እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ
የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ
ዘላለም መንግሥቱ
ደራሲ፥ ዶ/ር ሙሓመድ ዓሊ ኣልኹሊ
ትርጉም፥ አይታወቅም
አሳታሚ፥ ሑዳ ፕሬስ ሊሚትድ
የገጽ ብዛት፥ 91
የኅትመት ዘመን፥ 1989
ክፍል ሁለት
ባለፈው በክፍል 1 በዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ የተጻፈውን እስላምና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) የተሰኘ መጽሐፍ መገምገምና ማሔስ በመጀመር ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስን ስሕተት ሊያሰኝ የጣረበትን ነጥቦች ማየት ጀምረን ነበር። ሁለት ነጥቦች ብቻ ላይ ነበር የቆየነው። የመጀመሪያው 50 ሺህ ስሕተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖራቸውን በጭፍንነት ሲናገር ጥቅሶቹም እንኳ ያን ያህል እንደማያህሉ አይተን ነበር። ለአንድ ዶክተር እንዲህ የመሰለ ግልብ ክስ ማቅረብ ማንነቱን የሚገልጥ ሲሆን ምርምር ያልተደረገበት መሆኑን የሚያጋልጠው ማስረጃ ያለማቅረቡ ነው።
ሁለተኛው፥ ኦርጂናሌዎቹ ጠፍተዋል ላለው ተቆጥረው በቤተ መዘክሮች የተቀመጡ ከ25 ሺህ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ቁራጮች መኖራቸውን አውስተን የአሁኑ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ ጋር መስተያየት የሚችል መሆኑን በማሳየት ነበር። በዚህ በክፍል ሁለት ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተጻራሪ መሆናቸውን ለተናገረበት ምላሽ እሰጣለሁ። ተጻራሪ ሲል ያቀረባቸው ነጥቦች ብሉይ ትንሣኤ ሙታንን እንደማይቀበል አዲስ ኪዳን ግን እንደሚቀበል እና ብሉይ እግዚአብሔር ልጅ እንዳለው እንደማይቀበል አዲስ ኪዳን ደግሞ እንደሚያስተምር ነው። ሌላው በዚህ ክፍል የምጨምረው መጽሐፍ ቅዱስና ሳይንስ የሚጻረሩ መሆናቸውን ለማሳየትና መጽሐፍ ቅዱሳን ለማሳጣት ባቀረባቸው ሁለት ነጥቦች ላይ ምላስ እሰጣለሁ። ባለፈው ክፍል መግቢያ ላይ እንዳልኩት ይህ ግምገማና ሒስ ለመጽሐፉ ምላሽ ብቻ ሳይሆን እስልምናን መረዳትና በእኛ ስላለ ተስፋ ለሚጠይቁን መልስ ለመስጠት ዝግጁ ለመሆን ለምንሻ ሁሉ ጠቃሚ መሆኑን በማሰብ ነው።
ዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ ብሉይ እና አዲስ ኪዳን በእጅጉ የተለያዩ የእምነት መርሆዎች መሆናቸውን በተለይ ሁለት አሳቦችን በመጥቀስ ያብራራል። እነዚህ ሁለት አሳቦች የእግዚአብሔር ማንነት እና ዳግም ሕይወት ናቸው። ልዩነት ብሎ የጠቀሰው ብሉይ ኪዳን በአንድ እግዚአብሔር አዲስ ኪዳን ደግሞ በሦስት አማልክት ማመንን እንደሚያስተምሩና ብሉይ ኪዳን በዳግም ሕይወት እንደማያምንና አዲስ ኪዳን ደግሞ ይህንን እንደሚያስተምር ነው።
ተጻራሪ ኪዳኖች?
ጸሐፊው የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሰትነት ለመግለጥ የመጀመሪያው ክፍል ከኋለኛው ክፍል ጋር እንደሚጋጭ እንዲህ ሲል አቀረበ፤
ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ልጅም የለውም ይላል፡፡ ሐዲስ ኪዳን ግን ለእግዚአብሔር ልጅ ይሰጣል፤ ክርስትናም እግዚአብሔር ሦስት በአንድ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ብሉይ ኪዳን የፍርዱን ቀን ወይም መጪውን ሕይወት የማይቀበል ሲሆን ሐዲስ ኪዳን ግን ሁለቱንም ይቀበላል፡፡
እንዴት ልዩነት ይኖራቸዋል? እነኚህ ሁለት ኪዳኖች እውነት የእግዚአብሔር ቃል ቢሆኑ ኖሮ በነኛ መሠረታዊ የእምነት መርሆዎች ላይ ልዩነት ባልኖራቸው ነበር፡፡
በመጀመሪያ ስለ ኪዳን ምንነት መረዳት ተገቢ ነውና ይህን በማለት ልጀምር። ብሉይና አዲስ ኪዳናት ጸሐፊው እንዳለው እርስ በርስ የሚፋለሱ አይደሉም። ለክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ አንድ ክፍል ብቻ አይደለም። ብሉይ ኪዳን ትንሣኤ ሙታን የለም ብሎ አያስተምርም እንጂ አዲስ ኪዳን ይህን በግልጽ ካስተማረ በዚያ የሌለው ወይም በግልጽ ያልተሰጠው ትምህርት በዚህ መኖሩ የተጋጨ ሳይሆን የተሟላ ነው የሚያደርገው። ምክንያቱም አንድ መጽሐፍ ነዋ! በብሉይ ኪዳን በግልጽ ያልተነገሩ በርካታ አስተምህሮዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ማለት በአዲስ ኪዳን ተገለጡ፥ ግልጽ ሆኑ፥ ተፈቱ፥ ታዩ፥ ተፈጸሙ ማለት ነው እንጂ ተጻረሩ፥ ተፋለሱ ማለት አይደለም።
ጸሐፊው በለመደ ቋንቋው በመዘላበድ ‘እርስ በርሱ የሚፋለስ’ ያለው እውነት የሚፋለስ መሆኑን ለማብራራትና ለማሳየት በመሞከር ሳይሆን በሰማው ብቻ ተነሣስቶ ነው። ምክንያቱም ያቀረባቸው ነጥቦች ከመጽሐፉ ውስጥ የወጡ ሳይሆኑ የተባሉ ብቻ ናቸው።
እርስ በርሱ የሚፋለሰውን መጽሐፍ ቅዱስ ወይስ እርስ በርሱ የተጣጣመ፤ ግልጽና ብሩሕ የሆነውን ቁርኣን ነው ንጹህ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለው የሚመርጡት?
