ከሊመቱላህ
የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጥ ስያሜ
ቁርአን ከክርስትና ነገረ መለኮዊ አስተምሕሮዎች ጋር የተያያዙ ብዙ ሐሳቦችን በውስጡ ይዟል፡፡ በቁርአን ውስጥ ከተጠቀሱ ክርስትናን ከሚመለከቱ ጥቅሶች ይኼኛው ትኩረትን የሚስብ ሆኖ እናገኘዋለን፡-
ሱረቱ አል-ኒሳእ 4፡171
“እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው፤ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም፤ ተከልከሉ ለናንተ የተሻለ ይሆናልና፤ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለርሱ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ።”
በዚህ ክፍል የተጠቀሱት አመለካከቶች፡- ኢየሱስ መልእክተኛ ብቻ ነበር፣ አምላክ ሥላሴ አይደለም፣ አንድ ነጠላ አምላክ አለ፣ እርሱም ልጅ የለውም የሚሉት ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመናችንን ለመቃወም ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድ ሙስሊም ወገኖች በተደጋጋሚ የሚጠቅሱትን ይህንን ጥቅስ በትኩረት ያነበበ ሰው ከዚያ ያለፈ አንድምታ እንዳለው ይገነዘባል፡፡ በዚህ ክፍል ለኢየሱስ የተሰጡት ሦስቱ ስያሜዎች ሙስሊሞች እንደሌሎቹ መልእክተኞች መልእክተኛ ብቻ ነው ብለው ከሚያምኑት ይልቅ እኛ ክርስቲያኖች ከመልእክተኛነት ከፍ ባለ ሁኔታ እንደ አዳኝና ጌታ የምናምነውን የሚደግፉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
የመጀመርያው ስያሜ አል-መሲህ ሲሆን ይህ ስያሜ ከኢየሱስ ውጪ በቁርአን ውስጥ ለማንም አለመዋሉ ይታወቃል፡፡ ቁርአን ይህ ስያሜ ምን ማለት እንደሆነ ምንም ያስቀመጠው ትንታኔ የለም፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትርጓሜ እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡ በማስከተል የምናያቸው ሁለቱ ስያሜዎች ከሊማህ (ቃል) እና ሩኽ (መንፈስ) የሚሉት ናቸው፡፡ በዚህ ክፍል ከሊመቱሁ (የእርሱ ቃል) የሚለውን በመመልከት ሌላውን በቀጣይ ክፍል እናያለን፡፡
ይህ አጠራር ኢየሱስ ልዩ በሆነ መንገድ የአላህ የራሱ ቃል እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ያስቀምጥልናል፡፡ ስያሜው በሌሎች በሁለት የቁርአን ክፍሎች ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ በቁርአን 3፡39 ላይ መልአኩ ለዘካርያስ ያሕያ (ዮሐንስ) ከአላህ በሆነ ቃል (ከሊመቲም ሚናላህ) የሚያበስር (የሚመሰክር) እንደሆነ እና በ3፡45 ላይ መልአኩ ለማርያም ሲያበስራት ከእርሱ በሆነው ቃል (ከሊመቲም ሚንሁ) ብሏል፡፡ ቁርአን ልክ እንደ አል-መሲህ ሁሉ ስለ ቃሉ ምንነትም አያብራራም፡፡
እንደተለመደው ሙስሊም ጸሐፊያን ለኢየሱስ የተለየ ስያሜ የመሰጠቱን ትክክለኛ ምልከታ ላለመጠቀም ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ፡፡ ዩሱፍ አሊ የተባለ ተርጓሚ ስለ ሱራ 3፡39 እንዲህ ብሏል፡-
ልብ በሉ፡- “ከአላህ በኾነው ቃል” እንጂ “የአላህ ቃል” አይደለም፡፡ ይህን ቅጽል ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ይጠቀሙታል፡፡ በ 3፡59 ከታች ኢየሱስ በተዓምር ነው የተፈጠረው፡፡ አላህ “ሁን” ሲል ሆነ፡፡[1]
