መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ምዕራፍ ፪ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

ምዕራፍ ፪

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

አንድ መጽሐፍ ብዙ ተከታዮች ስላሉት ወይንም ደግሞ በውስጡ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚናገር ሐሳብ ስለ ተጻፈ ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ሊሆን አይችልም፡፡ መጽሐፍ  ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው ካልን ይህንን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ሊኖሩን ይገባል፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ደግሞ ሊነሱ የሚችሉ መስቀለኛ ጥያቄዎችን በሙሉ የማለፍ አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን አንድ ሐሳብ እንደ ማስረጃ መጠቀሱ በራሱ የሚፈጥረው ልዩነት አይኖርም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን የሚናገሩ እና ብዙ አማንያንን የሚያስከትሉ ኁልቈ መሣፍርት የሌላቸው መጻሕፍት በዓለማችን ላይ ይገኛሉ፡፡ በመካከላቸው ካለው ያለመጣጣም የተነሳ ከእነርሱ መካከል ሁለቱ እንኳ በአንድ ጊዜ እውነት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ መካከል ትክክለኛ ቃለ እግዚአብሔር ሊሆን የሚችለው አንዱ መጽሐፍ ብቻ ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ለይተን እናውቅ ዘንድ የሚያስችሉን የማያሻሙ፣ ግልፅ የሆኑ እና አብዛኞቹ ሰዎች ሊገነዘቧቸው የሚችሏቸው ማስረጃዎች ሊኖሩን ያስፈልጋል፡፡

አንዳንድ ኃይማኖቶች ቅዱሳት መጽሐፍታቸው እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ለማሳየት አሻሚ የሆኑና በግላዊ ስሜትና መረዳት ላይ የተመሰረቱ (Subjective) መስፈርቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የሞርሞን እምነት ተከታዮች አንድ ሰው በቅዱስ መጽሐፋቸው ላይ እጆቹን አድርጎ ቢፀልይ ልቡ አካባቢ የማቃጠል ስሜት እንደሚሰማውና በዚህ መፈተኛ ተጠቅሞ እውነተኛነቱን ማረጋገጥ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ሙስሊሞች ደግሞ ቁርኣን ከሁሉም መጽሐፍት የላቀ ሥነ ጽሑፋዊ ውበት ስላለው ይህ የፈጣሪ ቃል መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ይናገራሉ፡፡ ክርስቲያኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማረጋገጥ መሰል “ማስረጃዎችን” አይጠቅሱም፡፡ ከነዚህ ይልቅ ጠንካራ የሆኑ እና በግል ስሜት ላይ ያልተመሰረቱ (Objective) ማስረጃዎች አሉን፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ምንድናቸው? ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡-

የተፈጸሙ ትንቢቶች

ትንብያ ማለት ወደፊት የሚከሰቱ ሁኔታዎችን መናገር ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር እንደዚህ አይነት ስጦታን የሰጣቸው ሰዎች ነቢያት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከየትኛውም መመዘኛ ይልቅ ትንቢት ለቅዱሳት መጻሕፍት ትክክለኛነት እንደ ቋሚ መስፈርት ሊያገለግል ይችላል፡፡ ይህንን እውነታ በጥሩ ሁኔታ ሊያስረዳልን የሚችል ሀሳብ ዕውቁ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነት ጌርሃርድ ኔልስ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ እሳቸው ሀሳቡን የጠቀሱት ሚሽካት አል-መሳቢህ ከተሰኘ የሙስሊሞች መጽሐፍ መግቢያ ላይ ሲሆን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች እምነቶች ሊቃውንትም ጭምር ከላይ ከተቀመጠው አረፍተ ነገር ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ስለዚህም እንጠቅሰዋለን፡፡

“በተዓምራት ውስጥ ትንቢት ማለት ለወደፊት የሚሆኑ ነገሮችን አስቀድሞ መናገር ማለት ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ትንቢያ ሳይሆን ስለወደፊት ሚስጥራት ከመለኮታዊ ዕውቀት የሚመነጭ ንግር ነው፡፡ ትንቢት በሚከተለው ምክንያት ከሁም የላቀ (ተዓምር) ነው፡፡ ትንቢት በታሪክ ሊረጋገጥ ይችላል፣ ተዓምር ግን አይችልም፡፡ ተዓምራት የእግዚአብሔርን ኃይል ሲገልጹ ትንቢት ግን የእግዚአብሔርን የቅድሚያ እውቀት ይገልጻል፡፡ እውቀት ከኃይል እንደሚበልጥ ሁሉ ትንቢትም ከተዓምር ይበልጣል፡፡”[1]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡-

“በልብህም እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው።” ዘዳግም 18፡21-22

በሌላ ስፍራ ላይም እንደዚሁ ያህዌ እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል እንዲህ በማለት ይናገራል፡-

“እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።” ኢሳይያስ 42፡8-9

አሁንም ያህዌ እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል እንዲህ በማለት ይናገራል፣ በሐሰተኛ አማልክትም ይሳለቅባቸዋል፡

“የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ።” ኢሳይያስ 44:6-7

“ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ይላል እግዚአብሔር ማስረጃችሁን አምጡ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። ያምጡ፥ የሚሆነውንም ይንገሩን ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፥ የሚመጡትንም አሳዩን። አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ።” ኢሳይያስ 41፡21-23

አምላካችን እግዚአብሔር ለአምላክነቱ ያቀረበው አንዱና ትልቁ ማስረጃ የወደፊቱን የመናገር ችሎታውን ነው፡፡ እናም ይህ መስፈርት ከእርሱ የሆነው መጽሐፍና እውነተኛ ነቢያት የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ያገለግላል፡፡ ሐሰተኛ ነቢያትና ከእግዚአብሔር ያልሆኑ መጻሕፍት ስለ ወደፊቱ ሁኔታ በትክክል የማስታወቅ አቅም የላቸውም፡፡

ትክክለኛ የሆኑ ትንቢቶችን ትክክለኛ ካልሆኑ ትንቢቶች መለየት የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ አንድ “ትንቢት” ነገሩ ከተፈጸመ በኋላ ከተነገረ፣ ማንም ሰው በቀላሉ ሊገምተው የሚችለው አይነት ከሆነ (ለምሳሌ በሚቀጥለው ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሜዳልያ ያገኛሉ የሚል አይነት ለመፈጸሙ በከፊል ዋስትና ያለው ከሆነ)፣ ከሌሎች ምንጮች የተቀዳ ከሆነ፣ በጣም አጠቃላይ እንዲሁም አሻሚ መልዕክት ካለው እና ተናጋሪው እራሱ ሊፈጽመው ያቀደው ነገር ከሆነ እውነተኛ ትንቢት ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ትንቢት ነገሩ ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ የተነገረ ከሆነ እና የተባለውም ነገር በማያደናግር ሁኔታ በታሪክ ውስጥ ፍጻሜን ካገኘ፣ የተነገረው ትንቢት ከተናጋሪው ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ (ለመፈጸሙ የተናጋሪው ጥረት ሳይታከልበት) መፈጸም ከቻለ እንዲሁም አሻሚ ካልሆነ እንደ እውነተኛ ትንቢት ልንቀበለው እንችላለን፡፡

በማስከተል በሚገኙት ጥቂት ገጾች ውስጥ ከተፈፀሙ ብዙ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መካከል የተወሰኑትን እንመለከታለን፡:

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ ትንቢቶች

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለሚመጣው መሲህ የተነገሩ እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የተፈጸሙ ከ300 በላይ ትንቢቶች ይገኛሉ፡፡ ጆሽ ማክዱዌል የተሰኙ ክርስቲያን ሊቅ “Evidence That Demands a  Verdict” (ፍርድ የሚሻ ማስረጃ) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ 61 ትንቢቶችን ዘርዝረዋል፡፡ ከነዚህ ትንቢቶች መካከል ስምንቱን ብቻ ብትወስዱ ይላሉ ፕሮፌሰር ማክዱዌል፣ አንድ ሰው እነዚህን 8 ትንቢቶች የማሟላቱ አጋጣሚ ከ 1017 ወይንም ከ 100,000,000,000,000,000 ሰዎች አንድ ሰው ያህል ነው፡፡ ይህንንም በምሳሌ ሲያሰረዱ እንዲህ ይላሉ፡- የቴክሳስን ግዛት ብትወስዱ እና ከብር የተሰሩ ሳንቲሞችን ሁለት ጫማ ያህል ከፍታ እስኪኖረው ድረስ በግዛቱ ሁሉ ላይ ብታፈሱ፤ ከዚያም ከሳንቲሞቹ መካከል በአንዷ ላይ ምልክት አድርጋችሁ በግዛቱ ውስጥ በአንደኛው ስፍራ ብትቀብሩ፤ ከዚያም አንድ ሰው ወስዳችሁ አይኖቹን ብታስሩትና አንዷን የብር ሳንቲም እንዲያነሳ ብትነግሩት፣ በመጀመርያው ሙከራ ምልክት የተደረገባትን ሳንቲም የማንሳቱ እድል 1017 ነው![2]

የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከልደቱ ጀምሮ እስከ ትንሳኤው ድረስ ያለውን የጌታ ኢየሱስን ሕይወት በስፋት እና በዝርዝር ተንብየዋል፡፡ ከነዚህ በርካታ ትንቢቶች መካከል የተወሰኑትን በማስከተል እናቀርባለን፡፡

