ምዕራፍ አምስት የቁርኣን ግጭቶች ክፍል 1 “የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት” በሚል ርዕስ በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ

ምዕራፍ አምስት

የቁርኣን ግጭቶች 

ክፍል 1 [ክፍል 2]

ሙስሊም ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ቃል “አለመሆኑን” ለማሳየት ከሚያቀርቧቸው “ማስረጃዎች” መካከል ግጭቶች ናቸው የሚሏቸው ሐሳቦች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ መልስ የተሰጠባቸው ቢሆኑም መልሰው መላልሰው ያነሷቸዋል፡፡ በቁርአናቸውም ውስጥ ምንም ዓይነት ግጭት አለመኖሩንም በኩራት ይናገራሉ፡፡

  1. ፍሬ አልባ ሙግት

በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቁርኣን ውስጥ ይገኛሉ ተብለው በሚጠቀሱት ግጭቶች ዙርያ የሚደረጉት ውይይቶች ብዙ ጊዜ ፍሬያማ ሲሆኑ አይታይም፡፡ ለዚህ በዋናነት እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች ለነዚህ የግጭት ክሶች መልስ እንዳላቸው ማመናቸው ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ወይም ሙስሊም በወቅቱ ለሚጠየቀው ጥያቄ መልስ ባይኖረው እንኳ አጥጋቢ መልስ ከእርሱ የተሻለ ዕውቀት ባለቸው ወገኖች ዘንድ እንደሚገኝ ያምናል፡፡ ስለዚህ የግጭት ጥያቄ ለእምነቱ ባለው ታማኝነት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ያን ያህል አይደለም፡፡

ሙስሊም ምሑራን ግጭቶች ናቸው የሚሏቸውን ነጥቦች በተደጋጋሚ በማንሳት በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ሊደረጉ የሚገባቸውን ትክክለኛ ውይይቶች ችላ ማለታቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነት ተራ የሙግት ስልቶች ወጥተው ስለ አምላካችን ማንነትና ባሕርያት፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍታችን ምንጭ፣ ስለ እምነታችን መሥራቾች እውነተኛነት፣ ስለ ዘላለም ሕይወትና ስለመሳሰሉት ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች መወያየት እስካልጀመሩ ድረስ እውነትን ማወቅም ሆነ ማሳወቅ የሚችሉበት ዕድል ሊኖራቸው አይችልም፡፡

ሙስሊም ምሑራን ከዚህ ተራ ሙግት ወጥተው እውነተኛ ውይይቶችን የማድረግ ዝግጅት የማጣታቸው ዋናው ምክንያት ቁርኣን ብዙ ግጭቶች በውስጡ “አለመኖራቸውን” ለመለኮታዊነቱ እንደ ማስረጃ ማቅረቡ ነው፡፡ ቁርኣን 4፡82 ላይ እንዲህ ይላል፡-

“ቁርኣንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡”

ቁርኣን በውስጡ ብዙ መለያየት አለመኖሩን ከፈጣሪ ዘንድ ስለመሆኑ እንደ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ነገር ግን እርስ በርስ አለመጋጨት የየትኛውም መጽሐፍ ባሕርይ ሊሆን በመቻሉ ምክንያት አንድ መጽሐፍ እውነተኛ የፈጣሪ ቃል እንደሆነ ለማረጋገጥ ግጭት በውስጡ አለመኖሩ እንደ ማስረጃ ሊቀርብ አይችልም፡፡ የሆሜር፣ የሼክስፒር፣ የሐዲስ ዓለማየሁና የበዓሉ ግርማ የልበወለድ ሥራዎች ውስጥ ግጭት ላይኖር ይችላል፡፡ የፈጣሪ ቃል ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ አንድ ሰው ግጭት የሌለበትን መጽሐፍ በጥንቃቄ አዘጋጅቶ የፈጣሪ ቃል መሆኑን ስለተናገረ ብቻ የፈጣሪ ቃል ነው ብለን አንቀበለውም፡፡ መሰል መመዘኛዎች ምክንያታዊ መሠረት የላቸውም፡፡

በእርግጥ ይህ ጥቅስ በቁርኣን ውስጥ ምንም ዓይነት ግጭት አለመኖሩን አልተናገረም፤ ነገር ግን ብዙ ግጭት አለመኖሩን ነው የተናገረው፡፡ ስለዚህ ጥቂት ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሙስሊም ወገኖቻችን ምንም ዓይነት ግጭት በውስጡ አለመኖሩን በልበ ሙሉነት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡

ክርስቲያን ምሑራን ከሙስሊም ወገኖች ጋር የሚያደርጓቸው ውይይቶች በቁርኣንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ግጭቶች ዙርያ እንዲያጠነጥኑ ፍላጎት የላቸውም፡፡ የዚህ ምክንያቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱትን ጥያቄዎች መመለስ ስለማይችሉ ወይንም ደግሞ በቁርኣን ውስጥ ግጭቶች መኖራቸውን ማሳየት ስለማይችሉ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ርዕስ የተሻሉ አንገብጋቢ ርዕሶች በመኖራቸው ምክንያት እንዲህ ላሉ ከክብደት በታች ለሆኑ ሙግቶች ጊዜያቸውን መሠዋት ስለማይሹ ነው፡፡

  1. መልስ ይኖራቸው ይሆን?

እኔን ጨምሮ አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች የቁርኣን ግጭቶችን በተመለከተ ጽሑፎችን አዘጋጅተናል፡፡ ይህንን ማድረጋችን ሙስሊም ወገኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነሷቸው ክሶች በእነርሱም መጽሐፍ ላይ መነሳት እንደሚችሉ እንዲገነዘቡና ሁለት ዓይነት ሚዛኖችን መጠቀም በማቆም ሁለቱንም መጻሕፍት ፍትሓዊ በሆነ መንገድ መመዘን እንዲጀምሩ ከመርዳት አንጻር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ሲያብጠለጥሉና ሲወርፉ የኖሩት ሙስሊም ወገኖቻችን የነርሱኑ የሙግት ስልት በመጽሐፋቸው ላይ በመተግበራችን ሲቆጡና ሲያኮርፉ ማየት በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ አቶ ሐሰንም በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ብስጭትና ቁጣን በተሞሉ ቃላት “እኛ ብቻ እንናገራችሁ፤ እናንተ አፋችሁን ዝጉ!” የሚል ዓይነት አንድምታ ያላቸውን መልእክቶች አስተላልፈዋል (ገፅ 125-161)፡፡ በክርስቲያኖች ከቀረቡት የቁርኣን ግጭቶች መካከል ቀለል ቀለል ያሉ 13 ግጭቶችን መርጠው ለማስታረቅ 37 ገፆችን የፈጁ ቢሆንም እኛ ግን መልሶቻቸውን አጥጋቢ ሆነው አላገኘናቸውም፡፡ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡-

