የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች (Manuscripts)
ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች (Manuscripts) ከማተምያ ማሽን ዘመን በፊት በእጅ የተገለበጡ መዛግብት ናቸው፡፡ ይህ የጥናት ዘርፍ “ፓሌኦግራፊ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ፓሌኦግራፈሮች ጥንታውያን መዛግብትን ይሰበስባሉ፣ መቼታቸውን እንዲሁም በይዘት ለመጀመርያዎቹ ጽሑፎች ምን ያህል የቀረቡ እንደሆኑ ይመረምራሉ፡፡ ፊደላት ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለሚቀያየሩና ብዙ የጥንት ቋንቋዎች አናባቢዎችና ስርዓተ ነጥብ ስለሌሏቸው፤ የጽሑፍ ባለሙያዎችም ጊዜና ቦታን ለመቆጠብ ምህፃረ ቃላትን ስለሚጠቀሙ ጥንታውያን መዛግብትን ማንበብ በራሱ በብርቱ ጥረት የሚገኝ ልዩ ክህሎትን የሚጠይቅ ነው፡፡
በፓሌኦግራፊ ጥናት ዘርፍ እውቅናን ካተረፉ ምሑራን መካከል በአንድ ወቅት የብሪቲሽ ቤተ መዛግብት ተጠሪና የብሪቲሽ አካዳሚ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሰር ፍሬደሪክ ጆርጅ ኬንዮን ይገኙበታል፡፡ እኝህ ብዙ ዘመናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስን የእጅ ጽሑፎች በመመርመር ያሳለፉ ታላቅ ምሑር በአንድ ወቅት “ቅዱሳት መጻሕፍት ልክ መጀመርያ በተጻፉበት ይዘት ወደኛ በመምጣቸው ላይ የነበረው የመጨረሻው የጥርጣሬ መሠረት ተወግዷል” በማለት ጽፈው ነበር፡፡[1] ዕውቅ የአዲስ ኪዳን ምሑር የሆኑት ፍሬደሪክ ፊቪዬ ብሩስ፣ ሰር ፍሬደሪክ ጄ. ኬንዮንን “ስለ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ሥልጣናዊ ንግግር በማድረግ ረገድ ማንም የማይስተካከላቸው” ይሏቸዋል፡፡[2]
በጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ጥናት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ለኮፒዎች ብዛት እንዲሁም በይዘትና በዘመን ለመጀመርዎቹ ጽሑፎች ላላቸው ቅርበት ነው፡፡ በማስከተል እንደምንመለከተው የክርስቲያን አዲስ ኪዳን ከየትኛውም ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ የጥንት ሰነድ ጋር ሊወዳደር በማይችልበት ሁኔታ በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን እጅግ የላቀ ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው የአዲስ ኪዳን ምሑር ኤፍ. ኤፍ. ብሩስ የሚከተለውን ጽፈዋል፡-
“ለአዲስ ኪዳናችን ያለው ማስረጃ ማንም ሰው እርግጠኛነታቸውን አጠያያቂ ለማድረግ ከማያልማቸው ከብዙ ጥንታውያን ጽሑፎች እጅግ በጣም ይልቃል፡፡ አዲስ ኪዳን የዓለማውያን ጽሑፎች ስብስብ ቢሆን ኖሮ ታዓማኒነቱ ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ተቀባይነት ባገኘ ነበር፡፡ ከብዙ የሥነ መለኮት ምሑራን ይልቅ የታሪክ ተመራማሪዎች ብዙ ጊዜ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ላይ እምነት ለመጣል በጣም ዝግጁዎች መሆናቸው ብዙዎች የማይገምቱት እውነታ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሃይማኖት መጻሕፍት በመሆናቸው ብቻ በጥርጣሬ የሚያዩዋቸውና ከሌሎች ዓለማዊ ወይንም