ምዕራፍ አንድ የቁርኣን አሰባሰብና አዘጋገብ

ምዕራፍ አንድ

የቁርኣን አሰባሰብና አዘጋገብ

በዚህ ርዕስ ስር ኡስታዝ ሐሰን ታጁ ሐመረ ተዋህዶ በሚያዝያ 1999 ዓ.ም. እትሙ የቁርኣንን አሰባሰብና አዘጋገብ (Compilation and Transmition) በተመለከተ የሰነዘራቸው ሒሶች ናቸው ላሏቸው ነጥቦች ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ በመጽሔቱ አዘጋጆች የተነሱት ሐሳቦች በሚከተሉት ሁለት ነጥቦች ሊጠቀለሉ ይችላሉ፡-

  1. ቁርኣን በነቢዩ ሙሐመድ የሕይወት ዘመን ተሟልቶ አልተሰበሰበም፡፡
  2. ከርሳቸው ህልፈት በኋላ በአቡበከር ብሎም በኡሥማን ዘመን የተደረጉት የመሰብሰብና በአንድ ጥራዝ የማተም ተግባራት አጠራጣሪ ክስተቶችን ያቆሩ ናቸው (ገፅ 14)፡፡[1]

ጸሐፊው እነዚህን ሒሶች የረባ ማስረጃ በማቅረብ ማስተባበል አልቻሉም፡፡ በማስከተል በሙግቶቻቸው ውስጥ የሚገኙትን ክፍተቶች እንገልጣለን፡፡ የተባሉት ነገሮች እውነት መሆናቸውን ይበልጥ የሚያረጋግጡና እውነታዎቹን ለሚክዱ ሙስሊም ወገኖች ጉዳዩን የሚያጠብቁ ተጨማሪ ማስረጃዎችንም እንሰጣለን፡፡

ቁርኣን በቃል ተጠብቋልን?

ኡስታዝ ሐሰን ከላይ ለተጠቀሱት ሒሶች የሰጡት ቀዳሚው ምላሽ “ቁርኣን በቃል ተጠብቋል” የሚል ነው (ገፅ 15)፡፡ ቁርኣን በብዙ ሰዎች የተሸመደደ ጽሑፍ መሆኑ ከሌሎች መጽሐፍት ለየት እንደሚያደርገውና ላለመጥፋቱ አስተማማኝ ዋስትና እንደሆነ በመገረምና በመደመም ስሜት ጽፈዋል፡፡ በተጨማሪም “በየትኛውም ቋንቋ የተጻፈውን ብሉይ ኪዳን ወይም አዲስ ኪዳን በቃሉ የያዘ በአእምሮው የሸመደደ አንድም ግለሰብ በዓለም ላይ ለማግኘት ይቸግራል” ይላሉ፤ ዓለምን ሁሉ ዞረው የተመለከቱ ይመስል (ገፅ 15)፡፡ ምላሻችንን ከዚህ እንጀምራለን፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ 1,189 ምእራፎችና 31,103 ቁጥሮች ያሉት ሲሆን ቁርኣን ደግሞ 114 ምዕራፎችና 6236 ቁጥሮች ብቻ ነው ያሉት፡፡ በምዕራፍ ብዛት መጽሐፍ ቅዱስ ከቁርኣን ከአሥር እጥፍ በላይ ነው፡፡ በቁጥሮች ብዛት ደግሞ አምስት እጥፍ ይሆናል፡፡ በምዕራፍ ብዛት ከተሰላ አንድ ሰው ቁርኣንን ለመሸምደድ 5 ዓመት ቢፈጅበት መጽሐፍ ቅዱስን ለመሸምደድ ደግሞ 50 ዓመታትን ይወስድበታል፡፡ ስሌቱ በቁጥር ብዛት ከሆነ ቁርኣን 5 ዓመታትን ቢጠይቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ 25 ዓመታት ያስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ግዙፍ መጽሐፍ ከመሆኑ አንፃር መሸምደድ አስቸጋሪ ቢሆንም ይህንን በማድረግ ረገድ ስኬትን ያስመዘገቡ በርካታ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ዶ/ር ዊልያም ኤቫንስ የተባሉ ሰው የኪንግ ጀምስን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በሙሉና አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን የአዲስ ኪዳን ትርጉም በቃላቸው መሸምደድ የቻሉ ሰው ነበሩ፡፡ ይህ እንግዲህ የቁርኣንን ሰባት እጥፍ የሚሆን ጥራዝ የመሸምደድ ያህል ነው፡፡[2]

ሐሰን ታጁ ብዙ ሙስሊሞች ቁርኣንን መሸምደድ የቻሉባቸውን ተከታዮቹን አራት ምክንያቶች ጠቅሰዋል፡፡ የጠቀሷቸውን ምክንያቶች ሚዛን የሚደፉ ሆነው አላገኘናቸውም፡፡

  1. ቁርኣን “ለማጥናት ቀላል መሆኑ”

“ቁርኣን ለማስታወስ ቀላል ለማጥናትም ገር መሆኑ ከድንቅ ባሕርያቱ ነው” በማለት የቁርኣንን የሽምደዳ ሂደት ተዓምራዊ ለማስመሰል ይሞክራሉ (ገፅ 15-16)፡፡ ለዚህ አባባላቸው ሁለት የቁርኣን ጥቅሶችን ጠቅሰዋል (የጨረቃ ምዕራፍ 54፡17፣ የጭስ ምዕራፍ 44፡58)፡፡ ነገር ግን ቁርኣን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር አነስተኛ መጽሐፍ በመሆኑ ምክንያት በቀላሉ መሸምደድ ቢቻል አያስገርምም፡፡ የሽምደዳ ሂደቱም ፍፁም ተፈጥሯዊ እንጂ ተዓምራዊ አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ቁርኣንን ለመሸምደድ መስዋዕት የሚያደርጉትን ጊዜና ጉልበት ማንኛውም ሰው የትኛውንም ጽሑፍ ለመሸምደድ ቢያውል ውጤቱ ተመሳሳይ ሊሆን መቻሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ሆኖም ኡስታዙ ከተናገሩት በተጻራሪ ቁርኣንን መሸምደድ ከምንም በላይ እጅግ ከባድ መሆኑን ነቢዩ ሙሐመድ ተናግረዋል፡፡ ሳሂህ አል-ቡኻሪ ውስጥ እንዲህ ተብሏል፡-

አብዱላህ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል “… ቁርኣንን ማነብነብ ማቋረጥ የለባችሁም ምክንያቱም ከግመል ሩጫ በፈጠነ ሁኔታ ከሰው ልብ ውስጥ ይጠፋልና፡፡”[3]

አቡ ሙሳ እንደተረከው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ቁርኣንን ማነብነባችሁን አታቋርጡ፡፡ ነፍሴ በእጁ ባለችው ጌታ እምላለሁ ከእስር ከተለቀቁት ግመሎች ይልቅ ቁርኣን ሮጦ ይጠፋል (ከትውስታ ይጠፋል)፡፡”[4]

አቶ ሐሰን አክለውም ስለ ቁርኣን “ግልፅነት” እንዲህ ይላሉ፡- “ቁርኣን ቃሉ ብቻ ሳይሆን መልእክቱም ቀላልና ለአእምሮ የማይጎረብጥ ነው…” (ገፅ 15)

አቶ ሐሰን እየቀለዱ መሆን አለበት፡፡ ቁርኣንን መረዳት ይህን ያህል ቀላል ከሆነ ሙሐመድ ካለፉ ከ250 ዓመታት በኋላ ሐዲሳትን ለመሰብሰብ እንደዚያ መድከም ለምን አስፈለገ? በየዘመናቱ ግዙፍ ተፍሲሮች የሚጻፉትስ ለምን ይሆን?

ቁርኣን በውስጡ የሚገኙትን ታሪኮች በተሟላ ሁኔታ አያቀርብም፡፡ የጊዜ ቅደም ተከተልን አይጠብቅም፡፡ አንድን ታሪክ ወይም ትምህርት የት ጀምሮ የት እንደሚጨርስ አይታወቅም፡፡ በሐሳብ ፍሰት ረገድ እጅግ ደካማ ነው፡፡ አስባብ አን-ኑዙል የተሰኙ የቁርኣን አናቅፅ “የወረዱባቸውን” አውዶች የሚያስረዱ አጋዥ መጻሕፍት ባይኖሩ ኖሮ የቁርኣን አብዛኛው ክፍል ትርጉም አልባ በሆነ ነበር፡፡

በተጨማሪም ሚስቶችን መደብደብ የፈጣሪ ትዕዛዝ መሆኑን (4፡43)፣ ለወሲብ መጠቀሚያነት የተፈጠሩ ደናግላን በገነት ውስጥ ለሙስሊም ወንዶች መዘጋጀታቸውን (55:56፣ 55፡72-74)፣ የሰዎችን እጅና እግር እያፈራረቁ መቁረጥ የፈጣሪ ትዕዛዝ መሆኑን (5፡38)፣ አንድ ሰው የማደጎ ልጁን ሚስት ማግባት እንደሚችል (33፡4)፣ የአንድ ወንድ ምስክርነት ከሁለት ሴቶች ምስክርነት ጋር እኩል መሆኑን (2፡282፣ 4፡11)፣ የሴቶች የውርስ ድርሻ ከወንዶች በእጥፍ ያነሰ መሆኑን (4፡11)፣ ወዘተ. የሚናገር መጽሐፍ “መልእክቱ ለአእምሮ የማይጎረብጥ ነው” መባሉ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡

አቶ ሐሰን ቁርኣን “ፍፁም ግልፅ” ስለመሆኑ አሽሙር ቢጤ በታከለበት አባባል እንዲህ ብለዋል፡-

“ለሸሆች ብቻ የሚገባ ‹‹ሚስጥረ ካህናት››፣ አእምሮን ቆልፈው ‹‹በሞኝነት›› የሚያምኑት፣ እንደ በግ ‹‹በየዋህነት›› የሚቀበሉት መልእክት አልተካተተበትም፡፡” (ገፅ 16)

እንደርሱ ከሆነ በብዙ ምዕራፎች መጀመርያ ላይ የሚገኙትን ፊደላት ትርጉም ከአላህ ውጪ ማንም እንደማያውቅ ሙስሊም ምሑራን የሚናገሩት ለምን ይሆን? ከአላህ ውጪ ትርጉማቸውን ማንም የማያውቃቸው አናቅፅ በውስጡ መኖራቸውስ ስለምን ተጻፈ (ሱራ 3፡7)? እነዚህን ትርጉማቸው የማይታወቁትን አናቅፅ ሙስሊሞች “በሞኝነትና በየዋህነት” ተቀብለዋቸው የለምን? የአቶ ሐሰን ሃይማኖት በጭፍን እምነት መከተልን የሚጠይቅ ሃይማኖት ነው፡፡ ለዚህ ነው በቁርኣን ላይ ሒስ የሚሰነዝሩ ሰዎች ወይም በእስልምና ግራ ተጋብተው እምነቱን የለቀቁ ሰዎች የሚገደሉት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን፡-

  • እምነታችን በእውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚገባው ያስተምራል፡- “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፡፡” (1ተሰ. 5፡21)
  • በጭፍን ማመን እንደሌለብንና ሁሉንም መመርመር እንዳለብን ደጋግሞ ያሳስባል፡- “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” (1ዮሐ. 4፡1)
  • ክርስትና እውነት መሆን አለመሆኑን መርምረው የተቀበሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት ተችሯቸዋል፡- “እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” (ሐዋ. 17፡11)

በአንፃሩ ግን ነቢዩ ሙሐመድ አንድ ተከታያቸው ጥያቄዎችን ደጋግሞ በመጠየቁ ምክንያት በአላህ ዘንድ መጠላቱን ተናግረው ነበር፡፡ “ጥያቄ በማብዛትህ አላህ ጠልቶሃል” ነበር ያሉት፡፡[5] ጥያቄ ሳይጠይቁ በጭፍን ማመን የእስልምና ባሕርይ እንጂ የክርስትና ትምህርት አይደለም፡፡

2. ተነጣጥሎ “መውረዱ”

ቁርኣን በቃል እንዲጠና “ካቀለሉት ነገሮች” ብለው በሁለተኛነት የጠቀሱት ተከፋፍሎ “መውረዱን” ነው (ገፅ 16)፡፡ ለዚህ ድጋፍ ይሰጣል ያሉትን ተከታዩን ጥቅስ ጠቅሰዋል፡-

“ቁርኣንንም በሰዎች ላይ በዝግታ ላይ ኾነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው፡፡ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው፡፡” (17፡106)፡፡

አቶ ሐሰን ቁርኣን በ23 ዓመታት ውስጥ ተከፋፍሎ “የወረደው” በቃል ለማጥናት እንዲያመች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ የሚመስልና የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የቁርኣን አናቅፅ “የወረዱባቸውን” አውዶች የሚገልፁ ተፍሲሮችን (ማብራርያዎችን) ብናገላብጥ ሙሐመድ የሆነ ጉዳይ ሲገጥማቸው በወቅቱ ለተከሰተው ነገር መፍትሄ ሊሆን የሚችል “መገለጥ” ይናገሩ እንደነበር እንረዳለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ላይ የሚታየው መፃዒ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ፀጋ ስላልነበራቸው “መገለጦችን” ይናገሩ የነበሩት አስቀድመው ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን ያለፈውን ወይም አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ብቻ ነበር፡፡ አንዳንድ ትንቢት የሚመስሉ ይዘቶቹም ተራ ግምቶች ከመሆን ያለፉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ መጽሐፉን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስጽፈው መጨረስ ያልቻሉት “መገለጦቹን” ይናገሩ የነበሩት አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ብቻ ስለነበረ እንጂ ተከታዮቻቸው በቃል ለማጥናት እንዲቀላቸው በማሰብ አልነበረም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የቁርኣን ጥቅስ ይህንን እውነታ ለማስተባበል የተነገረ ደካማ ምላሽ ነው፡፡ መልእክቶቹን በጽሑፍ አስፍሮ በሚፈለገው ፍጥነት በቃል ማጥናት እየተቻለ አንዱ አንቀፅ ተጠንቶ እስኪያበቃ ድረስ ሌላ አንቀፅ “እንዳይወርድ” ማዘግየት ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ በወቅቱ የጽሑፍ አማራጭ ባይኖር ነበር ይህ አባባል ሊያስኬድ የሚችለው፡፡

3. “ልዩ የማስታወስ ችሎታ” የነበረው ሕዝብ?

“የቁርኣን መልዕክት መጀመርያ የወረደላቸው አረቦች እጅግ የሚያስደምም የማስታወስ ችሎታ ነበራቸው… ከእስልምና በፊት መጻፍ ወይም ማንበብ የሚችሉ ግለሰቦች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ አብዛኛው ማሕበረሰብ ግን መሐይም (ኡምይ) ነበር፡፡ ይህ ልዩ ተሰጥኦ የነበራቸው አረቦች በቋንቋ ዝግጅቱም፣ በውበቱም፣ በይዘቱም እጅግ የሚያስደምመውን ቁርኣን ለማጥናት አልተቸገሩም፡፡” (ገፅ 17)፡፡

ሐሰን ታጁ ለዚህ አባባላቸው ዋቢ የሚሆን ማስረጃ አልጠቀሱም፡፡ ለአረቦች ያላቸውን አድናቆት የገለፁበትን ይህንን አባባላቸውን በእምነት እንድንቀበል የፈለጉ ይመስላል፡፡ የአረብ ሕዝቦች እንደ ማንኛውም የጥንት ሕዝቦች ከሞላ ጎደል መሃይማን ስለነበሩ ዕውቀትን ለማስተላለፍ በሥነ-ቃል ላይ መደገፍ እንደነበረባቸው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን መሃይማን መሆናቸው ከሌሎች ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ ልዩ የማስታወስ ፀጋን እንዳጎናፀፋቸው በማስመሰል መናገር ሚዛን መሳት ነው፡፡

4. “የነቢዩ ሙሐመድ ግፊትና ማበረታቻ”

ነቢዩ ሙሐመድ ሙስሊሞች ቁርኣንን በቃላቸው እንዲያጠኑ ከተጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ ይህ ተግባር “እጅግ የሚያስጎመጅ ምንዳ፣ የሚያጓጓ ደረጃ እንደሚያስገኝ” መግለፅ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ቁርኣንን ያጠና ሰው ከብርሃን የተሠራ ዘውድ እንደሚደፋና ወላጆቹ ደግሞ የብርሃን ልብስ እንደሚጎናፀፉ ነቢዩ መናገራቸውን የሚያወሳ አንድ ምንጩ ከየትኛው መጽሐፍ ላይ እንደሆነ ያልገለፁትን ታሪክ ጠቅሰዋል (ገፅ 17)፡፡

እነኚህን የመሳሰሉ ማባበያዎች ብዙ ወጣቶች የቀለም ትምህርት ተምረው ምርታማ ዜጎች እንዳይሆኑ አእምሯቸውን በመቆለፍ ቁርኣንን በመሸምደድ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አድርገዋል፡፡ ክርስቲያኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስን መሸምደድ ለብፅዕና እንደሚያበቃ አያምኑም፡፡ መጽሐፉን አንብበን እስከተረዳንና በውስጡ የተጻፈውን እስከጠበቅን ድረስ ሽምደዳ ግዴታ አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጠልን መለኮታዊ መመርያ ቃሉን እንድናነብ፣ እንድንሰማና እንድንጠብቅ የሚል እንጂ እንድንሸመድድ የሚያስገድድ አይደለም (ራዕይ 1፡3)፡፡

ሙስሊም ወገኖቻችን ቁርኣን በትክክል ተጠብቆ ስለመቆየቱ የሚሰጡት ቀዳሚው ማስረጃ በቃል ተጠብቆ መቆየቱን ከሆነ ተከታዮቹን ሁለት ጥያቄዎች ማንሳት አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡

  • ነቢዩ ሙሐመድ ቁርኣንን በትክክል ሸምድደውት ነበርን?