  • የሰው ልጅ አፈጣጠር

ሰው ከምን ተፈጠረ? ለሚለው ጥያቄ ቁርኣን እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ምላሾችን ይሰጣል፡፡

ከውሃ (25፡54)፣ ከጭቃ (32፡7፣ 37፡11)፣ ከረጋ ደም (96፡1-2)፣ ከአፈር (30፡20)፣ ከሚቅጨለጨል ሸክላ (15፡26)፡፡

አቶ ሐሰን ለዚህ ግጭት መልስ የሰጡት እንዲህ በማለት ነው፡-

አላህ አደምን መፍጠር ሲሻ አፈጣጠሩን በ‹‹አፈር›› ጀመረ፡፡ ከአፈሩ ላይ ውሃ ሲያክልበት ‹‹ጭቃ›› ሆነ፡፡ ይህ ጭቃ ከጊዜ ብዛት ‹‹ጥቁርና የሚገማ›› ሆነ፡፡ ቀለሙም ጠረኑም ተቀየረ፡፡ ይህ ጭቃ ሲደርቅ እሳት ሳይነካው በፊት ‹‹የሚቅጨለጨል›› ተሰኘ፡፡ ከነዚህ ሁሉ ሂደቶች በኋላ አላህ ነፍስ ዘራበት እና አደም ‹‹ሰው›› ለመሆን በቃ… (ገፅ 126 መስመር ከኔ)

የዚህ ማብራርያ የመጀመርያው ችግር ቁርኣን በሌላ ቦታ አላህ ሰውን መፍጠር የጀመረው ከጭቃ መሆኑን መናገሩ ነው፡፡ ሱራ 32፡7 እንዲህ ይላል፡-

“ያ የፈጠረውን ነገር ሁሉ ያሳመረው የሰውንም ፍጥረት ከጭቃ የጀመረው ነው፡፡

አቶ ሐሰን ከላይ የተጠቀሱት የሰው አፈጣጠር ዓይነቶች ግጭት ሳይሆኑ የአፈጣጠር ሂደቶች እንደሆኑ ካመኑ አላህ በአፈር ወይስ በጭቃ ጀመረ? የሚለውን ማስታረቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሌላው ችግር የተጠቀሱት ነገሮች እንደ ግብኣት ከታሰቡ ነጣጥሎ መናገሩ ትርጉም የሚሰጥ አለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዳቦ ሲጋገር ውሃ እንደሚገባበት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን “ዳቦ ከውሃ ጋገርኩ” ብዬ ብናገር ትርጉም ይሰጣልን?

  • የመጀመርያው ሙስሊም ማነው?

ቁርኣን ለዚህ ጥያቄ የሰጣቸው ምላሾች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው፡፡ ሙሐመድ የመጀመርያው ሙስሊም እንደሆኑ ይናገራል (39፡12፣ 6፡163፣ 6፡14)፣ ነገር ግን አብረሃምና ኢስማኤል (2፡128፣ 3፡36)፣ የፈርዖን ድግምተኞች (7፡126) እንዲሁም ሐዋርያት (5፡111) ሙስሊሞች ነበሩ ይላል፡፡ በተጨማሪም እስልምና የነቢያት ሁሉ ሃይማኖት መሆኑን ይናገራል፡፡

አቶ ሐሰን ይህንን ግጭት “ሲያስታርቁ” እንዲህ ብለዋል፡-

… ነቢዩ ሙሐመድ የሌሎች ነቢያት ሐይማኖት የሆነውን እስልምናን የሰበኩ ቢሆንም ከነበሩበት ትውልድ አንፃር የመጀመርያው ሙስሊም ናቸው፡፡ (ገፅ 133)

በነቢዩ ሙሐመድ ዘመን አላህን ሲያመልኩ የነበሩ የአብረሃምን መንገድ የተከተሉ “ሐኒፎች” እንደነበሩ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ከመጠቀሱ አንጻር ይህ መልስ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ እነዚህ “የአብረሃም እምነት ተከታዮች” ዋረቃ ኢብን ናውፋል፣ ኡቤይዱላህ ኢብን ጃሽ፣ ኡሥማን ኢብን አል-ሑዋሪሥ እና ዘይድ ኢብን ዐምር መሆናቸውን ኢብን ኢስሐቅ ዘግቧል፡፡[1] እነዚህ ሰዎች የአብረሃምን ሃይማኖት በማወቅ ከሙሐመድ የቀደሙ በእርሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በቁርኣን ውስጥ አብረሃም ራሱ ሐኒፋ መሆኑ ተነግሯል፡-

“ኢብራሂም ይሁዳዊም ክርስቲያንም አልነበረም፡፡ ግን ወደ ቀጥተኛው ሃይማኖት የተዘነበለ [በአረብኛ ሐኒፈን] ሙስሊም ነበረ፡፡ ከአጋሪዎችም አልነበረም፡፡” (3፡67)

“«እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትክክለኛን ሃይማኖት ወደ እውነት አዘንባይ ሲኾን [በአረብኛ ሐኒፈን] የአብርሃምን መንገድ መራኝ፡፡ እርሱም ከአጋሪዎቹ አልነበረም» በል፡፡” (6፡161)

እስልምና የሰው ልጆች የተፈጥሮ ሃይማኖት መሆኑን ይናገራል (ሱራ 30፡30፣ 2፡138)፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ማንኛውም ህፃን ሲወለድ ሙስሊም ሆኖ እንሚወለድና ኋላ ላይ ራሱን ሲያውቅ በወላጆቹ ምክንያት የተፈጥሮ ሃይማኖቱን እንደሚለቅ ይናገራሉ፡፡[2] ስለዚህ በሙሐመድ ዘመን የነበሩት ህፃናት ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ከእሳቸው ቀድመው ሙስሊሞች ሆነው ነበር ማለት ነው፡፡

ሌላው አቶ ሐሰን ሙሴ የምእመናን መጀመርያ መሆኑን የሚገልፀውን ተከታዩን ጥቅስ ጠቅሰዋል፡-

“…ሙሳም ጮሆ ወደቀ፡፡ በአንሰራራም ጊዜ «ጥራት ይገባህ፡፡ ወዳንተ ተመለስኩ፡፡ እኔም (በወቅቱ) የምእምናን መጀመሪያ ነኝ» አለ፡፡” (ሱራ 7፡143)

(በወቅቱ) የሚለው በተርጓሚዎች የተጨመረ እንጂ በአረብኛው ውስጥ አይገኝም፡፡ ይህንን ማብራርያ በመጨመር ጥቅሱ የሚፈጥረውን ችግር ለማስወገድ ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ማብራርያ የሙሴ እናትና ሌሎች አማኞች በዘመኑ እንደነበሩ ከሚገልፁት የቁርኣን ጥቅሶች ጋር ይጋጫል፡-

“ወደ ሙሳም እናት «አጥቢው፣ በርሱም ላይ በፈራሽ ጊዜ በባሕሩ ውስጥ ጣይው አትፈሪም፣ አትዘኝም፣ እኛ ወዳንቺ መላሾቹና ከመልክተኞቹም አድራጊዎቹ ነንና» ማለትን አመለከትን፡፡” (ሱራ 28፡7)

