው ቃል “ኩስ” κος ለሚለው አገናዛቢ ዘርፍ ሲሆን “ጌታችን” ማለት ነው። “ኩስ” κος የሚለው “ኩርዮስ” κύριος ማለትም “ጌታ” ለሚለው ምጻረ ቃል ነው። ቀጣዩን ልዩነት ደግሞ እንመልከት፦
2ኛ ጴጥሮስ 1፥1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ *በአምላካችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ* ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ። ϲυμεων πετροϲ δουλοϲ και αποϲτο λοϲ ιυ χυ τοιϲ ϊϲο τιμον ημιν λαχου ϲιν πιϲτιν ειϲ δι καιοϲυνην του θυ ημων και ϲωτη ροϲ ιυ χυ

እዚህ አንቀጽ ላይ በኮዴክስ ቫቲካነስ “ቶዩ” θυ ብሎታል፥ “ቶዩ” የሚለው ቃል “ቴስ” Θς ለሚለው አገናዛቢ ዘርፍ ሲሆን “አምላካችን” ማለት ነው። “ቴስ” Θς የሚለው “ቴኦስ” θεός  ማለትም “አምላክ” ለሚለው ምጻረ ቃል ነው።
ታዲያ የቱ ነው ትክክል? ስንል ኮዴክስ ሳይናቲከስ በእድሜ ኮዴክስ ቫቲካነስን በ 20 ዓመት ስለሚበልጥ የቀደመው በአንጻራዊ ተአማኒት አለው።

መልስ፦

ጸሐፊው ብሂሉን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማቅረቡን ልብ በሉ፤ አንድን ሐሳብ በተለይ ሃይማኖታዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ማስረጃን ተንተርሶ ሙግትን ማዋቀር ለሙግቱ ቅቡልነት የመጀመሪያው መስፈርት ነው። ነገር ይህ ጸሐፊ ኮዴክስ ሳይናቲከስ ኮዴክስ ቫቲካነስን በዕድሜ እንደሚበልጠው በጨበጣ ከመናገር በዘለለ ማስረጃ ያላቀረበው ሙግቱን የሚደግፍ የረባ ምሑራዊ ምንጮች እንደሌሉት ስለተገነዘበ ይመስለኛል። ምክንያቱም በየትኛውም የምንባባዌ ሕያሴ ሊቃውንት ዘገባ መሠረት ኮዴክስ ሳይናቲከስ ኮዴክስ ቫቲካነስን እንደሚበልጥ አልተዘገበም። ይልቁንም የዘርፉ ሊቃውንት ኮዴክስ ቫቲካነስ  ከኮዴክስ ሳይናቲከስ ቢያንስ በ 10 አመት እንደሚቀድም ጠቅሰዋል[1] በለዘብተኝነቱና ክርስትናን በመቃወም የሚታወቀው ባርት ኤህርማን እንኳ ቫቲካነስ ቀዳሚም የተሻለ ተዓማኒነት እንዳለውም ገልጿል[2]። ከሁሉም ይልቅ ደግሞ ከቫቲካነስ ሆነ ከሳይናቲከስ ቢያንስ በ150 ዓመታት የሚቀድመው ፓፒረስ 72 2ኛ ጴጥሮስ 1፥1 ጌታ ከሚለው ይልቅ አምላክ የሚለውን አስቀምጦ እናገኛለን፦

ምስል፡ ፓፒረስ 72፤ 125-200 ዓ.ም

በምስሉ ላይ በቀይ ቀለም የተከበበው ቃል “አምላክ” የሚል ትርጕም ያለው ሲሆን ከሳይናቲከስ ቢያንስ 150 ዓመታት ይቀድማል። ስለዚህ ኋለኛው በቀዳሚው ይመዘናል እንጂ ቀዳሚው በኋለኛው አይመዘንም በሚለው በጸሐፊው በራሱ መሥፈርት ከሄድን  “አምላክ” የሚለው ቃል ይበልጥ ተዓማኒ ነው።

አብዱል፦

ሲቀጥል የ 2ኛ ጴጥሮስ ደራሲ በተለምዶ “ጴጥሮስ ነው” ይባል እንጂ አብዛኛውን ለዘብተኛ ሆነ ጽንፈኛ ምሁራን በጴጥሮስ ስም የተዋሸ “Pseudepigrapha” እንደሆነ ያትታሉ፥ ጴጥሮስ የሞተው ከ 65–67 ድኅረ-ልደት በሚገመት ጊዜ ሲሆን ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ግን ከ 100–150 ድኅረ-ልደት በሚገመት ጊዜ ነው። ዋቢ መጽሐፍ ይመልከቱ፦
Brown, Raymond E., Introduction to the New Testament, Anchor Bible, 1997, p. 767.