ሙሐመድ ተከታዮቻቸው ቁርኣንን እንዲሸመድዱ ብዙ አጓጊ ተስፋዎችን በመስጠት ቢያበረታቱም እርሳቸው ግን የቁርኣን አናቅፅ የመርሳት ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር ሙስሊሞች እንደ ተዓማኒ ምንጮች የሚቆጥሯቸው ሐዲሳት ይመሰክራሉ፡፡ ጥቂቶቹን እንጠቅሳለን፡-

“አይሻ እንዳስተላለፈችው፤ ነቢዩ አንድ ሰው በመስጊድ ውስጥ ቁርኣንን ሲያነበንብ ሰምተው እንዲህ አሉ፣ ‹ይህ ሰው እንዲህና እንዲያ በተሰኘው ሱራ ውስጥ የሚገኘውን እንዲህና እንዲያ የሚለውን የረሳሁትን አንቀፅ እንዳስታውስ ስላደረገኝ አላህ እዝነቱን ይስጠው፡፡›”[6]

በዚህ ሐዲስ መሠረት ሙሐመድ የረሱትን አንድ የቁርኣን ክፍል ከተከታዮቻቸው መካከል አንዱ ሲያነበንብ ሰምተው አስታውሰዋል፡፡ በሌላ የሐዲስ ዘገባ ደግሞ እንዲህ ተብሏል፡-

“አብዱላህ ኢብን መስዑድ እንዳስተላለፈው፤… ነቢዩ እንዲህ ብለዋል ‹እኔ ሰው በመሆኔ እናንተ እንደምትረሱት ሁሉ እረሳለሁ፤ ስለዚህ እኔ የረሳሁ እንደሆን አስታውሱኝ…›”[7]

የዚህ ሐዲስ አውድ ሙሐመድ በሰላት ወቅት ስግደት በማስረዘማቸው ምክንያት ተከታዮቻቸው በሥርኣቱ ላይ ለውጥ ተደርጎ እንደሆን ሲጠይቋቸው የሰጡትን መልስ የሚናገር ነው፡፡ ይህም የሙሐመድ ትውስታ እንደ ማንኛውም ሰው ድክመት እንደነበረበት ያሳያል፡፡

እስኪ በነቢዩ ሙሐመድና ተከታያቸው በነበረው በኡበይ ቢን ካዕብ መካከል የተደረገውን ይህን ምልልስ ደግሞ እንመልከት፡-

“ነቢዩ ቁርኣንን ሲያነበንቡ አንድ አያ (አንቀፅ) ዘለሉ፡፡ ጸሎቱን ከጨረሱ በኋላ ‹‹ኡበይ እዚህ መስጂድ ውስጥ ነውን?›› ብለው ጠየቁ፡፡

‹‹ይኸው አለሁ የአላህ መልእክተኛ ሆይ››

‹‹ታድያ ለምን አላስታወስከኝም?››

‹‹ያቺ አንቀፅ የተሻረች ስለመሰለኝ ነው››

‹‹አልተሻረችም ነገር ግን ረስቼያት ነው፡፡››”[8]

አላህ ራሱ ሆነ ብሎ ሙሐመድ ቁርኣንን እንዲረሱ ያደርጋቸው እንደነበር በቁርኣን ውስጥ ተጽፏል፡-

“ከአንቀጽ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ብጤዋን እናመጣለን፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መኾኑን አታውቅምን?” (የላም ምዕራፍ 2፡106)

“(ቁርኣንን) በእርግጥ እናስነብብሃለን፤ አትረሳምም፡፡ አላህ ከሻው ነገር በስተቀር፡፡ እርሱ ግልጹን የሚሸሸገውንም ሁሉ ያውቃልና፡፡” (87፡6-7)

እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያረጋግጡት ሙሐመድ “ወረዱልኝ” ያሏቸውን መገለጦች ይረሱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በነቢይነታቸው ላይ ጥርጣሬን እንዳያጭር መገለጦቹን የሚያስረሳቸው አላህ ራሱ መሆኑን ተናገሩ፡፡ አላህ ያወረደውን መገለጥ በማስረሳት አዲስ ሥራ ከሚፈጥር መጀመርያውኑ እነዚህን መገለጦች ባያወርድ አይሻልም ነበርን? መገለጡን ከአላህ ዘንድ ተቀበሉ የተባሉት ሙሐመድ መገለጡን መርሳት ከቻሉ የተከታዮቻቸው ትውስታስ እንዴት አስተማማኝ ሊሆን ይችላል?

  • የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች (ሶሐቦች) ቁርኣንን በትክክል ሸምድደውት ነበርን?

በፍፁም! ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ ለማሰባሰብ ጥረት በተደረገበት ወቅት ከሙሐመድ የተማሩ የተባሉት ሙስሊሞች ብዙ የቁርኣን ክፍሎችን መርሳታቸውን ተናዘዋል፡፡ አንድ ምሳሌ ከሳሂህ ሙስሊም ሐዲስ እንጥቀስ፡-

“አቡ ሀርብ ቢን አቡ አል-አስዋድ አባታቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት አቡ ሙሳ አል-ሸዐሪ የበስራ ቁርኣን አነብናቢዎችን አስጠሯቸው፡፡ ቁጥራቸው ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑቱ መጡ፡፡ ቁርኣንን አነበነቡት፤ እርሳቸውም እንዲህ አሏቸው ‹‹እናንተ አነብናቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን ከበስራ ነዋሪዎች ሁሉ ምርጦች ናችሁ፡፡ ማነብነባችሁን ቀጥሉ፡፡ (ነገር ግን) ለረጅም ጊዜ ማነብነባችሁ ከናንተ በፊት የነበሩትን ሰዎች ልቦች እንዳደነደነ ልቦቻችሁን እንዳያደነድን ተጠንቀቁ፡፡ በርዝመትና በጥንካሬ ከሱራ በረዓት ጋር የሚነፃፀር ሱራ እናነበንብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹የአደም ልጅ በኃብት የተሞሉ ሁለት ሸለቆዎች ቢኖሩት ሦስተኛውን ይመኛል፡፡ ከአፈር ውጪ የአደምን ልጅ ሆድ የሚሞላ ምንም ነገር የለም፡፡›› ከሱረት ሙሰቢሃት መካከል ከአንዱ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ሱራም እናነበንብ ነበር ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የማትፈፅሙትን ነገር ስለምን ትናገራላችሁ? እርሱም በናንተ ላይ ምስክር እንዲሆንባችሁ በአንገቶቻችሁ ላይ ተጽፏል፤ በዕለተ ትንሣኤም ከእርሱ ትጠየቃላችሁ፡፡››” [9]

በዚህ ሐዲስ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለቱ “መገለጦች” በዛሬው ቁርኣን ውስጥ አይገኙም፡፡ ሱራ በረዓት (አት-ተውባ) 129 አንቀፆች ያሉት ሲሆን ይህን ያህል ርዝመት ያለው አንድ ሙሉ ምዕራፍና ሌላ ርዝመቱ ምን ያህል እንደሆነ ያልተገለፀ፤ ነገርግን ‹ሙሰቢሃት› በመባል ከሚታወቁት በቁርኣን ውስጥ ከሚገኙ ሱራዎች ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሱራ መረሳቱ ተነግሯል፡፡

ታድያ የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች በዚህ ሁኔታ የቁርኣንን ክፍሎች ከመርሳታቸው የተነሳ በዛሬው ቁርኣን ውስጥ ያልተካተቱ “መገለጦች” መኖራቸውን ከተናዘዙ አቶ ሐሰንና መሰሎቻቸው ቁርኣን በትክክል ተሸምድዶ ሳይጨመርበትና ከላዩ ላይ ሳይቀነስ ለዚህ ዘመን እንደበቃ በማስመሰል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙት ለምን ይሆን? ፈጣሪ በሀሰት ይከብራልን?

ቁርኣን በሙሐመድ ዘመን በጽሑፍ መስፈሩ አለመለወጡን ያረጋግጣልን?

ሐሰን ታጁ በሐመረ ተዋህዶ ለተነሱት ሒሶች የሰጡት ሁለተኛው ምላሽ “ቁርኣን በነቢዩ ዘመን ተጽፏል” የሚል ነው (ገፅ 18-19)፡፡ ነገር ግን ይህ “መልስ” የማያስኬድባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡

  • በሰው አስተያየት የሚሻሻል “መገለጥ”

ሙሐመድ ቁርኣንን ሲያጽፉ የግለሰቦችን አስተያየቶችና ቅሬታዎች እየሰሙ ማስተካከያዎችን በማድረግ ነበር፡፡ ይህንን በተመለከተ ሳሂህ አል ቡኻሪ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሐዲስ እንዲህ ይላል፡-

“አል-በራ እንዳስተላለፉት፡- ‹ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም› የሚል ሱራ ወርዶ ነበር (4፡95)፡፡ ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹እስኪ ዘይድን ጥሩልኝ መጻፍያ ሰሌዳ፣ የቀለም ገንቦና (እንደ ብዕር የሚያገለግል) አጥንት ያምጣልኝ…› ከዚያ፡- ‹ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም… ብለህ ጻፍ› አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ዓይነ ስውሩ አምር ቢን ኡም መክቱም አጠገባቸው ተቀምጦ ነበር፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ለኔስ የሚሰጡት ትዕዛዝ ምንድነው? እኔ ዓይነ ስውር ሰው ነኝ፡፡› ስለዚህ በዚህኛው አንቀፅ ፋንታ ተከታዩ አንቀፅ ወረደ፡- ከምእመናን የጉዳት ባለቤት ከኾኑት በቀር ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም፡፡›”[10]

የአምላክ መገለጦች በሰዎች ቅሬታና አስተያየት ላይ ተመሥርተው የሚሻሻሉ፣ የሚሰረዙ፣ የሚደለዙ አይደሉም፡፡ ሙሐመድ የእውነት ከሰማይ መገለጥ ወርዶላቸው ከሆነ በወረደላቸው መገለጥ ላይ በመጨመር እንዲጻፍ ስላደረጉ እንዲጻፍ ያደረጉት መገለጥ የተበረዘ ነው ማለት ነው፡፡ መሰል ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው በፈጣሪ ትዕዛዝ መሠረት እንደሆነ በየዋህነት የሚያምን ሰው ካለ ስለ ፈጣሪ እውቀት ግንዛቤ የሌለው ጭፍን አማኝ መሆን አለበት፡፡ የፈጣሪ መገለጦች ፍፁማን በመሆናቸው በግለሰብ አስተያየትና ቅሬታ የሚሻሻሉ አይደሉም፡፡ እንዲህ ያለ ፌዝ በእውነተኛው አምላክ ዘንድ የለም፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ የአምላክን መገለጥ በርዘዋል አለበለዝያም ደግሞ መገለጡ ከጅምሩ እውነተኛ አይደለም፡፡

  • ጸሐፍት የሚያሻሽሉት “መገለጥ”

አብዱላህ ኢብን ሰዓድ ኢብን አቢ ሳርህ የተሰኘ የሙሐመድ የግል ጸሐፊ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለነቢዩ ሙሐመድ መገለጦችን በመጻፍ ያገለግላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን መገለጦችን ሲጽፍ ሳለ በየመሃሉ የማሻሻያ ሐሳቦችን ጣል ያደርግ ነበር፤ ሙሐመድም ብዙ ጊዜ በመስማማት በጽሑፉ ውስጥ እንዲካተት ይፈቅዱ ነበር፡፡ ሙሐመድ የሚናገሩት መገለጥ ከፈጣሪ ዘንድ ቢሆን ኖሮ የሰው ሐሳብ እንዲጨመርበት ሊፈቅዱ እንደማይችሉ ስለገባው ይህ ጸሐፊ እስልምናን በመተው ወደ መካ ከተማ ሸሸ፡፡ ኋላ ላይ ሙሐመድ መካን ድል ነስተው በያዙ ጊዜ ኢብን አቢ ሳርህ እንዲገደል አዘዙ፡፡ ነገር ግን በኡሥማን ተማፅኖ ከመገደል ተርፎ እንደገና ወደ እስልምና ተመለሰ፡፡

ኢብን አቢ ሳርህ እስልምናን ስለመካዱና ሙሐመድ ስላስተላለፉበት የሞት ብይን ኢብን ኢስሐቅ፣ አልጦበሪና ኢብን ሰዓድን በመሳሰሉት የሙሐመድ ግለ ታሪክ ጸሐፍት የተዘገበ ሲሆን የቁርኣንን መገለጦች እየጨመረና እየቀነሰ ስለመጻፉ ደግሞ አል-ኢራቂና ባይዳዊን የመሳሰሉት ሙስሊም ሊቃውንት ዘግበዋል፡፡[11] የሙሐመድ ጸሐፊ ቁርኣንን ስለመበረዙ በእስላማዊ ድርሳናት የተመዘገበው ይህ ታሪክ እውነት ከሆነ ሌሎች ጸሐፍት ተመሳሳይ ነገር ላለመፈፀማቸው ዋስትና የለንም፡፡

  • ሙሐመድ አንድ ቁርኣን ብቻ አልነበራቸውም

ይህንን የሚያረጋግጡ ሁለት ሐዲሳትን እንጠቅሳለን፡-

“ኡመር ቢን አል-ኸጧብ እንዳስተላለፈው፡- ነቢዩ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ሒሻም ቢን ሐኪም ሱራት አል-ፉርቃንን ሲያነበንብ እሰማው ነበር፤ የእርሱን መነባንብ ሳዳምጥ የአላህ መልእክተኛ እኔን ካስተማረበት መንገድ በብዙ መልኩ የተለየ መሆኑን አስተዋልኩኝ፡፡ እየጸለየ ሳለ ዘልዬ ልይዘው ጥቂት ቀርቶኝ ነበር ነገር ግን ጸሎቱን እስኪጨርስ ድረስ በትዕግስት ጠበኩትና ከላይ በለበሰው ልብሱ አንገቱን አንቄ ይዤ ‹‹አሁን ስታነበንብ የሰማሁትን ሱራ ማን አስተማረህ?›› አልኩት፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ናቸው ያስተማሩኝ›› አለኝ፡፡ እኔም ‹‹በእርግጥ ውሸት ተናግረሃል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ከዚህ በተለየ መንገድ ነው ያስተማሩኝ›› አልኩት፡፡ ስለዚህ ወደ አላህ መልእክተኛ ጎትቼ አመጣሁትና ‹‹ይህ ሰው እርስዎ ካስተማሩኝ መንገድ በተለየ ሁኔታ ሱረት አል ፉርቃንን ሲያነበንብ ሰማሁት!›› አልኳቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ‹‹(ኡመር ሆይ) ልቀቀው፤ ሒሻም ሆይ አነብንብ!›› አሉ፡፡ ሲያነበንብ በሰማሁት በዚያው መንገድ አነበነበ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ‹‹በዚህ መንገድ ነው የወረደው›› አሉ፡፡ ከዚያም ‹‹ኡመር ሆይ አነብንብ›› አሉ፡፡ እሳቸው ባስተማሩኝ መንገድ አነበነብኩኝ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ‹‹በዚህ መንገድ ነው የወረደው፡፡ ይህ ቁርኣን በሰባት የተለያዩ መንገዶች እንዲነበብ ተደርጎ ነው የወረደው ስለዚህ ለናንተ ቀላል መስሎ በታያችሁ መንገድ አነብንቡ›› አሉ፡፡”[12]

“ኢብን መስዑድ እንዳስተላለፉት፤ አንድ ሰው የቁርኣንን አንቀፅ በሆነ መንገድ ሲያነበንብ ሰማሁት፡፡ የአላህ መልእክተኛ ደግሞ ያንኑ አንቀፅ በተለየ መንገድ ሲያነበንቡት ሰማሁኝ፡፡ ስለዚህ ወደ ነቢዩ ወስጄው ስለ ጉዳዩ አሳወቅኋቸው፤ ነገር ግን በፊታቸው ላይ የቅሬታ ምልክት አየሁኝ፡፡ ከዚያ እንደዚህ አሉ፣ “ሁለታችሁም ትክክል ናችሁ ስለዚህ አትለያዩ፤ ከናንተ በፊት የነበሩት ሕዝቦች የጠፉት በመለያየታቸው ምክንያት ነውና፡፡”[13]

ሙስሊሞች ብዙ ጊዜ ሰባቱ የቁርኣን ቅጂዎች በአረብኛ ቋንቋ ዘዬዎች ምክንያት የተፈጠሩ የአንዱ ቁርኣን ሰባት የንባብ መንገዶች ብቻ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ኡመር ቢን ኸጧብና ሒሻም ከአንድ ጎሣ ስለነበሩ የተለያዩ ዘዬዎችን ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡[14] እነዚህ የተለያዩ የቁርኣን ቅጂዎች እንጂ የአንዱ ቁርኣን የተለያዩ ዘዬዎች አይደሉም፡፡

በሙሐመድ ዘመን ቁርኣን በጽሑፍ ተጠብቆ ከነበረ ከሰባቱ የትኛው ነው የተጻፈው? ሰባቱም ተጽፈው ከነበረ የኸሊፋ አቡበክር አንዱ ስብስብ ሰባቱንም ያካተተ ነበርን? ይህንን የሚጠቁም ማስረጃስ ይኖራልን? ኡሥማን ከሰባቱ ስድስቱን ዓይነት ቁርአኖች አጥፍተው ከነበረ ቁርኣን ፍጹማዊ በሆነ መንገድ በጽሑፍ ተጠብቋል ልንል እንችላለንን? በኋለኛው ዘመን እንዲወድሙ ከተደረገ ሰባቱ ቁርአኖች በሙሐመድ ዘመን በጽሑፍ መስፈራቸው ፋይዳው ምንድነው?