በቁርኣን መሠረት የሙሴ እናት የአላህን መልእክት መስማት የቻለች አማኝ ሴት ነበረች፡፡ በተጨማሪም በሙሴ ዘመን ከፈርዖን ባለሟሎች መካከል አማኝ የነበረ ሰው መኖሩን ቁርኣን ይናገራል (ሱራ 40፡28-46)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሙሴ በተገለጠለት በዚያው ጊዜ ወንድሙ አሮን የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማት ሊቀበለው ወደ መንገድ እንደወጣ ይናገራል (ዘጸአት 4፡14-28)፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ሙሴ በወቅቱ የመጀመርያው አማኝ እንዳልሆነ ያረጋግጡልናል፡፡ በሙሴ ዘመን የነበሩት የግብፅ አስማተኞች “የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች” መሆናቸውን የሚገልፀው የቁርኣን ጥቅስ ደግሞ ከላይ ያሉትን በሙሉ ያፈርሳል(ሱራ 7፡126)፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ አቶ ሐሰን አቅልለው ለማሳየት የሞከሩትን ያህል ቀላል አይደለም፡፡

  • ሰይፍና የእምነት ነጻነት

ቁርኣን በሃይማኖት ማስገደድ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? ለሚለው ጥያቄ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ምላሾችን ይሰጣል፡-

“በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡” (ሱራ 2፡256)

ይህንን አቋሙን በማፍረስ ሌላ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል፡-

“ሁከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሏቸው፡፡ ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡” (ሱራ 8፡39)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ሙስሊሞች “ከሃዲያንን” መጋደል የሚኖርባቸው “ሃይማኖት ሁሉ ለአላህ እስኪሆን ድረስ” ነው፡፡ በሌላ አባባል ሌላው ሃይማኖት ሁሉ ጠፍቶ እስልምና ብቻ እስኪቀር ድረስ ማለት ነው፡፡ ተከታዩን ደግሞ እንመልከት፡-

“የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡” (ሱራ 9፡5)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ ሙስሊሞች “ከሃዲያንን” ከመግደል መታቀብ ያለባቸው ሶላትን በደንቡ ሲሰግዱና እስላማዊውን ምጽዋት (ዘካት) ሲሰጡ ነው፡፡ በሌላ አባባል ጥሩ ሙስሊሞች እስኪሆኑ ድረስ ማለት ነው፡፡ አንድ እንጨምር፡-

“ከእነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው፡፡” (ሱራ 9፡29)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ “መጽሐፍን የተሰጡት” (አይሁድና ክርስቲያኖች ለማለት ነው) የእስልምናን ትምህርት ባለመቀበላቸው ምክንያት ተዋርደው ግብርን (ጂዝያን) እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡

እስላማዊ ትውፊቶች ደግሞ እንዲህ በማለት እነዚህን የቁርኣን ትዕዛዛት ያጠናክራሉ፡-

“ኢብን ዑመር እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤ ሰዎች ከአላህ በስተቀር ሊመለክ የሚገባው እንደሌለና ሙሐመድም ደግሞ መልእክተኛው መሆኑን እስኪመሰክሩ ድረስ እንዲሁም ሶላትን ደንቡን ጠብቀው እስኪሰግዱ ድረስና ዘካትን እስኪሰጡ ድረስ እንድዋጋቸው (በአላህ) ታዝዣለሁ፡፡ ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ በእስልምና ሕግ ከተደነገገው በስተቀር ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ከእኔ ይታደጋሉ፤ ድርሻቸውም በአላህ ይታሰብላቸዋል፡፡”[3]

“ነቢዩ ‹ማንኛውንም እስልምናን ለቆ የሚወጣ ሰው ግደሉት› ብለዋል፡፡”[4]

አቶ ሐሰን ከላይ ያሉትን ጥቅሶች ችላ በማለት ሱራ 9፡14 ላይ ስለ ጦርነት የተጻፈውን ከጠቀሱ በኋላ በሃይማኖት ማስገደድ አለመኖሩን ከሚናገረው ጥቅስ ጋር ለማስታረቅ በመታገል 10 ገፆችን ፈጅተዋል፡፡ ይህ በሥነ-አመክንዮ ሕግ a Strawman Argument Fallacy ይሰኛል፡፡ የጠያቂውን ትክክለኛ ጥያቄ ችላ ብለህ ራስህ የፈጠርከውን ሙግት የእርሱ በማስመሰል ሙግቱን ማፈራረስ እንደማለት ነው፡፡ እኛ በሃይማኖት ማስገደድ እንደሌለ የሚናገረው ጥቅስ ስለ ጦርነት ከሚናገሩት ጥቅሶች ሁሉ ጋር ይጋጫል አላልንም፡፡ ነገር ግን ሃይማኖትን ለማስቀየር መዋጋትን ከሚያዙት ጥቅሶች ጋር እንደሚጋጭ ነው የተናገርነው፡፡ አቶ ሐሰን ጥያቄያችንን አልመለሱም፡፡ ዳሩ ግን እስልምና ምን ዓይነት “ሰላማዊ” ሃይማኖት እንደሆነ ለማስረዳት በመሞከር አጭሩን ጥያቄ ያለልክ አስረዝመውታል፡፡

የእስልምናን “ሰላማዊነት” ለማስረዳት ከተጠቀሟቸው ሙግቶች መካከል አንዱ ነቢዩ ሙሐመድ ባደረጓቸው ጦርነቶች ላይ የሞቱት ሰዎች ቁጥር “አነስተኛ” ነው የሚል ሲሆን ነገር ግን የሰጡት እስታስቲክስ የተሳሳተ ሲሆን “ሰይፉን ፍለጋ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ካሠፈሩት ጋር ይጋጫል፡፡ ለምሳሌ ያህል እያየነው ባለነው መጽሐፍ ውስጥ በኒ ሙስጦሊቅ በተባለው ዘመቻ ላይ የሞቱ ሙስሊሞች አለመኖራቸውንና ከሌላው ወገን 3 መሞታቸውን የገለጹ ሲሆን “ሰይፉን ፍለጋ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ከሙስሊሞች 1 ከሌላው ወገን 6 መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡ በኸይበር ዘመቻ 19 ሙስሊሞች መሞታቸውንና ከሌለው ወገን የሞተ አለመኖሩን የገለጹ ሲሆን በ “ሰይፉን ፍለጋ” ውስጥ ከሌላው ወገን 93 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡ በድምር የሟቾች ቁጥር ከሙስሊሞች ወገን 317 መሆኑንና ከሌላው ወገን 439 መሆኑን የገለጹ ሲሆን በ “ሰይፉን ፍለጋ” ውስጥ ሙስሊሞች 328 መሆናቸውንና ሙስሊም ያልሆኑት 535 መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ አጠቃላይ ድምሩ 756 መሆኑን የገለጹ ሲሆን በ “ሰይፉን ፍለጋ” ውስጥ ድምሩን 863 አድርገውታል፡፡[5] የቱ ነው ትክክል?