የኪዳንን ምንነት የማያውቅ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ይቸግረዋል። ስለዚህ የኪዳንን ምንነት በመመልከት እንጀምር። ኪዳን ወይም ቃል ኪዳን በሰዎች መካከል ወይም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚደረግ ቃል መጋባት ነው። ጥንት በሰዎች መካከል፥ እኩያ ባልሆኑ ሰዎች መካከል፥ ቃል ኪዳን ማድረግ የተለመደ ነው። ኃያሉ ታናሹን ሊከላከልለትና ሊጠብቀው፥ አናሳው ደግሞ ኃያሉን ሊታዘዘውና ሊገዛለት ይህ ስምምነት ይደረጋል። ብሉይ ኪዳን እንዲህ ያሉ ኪዳናት በእግዚአብሔር ለአዳም፥ ለኖኅ፥ ለአብርሃም፥ ለዳዊት፥ ለሰሎሞን የተገባባቸው ታሪክ ነው።
አዲሱ ኪዳን ደግሞ ገና በብሉይ ኪዳን ዘመን ተስፋ የተሰጠ፥ እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር ብሎ በነቢዩ ኤርምያስ (ኤር. 31፥31) የተናገረበት ኪዳን ነው። ይህ ኪዳን የተፈጸመው በክርስቶስ ሞት አማካይነት ነው። ጌታ የመጨረሻ ራቱን ከሐዋርያቱ ጋር ሲበላ፥ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።አለ፤ ማቴ. 26፥27-28። አዲሱ ኪዳን በክርስቶስ በደሙ የተመሠረተ ኪዳን ነው። በተጨማሪ፥ ማር. 14፥24፤ ሉቃ. 22፥20፤ 1ቆሮ. 11፥25፤ ዕብ. 8፥8፤ 9፥15፤ 12፥24 ተመልከቱ።
ይህ የክርስቶስ ደም ስለ ኃጢአታችን መፍሰሱና እርሱ በመስቀል ላይ መሞቱ ቁርኣን በአጽንዖት የሚክደው ጉዳይ ነው። ይህ የክርስትና እንብርት የሆነ ጉዳይ በመሆኑ ቢክደው አያስደንቅም። ዮሐንስ በመልእክቱ በግልጽ እንደጻፈው የእውነተኛና የሐሰተኛ መንፈስ መለያ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን መቀበልና ያለመቀበል ነው፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 1ዮሐ. 4፥2-3። በሥጋ የመጣ ማለት ቀድሞ የነበረና ሥጋ ለብሶ የተገለጠ ማለት ነው። ደራሲው ስለ ክርስቶስ የሚያነሣበት ምዕራፍ ስለሚኖር በዝርዝር እዚያ እመለስበታለሁ።
ወደ ትችቱ ነጥብ ለመመለስ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን መናገሩ እውነት ነው። ዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ እንዳለው ግን ይህ የብሉይ ኪዳን ትምህርት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር አንድ መሆን ግልጽ ነው። ለምሳሌ፥ ዘዳ. 6፥4። አዲስ ኪዳንም ይህን ያስተምራል፤ ለነገሩ ሰውየው ኪዳናትን ሊለያይ የፈለገው የክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳን ብቻ አለመሆኑ ጠፍቶበት አይመስለኝም። የኪዳናቱን ልዩነት የእምነቱ ልዩነት ለማስመሰል ነው። አዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር አንድ አምላክ መሆኑን ያስተምራል። እንዲያውም ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ አጋንንትም እግዚአብሔር አንድ መሆኑን እንደሚያምኑ እንኳ ተጽፎልናል፤ እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። ያዕ. 2፥19። በተጨማሪ በአዲስ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር አንድ መሆን የተጻፈውን ለማየት ለምሳሌ፥ ሮሜ 15፥5-6፤ 1ቆሮ. 12፥6፤ ገላ. 3፥20፤ 1ጢሞ. 2፥5።
ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮት ስንመጣ ግን መለኮት በብሉይ አንድ አምላክ ሳለ በነጠላ ስም በብዙ ስም፥ በነጠላ ግስ በብዙ ግስ እግዚአብሔር የሚጠራባቸው ቦታዎች በመለኮትነቱ ውስጥ ከአንድ በላይ አካላት ለመኖራቸው አስረጅ ነው። ለምሳሌ፥ ኤሎሂም የተሰኘው ስም የነጠላ ሳይሆን የብዙ ስም ነው። ያህዌህ ወይም ይሆዋህ ደግሞ ነጠላ ነው። በብዙው ባለቤት ነጠላ ግስ ሲገባና በነጠላው ባለቤት የብዙ ግስ ሲገባ ይህን ግልጽ ያደርገዋል። ለምሳሌ፥ ዘፍ. 1፥1 በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ይላል። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ብዙ፤ ፈጠረ ነጠላ ነው። በዘፍ. 2፥18 ደግሞ፥ እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ይላል። እግዚአብሔር (ይሆዋህ) የነጠላ ባለቤት ሆኖ እንፍጠር የብዙ ግስ ነው። እንዲህ ያሉ ብዙ ምሳሌዎች ሲኖሩ ይህ እንግዲህ አንድ ምሳሌ ሆኖ ወደ ነጥቡ ያመለክተናል። ነጥቡም እግዚአብሔር አንድ አምላክ ሆኖ ሳለ በዚህ አንድ መለኮታዊ ኅልውና ውስጥ አካላት መኖራቸው ይታያል። ብሉይ ኪዳን በሰፊው ሳያብራራ እስከዚህ ድረስ ይገልጠዋል።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ ወይም እግዚአብሔር ወልድ በአካል ሥጋን ለብሶ አልተገለጠም ነበርና በአዲስ ኪዳን እንደተገለጠው ትምህርት የመሰለ ትምህርት አናገኝም። ይህ እውነት ግልጽ ሆኖ የተከሰተው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነው። ኢየሱስ በመጀመሪያ የነበረ ቃል፤ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ ቃል፤ እግዚአብሔር የነበረ ቃል መሆኑ ተጽፎአልና (ዮሐ. 1፥1) ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። ደግሞም መንፈስ ቅዱስ አምላክ መሆንኑም ተጽፎአል፤ ሐዋ. 5፥3-4። በተለያዩ ስፍራዎች አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት መጠቀሳቸው (ለምሳሌ፥ ማቴ. 28፥19-20፤ 2ቆሮ. 13-14) ትምህርተ ሥላሴን የተሟላ ያደርገዋል። ይህ በብሉይ ኪዳን በግልጽ ያልተብራራ ነው። ይህ በአዲስ ኪዳን መገለጡ ግን ተጻራሪ አያደርገውም።
እንግዲህ ዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ እንዳለው ብሉይ ኪዳን አንድ አምላክ፥ አዲስ ኪዳን ደግሞ ሦስት አማልክት የሚያስተምሩ አይደሉም። የሥላሴ አስተምህሮ ሙስሊሞች እንደሚረዱት ሦስት አማልክት ማለት ሳይሆን በአንድ መለኮት የተገለጡ ሦስት አካላት ማለት ነው። ቁርኣንና ሙስሊሞች የክርስቲያኖች አማልክት እግዚአብሔር ኢየሱስ እና ማርያም እንደሆኑ ነው የሚያቀርቡት። ዛሬ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን የመረመሩቱ ሥላሴ እግዚአብሔር፥ ኢየሱስና ማርያም ናቸው አይሉም። ግን ሦስት አማልክት የምናመልክና እግዚአብሔርን የምናጋራ እንደሆነ ያምናሉ። ነገር ግን ቢያንስ ቁርኣን በተጻፈበት ዘመን የነበረው የቀድሞው መረዳት ይህ መሆኑን እንመልከት፤
5፥17 እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ፣ በእርግጥ ካዱ፤ የመርየምን ልጅ አልመሲሕን እናቱንም በምድር ያለንም ሁሉ ለማጥፋት ቢሻ ከአላህ ማዳንን የሚችል ማነው? በላቸው። የሰማያትና የምድር የመካከላቸውም ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፤ የሚሻውን ይፈጥራል። አላህም በነገሩ ላይ ቻይ ነው።
5፥116 አላህም፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ ፦ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ)፤ ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፤ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል።
ስለዚህ ነው ክርስቲያኖች ሦስት አማልክት እንዳሉአቸው የሚያስተምሩትና ክርስቲያኖችን አጋሪ አድርገው የሚቆጥሩት። ጥንት በሙሐመድ ዘመንም ሆነ ከዚያ በፊትና ከዚያም በኋላ ክርስቲያኖች ሥላሴ ብለው እግዚአብሔርን፥ ኢየሱስንና ማርያምን እንደማያመልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ታሪክም ምስክር ነው። ለማርያም የተለየና ከተጻፈው ያለፈ አክብሮትና አድናቆት ባላቸው ወገኖችም ዘንድ እንኳ እንዲህ ያለው ትምህርት ከቶ አልተሰማም፤ አሁንም አይሰማም። እነዚህም እንኳ ሥላሴ የሚሉት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስን ነው እንጂ እግዚአብሔርን (አብን)፥ ኢየሱስንና ማርያምን አይደለም።
የእግዚአብሔር ልጅ
በገጽ 3-4፥ ሁለት የሐሰት ክሶችን በማቅረብ እንዲህ ይላል፤
ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ልጅም የለውም ይላል፡፡ ሐዲስ ኪዳን ግን ለእግዚአብሔር ልጅ ይሰጣል፤ ክርስትናም እግዚአብሔር ሦስት በአንድ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ብሉይ ኪዳን የፍርዱን ቀን ወይም መጪውን ሕይወት የማይቀበል ሲሆን ሐዲስ ኪዳን ግን ሁለቱንም ይቀበላል፡፡
እንዴት ልዩነት ይኖራቸዋል? እነኚህ ሁለት ኪዳኖች እውነት የእግዚአብሔር ቃል ቢሆኑ ኖሮ በነኛ መሠረታዊ የእምነት መርሆዎች ላይ ልዩነት ባልኖራቸው ነበር፡፡
“ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አንድ ነው ልጅም የለውም” ይላል ሲል ይህ አጠቃቀስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ሥልጣናዊ አጠቃቀስ ይመስላል። ግን እርሱ እንዳለው የሚል ቃል አለ? መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቅ ሰው እየጠቀሰ ሳይሆን እያለ መሆኑን ያስተውላል። ማለት ደግሞ መጥቀስ አይደለም። ይህ ማወናበጃ ብዙዎች አዋቂ ለመምሰልና ለማሳት የሚጠቀሙበት ስልት ነው። “አዲስ ኪዳን ግን ለእግዚአብሔር ልጅ ይሰጣል” ደግሞ ይላል። አባባሉ የወልድ ማንነት በአዲስ ኪዳን የተገለጠ መሆኑን ማመልከቱ ቢሆንም አገላለጡ ሰጪዎቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች መሆናቸውን መናገሩ ነው። ይህን በተመለከተ ዋናው ስሕተት ይህ ነው። ወልድ ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን ራሱ ገለጠ እንጂ አዲስ ኪዳን ልጅ ያልነበረውን ልጅ አላደረገውም። ማለትም፥ ከአብ ጋር የነበረውንና ያለውን ዘላለማዊ ቁርኝት ኢየሱስ ራሱ አስተማረ እንጂ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች አልጻፉትም። ጸሐፊዎቹ የጻፉት እርሱ ያስተማረውንና ካስተማረው የወሰዱትን እንጂ የፈጠሩትንና የፈለሰፉትን አይደለም።
ለምሳሌ፥ ኢየሱስ፥ እኔና አብ አንድ ነን አለ፤ ዮሐ. 10፥30። አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ። ምክንያቱን ሲናገሩ አንተ ሰው ሳለህ ራስህን አምላክ በማድረግህ ነው አሉ። ይህ ትምህርቱ ገብቶአቸዋል። ኢየሱስ የተከሰሰበትም የተሰቀለበትም ምክንያት ሌላ ሳይሆን ይህ ነው።
ሙሐመድ በሰበከበት ዘመን የተውሂድን (የአላህን አንድ ብቻነት) በመስበክ በመካ በካዕባ ውስጥ 360 ያህል አማልክት ይመለኩ የነበረበትን የብዝሐ አምልኮ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን አይሁድንና ክርስቲያኖችንም የከሰሰበት ሁኔታ ነበረ። አይሁድና ክርስቲያኖች የተውሂድ ተቃራኒ ትምህርት እንዳላቸው የተናገረበት አንድ ጥቅስ እንዲህ ይላል፥
9፥30 አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነዉ፣ አለች፤ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነዉ አሉ፤ ይህ በአፎቻቸዉ (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፤ የነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፤ አላህ ያጥፋቸዉ (ከእዉነት) እንዴት ይመለሳሉ!
ዑዘይር የተባለው ዕዝራ ነው። በአይሁድ መጽሐፍና ትምህርትም ሆነ በታሪካቸው ዕዝራን የእግዚአብሔር ልጅ ብለው እንደማያውቁ የተረጋገጠ ነው። ጥንትም ብለው አያውቁም፤ በሙሐመድ ዘመንም አልተባለም፤ ዛሬም ቢጠየቁ ይህን አይሉም። ይህ የቁርኣን ምዕራፍ (ምዕራፍ 9) እንደሚባለው የመጨረሻው ምዕራፍ ነው። [ቁርኣን በተነገረበት ቅደም ተከተል የተጻፈ አይደለም ከፊሉ በመካ፥ ከፊሉ በመዲና (አል መኪያ እና አል መዲኒያ ይባላሉ) የተነገረ ሆኖ ተሰባጥረው ነው የተጻፉት።] የመጨረሻው ምዕራፍ በመሆኑም እንደ መጀመሪያዎቹ የመካ ምዕራፎች የመጽሐፉ ሰዎች የሚባሉትን አይሁድና ክርስቲያኖች በልሥላሴ የሚቀርብ ሳይሆን እንደ ሐሰተኞች የሚፈርድና የሚኮንን ሆኖ ቀርቦአል። ስለ ዕዝራ የተነገረው ቃል ከላይ እንዳልኩት በየትም አይገኝም። አይሁድ እንዲህ ያለ ትምህርት ያስተማሩበት ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከቶም የለም። ያው እንደተለመደው ጠፍቷል ወይም ተሰርዟል ካልተባለ በቀር ያኔም፥ ዛሬም ተፈልጎ አይገኝም። ።
