መጽሐፍ ቅዱስ
ወደር የማይገኝለት ግሩም መጽሐፍ!
መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ የተለየ መጽሐፍ ነው።
- በስርጭት ደረጃ ወደር የማይገኝለት የምን ጊዜም ምርጥ መጽሐፍ ነው፡፡
- በብዙ ሰዎች በመነበብና በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ ወደር የማይገኝለት መጽሐፍ ነው፡፡
- የሥነ ቁፋሮና የታሪክ ምሑራን ትክክለኛነቱን ደግመው ደጋግመው አረጋግጠዋል፡፡ አንድ ዕውቅ የሥነ ቁፋሮ ምሑር እንዲህ አለ “የመጽሐፍ ቅዱስን መረጃ የተጻረረ አንድም የሥነ ቁፋሮ ግኝት እንዳልተገኘ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡” (1)
- ያጠኑትና ያመኑት ሰዎች እስከ ዛሬ ከተጻፉት መጻሕፍት መካከል ምርጡ መጽሐፍ መሆኑን ይመሰክሩለታል፡፡ የእግዚአብሔርን የልብ ሐሳብ ለማግኘት የምናነበው ብቸኛው መጽሐፍ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት ሕብረት ሊኖረን እንደሚችልና ከእርሱ ጋር ሕብረታችንን እንዴት ማሳደግ እንደምንችል ይነግረናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው?
መጽሐፍ ቅዱስ ጥምር ደራሲያን አሉት፡፡ አንደኛው ደራሲ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ነገር ግን ደረቅ በሆነ መንገድ መገለጡን በንግግር ከመግለጥ ይልቅ ለሰዎች በመግለጥና እነርሱን በማነሳሳት በራሳቸው ቃልና የአጻጻፍ ስልት እንዲጽፉ አድርጓል፡፡
“ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡” (2ጴጥ. 1፡20-21)
መጽሐፍ ቅዱስን እግዚአብሔር ስለገለጠው ሰብዓውያን ደራሲያንን ከስህተት እንደጠበቃቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ መርጠን የምንጥለው ምንም ነገር የለም፡፡ ጌታ ኢየሱስን የምንከተል ከሆን አጠቃላዩን መጽሐፍ ቅዱስ እርሱ በሚያየው መንገድ ልናይ ይገባናል፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡-
“እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፡፡ እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ፡፡” (ማቴ. 5፡17-18)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለምን ተጻፈ?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በዘመናት መካከል ከሕዝቡ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ይነግረናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ለምን ይነግረናል? የማወቅ ጉጉታችንን ለማርካት ነውን? በፍፁም! ለምን እዚህ እንደተገኘን፣ እርሱ ማን እንደሆነ፣ ከእርሱ ጋር እንዴት መገናኘት እንደምንችልና እንዴት መኖር እንዳለብን ሊነግረን ስለፈለገ ነው፡፡
“ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡” (መዝ. 119፡105)