የአረማውያን ጽሑፎች ይልቅ ለንደነዚህ ዓይነት ሥራዎች ብዙ ማስረጃዎችን የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፡፡ ከታሪክ ተመራማሪ ዕይታ አኳያ ለሁለቱም አንድ ዓይነት መስፈርት ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡ ነገር ግን ከሌሎች ጽሑፎች ይልቅ ለአዲስ ኪዳን መዛግብት ብዙ ማስረጃዎችን ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር አንጨቃጨቅም፡፡ [ይህንን የማናደርግበት] የመጀመርያው ምክንያት አዲስ ኪዳን በሰው ልጆች ላይ የሚያስቀምጠው ሁሉን አቀፍ እርግጠኛ የግል ምስክርነት የማያወላዳ በመሆኑና የዋናው ገፀ ባሕርይ ሥራና ባሕርይ ወደር የለሽ በመሆኑ ለእውነተኛነቱ የሚቻለውን ያህል ሁሉ እርግጠኞች መሆን ስለምንፈልግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሌሎች ተመሳሳይ ዕድሜ ካላቸው ጥንታውያን ጽሑፎች ይልቅ ለአዲስ ኪዳን በጣም የላቀ ማስረጃ በመኖሩ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ለአዲስ ኪዳን ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ5,000 በላይ የግሪክ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በጣም ምርጡ ወደ 350 ዓ.ም. የሚሄድ ሲሆን፤ ወሳኝ የሆኑት ሁለቱ የቫቲካን ላይብረሪ ግምጃ (ንብረት) የሆነው ኮዴክስ ቫቲካነስና በ1933 ዓ.ም. የብሪቲሽ መንግሥት ከሶቪዬት መንግሥት በ100,000 ፓዉንድ የገዛውና የብሪቲሽ ቤተ መዘክር ዋና ግምጃ የሆነው ኮዴክስ ሲናይቲከስ ናቸው፡፡ በጣም ወሳኝ የሆኑ በዚህች አገር ውስጥ [ብሪታንያ] የሚገኙት ሁለቱ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች በብሪቲሽ ቤተ መዘክር ውስጥ የሚገኘው በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈው ኮዴክስ አሌክሳንድሪኑስና በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘው በአምተኛው ወይንም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈው ወንጌላትንና የሐዋርያት ሥራን የያዘው ኮዴክስ ቢዛዬ ናቸው፡፡
የአዲስ ኪዳንን ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ከሌሎች ጥንታውያን የታሪክ ሥራዎች ጋር ብናነፃጽር ምን ያህል የበለፀገ እንደሆነ ልናደንቅ እንችላለን፡፡ ለቄሣር የጋሊክ ጦርነት (በ 58 እና 50 ዓ.ዓ. መካከል የተጻፈ) ብዙ የተለያዩ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፤ ነገር ግን ከነዚህ መካከል ጥሩ የሚባሉት ዘጠኙ ወይንም አስሩ ብቻ ናቸው፤ እንዲሁም ዕድሜ ጠገብ የሚባለው ከቄሣር ዘመን በጣም የዘገየ ነው፡፡ 142 ከሆኑት የሊቪ የሮማውያን ታሪክ መጻሕፍት መካከል (59 ዓ.ዓ. – 17 ዓ.ም.) የተረፉት 35 ብቻ ናቸው፤ ስለ እርሱም ማወቅ የቻልነው ከ20 ከማይበልጡ ውጤታቸው ምንም ሊሆን ከሚችል ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ሲሆን ከነዚህ መካከል እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የሚረዝም እድሜ ያላቸው የመጽሐፍ 3 እና 4 ቁርጥራጮች ብቻ ናቸው፡፡ ከ 14 የታሲተስ የታሪክ መጻሕፍት መካከል (100 ዓ.