ቁርአን በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ መስፈሩ አለመለወጡን ያረጋግጣልን?
ሙስሊም ወገኖች ቁርአን በትክክል ተጠብቆ ስለመቆየቱ ከሚጠቅሷቸው “ማስረጃዎች” መካከል አንዱ በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ መስፈሩን ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን በጽሑፍ አለመስፈራቸውን በመጥቀስ ለማጣጣል ሲሞክሩና በመሐመድ ዘመን ቁርአን በጽሑፍ መስፈሩን እንደ አንድ ጥንካሬ በመቁጠር ሲገደሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በክርስቶስ ሐዋርያትና በቅርብ ወዳጆቻቸው የተጻፉ በመሆናቸው በተዓማኒነታቸው ላይ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለንም፡፡ ለጠያቂዎችም ከበቂ በላይ ማስረጃዎችን ማቅረብ እንችላለን፡፡ ዳሩ ግን ቁርአን በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ ሰፍሮ ነበር መባሉ ለተዓማኒነቱ የሚጨምረው ምንም ነገር የለም፡፡ ሲጀመር አንድ መጽሐፍ በትክክል ተጠብቆ መቆየቱ ይዘቱን ትክክል አያደርገውም፡፡ የግብፃውያን፣ የግሪካውያን፣ የሮማውያን፣ የፋርሳውያን፣ የመካከለኛው አውሮፓውያንና የመሳሰሉት ሕዝቦች ብዙ ጽሑፎች በትክክል ተጠብቀው ለዚህ ዘመን በቅተዋል፤ ዳሩ ግን በውስጣቸው የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ትክክል ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ቁርአን ምንጩ የተሳሳተ በመሆኑ (ከፈጣሪ ዘንድ ባለመሆኑ) በትክክል ተጠብቆ መቆየቱ ለተዓማኒነቱ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ በትክክል ተጠብቆ ቆይቷል ከተባለ (ተጻራሪውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንዳሉ ሳንዘነጋ) በትክክል የተጠበቀ ሐሰት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ የሆነው ሆኖ ቁርአን በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ ሰፍሯል መባሉ በትክክል ለመጠበቁ የረባ አስተዋፅዖ ሊኖረው እንደማይችል የሚያሳዩ ምክንያቶችን በዝርዝር እናቀርባለን፡፡ ተከታዮቹ ነጥቦች ለሐሰን ታጁ መጽሐፍ ከሰጠነው ምላሽ የተወሰዱ ናቸው፡፡
ሐሰን ታጁ ቁርአን በትክክል አልተጠበቀም በሚል በሐመረ ተዋህዶ ለተነሱት ሒሶች የሰጡት ሁለተኛው ምላሽ “ቁርአን በነቢዩ ዘመን ተጽፏል” የሚል ነው (ገፅ 18-19)፡፡ ነገር ግን ይህ “መልስ” የማያስኬድባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡
1. በሰው አስተያየት የሚሻሻል “መገለጥ”
መሐመድ ቁርአንን ሲያጽፉ የግለሰቦችን አስተያየቶችና ቅሬታዎች እየሰሙ ማስተካከያዎችን በማድረግ ነበር፡፡ ይህንን በተመለከተ ሳሂህ አል ቡኻሪ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሐዲስ እንዲህ ይላል፡-