ያለ እግዚአብሔር ቃል ይህንን ሁሉ ማወቅ አንችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ለሕይወት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል ካልሆነ በስተቀር ሳይንስ ለሕይወት ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጠን አይችልም፡፡
ኤርዊን ሽሮዲንጀር የተሰኘ የኖቤል ተሸላሚ የፊዚክስ ምሑር በሳይንሱ ዓለም እጅግ ወሳኝ ቀመር ሊባል የሚችለውን ቀመር የፈጠረና የሞገድን ንቅናቄ ያገኘ ሰው ነበር፡፡ ለሳይንስ ፍቅር ቢኖረውም ውሱንነት እንዳለበት ያውቅ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ሳይንስ ስለ እውኑ ዓለም ያለው ዕይታ ጎደሎ መሆኑ በጣም አስገርሞኛል፡፡ ብዙ መረጃዎችን ይሰጣል፣ ልምዶቻችንን ሁሉ አስገራሚ መስመር አስይዞ ያብራራልናል፣ ነገር ግን ለልባችን ቅርብ በሆነው ወሳኝ ጉዳይ ዙርያ ጸጥ ብሏል፡፡ ስለ ቀይና ስለ ሰማያዊ፣ ስለ መራራና ስለ ጣፋጭ፣ ስለ አካላዊ ስቃይና ስለ ደስታ ምንም አይነግረንም፡፡ ስለ ቆንጆና ስለ አስቀያሚ፣ ስለ ጥሩና ስለ መጥፎ፣ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ዘላለም ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሳይንስ አንዳንዴ ጥያቄዎችን ጠቅለል አድርጎ የሚመልስ ይመስላል ነገር ግን መልሶቹ ብዙ ጊዜ ደካማ ከመሆናቸው የተነሳ ትኩረት እንኳ የሚስቡ አይደሉም፡፡” (2)
ሌሎች ደግሞ ለሕይወት ጥያቄዎች በፍልስፍና በኩል መልስ የሚያገኙ ይመስላቸዋል፡፡ ፍሬድሪክ ኮፕለስቶን በሰው ልጆች ታሪክ ከተነሱት ታላላቅ ፈላስፎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ሲሆን ስለ ፍልስፍና ታሪክ የጻፈው በጣም የተሟላና አድናቆትን ያተረፈው ድርሰቱ ይገኝበታል፡፡ በጥቃቅን ፊደሎች ጽፎ ያሳተመው ባለ 17 ቅፅ መጽሐፉ “የሃያኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ምሑራዊ አበርክቶት” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ (Genete Weigel)
ለሰባ ዓመታት ያህል በፍፁም ልቡ ፍልስፍናን ካጠና በኋላ ለሕይወት ጥያቄዎች መልስ አግኝቶ ይሆን? ከመሞቱ ከአንድ ዓመት በፊት በታተመው ግለ ታሪኩ ውስጥ በሕይወቱ ውስጥ የሚያስፈልጉትን መልካም ነገሮች በማቅረብ ረገድ ፍልስፍናን ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ማግኘቱን አስነብቧል፡፡ ጥሩ ጭንቅላት የተባሉት እንኳ ውሱንነቶች ስላሉባቸው “ያለጥርጥር ሃይማኖታዊ መገለጥ ያስፈልጋቸዋል…” በማለት ጽፏል፡፡ (3)
ያ የእግዚአብሔር መገለጥ በሕይወታችን ውስጥ ያለው ቦታ ምንድነው? በኮትለስቶን መሠረት “… እግዚአብሔር ያንን ወይም ይህንን እውነት የገለጠው የሆነ አጓጊ ዕውቀትን ከመስጠት አኳያ ብቻ አይደለም፡፡ መለኮታዊ መገለጥ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነው የመጣው፡፡ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሕይወት እንዲሆንላቸውና እንዲበዛላቸው መምጣቱን መናገሩ ተጽፏል፡፡” (4)
ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን በቃሉ በኩል ገልጧል፡፡
እንዴት ነው የተዋቀረው?
የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብሉይ ኪዳን ተብሎ ይታወቃል፡፡ አራት ክፍሎች አሉት፡፡
ፔንታቱክ ወይም ሕግ (ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም) የፍጥረትን አጀማመር በመተረክ ይጀምራል፡፡ ስለ አይሁድ ሕዝብ አመጣጥ ይተርካል፡፡ በሙሴ መሪነት ከባርነት ተዓምራዊ በሆነ መንገድ መውጣታቸውንና የአሥርቱን ትዕዛዛት አመጣጥ ይተርካል፡፡
የታሪክ መጻሕፍት (ከኢያሱ እስከ አስቴር) ከሙሴ ሞት በኋላ እስራኤላውያን መጀመርያ በኢያሱ ተመሩ፤ ከዚያም በመሳፍንት፡፡ ከመሳፍንት ዘመን በኋላ አንዳንዴ መልካም አንዳንዴ ደግሞ ክፉ የነበሩት ነገሥታት ነገሡባቸው፡፡ “በዓይኖቻቸው ፊት መልካም መስሎ የታያቸውን” ብቻ በማድረጋቸው ሳብያ እግዚአብሔር ባዕዳን እንዲገዟቸው አደረገ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ አምላካቸው ስለተመለሱ ምሕረቱ የማያልቀው አምላካቸው ወደ ምድራቸው መለሳቸው፡፡
የቅኔ ወይም የጥበብ መጻሕፍት (ከኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን) እነዚህ ጽሑፎች የዳዊት የጸሎት ጽሑፎችን (መዝሙራት) እና የሰለሞን የጥበብ ጽሑፎችን (ምሳሌዎችን) ያጠቃልላሉ፡፡
ነቢያት (ከኢሳይያስ እስከ ሚልኪያስ) ነቢያት አንዳንዴ መፃዒ ነገሮችን ቢናገሩም ወቅታዊ መልእክቶችን ከእግዚአብሔር በመቀበልና ለሕዝቡ በመንገር ይታወቃሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ አምስት መጻሕፍት “ዋና (አበይት) ነቢያት” ሲባሉ የመጨረሻዎቹ አሥራ ሁለቱ ደግሞ “ደቂቃን ነቢያት” በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ቃላት ከነቢያቱ አስፈላጊነትና ከመልካምነታቸው ጋር የተያያዙ ባለመሆናቸው ግራ መጋባት የለብንም፡፡ አበይት ነቢያት ከደቂቃን ነቢያት መጻሕፍት የረዘሙ መጻሕፍትን በመጻፈቸው ብቻ ነው ይህንን ስያሜ ያገኙት፡፡
ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አዲስ ኪዳን በመባል ይታወቃል፡፡ እርሱም አራት ክፍሎች አሉት፡፡
ወንጌላት (ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ) በአራት ሰዎች የተጻፉ የኢየሱስ ሕይወት ዘገባዎች ናቸው፡፡ ጸሐፊያኑ ከኢየሱስ ጋር አብረው የኖሩ ወይንም ደግሞ የእርሱን ሕይወት ከዐይን ምስክሮች በጥልቀት ያጠኑ ናቸው፡፡
የሐዋርያት ሥራ የመጀመርያይቱን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይናገራል፡፡
መልዕክቶች (ከሮሜ እስከ ይሁዳ) የክርስትናን ሕይወት እንዴት መረዳትና መኖር እንዳለብን ያብራራሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ አሥራ ሦስቱ በሐዋርያው ጳውሎስ የተጻፉ ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ስምንቱ (አጠቃላይ መልዕክታት) በሌሎች አምስት ጸሐፊያን የተጻፉ ናቸው፡፡
የዮሐንስ ራዕይ ስለ ኢየሱስ ዳግም ምፅዓት፣ ስለ ዓለም ፍፃሜና እግዚአብሔር ስለሚያመጣቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የሚናገር በጣም ትዕምርታዊ የሆነ የትንቢት መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ ቅደም ተከተልን የጠበቀ ነውን?
በብሉይ ኪዳን ውስጥ ፔንታቱክና የታሪክ መጻሕፍት በጊዜ ቅደም ተከተል ነው የተቀመጡት፡፡ የተቀሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በነዚህ የታሪክ መጻሕፍት የጊዜ ቅደም ተከተል ውስጥ መግባት የሚችሉ ናቸው፡፡
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ወንጌላት የኢየሱስን ታሪክ ይተርካሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ ወንጌላት ካቆሙበት ታሪኩን ይቀጥላል፡፡ መልዕክታቱ በጊዜ ቅደም ተከተል ሳይሆን በርዝመት የተደረደሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የሐዋርያት ሥራ በተጻፈበት የጊዜ ቅደም ተከተል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ኋላ ላይ የተጻፉ ናቸው፡፡ ራዕይ መጨረሻ ላይ ነው የተጻፈው፡፡
የምዕራፍና የቁጥር አከፋፈሎች በመጀመርያዎቹ ጽሑፎች ውስጥ አልነበሩም፡፡ አንባቢያን አንድን መረጃ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ለማስቻል ከብዙ ጊዜ በኋላ የተጨመሩ ናቸው፡፡
እንዴት ነው ልዩ የሆነው?