በኒ ቁረይዛ በተሰኘው ጦርነት ላይ በሙስሊሞች እጅ የተገደሉትን ወደ 850 የሚሆኑ አይሁዶችን ለምን እንዳልደመሩ ሲገልጹ “በችሎት ውሳኔ የተፈረደባቸው ስለሆኑ ነው” የሚል ምክንያት ሰጥተዋል፡፡[6] ነገር ግን ይህ የሟቾችን ቁጥር ለማሳነስ የተሰጠ ደካማ ምክንያት ነው፡፡ ሙሐመድ የበኒ ቁረይዛ አይሁዶችን ከማረኩ በኋላ ከተከታዮቻቸው ጋር በመመካከር በበነጋው ለአቅመ አዳም የደረሱትን ወንዶች ሁሉ በመግደል ሴቶችና ህፃናትን ለባርነት አከፋፍለዋል፡፡ ይህ በምንም መንገድ ፍትሃዊ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡

አቶ ሐሰን ስለ እስልምና “ሰላማዊነት” ያቀረቡትን ሰበካ በገዛ እጃቸው ከአረብኛ ወደ አማርኛ ከተረጎሙት ከተከታዩ የጥላቻ ትዕዛዝ ጋር እንዴት ያስታርቁት ይሆን?

“ነቢዩ (የአላህ ሰላምና በረከት በእሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ብለዋል ‹አይሁድን ወይንም ክርስቲያኖችን ቀድማችሁ ሰላም አትበሉ፡፡ በመንገድ ላይ ቢመጡባችሁ ወደ ጠባቡ የመንገድ ጠርዝ ግፏቸው፡፡›[7]

  • ቁርኣንን ማን አወረደው?

አላህ እንዳወረደው ይናገራል፡-

“ቁርኣንንም በሰዎች ላይ በዝግታ ላይ ኾነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው፡፡ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው፡፡” (ሱራ 17፡106)

ጂብሪል አወረደው ይላል፡-

“እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት ሙስሊሞቹንም ለመምራትና ለማብሰር (ቁርኣንን) ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው፡፡” (ሱራ 16፡102)

አቶ ሐሰን እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡-

… የቁርአኑ ምንጭ አላህ ከመሆኑ አኳያ ቁርአኑን አላህ እንዳወረደው ተገልጿል፡፡ የመልእክቱ አድራሽ … ደግሞ መልአኩ ጅብሪል ከመሆኑ አኳያም ጅብሪል የቁርኣን አውራጅ እንደሆነ ተወስቷል፡፡ (ገፅ 143)

[በቅንፍ ያለው የተርጓሚዎቹ ጭማሬ ሲሆን ቁርኣን በአንድም ቦታ ቅዱሱ መንፈስ ጂብሪል መሆኑን አልገለጸም፡፡ ጂብሪል በአረብኛ ቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው ሦስት ጊዜ ብቻ ሲሆን (ሱራ 2፡98፣ 2፡97፣ 66፡4) በአማርኛ የቁርኣን ትርጉም በቅንፍ (ጂብሪል) ተብለው የገቡት በሙሉ የተርጓሚዎቹ ጭማሬ እንጂ በአረብኛው ውስጥ አይገኙም፡፡]

ይህ እንዳለ ሆኖ አንድ የቁርኣን ጥቅስ በጥያቄው ላይ በማከል የአቶ ሐሰንን ምላሽ ዋጋ ማሳጣት ይቻላል፡፡ ሱራ 81፡19 እንዲህ ይላል፡-

إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ     “ኢነሁ ለቀውሉ ረሱሊህን ከሪም፡፡”

“እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡”

የቁርኣን ምንጭ አላህ ከሆነ “የመልእክተኛ ቃል” ስለምን ተባለ? ይህ ቁርኣን ቃል በቃል ከአላህ የመነጨ አለመሆኑን አያመለክትምን?

  • ለነቢዩ ሙሐመድ የተሰጠ ፈቃድ

ቁርኣን ነቢዩ ሙሐመድ ሚስቶችን ያለገደብ እንዲያገቡ ፈቅዶላቸዋል፡-

“አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ እነዚያን መህሮቻቸውን የሰጠሃቸውን ሚስቶችህን፣ አላህ ባንተ ላይ ከመለሰልህም እነዚያን እጅህ የጨበጠቻቸውን ምርኮኞች፣ እነዚያንም ከአንተ ጋር የተሰደዱትን የአጎትህን ሴቶች ልጆች፣ የአክስቶችህንም ሴቶች ልጆች፣ የየሹማህንም ሴቶች ልጆች፣ የየሹሜዎችህንም ሴቶች ልጆች (ማግባትን) ለአንተ ፈቅደንልሃል፡፡ የአመነችንም ሴት ነፍሷን (ራሷን) ለነቢዩ ብትሰጥ ነቢዩ ሊያገባት የፈለገ እንደ ኾነ ከምእምናን ሌላ ላንተ ብቻ የጠራች ስትኾን (ፈቀድንልህ)፡፡ በእነርሱ (በምእምናን) ላይ በሚስቶቻቸውና እጆቻቸው በጨበጧቸው (ባሮች ነገር) ግዴታ ያደረግንባቸውን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ ባንተ ላይ ችግር እንዳይኖር (ያለፉትን ፈቀድንልህ)፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (ሱራ 33፡50)

ይህ አንቀፅ ቀጥሎ ካለው ጋር እንደሚጋጭ ተነግሯል፡-

“ከእነዚህ በኋላ እጅህ ከጨበጠቻቸው (ባሮች) በስተቀር ሴቶች ለአንተ አይፈቀዱልህም፡፡ ከሚስቶችም መልካቸው ቢደንቅህም እንኳ በእነርሱ ልታላውጥ (አይፈቀደልህም)፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡” (ሱራ 33፡52)

አቶ ሐሰን ሁለቱ አናቅፅ እንደማይጣረሱ ገልፀዋል፡፡ ለኔ ከግጭት ይልቅ ጎልቶ የሚታየኝ ችግር ለሙሐመድ የተሰጣቸው ድንበር ዘለል ፈቃድ ነው፡፡ በጋብቻ የተጣመሯቸው ሴቶች አልበቃ ብለዋቸው የጦር ምርኮኞች፣ በአባትና በእናቱ ወገን ያሉ የአጎትና የአክስት ልጆች እንዲሁም ሊያገቧቸው ፈቃደኛ የሆኑ ሙስሊም ሴቶች ሁሉ እንደተፈቀዱላቸው መነገሩ ህሊናን ይጎረብጣል፡፡ ቅዱስና ሃያል የሆነው አምላክ የአንድን ግለሰብ የሥጋ መሻት ለማርካት እንዲህ ያሉ ትዕዛዛትን በዘላለማዊው ቃሉ ውስጥ እንዳካተተ መነገሩ የማይታመን ነው፡፡ በኔ ዕይታ ይህ አንቀፅ ቁርኣን ከእውነተኛው አምላክ ዘንድ ላለመሆኑና የአንድን ግለሰብ የግል ፍላጎት ለመሙላት የተጻፈ ድርሳን ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አንድ የቁርኣን ጥቅስ ብናክል ግጭቱ የት ጋ እንዳለ እንገነዘባለን፡-