“አል-በራ እንዳስተላለፉት፡- ‹ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም› የሚል ሱራ ወርዶ ነበር (4፡95)፡፡ ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹እስኪ ዘይድን ጥሩልኝ መጻፍያ ሰሌዳ፣ የቀለም ገንቦና (እንደ ብዕር የሚያገለግል) አጥንት ያምጣልኝ…› ከዚያ፡- ‹ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም… ብለህ ጻፍ› አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ዓይነ ስውሩ አምር ቢን ኡም መክቱም አጠገባቸው ተቀምጦ ነበር፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ለኔስ የሚሰጡት ትዕዛዝ ምንድነው? እኔ ዓይነ ስውር ሰው ነኝ፡፡› ስለዚህ በዚህኛው አንቀፅ ፋንታ ተከታዩ አንቀፅ ወረደ፡- ‹ከምእመናን የጉዳት ባለቤት ከኾኑት በቀር ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም፡፡›”[1]
በቁርአን ውስጥ የዑመር አስተያየቶች እንደተካተቱ እስላማዊ ምንጮች ያስረዳሉ፡-
“ኢብን ማርዳውያህ በተናገረው መሠረት ሙጃሂድ እንዲህ ብሏል፡- ዑመር አስተያየት ሲኖረው በዚያ ላይ ቁርአን ይወርዳል (የእርሱን ቃል ለማረጋገጥ)፡፡ ኢብን አስካሪ በተናገረው መሠረት አሊ እንዲህ ብሏል፡- የዑመር የተወሰኑ አስተያየቶች ቁርአን ውስጥ ይገኛሉ፡፡”[2]
የአምላክ መገለጦች በሰዎች ቅሬታና አስተያየት ላይ ተመሥርተው የሚሻሻሉ፣ የሚሰረዙ፣ የሚደለዙ አይደሉም፡፡ መሐመድ የእውነት ከሰማይ መገለጥ ወርዶላቸው ከሆነ በወረደላቸው መገለጥ ላይ በመጨመር እንዲጻፍ ስላደረጉ እንዲጻፍ ያደረጉት መገለጥ የተበረዘ ነው ማለት ነው፡፡ መሰል ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው በፈጣሪ ትዕዛዝ መሠረት እንደሆነ በየዋህነት የሚያምን ሰው ካለ ስለ ፈጣሪ እውቀት ግንዛቤ የሌለው ጭፍን አማኝ መሆን አለበት፡፡ የፈጣሪ መገለጦች ፍፁማን በመሆናቸው በግለሰብ አስተያየትና ቅሬታ የሚሻሻሉ አይደሉም፡፡ እንዲህ ያለ ፌዝ በእውነተኛው አምላክ ዘንድ የለም፡፡ ስለዚህ መሐመድ የአምላክን “መገለጥ” በርዘዋል አለበለዝያም ደግሞ መገለጡ ከጅምሩ እውነተኛ አይደለም፡፡
2. ጸሐፍት የሚያሻሽሉት “መገለጥ”
አብዱላህ ኢብን ሰዓድ ኢብን አቢ ሳርህ የተሰኘ የመሐመድ የግል ጸሐፊ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለመሐመድ መገለጦችን በመጻፍ ያገለግላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን መገለጦችን ሲጽፍ ሳለ በየመሃሉ የማሻሻያ ሐሳቦችን ጣል ያደርግ ነበር፤ መሐመድም ብዙ ጊዜ በመስማማት በጽሑፉ ውስጥ እንዲካተት ይፈቅዱ ነበር፡፡ መሐመድ የሚናገሩት መገለጥ ከፈጣሪ ዘንድ ቢሆን ኖሮ የሰው ሐሳብ እንዲጨመርበት ሊፈቅዱ እንደማይችሉ ስለገባው ይህ ጸሐፊ እስልምናን በመተው ወደ መካ ከተማ ሸሸ፡፡ ኋላ ላይ መሐመድ መካን ድል ነስተው በያዙ ጊዜ ኢብን አቢ ሳርህ እንዲገደል አዘዙ፡፡ ነገር ግን በኡሥማን ተማፅኖ ከመገደል ተርፎ እንደገና ወደ እስልምና ተመለሰ፡፡
ኢብን አቢ ሳርህ እስልምናን ስለመካዱና መሐመድ ስላስተላለፉበት የሞት ብይን ኢብን ኢስሐቅ፣ አልጦበሪና ኢብን ሰዓድን በመሳሰሉት የመሐመድ ግለ ታሪክ ጸሐፍት የተዘገበ ሲሆን የቁርአንን መገለጦች እየጨመረና እየቀነሰ ስለመጻፉ ደግሞ አል-ኢራቂና ባይዳዊን የመሳሰሉት ሙስሊም ሊቃውንት ዘግበዋል፡፡[3] የመሐመድ ጸሐፊ ቁርአንን ስለመበረዙ በእስላማዊ ድርሳናት የተመዘገበው ይህ ታሪክ እውነት ከሆነ ሌሎች ጸሐፍት ተመሳሳይ ነገር ላለመፈፀማቸው ዋስትና የለንም፡፡
3. መሐመድ አንድ ቁርአን ብቻ አልነበራቸውም