አንድ ቀን የምዕራቡ ዓለም ምርጥ ቤተ መጻሕፍት ተወካይ ወደ ጆሽ ማክዱዌል በመምጣት የሽያጭ ክፍል ኃላፊ ሆኖ እንዲሠራላቸው ጠየቀው፡፡ ከዚያም ተወካዩ ታላላቆቹን መጻሕፍት በቅደም ተከተል ከጠቀሰለት በኋላ ጆስ ማክዱዌል ለሰውየው አንድ ጥያቄ አቀረበ፡፡ “እስኪ አሥሩን ደራሲያን ውሰድ” አለው፡፡ “ሁሉም ተመሳሳይ በሆነ የሕይወት ጉዞ ላይ ያሉ፣ ከአንድ ትውልድ የሆኑ፣ ከአንድ ቦታ የተገኙ፣ በአንድ ዘመን የኖሩ፣ አንድ ዓይነት የአጻጻፍ ሥልት ያላቸው፣ አንድ ይዘት ያለውን ጽሑፍ የሚጽፉ፣ አንድ ቋንቋ ያላቸውና አነጋጋሪ በሆነ አንድ ርዕስ ላይ የሚጽፉ ናቸው እንበል፡፡ እነዚህ ሰዎች መስማማት ይችላሉን?” ሰውየው “በፍጹም አይስማሙም!” የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ ዶሽ ማክዱዌል ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡- “ውጤቱ ምንድነው የሚሆነው?” የሰውየው ምላሽ ፈጣን ነብር “የተለያዩ ሐሳቦችን የያዘ ጽሑፍ፡፡”
ከጥቂት ቀናት በኋላ ያ ሰው ክርስቶስን የሕይወቱ ጌታ አድርጎ ተቀበለ፡፡ (5) ጆሽ ማክዱዌል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተከታዩን መረጃ ነበር ለሰውየው ያካፈለው፡-
- 66 መጻሕፍት አሉት
- በ 40 የተለያዩ ጸሐፍት የተጻፈ ነው
- በ 1600 ዓመታት መካከል የተጻፈ ነው
- ከተለያየ የሕይወት መንገድ በመጡ፣ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ በኖሩ፣ በሦስት የተለያዩ አሕጉራት ላይ በኖሩ፣ በሦስት ቋንቋዎች በጻፉ፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ አጨቃጫቂ ርዕሶች ላይ በጻፉ ሰዎች የተዘጋጀ ነው፡፡
ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው በመቶዎች በሚቆጠሩ አጨቃጫቂ ርዕሶች ላይ እርስ በርሱ ሙሉ በሙሉ የተስማማ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ይህ እንግዲህ ተዓምር የምንለው ነው!
ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት የሚገባንን ሁሉ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
መጀመርያ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት እንዲያነሳሳህና መረዳትን እንዲሰጥህ ጸልይ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አንዱ ሥራ የእግዚአብሔርን እውነት መግለጥ ነውና፡፡
“እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም፡፡ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም፡፡” (1ቆሮ. 2፡12-13)
ሁለተኛ የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ፣ ለመወያየት፣ በተማርከው ላይ ለመጸለይና ለመታዘዝ ራስህን ስጥ፡፡
“ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ፡፡” (1ጴጥ. 2፡2-3)
የሚበሉትን ሥጋ በአሸዋ በመሸፈንና ከላይ እሳት በማንደድ ስለሚያበስሉ ጎሣዎች ሰምቼ ነበር፡፡ ችግሩ የተወሰነው አሸዋ ሥጋው ውስጥ ይቀራል፡፡ ይህ ደግሞ ጥርሳቸውን በመሸራረፍ ለዘላቂ ችግር ይዳርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ አዛውንቶቻቸውን ለመመገብ ወጣቶቹ ሥጋውን ያኝኩና በጉጉት ለሚጠብቋቸው አዛውንቶች ይሰጧቸዋል፡፡
ይህ ልማድ አስቀያሚ የሚመስለውን ያህል የብዙ ክርስቲያኖችን አኗኗር ይገልጻል፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል በራሳቸው ከማንበብ ይልቅ ሌሎች ሰዎች አስቀድመው ያላመጡትን ያነባሉ፡፡ ጤናማ የሆነውን ጥርሳቸውን ተጠቅመው የእግዚአብሔርን ቃል በራሳቸው ከመመገብ ይልቅ፣ ማለትም ባለበት ሁኔታ አንብበው ከማሰላሰል ይልቅ በሌሎች ሰዎች ትምህርት ላይ ሙሉ በሙሉ ይደገፋሉ፡፡
ነገር ግን ንባብ የማትወድ ሰው ብትሆን ወይንም መጽሐፍ ቅዱስ ልክ እንደ አሸዋ ደረቅ መስሎ የሚታይህ ከሆነስ? አንድ ወጣት ሰው ያደረገውን ልንገርህ፡፡ ይህ ወጣት ቃለ እግዚአብሔርን ዕለት ዕለት መመገብ እንዳለበት ከላይ ከተጠቀሰው ቃል ተረድቷል፡፡ 1ዮሐንስ 5፡14-15 ላይ የተጻፈውን ቃል በማንበብ ደግሞ እንደ ፈቃዱ የሆነውን ነገር በጸሎት የምንጠይቅ ከሆነ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን ተረድቷል፡፡
“በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን፡፡”
ስለዚህ እግዚአብሔር የቃሉን ጥማት እንዲሰጠው ደጋግሞ ቢጸልይ እግዚአብሔር እንደሚሰጠው ባለ ሙሉ ተስፋ ነበር፡፡ በመታዘዝ ልብ ሆኖ አዲስ ኪዳንን ለተወሰነ ጊዜ ካነበበ በኋላ እግዚአብሔር የቃሉን ጥማት ሰጠው፡፡ ያ ወጣት ሰው አሁን የዚህ ጽሑፍ ደራሲ ነው!
ሦስተኛ ቃሉን በማጥናትና በማንበብ ብርቱ ከሆኑት ተማር፡፡ የክርስትና ሕይወት ለብቻችን ተነጥለን የምንኖረው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹን ቃሉን እንዲያጠኑ፣ እንዲተረጉሙና እንዲተገብሩ መርጧቸዋል፡፡
“ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ፡፡” (2ጢሞ. 2፡2)
“እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፡፡” (ኤፌ. 4፡11-13)
በአማኞች ጉባኤ ውስጥ በመሆን ከሌሎች ጋር በጋራ ማምለክና በሳል የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚሰጡትን ትምህርት መስማት ትችላለህ፡፡ በአነስተኛ ቡድኖች ውስጥ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ቃል ትርጉም ልትወያይ ትችላለህ፡፡ ሕያውና የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አባል መሆን መጽሐፍ ቅዱስህን በግልህ እንድታጠና ያነሳሳሃል፤ ትክክለኛ መረዳትም እንዲኖርህ ይጠብቅሃል፡፡
“ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ፡፡” (ዕብ. 10፡24-25)
ማጣቀሻዎች
- Nelson Glueck, Rivers in the Desert: History of Negev (Philadelphia, PA: Jewish Publication Society of America, 1969), 31.
- Cited from Dr. Henry F. Schaefer, III, Scientists and Their Gods, http://leaderu.com/offices/schaefer/scientists.html (2001).
- Frederick Copleston SJ, A History of Philosophy Vol. 1: Greece and Rome From the Pre-Socratics to Plotinus, Part 1 (New York, NY: Doubleday, 1993), 7.
- Frederick Copleston SJ, Memories of Philosopher (Kansas City, MO: Sheed and Ward, 1993), 44.
- Josh McDowell, Evidence That Demands a Verdict, 1 (San Bernardino, CA: Here’s Life Publishers, 1979), 17.