  • ሙሐመድ በመካ “የተጻፉትን” የቁርኣን ጽሑፎች ይዘው መሰደዳቸውን የሚጠቁም ማስረጃ የለም

የቁርኣን ሁለት ሦስተኛው በመካ “እንደወረደ” ይታመናል፡፡ ነገር ግን ይህ የቁርኣን ክፍል ተጽፎ ከነበረ ሙስሊሞች በሂጅራ ወቅት እነዚህን ጽሑፎች ይዘው ወደ መዲና መሄዳቸውን የሚገልፅ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባለመኖሩ ጠፍተዋል ማለት ነው፡፡ ነፍሳቸውን ለማትረፍ በሽሽት ላይ የነበሩት ሙስሊሞች ድንጋይና አጥንትን የመሳሰሉ ቁሳ ቁሶችን ይዘው መንቀሳቀስ መቻላቸው በራሱ የማይመስል ነው፡፡ ስለዚህ የቁርኣን ሁለት ሦስተኛ ጽሑፍ ሙሐመድ ገና በሕይወት ሳሉ ጠፍቶ ከነበረና ወደ ቀጣዩ ትውልድ ካልተሸጋገረ በጽሑፍ መስፈሩ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ለቁርኣን ተዓማኒነትም የሚጨምረው ምንም ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ሙሐመድ በመካ ከተማ ሳሉ ቁርኣን በጽሑፍ መስፈሩን የሚጠራጠሩ ሊቃውንት ብዙ ናቸው፡፡[15]

  • የመጀመርያዎቹ የቁርኣን ጽሑፎች ተቃጥለዋል

ኡሥማን ኢብኑ አፋን ቁርኣንን አንድ ወጥ መልክ ለማስያዝ ጥረት ባደረገበት ወቅት ከእርሱ በፊት የነበሩትን የቁርኣን ጽሑፎች አውድሟቸዋል፡፡[16] በሐፍሳ ዘንድ ቀርቶ የነበረውን አንዱን ስብስብ ማርዋን የተሰኘ ሰው አቃጥሎታል፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ ያጻፏቸው የቁርኣን ክፍሎች ሆነ ተብለው እንዲወድሙ ስለተደረገ ዛሬ ካሉት ቁርአኖች ጋር አንድ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ይህንን ርዕስ ከአፍታ በኋላ በስፋት እንዳስሰዋለን፡፡

የአቡበክር የማሰባሰብ ሂደት ከጥርጣሬ የፀዳ ነበርን?

ሐሰን ታጁ ቁርኣን በነቢዩ ዘመን በአንድ ጥራዝ ለምን እንዳልተሰበሰበ ሲገልፁ “በየጊዜው በመውረድ ሂደት ላይ ስለነበርና ጽሑፉ ስላልተጠናቀቀ ነው” ይላሉ (ገፅ 19)፡፡

ቀደም ሲል እንደገለፅነው የቁርኣን ሁለት ሦስተኛው በሙሐመድ ዘመን በጽሑፍ መጠበቁን የሚያመለክት የረባ ማስረጃ የለም፡፡ ሆኖም ቁርኣን በሙሐመድ ዘመን በአንድ ጥራዝ ያለመሰብሰቡ ምክንያቱ ሐሰን ታጁ የጠቀሱት ብቻ አይደለም፡፡ አል-ሱዩጢ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ እንዲህ ይላሉ፡-

“ነቢዩ ሙሐመድ የተወሰኑ ሕግጋትንና ንባባትን የመሻር ሐሳብ ስለነበራቸው ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ አልሰበሰቡትም፡፡”[17]

ቁርኣንን ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ጥራዝ እንዲሰበሰብ ያደረጉት ኸሊፋ አቡበክር ሲዲቅ ነበሩ፡፡ አቶ ሐሰን ቁርኣን በአቡበክር ዘመን የተሰበሰበበትን ሂደት ሲገልፁ፡- “ሐርበሪዳ” በተሰኘ የአመፅ ጦርነት ምክንያት የማማ በተባለ ቦታ በርካታ የነቢዩ ባልንጀሮች የሞቱበት ሁኔታ መከሰቱን፤ ከነዚህ መካከል በቁርኣን ሊቅነታቸው የታወቁ 70 ያህል ሶሐቦች መሞታቸውን፤ የቁርኣን አዋቂዎች ሞተው ያለቁ እንደሆን ቁርኣንን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሂደት ሊቋረጥ መቻሉ ዑመርን እንዳሰጋው፤ ስለዚህ ቁርኣን የተጻፈባቸው ቁሳቁሶች ሁሉ በኸሊፋው ኃላፊነት ስር እንዲሰበሰቡ ሐሳብ እንዳቀረበ፤ በዚህም መሠረት የማሰባሰቡን ሂደት “ምግባረ ሰናይ” የነበረው ዘይድ በበላይነት እንዲመራው እንደተመረጠና ይህንኑ እንዳከናወነ አትተዋል (ገፅ 20-22)፡፡ ነገር ግን በማሰባሰቡ ሂደት ወቅት የነበረውን አጨቃጫቂ ሁኔታና ሸፍጥ ሳይገልፁ አልፈዋል፡፡ በአቡበክር ዘመን የተደረገው ቁርኣንን የማሰባሰብ ሂደት አጠራጣሪ የሚሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡-

  1. የመጀመርያው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር ስለዚህ የማሰባሰብ ሂደት የሚናገሩት ድርሳናት በወቅቱ የተጻፉ ሳይሆኑ ነገሩ ከተከሰተ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉ መሆናቸው ነው፡፡ ዘጋቢዎቹ ምንም ያህል ቅኖችና ሐቀኞች ቢሆኑ ታሪኩ በጊዜ ርዝመት መበረዝ መቻሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በዚህ ሂደት ወቅት አስደንጋጭ የሆኑ ጉዳዮች ሳይዘገቡ የመታለፋቸው ሁኔታ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ታሪኩ መቀየሩን ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል አንዱ በአቡበክር ዘመን ቁርኣን በወረቀት ላይ እንደተጻፈ መነገሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሐቀኛ በሆኑት የታሪክ መዛግብት መሠረት ሙስሊሞች ፐፓይረስ የተሰኘውን ከደንገል የሚዘጋጅ መጻፍያ መጠቀም የጀመሩት በዑመር ዘመን ግብፅን ከወረሩ በኋላ ነበር፡፡ ወረቀት በሙስሊሞች ጥቅም ላይ የዋለው ደግሞ አቡበክር ካለፉ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ ሰመርቃንድ በተሰኘ ቦታ ነበር፡፡ በባግዳድ ወረቀትን ማምረት የተጀመረው በስምንተኛው ክፍለ ዘመን መገባደኛ በቻይናውያን እርዳታ ነበር፡፡[18]
  2. ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ የማሰባሰብ ሂደት ለመጀመርያ ጊዜ በአቡበክር ትዕዛዝ በዘይድ አማካይነት እንደተከናወነ በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ ቢነገርም[19] ይህንን የሚጣረስ ሌላ ዘገባ አለ፡-

“ኢብን ቡራይዳህ እንዳስተላለፉት፤ ለመጀመርያ ጊዜ ቁርኣንን በሙሳሂፍ (ጥራዝ) የሰበሰበው የአቡ ሁዛይፋህ ባርያ የነበረውና ነፃ የወጣው ሰሊም ነበር፡፡”[20]

(ሰሊም ቁርኣንን እንዲያስተምሩ በነቢዩ ሙሐመድ ሥልጣን ከተሰጣቸው አራት ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡)[21]

እንግዲህ ሙስሊም ምሑራን ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ዘገባዎችን ተጋፍጠዋል፡፡ ከሁለቱ አንዱ የግድ ውሸት መሆን አለበት፡፡ ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ የሰበሰበው የመጀመርያው ሰው ማነው? የሚለውን ቀላል ጥያቄ ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ መመለስ ያልቻሉ ድርሳናት ሌሎች ትርክቶቻቸው አስተማማኝ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

  1. በሙሐመድ ዘመን በቁርኣን ውስጥ የተካተቱ ነገር ግን ዘይድ ያስወገዳቸው ክፍሎች ነበሩ፡፡ እስላማዊ ድርሳናት እንዲህ ሲሉ ይናዘዛሉ፡-

“አብዱላህ ቢን አባስ እንዳስተላለፉት፤ ኡመር ቢን ኸጧብ በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ምስባክ ላይ ተቀምጠው እንዲህ አሉ፡- ‹‹አላህ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) በእውነት ላካቸው፤ መጽሐፍንም አወረደላቸው፤ በእርሳቸው ላይ በተወረደው ውስጥ በድንጋይ የመውገር አንቀፅ ነበር፡፡ አነብንበነዋል፣ በትውስታችን ውስጥ መዝግበነዋል እንዲሁም ተረድተነዋል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በድንጋይ ወግሮ የመግደልን ቅጣት ይተገብሩ ነበር፤ ከእርሳቸው በኋላ እኛም ተመሳሳይ ነገር እንፈፅም ነበር፡፡ በጊዜ ሂደት ሰዎች ‹በአላህ መጽሐፍ ውስጥ የውግረትን ሕግ አላገኘንም› በማለት በአላህ የተደነገገውን ይህንን ድንጋጌ ችላ እንዳይሉ እፈራለሁ፡፡ ዝሙትን የሚፈፅሙ ባለትዳር ወንዶችና ሴቶች በማስረጃ ከተረጋገጠ፣ እርግዝና ከተፈጠረ ወይም ከተናዘዙ እንዲወገሩ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ የተቀመጠ ግዴታ ነው፡፡››”[22]

በአንድ ዘገባ መሠረት ዑመር ይህንን አንቀፅ በዘይድ ወደሚመራው ኮሚቴ ባመጣ ጊዜ ዘይድ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፤ የሰጠው ምክንያት ደግሞ ከዑመር ውጪ ሌላ ምስክር ስላላገኘ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡[23] ነገር ግን ይህ አንቀፅ የቁርኣን አካል እንደነበር የሙሐመድ ሚስት አይሻ መመስከሯ ተነግሯል፡፡[24] ዘይድ ቁርኣንን ሲሰበስብ በጽሑፍ ሊገኝ ያልቻለው በፍየል ስለተበላ መሆኑም ተዘግቧል፡፡[25]

ይህ አንቀፅ በሙሐመድ ዘመን የቁርኣን አካል እንደነበር በመናገራቸው ዑመርና አይሻ ቅጥፈት ፈጽመው ይሆን? ከአራቱ ኸሊፋዎች መካከል አንዱና የሙሐመድ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ዑመር እንዲሁም የነቢዩ ሚስት አይሻ የሰጡት ምስክርነት ካልታመነ የማን ምስክርነት ሊታመን ነው? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሌሎች ብዙ የቁርኣን ክፍሎች አለመካተታቸውን እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

  1. በየማማ በተደረገው ጦርነት ወቅት ከሞቱት ሰዎች ጋር የጠፉ የቁርኣን አናቅፅ እንደነበሩ እስላማዊ ትውፊቶች ይመሰክራሉ፡፡ ይህ ማለት ሁሉም የቁርኣን ክፍሎች በሁሉም አነብናቢዎች እኩል በሆነ ሁኔታ አልተሸመደዱም ነበር ማለት ነው፡፡ ይህንን የሚያረጋግጡ ድርሳናት እነሆ፡-

ኢብን አቢ ዳውድ የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡- “ብዙ የወረዱ የቁርኣን ጥቅሶች በየማማ ጦርነት ላይ በሞቱት ብዙ ሰዎች ይታወቁ ነበር … ከጦርነቱ በተረፉት ሰዎች ግን አይታወቁም ነበር እንዲሁም በጽሑፍ አልሠፈሩም ነበር፡፡ ቁርኣን ሲሰበሰብ አቡበክር፣ ዑመርም ሆነ ኡሥማን አያውቋቸውም ነበር፡፡ ከእነርሱ በኋላ በነበረ አንድም ሰው ጋ ማግኘት አልተቻለም፡፡”[26]

አል-ሱዩጢ፣ ኢትቃን በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ተከታዩን ማስጠንቀቅያ አስፍረዋል፡- “ከእናንተ መካከል ማንም ሰው ሙሉውን ቁርኣን አግኝቼዋለሁ ብሎ መናገር የለበትም፡፡ የቁርኣን አብዛኛው ክፍል የጠፋ ሆኖ ሳለ ሁሉን አውቃለሁ ብሎ መናገር እንዴት ይቻላል? ከዚህ ይልቅ የተረፈውን አግኝቼዋለሁ ብሎ ይናገር፡፡”[27]

በዚህ ሁሉ ችግሮችና ውዝግቦች የታጀበው የአቡበክር ቁርኣንን የማሰባሰብ ሂደት ተዓማኒነት ሊኖረው የሚችለው በምን መስፈርት ነው? ሐሰን ታጁ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በመነሳታቸው ፀፀት ውስጥ መግባት መጀመራቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡

የኡሥማን የእርማት ሂደት ከጥርጣሬ የፀዳ ነበርን?

ሐሰን ታጁ በኡሥማን ዘመን ስለተደረገው ቁርኣንን የማረምና የማስተካከል ሥራ ያቀረቡት ሐተታ በአሳሳች ምልከታዎች የተሞላ ነው፡፡ ኡሥማን ቁርኣንን ለምን ማረም እንዳስፈለገው ሲገልፁ እዲህ ብለዋል፡-

የእስልምና ግዛት እያደር እየሰፋ፤ ለአረብኛ ቋንቋ እንግዳ የሆኑ ሕዝቦች የሙስሊሙን ኡምማህ እየተቀላቀሉ ሄዱ፡፡ በዚያ ወቅት ቁርኣን በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ያልተበተነና በቃል የሚተላለፍ በመሆኑ የንባብ ስልት ለአዳዲስ ሰላሚዎች ማስቸገሩ እና ልዩነትም መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በአርመንያና በአዘርቤጃን ዘመቻ ላይ የተሳተፈው ሁዘይፋህ ቢን አልየማን በቁርኣን የንባብ ስልት ላይ የተከሰተውን ልዩነት ማስተዋሉ አልቀረም፡፡ በዚህ ሳቢያ የደረሰውን መወዛገብም አስተዋለ፡፡ እናም ኡሥማን ዘንድ በመቅረብ እንዲህ ሲል ተማፀናቸው፡- ‹‹ሕዝበ ሙስሊሙ ልክ እንደ አይሁዶችና ክርስቲያኖች በሃይማኖት መጽሐፉ ከመወዛገቡ በፊት አንዳች መላ ዘይዱ፡፡›› (ገፅ 22-23)

ሙስሊሙ ማሕበረሰብ በቁርኣን ላይ መለያየት የጀመረው ለአረብኛ ቋንቋ እንግዳ የሆኑ ሕዝቦች በመስለማቸው ምክንያት ብቻ ሳይሆን በዋናነት የሙሐመድ ባልደረቦች ይጠቀሟቸው የነበሩ የተለያዩ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ቁርአኖች በመሰራጨታቸው ነበር፡፡ የኢራቅና የሦርያ ሙስሊሞች ለጂሃድ በአርመንያና በአዘርባጃን ድንበር ላይ በተገናኙ ጊዜ ‹ትክክለኛው የቁርኣን ቅጂ የቱ ነው?› በሚለው ጥያቄ ላይ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ከሦርያ የመጡ የሁምስ ሙስሊሞች የአል ሚቅዳድ ኢብን አል-አስዋድን ቅጅ ይቀበሉ የነበረ ሲሆን የተቀሩት የሦርያ ሙስሊሞች ደግሞ የኢብን ከዕብን ቅጂ ይከተሉ ነበር፡፡ በኢራቅ የነበሩት የበስራ ሙስሊሞች የአቡ ሙሳን ንባብ ይከተሉ የነበረ ሲሆን የኩፋ ሙስሊሞች ደግሞ የኢብን መስዑድን ይከተሉ ነበር፡፡[28] ስለዚህ የመለያየቱ አብይ መንስኤ የተለያዩ የቁርኣን ቅጂዎች መሰራጨት እንጂ የአረብኛ ቋንቋ ችግር አልነበረም፡፡ የኡሥማን ዓላማ የግጭት መንስኤ የሆኑትን እነዚያን የተለያዩ የቁርኣን ቅጂዎች በማስወገድ ወጥ የሆነ የንባብ ሥልት ያለውን አንድ ቅጂ ማዘጋጀት ነበር፡፡

ከእስላማዊ ድርሳናት ከምናገኛቸው መረጃዎች በመነሳት የኡሥማን የእርማት ሥራ እጅግ አጠራጣሪ የሚሆንባቸውን ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ እንችላለን፡-

  1. የኡሥማን ቅጂ በአቡበክር ዘመን በዘይድ ተዘጋጅቶ በዑመር እጅ በነበረውና የዑመር ልጅ ሐፍሷ[29] በወረሰችው ጥራዝ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡[30] የዚያ ጥራዝ የአሰባሰብ ሂደት እጅግ አጠራጣሪ መሆኑን ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡
  2. ዘይድ የሙሐመድ ጸሐፊ የነበረ ቢሆንም ቁርኣንን እንዲያስተምሩ በሙሐመድ ዕውቅና ከተሰጣቸው አራቱ አነብናቢዎች መካከል አልነበረም፡፡ አራቱ አነብናቢዎች አብዱላህ ኢብን መስዑድ፣ ሰሊም፣ ሙዓዝና ኡበይ ቢን ከዕብ ነበሩ፡፡[31] ቁርኣንን እንዲያስተምሩ በሙሐመድ ዕውቅናና ሥልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦች እያሉ ዘይድ ለዚህ ሥራ መመረጡ ጥያቄን ያጭራል፡፡
  3. ቁርኣንን የማነብነብ ብቃቱ በሙሐመድ የተመሰከረለትና ቁርኣንን እንዲያስተምር ተሹሞ የነበረው ኢብን መስዑድ[32] ከኮሚቴው ውስጥ እንዲገለል ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳም ቅሬታውን እንዲህ በማለት ገልፆ ነበር:-