ስለ ክርስቶስ አምላክነት ግን ከላይ እንደተጠቀሰውና ጸሐፊው እንደመሰለው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የፈጠሩት ሳይሆን ራሱ ኢየሱስ ያስተማረው ነው። ኢየሱስ ያለውንና ያስተማረውን ካልሆነ ሊታመንም ያልተገባው ውሸታም ነው እንጂ ነቢይ ብለው ሊቀበሉትም ያልተገባ አታላይ ነው። እውነተኛ ነው የምንል ከሆነ ስለራሱ ያለውን፥ ያስተማረውን ሁሉ መቀበል ይገባናል። የምንቀበል ከሆነ ኢየሱስ ያለውንና ያስተማረውን የሆነ መሢሕ፥ ከዘላለም የነበረና ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነ አምላክ ነው። ስለ አንድ ሰው የምናውቀው ሌላ ሰው ስለዚያ ሰው ከሚናገረው ይልቅ ያ ሰው ራሱ ስለራሱ ከሚናገረው ነው። በቁርኣን ውስጥ ስለ ኢየሱስ ትምህርትና ስለማንነቱ ከአፉ የሚደመጥ ምንም አናገኝም። ስለ ኢየሱስ ማንነት ምስክርነቱን የሚናገረውም ፍርዱን የሚበይነውም ሙሐመድ ነው። የዶ/ር ዓሊ መጽሐፍ ስለ ክርስቶስ የሚናገረው ሌላ ሰፊ ክፍል ስላለ ወደዚያ ወደፊት እንመጣለን። እዚህ ሳይስተዋል መታለፍ የሌለበትን አንድ ነጥብ ብቻ፥ ማለትም፥ የኢየሱስ ኅልውና በቤተ ልሔም ሲወለድ ያልተጀመረና ለእግዚአብሔር ልጅ የሰጡት የወንጌል ጸሐፊዎች አለመሆናቸውን፥ ጸሐፊዎቹ ኢየሱስ ራሱ ከዘላለም የነበረ የአብ ልጅ መሆኑን የተናገረውን መጻፋቸውን፥ አስተውለን ወደ ሁለተኛው ነጥብ እንለፍ።
ብሉይ ኪዳንና ትንሣኤ ሙታን
የዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ ሁለተኛ ነጥብ ብሉይ ኪዳን የፍርድ ቀንን እና መጪውን ሕይወት የማይቀበልና አዲስ ኪዳን ይህንን የሚቀበል መሆኑን ጽፎአል። ይህ በብሉይ ኪዳን ላይ የተከፈተ የሐሰት ክስ ነው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ብሉይና አዲስ አንድና ወጥ መልእክት ያላቸው መሆኑና ይህ የዘላለማዊ ሕይወት ተስፋ በእጅጉ የተብራራው በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ደራሲውም አዲስ ኪዳን ይህን የፍርድ ቀንና መጪውን ፍርድ እንደሚቀበል ስላመነ ይህንን ከአዲስ ኪዳን ማብራራት ትቼ ብሉይ ኪዳን ፍርድንና መጪውን ሕይወት እንደሚቀበል የጥቂት ጥቅሶች ማስረጃ ላቅርብ።
ኢዮብ፥ እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ አለ፤ ኢዮ. 19፥25-26።
ዳዊት፥ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ ብሎ ተናገረ፤ መዝ. 16፥10-11።
ደግሞም እንዲህ አለ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ይቀበለኛልና ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል። መዝ. 49፥15።
ኢሳይያስ፥ ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም አለ፤ ኢሳ. 26፥19።
ዳንኤል እንዲህ አለ፥ በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና። ዳን. 12፥2።
ታዲያ እንዲህ የሚሉ ግልጽ የሆኑ ትምህርቶች ኖረውበት ብሉይ ኪዳን ስለመጪው ሕይወት አያምንም አይቀበልም ማለት ቅጥፈት አይደለም? እርግጥ ነው፤ በስፋት ስለ ትንሣኤ ሙታን አላስተማረም። አብዛኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በባህርያቸው ታሪካዊና በዘመኑ ላይ ያተኮሩ ትንቢታዊ መጻሕፍት ናቸው። ስለዚህ በነባራዊው ሁኔታቸው ላይ ያተኮሩ ናቸው። በአዲስ ኪዳን በግልጽና በትንታኔ እንደምናገኘው የሰፋና የጠለቀም ባይሆን ትምህርቱ፥ ማለትም ከሞት በኋላ ሕይወትና ፍርድ፥ ሽልማትና ቅጣት፥ ዘላለማዊነትም አለ እንጂ በደፈናው ከቶም እንደሌለና ተጻራሪ አስመስሎ ማቅረብ ሐሰት ብቻ ሳይሆን እኩይ ግፊት ያለበት ትምህርትም ነው።
ከቅይጥ ጸሐፊዎቹና ከብርዝ ይዘቶቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ነው? ወይስ አንድ ወጡን ቁርኣን ነው የጠራ የእግዚአብሔር ቃል አድርገው ለመቀበል የሚዳዳዎት?
የዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ መጽሐፍ በክፍል አንድ እንደጻፍኩት መነሻው ቃሉን መርምሮ ምላሽ መስጠት ሳይሆን ከጅምር እስከ ድምዳሜ የተሳሳተ አድርጎ በመሳል ለበሰሉና ቃሉን ለሚያውቁ ሰዎች ሳይሆን በእስልምና ከባቢ ውስጥ ላሉ ወይም ቃሉን ከቶም ላላዩና ላላነበቡ መጽሐፉን አጥላልቶ በማቅረብ እንዲያጣጥሉት ለማበረታታት ነው። ሰዎች አንድን ክስ ሳይመረምሩ እንዲፈርዱ ማስገደድ እንደማለት ነው። በእውነት መጽሐፍ ቅዱስን ከልብ የሚመረምር ማንም ሊረዳው የሚችለው እርስ በርሱ የሚፋለስ ሳይሆን በአስገራሚ ሁኔታ በዘመናትና በስፍራ የተራራቁ በቁጥርም ብዙ የሆኑ ሰዎች የጻፉት አንድ ወጥ መልእክት መሆኑን ነው። ጸሐፊው ቅይጥ ጸሐፊዎችና ብርዝ ይዘት የሚለውን ለማብራራት ያቀረበው ማስረጃ ሳይኖር ነው ወደ ምርጫ ድምድዳሜ የተንደረደረው።
ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ፥ ሳይንስና ቁርኣን
የዶ/ር ዓሊ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስና ሳይንስ እንደሚጋጩ ቁርኣን ግን እንዲያውም በቅርቡ የተገኙ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ሳይቀር አጠቃልሎ የያዘ መሆኑን በአንድ ንዑስ ርእስ ስር ጽፎአል።
በመጀመሪያ መስተዋል ያለበት ነገር መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሰዎች ደኅንነትን ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለማሳየት እንዲጻፍ ያደረገው መጽሐፍ እንጂ ለሳይንሳዊ አእምሮና ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥበት የተጻፈ መጽሐፍ አለመሆኑ መታወቅ አለበት። ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ በተመሳሰሉባቸው ጉዳዮች መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ ተፈትሾ ትክክለኛ ሆኖ መገኘቱን የሚያስቡና ይህ የሚያስደስታቸው ሰዎች የጌታን ቃል እና የቃሉን ጌታ ጠንቅቀው ያልተገነዘቡ ሰዎች ናቸው። ለሳይንስ በቂ ጊዜ ስጡት፤ አንድ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ስር ይንበረከካል። እውነተኛ ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ይጻረራሉ ማለት አይደለም። በተለምዶ ሳይንስ የሚባለው ሁሉ ግን እውነት ነው ማለትም አይደለም። ጤናማ ሳይንስ አለ። መለኮታዊ ኅልውናን በጭፍን የሚጻረር ሳይንስ ተብዬም አለ። ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ ግን፥ በእውነቱ የሰው ልጅ መሠረታዊ ጉድለት ሳይንሳዊ እውቀት ሳይሆን መለኮታዊ እውነት ነው።
ጽንፈ ዓለም (ዩኒቨርስ) እና ፍጥረት በዝግመት ተገኘ የሚለው ከቃሉ የሚጣላ ሳይንስ ነው። ጸሐፊው ሳይንስን ሲደግፍ ሰው ከዝንጀሮ መምጣቱን መቀበሉ አይመስለኝም። ወይም መሬት ከቢልዮን ዓመታት በፊት በዝግመት መምጣቷን መቀበሉም አይመስለኝም። አቀራረቡ ሳይንስን ወግኖ የሚቆም ይመስላል። ከሆነ ከራሱ መጽሐፍም ጋር መጣላቱ ነው። ወይስ መክሰሻ ብቻ ፈልጎ ማቅረቡ ነው? ከልባቸው የተሰጡ ክርስቲያኖች በሳይንስ እውቀት የመጠቁ መሆናቸውና ከቀደምት ታዋቂ ሳይንቲስቶች በርካቶቹ እግዚአብሔርን የሚወድዱና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡና የሚታዘዙ መሆናቸው ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስን ተጻራሪ አድርገው አለመመልከታቸውን ያረጋግጣል። ዛሬ ዛሬ የሳይንስ ጠበብቶችም እንኳ ረቂቅና ትንግርታዊ ለሆነው ፍጥረት በራሱ ያለመምጣት ምላሽ ሲሰጡ እግዚአብሔር ፈጠረው ላለማለት በIntelligence Design ወይም Intelligent Designer ተፈጠረ ይላሉ።
የዶ/ር ዓሊ መጽሐፍ የራሱ የጸሐፊው ነቢይ እንኳ ያላጣጣለውን መጽሐፍ ለማጣጣል ዘመናዊ ምክንያት ማፈላለጉ የሚያስገርምም ነው። ይህ እኮ አላስተዋለውም እንጂ ከራሱ ጋርም የሚያጋጨው ነው። እንዲጠይቅበት ወይም እንዲያረጋግጥበት በራሱ ነቢይም የተነገረውን መጽሐፍ ለማጣጣል ምክንያት ፈልጎ ሁለት አግኝቶ አቀረበ። ካቀረባቸው ሁለት ነጥቦች አንዱ ዘፍ. 1፥5ን በመጥቀስ ፀሐይና ጨረቃ ኋላ የተፈጠሩ ሆነው ሳለ እንዴት ብርሃንና ጨለማ ሊኖር ይችላል? ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይጋጫልና ስሕተት ነው የሚል ነው።
(ዘፍጥረት 1፡5) ላይ እግዚአብሔር ብርሃንን፣ ጧትና ሌሊትን በመጀመርያው የፍጥረት ቀን እንደፈጠረ ተጠቅሷል፡፡ በመቀጠልም ጨረቃን፣ ፀሐይንና ከዋክብትን በአራተኛው ቀን ፈጠረ (ዘፍጥረት 1፡14) እያለ ይቀጥላል፡፡ የብርሃን ምንጮች የሆኑት ዘግየት ብለው ከሦስት ቀናት በኋላ የተፈጠሩ ከሆኑ ብርሃን፣ ጧትና ማታ በመጀመርያው ቀን እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ?
ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣጣል ታጥቀው የሚታገሉ ሰዎች እንደሚያደርጉት ይህ ጸሐፊም ጥቅስን ከዐውዱ ፈልቅቆ ነው የጠቀሰው። ገና በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለና ብርሃን ተፈጠረ። ስለዚህ ፀሐይና ጨረቃም ሳይኖሩ ብርሃን ነበረ ማለት ነው። እግዚአብሔር ራሱ ብርሃን መሆኑ በቃሉ ተጽፎአል። ለእግዚአብሔር ቀንን ለመቁጠር እነዚህ ነገሮች ያስፈልጉታል ማለት አይደለም። ይህ አጠያያቂ ሊሆን ያልተገባው ነገር ነው። ለኛ ትልልቆቹ የብርሃናት ምንጮች ፀሐይና ጨረቃ ስለሆኑ የጊዜ መለኪያችን እነርሱ ናቸው። ከነዚህ መፈጠር በፊት ብርሃን ከኖረ ችግሩ ምንድርነው? እንዳለ ደግሞ በግልጽ ተጽፎአል።
ወይም መሬት ገና ያልተገለጠችና የተሸፈነች ናትና የተፈጠሩት ተገልጠው እንዳልታዩ ይስተዋላል። የተፈጠሩት ሁሉ ቀድሞውኑ ተፈጥረው ኋላ ሥራቸውና ስፍራቸው ነው የተመደበው። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ለተፈጠሩት ነገሮች በመጨረሻዎቹ ሦስት ቀናት የተደረጉትና የተፈጠሩት ሙሉ አድራጊዎች ናቸውና። ጸሐፊው በስሕተት ወይም ለማሳሳት ሆን ብሎ እንደጻፈው “ጨረቃን ፀሐይንና ከዋክብትን በአራተኛው ቀን ፈጠረ” አይልም። ቃሉ ፈጠረ ሳይሆን ይሁኑ አለ እና አደረገ ነው የሚለው። ስፍራን አድራጎትን እና የሥራ ድርሻን መግለጡ ነው።
ሁለተኛ ስሕተት አድርጎ ያቀረበውን እንዲህ ጽፎታል፤
ሌላው ምሣሌ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ውኃ (ዘፍጥረት 1፡2) በመጀመርያው ቀን የተፈጠረ ሲሆን ሳይንስ የሚያረጋግጠው ግን ዩኒቨርስ የጀመረው በጋስ ደመና ዓይነት መሆኑን ነው፡፡ ታድያ ጋስ የውቂያኖሶችን ውኃ እንዴት ሊሸከም ይችላል?
ዘፍ. 1፥1 ሰማይና ምድር ተፈጠሩ ካለ በኋላ ዘፍ. 1፥2 የሚለው ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር ነው። ጋስ የውቅያኖሶችን ውኃ ስለመሸከሙ የሚናገር ቃል በዚህ ጥቅስ ውስጥ የለም። ይህንን ከየት እንዳገኘው አይጽፍም። ወይም ተርጓሚዎቹ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን እንዴት እንደተጻፈ ከቶም አላነበቡትም። እንደ ተርጓሚ ቢያንስ ማየት ነበረባቸው። ስለዚህ ጸሐፊው ሊያጣጥል የፈለገው አሳብ ራሱ በቃሉ ውስጥ የለም። ክሱ ራሱ የተመሰረተበት ወንጀል በዘፍ. 1፥2 ውስጥ የለም። ታዲያ ይህ ያልተጻፈውን እንደተጻፈ አድርጎ የማቅረብ ሐሰት ዓላማው ምንድርነው?
ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት መሆኑን ለማረጋገጥ ታማኝ ምስክር አድርጎ የጠራው ሳይንስን ሲሆን ሳይንስ ዩኒቨርስ የጀመረው እንደዚህ ነው በማለቱ ዩኒቨርስ የተጀመረ እንጂ የተፈጠረ አለመሆኑን አምኖ ይቀበላል ማለት ነው። እና ይህ ሰው በፈጣሪ ያምናል ወይስ ፍጥረት በራሱ የተገኘ ነው ብሎ ይቀበላል? ተብሎ ቢጠየቅ ከጽሑፉ እንደምንረዳው የተፈጠረ ሳይሆን ሳይንስ እንደሚለው በዝግመት የተገኘ አድርጎ የሚቀበል መሆኑ ይታያል።
ሌላው የሚያስተዛዝበው ነገር ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስን ባወገዘበት ነገር ሳይንሳዊ ግኝቶችና ቁርኣን ከተጣሉ ምላሽ እንዳለው አለመናገሩ ነው። ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳተ እንደሆነ አድርጎ ባቀረበበት ስሕተት ላይ የራሱን መጽሐፍ ምላሽ አለመስጠቱ ነው። ገጽ 5 እንዲህ ይላል፤
የእስላም መጽሐፍ የሆነው ቁርኣን ግን ከሳይንሳዊ እውነታዎች ጋር ፈጽሞ አይቃረንም፡፡ ይልቅዬ ከቅርብ ዘመን ወዲህ እንጂ በሰው ልጅ ዘንድ ያልታወቁ ሳይንሳዊ እውነታዎችን አጠቃሎ ይዟል፡፡
እንደተለመደውም መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይጻረራል የሚላቸውን ሁለት ምሳሌዎች ሲያቀርብ “አጠቃሎ ይዟል” ካላቸው ውስጥ ቁርኣንና ሳይንስ የሚወዳጁባቸውን አንድም አስረጅ አላቀረበም። ለነገሩ ቁርኣንን የተዋጣለት የሳይንስ ግኝቶች ሁሉ ያረጋገጡትና ያደነቁት አድርገው የሚያቀርቡ የዋሆች ወይም አሳቾች ብዙ ናቸው። ጸሐፊው እንዳለው ቁርኣንና ሳይንስ ጠበኞች እንደሆኑ በጥቂቱም ቢሆን እንይ።
ሀ. በ18፥85-86
መንገድንም (ወደ ምዕራብ) ተከተለ። ወደ ፀሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት፤ ባጠገቧም ሕዝቦችን አገኘ፤ ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም (በመግደል) ትቀጣለህ ወይም በነርሱ መልካም ነገርን (መማረክን) ትሠራለህ አልነው።