ልደቱን በተመለከተ

ከድንግል ስለመወለዱ፡

“ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ኢሳይያስ 7፡14

ፍፃሜው፡

በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል

ጌታችን ኢየሱስ በተወለደበት ስፍራ ላይ እንደተሰራ የሚታሰብ በቤተልሔም የሚገኝ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን (The Church of Nativity)

የፎቶ ምንጭ፡ wherejesuswalked.net

የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” (ሉቃስ 1፡26-38) በተጨማሪም ማቴዎስ 1፡17-25

በቤተ ልሔም ስለመወለዱ፡

“አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” (ሚክያስ 5፡2)

ፍፃሜው፡

እንደሚታወቀው ጌታችን ኢየሱስ በምድረ እስራኤል በተወለደበት ዘመን መላዋ እስራኤል በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች፡፡ የጌታ እናት ማርያም እና እጮኛዋ ዮሴፍ ይኖሩ የነበሩት ከዳዊት ከተማ (ከቤተ ልሔም) የሦስት ቀን መንገድ ያህል ርቃ በምትገኝ ናዝሬት በመባል በምትታወቅ ትንሽዬ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የብሉይ ኪዳን ትንቢት የሚናገረው መሲሁ በቤተ ልሔም ከተማ እንደሚወለድ ነው፡፡ በቤተልሔም ከተማ ያልተወለደ ማንም ሰው መሲህ መሆኑን ቢናገር  ከመሲሁ ምልክቶች መካከል በጣም ግልፅ እና አስፈላጊ የሆነውን መስፈርት ስለማያሟላ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ናዝሬት ከቤተ ልሔም ያላት ርቀት እና የጌታ እናት የማርያም የመውለጃዋ ወራት መቃረብ ከግምት ውስጥ ሲገባ ትንቢቱ ሊፈፀም የሚችልበት መንገድ ያለ አይመስልም ነበር፡፡ ነገር ግን የሉኣላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አረማዊ የሆነው የሮም ንጉስ አውግስጦስ ቄሣር በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ ወደየትውልድ ቦታዎቻቸው በመሄድ እንዲመዘገቡ ትዕዛዝ እንዲያወጣ አነሳሳው፡፡ ዮሴፍ እና ማያርም ሁለቱም ከዳዊት ቤት ወገን በመሆናቸው ምክንያት ለምዝገባ ወደ ዳዊት ከተማ መሄድ ነበረባቸው፡፡ መድኃኒት የሆነው ክርስቶስ ዮሴፍ እና ማርያም ቤተልሔም በደረሱባት ምሽት በመወለዱ ምክንያት ከልደቱ በፊት 500 ዓመታትን በመቅደም የተጻፈው ትንቢት ተፈፀመ!

“በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።” (ሉቃስ 2፡1-20) በተጨማሪም ማቴዎስ 2፡1-6

ሞቱን በተመለከተ

እንደሚገረፍ፣ እንደሚሰቀል

 

ጌታችን ኢየሱስ እንደተሰቀለበት እና እንደተቀበረበት በሚታመን ቦታ ላይ የተሰራ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን

የፎቶ ምንጭ: Oxford Bible Atlas, Fourt Edition

“የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፡፡ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፡፡ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር። 53፡1-10

ፍፃሜው፡

“በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ እየቀረቡም፡- የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም ደግሞ ወደ ውጭ ወጥቶ፡- እነሆ፥ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ አላቸው። ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም፡- እነሆ ሰውዬው አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፡- እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት አላቸው። አይሁድም መልሰው። እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት።” (ዮሐንስ 19፡1-7) በተጨማሪም ሉቃስ 23፡33-49

በሚስማር እንደሚቸነከር፣ ልብሱን እንደሚከፋፈሉ፣ በቀሚሱም ላይ እጣ እንደሚጣጣሉበት

“ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም። ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።” መዝሙር 22፡16-18

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሰዎችን በመስቀል ላይ ሰቅሎ መግደል የተጀመረው ፎኔሽያን በተሰኙ ሕዝቦች ሲሆን ጊዜው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት 600 ዓ.ዓ. አካባቢ ነበር፡፡ ሮማውያንም ይህንን ልማድ የወሰዱት ከነዚህ ሕዝቦች ነበር፡፡ ይህ ትንቢታዊ መዝሙር በንጉሥ ዳዊት የተጻፈው ከክርስቶስ ልደት በፊት 1000 ዓ.ዓ. አካባቢ በመሆኑ ስቅለት ባልተጀመረበት ዘመን ጸሐፊው እጆችን እና እገሮችን ስለመቸንከር መናገር መቻሉ በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡

ፍፃሜው፡

“ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።” ዮሐንስ 19፡23-25

ቀጥሎ የሚገኘው በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረ ትንቢት ገና ያልተፈፀመ ሲሆን የክርስቶስን መወጋት እግረ መንገዱን የሚጠቅስ ነው፡-

“በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል።” ዘካርያስ 12፡10

ነቢዩ ዘካርያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት 500 ዓመታት ያህል ቀደም ብሎ የኖረ ሲሆን እስራኤላውያን ባለማወቅ የወጉት ሲጠብቁት የነበሩትን መሲህ መሆኑን በመገንዘብ ብሔራዊ ንስሐ የሚገቡበት እና ለሰሩት ስህተትም የሚያለቅሱበት ቀን እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ትንቢት ገና በመጨረሻው ዘመን እንደሚፈፀም የሚጠበቅ ቢሆንም መሲሁ ከመሰቀሉ በፊት የተነገረ በመሆኑ እና መወጋቱን የሚጠቅስ በመሆኑ በከፊል ተፈፅሟል፡፡ እንደሚፈፀም የሚጠበቀውም ክፍል ወደፊት ጊዜው ሲደር ለመፈፀሙ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ከሙታን እንደሚነሳ

“እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።” ኢሳይያስ 53፡10-12

“ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ።” መዝሙር 16፡8-11

ፍፃሜው፡

“ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ። ቃሎቹንም አሰቡ፥ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው።” ሉቃስ 24፡1-9

“እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አሥነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ። ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አሥነ ሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” የሐዋርያት ሥራ 2፡23-32

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ዕውቅ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነት ጀስሊን ማክዱዌል (ጆሽ ማክዱዌል በሚለው ስማቸው ይበልጥ ይታወቃሉ) በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተነገሩትን ትንቢቶች በሚገባ የመረመሩና በመጻሕፍቶቻቸው ውስጥ ያሰፈሩ ሰው ናቸው፡፡ “ፍርድ የሚሻ ማስረጃ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ካስቀመጧቸው ስለ ጌታ ኢየሱስ ከተነገሩ ትንቢቶች መካከል አንዱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል ጥፋትም ተቀጥሮአል።” ዳንኤል 9፡24-27

በዳንኤል 9፡24-27 ላይ የኢየሱስን መምጣት አስመልክቶ በትንቢት የተቀመጠ የጊዜ መስመር አለ፡፡ ትንቢቱንና በ70 ሱባኤዎች የተቀመጠውን የጊዜ መለክያ ለመረዳት ስለ ሱባኤ ያለውን የአይሁድ ፅንሰ ሐሳብ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ “ሱባኤ” ለሚለው ቃል የእብራይስጥ አቻው “ሻቡአ” የሚል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎምም “ሰባት” ማለት ነው፡፡ በእብራይስጥ የ70 ሱባኤዎች እሳቤ ሰባት ጊዜ ሰባ (ዓመታት) ነው፡፡ መሲሁን በተመለከተ ትንቢቱ በሶስት ክፍሎች ቀርቧል፡፡ የመጀመርያው ክፍል እንደሚናገረው በ69 ሱባኤዎች መጨረሻ ላይ መሲሁ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣል፡፡ (ሰባት እና 62 ሱባኤዎች 69 የሰባት አመታት ጊዜ ነው የሚል ግንዛቤ አለ፡፡) የስድሳ ዘጠኙ ሱባኤዎች የጅማሬ ነጥብ ኢየሩሳሌምን የማደስና እንደገና የመገንባት አዋጅ ነው፡፡ ቀጥሎ ባለው ጥቅስ መሠረት ይህ አዋጅ የወጣው በ444 ዓ.ዓ. እንደ ነበር እንገነዘባለን፡-

“በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር…” ነህምያ 2፡1

አርጤክስስ የነገሠው በ465 ዓ.ዓ. ነበር፡፡

በዚህ ስፍራ ቁርጥ ያለ ቀን ባለመነገሩ እንደ አይሁድ ልማድ መሠረት ይህንን ቀን የምንረዳው የወሩ የመጀመርያው ቀን እንደሆነ ነው፣ ማለትም ኒሳን 1/ 444 ዓ.ዓ.፡፡ ይህ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 5/444 ዓ.ዓ. ይሆናል፡፡ (ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩት ዓመታት ወደ ኋላ እንደሚቆጠሩ ልብ ይሏል፡፡)

ሁለተኛው የትንቢቱ ክፍል መሲሁ ከመጣ በኋላ እንደሚገደል ይናገራል፡፡ ከዚያም የሚመጣው አለቃ ኢየሩሳሌምንና ቤተመቅደሱን ያጠፋል፡፡

በዳንኤል 9፡24-26 መሠረት ይህ ሁሉ የሚሆነው ከ69 ሱባኤዎች በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን ዳንኤል 9፡24 69 ብቻ ሳይሆን 70 ሱባኤዎችን ይጠቅሳል (7+62+1)፡፡ በ9፡27 ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻው ሱባኤ ገና ወደሚመጣ ሌላ ሰው የሚያመለክት ይመስላል፡፡

