ሴቶች በቁርኣን በሐዲስና በመጽሐፍ ቅዱስ

ሴቶች በቁርኣን በሐዲስና በመጽሐፍ ቅዱስ

1. ሴቶች በቁርኣን

ቁርኣን ሴቶችን በተመለከተ ግልፅና ማብራርያ የማይሻ አስተምህሮ አለው፡፡ አጠቃላይ ሐሳቡም ሴቶች ከወንዶች እንደሚያንሱና ወንዶች የሴቶች የበላይ እንደሆኑ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የሴቶችን ፍጥረት ከሰው ደረጃ ዝቅ በማድረግ ለጥቃት ያጋልጣቸዋል፡፡ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናያለን፡-
ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ ብልጫ አላቸው፡- 2፡228 “… ለነርሱም (ሴቶች) የዚያ በነሱ ላይ ያለባቸው (ግዳጅ) ብጤ በመልካም አኗኗር (በባሎቻቸው ላይ መብት) አላቸው፡፡ ለወንዶችም (ጣጣቸውን ስለሚሸከሙ) በነሱ ላይ ብልጫ አላቸው፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡”

በዚህ ስፍራ ላይ “ጣጣቸውን ስለሚሸከሙ” የሚለው ንግግር በአረቢኛው ቁርኣን ውስጥ የሌለ ሲሆን በተርጓሚዎቹ የተጨመረ ማብራራርያ ነው፡፡ ይህንንም ሀሳብ በመጨመር ይህ ጥቅስ ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን ችግሮች ለመቀነስ ሞክረዋል፡፡ ይህ እንዲያውም ችግሩን ያከረዋል እንጂ በፍፁም አያለዝበውም፡፡ “ጣጣ” የተባለው ባሎች ለሚስቶቻቸው የሚያወጡት ወጪ ከሆነ በእጅጉ ያስገርማል፡፡ እውነተኛው አምላክ በእንዲህ ዓይነት እንቶ ፈንቶ ምክንያቶች ላይ ተመስርቶ ደረጃ የሚመድብ አምላክ አይደለም፡፡ በብዙ ማሕበረሰቦች ውስጥ እንዲያውም ከወንዶች ይልቅ ብዙ “ጣጣ” የሚሸከሙት ሴቶች በመሆናቸው በዚህ ደረጃ እንመድብ ከተባለ የበላይነቱ የሚገባው ለሴቶች እንጂ ለወንዶች አይደለም፡፡1

ሴቶች ለባሎቻቸው እርሻ ስለሆኑ በፈለጉበት ሁኔታ “ሊደርሷቸው” ይችላሉ፡- 2፡223 “ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው፡፡ እርሻችሁን በፈለጋችሁት ሁኔታ ድረሱ”
ጋብቻ ክቡር መኝታውም ቅዱስ መሆኑ እሙንና ቅቡል ነው፡፡ ታድያ ይህ ሊሆን የሚችለው የሴቷም ፍላጐትና ስሜት ጭምር ከተጠበቀ ብቻ ነው፡፡ ባል ሚስቱን እንደ ግል እርሻው በመቁጠር በፈለገው ሁኔታ ልድረስ ቢል በሴቷ ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ሴቶችን ከእርሻ ጋር ማመሳሰልና “በፈለጋችሁት ሁኔታ ድረሱ” የሚለው አባባል ለሰው ህሊና ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡

ባሎች ሚስቶቻቸውን በመምታት መቅጣት ይችላሉ፡- 4፡34 “እነዚያም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገስፁዋቸው በመኝታዎችም ተለዩዋቸው (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም፡፡ ቢታዘዟችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ አላህ የበላይ ታላቅ ነውና፡፡”

አሁንም እንደተለመደው የቁርኣን ተርጓሚዎች ቃላትን በቅንፍ ውስጥ በመጨማመር የመጽሐፋቸውን ገመና ለመሸፈን ሞክረዋል፡፡ “ሳካ ሳታደርሱ (አካላዊ ጉደት ሳታደርሱ)” የሚለውን ሀሳብ መጨመራቸው “ምቱዋቸው” የሚለው የቁርኣን ትዕዛዝ ከህሊናቸው ጋር ግጭትን እንደፈጠረ ያሳያል፡፡ በትዕግስትና በፍቅር መምከር እየተቻለ መደብደብ ለምን ያስፈልጋል? ምድራዊ መንግሥታት እንኳ ሚስቶችን መምታት ጎልዳፋ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ የዜጎቻቸውን መብት የሚያስከብሩ ህግጋትን አውጥተዋል፡፡ ሴትን ልጅ መምታት ኢ-ሞራላዊ የሆነ ኋላ ቀር ተግባር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ትዕዛዝ ሊመነጭ የሚችለው ለሴት ልጅ ዝቅተኛ ግምት ካለው አዕምሮ እንጂ ቅዱስ ከሆነው አምላክ ዘንድ ከቶ ሊሆን አይችልም፡፡ ማንም ሰብኣዊነት የሚሰማው ሰው እንዲህ አይነቱን ጎጂ ልማድ መቃወምና መታገል ይኖርበታል፡፡