ም.) አራት ከግማሽ የሚሆኑቱ ብቻ ናቸው መትረፍ የቻሉት፡፡ በእርሱ ከተጻፉት 16 የተከታታይ ዘመናት ታሪኮች መጻሕፍት መካከል አስሮቹ ሙሉ በሙሉና ሁለቱ ደግሞ በከፊል ተርፈዋል፡፡ በነዚህ አንዱ ከዘጠነኛው ክፍለ ዘመንና አንዱ ከአስራ አንደኛው ክፍለ ዘመን በሆኑ ሁለት ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች የተለያዩ ክፍሎች ላይ ሙሉ በሙሉ የተመረኮዙ ሁለት ታላላቅ ሥራዎች አሉ፡፡ የተለያዩ አነስተኛ ሥራዎቹ (Dialogue de Orateribus, Agricola, Germania) ሁሉም የመጡት ከአስረኛው ክፍለ ዘመን ኮዴክስ ነው፡፡ ስለ ቱሳይዲደስ ታሪክ (460 ዓ.ዓ.) ማወቅ የቻልነው ከስምንት ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ላይ ነው፡፡ ዕድሜ ጠገብ የሚባለው በ900 ዓ.ም. የነበረ ሲሆን ጥቂት የፓፒረስ (የቄጤማ ላይ ጽሑፎች) ቁርጥራጮች ደግሞ ከክርስቲያን ዘመን መጀመርያ ጀምሮ የነበሩ ናቸው፡፡ የሄሮዱተስ ታሪክም ተመነሳሳይ ነው (488-428 ዓ.ዓ.)፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ምሑር የሄሮዱተስ ወይንም ደግሞ የቱሳይዲደስ ሥራዎች ከመጀመርዎቹ ጽሑፎች 1,300 ዓመታት ያህል የዘገዩ በመሆናቸው ምክንያት ተኣማኒነታቸው ጥርጣሬ ውስጥ መግባቱን መስማት አይፈልግም፡፡
ነገር ግን የአዲስ ኪዳን ሁኔታ ምንኛ ከዚህ የተለየ ነው! ከምናውቃቸው ከሌሎች በሺዎች ከሚቆጠሩ ሁሉ ይልቅ ዕድሜ ጠገብት ከሆኑት ከዚህ በላይ ከጠቀስናቸው ምርጥ የአራተኛው ክፍለ ዘመን ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች በተጨማሪ ከነርሱ ደግሞ ከ100 እስከ 200 ዓመታት የሚቀድሙ በርካታ የአዲስ ኪዳን የፓፒረስ ቅጂዎች አሉ፡፡ መኖሩ በ1931 ዓ.ም. ይፋ የሆነው የቸስተር ቢቲ የመጽሐፍ ቅዱስ ፓፒሪ አስራ አንድ የፓፒረስ ጥራዞችን የያዘ ሲሆን ከነዚህ መካከል ሦስቱ አብዛኞቹን የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ይዘዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ አራቱን ወንጌላት ከሐዋርያት ሥራ ጋር የያዘ ሲሆን ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ የመጣ ነው፤ ሌላኛው ጳውሎስ ወደ አብያተ ክርስቲያናት የላካቸውን መልዕክቶችና የዕብራውንን መልዕክት የያዘው በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተገለበጠ ነው፤ የዮሐንስ ራዕይን የያዘው ደግሞ ከተመሳሳይ ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ የመጣ ነው […]
አሁንም ዮሐንስ 18፡31-33፣ 37ን የያዘ ዕድሜ ጠገብ የፓፒረስ ኮዴክስ ቁርጥራጭ ማንቸስተር ከተማ በጆን ሪላንድ ላይብረሪ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ፓሌኦግራፊ ላይ በመመሥረት እድሜው ተለክቶ 130 ዓ.ም. ሆኗል፡፡ በተለምዶ እንደሚነገረው ከወንጌላት ሁሉ በስተመጨረሻ በ90 እና 100 ዓ.ም. መካከል በኤፌሶን እንደተጻፈ ሲሆን በተጻፈ በ40 ዓመታት ውስጥ በግብፅ ውስጥ ይዘዋወር ነበር (ይህ ፓፒረስ እንደሚመስለው መነሻው በ1917 ዓ.ም. ከተገኘበት ከግብፅ ከሆነ ማለት ነው)፡፡ ይህ በግማሽ ምዕተ ዓመት ከሁሉም የሚቀድም የአዲስ ኪዳን ቁርጥራጭ እንደሆነ ይታሰባል፡፡
