ሙስሊሞች የኢየሱስን አምላክነት የማይቀበሉበት ስውር ምክንያት

ሙስሊሞች የኢየሱስን አምላክነት የማይቀበሉበት ድብቅ ምክንያት

Kinfe G.

ሙስሊሞችንና አምላክ የለሾችን በእምነት ዙሪያ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ፍጥረታት የፈጣሪን መኖር እያመላከቱ ሳለ አምላክ የለሾች (Atheists) «ፈጣሪ እራሱ ተገልጦ ‘እኔ አምላካችሁ ነኝ፤ አምልኩኝ’ ካላለ በስተቀር አምላክ መሆኑን አናምንም» ይላሉ፡፡ ሙስሊሞችም በተመሳሳይ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመስክሮ ሳለ «ኢየሱስ እራሱ ቃል በቃል ‘እኔ አምላክ ነኝ፣ አምልኩኝ’ እስካላለ ድረስ አምላክ መሆኑን አናምንም» ይላሉ፡፡

ሙስሊም ወገኖች የማያስተውሉት አንድ ጉዳይ ቢኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው አምላክነቱንና መለኮታዊ ክብሩን ለማወጅ አለመሆኑን ነው፡፡ አምላክነቱን ለማወጅ ቢሆንማ ኖሮ እንደ ሰው ተወልዶ በምድር ላይ መኖር ባላስፈለገው ነበር፡፡ የፍጥረቱ ሁሉ ፈጣሪ፣ የአብ ዘላለማዊ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ የኖረው ለሰው ልጆች ቤዛ ሊሆን እንጂ በምድር ላይ አምልኮትና ክብር መቀበልን ዋና ተልእኮው አድርጎ አልመጣም፡፡ ነገር ግን በዘመኑ የኢየሱስን ማንነትና አላማውን የተገነዘቡ ሰዎች አምላክነቱን አምነው መስክረውለታል፣ ሰግደውለታልም፡፡

የማቴዎስ ወንጌል 2፡1-11 እንዲህ ይላል፡-

“1 ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፦ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ … 11 ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።”

ኢየሱስ ገና ከመወለዱ ነበር ጌትነቱ የተመሰከረለት፡፡ ይህንን የተረዱት ጠቢባንም ወድቀው በመስገድ ለአምላክነቱ የሚገባውን ክብር ሰጥተውታል፡፡ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ግን ምድራዊ ንግሥናውን የሚቀናቀን መስሎት ሊገድለው ሲያሳድደው፤ ኢየሱስ የመጣበት ዓላማ ራሱን ዝቅ አድርጎ መከራን መቀበል እንጂ አምላክነቱን ማረጋገጥ ባለመሆኑ ሄሮድስን መቅሰፍ ሲችል ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በስደት እንደሰው ተንገላታ፡፡ ሰዎች አምላክነቱን ተገንዝበው ተገቢውን ክብር ሲሰጡት ግን አንድም ጊዜ ተቃውሞን አላሰማም፡፡ ለዚህ የሚሆኑ አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

“እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት።” (ማቴዎስ 8፡2)

“ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኰንን መጥቶ፦ ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት።” (ማቴዎስ 9፡18)

“በታንኳይቱም የነበሩት፦ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት።” (ማቴዎስ 14፡33)

“እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና፦ ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።” (ማቴዎስ 28፡9)

“ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፡፡” (ማርቆስ 5፡6)

“እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡” (ሉቃስ 24፡52)

“እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።” (ዮሐንስ 9፡38)

“ቶማስም፦ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።” (ዮሐንስ 20፡28-29)

ኢየሱስ አምላክ ባይሆን ኖሮ ሰዎች ማንነቱን ተረድተው ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ስግደትና አምልኮ ሲሰጡት ከመቀበል ይልቅ በተቃወማቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን አላደረገም፡፡

«ኢየሱስ ቃል በቃል አምላክ ነኝ፣ አምልኩኝ» ካላለ በስተቀር አምላክ መሆኑን አላምንም ብሎ መካድ ልክ እንደ እምነት የለሾች «ፈጣሪ እራሱ ተገልጦ ‘እኔ አምላካችሁ ነኝ፤ አምልኩኝ’ ካላለና አምላክ መኖሩን በአይኔ ካላየሁ አላምንም» እንደ ማለት ነው፡፡