ከባሏ ለሦስተኛ ጊዜ የተፋታች ሴት የመጀመሪያ ባሏን መልሳ ማግባት የምትችለው ሌላ ወንድ አግብታ ከፈታች ብቻ ነው፡- 2፡230 “(ሦሰተኛ) ቢፈታትም ከዚህ በኋላ ሌላን ባል እስከምታገባ ድረስ ለርሱ አትፈቀድለትም፡፡ (ሁለተኛው ባል) ቢፈታተም የአላህን ህግጋት መጠበቃቸውን ቢያውቁ በመማለሳቸው በሁለቱም ላይ ኃጢአት የለባቸወም፡፡”

ለሦስተኛ ጊዜ መፋታት ጥሩ ባይሆንም ነገር ግን መልሶ መታረቅ ደግሞ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ ከፍቺ በኋላ ከቀድሞ ባሏ ጋር የመታረቅ እድል ያገኘች ሴት ይህንን እርቅ ከመፈፀሟ በፊት ሌላ ወንድ አግብታ መፍታት ለምን ያስፈልጋታል? ከቀደሞ ባሏ ጋር መታረቅ እየፈለገች ነገር ግን እርሷ ሳትፈልግ “ሌላ ባል አግብተሽ ካልፈታሽ በስተቀር ከቀድሞ ባልሽ ጋር መታረቅ አትችይም” ማለትስ ምን የሚሉት መፍትሄ ነው?

የአንድ ወንድ ምስክርነት ከሁለት ሴቶች ምስክርነት ጋር እኩል ነው፡- 2፡282 “ከወንዶቻችሁም ሁለትን ምስክሮች አስመስክሩ፡፡ ሁለትም ወንዶች ባይሆኑ ከምስክሮች ሲሆኑ ከምትወዷቸው የሆኑን አንድ ወንድና አንድኛዋ ስትረሳ አንደኛዋን ታስታስውሳት ዘንድ ሁለት ሴቶች (ይመስክሩ)፡፡”
የዚህ ጥቅስ አውደ ንባብ የሚናገረው ስለ ብድር እዳ ውል ነው፡፡ አንድ ሰው ለሌላ ሰው ገንዘብ ማበደሩን አይቶ ለመመስከር የአንዲት ሴት ምስክርነት ከአንድ ወንድ ምስክርነት እኩል ተቀባይነት የማይኖረው ምን ስለሆነ ነው? ይህ ጥቅስ የሴቶች የማስታወስ ችሎታ ከወንዶች ያነሰ መሆኑን ለመግለፅ ያለመ መሆኑን ብዙ ሐዲሳት ያሳያሉ፡፡

በገነት ውስጥ ለሙስሊም ወንዶች የስሜት ማርኪያ እንዲሆኑ የተፈጠሩ ሴት ፍጥረታት ይገኛሉ፡- 78፡30-33 “ለጥንቁቆቹ መዳኛ ስፍራ አልላቸው፡፡ አትክልቶችና ወይኖችም፡፡ እኩያዎች የኾኑ ጡተ ጉቻማዎችም፡፡ የተሞሉ ብርጭቆዎችም፡፡”

44፡51-54 “ጥንቁቆቹ በእርግጥ በጸጥተኛ መኖሪያ ውስጥ ናቸው፡፡ በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡ ፊት ለፊት የተቅጣጩ ኾነው ከስስ ሐርና ከወፍራም ሐር ይለብሳሉ፡፡ (ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ ዓይናማዎች የኾኑን ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን፡፡”

56፡34-36 “ከፍ በተደረጉ ምንጣፎችም (ሴቶችም መካከል)፡፡ እኛ አዲስ ፍጥረት አድርገን (ለእነርሱ) ፈጠርናቸው፡፡ ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎች እኩያዎች (አደረግናቸው)፡፡ ለቀኝ ጓዶች (አዘጋጀናቸው)፡፡”
አንድ ሙስሊም ወንድ በገነት ውስጥ የ100 ወንዶች ጉልበት እንደሚያገኝ ቲርሚዚ መዘገቡን ሚሽካት አል መሳቢህ የተሰኘው የሐዲሳት ስብስብ መጽሐፍ ይጠቅሳል፡፡[1]