“ሙስሊሞች ሆይ! ቁርኣንን እንዳልጽፍ እኔን በማግለል እስልምናን ስቀበል [ገና ሳይወለድ] በአባቱ አካል ውስጥ በካፊርነት ለነበረው ሰው [ለዘይድ] ኃላፊነት ተሰጠ፡፡”[33]

ኢብን መስዑድ ያቀረበው ይህ ቅሬታ ተገቢ ነበር፡፡

  1. ኢብን መስዑድ በኡሥማን ትዕዛዝ በዘይድ ተዘጋጅቶ የነበረውን ቁርኣን ጨምሮ ሕዝበ ሙስሊሙ የተጭበረበረ ንባብ የሚከተል መሆኑን በማሳወቅ በግልፅ ተቃውሟል፡፡[34] የኩፋ ሕዝቦች በኡሥማን ውሳኔ የፀደቀውን አዲሱን ቁርኣን እንዳይቀበል አድርጓል፡፡[35] በዚህም ምክንያት የኩፋ ሕዝብ አል-ሐጃጅ ኢብን ዩሱፍ አል-ሣቃፊ ሥልጣን እስከያዘበት ዘመን ድረስ የኢብን መስዑድን ቁርኣን ተቀብሎ ኖሯል፡፡[36]
  2. ኡሥማን በቁረይሽ ዘዬ ከተጻፈው አዲሱ ቁርኣን ውጪ ሌሎች ቁርአኖችን በማቃጠል እንዲወድሙ በማድረጉ በዘመኑ በነበሩት ሙስሊሞች ዘንድ ተነቅፏል፡፡ “ቁርኣንን የቀደደ ሰው” እስከመባልም ደርሷል፡፡[37]
  3. ኡሥማን የቀደሙትን ቁርአኖች አቃጥሎ የእርሱን ብቻ ኦፊሴላዊ በማድረጉ ምክንያት የመረጃ ስወራ አለመኖሩን እርግጠኞች ሆነን መናገር አንችልም፡፡
  4. ኡሥማን አዲሱን ቁርኣን ኦፊሴላዊ በማድረግ ሌሎችን ቢያቃጥልም የሐፍሷን ቁርኣን ሳያቃጥል በመመለሱና በሌሎች አነብናቢዎች የተዘጋጁትን ቁርአኖች በሙሉ ሳያጠፋ በማለፉ ምክንያት ሌሎች የቁርኣን ቅጂዎች በድጋሚ ችግር መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ የእነዚህ ንባቦች የተወሰኑ ክፍሎች ኢብን አቢ ዳውድ አል ሲጂስታኒና አቡ አል-ፈሥ ዑሥማንን የመሳሰሉ ጥንታውያን ሙስሊም ሊቃውንት በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ ተጠብቀዋል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ሲገመገሙ በቁርኣን ውስጥ ከፍተኛ ለውጦች መደረጋቸውን ያመለክታሉ፡፡[38]
  5. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተገኙት ከኡሥማን ቁርኣን ላይ እንደተገለበጡ የሚነገሩት ጥንታዊ የቁርኣን ጽሑፎች እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ ሲሆኑ ብዙ ግጭቶች በመካከላቸው ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ጽሑፎች ማየት የሚፈልግ በግርጌ ማስታወሻው ላይ የተሰጡትን ድረ-ገፆች በመጎብኘት ፎቶግራፎቹን ማግኘት ይችላል፡፡[39]

ከላይ ከጠቀስናቸው ነጥቦች አኳያ ሐሰን ታጁ የቁርኣን አሰባሰብ ጥርጣሬን ሊያጭሩ ከሚችሉ ነገሮች የፀዳ መሆኑን ለማሳየት በመጽሐፋቸው ውስጥ ገፅ 18-27 ያሠፈሯቸው ሐሳቦች በሙሉ ውድቅ ናቸው፡፡ ቁርኣን በሙሐመድ ዘመንም ሆነ በኸሊፋዎች ዘመን በትክክል መጠበቁን እንድናምን የሚያስችል ማስረጃ የለም፡፡ በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት ማስረጃዎች ከዚያ በተፃራሪ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ አቶ ሐሰን የቃላት ጂምናስቲክ ከመጫወት በዘለለ በሐመረ ተዋህዶ መጽሔት የተነሱትን ሙግቶች ማስተባበል አልቻሉም፡፡

አስገራሚ ክህደት

አቶ ሐሰን በመጽሐፋቸው ገፅ 27-28 ላይ “አስቂኝ ተረት” በሚል ርዕስ ስር አንድ አስገራሚ ነገር ጽፈዋል፡-

ኦሪየንታሊስቶች እና የክርስቲያን ሚሽነሪዎች ከጥንት ይዞ በየ መጽሐፎቻቸው ደጋግመው የሚያነሱት አንዲት ተረት አለች፡፡ እኔ ለመጀመርያ ጊዜ ሳያት ከምራቸው አልመሰለኝም ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ሲደጋግሟት ‹‹ከምር›› እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ በቅርቡ በርካታ ቀሳውስት በትብብር በቁርኣን ላይ በጻፉት ሂስ ውስጥም በቁምነገር አንስተዋታል፡፡

ተረቷን እንዳስተላለፈቻት የተነገረው አኢሻ ናት፡፡ እንዲህ ብላለች ሲሉ ያወጋሉ፡-

“ስለ ውግረትና ስለ ጥቢ የሚያወሩ የቁርኣን መልእክቶች የተጻፉበት ወረቀት ከአልጋየ ስር ነበር፡፡ ነቢዩ በሞቱ ጊዜ በእርሳቸው ሞት ሳብያ በሐሳብና በሥራ ተጠምጄ እያለ አንዲት ላም ወደቤታችን በመግባት እነዚህን ወረቀቶች በላቻቸው፡፡”

ይህ ዘገባ በሐዲስ ጥናት መስፈርት የመጨረሻው አስከፊ ቅጥፈት (መውዱእ) ነው፡፡ እነርሱ ግን ለዚህ ግድ የላቸውም፡፡ ተረትም ቢሆን ለትችት ካገለገለ ምን ገዷቸው፡፡ (ገፅ 27-28፤ መስመርና አፅንዖት ከኔ)

ከላይ አቶ ሐሰን የጠቀሱት ትርጉም ጥቂት ማስተካከያ ያስፈልገዋል፡፡ የኛን ትርጉም እስኪ እናስቀምጥ፡-

“ስለ ውግረትና ጎልማሳ ወንዶችን አሥር ጊዜ ጡት ስለማጥባት የሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች ወርደው ነበር፡፡ የተጻፈበትም ወረቀት ከእኔ ጋ በእኔ ትራስ ስር ነበር፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሕይወታቸው ባለፈ ጊዜ በህልፈታቸው ተዋክበን ሳለን ለማዳ በግ[40] ገብታ በላችው፡፡”[41]

ይህ ሐዲስ ከስድስቱ የሐዲስ ስብስቦች መካከል አንዱ በሆነው በሱናን ኢብን ማጃህ ውስጥ ከመዘገቡ በተጨማሪ በተከታዮቹ እስላማዊ መጻሕፍት ውስጥ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡-

  • Musnad Ahmad Ibn Hanbal. vol. 6. p. 269
  • Ibn Qutbah, Tawil Mukhtalafi ‘l-Hadith (Cairo: Maktaba al-Kulliyat al-Azhariyya. 1966) p. 310
  • As-Suyuti, ad-Durru ‘l-Manthur, vol. 2. p. 13

ሐሰን ታጁ ይህንን ሐዲስ “የመጨረሻው አስከፊ ቅጥፈት (መውዱእ) ነው” ማለታቸው አስገራሚ ቅጥፈት ነው፡፡ ይህ ሐዲስ የሚገኝበትን የኢብን ማጃህ ዘገባ ቦታውን አውጥቶ የተመለከተ ሁሉ በሐዲስ ሊቃውንት የተሰጠውን ደረጃ በግልፅ ማየት ይችላል፡፡ ሊቃውንቱ ለዚህ ሐዲስ የሰጡት ደረጃ (Grade) “መውዱእ” ሳይሆን “ሐሰን” (መልካም ወይም ጥሩ) የሚል ነው፡፡[42] አንባቢያን አይተው ይፈርዱ ዘንድ የሐዲሱን ፎቶ ግራፍ አስቀምጠናል፡፡

የ “ሐሰን” ደረጃ የተሰጠው ሐዲስ “ሌሎች መስፈርቶች ተሟልተው የማስታወስ ችሎታው ደከም ያለ የዘገባ አስተላላፊ የተሳተፈበት ዘገባ” መሆኑን አቶ ሐሰን ራሳቸው በዚሁ መጽሐፍ ገፅ 56 ላይ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ከአንድ ችግር በስተቀር “ሐሰን” (ጥሩ) ሐዲሳት የሳሂህ (ተዓማኒ) ሐዲሳትን መስፈርቶች በሙሉ ያሟላሉ፡፡ አቶ ሐሰን ይህንን ሐዲስ ከደረጃው አውርደው “መውዱእ” ማለታቸው እርሳቸውን ከመሰለ ሙስሊም የማይጠበቅ አስከፊ ቅጥፈት ነው፡፡

የሆነው ሆኖ “የውግረትና የጥቢ ሐዲስ” በሳሂህ ሐዲሳት ውስጥ የተዘገበ በመሆኑ[43] በኢብን ማጃህ ውስጥ የተጠቀሰው የፊየል/በግ ታሪክ “መውዱእ” መሆን አለመሆኑ ቁርኣንን የተቀጣጠፈ ሰነድ ከመሆን አያድነውም፤ ስለዚህ አቶ ሐሰን የዚህን ሐዲስ ተዓማኒነት መካዳቸው የትም አያደርሳቸውም፡፡ ጥቅሱ በፊየል፣ በግመል፣ በእሳት ወይም በውኀ ተበልቶ ቢጠፋ ቁምነገሩ ያለው በአጠፋፉ ሁኔታ ላይ ሳይሆን በመጥፋቱ ላይ በመሆኑ የፊየሊቷ ታሪክ እውነት አይደለም ቢባል እንኳ ከቁርኣን መሰረዙ በሳሂህ ሐዲሳት እስከተረጋገጠ ድረስ ቁርኣን ሐሰተኛ ሰነድ መሆኑ ሊታበል የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ሰባኪያን የማያዋጣቸውን የክህደት ጎዳና በመተው ሕዝባቸውን ከማታለል ሊታቀቡና እውነታውን ሊጋፈጡ ያስፈልጋቸዋል፡፡

አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

“ለውይይት ያህል ግን ዘገባው እውነት ነው ብንል እንኳ በወቅቱ የነበረው አንድ የቁርኣን ቅጂ ብቻ ነውን? ደግሞስ ቁርኣን በሺዎች በሚቆጠሩ የነቢዩ ባልደረቦች ልቦና ውስጥ ተጽፎ አልነበረምን?” (ገፅ 28)

አቶ ሐሰን በዚህ አባባላቸው ውስጥ ሁለት ሀሰተኛ ቅድመ ግንዛቤዎችን አንፀባርቀዋል፡፡ የመጀመርያው ሁሉም የቁርኣን ጥቅሶች በወቅቱ ከአንድ በላይ በሆኑ ቁሶች ላይ ተጽፈዋል የሚል ነው፡፡ ይህ መሠረት አልባ ቅድመ ግንዛቤ ነው፡፡ አቶ ሐሰን በዚሁ መጽሐፋቸው ገፅ 72 ላይ ዘይድ ቁርኣንን በሚሰበስብበት ወቅት የሱራ አል-አሕዛብ 23 አንቀፅ የተጻፈበት ቁስ በመታጣቱ ምክንያት በፍለጋ ከአንድ ወዳጁ ዘንድ እንዳገኘና ስለ ትክክለኛነቱ ሁለት ሰዎችን በማስመስከር በቁርኣን ውስጥ እንዳካተተው ጽፈዋል፡፡ ይህ መረጃ በአንድ ቁስ ላይ ብቻ የተጻፉ የቁርኣን ጥቅሶች መኖራቸውን በማረጋገጥ የመጀመርያ ቅድመ ግንዛቤያቸውን መቀመቅ ይከተዋል፡፡ በፊየል የተበላው ቁስ አንቀፁን የያዘ ብቸኛ ቁስ ላለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉምና፡፡

ሁለተኛው ሀሰተኛ ቅድመ ግንዛቤ ደግሞ ሁሉም የቁርኣን ክፍሎች በሁሉም የነቢዩ ባልደረቦች ተሸምድደዋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን አቶ ሐሰን ለዚህ የሚሆን አንድም ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም፡፡ በሐዲሳት ውስጥ የሚገኙት ማስረጃዎች ከዚህ በተጻራሪ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሙስሊሞች ረጃጅም የቁርኣን ምዕራፎችን ሳይቀር ረስተዋል፡፡ ይህ አንቀፅ ራሱ ዑመርና አይሻን በመሳሰሉት ለሙሐመድ እጅግ ቅርብ በነበሩት ሰዎች ትውስታ ውስጥ ብቻ ነበር የተገኘው፡፡ የውግረትን ጥቅስ ዑመር በዘይድ ወደሚመራው አሰባሳቢ ኮሚቴ በወሰደ ጊዜ ሌላ ምስክር ባለመምጣቱ በቁርኣን ውስጥ እንዳይካተት ተደርጓል፡፡[44] አስገራሚው ነገር ሙስሊሞች ዛሬ እነዚህን ሕግጋት መተግበራቸው ነው፡፡ ይህም የኡሥማን አዲሱ ቁርኣን ያልተሟላ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው!

ቅጥፈተ ኡስታዝ

ኡስታዝ ሐሰን ከገፅ 63-76 ላይ “ቅጥፈተ ሐመር” በሚል ርዕስ ስር የመጽሔቱ አዘጋጆች የፈፀሟቸው “ቅጥፈቶች” ናቸው ያሏቸውን የተለያዩ ነጥቦች አንስተዋል፡፡ ነገር ግን አስገራሚ በሆነ ሁኔታ የእኩለ ቀን ያህል ግልፅ የሆኑ ሃቆችን ለማስተባበል ሲፍጨረጨሩና በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ ተመዝግበው በሙስሊም ሊቃውንት ዘንድ የሚታወቁ ሐዲሳትን ህልውና ዓይናቸውን በጨው አጥበው ሲክዱ ይታያሉ፡፡

  • ይዘቱን መመርመር ኃጢአት አይደለምን?

የሐመረ ተዋህዶ ጸሐፊያን ሙስሊሞች ቁርኣንን መመርመር ድፍረትና ኃጢአት መሆኑን ማመናቸውን የጻፉትን በመጥቀስ “ነጭ ውሸት” ነው ይላሉ – ኡስታዙ፡፡ ብዙ የቁርኣን ማብራሪያዎች (ተፍሲሮች) መኖራቸውን እንዲሁም በመስጊዶች አካባቢ መጠናቱንና “መተንተኑን” እንደ ማስረጃ በመጥቀስ የአባባሉን “ስህተትነት” ለማስረዳት ይሞክራሉ (ገፅ 63-64)፡፡ ነገር ግን ሐመሮች እየተናገሩ ያሉት በእስላማዊ አስተሳሰብ ስለተቃኘውና እንደ ጋሪ ፈረስ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ለማየት ስለሚያስገድደው እንደዚህ ዓይነቱ “ጥናትና ምርምር” ሳይሆን ነፃ በሆነ አእምሮ ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን ለማረጋገጥ በሁሉም አቅጣጫ ስለሚደረግ ፍተሻ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት በክርስቲያንና ዓለማውያን ምሑራን ይዘቱ ተፈትሿል፣ ታሪኩ ተጠንቷል፣ ጽሑፉ ተመርምሯል፡፡ ውጤቱ ደግሞ በእርሱ ላይ ያለንን መተማመን በእጅጉ የሚያጠነክር እንጂ የሚሸረሽር አይደለም፡፡ እስልምና እንዲህ ያለውን ፍተሻ እንደማይፈቅድ ለማወቅ በዚህ ሁኔታ ቁርኣንን ለመመርመር በሞከሩት ሊቃውንት ላይ የደረሰውንና እየደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ማየቱ በቂ ነው፡፡

ቁርኣንን መመርመር የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን ነፃ በሆነ አእምሮ ምሑራዊ አካሄዶችን በመጠቀም ምርመራ የሚያደርጉትን ምሑራን እንደ ጠላት መቁጠር በሙስሊሞች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ቁርኣንን አስመልክቶ ምሑራዊ ጥናት ያደረጉ ምዕራባውያን ኦሪዬንታሊስቶችን አቶ ሐሰን በዚሁ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ በጻፉት ሁኔታ በጠላትነት መፈረጅና ማጠልሸት በሙስሊም ጸሐፊያን ዘንድ የተለመደ ነው (ገፅ 13)፡፡

ሙስሊም አገራትና መሪዎች በጥንታውያን የቁርኣን የእጅ ጽሑፎች ላይ ጥልቅ ጥናቶች እንዳይደረጉ በሊቃውንት ላይ እግድ መጣላቸውና ከዕይታ እንዲሰወሩ ማድረጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የሰነዓ የእጅ ጽሑፎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ “አትላንቲክ መንዝሊ” የተሰኘ መጽሔት ከነዚህ ጥንታዊያን የእጅ ጽሑፎች በመነሳት የቁርኣንን በትክክል ተጠብቆ መቆየት የሚገመግም ጽሑፍ ይዞ መውጣቱ በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ቁጣና ተቃውሞን ቀስቅሶ ነበር፡፡ በአዘጋጆቹም ላይ ማስፈራርያ ደርሷል፡፡[45] ቴዎ ቫን ጎግ የተሰኘ ስዊድናዊ የፊልም ባለሙያና ደራሲ ሴቶች በቁርአናዊ ትዕዛዛት ምክንያት በእስልምና ውስጥ የሚደርስባቸውን ጭቆና የተመለከተ የአሥር ደቂቃ ፊልም በመሥራቱ ሳብያ በ2004 ዓ.ም. በአምስተርዳም አደባባይ ተገድሏል፡፡[46] ኁልቁ መሣፍርት የሌላቸውን መሰል ታሪኮች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሐሰን ታጁ ጉዳዩን ወደ ክርስቲያኖች ለማዞር በመካከለኛው ዘመን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ የነበራትን ኢ-ክርስቲያናዊ አቋም ለመጥቀስ ሞክረዋል (ገፅ 64)፡፡ ነገር ግን በዚያን ዘመን የነበረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አቋም ክርስቲያናዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ክርስቲያኖች ያንን ከሚመስል አመለካከት ተላቀው ወደ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ከተመለሱ ብዙ ክፍለ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን ስለመረመረ ወይም ስለተቃወመ የሚሰደድና የሚገደል ሰው የለም፡፡ አክራሪ እስልምና ግን ምርመራና ትችትን ስለሚፈራ ከልደቱ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ራሱን በሰይፍ መከላከሉን ቀጥሏል፡፡ ይህንንም ባሕርዩን መቼም ቢሆን የመለወጥ ተስፋ ያለው አይመስልም፡፡

  • ቁርኣን ቀኖናዊ የሆነው መች ነበር?