የቅርብ ጊዜ ግኝት የሆነው የተመሳሳይ ወንጌል [ዮሐንስ] ፓፒረስ ቀዳማይ ጽሑፍ የሪላንድ ፓፒረስን ያህል ዕድሜ ጠገብ ባይሆንም በንፅፅር ግን የተሻለ ተጠብቋል፡፡ ይህ መገኘቱ በ1956 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ቦድመር ሁለት የተባለ ፓፒረስ ነው፡፡ በ200 ዓ.ም. የተጻፈ ሲሆን የዮሐንስን ወንጌል የመጀመርያዎቹን 14 ምዕራፎች ነገር ግን በመሃል አንድ የተዘለለ ክፍል (22 ቁጥሮች) ሲኖሩት፣ በርከት ያለ የመጨረሻዎቹን ሰባት ምዕራፎች ክፍልም አካቷል፡፡”[3]
ጆሽ ማክዱዌል “Evidence That Demands a Verdict” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን መረጃ አስፍረዋል፡-
“ከ5,686 በላይ የሚሆኑ የታወቁ የአዲስ ኪዳን የግሪክ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ በተጨማሪም 10,000 የላቲን ቩልጌቶችና ሌሎች 9,300 ቀዳሚያን ቅጂዎች፣ በአጠቃላይ ከዚያ ካልበለጡ ወደ 25,000 የሚሆኑ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ ከጥንት መዛግብት መካከል አንዱም እንኳ ይህንን ያህል ቁጥርና የማረጋገጫ ብዛት ወደ ማስመዝገብ የቀረበ የለም፡፡ በንፅፅር እስከ አሁን የተረፉ 643 የእጅ ጽሑፎች ብቻ ያሉት የሆሜር ኢሊያድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡”[4]
ከነዚህ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፦
ቀጥሎ የሚገኘው ሰንጠረዥ የአዲስ ኪዳንንና ዓለማውያን የሆኑ መዛግብትን ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች በንፅፅር ያሳያል፡፡
ጸሐፊው | የተጻፈበት ጊዜ | እድሜ ጠገቡ ኮፒ | የጊዜ ልዩነት | የኮፒዎች ቁጥር |
ዓለማውያን ጽሑፎች | ||||
ሄሮዶተስ (ታሪክ) | 480-425 ዓ.ዓ. | 900 ዓ.ም. | 1,300 ዓመታት | 8 |
ቱሳይዲደስ (ታሪክ) | 460-400 ዓ.ዓ. | 900 ዓ.ም. | 1,300 ዓመታት | 8 |
ፕሌቶ (ፍልስፍና) | 400 ዓ.ዓ. | 900 ዓ.ም. | 1,300 ዓመታት | 7 |
አርስቶትል (ፍልስፍና) | 384-322 ዓ.ዓ. | 1,100 ዓ.ም. | 1,400 ዓመታት | 5 |
ቄሣር (ታሪክ) | 100-44 ዓ.ዓ. | 900 ዓ.ም. | 1,000 ዓመታት | 10 |
ፕሊኒ (ታሪክ) | 61-113 ዓ.ም. | 850 ዓ.ም. | 750 ዓመታት | 7 |
ሱቶኒዩስ (ታሪክ) | 70-140 ዓ.ም. | 950 ዓ.ም. | 800 ዓመታት | ? |
ታሲተስ (ታሪክ) | 100 ዓ.ም | 1.100 ዓ.ም. | 1,000 ዓመታት | 20 |
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች (እነዚህ በተናጠል ያሉ ጽሑፎች መሆናቸውን ልብ ይሏል) | ||||
የእጅ ጽሑፉ መጠርያ | የተጻፈበት ጊዜ | እድሜ ጠገቡ ኮፒ | የጊዜ ልዩነት | |
መግደላን የእጅ ጽሑፍ (ማቴዎስ 26) | 1ኛ ክ.ዘ. | 50-56 ዓ.ም. | ከመጀመርው ጽሑፍ ጋር አብሮ የነበረ (?) | |
ጆን ሪላንድ (ዮሐንስ) | 90 ዓ.ም. | 130 ዓ.ም. | 40 ዓመታት | |
የቦድሜር ፓፒሪ ሁለት (ዮሐንስ) | 90 ዓ.ም. | 150-200 ዓ.ም. | 60-100 ዓመታት | |
ቸስተር ቤቲ ፓፒሪ (አዲስ ኪዳን) | 1ኛ ክ.ዘ. | 200 ዓ.ም. | 150 ዓመታት | |
ዲያተሳሮን በታሺያን (ወንጌላት) | 1ኛ ክ.ዘ. | 200 ዓ.ም. | 150 ዓመታት | |