ይህንን የሚያረጋግጡ ሁለት ሐዲሳትን እንጠቅሳለን፡-
“ኡመር ቢን አል-ኸጧብ እንዳስተላለፈው፡- ነቢዩ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ሒሻም ቢን ሐኪም ሱራት አል-ፉርቃንን ሲያነበንብ እሰማው ነበር፤ የእርሱን መነባንብ ሳዳምጥ የአላህ መልእክተኛ እኔን ካስተማረበት መንገድ በብዙ መልኩ የተለየ መሆኑን አስተዋልኩኝ፡፡ እየጸለየ ሳለ ዘልዬ ልይዘው ጥቂት ቀርቶኝ ነበር ነገር ግን ጸሎቱን እስኪጨርስ ድረስ በትዕግስት ጠበኩትና ከላይ በለበሰው ልብሱ አንገቱን አንቄ ይዤ ‹‹አሁን ስታነበንብ የሰማሁትን ሱራ ማን አስተማረህ?›› አልኩት፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ናቸው ያስተማሩኝ›› አለኝ፡፡ እኔም ‹‹በእርግጥ ውሸት ተናግረሃል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ከዚህ በተለየ መንገድ ነው ያስተማሩኝ›› አልኩት፡፡ ስለዚህ ወደ አላህ መልእክተኛ ጎትቼ አመጣሁትና ‹‹ይህ ሰው እርስዎ ካስተማሩኝ መንገድ በተለየ ሁኔታ ሱረት አል ፉርቃንን ሲያነበንብ ሰማሁት!›› አልኳቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ‹‹(ኡመር ሆይ) ልቀቀው፤ ሒሻም ሆይ አነብንብ!›› አሉ፡፡ ሲያነበንብ በሰማሁት በዚያው መንገድ አነበነበ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ‹‹በዚህ መንገድ ነው የወረደው›› አሉ፡፡ ከዚያም ‹‹ኡመር ሆይ አነብንብ›› አሉ፡፡ እሳቸው ባስተማሩኝ መንገድ አነበነብኩኝ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ‹‹በዚህ መንገድ ነው የወረደው፡፡ ይህ ቁርአን በሰባት የተለያዩ መንገዶች እንዲነበብ ተደርጎ ነው የወረደው ስለዚህ ለናንተ ቀላል መስሎ በታያችሁ መንገድ አነብንቡ›› አሉ፡፡”[4]
“ኢብን መስዑድ እንዳስተላለፉት፤ አንድ ሰው የቁርአንን አንቀፅ በሆነ መንገድ ሲያነበንብ ሰማሁት፡፡ የአላህ መልእክተኛ ደግሞ ያንኑ አንቀፅ በተለየ መንገድ ሲያነበንቡት ሰማሁኝ፡፡ ስለዚህ ወደ ነቢዩ ወስጄው ስለ ጉዳዩ አሳወቅኋቸው፤ ነገር ግን በፊታቸው ላይ የቅሬታ ምልክት አየሁኝ፡፡ ከዚያ እንደዚህ አሉ፣ “ሁለታችሁም ትክክል ናችሁ ስለዚህ አትለያዩ፤ ከናንተ በፊት የነበሩት ሕዝቦች የጠፉት በመለያየታቸው ምክንያት ነውና፡፡”[5]
ሙስሊሞች ብዙ ጊዜ ሰባቱ የቁርአን ቅጂዎች በአረብኛ ቋንቋ ዘዬዎች ምክንያት የተፈጠሩ የአንዱ ቁርአን ሰባት የንባብ መንገዶች ብቻ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ኡመር ቢን ኸጧብና ሒሻም ከአንድ ጎሣ ስለነበሩ የተለያዩ ዘዬዎችን ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡[6] እነዚህ የተለያዩ የቁርአን ቅጂዎች እንጂ የአንዱ ቁርአን የተለያዩ ዘዬዎች አይደሉም፡፡
በመሐመድ ዘመን ቁርአን በጽሑፍ ተጠብቆ ከነበረ ከሰባቱ የትኛው ነው የተጻፈው? ሰባቱም ተጽፈው ከነበረ የኸሊፋ አቡበክር አንዱ ስብስብ ሰባቱንም ያካተተ ነበርን? ይህንን የሚጠቁም ማስረጃስ ይኖራልን? ኡሥማን ከሰባቱ ስድስቱን ዓይነት ቁርአኖች አጥፍተው ከነበረ ቁርአን ፍጹማዊ በሆነ መንገድ በጽሑፍ ተጠብቋል ልንል እንችላለንን? በኋለኛው ዘመን እንዲወድሙ ከተደረገ ሰባቱ ቁርአኖች በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ መስፈራቸው ፋይዳው ምንድነው?