ሐመረ ተዋህዶ “ቁርኣን እንደ መጽሐፍ ሆኖ ቀኖናዊ የተደረገው ወደ ስምንተኛውና ዘጠነኛው መቶ ዓመት ላይ ነው” በማለት ያሠፈረውን በመጥቀስ “ቅጥፈት” ነው ይላሉ – አቶ ሐሰን (ገፅ 64)፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚጠቅሱት ቁርኣን በአቡበክር ዘመን “በአንድ መጠረዙንና” በኡሥማን ዘመን ደግሞ “ተባዝቶ” መሰራጨቱን ነው፡፡ ሐመረ ተዋህዶ በሌላ ቦታ ላይ ቁርኣን በኡሥማን ዘመን በመጽሐፍ መልክ መዘጋጀቱን እንደጻፈ በመጥቀስ አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡- “እንዲህ ዓይነቱን የሐሳብ መጣረስ ምን ትሉታላችሁ? ወይስ ኡሥማን ኸሊፋ የተደረጉት በ8ኛው ወይም 9ኛው መቶ ዓመት መስሎት ይሆን?” (ገፅ 65)፡፡

ሰውየው የቀኖናን ፅንሰ ሐሳብ የተረዱት አይመስልም፡፡ ቀኖና የሚለው ቃል “ካኖን” ከሚል የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን “የመለኪያ ብትር” ወይም “ደንብ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ እውነተኛ የፈጣሪ ቃል እንደሆኑ የታመነባቸውን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ዝርዝርና ቅርፅ ያመለክታል፡፡

አንድ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ በአንድ ጥራዝ ስለተጠረዘ ቀኖናዊ አይሆንም፡፡ ቁርኣን የመጨረሻ መልኩን ለመያዝ በተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ አልፏል፡፡ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉት እስላማዊ ድርሳናት ትክክል ከሆኑ መጀመርያ በሙሐመድ ተከታዮች ትውስታ ውስጥ የነበረና በተለያዩ የተበታተኑ ቁሶች ላይ ባልተሟላ ሁኔታ የተጻፈ ጽሑፍ ነበር፡፡ ኸሊፋ አቡበክር እነዚህን ጽሑፎች አንድ ላይ ሰብስበው በአንድ ጥራዝ አስጻፏቸው፡፡ ሦስተኛው ኸሊፋ ኡሥማን ደግሞ አንድ ወጥ የሆነ አነባበብ ያለውን ቁርኣን በማዘጋጀት ሌሎች ጽሑፎችን በማቃጠል ይኸኛውን ኦፊሴላዊ አደረጉ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ቁርአኖችን ማጥፋት ሙሉ በሙሉ አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ የማረምና የማስተካከል ሂደቱ ከዚያ ወዲህ ለረጅም ዘመናት ስለቀጠለ በሁለቱ ኸሊፋዎች ዘመን ቀኖናዊ እንደሆነ መደምደም አይቻልም፡፡ በምሑራን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ቁርኣን አሁን ያለውን መልክ ለመያዝ ቢያንስ ሦስት ክፍለ ዘመናት አስፈልገውታል፡፡[47]

በቁርኣን አነባበብ ምክንያት የተፈጠረው ልዩነት እስከ አሥረኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ዘልቆ ነበር፡፡ ኢብን ሙጃሂድ የተሰኘው የባግዳድ አነብናቢ ከፖለቲካ መሪዎች ጋር በመመሳጠር የኢብን መስዑድና የሌሎች ሙስሊም ሊቃውንት ንባባት እንዲታገዱ አድርጓል፡፡ ኢብን ሻነቡዝን የመሳሰሉት ሊቃውንት የገዛ ንባባቸውን እንዲተው በሚል ግርፋት ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ኢብን ሚቅሳምን የመሳሰሉት ሊቃውንት እንዲሁ ንባባቸውን እንዲጥሉ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል፡፡[48]

አቶ ሐሰን ከዚሁ ርዕስ ሳይወጡ የተናገሯትን አንዲት ነገር እንጥቀስ፡-

“አቡበክር በነቢዩ ዘመን የተጻፉ የቁርኣን መጽሐፎችን በአንድ ጠርዘው አስቀመጡ፡፡ ኡሥማን ይህን ጥራቅ[?] በብዙ ቅጅዎች በማባዛት ለሁሉም የሙስሊም ግዛቶች አሰራጩ፡፡” (ገፅ 65)

በመጀመርያ ደረጃ በነቢዩ ዘመን “የቁርኣን መጽሐፎች” የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ የቁርኣን የተለያዩ ክፍሎች አጥንት፣ ሰሌን፣ ድንጋይና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ በተበታተነ ሁኔታ ተጽፈው የነበሩ ሲሆን “መጽሐፍ” ተብለው ለመጠራት የሚበቁ አልነበሩም፡፡ ኸሊፋ አቡበክርም እነዚህ ቁሳቁሶች አንድ ላይ እንዲጠረዙ አላደረጉም፡፡ ይልቁኑ በተሻለ ቁስ ላይ በመጽሐፍ መልክ እንዲጻፍ ነበር ያደረጉት፡፡ ይህ መጽሐፍ ደግሞ በኡሥማን ዘመን በሐፍሷ ቤት ተቀምጦ ነበር፡፡[49] አጥንት፣ ሰሌንና ድንጋይን የመሳሰሉ ቁሶችን አንድ ላይ እንደ መጽሐፍ መጠረዝ የማይመስል ነው፡፡ የኡሥማን ተግባርም አቡበክር ያዘጋጁትን ጽሑፍ ገልብጦ ከማሰራጨት ያለፈ ነበር፡፡

  • የቁርኣን አናቅፅ ላይገኙ ጠፍተዋል!

ሐመረ ተዋህዶ ቁርኣንን በቃላቸው ካጠኑ ሰዎች ብዙዎቹ በየማማ ጦርነት ላይ በመሞታቸው ምክንያት ብዙ የቁርኣን አንቀፆች ላይገኙ መጥፋታቸውን የሚናገር ዘገባ ከሳሂህ አል-ቡኻሪ ማግኘታቸውን እንደገለፁ አቶ ሐሰን ይጠቅሳሉ (ገፅ 65)፡፡ ይህ አባባል “ቅጥፈት” መሆኑን ለማሳየት የተለያዩ ነጥቦችን ጠቅሰዋል፡፡ በአቶ ሐሰን መሠረት፡-

  • “ብዙዎቹ የቁርኣን አናቅፅ ላይገኙ ጠፍተዋል” የሚለው አባባል የሐመሮች ጭማሬ ነው፡፡ (ገፅ 66)

በየማማ በተደረገው ጦርነት ሳብያ ቁርኣንን በቃላቸው ካጠኑት ሰዎች ጋር የሞቱና ያልተመዘገቡ አናቅፅ ስለመኖራቸው በአል-ቡኻሪ ሐዲስ ውስጥ በቀጥታ አነጋገር ባለመመዝገቡ ከኡስታዙ አባባል ጋር በከፊል እስማማለሁ፡፡ ስለዚህ ሐመሮች እዚህች ጋር መጠነኛ የምንጭ ስህተት ፈፅመዋል፡፡ ነገር ግን የጠቀሱት ምንጭ ትክክል ባይሆንም በሌሎች እስላማዊ ድርሳናት ውስጥ የተዘገበ በመሆኑ አባባሉ ሊታበል የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ሌሎች እስላማዊ መጻሕፍት ይህንን እውነታ በግልፅ አስፍረዋል፡፡

ኢብን አቢ ዳውድ “ኪታብ አል-መሳሂፍ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ተከታዩን ዘገባ አስፍረዋል፡-

“…ብዙ የወረዱ የቁርኣን ጥቅሶች በየማማ ጦርነት ላይ በሞቱት ብዙ ሰዎች ይታወቁ ነበር …. ከጦርነቱ በተረፉት ሰዎች ግን አይታወቁም ነበር እንዲሁም በጽሑፍ አልሠፈሩም ነበር፡፡ ቁርኣን ሲሰበሰብ አቡ በክር፣ ዑመርም ሆነ ኡሥማን አያውቋቸውም ነበር፡፡ ከእነርሱ በኋላ በነበረ አንድም ሰው ጋ ማግኘት አልተቻለም፡፡”[50]

አል-ሱዩጢ፣ “አል-ኢትቃን ፊ ዑሉም አል-ቁርኣን” በተሰኘው መጽሐፋቸው ክፍል 2 ገፅ 25 ላይ ቁርኣን ሳይሸራረፍ እንደተጠበቀ ለሚያምኑ ሙስሊሞች ከአብዱላህ ቢን ዑመር የተላለፈውን እንዲህ የሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስፍረዋል፡-

“ከእናንተ መካከል ማንም ሰው ሙሉውን ቁርኣን አግኝቼዋለሁ ብሎ መናገር የለበትም፡፡ የቁርኣን አብዛኛው ክፍል የጠፋ ሆኖ ሳለ ሁሉን አውቃለሁ ብሎ መናገር እንዴት ይቻላል? ከዚህ ይልቅ የተረፈውን አግኝቼዋለሁ ብሎ ይናገር፡፡”[51]

አቶ ሐሰን ሃቀኛ መምህር ቢሆኑ ኖሮ ዘገባው በቡኻሪ ውስጥ እንደማይገኝና በሌሎች መጻሕፍት ውስጥ እንደሚገኝ በመግለፅ እርማት መስጠት ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ሃቀኛ ስላልሆኑ የምንጩን ስህተትነት ተገን በማድረግ የዘገባውን መኖር ክደው አልፈዋል፡፡ ትልቅ ቅጥፈት ነው፡፡

  • “ሐመሮች በነቢዩ ዘመን የተከተቡ የቁርኣን መልእክቶች ‹‹እግር አውጥተው›› ወደ ጦርነት የሄዱ አስመስለዋል፡፡ የዘመቱት ጽሑፎቹ ሳይሆኑ… ሊቃውንት ናቸው፡፡” (ገፅ 66)

“ሊቃውንቱ ቢሞቱ እንኳ ጽሑፎቹ ስለነበሩ ከቁርኣን የሚጎድል ነገር የለም” ለማለት ነው ይህንን የጻፉት፡፡ ነገር ግን ሁሉም የቁርኣን ክፍሎች በሙሐመድ ዘመን በጽሑፍ እንደሠፈሩ የሚያመለክት ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ ቀደም ሲል እንዳየነው በእጃችን የሚገኙት ማስረጃዎች ከዚህ በተፃራሪ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ይህ አባባላቸው አነብናቢዎቹ ቢሞቱ አንድ አንቀፅ የቁርኣን አካል ሆኖ ለመመዝገብ በጽሑፍ መስፈሩ ብቻ በቂ ነው ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ያመራል፡፡ ይህ ደግሞ በገዛ መጽሐፋቸው ውስጥ ባሠፈሩት መረጃ መሠረት እንኳ ትክክል አይደለም፡፡ ዘይድ አንድን በጽሑፍ የሠፈረ የቁርኣን ክፍል የስብስቡ አካል አድርጎ ለመቁጠር ስድስት ሰዎች እንዲያረጋግጡት ያደርግ እንደነበር ገፅ 24 ላይ ጽፈዋል፡፡ በራሳቸው ኑዛዜ መሠረት በጽሑፍ የሠፈረ የቁርኣን ክፍል ምስክር ከሌለው ተቀባይነት ስለማያገኝ በቃላቸው ያጠኑት ሞተው ጽሑፉ ብቻ ቢቀር ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ ከላይ የተቀመጠው ሙግታቸው ውድቅ ነው፡፡

  • “…በጦርነቱ ከሞቱት ሌላ አራቱ ኸሊፋዎችን ጨምሮ በርካታ የቁርኣን ሊቃውንት በሕይወት ነበሩ…” (ገፅ 66 እና 67)

ይህም አባባል ሁሉም የቁርኣን ክፍሎች በሁሉም የሙሐመድ ባልደረቦች በእኩል ሁኔታ ተሸምድደዋል የሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤን ያዘለ ነው፡፡ ይህ ፈፅሞ የተሳሳተ ነው፡፡ ስለ ውግረትና ስለ ጥቢ የሚያወሳውን ጥቅስ ከአራቱ ኸሊፋዎች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃው ዑመር ወደ ዘይድ ባመጣው ጊዜ “ከራሱ ውጪ ሌላ ምስክር ማቅረብ አልቻለም” በሚል እንዳልተቀበለው ቀደም ሲል አይተናል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ይህንን ጥቅስ ዘይድም ሆነ አሰባሳቢ ኮሚቴው እንደማያስታውሱት ነው፡፡ ብዙ ጥቅሶች በመረሳታቸው ሳብያ በቁርኣን ውስጥ አለመካተታቸውንም አይተናል፡፡

ቁርኣን ፍፁም በሆነ ሁኔታ “በሺዎች በሚቆጠሩ የነቢዩ ባልደረቦች” ዘንድ እንደተሸመደደ በማስመሰል አቶ ሐሰን በተደጋጋሚ መናገራቸው በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡

  • የዘይድ ስብስብ ተዓማኒ አይደለም

አቶ ሐሰን “ቁርኣን በሺዎች በሚቆጠሩ የነቢዩ ባልደረቦች ልቦና ውስጥ በማይፋቅ ሁኔታ ተጽፎ ነበር” የሚለውን ቅጥፈታቸውን ያለ ምንም ማስረጃ በመደጋገም “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” የሚለውን ብሂል ከልባቸው ማመናቸውን አረጋግጠውልናል (ገፅ 67-68)፡፡

በኸሊፋ አቡበከር ዘመን በዘይድ የተደረገው የማሰባሰብ ሂደትም ሆነ በኡሥማን ዘመን አርሞ ወጥ መልክ የማስያዝ ሂደት በብዙ ችግሮች የተሞላ እንደነበር ቀደም ሲል በማስረጃዎች አስደግፈን ተመልክተናል፡፡ በእርግጥ ዘይድ “ይህንን ኃላፊነት ከሚሰጡኝ ተራራ ግፋ ቢሉኝ ይቀለኝ ነበር” ማለቱ ተዘግቧል፡፡[52] ይህ የዘይድ አባባል ኃላፊነቱ ምን ያህል እንደከበደው አመላካች ነው፡፡ ነገር ግን አቶ ሐሰን “… የቁርኣን አናቅፅ ስለ አደራ ያስተላለፉትን መልእክት የተረዳ ሙስሊም የትኛውም ኃላፊነት ሲሰጠው ተራራ ግፋ የተባለ ያህል ቢሰማው የሚገርም አይደለም” በማለት የሥራውን ክብደት ለማጣጣል ሞክረዋል (ገፅ 66-67)፡፡ ለዚህ ድጋፍ ይሰጣቸው ዘንድ የጠቀሱት ጥቅስ ደግሞ አስገራሚ ነው፡-

“እኛ አደራን በሰማያትና በምድር፣ በተራራዎችም ላይ አቀረብናት፡፡ መሸከሟንም እንቢ አሉ፡፡ ከእርሷም ፈሩ፡፡ ሰውም ተሸከማት፡፡” (የአሕዛብ ምዕራፍ 33፡72)

አቶ ሐሰን ጥቅሱን ቆርጠው ነው የጠቀሱት፡፡ ሙሉ አንቀፁ እንዲህ ይነበባል፡-

“እኛ አደራን በሰማያትና በምድር፣ በተራራዎችም ላይ አቀረብናት፡፡ መሸከሟንም እንቢ አሉ፡፡ ከእርሷም ፈሩ፡፡ ሰውም ተሸከማት፡፡ እርሱ በጣም በደለኛ ተሳሳች ነውና፡፡”

ይህ ጥቅስ ሰው የፈጣሪውን አደራ መሸከም እንደሚከብደው ብቻ ሳይሆን አደራውን ለመሸከም እንደማይበቃ ነው የሚናገረው፡፡ አደራውን ለመሸከም መድፈሩ ደግሞ በደለኛና ተሳሳች የመሆኑ ምልክት ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ ስለዚህ ቁርኣንን የማሰባሰብ ሂደት ከፈጣሪ ዘንድ የመጣ አደራ ነው ከተባለ በራሱ በጥቅሱ መሠረት ይህንን ተግባር ያከናወኑ ሰዎች ኃላፊነቱን ለመሸከም መድፈራቸው በደለኛና ተሳሳች የመሆናቸው ምልክት ነበር ማለት ነው፡፡ የአንድ ጥቅስ አውድ ሐሳባችንን እስካልደገፈ ድረስ የኛን ሐሳብ እንዲገልፅልን ለማድረግ አቶ ሐሰን በፈፀሙት መንገድ ቆርጦ በማምጣት መደንቀር አግባብ አይደለም፡፡