“ከሴቶች ለእናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት ሦስት ሦስትም አራት አራትም አግቡ፡፡ አለማስተካከልንም ብትፈሩ አንዲትን ብቻ ወይም እጆቻችሁ ንብረት ያደረጉትን ያዙ፡፡ ይህ ወደ አለመበደል በጣም የቀረበ ነው፡፡” (ሱራ 4፡3)

በዚህ ጥቅስ መሠረት አንድ ሙስሊም ወንድ እስከ አራት ሚስቶች ብቻ ነው እንዲያገባ የተፈቀደለት፡፡ በአንድ ወቅት ስምንት ሚስቶች የነበሩትን አንድ ሙስሊም አራቱን ብቻ በመምረጥ የተቀሩትን እንዲፈታ ሙሐመድ ትዕዛዝ ሰጥተውት ነበር፡፡[8] ነገር ግን ለሙሐመድ የተሰጣቸው ፈቃድ ይህንን ትዕዛዝ የሚያፈርስ ነው፡፡ እናም አቶ ሐሰን ይህንን ግጭት ማስታረቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

  • የስግደት አቅጣጫ

ቁርኣን ሱራ 2፡115 ላይ እንዲህ ይላል፡-

“ምሥራቁም ምዕራቡም የአላህ ነው (ፊቶቻችሁን) ወደ የትም ብታዞሩ የአላህ ፊት እዚያ ነው፡፡ አላህ ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነውና፡፡”

በሌላ ቦታ ደግሞ ፊትን ወደ መካ አቅጣጫ ብቻ ማዞርን ያዛል፡-

“ከየትም ከወጣህበት ስፍራ ፊትህን ወደ ተከለለው መስጊድ አግጣጫ አዙር፡፡ በየትም ስፍራ ብትኾኑ ለሰዎቹ እነዚያ ከነሱ የበደሉት ሲቀሩ (ሃይማኖታችንን ይክዳሉ ቂብላችንን ይከተላሉ በማለት) በናንተ ላይ መከራከሪያ እንዳይኖራቸው ፊቶቻችሁን ወደ አግጣጫው አዙሩ፡፡” (ሱራ 2፡150)

አቶ ሐሰን ለዚህ ግጭት መልስ ሲሰጡ እንዲህ አሉ፡-

… የአንቀጹ መልእክት ‹‹ወደ ፈለጋችሁት አቅጣጫ ዙሩና ስገዱ›› የሚል ሳይሆን፡- ‹‹ከበይተል መቅዲስ ወደ ከእባ በመዙራችሁ አይሁዶችና ሙናፍቃን ማፌዛቸው አግባብ አይደለም፡፡ የአላህ ትእዛዝ እስከሆነ ድረስ በአዲሱ የስግደት አቅጣጫም አላህ ይገኛል›› ማለት ነው… (ገፅ 147)

እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ትልቁ ጥያቄ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ዞሮ መስገድ የአላህ ትዕዛዝ ከነበረ ካዕባ በጣዖታት ተሞልቶ በነበረበት ሁኔታ ወደዚያ ፊትን አዙሮ መስገድ ለምን አስፈለገ? የሚል ነው፡፡ ለኔ አሁንም ከግጭት ይልቅ ጎልቶ የሚታየኝ የአንድ ግለሰብ ፍላጎት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ እስላማዊ ትውፊቶች እንዲህ ይላሉ፡-

“ዩኑስ ኢብን አብድ አል-ዐላ ኢብን ዋህብ ኢብን ዘይድ እንዳስተላለፈው፡ ነቢዩ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ ለአስራ ስድስት ወራት ያህል ዞረው ከሰገዱ በኋላ አይሁድ ‹‹በአላህ እንምላለን ሙሐመድና ተከታዮቹ እኛ እስክንመራቸው ድረስ ቂብላ ወዴት አቅጣጫ እንደሆነ አያውቁም ነበር›› ብለው መናገራቸውን ሰሙ፡፡ ይህም ነቢዩን አስቆጣቸው ስለዚህም ፊታቸውን ወደ ሰማይ ገልብጠው ተመለከቱ፡፡ አላህ እንዲህ አለ፤ “የፊትህን ወደ ሰማይ መገላበጥ በእርግጥ እናያለን፡፡ [ወደምትወዳትም ቂብላ እናዞርሃለን፡፡]”[9]

ሙሐመድ የስግደት አቅጣጫን የቀየሩት በአይሁድ ማላገጥ ስለተናደዱ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የፈጣሪ መገለጦች በግለሰብ ስሜት ላይ ተመሥርተው የሚለዋወጡ አይደሉም፡፡

  • ዒሳና አደም

ቁርኣን የዒሳ አፈጣጠርና የአዳም አፈጣጠር ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራል፡-

“አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው፡፡ ከዐፈር ፈጠረው፡፡ ከዚያም ለርሱ (ሰው) «ኹን» አለው፤ ኾነም፡፡” (ሱራ 3፡59)

ነገር ግን የዒሳ (የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም) አፈጣጠርና የአዳም አፈጣጠር የተለያዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

አቶ ሐሰን እንዲህ በማለት መልስ ሰጥተዋል፡-

… ንጽጽሩ ያስፈለገው ኢሳ ያለ አባት በመወለዱ ብቻ ‹‹አምላክ›› ያሉትን ወገኖች ስህተት ለማስረዳት ነው፡፡ ኢሳ ያለ አባት መወለዱ አምላክ ወይም የአምላክ ልጅ አያሰኘውም፡፡ ልክ እንደ አደም ሰው ነው፡፡ አላህ ኢሳን በኹን ቃሉ ያለ አባት እንደፈጠረው ሁሉ አደምንም ያለ እናትና ያለ አባት ፈጥሯቸዋል፡፡ ያለ ወላጅ መፈጠር ለአምላክነት ደረጃ የሚያበቃ ቢሆን ኖሮ ለዚህ ደረጃ ያለ ወላጆች የተፈጠሩት አደም ይበልጥ ተገቢ ናቸው፣ የሚል መልእክት ነው አንቀጹ የያዘው፡፡ (ገፅ 147)

