በሒርና ከተማ ሙስሊም ጂሃዳውያን በፈጸሙት ጥቃት አንድ ክርስቲያን ወጣት በከባድ ሁኔታ ቆሰለ
ጥቃቱ የደረሰው ከአዲስ አበባ 400 ኪ.ሜ. ርቃ በምትገኘው የሒርና ከተማ ሲሆን ለደህንቱ ሲባል ስሙ እንዲጠቀስ ያልተፈለገ አንድ የ27 ዓመት ክርስቲያን ወጣት በቤቱ ተቀመጦ ሳለ ገጀራ የያዙ ሙስሊሞች ባደረሱበት ጥቃት ለከባድ የመቁሰል አደጋ ተዳርጓል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁላይ 16/ 2017 በደረሰው በዚህ ጥቃት ወጣቱ ጭንቅላቱ አካባቢ ከደረሰው ከባድ ቁስለት የተነሳ አስቸኳ የነፍስ አድን ቀዶ ጥገና አስፈልጎታል፡፡ የአካባቢው ክሊኒክ ወደ አሰበ ተፈሪ ሆስፒታል የላከው ሲሆን ሆስፒታሉ ወደ አዳማ አስተላልፎታል፡፡ ህክምናው ከአቅም በላይ በመሆኑ ምክንያት የአዳማ ሆስፒታል ወደ አዲስ አበባ ማስተላለፍ የነበረበት ቢሆንም በመንገድ ላይ ሕይወቱ እንዳታልፍ የሰጋው ዶክተር አስቸኳይ ቀዶ ጥገና በማድረግ ሕይወቱን ሊያተርፍ ችሏል፡፡
ጥቃት አድራሾቹ ይህንን ጥቃት የፈፀሙበት ምክንያት ወጣቱ ለሙስሊሞች ወንጌልን ሰብኳል በሚል መነሻ እንደሆነ የዜናው ምንጭ ገልጿል፡፡ በቡድን የተደራጁት ሙስሊሞች መጀመርያ በአካባቢው በምትገኝ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት በመፈፀም በጣርያና ግድግዳ ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላ ወደ ግለሰቡ ቤት በማቅናት ጥቃቱን መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡
ኦፕን ዶርስ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም ባወጣው መረጃ መሠረት በፈረንጆቹ 2017 በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ጨምሮ ታይቷል፡፡ በመረጃው መሠረት በሰዎችና በመጓጓዣዎች ላይ የደረሱ አካላዊ ጥቃቶች፣ ግድያና ያለ ፍትህ መታሰርን ጨምሮ ከ100 በላይ ጥቃቶች ተፈፅመዋል፡፡
የዜናው ምንጭ World Watch Monitor ነው፡፡