ሴት የነካ ወንድ ልክ እንደሰከረ ሰው፣ እንደታመመ ሰው እና ከዓይነ ምድር እንደመጣ ሰው ሁሉ ታጥቦ ከርክሰቱ ካልነፃ መጸለይ አይችልም፡- 4፡43 “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ኾናችሁ የምትሉትን ነገር እስከምታውቁ የረከሳችሁም ስትኾኑ መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር (አካላታችሁን) እስከምትታጠቡ ድረስ ስግደትን አትቅረቡ፡፡ በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም፥ ወይንም ከእናንተ አንዱ ከዓይነምድር ቢመጣ፥ ወይንም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ፣ ንጹሕ የኾነን የምድር ገጽ አስቡ፡፡ ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁንም (በርሱ) አብሱ፡፡ አላህ ይቅር ባይ መሓሪ ነውና፡፡”

ዕድሜያቸው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱትን ሴቶች ማግባት ይቻላል፡- 65፡4 “እኒያም ከሴቶቻቸው ከአደፍ ያቋረጡት (በዒዳቸው ሕግ) ብትጠራጠሩዒዳቸው ሦስት ወር ነው፡፡ እኒያም ገና አደፍን ያላዩት (ዒዳቸው እንደዚሁ ነው)፡፡ የእርግዝና ባለቤቶችም ጊዜያቸው እርጉዛቸውን መውለድ ነው፡፡አላህንም የሚፈራ ሰው ከነገሩ ሁሉ ለርሱ መግራትን ያደርግለታል፡፡”

ይህንን ጥቅስ ግልፅ ለማድረግ ያህል፡- አንድ ሙስሊም ወንድ አንዲትን የወር አበባዋ የተቋረጠ ሴት ለመፍታት ቢፈልግ ለሦስት ወር ያህል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳይፈፅምይቆያል፡፡ ለአቅመ ሔዋን ባለመድረሷ ምክንያት የወር አበባ ያላየችን ሴት ለመፍታት ቢፈልግ እንዲሁ ሦስት ወር ያህል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳይፈፅም ይጠብቃል፡፡ ይህ የቁርኣን ሐታቾች የሚስማሙበት እስላማዊ መመርያ ነው፡፡ ሰይድ አቡል ዓላማውዱዲ የተሰኙ ፓኪስታናዊ ሙስሊም ሊቅ ይህንን ጥቅስ በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡- “ገና አደፍን ያላዩትን (የወር አበባ ያላዩትን) መፍታት የሚቻልበትን መመርያየሚሰጠው ይህ የቁርኣን ጥቅስ እንዲህ አይነት ሴቶችንም ማግባት እንደሚቻል በግልፅ የሚያሳይ ነው፤ በመሆኑም ቁርኣን ያፀደቀውን ይህንን ተግባር ማንም የመከልከል መብት የለውም፡፡”[2] ማውዱዲ በሙስሊሙ ዓለም እጅግ የተከበሩ ዕውቅ የቁርኣን ተንታኝ የነበሩ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ቁርኣን ሴቶችን በተመለከተ ያለው አስተምህሮ የሴቶችን ተፈጥሮና ስብዕና በእጅጉ ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከማርያም ስም በስተቀር የአንዲት ሴት ስም እንኳ አልተጠቀሰም፡፡[3] በእስልምናም ውስጥ ሴት ነቢያት አይታወቁም፡፡ እድሜ ልካቸውን በጥቁር ጨርቅ ተጀቡነው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ወንዶች እስከ አራት እንዲያገቡና ከዚያም አልፈው ቁባቶችን እንዲይዙ ሲፈቀድላቸው ሴቶች ግን ከወንዱ መልካም ፈቃድ ውጭ ምንም መወሰን እንዳይችሉ በአስጨናቂ ህግጋት ታጥረዋል (ሱራ 4፡3)፡፡

2. ሴቶች በሐዲስ መጻሕፍት

በተለያዩ ሐዲሳት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ ትዕዛዛትና ህግጋትም እንዲሁ የሙስሊም ሴቶችን ስቃይ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡-

ሴቶች ለባሎቻቸው እንደ ባርያ ናቸው፡-
“ባርያ የጌታው ንብረት ጠባቂ ሲሆን ሚስት ደግሞ የባሏ ቤትና ልጆች ጠባቂ ናት፡፡”[4]