ኮዴክስ ቫቲካነስ (መጽሐፍ ቅዱስ) | 1ኛ ክ.ዘ. | 325-350 ዓ.ም. | 275-300 ዓመታት | |
ኮዴክስ ሲናይቲከስ (መጽሐፍ ቅዱስ) | 1ኛ ክፍለ ዘመን | 350 ዓ.ም. | 300 ዓመታት |
(Jay Smith. British Museum Tour, p. 19)
ከነዚህ የግሪክ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች በተጨማሪ የተለያዩ ዕድሜ ጠገብት የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች አሉን፡፡ ለመጥቀስ ያህል፡- ቅብጥ (ኮፕቲክ) (3ኛው እና 4ኛው ክፍለ ዘመናት መጀመርያ ላይ)፣ አርመን (400 ዓ.ም.)፣ ጎቲክ (4ኛው ክፍለ ዘመን)፣ ጆርጅያንኛ (5ኛው ክፍለ ዘመን)፣ ኢትዮጵያንኛ ወይንም ግዕዝ (6ኛው ክፍለ ዘመን)፣ እና ኑቢያ (6ኛው ክፍለ ዘመን) ናቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም ከኒቅያ ጉባኤ በፊት (320 ዓ.ም. በፊት) የተጻፉ የአዲስ ኪዳንን የተለያዩ ክፍሎች የሚጠቅሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የጥንት አባቶች ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡ክርስቲያን አቃቤ እምነት የሆኑት ኖርማን ጌይዝለር እንደጻፉት ከሆነ እስከ 4ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ብቻ በአባቶች የተጠቀሱትን ከ 36,000 በላይ ጥቅሶች አንድ ላይ ብንቀጣጥል ከ11 ቀጥሮች (ከግማሽ ገጽ ያነሰ) በስተቀር ሁሉንም የአዲስ ኪዳን ክፍል መልሰን መጻፍ እንችላለን! ቀጥሎ የሚገኘውን ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡-
ጸሐፊው | ወንጌላት | ሐዋርያት ሥራ | ጳውሎስ መልዕክቶች | ሌሎች መልዕክቶች | ራዕይ | ድምር |
ዮስጦስ ሰማዕት | 268 | 10 | 43 | 6 | 3 የቀጥታ ጥቅሶች፣ 266 ማመላከቻዎች | 330 |
ኢሬኔዎስ | 103 | 194 | 499 | 23 | 65 | 1,819 |
የእስክንድሪያው ቀለሜንጦስ | 1,107 | 4 | 1,127 | 207 | 11 | 2,406 |
ኦሪጎን | 9,231 | 349 | 7778 | 399 | 165 | 17,992 |
ጠርጡሊያኖስ | 3,258 | 502 | 2,609 | 120 | 205 | 7,258 |
ሂጶሊጦስ | 734 | 42 | 387 | 27 | 188 | 1,378 |
ኢዮስቢዮስ | 3,258 | 211 | 1,592 | 88 | 27 | 5,176 |
ጠቅላላ ድምር | 19,368 | 352 | 14,035 | 70 | 664 | 36,289 |
(Jay Smith. British Museum Tour, p. 19)
ወደ ብሉይ ኪዳን ስንመጣ እንደዚሁ ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ማየት እንችላለን፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው “የቁምራን ጥቅልሎች” ወይንም ደግሞ “የሙት ባህር ጥቅልሎች” በመባል የሚታወቁ ጥንታውያን የብሉይ ኪዳንና ሌሎች ሰነዶች መገኘት ነው፡፡ ቁምራን በሙት ባህር አካባቢ የሚገኝ እሴናውያን የተባሉ ሃይማኖተኛ ማሕበረሰቦች ይኖሩበት የነበረ አካባቢ ነው፡፡ የዚህ በጥንታውያን መዛግብት ጥናት ዘርፍ ከሁሉም የላቀ ስኬት እንደሆነ የተነገረለት ግኝት ታሪክ በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