ሙስሊም ወገኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክነቱ የተመሰከረውን በማጣጣል ኢየሱስ ክርስቶስ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ቃል በቃል «‹እኔ አምላክ ነኝ፣ አምልኩኝ›› ብሎ የተናገረበትን ቦታ እንድናሳያቸው ይጠይቁናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ «መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ተራበ፣ ተጠማ፣ ደከመ፣ ወዘተ.» ይላል ይሉና፤ ከዚህም በመነሳት «የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚደክም አምላክ የለንም» በማለት የኢየሱስን አምላክነት ይክዳሉ። የሚገርመው ግን፣ በአንድ በወገን ኢየሱስ ቃል በቃል የተናገረውን ብቻ ነው የምንቀበለው እያሉ በሌላ ወገን ደግሞ ኢየሱስ እራሱ ቃል በቃል ያልተናገረውን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን ጥቅስ አምነው ተቀብለዋል። ደግሞም ነብያትና ሐዋርያት የመሰከሩትንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተተውን የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጠውን ማስረጃ ስንጠቅስላቸው «ይህን ያለው እገሌ ነው፣ ኢየሱስ አይደለም፣ ስለዚህ ተቀባይነት የለውም» ይላሉ፡፡

ለመሆኑ በቁርኣን ውስጥ የተጻፈውን የተናገረው ማን ነው? እያንዳንዱ የቁርኣን ቃል «ነብዩ» ሙሐመድ ተገለጠልኝ ያለው አይደለምን? ሲገለጥለት ማን አየ? እሱ እራሱ ተገለጠልኝ ያለውን ነው እንዲጻፍ ያዘዘው። ስለዚህ ቁርኣን ውስጥ የተባለው በሙሉ ሙሐመድ አላህ እንደነገረው የተናገረው ነው፤ ሙሐመድ ደግሞ በዐይን እማኞች በተላለፉት ሐዲሳት ከተጻፈው የሕይወት ታሪኩ አንጻር ሲታይ እንኳንስ ለመጨረሻ ነብይነት መመረጥ ይቅርና ጭራሽ ለነቢይነት የሚያበቃ ስብዕና አልነበረውም፡፡ ለበለጠ መረጃ የሙሐመድን ነቢይነት የማልቀበልባቸው 12 ምክንያቶች በሚል ርዕስ የተጻፈውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡

ሙስሊም ወገኖች የኢየሱስን አምላክነት የማይቀበሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ‹‹እኔ አምላክ ነኝና አምልኩኝ›› ስላላለ አይደለም፡፡ ቃል በቃል መናገር ከልብ የሚያምኑበት መስፈርት ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ›› ‹‹ስለ ሰው ልጆች ለመሞት ነው የመጣሁት›› ‹‹እሰቀላለሁ›› ወዘተ. ብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃል ስለተናገረ እነዚህን መሠረታዊ እውነቶች በተቀበሉ ነበር (ማቴዎስ 20፡28፣ 26፡28፣ ማርቆስ 10፡45፣ 14፡24፣ ሉቃስ 18፡32-33፣ 22፡20፣ 24፡6-7፣ ማቴዎስ 27፡43፣ ዮሐንስ 10፡36፣ 11፡4፣ 19፡7)፡፡ ጉዳዩ የእምነትና የክህደት ጉዳይ እንጂ የአጻጻፍ ሁኔታ አይደለም፡፡ ሙስሊም ወገኖች ቁርኣንና ሌሎች እስላማዊ መጻሕፍት የሚያስተምሩት ትምሕርት በምንም ዓይነት የአጻጻፍ ሁኔታ ተጽፎ ቢገኝ ‹‹ይህንን እከሌ ቃል በቃል ስላልተናገረ አንቀበልም፤ ይኸኛውን ደግሞ እከሌ ቃል በቃል ስለተናገረ እንቀበላለን›› አይሉም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስንም ቃል ‹‹ኢየሱስ ስላልተናገረ አንቀበልም›› የሚሉት ለክርክር እንጂ ኢየሱስ ቢናገር ስለሚቀበሉ አይደለም፡፡ ለእነርሱ እውነትን የመቀበያ መሥፈርታቸው አንድና አንድ ነው፤ እርሱም የሙሐመድ ትምሕርት ብቻ ነው፡፡ ከትምሕርቱ ጋር የሚስማማውን ይቀበላሉ የማይስማማውን አይቀበሉም፡፡ ሙሐመድ ያመነውን ያምናሉ፤ የካደውን ይክዳሉ፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ሚዛን የማይደፉ ሙግቶችን በማብዛት ነገሮችን ያወሳስባሉ፡፡

እውነትን ከልቡ የሚፈልግ ሰው የቅዱሳት መጻሕፍትን ማስረጃዎች ሁሉ በማጤን ከድምዳሜ ይደርሳል እንጂ እርሱ በሚፈልገው መንገድ የተጻፈችን አንዲት ጥቅስ ‹‹ካላየሁ›› ብሎ ሙጭጭ አይልም፡፡ እንዲህ ያለው ክርክር እስልምናንም ጭምር የሚጎዳ መሆኑን ለማወቅ የት እንደተጻፈ አሳዩን በሚል ርዕስ የተጻፈውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡ የኢየሱስን አምላክነት ለማወቅ የሚፈልጉ ሀቀኛ ሙስሊም ከሆኑ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ተናግሯልን? የሚለውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡

ጌታ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን፣ አሜን!

 

መሲሁ ኢየሱስ