በአቶ ሐሰን አመለካከት መሠረት ሁሉም የቁርኣን አናቅፅ በሙሐመድ ዘመን ተጽፈዋል፤ “በሺዎች” በሚቆጠሩ የነቢዩ ባልደረቦችም ተሸምድደዋል፡፡ ስለዚህ ማሰባሰብ ብዙም የሚከብድ ሥራ አይደለም፡፡ ዘይድ የማሰባሰብ ሥራውን ከሚሠራ ተራራ መግፋት መምረጡ ለኃላፊነቱ የሰጠውን ከፍተኛ ግምት እንጂ የሥራውን ክብደት አያመለክትም – እንደ አቶ ሐሰን፡፡ ነገር ግን እውነቱ እንደርሱ አይደለም፡፡ በዚህ የማሰባሰብ ሂደት ወቅት ጭቅጭቆችና አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ በፍለጋ የተገኙ፣[53] ሳይካተቱ የቀሩ፣[54] ይዘታቸው የተቀየረ[55] አናቅፅ ነበሩ፡፡ በአቡበክርም ሆነ በኡሥማን ዘመን የአረብኛ ፊደላት የድምፅ ምልክቶች ስላልነበሯቸው አዲሶቹ ቁርአኖች በብዙ መንገድ የሚነበቡ ግራ የተጋቡ ጽሑፎች ነበሩ፡፡[56] የጥራዙ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ኡሥማን ይዘቱን በመመዘን ፍፅምና እንደሚጎድለውና ሰዋሰዋዊ ስህተቶች እንዳሉበት እንዲህ ሲል ተናግሯል፡-

“ሰዋሰዋዊ ህፀፆች አሉበት፡፡ አረቦች እንደየዘይቤያቸው ያርሙታል፡፡”[57]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፡-

“ጸሐፊው የሣቃፍ ሰው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ነገሮች በውስጡ ባልተገኙ ነበር፡፡”[58]

ሱራ 20፡63 መስተካከል እንደሚገባው በተነገረው ጊዜ እንዲህ በማለት እምቢታውን ገልጿል፡-

“ይሁን ግድ የለም፡፡ የተፈቀደውን አይከለክልም፤ ያልተፈቀደውንም አይፈቅድም፡፡”[59]

አቶ ሐሰን ይህንን በሚመስሉ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ችግሮችና ውዝግቦች የተከበበውን የዘይድን ሥራ ነው እንግዲህ “እንከን አልባ የፈጣሪ ቃል” መሆኑን ለማረጋገጥ የሚደክሙት፡፡

የተለያዩ የንባብ ሥልቶች ወይስ የተለያዩ ቁርአኖች?

አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

“ነቢዩ ሙሐመድ የተወሰኑ የቁርኣን ቃላትን ዘርፈ ብዙ ትርጉምና መልእክት ሊይዙ በሚችሉበት አኳኋን ያነቡ ነበር፡፡ ተከታዮቻቸውም ከመልእክቱ ባለቤት ይህንን ስልት ተማሩ፡፡ ሰባት የንባብ ስልቶች ነበሩ፡፡ በነዚህ ስልቶች የተካኑ ሊቃውንት ተፈጠሩ…

የተለያዩ የንባብ ስልት ማለት አንዱን የቁርኣን ቃል በተለያየ መንገድ ማንበብ ማለት እንጅ የተለያዩ ቁርአኖች ማለት አይደለም፡፡ የንባብ ስልቱ መለያየት ቁርኣን ተጨማሪ ቃላት ሳያባክን ብዙ መልእክቶችን እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡” (ገፅ 69)

ለዚህ የሚሆኑ ምሳሌዎች ናቸው ያሏቸውን ሁለት ጥቅሶች በመጥቀስ አንዱ የአረብኛ ቃል እንዴት በተለያየ መንገድ ሊነበብ እንደሚችል ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የጠቀሱት የመጀመርያው ጥቅስ የማዕድ ምዕራፍ 5:6 ላይ የሚገኘውን ነው፡፡ በንባቡ ውስጥ የሚገኘው እጥበትን የተመለከተው የአረብኛ ቃል “አርጁለኩም” ተብሎ ሲነበብ በሶላት ሰዓት እግሮችን እስከ ቁርጭምጭሚት ማጠብ የሚል ትርጉም እንደሚሰጥና “አርጁሊኩም” ተብሎ ሲነበብ ደግሞ ‹ኹፍ› በተሰኘው የውዱ ስርዓት ጊዜ እግሮችን እስከ ቁርጭምጭሚት ድረስ ማበስን እንደሚያመለክት ገልፀዋል (ገፅ 70)፡፡

አቶ ሐሰን ስለ ጉዳዩ በእርግጠኛነት ቢናገሩም ከነቢዩ የተገኘው ትክክለኛው ንባብ የትኛው እንደሆነ በሙስሊም ሊቃውንት መካከል ስምምነት የለም፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች “አርጁለኩም” የሚለውን በመቀበል በሰላት ሰዓት እግሮቻቸውን የሚያጥቡ ሲሆን የሺኣ ሙስሊሞች ደግሞ “አርጁሊኩም” የሚለውን አነባበብ በመቀበል በውሃ ያብሳሉ፡፡ ሁለቱም አንጃዎች ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ሌላው ወገን “ተሳስቷል” በማለት ይወነጅላሉ፡፡[60] ክርክሩ የጥንት ሲሆን እስከዚህ ዘመን ድረስ ቀጥሏል፡፡[61]

አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

“ቁርኣን በንባብ ስልቶቹ መለዋወጥ ብቻ ሁለት የተለያዩ ሕግጋትን በአንድ አንቀፅ ውስጥ በማዘል ራሱን ከማንዛዛት አድኗል፡፡” (ገፅ 70)

በፍፁም አላዳነም፡፡ ቁርኣን በዚህ ቦታ በሁለት መንገዶች መነበብ መቻሉ ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ትዕዛዛትን በመስጠት ሙስሊሞችን ለክፍፍልና ለንትርክ ዳርጓል፡፡ ሱኒና ሺኣን ከሚያከራክሩ የቁርኣን ጥቅሶች መካከል አንዱ ይኸኛው ነው፡፡

ሁለተኛው የሰጡት ምሳሌ ደግሞ የንስሐ ምዕራፍ 9፡128 ላይ የሚገኘውን ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-

“‹‹አንፉሲኩም›› የሚለውን ቃል ‹‹አንፈሲኩም›› በሚል ሌላ ስልት ነቢዩ አንብበውታል፡፡ በመጀመርያው ንባብ መሠረት ‹‹ነቢዩ ሙሐመድ ከመካከላችሁ የተነሳ፣ ለናንተ እንግዳ ያልሆነ፣ ማንነቱን የምታውቁት ነቢይ ነው›› የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡

በሁለተኛው ንባብ መሠረት ደግሞ ‹‹ከመካከላችሁ ስብእናው ወደር የማይገኝለት›› ይሆናል ትርጉሙ፡፡ ሁለቱም መልእክቶች ነቢዩ ሙሐመድን ገላጭ ሲሆኑ ቁርኣን ቃላት ሳያባክን በንባብ ስልት ለውጥ ብቻ አካቷቸዋል፡፡” (ገፅ 70)

አሁንም አቶ ሐሰን ለአንባቢያኖቻቸው የሰጡት መረጃ የተሳሳተ ነው፡፡ በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ እንደተዘገበው ከሆነ ኢብን አባስና ሌሎች አንባቢያን “ሚን አንፈሲኩም” በማለት የሚያነቡ ሲሆን የሚሰጡት ማስረጃ ደግሞ ነቢዩ ሙሐመድ፣ ልጃቸው ፋጢማና ሚስታቸው አይሻ በዚሁ መንገድ ማንበባቸውን ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ አንባቢያን ይህንን በሙሐመድና በቤተሰባቸው የታወቀውን ንባብ በመለወጥ “ሚን አንፉሲኩም” በማለት ያነቡታል፡፡ በአሁኖቹ የአረብኛ ቁርኣን ህትመቶች ውስጥ የሚገኘው በሙሐመድና በቤተሰባቸው የታወቀው ሳይሆን ይኸኛው ነው፡፡[62] ይህም ደግሞ ቁርኣን በሂደት መበረዙን አመላካች ነው፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው አቶ ሐሰን የቁርኣንን የተለያዩ “የንባብ ሥልቶች” ለማብራራት የጠቀሷቸው ሁለቱም ምሳሌዎች “ሰባቱ” ንባቦች “የንባብ ሥልቶች” ብቻ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ አይደሉም፡፡ እስላማዊ ትውፊቶችንና የቀደሙትን የቁርኣን የእጅ ጽሑፎች በጥልቀት ያጠናን እንደሆነ ብዙ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ቁርአኖች እንደነበሩና እነዚህ ቁርአኖች የሚፈጥሯቸውን ችግሮች ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን እናያለን፡፡ ይህም ሆኖ እስከዚህ ዘመን ድረስ የዘለቁ በህትመት ላይ ያሉ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ንባቦች ያሏቸው ቁርአኖች አሉ፡፡

ሙስሊሞች የንባብ ሥልቶች ብቻ እንደሆኑ የሚያምኗቸው የቁርኣን ልዩነቶች ሁለት መልክ አላቸው፡-

  • አህሩፍ

ሙሐመድ ቁርኣንን በሰባት መንገዶች (አህሩፍ) እንዲያነበንቡ እንደተፈቀደላቸው በትውፊቶች ውስጥ የተነገረ ቢሆንም የአህሩፍ ትርጉም በግልፅ አልተነገረም፡፡ ስለ አህሩፍ ምንነቶች በጥቂቱ ወደ 35 አመለካከቶች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ትክክለኛው የትኛው እንደሆነ ስምምነት የለም፡፡ ይህ በሙሐመድ ሞት ጊዜ አንድ እንከን የለሽ የቁርኣን ቅጂ ብቻ እንደነበር የሚናገረውን ሐሳብ ውድቅ ያደርጋል፡፡[63]

  • ቂርአት

ኢብን ሙጃሂድ በተባለው ሙስሊም ሊቅ የተጠቀሱት “ሰባቱ ቂርኣት” “ከሰባቱ አህሩፍ” ጋር ሊምታቱ እንደማይገባ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ኢብን ሙጃሂድ የለያቸው ሰባቱ ቅጂዎች ከሙሐመድ ሰባቱ የንባብ ስልቶች ጋር አንድ እንደሆኑ አልተናገረም፤ ሰባቱን ለመለየት የተጠቀማቸውን መመዘኛዎች የሚያሟሉ ሌሎች ሦስት ስለተገኙ ከሰባቱ ጋር እኩል በሆነ ሁኔታ በሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ በብዙ ቡድኖች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ተጨማሪ የንባብ ሥልቶችም ነበሩ፡፡ ችግሩን የሚያብሰው ደግሞ እነዚህ ሰባት፣ አሥርና ሌሎች ንባቦች የተመረጡት በወቅቱ ከነበሩ በጥቂቱ ሃምሳ ሊሆኑ ከሚችሉ ቅጂዎች መካከል ነበር፡፡ ይህ ቁጥር በዚህ ዘመን እንኳ በጽሑፍ ቅጂዎች እንደሚገኙ የሚነገርላቸውን የኢብን መስዑድ፣ ኡበይ ቢን ከዕብ እና የዐሊ ስብስቦችን አያጠቃልልም፡፡[64]

  • በትውፊቶች የተመዘገቡ በጥንታውያን ቁርአኖች ውስጥ የነበሩ ልዩነቶች

የሙሐመድ ባልደረቦችና ከነርሱ በኋላ የተነሱት ሙስሊም ትውልዶች የተለያዩ ቁርአኖች እንደነበሯቸው በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ከቃላት ልዩነት አንስቶ እስከ ምዕራፎች ልዩነት ድረስ ያሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ በጥንታዊ ቁርአኖች መካከል የነበሩት ልዩነቶች አቶ ሐሰንና መሰሎቻቸው አቅልለው ለማሳየት እንደሚሞክሩት አይደለም፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ሙስሊሞች ስለ መለኮታዊ መገለጥ ካላቸው አመለካከት አኳያ ከባድ ችግር የሚያስከትሉና ቁርኣን እውነተኛ የአምላክ ቃል እንዳልሆነ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

ከኡሥማን ቁርኣን ጋር ተፎካካሪ የነበሩ ወደ አሥራ ሁለት የሚሆኑ ቁርአኖች እንደነበሩ ታሪኩን ያጠኑ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ቁርአኖቹ በአነብናቢዎቻቸው ስም የተሰየሙ ሲሆን የሚከተሉት ናቸው፡-[65]

የኡሥማን ቁርኣን ተፎካካሪ የነበሩ ቁርአኖች
ሰሊም ኢብን መዕቃል ዐብደላህ ኢብን መስዑድ
አብደላህ ኢብን አባስ አይሻ ቢንት አቡበክር
ዑቅባ ኢብን አምር አሊ ኢብን አቡጧሊብ
አል-ሚቅዳድ ኢብን አል አስዋድ አብደላህ ኢብን አል ዙበይር
አቡ ሙሳ አል-አሽዓሪ አብደላህ ኢብን ዑመር
ኡበይ ኢብን ከዕብ ኡም ሰላማ

ከላይ የተጠቀሱት ቁርአኖች ከመጀመርያው ሙስሊም ትውልድ መካከል የነበሩ ሲሆኑ ተከታዮቹ ደግሞ ከሁለተኛው ሙስሊም ትውልድ መካከል ናቸው፡-[66]

በሁለተኛው ሙስሊም ትውልድ ዘመን የነበሩ ቁርአኖች
ዑባይድ ኢብን ዑመይር አል-ለይሢ ዐልቃማ ኢብን ቀይስ
ዐጠዓ ኢብን አቢ ረባህ ሙሐመድ ኢብን አቢ ሙሳ
ዐክራም ሐታን ኢብን አብደላህ አል-ረቃሺ
ሙጃሂድ ሳሊህ ኢብን ኪሳን
ሰዒድ ኢብን ጁበይር ጣልሀ ኢብን ሙሰሪፍ
አል-አስዋድ ኢብን ዘይድ

በቁርአኖቹ መካከል የሚገኙትን ልዩነቶች ለማስረዳት ያህል ከአንደኛው የሙስሊም ትውልድ ከነበሩት ቁርአኖች መካከል ሁለቱን እንደ ምሳሌ እንጠቅሳለን፡-

  • የኡበይ ቢን ከዕብ ቁርኣን

ኡበይ ቢን ከዕብ ከአራቱ አነብናቢዎች መካከል አንዱ ሲሆን የመጀመርያው አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ነበር፡፡[67] የራሱን ቁርኣን ያዘጋጀ ሲሆን በሁለት መንገዶች ከኡሥማን ቁርኣን ይለያል፡፡ የመጀመርያው የሱራዎቹ አቀማመጥ ነው፡፡ ሁለተኛውና ይበልጥ ጉልህ የሆነው ልዩነት ደግሞ ሱረት አል-ኸልዕ (የመለያየት ምዕራፍ) እና ሱረት አል-ሐፍድ (የችኮላ ምዕራፍ) የተሰኙ ተጨማሪ ምዕራፎችን በውስጡ የያዘ መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ምዕራፎች ኖልዴክና ሐመር በተሰኙ ሊቃውንት ታትመው ለዓለም ሕዝብ ይፋ ሆነዋል፡፡[68]

  • የአብደላህ ኢብን መስዑድ ቁርኣን

አብደላህ ኢብን መስዑድ በሙሐመድ ከተመረጡት አራቱ አነብናቢዎች መካከል አንዱ እንደነበር ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡ ሱራ 1፣ ሱራ 113 እና ሱራ 114 ጸሎቶች እንጂ የቁርኣን ጥራዝ አካል እንዳልሆኑ ያምን ስለነበር ከራሱ ቁርኣን ውስጥ አስወግዷቸው ነበር፡፡ ሱራ 3፡19 እንዲሁም አንቀፅ 39 ላይ አሁን ካለው ቁርኣን የተለየ ንባብ ይከተል ነበር፡፡[69] ኢብን መስዑድ የዘይድን ቁርኣን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል፡፡[70]

  • የሺኣ ሙስሊሞች ተቃውሞ

በኡሥማን ዘመን ቁርኣን አንድ ወጥ መልክ እንዲኖረው ጥረት ከተደረገ በኋላ በማስከተል በነበሩት አሥርተ ዓመታት በመሪዎች ምርጫ፣ በትክክለኛ ሃይማኖታዊ ሥርኣቶችና በቁርኣን ዙርያ በሙስሊሞች መካከል ብዙ አለመግባባትና ጠብ ተከስቶ ነበር፡፡ በሺኣዎች አመለካከት መሠረት ዐሊ የሙሐመድ የመጀመርያው ተተኪ መሆን ነበረበት፡፡ የጥንቶቹ ሺኣዎች የእርሱ የቁርኣን ቅጂ ትክክለኛው እንደነበረና ሌሎች ቁርአኖች የተበረዙ እንደሆኑ ያምኑ ነበር፡፡ አል-ባቂላኒ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ተከታዩን ጽፈዋል፡-