በ1947 ዓ.ም. አንድ ቤዱዊን ወጣት ልጅ የጠፋችበትን ፍየል ፍለጋ ወደዚህ ታሪካዊ ስፍራ አመራ፡፡ ፍየሊቱ እንዳለችበት ወደ ገመተው ዋሻ ድንጋይ ቢወረውር የተወረወረው ድንጋ ፍየል ከመምታት ይልቅ 2000 ዓመታት ያህል እድሜ ያለውን ዓለምን ሁሉ ሊያስደንቅ ያለን ማሰሮ መታ፡፡ በሰማው ድምፅ ግራ በመጋባት የበለጠ ለማወቅ ወደ ዋሻው ውስጥ የዘለቀው ወጣት ልጅ በማሰሮው ውስጥ ያገኘው ነገር ቢኖር የፓፒረስና የብራና መጻሕፍት ጥቅልሎችን ነበር፡፡
የነዚህን ጥንታውያን ቅርሶች ዋጋ ያላወቀው ወጣት ልጅ ወደ ከተማ በመውሰድ የጥንታውያን መዛግብት ሻጭ ለነበረ ካንዶ ለተባለ ሰው ሰባት ጥቅልሎችን ሸጠለት፡፡ ይህም ሰው ከጥቅልሎቹ መካከል ሦስቱን ለአንድ የእስራኤል ዩኒቨርስቲ መምህርና የተቀሩትን አራቱን ደግሞ በገዳም ውስጥ ለሚኖር አንድ ሦርያዊ መነኩሴ ሸጠ፡፡ ማር አትናሲውስ የተባሉት እኝህ ሦርያዊ ሰው እነዚህን ጥቅልሎች ወደ አሜሪካን ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ሪሰርች ባመጡበት ወቅት ነበር የቁምራን አካባቢ የምዕራባውያን ምሑራንን ትኩረት ማግኘት የቻለው፡፡ የመጀመርዎቹ ጥቅልሎች የተገኙበት ዋሻ በ1949 ዓ.ም. “አንድ ቁጥር ዋሻ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በ 1949 ዓ.ም. እና በ 1956 ዓ.ም. መካከል የተለያዩ ጥንታውያን ቁሳቁሶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጻሕፍት ጥቅልል ቁርጥራጮችን የያዙ አስር ተጨማሪ ዋሻዎች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በተገኙት በነዚህ ዋሻዎች ውስጥ በ250 ዓ.ዓ. እና በ68 ዓ.ም. መካከል የተጻፉ ወደ 800 የሚሆኑ በእብራይስጥ፣ በግሪክና በአራማይክ ቋንቋ የተጻፉ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፣ የአፖክሪፋ መጻሕፍት፣ የተለያዩ መዝሙሮች፣ የእሴናውንን እምነት የሚገልጹ ጽሑፎችና ሌሎች ጥንታውያን መዛግብት ተገኝተዋል፡፡ ከመጽሐፈ አስቴር በስተቀር ሁሉንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚወክሉ የእጅ ጽሑፎችና ቁርጥራጮች የተገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል አስደናቂው የትንቢተ ኢሳይያስን ሙሉ መጽሐፍ የያዘው ከክርስቶስ ልደት በፊት 200 ዓመታትን በመቅደም እንደ ተጻፈ የተረጋገጠው የብራና ጥቅልል ነው፡፡
ሌላው አስደናቂ ነገር ደግሞ ጆሴ ኦ’ክላሃን የተባሉ እስፔናዊ ፓሌኦግራፈር የማርቆስ፣ ሐዋርያት ሥራ፣ ሮሜ፣ 1ጢሞቴዎስ፣ 2ጴጥሮስና ያዕቆብ መልዕክት ጥቂት ክፍሎችን በተወሰኑ ቁርጥራጮች ላይ ማንበብ መቻላቸውን መናገራቸው ነው፡፡ ስለ ጉዳዩ ኒውዮርክ ታይምስ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር ፡- “የአባ ኦ’ክላሃን መላምት ተቀባይነት ካገኘ በትንሹ የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ከኢየሱስ ሞት በኋላ ጥቂት ዓመታትን ብቻ በመዘግት መጻፉን ያረጋግጣል፡፡”[5]
እነዚህ ሁሉ አስደናቂ ግኝቶች ታዋቂው የጥንታውያን መዛግብት አጥኚ ሰር ሮበርት ኬንዮን አዲስ ኪዳንን በተመለከተ የተናገሩትን ከምሑራዊ ጥናትና ምርምር የመነጨ ንግግር ያስታውሱናል፡- “የመጀመርያው ጽሑፍ በተጻፈበት ጊዜና በቀዳሚው ጽሑፍ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት ምንም የለም እስኪያስብል ድረስ በጣም አናሳ ሆኗል እናም ቅዱሳት መጻሕፍት ልክ መጀመርያ በተጻፉበት ይዘት ወደኛ በመምጣቸው ላይ የነበረው የመጨረሻው የጥርጣሬ መሠረት ተወግዷል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተዓማኒነትና አጠቃላይ ተግባቦት በመጨረሻ እንደተረጋገጠ ሊቆጠር ይችላል፡፡”[6]
ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ማስረጃዎች በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚያረጋግጡ ሌሎች ማሳያዎችም አሉ፡፡ ይህ መጽሐፍ ሰዎችን የመለወጥ ኃይሉ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹን እንኳ የመማረክ መለኮታዊ ኃይል አለው፡፡ ተስፋዎቹ እጅግ ጽኑዓን ናቸው፡፡ ቃሉን በማመን ከበሽታቸው የተፈወሱ፣ በክፉ መንፈሳውያን ኃይላት ላይ ድልን ያገኙ፣ የተጽናኑ፣ የተለያዩ የሕይወት ፈተናዎችን ያሸነፉ በጣም ብዙ ምስክሮች አሉ፡፡ ሰይጣን ይህንን መጽሐፍ ለማጥፋት ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ ሰዎችን በመጠቀም በቃሉ አገልጋዮች ላይ መከራና ስደትን ቢያደርስም ነገር ግን ዛሬ ይህ መጽሐፍ በስርጭትም ሆነ በተነባቢነት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ፣ በብዙ የዓለም ክፍሎች የተሰራጨ፣ በብዙ ኮፒዎች የተባዛና በብዙ ሰዎች የተነበበ መጽሐፍ የለም፡፡ ይህ እውነታ መጽሐፍ ቅዱስ ከደረሰበት ከፍተኛ የሆነ ከምድረ ገጽ የማጥፋት ዘመቻ አንጻር ሲታይ እርሱን የሚጠብቅ አንዳች መለኮታዊ ኃይል መኖሩን እንድናምን ያስገድደናል፡፡
ይህ መጽሐፍ ለሰው ልጆች የሚሰጠው እንከን የለሽ የግብረ ገብነት መመርያ ለመለኮታዊነቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሥነ ምግባር መርህ በመስጠት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛውም ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ መጽሐፍ የላቀ ነው፡፡
ሌላው የዚህ ታላቅ መጽሐፍ አስደናቂ ባህርይ የመልዕክቱ ወጥነት ነው፡፡ በብዙ ሰዎች፣ በብዙ አገራትና ሰፊ በሆነ የዘመን ልዩነት የተጻፈ ቢሆንም መዕከላዊ መልዕክቱ አንድ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከሚሉት በተጻራሪ ከሥነ አመክንዮአዊ መጣረሶችም ነፃ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተዋወቃችሁ ወገኖች ካላችሁ አግኝታችሁ ታነቡት ዘንድ እናበረታታችኋለን፤ ከዚያም ይህ መጽሐፍ መለኮታዊ መሆን አለመሆኑን በመመርመር ወደ ራሳችሁ ድምዳሜ ለመምጣት ሞክሩ፡፡ በውጤቱም በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የሚገኘውን የዘላለምን ሕይወት እንደምታገኙ ባለ ሙሉ ታስፋዎች ነን፡፡
ማጣቀሻዎች
[1] Bruce, FF. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, p. 11 of PDF
[2] Ibid.
[3] Ibid., pp. 7-9
[4] McDowell, Josh. Evidence That Demands a Verdict, pp. 34
[5] Geisler, Norman L. Baker Encyclopedia of Christian Apologetics, 1999, pp. 18-19
[6] Bruce, FF. The New Testament Documents, p. 11