ስለዚህ በነቢዩ ዳንኤል ትንቢት መሠረት ኢየሩሳሌምን ለመጠገንና ለመስራት አዋጅ ከወጣበት ጊዜ፤ ማለትም ከኒሳን 1/444 ዓ.ዓ. ጀምሮ መሲሁ ወደ ኢየሩሳሌም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ 483 ዓመታት (69×7) ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ አመት 360 ቀናት ካሉት የአይሁድ ዓመት ጋር እኩል ነው፡፡ (ይህም በአጠቃላይ 173,880 ቀናት ይሆናል፡፡)

የስድሳ ዘጠኙ ሱባኤዎች ፍፃሜ በዘካርያስ 9፡9 ላይ በተተነበየው መሠረት የክርስቶስ ራሱን እንደመሲሁ ለእስራኤል መግለጥ ነው፡፡ በዳንኤል ውስጥ የሚገኘውን ይህንን ትንቢት እና ተያያዥ የሆኑ ጊዜያትን የመረመሩ ኤች ሆኤህነር የተሰኙ ሊቅ[3] የክስተቱን ጊዜ እንደሚከተለው አስልተውታል፡-

“ስድሳ ዘጠኙን ሱባኤዎች እያንዳንዳቸውን በሰባት ዓመታት እና እያንዳንዱን አመት በ360 ቀናት ብናባዛ 173,880 ቀናትን እናገኛለን፡፡ በዚህ መሠረት በ444 ዓ.ዓ. እና በ33 ዓ.ም. መካከል ያለው ልዩነት 476 የፀሐይ ዓመታት ናቸው፡፡ 476ን በ365.24219879 ወይም በ365 ቀናት፣ 5 ሰዓታት፣ 48 ደቂቃዎች፣ 45.975 ሴኮንዶች ብናባዛ [በአንድ ዓመት ውስጥ 365  1/4 ቀናት ናቸው ያሉት] የምናገኘው ውጤት 173,855 ቀናት፣ 6 ሰዓታት፣ 52 ደቂቃዎች፣ 44ሴኮንዶች፣ ወይንም 173,855 ቀናት ይሆናሉ፡፡ ይህ በ444 ዓ.ዓ. እና በ33 ዓ.ም. መካከል መቆጠር የነበረባቸውን 25 ቀናት ብቻ የሚያስቀር ይሆናል፡፡ ሃያ አምስቱን ቀናት በመጋቢት 5 (444 ዓ.ዓ.) ላይ ብንደምር ኒሳን 10/ 33 ዓ.ም. ወደ ሆነው ወደ መጋቢት 30 (33 ዓ.ም.)  እንመጣለን፡፡ ይህም ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት እለት ነው፡፡”

ስድሳ ዘጠኙ ሱባኤ ከመደምደሙ በፊት እና ሰባኛው ሱባኤ ከመግባቱ በፊት ሁለት ክስተቶች መታየት አለባቸው፡- የመሲሁ ሞት (ዳንኤል 9፡26) እና የኢየሩሳሌምና የቤተመቅደሱ (በሮማዊው) ልዑል (ታይተስ ወይም ቲቶ) በ70 ዓ.ም. ላይ መደምሰስ ነው፡፡ ስሌቶቹ በሙሉ እና የአዋጁ በ444 ዓ.ዓ. መውጣት ትክክል ከሆነ ክርስቶስ የተሰቀለው ወደ ኢየሩሳሌም በክብር መግባቱን ተከትሎ ሚያዝያ 3/33 ዓ.ም. ነው የሚሆነው፡፡[4]

ከላይ የተቀመጠው ትንታኔ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ ይዘት ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ በዓለማችን ላይ የሚገኝ የትኛውም የኃይማኖት መጽሐፍ እንደዚህ ዓይነት ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ትንቢታዊ ይዘት የለውም፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

የባቢሎንን ምርኮ በተመለከተ ኤርሚያስ የተናገረው ትንቢት

በቅጽል ስሙ “አልቃሻው ነቢይ” በመባል የሚታወቀው ነቢዩ ኤርምያስ በነቢይነት ያገለገለው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ626 ዓ.ዓ. አካባቢ ነበር፡፡ የይሁዳ ህዝብ ከኃጢዓታቸው እንዲመለሱና ንስሐ እንዲገቡ እግዚአብሔር በተደጋጋሚ ነቢያቱን ልኮ ቢናገራቸውም ሊመለሱ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የባቢሎንን ንጉስ ናቡ ከደነፆርን እንደሚያመጣባቸው እና ይሁዳም እንደምትሸነፍ፣ ምድራቸውም እንደምትጠፋ፣ ተማርከውም ወደ ባቢሎን ለ70 ዓመታት ያህል እንደሚወሰዱ፣ ሰባው ዓመት በተፈፀመ ጊዜ ግን ባቢሎን እንደምትሸነፍ፣ ጌታም የይሁዳን ህዝብ ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ቅድስት አገር እንደሚመልሳቸው ነቢዩ ኤርምያስ ተናግሮ ነበር፡፡ (ኤርምያስ 25፡8-14፣ 29፡10-11)