ይህ አንቀጽ ፀሐይ ወደ ጥቁር ጭቃ ምንጭ ስትጠልቅ ዙልቀርነይን የተባለው ሰው እንዳገኛት ይናገራል። በአማርኛው የግርጌ ማስታወሻ ተደርጎለት “በዓይን አስተያየት በውኃ ውስጥ የምትጠልቅ መስላ” የሚል ተጨምሮአል። ቢሆንም በዓይን አስተያየት በስተ ፀሐይ መጥለቂያ ቅላት እንጂ ጥቁር ጭቃ አይታይም። በሌሎች ትርጉሞችይህ በአማርኛው ቁርኣን የተጻፈው አይገኝም። ይህ ከሳይንሱ ጋር እርቅ ለመፍጠር ታስቦ የተጨመረ ነው።
ለ. አሁንም ዓለማትን በተመለከተ በሌላ ስፍራ ሰባት ሰማይና ሰባት ምድር መፈጠራቸው ተጠቅሶአል። በ65፥12
አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፤ ከምድርም መሰላቸውን (ፈጥሮአል)፤ በመካከላቸውም ትእዛዙ ይወርዳል፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አላህም በነገሩ ሁሉ በእውቀት ያካበበ መሆኑን ታውቁ ዘንድ (ይህንን አሳወቃችሁ)።
ጋስ የውቅያኖሶች ተሸካሚ መሆንን ወይም ያለመሆን መርምሮ ከዩኒቨርስ ሕግ ጋር አይስማማም ያለው ይህ የሰባት ሰማያትና የመሰላቸው (ሰባት ምድሮች?) ከዩኒቨርስ ወይም ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር መስማማቱን ሊያብራራ ይችል ይሆን?
ሐ. ስለ ሰማይ ከተነሣ 67፥5 የሚለውን እንይ፤
ቅርቢቱን ሰማይም በእርግጥ በመብራቶች (በክዋክብት) አጌጥናት፤ ለሰይጣናትም መቀጥቀጫዎች አደረግናት። ለነርሱም (ለሰይጣኖች) የእሳትን ቅጣት አዘጋጀን።
ይህ አንቀጽ እና 37፥6 እና 10 ተጨምረው ከዋክብት፥ በተለይም አብሪ ወይም ተወርዋሪ ከዋክብት የሰይጣናት መቀጥቀጫ መሆናቸው ተጽፎአል። በአንድ የእንግሊዝኛ ቁርኣን ትርጉም [The Noble Qur’an] ‘And indeed We have adorned the nearest heaven with lamps, and We have made such lamps [as] missiles to drive away the Shayatin [devils], and have prepared for them the torment of the blazing fire’ ይላል። ይህስ ከዶ/ር ዓሊ የዩኒቨርስ ሕግ ጋር ይስማማ ይሆን?
መ. አሁንም ከዶ/ር ዓሊ የዩኒቨርስ ሕግ ሳንወጣ 88፥20 የሚለውን እንይ፥
ወደ ምድርም እንዴት እንደተዘረጋች (አይመለከቱምን?)
ይህ ስለመሬት ዝርግነት የሚናገር ነው። መሬት ጠፍጣፋ ወይም ዝርግ ናት ማለት ነው።
ሠ. 86፥6-7 የወንድ የብልት ዘር የሚመነጨው ከየት ነው?
ሰውም ከምን እንደተፈጠረ ይመልከት። ከተስፈንጣሪ ውሃ ተፈጠረ።ከጀርባና ከእርግብግብቶች መካከል የሚወጣ ከሆነ (ውሃ)።
እርግብግብት የሚለውን የእንግሊዝኛው ትርጉም የጎድን አጥንት ይለዋል፤ He was created from a fluid, ejected, emerging from between the backbone and the ribs ይላል። ሰው የተፈጠረበት ተስፈንጣሪ ውኃ ወይም የሰው የዘር ፈሳሽ የሚመነጨው ከጀርባና ከጎድን አጥንት መካከል ነውን?
ይህንን ነው ጸሐፊው፥ “ቁርኣን ግን ከሳይንሳዊ እውነታዎች ጋር ፈጽሞ አይቃረንም” የሚለው። እውነት አይቃረንም? እነዚህን ሰውየው፥ “አይቃረንም” ያላቸውን ተቃርኖዎች ለማስተዋልና ለማጤን ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም።
እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ – ዋናው ማውጫ
ለተጨማሪ ንባብ
- እስላማዊ አጣብቂኝ :- መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ቁርኣን ዋሽቷል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ካልተበረዘ ቁርኣን የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም!
- ኢንጂል ተበርዟልን?
- በእጃችን የሚገኙት ብሉይና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመን በአይሁዶችና በክርስቲያኖች እጅ ነበሩ፤ ቁርኣንም ይመሰክርላቸዋል
- ሃምሳ ሺህ ስህተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ? የአሕመድ ዲዳት ቅጥፈት
- የመጽሐፍ ቅዱስ አዘጋገብ [ክፍል 1] [ክፍል 2]
- የቁርኣን ታሪካዊ ስህተቶች
- በቁርኣን ውስጥ ሳይንሳዊ ትንብያዎች ይገኛሉን?