አንዳንድ ሺኣዎች እንዲህ ብለው ነበር፡- “የሙስሊሙ ማሕበረሰብ (ኡማ) በቁርኣን አስተላለፍ ላይ እጅግ የከፋ ልዩነት ውስጥ ገብቶ አገኘነው፡፡ ከልዩነታቸው ጥልቀት የተነሳ ትክክለኛነቱን ከብርዘቱ፤ ጉድለቱን ከጭማሬው [የተቀነሰውንና የተጨመረውን] መለየት ተስኖናል፡፡ በዚህ መገለጥ ውስጥ የሁሉንም ቅደም ተከተል ማወቅ ቸግሮናል፡፡ ከፊትም ሆነ ከኋላ የመጣውን ማወቅ አልቻልንም፡፡” ከሕዝቦቻቸው መካከል የተወሰኑቱ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ለእርሱና ለሕዝቡ ዕውቀት ከተሰጠው ከኢማሙ በስተቀር ከውስጡ የጎደለውን የሚያውቅ የለም፡፡” የሆነ ነገር በእርሱ ላይ መጨመሩን የሚያስተባብሉና የተወሰነ ክፍሉ መጥፋቱን የሚናገሩት ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡- “የዝግጅትና የቅንብሩን፤ አብዛኛውን በምዕራፍ የመከፋፈሉን እንዲሁም የኋላውን ወደፊት የፊቱን ደግሞ ወደ ኋላ የመውሰድ ኃላፊነቱን ወስደው የነበሩት አቡበክርና ተከታዮቹ ነበሩ፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙ አናቅፅ ካለቦታቸው ገብተዋል፤ ከተገቢ ቦታዎቻቸውም ተወግደዋል፡፡”[71]

ጥንታውያን ሺኣዎች አቡበክርና ኡሥማንን ቁርኣንን በርዘዋል በማለት ይከሷቸዋል፡፡ ዐሊና ቤተሰቡን የተመለከቱ ክፍሎችን እንደሰረዟቸው፤ ሙሐጂሩንና አል አንሷር መጥፎ ሥነ ምግባር ማሳየታቸውን በቀጥታ የሚናገሩትን እንዳስወገዷቸው ይናገራሉ፡፡[72] በአሥራኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ የሺኣ ጽሑፎች ወደ አምስት መቶ የሚሆኑ የቁርኣን ጥቅሶች መበረዛቸውን ይናገራሉ፡፡[73]

ትንኝን የሚያጠሩ ግመልን የሚውጡ

አቶ ሐሰን “ነጭ ውሸት” በሚል ርዕስ ስር ሐመረ ተዋህዶ ተከታዩን መረጃ እንዳሠፈረ ጽፈዋል፡-

“…መስዑድ ሰባ ሱራዎችን በቃሉ አጥንቶ በነበረበት ጊዜ እንኳ ዘይድ ገና ያልተወለደና ከመስዑድም ሆነ ከከዕብ አንፃር በዕድሜው ልጅ ስለነበር የእርሱ ስብስብ መመረጡ መስዑድና ከዕብን አስቆጥቷቸዋል፡፡” (ገፅ 71)

ይህንን አባባል እንዲህ በማለት ያጣጥሉታል፡-

ይህቺ እንግዲህ ‹‹ነጭ ውሸት›› የምትባል ናት፡፡ ሐመሮች ይህችን ስለሚያውቁ ምንጭ ከመጥቀስ ታቅበዋል፡፡ በእርግጥ የሚጽፉት ‹‹በበረታቸው ውስጥ›› በሞኝነት ለሚቀበላቸው ‹‹የዋህ አማኝ›› በመሆኑ መረጃ ፍለጋ ስለምን ራሳቸውን ያድክሙ! (ገፅ 71)

አቶ ሐሰን በዚህ የቅጥፈት ፊኛ ውስጥ የነፉት አየር ከልክ በላይ በመሆኑ የሚያስከትለው የፍንዳታ ድምፅ በዚያው መጠን እጅግ ከፍ ይልባቸዋል፡፡ ተከተሉኝማ፡፡

ኡበይ ቢን ከዕብም ሆነ አብደላህ ኢብን መስዑድ ዘይድ ካዘጋጀው ቁርኣን ጋር የማይስማሙ የየራሳቸውን ቁርአኖች አዘጋጅተው እንደነበር ቀደም ሲል በማስረጃዎች አስደግፈን ተመልክተናል፡፡ ይህ የዘይድን ቁርኣን አለመቀበላቸውን ለማሳየት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ መስዑድ የዘይድ ስብስብ በመመረጡ ምክንያት ተቃውሞውን እንዲህ በማለት ገልፆ እንደነበር ኢብን አቢ ዳውድ ዘግቧል፡-

“ዘይድ ኢብን ሣቢት እስልምናን ከመቀበሉ በፊት ሰባ ሱራዎችን ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በትክክል ተምሬ ነበር፡፡”[74]

“ዘይድ ገና ህፃን በነበረ ጊዜ ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሰባ ሱራዎችን በቀጥታ ተምሬ ነበር፡፡ ከአላህ መልእክተኛ በቀጥታ ያገኘሁትን መተው አለብኝን?”[75]

“ሙስሊሞች ሆይ! ቁርኣንን እንዳልጽፍ እኔን በማግለል እስልምናን ስቀበል [ገና ሳይወለድ] በአባቱ አካል ውስጥ በካፊርነት ለነበረው ሰው [ለዘይድ] ኃላፊነት ተሰጠ፡፡”[76]

እንደ ኢብን ሰዓድ ዘገባ ኡሥማን ሌሎች የቁርኣን ቅጂዎች እንዲወድሙና የዘይድ ቁርኣን ብቻ ኦፊሴላዊ እንዲሆን ትዕዛዝ በሰጠበት ወቅት ኢብን መስዑድ በኩፋ ውስጥ ተከታዩን ኹጥባ (ስብከት) ማድረጉ ተነግሯል፡-

“ሰዎች በቁርኣን ንባባቸው የማጭበርበርን ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ እኔ ግን ከዘይድ ኢብን ሣቢት በላይ በምወደው (በነቢዩ) ንባብ መሠረት ማንበብን እመርጣለሁ፡፡ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ በሌለው እምላለሁ! ዘይድ ኢብን ሣቢት ሁለት ጋሜ የነበረው ህፃን ሆኖ በህፃናት መካከል ይጫወት በነበረበት ዘመን ከአላህ መልእክተኛ (የአላህ በረከት በእርሱ ላይ ይሁንና) ከሰባ በላይ ሱራዎችን ተምሬ ነበር፡፡”[77]

አት-ትርሚዚ ሐዲስ ውስጥ ደግሞ ተከታዩ ዘገባ ሰፍሯል፡-

“አዝ-ዙህሪ እንዳስተላለፈው፤ ኡበይ ቢን አብዱላህ ቢን ኡጥባህ እንደነገረኝ አብደላህ ቢን መስዑድ ዘይድ ቢን ሣቢት ሙሳሒፉን በመጻፉ ደስተኛ ስላልነበረ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹እናንተ የሙስሊም ሕዝቦች ሆይ! የዚህን ሰው ሙሳሒፍ እና የእርሱን ንባብ ከናንተ አስወግዱ፡፡ በአላህ እምላለሁ! እኔ እስልምናን ስቀበል በከሃዲ ሰው እርግብግቢት ውስጥ ነበር፡፡› አብደላህ ኢብን መስዑድ አክሎም እንዲህ አለ፡- ‹እናንተ የኢራቅ ሕዝቦች ሆይ! ከናንተ ጋር ያሉትን ሙሳሒፎች ያዟቸው፤ ደግሞም ደብቋቸው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ‘የሆነ ነገር የሚሰውር ሰው በዕለተ ትንሣኤ የሰወረውን ነገር ይዞ አላህን ይገናኘዋል፡፡’ ስለዚህ አላህን ሙሳሒፉን ይዛችሁ ተገናኙት፡፡› አዝ-ዙህሪ እንደተናገረው ‹ከተከበሩ የአላህ መልእክተኛ ባልደረቦች መካከል አንዳንዶቹ ይህንን የኢብን መስዑድ አመለካከት አልወደዱትም ነበር፡፡›”[78]

[ጃሚ አት-ትርሚዚ የሐዲስ ስብስብ ውስጥ ይህ ሐዲስ “ሳሂህ” ወይም ‹የታመነ› መሆኑ ተገልጿል!]

ከላይ ከተመለከትናቸው ዘገባዎች አንፃር የሐመረ ተዋህዶ ጽሑፍ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ሐሰን ታጁ ዘጋባውን “ነጭ ውሸት” ማለታቸው በራሱ “ነጭ ውሸት” መሆኑ ባቀረብናቸው ማስረጃዎች ተረጋግጧል፡፡

ኡስታዙ በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ በግልፅ የሠፈረ ሌላም ታሪክ ክደዋል፡፡ ሐመሮች እንዲህ ብለው መጻፋቸውን ይጠቅሳሉ፡-

“የሐፍሷ ቅጅ እንኳ ማርቫን[79] በተባለ የመዲና ገዥ ተቃጥሏል፡፡” (ገፅ 74)

አቶ ሐሰን እንዲህ በማለት “መልስ” ሰጥተዋል፡-

“በእርግጥ ይህ ቅጥፈት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ማርቫን የሚባል የመዲና ገዥ በታሪክ አይታወቅም፡፡ የሐፍሷ ቅጅም አልተቃጠለም፡፡” (ገፅ 74)

“ውሸታም!” እንዳንላቸው ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ በአቡ በክር ትዕዛዝ በዘይድ ተዘጋጅቶ የነበረው ቁርኣን ሐፍሷ ቢንት ዑመር በተሰኘችው የሙሐመድ ሚስት እጅ ነበር፡፡ ኡሥማን በዘይድ አማካይነት እንዲዘጋጅ ላደረገው ቁርኣን መነሻ ያደረገው የሐፍሷን ቁርኣን ሲሆን ሌሎች ቅጂዎችን የእሳት ሲሳይ ቢያደርግም ይኸኛውን ግን ሳያቃጥል መልሶላት ነበር፡፡ ይህ ቅጂ ማርዋን ኢብን አል-ሐካም የተሰኘ ሰው የመዲና ገዢ እስከሆነበት ዘመን ድረስ በእጇ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሷ ሞት በኋላ ማርዋን የሐፍሷ ወንድም የነበረው አብደላህ ኢብን ዑመር ቅጂውን እንዲልክለት ጠየቀው፤ እርሱም ላከለት፡፡ እስላማዊ ድርሳናት ውስጥ በግልፅ እንደሠፈረው ማርዋን “ከኡሥማን ቁርኣን የተለየ ነገር በውስጡ ይኖር ይሆናል በሚል ፍርሃት አቃጠለው፡፡”[80] አቶ ሐሰን ግን ይህንን አገር ያወቀውንና ፀሐይ የሞቀውን ታሪክ ክደዋል፡፡ ሳያውቁ ቀርተው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ይህንን ታሪክ “ለየዋህ” ተከታዮቻቸው ማሳወቅ የቁርኣንን ተዓማኒነት መቀመቅ እንደሚያወርደው ስለገባቸው የተሻለ ምርጫ አልታያቸውም፡፡

ሌላው በአቶ ሐሰን ሙግት ውስጥ የሚታየው ትልቅ ችግር ጥቃቅን ስህተቶችን እጅግ አጋኖ በማሳየት ትክክለኛውን ጥያቄ ትኩረት መንፈግ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል “የጠፉ የቁርኣን አንቀፆች” በሚለው ርዕስ ስር ሱራ 33፡23 ጠፍቶ መገኘቱን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡-

የሐመሮችን ቅጥፈት እንመልከት፡- ‹‹እንደ ሰሂሪ ቡኻሪ፣ የዘይድ መጽሐፍ ተቀድቶ ወደ ሰባቱም የተለያዩ ከተሞች የተላከ ቢሆንም፣ ዘይድ ሙሐመድ ያለው ቃል ከእርሱ መጽሐፍ ውስጥ ያልተጨመረ መሆኑን በድንገት አስታወሰ፡፡ ያልጨመረው አንቀጽ የሱራ 33 ቁጥር 23 አንቀጽ ነው፡፡ ከዚያም ይህንን ቃል ከኢብን አል አስዓሪ እስኪያገኘው ድረስ ጠብቆ ፈለገው ይላል፡፡›› (ገፅ 72)

አቶ ሐሰን ይህንን ብቻ ከጠቀሱ በኋላ ሐመሮች ያቀረቡትን ዋና ሙግት ቆርጦ በመጣል ሙግቱን ሊለውጡ በማይችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ሐመሮች በዚህ አላቆሙም፡፡ በማስከተል እንዲህ ብለው ተሟግተዋል፡-

የቁርኣን ብቸኛና ትክክለኛ ቅጂ ተብለው ከተሰራጩ በኋላ እንኳ ዛይድ የተረሳ ቃል ከአንድ ሰው እንዳገኘ እናያለን፡፡ ይህም በስብስቡ ሂደት ከአንድ ሰው ብቻ እንደተገኘው ቃል ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህ የተላኩት ሰባቱ ቅጂዎች ሙሉና ፍጹም አልነበሩም ማለት ነው፡፡ የበለጠ የሚያሳስበው ደግሞ የቁርኣን ስብስብ የተመሠረተው በአንድ ሰው የመሰብሰብና የማስታወስ ችሎታ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ቁርኣንን በሙሉ በቃሉ የያዘ ሰው ያልነበረ የመሆኑ ነገር ግልፅ ነው፡፡ ሌሎች የተረሱ ወይም የተዘለሉ አንቀፆች ላለመኖራቸው ምን ማረጋገጫ አለ?[81]

የመደምደሚያውን ጥያቄ አቶ ሐሰን አልመለሱትም፤ መቼም ቢሆን መመለስ አይችሉም፡፡ ዳሩ ግን ይህንን ዋና ነጥብ ችላ በማለት ምን ላይ እንዳተኮሩ እንመልከት፡፡ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

  • ‹‹የዘይድ መጽሐፍ ቅጆች ወደ ሰባቱም ግዛቶች ከተሰራጨ በኋላ›› ማለታቸው ቅጥፈት ነው፡፡ ከቡኻሪ ዘገባ ላይ ቅጥፈት አክለዋል፡፡ ገና በመሰብሰብ ላይ እያለ የሆነውን አዛብተው አቅርበዋል፡፡ (ገፅ 72)

ቁርኣን ከመሰብሰቡ በፊትም ሆነ ተሰብስቦ ከተሰራጨ በኋላ አንቀፁ መገኘቱ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ የሐመሮች ዋና ሙግት በአንድ ሰው ምስክርነትና የማስታወስ ችሎታ ላይ ተመሥርተው በቁርኣን ውስጥ እንዲካተቱ የተደረጉ አናቅፅ አሉ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የተረሱ አናቅፅ ላለመኖራቸው ምን ዋስትና አለ? የሚለው ጥያቄ ከዚህ አንፃር መመለስ ይኖርበታል፡፡ አቶ ሐሰን ይህንን ጥያቄ መመለስ ስላልቻሉ በዘዴ አልፈውታል፡፡

ዳሩ ግን የሐዲሱን አውድ ያነበብን እንደሆነ ሐመሮች ትክክል መሆናቸውንና ኡስታዙ ቅጥፈት መፈፀማቸውን ማየት እንችላለን፡፡ ሐዲሱ የቁርኣንን አሰባሰብ ሙሉ ታሪክ ጨምቆ ካቀረበ በኋላ በተለያዩ ቁሶች ላይ የተጻፉ የቁርኣን ክፍሎች እንዲቃጠሉ ተደርጎ በዘይድ የተዘጋጀው ቁርኣን ኮፒዎች ወደ ተለያዩ ግዛቶች እንደተላኩ ይተርካል፡፡ በመቀጠልም ዘይድ የሱራ አል አሕዛብ 23ኛ አንቀፅ መዘለሉን በማስታወስ ፍለጋ አድርጎ ኹዘይማ ዘንድ እንዳገኘውና እንዲጻፍ እንዳደረገው በመግለፅ ይደመድማል፡፡ አንባቢያን የሐዲሱን አውድ ማየት ይችሉ ዘንድ በሙስሊም ሊቃውንት ወደ እንግሊዘኛ የተተረጎመውን ክፍል እነሆ፡-

…when they had written many copies, Uthman returned the original manuscripts to Hafsa. Uthman sent to every Muslim province one copy of what they had copied, and ordered that all the Qur’anic materials whether written in fragmentary manuscripts or whole copies, be burnt. Said bin Thabit added, “A verse from Surat Ahzab was missed by me when we copied the Qur’an and I used to hear Allah’s Apostle reciting it. So we searched for it and found it with Khuzaima-bin-Thabit al Ansari.”[82]

ይህ ሐዲስ እንደሚያስረዳው ዘይድ አንቀፁ አለመካተቱን ያስተዋለው ቁርኣን ከተሰራጨ በኋላ ነበር፡፡

አቶ ሐሰንን ሊያሳስባቸው የሚገባው ሌላ ጉዳይ ቢኖር ይህ አንቀፅ በኸሊፋ አቡበክር ዘመን ተሰብስቦ በሐፍሷ ዘንድ በተቀመጠው ጥራዝ ውስጥ ያልነበረ መሆኑ ነው፡፡ በዚሁ መጽሐፋቸው ገፅ 24 ላይ ኡሥማን ያደራጀው ኮሚቴ “ፎቶኮፒ ሊባል በሚችል መንገድ” ሌሎች ኮፒዎችን ከዚህ ቁርኣን ላይ እንዳዘጋጀ ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን ዘይድ ይህንን አንቀፅ ለማግኘት ፍለጋ ማድረጉ በአቡበክር ዘመን ተዘጋጅቶ የነበረው ቁርኣን የተሟላ እንዳልነበረና የኡሥማን ቁርኣን የተለየ መሆኑን በማመልከት ይህንን የተለመደ የሙስሊሞች እምነት ውድቅ ያደርጋል፡፡ በአቡበክር ዘመን በተጻፈው የሐፍሷ ቅጂ ውስጥ ይህ ጥቅስ ቢኖር ኖሮ ባልተዘለለም ነበር፤ እንደ አዲስ ፍለጋ ማድረግም ባላስፈለገ ነበር፡፡ አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