በዚህ ትንቢት ውስጥ የተነገረ የትኛውም ነጥብ አሻሚ አይደለም፤ እንዲሁም እነዚህ የተነገሩ ነገሮች ከኤርምያስ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ እና በራሳቸው ጊዜና ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በእርሱ ግፊት ወደ ፍጻሜ ሊመጡ የሚችሉ ነገሮች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ፍፃሜው

ይህ የምትመለከቱት የሸክላ ማህተም በ1975 ዓ.ም. በቁፋሮ የተገኘ የባሮክ ወልደ ኔርያ ማህተም ነው፡፡ ባሮክ በወቅቱ የነቢዩ ኤርምያስን ትንቢቶች ሲጽፍ የነበረ ጸሐፊ ነበር (ኤርምያስ 36፡4)፡፡ የዚህ ማህተም መገኘት የትንቢተ ኤርምያስን መጽሐፍ ታሪካዊነት ያረጋግጣል፡፡

የፎቶ ምንጭ፡ biblicalstudies.info

 ሥነ ቁፋሮ እና የጥንታዊ ታሪክ ጥናት እንዳረጋገጡት ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ይህ ትንቢት በትክክል ተፈፅሟል፡፡ በዚህም መሠረት በ606 ዓ.ዓ. (ትንቢቱ ከተነገረ ከ20 ዓመታት በኋላ) የናቡ ከደነፆር ወታደሮች ይሁዳን እንደወረሩ እና (ሌሎች ህዝቦችን ጨምሮ) በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁድን ወደ ባቢሎን ማርከው መውሰዳቸውን እንመለከታለን፡፡ የምርኮውም ሁኔታ ኢየሩሳሌም በ605 ዓ.ዓ. እስክትፈርስ ድረስ እና የይሁዳ ህዝብ በሙሉ ተማርኮ እስኪሄድ ድረስ ቀጥሏል፡፡ ይህ የአይሁድ ህዝብ የምርኮ ዘመን ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን አገዛዝ ስር እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ የቆየ ሲሆን ነቢዩ ኤርምያስም በ595 ዓ.ዓ. የተናገረው ተያያዥ ትንቢት (የባቢሎን በሜዶናውያን ስር መውደቅ) በዚሁ ፍፃሜን አግኝቷል፡፡ ከዚያም የፋርስ (የአሁኗ ኢራን) ንጉስ የነበረው ቂሮስ አይሁድ ወደ ሃገራቸው ይመለሱ ዘንድ በ536 ዓ.ዓ. አዋጅ አወጣ፡፡ በዚህም መሠረት ብዙ አይሁድ ወደ ቅድስት አገር ተመልሰዋል፡፡ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ሁሉም ይመለሳሉ የሚል የተስፋ ቃል ስላልተሰጠ ፍቃደኛ የሆነ ብዙ ህዝቦች ተመልሰዋል፡፡ ምርኮውም እንደተባለው በ70 ዓመት አናቱ ላይ ተጠናቋል፡፡ ይህ እጅግ የሚያስደንቅ ትንቢት ነው፡፡

የእስራኤላውያን እንደገና ወደ ምድራቸው መመለስ እና የእስራኤል መንግሥት ምስረታ

በዓለም ታሪክ እንደ አይሁድ ሕዝብ የተሰደደና መከራ የደረሰበት ሕዝብ የለም ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡ የጥንቱን ዓለም ታሪክ ስናጠና ከአይሁድ ሕዝብ በላይ ጠንካሮች የነበሩ ብዙ ሕዝቦች ከምድረ ገፅ ጠፍተዋል፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ግን የደረሰበትን መከራና እንግልት ሁሉ ተቋቁሞ በዚህ ባለንበት ክፍለ ዘመን በወታደራዊ ኃይልና በቴክኖሎጂ በዓለም ላይ ጠንካሮች ከሚባሉ ሕዝቦች ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡ በእርግጥ የዚህ በአንድ ወቅት አገር አልባ የነበረ ሕዝብ ታሪክ ለብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች በእጅጉ እንቆቅልሽ ነው፡፡ የአይሁድን ታሪክ ትኩረት ሰጥቶ ያጠና ሰው ከዚህ ሕዝብ በስተጀርባ አንዳች መለኮታዊ ኃይል መኖሩን መገንዘቡ አይቀርም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል የሚከተለውን ብለው ነበር፡-