ባሎች ሚስቶቻቸውን መምታት ይችላሉ፡-
“ዑመር እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹ባል ሚስቱን ለምን እንደመታት መጠየቅ የለበትም፡፡›” አቡዳውድና ኢብን ማጃህ ዘግበውታል፡፡[5]

የገሃነም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሴቶች ናቸው፡-
“ሴቶች ሆይ ምፅዋት ስጡ የገሃነም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሴቶች መሆናቸውን አይቻለሁና፡፡ ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ ለምንድነው?› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ብዙ ጊዜ ትሳደባላችሁ፤ ለባሎቻችሁም ምስጋና ትነፍጋላችሁ፡፡ በዕውቀትና በሃይማኖት ከእናንተ በከፋ ሁኔታ ጎደሎ የሆነ አላየሁም›… ሴቶቹም እንዲህ ብለው ጠየቁ፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ በዕውቀትና በሃይማኖት ጎደሎዎች የሆንነው እንዴት ነው?› እርሱም ‹የሁለት ሴቶች ምስክርነት ከአንድ ወንድ ምስክርነት ጋር እኩል አይደለምን?› በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በአዎንታ መለሱ፡፡ ‹ይህ በዕውቀት ጎደሎዎች መሆናችሁን ያሳያል፡፡ ሴት በወር አበባ ጊዜዋ መጸለይም ሆነ መፆም አለመቻሏ እውነት አይደለምን?› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ሴቶቹም በአዎንታ መለሱ፡፡ ‹ይህ በሃይማኖት ጎደሎ መሆናችሁን ያሳያል› በማለት መለሱላቸው፡፡”[6]

ሴት መሪ መሆን አትችልም፡-
“አቡበከር እንዳስተላለፉት በአል ጀመል (ግመል) ዘመቻ ወቅት አላህ (ነቢዩ ሲናገር በሰማሁት ቃል) አጣቀመኝ፡፡ ነቢዩ የፋርስ ሰዎች የኾስራውን ሴት ልጅ እንዳነገሷት ሲሰሙ እንዲህ ብለው ነበር፡- ‹በሴት የሚመራ ሕዝብ ፈፅሞ ስኬታማ አይሆንም፡፡›”[7]

ሙሐመድ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችን ሕፃን አግብተዋል፡-
“የሐሺም አባት እንዳስተላለፉት፡- ከዲጃ ነቢዩ ወደ መዲና ከመሄዳቸው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር ሕይወቷ ያለፈው፡፡ ወደዚያ በሄዱ በሦስት ዓመታት ውስጥ አይሻን አገቧት፡፡ ጋብቻውንም ያሟሉት እርሷ ዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ነበር፡፡”[8]

ሙሐመድ የሴት ግርዛትን አፅድቀዋል፡-
“ኡም አቲያ አል አንሳርያ እንዳስተላለፉት፤ አንዲት ሴት በመዲና ውስጥ ግርዛትን ትፈፅም ነበር፡፡ ነቢዩ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ አሏት ‹በጣም አድርገሽ መቁረጥ የለብሽም ምክንያቱም እርሱ ለሴት የተሻለ ነው፤ ባልም ይበልጥ የሚወደው ነገር ነው፡፡›”[9]
በዚህ ሐዲስ መሠረት ሙሐመድ አገራረዝ እንዴት መሆን እንዳለበት አስተያየት በመስጠት ድርጊቱን አፀደቁ እንጂ ግርዛት ትክክል አለመሆኑን አልተናገሩም፡፡

ጸሎት በሴት ምክንያት ይቋረጣል፡-
“አቡ ዘር እንዳስተላለፈው፡- የአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ብለዋል፡- ከመካከላችሁ አንድ ሰው ለጸሎት በሚቆምበት ሰዓት… ከፊት ለፊቱ የኮርቻ ያህል መጠን ያለው ነገር የማይኖር ከሆነ ጸሎቱ (በፊቱ በሚያልፍ) አህያ፣ ሴት እና ጥቁር ውሻ ይቋረጣል፡፡ እኔም አቡ ዘር ሆይ ጥቁር ውሻን ከቀይ ወይም ከቢጫ የሚለየው ምንድነው? ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እርሱም የወንድሜ ልጅ ሆይ አንተ እንደጠየቅኸኝ ሁሉ እኔም የአላህን መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ጠይቄያቸው ነበር፤ ‹ጥቁር ውሻ ዲያብሎስ ነው› በማለት ነበር የመለሱልኝ፡፡”[10]

3. ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ

እስኪ እነዚህን እስላማዊ ትምህርቶች እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያነፃፅሩ፡፡

ባሎች ሚስቶቻቸውን መውደድና ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
“ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ፡፡ ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ፡፡ ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ፡፡” (1ቆሮንቶስ 7፡3-5)፡፡

“ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ፡፡ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፡፡ የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ፡፡ ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ፡፡” (ኤፌሶን 5፡25-33)፡፡

“ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው፡፡” (ቆላስይስ 3፡19)፡፡

“እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው፡፡” (1ጴጥሮስ 3፡7)፡፡

“ደካማ ፍጥረት” (Weak Vessels) የሚለው ሴቶች በስሜት እና በአካል ከወንድ አንፃር ደካሞችና እንክነብካቤ የሚያሻቸው መሆናቸውን እንጂ በመንፈስና በአዕምሮ ደካማ መሆናቸውን አያሳይም፡፡ ወንዶች ሴቶችን ካላከበሩ ጸሎታቸው እግዚአብሔር ዘንድ እንደማይደርስ መነገሩ ሴቶች በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ደረጃና በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ የሚገልፅ ነው፡፡

ወንዶችና ሴቶች እኩል ናቸው፡-

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡” (ገላቲያ 3፡28)፡፡

እኩል በአምሳለ እግዚአብሔር ተፈጥረዋል፡-
“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡፡ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡” (ዘፍጥረት 1፡26-27)፡፡
“የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው፡፡” (ዘርጥረት 5፡1-2)፡፡

ከላይ ያየናቸው ጥቅሶች ሴቶች ከወንዶች እኩል መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ሲሆኑ ቀደም ሲል ከተመለከትናቸው እስላማዊ መመርያዎች በተፃራሪ የቆሙ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሴት ነቢያት በብዛት ተጠቅሰዋል (ዘጸአት 15፡20፣ መሣፍንት 4፡4፣ 1ዜና 34፡22፣ የሐዋርያት ሥራ 21፡9)፡፡ ከሐዋርያት ጋር ሲያገለግሉ የነበሩ ሴት አገልጋዮች ነበሩ (ሮሜ 16፡1፣ 7)፡፡ የኢየሱስ ትንሳኤ የመጀመርያዎቹ ምስክሮች ሴቶች ነበሩ (ማቴዎስ 28፡1-9፣ ማርቆስ 16፡1-8፣ ሉቃስ 24፡1-11፣ ዮሐንስ 20፡1-10)፡፡ ሴቶች ለምስክርነት በማይቀርቡበት በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የክርስትና መሠረት የሆነውን የክርስቶስን ትንሣኤ ለመመስከር መመረጣቸው ምንኛ አስደናቂ ነገር ነው!

ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን፤ ከላይ ከተረዘሩት እውነታዎች አንፃር ትክክለኛው የአምላክ መንገድ የትኛው ይመስላችኋል? እግዚአብሔር የልብ ዓይኖቻችሁን በመክፈት የእውነትና የነፃነት መንገድ ወደ ሆነው፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተመሠረተው ትክክለኛ መንገድ ይመራችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] Mishkat Al-Masabih: vol. 3, p. 1200
[2] Sayid abul A’La maududi. The meaning of the Qur’an, Vol. 5 pp. 599 & 617
[3] በአማርኛው ትርጉም ውስጥ በቅንፍ ተቀምጠው የምናያቸው በተርጓሚዎቹ የተጨመሩ እንጂ በአረብኛው ውስጥ የሚገኙ አይደሉም፡፡
[4] Sunan Abu Dawud vol.2 no.2922, p.827
[5] Mishkat Al-Masabih: vol. 2, p. 693
[6] Sahih Al-Bukhari vol.1 no.301 p.181. See also Sahih Muslim vol.2 book 4 no.1982,1983 p.432
[7] Sahih Al-Bukhari vol.9 no.219 p.170-171
[8] Bukhari: vol. 5, bk. 58, no. 236, Khan
[9] Sunan Abu-Dawud: bk. 41, no. 5251. “Reliance of the Traveller – A Classic Manual of Islamic Sacred Law” የተሰኘ በአልአዝሃር ዩኒቨርሲቲ አፅዳቂነት የታተመ የሸሪኣ ሕግ መጽሐፍ ገፅ 59 ላይ የሴት ልጅ ግርዛት በእስልምና ግዴታ (Obligatory) መሆኑን ይገልፃል፡፡
[10] Sahih Muslim, Book 004, Number 1032

 

ሴቶች በእስልምና