  • ‹‹በድንገት አስታውሶ›› የሚል ቃልም አክለዋል፡፡ ይህም ሌላ ቅጥፈት ነው፡፡ ዘይድ በድንገት አይደለም ያስታወሰው፡፡ አንቀጹን እርሱም ሆነ ሌሎች ሶሐቦች ያውቁታል፡፡ ‹‹በድንገት›› ማስታወስ አያስፈልገውም፡፡ (ገፅ 73)

የጠፋውን አንቀፅ ማፈላለግ የተጀመረው ቁርኣንን የማረምና መልክ የማስያዝ ሥራው ተጠናቆ በተለያዩ ኮፒዎች ተዘጋጅቶ ዋና ዋና ወደሚባሉት የእስላም ግዛቶች ከተላከ በኋላ እንደነበር ሐዲሱ ያስረዳል፡፡ በወቅቱ በትውስታቸው ውስጥ ከነበረ ስለምን ተዘለለ? አቶ ሐሰን አንቀፁን ከዘይድ ውጪ ሌሎች የኮሚቴው አባላት ስለማወቃቸው ምን ማስረጃ አላቸው? ዘይድ ስለ ራሱ እንጂ ስለ ሌሎች ሶሃቦች መናገሩ አልተጻፈ፡፡ በማስከተል እንዲህ ብለዋል፡-

  • ሐመሮች ከእንግሊዘኛ ያገኙትን ጽሑፍ ከነቡግሩ ስለተረጎሙ ሶሂህ ቡኻሪን ሰሂሪ ቡኻሪ፣ ኢብን ኹዘይማን ኢብን አል አስክሪ እያሉ የስም እና የሐሳብ ግድፈት መፈጸም ባህሪያቸው ነው፡፡ (ገፅ 73)

አቶ ሐሰን ሰዎች ያላሉትን እንዳሉ በማስመሰል ማቅረብ ባሕርያቸው ነው፡፡ እኔ ባደረኩት የአርትዖት ንባብ ሐመሮች ሳሂህ (ሶሂህ) አል-ቡኻሪን “ሰሂሪ ቡኻሪ” ብለው በስህተት የጻፉት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን[83] አቶ ሐሰን ቃሉ የተጠቀሰባቸውን ቦታዎች ባገኙ ቁጥር ስህተቱን የደጋገሙ ለማስመሰል ተስተካክሎ የተጻፈውን በመተው በፊደል ግድፈት ምክንያት የተፈጠረውን የመጀመርያውን ስህተት በመተካት ጽፈዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ተግባር እንግሊዘኛው “Silly” ይለዋል፡፡ አይረቤ እንደማለት ነው!

ሐመሮች አቶ ሐሰን እንዳሉት “ኢብን አል አስዓሪ”ም ሆነ “ኢብን አል አስክሪ” ብለው አልጻፉም፤ ነገር ግን “ኢብን አስናሪ” ብለው ነው የጻፉት፡፡[84] የኹዘይማ ኢብን ሣቢት አል-አንሳሪ የመጨረሻ ስም መሆኑ ነው፡፡ አጻጻፉ ግድፈት ቢኖርበትም ቅን አስተሳሰብ ያለው ሁሉ ማንን ለመጥቀስ እንደፈለጉ ይረዳል፡፡ የመጽሔቱ አዘጋጆች በቁርኣን ላይ ጽሑፎችን ሲጽፉ የመጀመርያቸው በመሆኑ አንዳንድ የአረብኛ ቃላትን አስተካክለው አለመጻፋቸው አያስገርምም፡፡ አቶ ሐሰን ግን የፊደል ግድፈቶችን በመለቃቀም ዋና ሙግቶችን ችላ ብለው ጉዳዩን እርባና ቢስ ወደሆነ ክርክር ለውጠውታል፡፡ እንዲህ ማድረጋቸው ለቀረበው ትክክለኛ ሙግት መልስ ማጣታቸውን ያመለክታል፡፡ ይህንን ክፍል “ትንኝን የሚያጠሩ ግመልን የሚውጡ” የሚል ርዕስ የሰጠነው በዚሁ ምክንያት ነው! (ማቴዎስ 23፡24 ይመልከቱ፡፡)

የሚገርመው ነገር አቶ ሐሰን ራሳቸው ክርስቲያናዊ ቃላትን ሲጠቅሱ ለቁጥር የሚያታክቱ ግድፈቶችን መፈጸማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹ኖስቲክ› የሚለውን ‹ግኖስቲክ› ብለው ጽፈዋል (ገፅ 103)፡፡ Gnostic የመጀመርያዋ ፊደል ድምፅ አልባ ናት፡፡ (ሐመሮችም ሲጽፏት ተመሳሳይ ስህተት ፈፅመዋል)፡፡ አቶ ሐሰን ይባስ ብለው ‹ኮዴክስ ሲናይቲከስ› የሚለውን ‹የሲያትል ጽሑፍ› ብለውታል (ገፅ 43)፡፡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞችን በትክክል አልጻፉም፡፡ ኢየሱስን ‹እየሱስ›፣ ማቴዎስን ‹ማቲዮስ›፣ ጢሞቴዎስን ‹ጢሞቲዮስ›፣ ቆሮንቶስን ‹ቆረንጦስ›፣ ዮሐንስን በብዙ ቦታ ‹ዩሐንስ› ብለው ጽፈዋል፡፡ እኛ ግን እሳቸው እንዳደረጉት እንዲህ ያሉ ግድፈቶችን እየለቃቀምን ልንተቻቸው አንሻም፡፡ የአስተሳሰብ ደረጃችን ከዚህ ከፍ ያለ መሆኑን ስለምናምን እንዲህ ያሉ ተራ ሙግቶችን አንጠቀምም፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በቅንፍ (ገፅ __) ተብሎ የተጠቀሰው ሁሉ “የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት” በሚል ርዕስ በኡስታዝ ሐሰን ታጁ የተጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡

[2] ዶ/ር ኤቫንስ “Bible Memorization Techniques” በሚል ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስን በቃል እንዴት ማጥናት እንደሚቻል የሚያስተምር መጽሐፍ የጻፉ ሲሆን ይህንን መጽሐፍ ማንበብ የሚፈልግ ሰው www.memorizethebible.com ድረ ገፅ ላይ ማግኘት ይችላል፡፡

[3] Sahih al-Bukhari, Vol. 6, Bk. 61, No. 550

[4] Sahih al-Bukhari, Vol. 6, Bk. 61, No. 552

[5] Sahih al-Bukhari. Vol. 1, No. 91, 92; Vol. 2. No. 555; Vol. 3, No. 591

[6] Sahih al-Bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 556; also Sahih Muslim: bk. 4, no. 1720

[7] Sunan Abu Dawud: bk. 2, no. 1015; also Sahih al-Bukhari: vol. 1, bk. 8, no. 394

[8] `Abdul Rahman al Tha`alibi, “al Jawahir al Hisan fi tafsir al Qur’an”, 2 vols., Algiers, 1905, vol. 1, p. 95; Cited in: John Burton, Collection of the Qur’an, 1977, pp. 65-66

[9] Sahih Muslim 5:2286; Jalal al Din `Abdul Rahman b. abi Bakr al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; Halabi, Cairo, 1935/1354, part 2, p. 25

[10] (Qur’an 4.95) (Sahih al-Bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 512; also Sahih Muslim: bk. 20, no. 4676-4677)

[11] Al-Wahidi Al-Naysaboori. Asbaab Al-Nuzool; p. 126 Beirut’s Cultural Libary Edition “Tub’at Al-Maktabah Al-thakafiyyah Beirut”

http://www.answering-islam.net/Quran/Sources/sarh.html

[12] Sahih al-Bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 514

[13] Sahih al-Bukhari: vol. 4, bk. 56, no. 682

[14] https://islamqa.info/en/5142 (በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው በዓለም ዙርያ በሚገኙ ታላላቅ ሙስሊም ሊቃውንት የሚተዳደር የፈተዋ (የእስላማዊ ድንጋጌ) ድረ-ገፅ ነው፡፡)

[15] The Qur’an Dilemma; Former Muslims Analyze Islams Holiest Book. 2001, Vol. 1, pp. 49-50

[16] Sahih Bukhari 6.510

[17] Al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; p. 378; Cited in: The Qur’an Dilemma; Former Muslims Analyze Islams Holiest Book. 2001, Vol. 1, p. 49

[18] The Qur’an Dilemma. Vol. 1, p. 51

[19] Ibn Abi Dawud, Kitab al-Masahif, p. 5

[20] Al Suyuti. Al-Itqan; p. 135

[21] Sahih al-Bukhari, Volume 6, Book 61, Number 521

[22] Sahih Muslim, 17:4194

[23] Al Suyuti. Al Itqan;  p. 385;፤ Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 52

[24] Sahih Muslim, book 8, no. 3421

[25] Sunan Ibn Majah; 3፡9፡1944

[26] Al Suyuti. Al- Itqan fi `ulum al Qur’an; part 2, p. 25; Cited in Ibn Warraq. Which Koran?: Variants, Manuscripts, Linguistics; Prometheus Books, 2011, p. 24

[27] Al Suyuti. A- Itqan fi `ulum al Qur’an; part 2, p. 25; Cited in: Ibn Warraq. Which Koran?; p. 24

[28] The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 52

[29] ሐፍሷ የሁለተኛው ኸሊፋ የዑመር ኢብን አል-ኸጧብ ልጅ ስትሆን ከነቢዩ ሙሐመድ ሚስቶች መካከል አንዷ ነበረች፡፡

[30] Sahih al-Bukhari, vol. 6, bk 61, no. 510

[31] Sahih al-Bukhari, Vol. 6, Bk 61, no. 521

[32] Ibid.

[33] Ibn Abi Dawud al-Sijistani. p. 24-25; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[34]  Ibn Sa’d’s Kitab al-Tabaqat al-Kabir, English translation by S. Moinul Haq, M.A., PH.D assisted by H.K. Ghazanfar M.A. [Kitab Bhavan Exporters & Importers, 1784 Kalan Mahal, Daryaganj, New Delhi- 110 002 India], Volume 2, p. 444

[35] Nöldoke, Tarikh al-Qur’ān 280, 339; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[36] Encyclopedia of the Qur’ān Vol. 1, p. 348; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[37] Ibn Warraq. The Origins of the Koran: Classic Essays on Islam’s Holy Book; Prometheus Books, Amherst NY, 1998, p. 102

[38] The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 59

[39] http://www.qurantext.net

www.answering-islam.net/PQ/A1.htm#AppendA

[40] ሌሎች ሐዲሳት ፊየል ይላሉ፡፡

[41] Sunan Ibn Majah; 3፡9፡1944

[42] ሱናን ኢብን ማጃህ በጥራዝ መልክ ማግኘት የማይችል ሰው ወደ ተከታዩ ድረ-ገፅ በመሄድ ማረጋገጥ ይችላል፡- http://www.sunnah.com/ibnmajah/9

[43] Sahih Muslim, 8: 3421; 17: 4194

[44] Al Suyuti. Al Itqan;  p. 385;፤ Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 52

[45] http://www.theatlantic.com/issues/99jan/koran.htm

  http://answeringislam.net/Quran/Text/atlantic_mr.html

[46] http://www.nytimes.com/2004/11/03/world/europe/dutch-filmmaker-an-islam-critic-is-killed.html

[47] Keith Small. Holy Books Have History: Textual History of the New Testamente and the Qur’an; 2010, p. 1

[48] Ibn Warraq. Which Koran?: Variants, Manuscripts, Linguistics; Prometheus Books, 2011, p. 34

[49] Sahih al-Bukhari, Vol. 6, bk 60, no. 201)

[50] Ibn abi Da’ud. Kitab al Masahif, p. 23; Cited in Ibn Warraq. Which Koran?; p.24

[51] Al Suyuti. A- Itqan fi `ulum al Qur’an; part 2, p. 25; Cited in Ibn Warraq. Which Koran?; p.24

[52] Sahih al-Bukhari, Vol. 6, bk 60, no. 201

[53] Ahmad b. `Ali b. Muhammad al `Asqalani, ibn Hajar, Fath al Bari, 13 volumes, Cairo, 1939/1348, vol. 9, p. 9; Cited in: John Burton, Collection of the Qur’an, 1977, p. 119

[54] አል ቡኻሪ የሚከተለውን ዘግቧል “አነስ ኢብን ማሊክ እንዳስተላለፈው ‹‹በቢር ማዑና የሞቱትን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ የሚል አያት እንቀራ ነበር፡- ‹ለሕዝባችን ጌታችንን እንዳገኘነውና በኛ ደስ መሰኘቱን እኛንም ማስደሰቱን ንገሩልን፡፡› ነገር ግን ይህ አያ ከቁርኣን ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል››፡፡” Sahih Bukhari, vol. 5, p. 288

[55] Jami‘ At-Tirmidhi, Volume 5, Chapter 2. Regarding Surat Al-Baqarah, pp. 302-303

[56] Arthur Jeffery. Al-Masahif. By Abubakr ‘Abd Allah Ibin Abi Dawud Ibin al-Asha’ath al-Sijistani. Damascus: Dar al-Takwin, 2004, p. 7-8; Cited in: The Qur’an Dilemma, Vol. 1, p. 56

[57] Abu Dawud al-Sijistani. P. 41; Cited in: The Qur’an Dilemma, Vol. 1, p. 56

[58] Ibid., p. 42

[59] Abu Abdallah Muhammad Ibn Ahmad al-Qurtubi. Al-Jami’ li-Ahkam al-Qur’an wa-Mubayin li-ma Tadammanahu min al-Sunna wa Aay al-Furqān. Ed. ‘Abd Allah Ibn ‘Abd al-Muhsin al-Turki. Vol. 14, 2006, p. 90; Cited in:  The Qur’an Dilemma, Vol. 1, p. 56

[60] ‘Abd al-Latif al-Khatib. Mu’jam al-Qir’āt; Damascus; Dār Sa’d al-Din, AH 1422/ 2002, Vol. 3, p. 482; Cited in: The Qur’an Dilemma; pp. 373-374

[61] http://quransmessage.com/articles/washing-wiping%20FM3.htm የጥቅሱን ትክክለኛ ንባብ በተመለከተ በሱኒና በሺኣ ሙስሊሞች መካከል ያለውን ንትርክ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ የሚያቀርብ ድረ-ገፅ ነው፡፡

[62] al-Khatib. Mu’jam al-Qir’āt; Cited in: The Qur’an Dilemma; p. 534-535

[63] Keith Small. Holy Books Have History; p. 103

[64] Ibid., 104

[65] Abū Mūsā al-Harīrī. ‘Ālam al-Mu’jizāt. Beirut: Dār li-Ajl al-Ma’rif, 1982, pp. 164-166; Cited in: Qur’an the Dilemma, pp. 56-67

[66] Al-Sijistani, pp. 98-102; Cited in: Qur’an the Dilemma, p. 57

[67] Muhammad Hassan Jabal. Wathāqat Naql al-Nass al-Qur’āni. Tanta: Dar al-Sahāba li-l-Turāth, 2001, p. 176; Cited in: The Qur’an Dilemma, p. 57

[68] Theodore Nöldeke. Tarikh al-Qur’ān. Trans. Genetes Tāmir. Beirut: Konrad-Adenauer-Stiftung, 2004, 266-267; Cited in: The Qur’an Dilemma, p. 57; As-Suyuti, Al-Itqan, p.152-153

[69] Abu Bakr `Abdullah b. abi Da’ud, “Kitab al Masahif”, ed. A. Jeffery, Cairo, 1936/1355, p. 17

[70] Ibn Sa’ad. Kitab al tabaqat al kabir; vol. 2, p. 444

[71] Abū Bakr Ibn Al Tayyīb al-Bāqilānī. Al-Intisār li-l-Qur’ān. Ed. Muhammad ‘Isām al-qudāt. Beirut: Dār Ibn Hazm, 2001, p. 71; Cited in: The Qur’an Dilemma, p. 58

[72] Nöldeke, Tarikh al-Qur’an pp. 322-323; Cited in: The Qur’an Dilemma, p. 58

[73] Ibid., p. 324; The Qur’an Dilemma, p. 58

[74] Ibn Abi Dawud. Kitab al-Masahif, p.17; Cited in: John Gilchrist. Jam’ Al-Qur’an – The Codification of the Qur’an Text A Comprehensive Study of the Original Collection of the Qur’an Text and the Early Surviving Qur’an Manuscripts; Republic of South Africa, 1989, p. 66

[75] Ibn Abi Dawud. p.15; Cited in: Ibid.

[76] Ibn Abi Dawud. p. 24-25; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[77] Ibn Sa’d. Kitab al-Tabaqat al-Kabir, Vol. 2, p.444; Cited in: Ibid.

[78] English Translation of Jami‘ At-Tirmidhi. Compiled by Imam Hafiz Abu ‘Eisa Mohammad Ibn ‘Eisa At-Tirmidhi; translated by Abu Khaliyl; Darussalam Publishers & Distributors, First Edition, 2007, Vol. 5, pp. 414

[79] ሐመሮች ማርቫን ያሉት ማርዋን የተሰኘውን የመዲና ገዥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የንባብ ልዩነት እንጂ ከስህተት የሚቆጠር አይደለም፡፡

[80] Ibn Abi Dawud. Kitab al-Masahif, p.24

[81] ሐመር፣ 1999፣ ገፅ 27-28

[82] Sahih al-Bukhari Vol. 6, No. 510

[83] ሐመር፣ 1999፣ ገፅ 26

[84] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 27

ለሐሰን ታጁ ምላሽ ዋናው ማውጫ