አብዛኛው ሙስሊም ሕብረተሰብ ኢየሱስ ከአላህ የሆነ ቃል የተባለው አዳም እንደተፈጠረው (3፡59) ሁሉ እርሱም አላህ ሁን (ኩን) ሲለው ስለሆነ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ኢማም ራዚ እና አንዳንድ ዘመናዊ ጸሐፊያን እንደሚስማሙት “የአላህ ቃል” የሚለው ኢየሱስ በፈጣሪ የትእዛዝ ቃል ከመፈጠሩ ያለፈ ምንም ትርጉም እንደሌለው እናምናለን፡፡”[2]
ሙስሊም መምህራን ይህንን ሐሳብ ሲያብራሩ ከአላህ የሆነ ቃል እንጂ የአላህ ቃል (word from Allah እንጂ word of Allah) አይደለም ይሉናል፡፡ ይህ ደካማ ሙግት ነው፡፡ ምክንያቱም ከአላህ የሆነው ቃል የማን ቃል ነው? If Jesus is a word form Allah, whose word is he? የሰው ቃል ነው ወይንስ የሌላ ፍጥረት? ከአላህ ዘንድ የሆነ ቃል ሁሉ የአላህ ቃል ነው፡፡
ሌሎች ደግሞ ለኢየሱስ የፈጣሪ ቃል ተገልጦለት ስለነበር በዚህ አግባብ እንጂ የተለየ ትርጉም ስላለው አይደለም ከአላህ የሆነ ቃል የተባለው የሚል ሙግት አላቸው፡፡ አንድ አሕመዲያ ጸሐፊ እንዲህ ይላል፡፡
ስለ ማርያም መጽሐፉ እንዲህ ይላል፡- “እርሷም የጌታዋን ቃል በእውነት ተቀበለች”፡፡ ስለዚህ እዚህ ጋ አረጋጋጯ ማርያም ናት እንጂ ኢየሱስ አይደለም፡፡ በመሆኑም ካሊማህ ለሚለው ቃል ሊሰጠው የሚችለው ብቸኛ ትርጉም ማርያም ከጌታዋ የተቀበለችው ትንቢታዊ ቃል መሆኑ ነው፡፡ ይህም ስለ ኢየሱስ መወለድ የተነገረው መለኮታዊ የሆነው መልእክት ነው…[3]
ይሁን እንጂ የተለመደው ሙግት ከላይ መጀመርያ ያየነው ሲሆን በአሕመዲያ ጸሐፊ የተነገረውን የሚያምኑት ጥቂት ሙስሊሞች ብቻ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ባልተለመደ ሁኔታ አዳም በተፈጠረበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው የአላህ ቃል የተባለው የሚለው የተለመደ ሙግት ነው፡፡ ይህንንም ሙግት በትኩረት ስናጠናው ውድቅ ይሆናል፡፡ አብዱል ሃቅ የተሰኘ ክርስቲያን ጸሐፊ ኢየሱስ ከአላህ የሆነ ቃል መባሉን በተመለከተ የሙስሊሞች ትርጓሜ ለምን እንደማያስኬድ ያብራራልናል፡-
አል ባይዳዊ “ከአላህ የኾነው ቃል” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክት ሲሆን ይህም እርሱ ከአላህ በኾነ ትእዛዛዊ ቃል ያለ አባት በመወለዱ ነው ብሏል፡፡[4] ይህንን አመክንዮ በመጠቀም አዳም ራሱ ከአላህ የኾነ ቃል ተብሎ መጠራት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም እሱም ከአላህ በኾነ ትእዛዛዊ ቃል ከአፈር ተፈጥሯልና (ሱራ 3፡59)፡፡ ነገር ግን የትም ቦታ ላይ ቁርአን አዳምን በዚህ መጠሪያ አይጠራውም፡፡ ይህ መጠሪያ ለኢየሱስ በልዩነት የተሰጠ ልዩ መጠሪያ ነው፡፡[5]
ሙስሊም ወገኖች እዚህ ጋ በትኩረት ሊመለከቷቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮችአሉ፡፡ የመጀመርያው ይህ መጠሪያ ለኢየሱስ ብቻ መዋሉን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሱራ 4፡171 ላይ ከአላህ የኾነ ቃል ሳይሆን የአላህ ቃል መባሉን ነው፡፡ ኢየሱስ የአላህ ቃል የተባለው በቃል በመረገዙ ምክንያት ከሆነ አዳምም የአላህ ቃል ሊባል ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ቁርአን አስተምህሮ ሁለቱም በተመሳሳይ አፈጣጠር ነው የተፈጠሩት፡፡ እዚህ ጋ ሙስሊም ወገኖች አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ “ሁን” በሚለው ቃል መፈጠሩ የአላህ ቃል ነው ካስባለው ሰማይ፣ ምድር፣ ዛፍ፣ ድንጋዩ፣ እንስሳት፣ እኛ ሰዎች፣ ሰይጣንን ጨምሮ ሁላችንም የአላህ ቃል ነን ማለት ነው፡፡ ሰይጣን “ሁን” በሚለው ቃል ተፈጥሯልና የአላህ ቃል ልንለው ነው? እንዲህ የሚያምን ሙስሊም ይኖራል?