ይህ የ Straw-man Argument Fallacy ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ላይ “ኢየሱስ አምላክ የሆነው ያለ አባት ስለተወለደ ነው” አይልም፡፡ የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች ከመኖራቸው አንፃር እምነታቸውን የሚያውቁ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን ሙግት አያቀርቡም፡፡ ኢየሱስ አምላክ ስለሆነ ከድንግል ተወለደ እንጂ ከድንግል ስለተወለደ አምላክ አልተባለም፡፡ ከመወለዱ በፊትም አምላክ ነው (ዮሐ. 1፡1)፡፡ የቁርኣን ደራሲ ከገዛ አለማወቁ በመነሳት ይህንን ሐሳብ አቅርቧል፤ አለበለዚያም ደግሞ አንዳንድ ዕውቀት የጎደላቸው “ክርስቲያኖች” የተናገሩትን በመስማት ይህንን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ይሁን በዚያ ይህ ቃል ሁሉን አዋቂ ከሆነው አምላክ ዘንድ የመጣ ሊሆን አይችልም፡፡

ይህ የቁርኣን ጥቅስ የአዳምን አፈጣጠር አስመልክቶ በሌሎች ቦታዎች ላይ ከተነገሩት ጋር ይጣረሳል፡፡ በጥቅሱ መሠረት አዳም ከአፈር በአላህ የይሁን ቃል ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን ቁርኣን በሌላ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል፡-

“ጌታህ «ለመላእክት እኔ ሰውን ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ» (አስታውስ)፡፡ ‹ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበት ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ› (አልኩ)፡፡ መላእክትም መላውም ባንድነት ሰገዱ፡፡ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ ኮራ፤ ከከሓዲዎቹም ነበር፡፡ (አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! በሁለት እጆቼ (በኃይሌ) ለፈጠርኩት ከመስገድ ምን ከለከለህ? (አሁን) ኮራህን? ወይስ (ፊቱኑ) ከትዕቢተኞቹ ነበርክ?» አለው፡፡” (ሱራ 38፡71-72)

በዚህ ጥቅስ መሠረት አላህ አዳምን ከጭቃ ከፈጠረው በኋላ “መንፈሱን” በመንፋት ሕያው አድርጎታል፡፡ በቀደመው ጥቅስ መሠረት ግን ከፈጠረው በኋላ “ሁን” በሚል ቃል ሕያው አድርጎታል፡፡ በቃሉ ሕያው ካደረገው መንፈሱን መንፋት ለምን አስፈለገ? በመንፈሱ ሕያው ካደረገው “ሁን” የሚለውን ቃል መናገር ለምን አስፈለገ?

ሌላው የጥቅሱ ችግር ዒሳና አዳምን ማመሳሰሉ ነው፡፡ ነገር ግን በቁርኣን መሠረት ሁለቱ በፍፁም አይመሳሰሉም፡፡

  • ዒሳ ከድንግል ተወለደ፤ አዳም ግን አልተወለደም (ሱራ 3፡47፣ 19፡16-21)
  • ዒሳ ኃጢአት አልባ ነው፤ አዳም ግን አይደለም (ሱራ 19፡19፣ 3፡35፣ Sahih Al-Bukhari, Volume 4, Book 55, Number 641; see also Volume 4, Book 54, Number 506፣ ሱራ 20፡115-123፣ 7፡19-27)
  • ዒሳ የአላህ መንፈስና ቃሉ ነው፤ አዳም ግን በመንፈሱና በቃሉ የተፈጠረ ነው (ሱራ 3፡45፣ 4፡171)
  • ዒሳ ንጉሥ[10] የሆነ መሲህ ነው፤ አዳም አይደለም (ሱራ 3፡45)
  • ዒሳ በሚመጣው ዓለም የተከበረ ነው፤ ለአዳም ግን እንደርሱ አልተባለም (ሱራ 3፡45)
  • ዒሳ ወደ ሰማይ አርጓል፤ አዳም ግን ሞቷል (ሱራ 3፡55፣ 4፡158)
  • ዒሳ ተመልሶ በመምጣት ጀዳልን ይገድለዋል፤[11] አዳም እስከ ዕለተ ትንሣኤ ሞቶ ይቆያል (ሱራ 43፡61)
  • ዒሳ ተዓምራትን አድርጓል፤ አዳም አላደረገም (ሱራ 3፡48-49፣ 5፡110)[12]

 

  • ግልጽ ወይስ አሻሚ?

ቁርኣን እንዲህ ይላል

“እኛ ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን አደረግነው፡፡” (ሱራ 43፡3)

ሌላ ቦታ ደግሞ እንዲህ ይላል፡-

“እርሱ ያ በአንተ ላይ መጽሐፉን ያወረደ ነው፡፡ ከእርሱ (ከመጽሐፉ) ግልጽ የኾኑ አንቀጾች አልሉ፡፡ እነሱ የመጽሐፉ መሠረቶች ናቸው፡፡ ሌሎችም ተመሳሳዮች አልሉ፡፡ እነዚያማ በልቦቻቸው ውስጥ ጥመት ያለባቸው ሰዎች ማሳሳትን ለመፈለግና ትችቱን ለመፈለግ ከርሱ የተመሳሰለውን ይከታተላሉ፡፡ (ትክክለኛ) ትችቱንም አላህ ብቻ እንጅ ሌላ አያውቀውም፡፡ በዕውቀትም የጠለቁት «በርሱ አምነናል፤ ሁሉም ከጌታችን ዘንድ ነው» ይላሉ፡፡ የአእምሮ ባለቤቶችም እንጅ (ሌላው) አይገሰጽም፡፡” (ሱራ 3፡7)

አቶ ሐሰን እንዲህ በማለት “ያስታርቃሉ”፡-

… የመጀመርያው አንቀጽ ነቢዩ የነበሩበትን ማሕበረሰብ ‹‹ቁርኣን በይብራይስጥ ወይም በሌላ ቋንቋ ሳይሆን በአረብኛ ያደረግነው በቀላሉ እንድትረዱት፣ መልእክቱ እንዲገባችሁ ነው›› ሲል ያናግራል ፡፡ ሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ ይህ በአረብኛ ቋንቋ የወረደው ቁርኣን ሁለት ዓይነት አናቅጽ መያዙን ይገልጻል፡፡ አንደኛው ግልጽና የማያሻማ፣ ሁለተኛው አሻሚ… ግልጽና የማያሻሙ (ሙህከም) የተባሉት ሰዎች በአእምሯቸው ሊደርሱባቸው የሚችሉ መልእክቶች፣ ከሌላ ጋር ሳያመሳክሩ በቀላሉ የሚረዷቸው ግልጽ ህግጋት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሶላት ስገድ››…

አሻሚዎችን በተመለከተ አንቀጹ ሁለት መልእክቶችን ይዟል፡፡

  • ትርጉማቸውን አላህ እንጅ ሌሎች አያውቋቸውም፡፡
  • ትርጉማቸውን አላህና ጥልቅ እውቀት ያላቸው ሰዎች እንጅ ሌሎች አያውቋቸውም፡፡

አንቀጹ እነዚህን መንታ ትርጉሞች ሊይዝ የቻለው ሁለት አይነት የአነባብ ስልት በመኖሩ ነው … (ገፅ 149)