“አንዳንድ ሰዎች አይሁድን ይወዷቸዋል አንዳንዶች ደግሞ ይጠሏቸዋል ነገር ግን በዓለም ላይ ከታዩ በጣም ጠንካራና አስገራሚ ሕዝቦች መካከል ግንባር ቀደም መሆናቸውን የሚክድ አሳቢ ሰው አይኖርም”[5]

በረሃብ የተጎዱ እስረኞች በማኡታውሰን የማጎርያ ካምፕ ውስጥ፡፡ እነዚህ እስረኞች የናዚን ሰራዊት መሸነፍ ተከትሎ ግንቦት 1945 ዓ.ም. ነፃ የወጡ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በነዚህ የማጎርያ ካምፖች ውስጥ ወደ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁድ በአሳቃቂ ሁኔታ በግፍ ተጨፍጭፈዋል፤ ሌሎች ብዙዎች ደግሞ አካላቸው በጣም በሚዘገንን ሁኔታ እየተቆራረጠ ለተለያዩ ምርምሮችና ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ውሏል፡፡

የፎቶ ምንጭ፡ wikipedia.net

ዘሌዋውያን 26፡14-16 ላይ እንደምናነበው ትዕዛዛቱን በጥንቃቄ የማይከተሉ ከሆነ ሊደርስባቸው የሚችለውን አስፈሪ ቅጣት እግዚአብሔር በባርያው በሙሴ በኩል ይነግራቸዋል፡፡ ከተዘረዘሩት ቅጣቶች መካከልም በጠላት ተማርኮ መወሰድ እና በባዕድ ምድር በታላቅ ውርደት ውስጥ መኖር ይገኝበታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እና በሌሎች ብዙ የታሪክ መዛግብት ውስጥ ተጽፎ የምናየው የእስራኤላውያን ታሪክ እንደሚመሰክረው ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት እግዚአብሔር በባርያው በሙሴ እና በሌሎች ነቢያት በኩል የተናገረው የቅጣት አይነት ሁሉ ደርሶባቸዋል፡፡ በተለይ ዘሌዋውያን ምዕራፍ 26ን አንብቦ አይሁድ በክፍለ ዘመናት መካከል ካሳለፏቸው ታሪኮች ጋር ያነጻፀረ ሰው በእጅጉ መደመሙ አይቀርም፡፡ ነገር ግን በዚያው ምዕራፍ ቁጥር 44 ላይ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ፈፅሞ የማያጠፋቸው መሆኑን እንዲህ በማለት ይናገራል፡-

ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም። እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸውን የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስባለሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

በአንድ ወቅት ሲገዟቸው የነበሩ አሦራውያን፣ ባቢሎናውያንና ሮማውያንን የመሳሰሉ ኃያላን ሕዝቦች ስልጣኔዎቻቸው ደብዛቸው ሲጠፋ አይሁድ ግን የደረሰባቸውን መከራና እንግልት ሁሉ ተቋቁመው ሕልውናቸው ሳይጠፋ እስከዛሬ ድረስ መቆየታቸው ብሎም እንደ ሕዝብና መንግሥት ተደራጅተው በራሳቸው አገር ተመልሰው መኖር መጀመራቸው የእግዚአብሔር ተዓምራዊ ስራ ከመሆን ውጪ ሌላ ማብራርያ ሊኖረው አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሁሉ ክስተቶች አስቀድሞ መተንበዩ ደግሞ ከዚህ ሕዝብ ታሪክ በስተጀርባ መለኮታዊ ኃይል መኖሩን ያረጋግጣል፤ መጽሐፉም ደግሞ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህንን በተመለከተ ከተጻፉ ትንቢቶች መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡-

እስራኤላውያን ከየሃገሩ ይሰበሰባሉ

“የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ አታክልትንም ያበጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር” አሞፅ 9፡14-15

ነቢዩ አሞፅ የእስራኤላውያንን በድጋሜ ወደ ምድራቸው መመለስ ከተናገረ በኋላ ከእንግዲህ ወዲህ ከምድራቸው ላይ ፈፅሞ እንደማይነቀሉ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት እስራኤል ያላትን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የቴክኖሎጂ አቅም ስንመለከት አንዳች መለኮታዊ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር በዙርያዋ የሚገኙት ጠላቶችዋ እንደሚያልሙት ከዓለም ካርታ ላይ ልትፋቅ እንደማትችል ግልፅ ነው፡፡

“ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል። የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ። የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ። ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል።” ኢሳይያስ 60፡4-9