መልስ፦

የ 2ኛ ጴጥሮስ አዘጋጅ የክርስቶስ ደቀመዝሙር የነበረው ጴጥሮስ ነው። ሬይሞንድን ይህንን ግምት በመጽሐፋቸው ቢጠቅሱም ቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶች የ2ኛ ጴጥሮስ ምንባቦች በተደጋጋሚ በጽሑፎቻቸው ላይ ከመጥቀሳቸው አንጻር ብዙ ሊቃውንት የማይስማሙበት ግምት ነው[3] ለምሳሌ የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የነበረው ቀለምንጦስ ዘሮም ከ2ኛ ጴጥሮስ 3፥4 [4]፤ እንዲሁም 2ኛ ጴጥሮስ 1፥2[5]፤ 2ኛ ጴጥሮስ 3፥10፤[6]። የሔርማሱ እረኛ 2ኛ ጴጥሮስ 3፥9[7]። ሔሬኔዎስ 2ጴጥሮስ 3፥8 [8]። ዮስቶንዮስ ሰማዕት 2ኛ ጴጥሮስ 2፥1፤[9]፤ ጠቅሰዋል። ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች 2 ጴጥሮስን በመቀበል ረገድ ያሳዩትን መዛግብት በብዙ  ሊቃውንት ዘንድ 2ጴጥሮስ ተቀባይነቱን በእጅጉ ያጎላዋል። ፕሮፌሰር ብሩስ ሜዝገር የተባሉ ስመጥር የአዲስ ኪዳን ምንባባዌ ሕያሴ ሊቅ አሁን በእጃችን ያሉት ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት በጥንቃቄ እንደተላለፉ እንዲህ ያስነብባሉ፦

“The slowness of determining the final limits of the canon is testimony to the care and vigilance of early Christians in receiving books purporting to be apostolic. But, while the collection of the New Testament into one volume was slow, the belief in a written rule of faith was primitive and apostolic… In the most basic sense neither individuals nor councils created the canon; instead they came to perceive and acknowledge the self-authenticating quality of these writings, which imposed themselves as canonical upon the church.”[10]

                    ማጠቃለያ

ሐዋርያው ጴጥሮስ አይሁዳዊ እንዲሁም በአይሁዳውያን ማሕበረሰብ የያሕዌን ማንነት እየሰማ የኖረ ሰው ነው። ነብየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እስራኤል አንድ አምላክ ብቻ ነው እንዳለው እና ሌላ አምላክ እንደሌለ ይናገራል፦

““ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም።””  — ኢሳይያስ 43፥10 (አዲሱ መ.ት)

በሌላ ምዕራፍ ላይ ደግሞ ከያህዌ ውጪ አምላክ አዳኝ እና ጻድቅ እንደሌለ ይናገራል፤

ኢሳይያስ 45፥21፦ “ይህን አስቀድሞ ማን ዐወጀ? ከጥንትስ ማን ተናገረ? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ጻድቅና (δίκαιος) አዳኝ(σωτήρ) የሆነ አምላክ(θεός)፣ ከእኔ በቀር ማንም የለም፤ ከእኔ ሌላ አምላክ የለም።”

ሐዋርያው ጴጥሮስ ይኼ በዘመነ ብሉይ የተነገረለት “አምላክ፤ ጻድቅ እና አዳኝ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በመልዕክቱ ገልጿል፦

2ኛ ጴጥሮስ 1፥1 “በአምላካችንና(θεοῦ) በአዳኛችን(σωτῆρος) በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ(δικαιοσύνῃ) በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤”

ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሕዌ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን ያረጋግጣሉ!


ማጣቀሻዎች

[1] J.K.Elliot, New Testament Textual Criticism: The Application of Thoroughgoing Principles, page 65
[2] Bart D.Ehrman, studies in the textual criticism of the new testament, 2006: page 123
[3] The Authenticity of 2 Peter. Michael J. Kruger [PDF]  
[4] 1Clem 23:3
[5] 1 Clem 21.5
[6] 1 Clem 23.5
[7] Similitude8.11.1
[8]Irenaeus, Against Heresies 5.23.2
[9] Justin Martyr Dialogue with Trypho 82.1.
[10] Metzger, The New Testament: Its Background, Growth, and Content [New York: Abingdon Press, 1965], p. 276)