አቶ ሐሰን በዚህ ላይ ሰፊ ሐተታ የሰጡ ቢሆንም ሌሎች የቁርኣን ጥቅሶችን ያላገናዘበ ምላሽ በመሆኑ መጥቀሱ ፋይዳ የለውም፡፡ እስኪ ይህንን ምላሽ ከተከታዮቹ ጥቅሶች ጋር እናገናዝብ፡-

“እርሱ ያ መጽሐፉን የተብራራ ኾኖ ወደእናንተ ያወረደ ሲኾን «ከአላህ ሌላ ዳኛን እፈልጋለሁን?» (በላቸው)፡፡ እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው እርሱ ከጌታህ ዘንድ በእውነት የተወረደ መኾኑን ያውቃሉ፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን፡፡” who has revealed to you the Book explained in detail (ሱራ 6፡114)

“…መጽሐፉንም ለሁሉ ነገር አብራሪ፣ መሪም፣ እዝነትም፣ ለሙስሊሞችም አብሳሪ ኾኖ ባንተ ላይ አወረድነው፡፡” We have sent down to you the Book as clarification for all things (ሱራ 16፡89)

አንቀጾቹ የተብራሩ የኾነ መጽሐፍ ነው፡፡ ዐረብኛ ቁርኣን ሲኾን ለሚያውቁ ሕዝቦች (የተብራራ) ነው፡፡” A Book whose verses have been detailed (ሱራ 41፡3)

በነዚህ ጥቅሶች መሠረት ቁርኣን አሻሚና ስውር ሳይሆን የተብራራና ሁሉንም ነገር የሚያብራራ ነው፡፡ ስለዚህ በመጽሐፉ ውስጥ ያልተብራራ፣ አሻሚና ስውር ነገር ከተገኘ እነዚህ ጥቅሶች ስህተት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሱራ 3፡7 ላይ ትክክለኛ ትርጉማቸውን ከአላህ በስተቀር ማንም የማያውቃቸው ስውር አናቅፅ መኖራቸውን ይናገራል፡፡ ስለዚህ የትኛው ነው ትክክል? አቶ ሐሰን እንዳደረጉት “ግልፅ የሆኑቱ እንዲህና እንዲያ ያሉት ናቸው፤ ስውሮቹ ደግሞ እንዲህና እንዲያ ያሉት ናቸው” ብሎ ሐተታ ማብዛት መልስ አይሆንም፡፡ ቁርኣን አንዱ ቦታ ላይ ግልፅ አለመሆኑን ተናግሮ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ግልፅና እንዲያውም ሁሉንም ነገር ግልፅ ለማድረግ እንደመጣ ይናገራል፡፡ ግጭቱ የነጭና የጥቁር ያህል ነው፡፡

የሚገርመው ነገር ነቢዩ ሙሐመድ ቁርኣን ግልፅ መሆኑን ሲሰብኩ ኖረው የነጅራን (የመን) ክርስቲያኖች የገዛ መገለጦቻቸውን ተጠቅመው በጥያቄ ሲያፋጥጧቸው ግልፅ ያልሆኑ አንቀፆች በውስጡ መኖራቸውን እንደተናገሩ እስላማዊ ምንጮች ይናዘዛሉ፡፡[13] አቶ ሐሰን ራሳቸው ይህንን ታሪክ ጠቅሰውታል (ገፅ 152)፡፡ ነገር ግን ሌላ ቦታ ላይ ቁርኣን ልዩነቶችን ለማብራራት እንደመጣ ይናገራል፡-

“ባንተም ላይ መጽሐፉን አላወረድንም፤ ያንን በርሱ የተለያዩበትን ለነርሱ ልታብራራላቸውና ለሚያምኑትም ሕዝቦች መሪና እዝነት ሊኾን እንጂ፡፡” (ሱራ 16፡64)

“ልዩነቶችን ለማብራራት” እንደመጣ የተነገረለት ቁርኣን ግልፅ ያልሆኑ መገለጦችን በማካተት የልዩነት ምክንያት መሆኑ እንዴት ይታያል?

  • አንድ ሺህ ወይስ ሃምሳ ሺህ?

በአላህ ዘንድ ስላለው የጊዜ አቆጣጠር ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ከምትቆጥሩት (ዘመን) ልኩ ሺህ ዓመት በሆነ ቀን ውስጥ ወደርሱ ይወጣል (ይመለሳል)፡፡” (ሱራ 32፡5)

“አላህም ቀጠሮውን በፍጹም የማይጥስ ሲሆን በቅጣት ያቻኩሉሃል፡፡ እጌታህም ዘንድ አንዱ ቀን ከምትቆጥሩት (ቀን) እንደ ሺሕ ዓመት ነው፡፡” (ሱራ 22፡47)

በዚህ ጥቅስ መሠረት አንድ ቀን አንድ ሺህ ዓመት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በተከታዩ ጥቅስ መሠረት ደግሞ አንድ ቀን ሃምሳ ሺህ ዓመት መሆኑ ተነግሯል፡-

“መላእክቱና መንፈሱም ልኩ አምሳ ሺሕ ዓመት በኾነ ቀን ውስጥ ወደእርሱ ያርጋሉ፤ (ይወጣሉ)፡፡” (ሱራ 70፡4)

አቶ ሐሰን እንዲህ ሲሉ መልስ ይሰጣሉ፡-

… ሁለቱ አንቀጾች ስለ ሁለት የተለያዩ ነገሮች የሚያወጉ ናቸው፡፡ የመጀመርያው የሰው ልጆች ስራ ወደ ሰማይ የሚያርገው መጠኑ በምድራዊ አቆጣጠር አንድ ሺህ ዓመታት የሚያስኬድ ርቀት ተጉዞ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ መላእክት ወደ አምላክ የሚያርጉበትን የጊዜ መጠን ያወሳል… (ገፅ 154-155)

አቶ ሐሰን ጥቅሶቹ የሚሉትን አልተገነዘቡም፡፡ በመጀመርያው ጥቅስ መሠረት የሰው ልጆች ሥራ ወደ ሰማይ የሚያርገው መጠኑ በሰው አቆጣጠር አንድ ሺህ ዓመት በሆነ ቀን ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መሠረት አንድ ሺህ የሰው ዓመት ከአንድ ቀን ጋር እኩል ነው፡፡ ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ መላእክት ወደ አምላክ የሚያርጉት መጠኑ በሰው አቆጣጠር ሃምሳ ሺህ በሆነ ቀን ውስጥ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህ በዚህ መሠረት ሃምሳ ሺህ የሰው ዓመት ከአንድ ቀን ጋር እኩል ነው፡፡

አቶ ሐሰን ይህንን ጉዳይ አቅልለው ለማሳየት ቢሞክሩም ሙስሊም ሊቃውንት ግራ የተጋቡበት ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አል ቁርጡቢ የተሰኘው ሙስሊም ሊቅ እንዲህ ብሏል፡-