በዚህ ትንቢት ውስጥ እንደተመለከተው የተበተኑት አይሁዳውያን በየብስ ብቻ ሳይሆን በባህርና በአየርም ጭምር ወደ ምድራቸው ይመለሳሉ፡፡ አውሮፕላን ባልተሠራበት ዘመን ሰዎች በአየር ላይ እየበረሩ ወደ ምድራቸው እንደሚመለሱ ነቢዩ መናገር መቻሉ በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ትንቢት የተፈፀመና ገና ሊፈፀም ያለ ገፅታ እንዳለው ልብ ይሏል፡፡

“አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።  ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም። አትከልክል ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።” ኢሳይያስ 43፡1-7

ከላይ በተጠቀሰው ትንቢት ውስጥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከአራቱም የምድር ዋልታዎች እንደሚሰበስብ ይናገራል፡፡ በዚህም መሠረት ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ ሃገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተበትነው ይኖሩ የነበሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአይሁድ ትሩፋን ወደ ቅድስት አገር ተመልሰዋል እየተመለለሱም ይገኛሉ፡፡ ራሽያ፣ አሜሪካና ደቡብ አፍሪካን ከመሳሰሉ ከእስራኤል እጅግ ከራቁ አገራት እንኳ ሳይቀር ብዙዎች ተመልሰው አባቶቻቸው ከ2000 ዓመታት በፊት በግዳጅ በተፈናቀሉባት ምድር ኑሯቸውን መስርተዋል፡፡ የሚከተለው ትንቢት እንዲሁ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖሩ አይሁድ የሚናገር ሲሆን ዛሬ ተፈፅሞ በአይኖቻችን የምንመለከተውን እውነታ ያንፀባርቃል፡- “ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል።” ሶፎንያስ 3፡9

የእስራኤል መንግሥት በአንድ ቀን እንደምትመሠረት

“ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና።” ኢሳይያስ 66፡8

የእስራኤል የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴቪድ ቤን-ጉሪዮን የእስራኤልን መንግሥት ምስረታ ሲያበስሩ (ግንቦት 14/1948)፡፡ ከእሳቸው በላይ ተሰቅሎ የሚታየው ፎቶ ግራፍ የእስራኤልን መንግሥት የምስረታ ራዕይ ያስቀመጠው እና የፅዮናውያን ንቅናቄ መስራች የሆነው በትውልዱ ደግሞ ኦስትሪያዊ የሆነው አይሁድ ጋዜጠኛ ቴዎዶር ሄርዝል ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው የኢሳይያስ ትንቢት ግንቦት 14/1948 ዓ.ም. የሆነውን ታሪካዊ ክስተት በትክክል የሚገልፅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚያን ዕለት ባልተጠበቀ ሁኔታ በብዙ ምዕተ ዓመታት የእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የእስራኤል ነፃ መንግሥት ታወጀ፡፡  ይህ አዋጅ በወጣበት በዚያኑ እለት አሜሪካ ለሉኣላዊቷ የአይሁድ መንግሥት ዕውቅናን የሰጠች ሲሆን ይህ ሁሉ ከመሆኑ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካባቢውን ታስተዳድር ዘንድ ለብሪታኒያ የሰጠው ውክልና የጊዜ ገደቡ ተጠናቆ ነበር፡፡ በዓለም ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ በዙርያዋ ካሉ ከእርሷ እጅግ ከገዘፉ ጠላቶቿ ራሷን በብቃት መከላከል የቻለች አገር በአንድ ጀምበር ተመስርታ በሁለት እግሮችዋ መቆም ቻለች፡፡ ይህም ለብዙዎች ድንቅ ነው፡፡

እንግዲህ ከላይ የተመለከትናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ በመቶዎች ከሚቆጠሩ አስደናቂ ትንቢቶች መካከል የተወሰኑት ብቻ ናቸው፡፡ ማንኛውም ፍላጎቱ ያለው አንባቢ በዚህ ርዕስ ላይ የተጻፉ ሌሎች ጽሑፎችን ማንበብ ይችላል፡፡ እነዚህን እውነታዎች በጥንቃቄ ካጠና በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በሌሎች መለኮታዊ ምንጭ በሌላቸው ኃይማኖታዊ መጻሕፍት ደረጃ ላይ የሚያሰቀምጥ ወይንም ደግሞ መለኮታዊነቱን የሚክድ ፍትሐዊ ፍርድ መስጠት የሚችል ባለ አዕምሮ ይኖራል የሚል ግምት የለንም፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] ጌርሃርድ ኔልስ፡ ለሙስሊሞች ጥያቄዎች የክርስቲያኖች መልሶች ገፅ 59

[2] Josh McDowell, Evidence That Demands a Verdict, Vol. 1, pp.144, 167

[3] H.Hoehner, Chronological Aspect of the Life of Christ, Zondervan Publishing

[4] Evidendce That Demands a Verdict pp. 197-201

[5] Sinclair-Stevensohn, The Controversy of Zion, London, 1996, X1

መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ዋናው ማውጫ