4. መሐመድ በመካ “የተጻፉትን” የቁርአን ጽሑፎች ይዘው መሰደዳቸውን የሚጠቁም ማስረጃ የለም
የቁርአን ሁለት ሦስተኛው በመካ “እንደወረደ” ይታመናል፡፡ ነገር ግን ይህ የቁርአን ክፍል ተጽፎ ከነበረ ሙስሊሞች በሒጅራ ወቅት እነዚህን ጽሑፎች ይዘው ወደ መዲና መሄዳቸውን የሚገልፅ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባለመኖሩ ጠፍተዋል ማለት ነው፡፡ ነፍሳቸውን ለማትረፍ በሽሽት ላይ የነበሩት ሙስሊሞች ድንጋይና አጥንትን የመሳሰሉ ቁሳ ቁሶችን ይዘው መንቀሳቀስ መቻላቸው በራሱ የማይመስል ነው፡፡ ስለዚህ የቁርአን ሁለት ሦስተኛ ጽሑፍ መሐመድ ገና በሕይወት ሳሉ ጠፍቶ ከነበረና ወደ ቀጣዩ ትውልድ ካልተሸጋገረ በጽሑፍ መስፈሩ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ለቁርአን ተዓማኒነትም የሚጨምረው ምንም ነገር የለም፡፡ እንዲያውም መሐመድ በመካ ከተማ ሳሉ ቁርአን በጽሑፍ መስፈሩን የሚጠራጠሩ ሊቃውንት ብዙ ናቸው፡፡[7]
5. የመጀመርያዎቹ የቁርአን ጽሑፎች ተቃጥለዋል
ኡሥማን ኢብኑ አፋን ቁርአንን አንድ ወጥ መልክ ለማስያዝ ጥረት ባደረገበት ወቅት ከእርሱ በፊት የነበሩትን የቁርአን ጽሑፎች አውድሟቸዋል፡፡[8] በሐፍሳ ዘንድ ቀርቶ የነበረውን አንዱን ስብስብ ማርዋን የተሰኘ ሰው አቃጥሎታል፡፡ ስለዚህ ቀዳሚያን የቁርአን ጽሑፎች ሆነ ተብለው እንዲወድሙ ስለተደረገ ዛሬ ካሉት ቁርአኖች ጋር አንድ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ይህንን ርዕስ ከአፍታ በሌላ ጽሑፍ በስፋት እንዳስሰዋለን፡፡
ማጠቃለያ
ቁርአን በመሐመድ ዘመን ተጽፎ ነበር ከተባለ ለተዓማኒነቱ የሚጨምረው አንዳችም ፋይዳ የለም፡፡ መሐመድ ራሳቸው በሰው አስተያየት ያሻቸውን እየጨመሩ ቁርአንን ሲሻሽሉ ከነበረ፣ ጸሐፍታቸው የገዛ ፈጠራዎቻቸውን እያከሉ ቀላቅለው ሲጽፉ ከነበረ፣ መሐመድ የተለያዩ ቁርአኖች ከነበሯቸውና እነዚያ ቁርአኖች ደግሞ ከአንድ ጎሣ የነበሩ አንድ ዓይነት የአረብኛ ዘዬን የሚናገሩ ሰዎችን እንኳ የማያግባቡ ከነበሩ እንዲሁም እነዚያ ቁርአኖች ሁሉ በጽሑፍ ስለመስፈራቸው ማረጋገጫ ከሌለ፣ በመካ የተጻፈው ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ቁርአን የተጻፈባቸው ቁሶች ስለመጠበቃቸው ማረጋገጫ ከሌለ፣ እንዲሁም የመጀመርያዎቹ የቁርአን ጽሑፎች በኡሥማን ዘመን ከተቃጠሉ ቁርአን በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ መስፈሩ በትክክል ለመጠበቁ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡
[1] (Qur’an 4.95) (Sahih al-Bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 512; also Sahih Muslim: bk. 20, no. 4676-4677)
[2] The History of the Khalifas Who Took the Right Way, p. 123
[3] Al-Wahidi Al-Naysaboori. Asbaab Al-Nuzool; p. 126 Beirut’s Cultural Libary Edition “Tub’at Al-Maktabah Al-thakafiyyah Beirut”
http://www.answering-islam.net/Quran/Sources/sarh.html
[4] Sahih al-Bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 514
[5] Sahih al-Bukhari: vol. 4, bk. 56, no. 682
[6] https://islamqa.info/en/5142 (በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው በዓለም ዙርያ በሚገኙ ታላላቅ ሙስሊም ሊቃውንት የሚተዳደር የፈተዋ (የእስላማዊ ድንጋጌ) ድረ-ገፅ ነው፡፡)
[7] The Qur’an Dilemma; Former Muslims Analyze Islams Holiest Book. 2001, Vol. 1, pp. 49-50
[8] Sahih Bukhari 6.510
በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ
ቅዱስ ቁርአን