“መላእክቱና መንፈሱም ልኩ አምሳ ሺሕ ዓመት በኾነ ቀን ውስጥ ወደ እርሱ ያርጋሉ” የሚለው አንቀፅ ከቀደመው አንቀፅ ጋር ይጋጫል (ሱራ 32፡5)፡፡ አብደላህ ኢብን ፋይሩዝ አል-ዲልሚ ስለዚህ አንቀፅ አብደላህ ኢብን አባስን ጠይቆት ነበር፡፡ … እርሱም ሲመልስ “እነዚህ ሃያል በሆነው አላህ የተጠቀሱ ቀናት ናቸው፣ ምን እንደሆኑም አላውቅም፡፡ ስለዚህ የማላውቀውን መናገር እጠላለሁ” አለ፡፡[14]

አል ቁርጡቢ ተመሳሳይ ምላሾችን የሰጡ ሌሎች ሙስሊም ሊቃውንትን ጠቅሷል፡፡ ጥንታውያን ሙስሊም ሊቃውንት እነዚህን አናቅፅ ማስታረቅ ቀላል እንዳልሆነ ስለገባቸው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ አቶ ሐሰን ግን እርግጠኛ ሆነው ይናገራሉ፡፡

  • ሃያ ወይስ መቶ?

ቁርኣን ስንት ሙስሊሞች ከስንት “ከሃዲያን” ጋር መዋጋት እንዳለባቸው የተለያዩ ትዕዛዛትን ይሰጣል፡-

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ምእምናንን በመዋጋት ላይ አደፋፍራቸው፡፡ ከእናንተ ውስጥ ሃያ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ፡፡ ከእናንተም መቶ ቢኖሩ ከእነዚያ ከካዱት እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች ስለኾኑ ሺህን ያሸንፋሉ፡፡” (ሱራ 8፡65)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ሃያ ሙስሊሞች ሁለት መቶን፣ መቶ ደግሞ አንድ ሺህን ይገጥማሉ፡፡ የዚህ ምጥንጥን አንድ ለአሥር ነው፡፡

“አሁን አላህ ከእናንተ ላይ አቀለለላችሁ፡፡ በእናንተ ውስጥም ድክመት መኖሩን ዐወቀ፡፡ ስለዚህ ከእናንተ መቶ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ፡፡ ከእናንተም ሺህ ቢኖሩ በአላህ ፈቃድ ሁለት ሺህን ያሸንፋሉ፡፡ አላህም ከታጋሾቹ ጋር ነው፡፡” (ሱራ 8፡66)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ መቶ ሙስሊሞች ሁለት መቶን፣ አንድ ሺህ ደግሞ ሁለት ሺህን እንደሚገጥሙ ተነግሯል፡፡ የዚህ ምጥንጥን አንድ ለሁለት ነው፡፡

አቶ ሐሰን እነዚህ ጥቅሶች ሙስሊሞች በተለያዩ የዝግጅት ደረጃዎች ላይ ባሉበት ሁኔታዎች ውስጥ ሊገጥሟቸው የሚችሏቸውን የጠላት መጠን የሚገልጹ እንጂ ግጭት እንዳልሆኑ አስረድተዋል (ገፅ 156)፡፡ ነገር ግን እነዚህን ትዕዛዛት ከግጭት ለመቁጠር የሚያበቃ ምክንያት አለ፡፡ ኢብን ኢስሐቅ የተሰኘው ዘጋቢ እንደተናገረው አላህ ይህንን ትዕዛዝ በሰጠበት ዕለት ሙስሊሞች ትዕዛዙ ስለከበዳቸው መደናገጣቸውንና አላህ ትዕዛዙን በሌላ ትዕዛዝ በመሻር ሁለተኛውን “መገለጥ እንዳወረደ” ዘግቧል፡፡[15] አላህ ሁሉን አዋቂ ከሆነ ትዕዛዙ እንደሚከብዳቸው አስቀድሞ በማወቅ ትክክለኛውን ትዕዛዝ ከማውረድ ይልቅ ተግባራዊ ሊሆን የማይችለውን አውርዶ እንደገና መሻር ለምን አስፈለገው?

ሁለተኛው ጥቅስ “አሁን አላህ ከእናንተ ላይ አቀለለላችሁ፡፡ በእናንተ ውስጥም ድክመት መኖሩን ዐወቀ” በማለት የአላህን ሁሉን አዋቂነት ከጥርጣሬ ውስጥ ይጨምራል፡፡ አላህ በሙስሊሞች ውስጥ ድካም መኖሩን ያወቀው ትዕዛዙን ከሰጠ በኋላ እንደሆነ ያስመስላልና፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] Guillaume. The Life of Muhammad; p. 99

[2] Sahih Al-Bukhari, Vol. 2, Book 23, Number 467 & 441

[3] Sahih Al-Bukhari; Vol. 1 Book 2, Number 24

[4] Sahih al-Bukhari, 52:260; 83:37; 84:57; 89:271; 84:58; Abu Dawud, 4346

[5] ሐሰን ታጁ፡፡ ሰይፉን ፍለጋ፤ ከመካ እስከ ቫቲካን፣ 2006፣ ገፅ 195፤ ሐሰን ታጁ፡፡ የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት፣ 2001፣ ገፅ 137-138

[6] ዝኒ ከማሁ

[7] ኢማም አን-ነወዊ፡፡ ሪያዱ ሷሊሒን፤ ከሐዲስ ቁጥር 811-1896፣ ቅፅ 2፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ፣ ገፅ 42፡፡ በተጨማሪም Sahih Muslim, 2167; Sahih al-Bukhari Book 25, Number 5389  ይመልከቱ

[8] Sunan Abu Dawud, Book 12, Number 2233; Al-Tirmidhi, Number 945 taken from the Alim CD-ROM Version

[9] The History of Al-Tabari: The Foundation of the Community; translated by M. V. McDonald, annotated by W. Montgomery Watt [State University of New York Press (SUNY), Albany 1987], Volume VII, pp. 24-25

[10] Tanwîr al-Miqbâs min Tafsîr Ibn ‘Abbâs; source፡ http://altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=73&tSoraNo=3&tAyahNo=45&tDisplay=yes&UserProfile=0

[11] Sahih Al-Bukhari, Vol. 4, Book 55, Number 657

[12] ለበለጠ መረጃ Sam Shamoun: www.Answering-Islam.Org/quran/contra/jesus_unlike_adam.html ይጎብኙ፡፡

[13] Tabari, VI pp. 150-151; Tafseer Ibn Katheer: http://tafsir.com/default.asp?sid=3&tid=7700

[14] Al-Qurtubi’s Tafseer, Online Edition: http://quran.al-islam.com/Tafseer/DispTafsser.asp?l=arb&taf=KORTOBY&nType=1&nSora=32&nAya=5

[15] Guillaume. The Life of Muhammad; p. 326

ለሐሰን ታጁ ምላሽ ዋናው ማውጫ