የሚገርመው ነገር በቁርአን ውስጥ አዳም አንድም ቦታ የአላህ ቃል አልተባለም፡፡ መላእክትም ቢሆኑ ሌሎች ፍጥረታትም ከኢየሱስ ውጪ የአላህ ቃል የተባለ የለም፡፡ ኢየሱስ የአላህ ቃልና መንፈስ መሆኑ በሐዲስም ተመስክሯል፡-
እነሱም ወደ አዳም መጥተው እንዲህ ይሉታል፡- አባታችን ሆይ የገነትን በር ክፈትልን፡፡ እርሱም ይላቸዋል፡- ከገነት ያወጣችሁ ምንድነው? የአባታችሁ ኃጢአት አይደለምን? እኔም ይህን የሚያደርግ ስልጣን ላይ አይደለሁም፡፡ የአላህ ወዳጅ (ጓደኛ) ወደ ሆነው ወደ አብርሃም ሂዱ፡፡ ቅዱሱ ነቢይም እንዲህ አለ፡፡ አብርሃምም እንዲህ አለ፡– እኔ ይህን በሚያደርግ ስልጣን ላይ አይደለሁም፡፡ ከምንም በላይ እኔ ለአላህ ወደጁ ነበርኩ፤ ነገር ግን አላህ ፊት ለፊት ወዳናገረው ወደ ሙሴ ሂዱ፡፡ እነሱም ወደ ሙሴ መጡ፡፡ ነገር ግን እሱም እንዲህ አለ፡- እኔ ይህንን የሚያደርግ ስልጣን ላይ አይደለሁም፡፡ የአላህ ቃል እና የአላህ መንፈስ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ሂዱ…[6]
በዚህ ሐዲስ እንደምንመለከተው ሦስቱ ሰዎች የየራሳቸው የሆነ ልዩ መጠርያ አላቸው፡፡ አዳም የሰው ዘር አባት፣ አብርሃም የአላህ ወዳጅ፣ ሙሴ አላህን ፊት ለፊት ያነጋገረና ኢየሱስ የአላህ ቃልና መንፈስ የሆነ፡፡ እነዚህ መጠርያዎች ለእያንዳንዳቸው በልዩነት የተሰጡ መሆናቸውን መገንዘብ ከባድ አይደለም፡፡ ከአዳም ውጪ ሌላ የሰው ልጆች ሁሉ አባት ተብሎ የሚጠራ የለምና፣ ከአብርሃ፣ ውጪ የአላህ ወዳጅ ተብሎ የሚጠራ የለምና፣ ከሙሴ ውጪ አላህን ፊት ለፊት ያየ ተብሎ የሚጠራ የለምና፤ ከኢየሱስ ውጪ የአላህ ቃልና የአላህ መንፈስ ተብሎ የተጠራ የለምና፡፡ ይህንም ወደ አንድ ድምዳሜ ይወስደናል፡፡ ከሊማቱላህ እና ሩህአላህ ለኢየሱስ ብቻ የተገቡ ስሞች ናቸው፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ከዚህ ስያሜ በስተጀርባ ያለውን አንድምታ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል፡፡ በተለይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ስያሜ ለኢየሱስ እንደሚያውለው ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ልንመረምር ይገባናል፡፡
ራዕ 19፡13 “በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።”
ሱራ 4፡171 ላይ ኢየሱስ የአላህ ቃል እንጂ ሁለቱ ሱራዎች ላይ እንደምናነበው ከአላህ የኾነ ቃል አይደለም የተባለው፡፡ ይህም ኢየሱስ የፈጣሪ ቃል የተገለጠለት በመሆኑ ወይም በቃል ስለተፈጠረ መሆኑን ሳይሆን እርሱ ራሱ የአላህ ቃል መሆኑን ነው የሚያመለክተን፡፡ ስያሜውም ማንነቱን የሚያመለክት እንጂ ስለአፈጣጠሩ የሚናገር አይደለም፡፡ አንድ ክርስቲያን ጸሐፊ ስለ ሱራ 3፡45 ተመሳሳይ የሆነ ነጥብ ያስቀምጣል፡፡
ከላይ በጠቀስነው የቁርአን ክፍል ክርስቶስ “ከእርሱ የኾነ ቃል” ተብሏል፤ ይህም “የአምላክ ቃል” ነው፡፡ አረብኛው እንደሚያመለክተው “የአላህ ቃል” ነው እንጂ “ከአላህ የኾነ ቃል” አይደለም፡፡ (ከሊማቱላህ ነው እንጂ ከሊማቲሚን ካሊማቱላህ አይደለም)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የአላህ ቃል ወይም መገለጫ አንደሆነ እናያለን፡፡ ሌላ ማንም ነቢይ በዚህ ስም አልተጠራም፡፡[7]
ኢየሱስ ራሱ ልዩ የሆነ የአምላክ ለሰው ልጆች መገለጥ መሆኑ ግልፅ ሆኖ ይታያል፡፡ ልብ በሉ፤ ለኢየሱስ ቃል ከሰማይ አልመጣለትም፤ ኢየሱስ ራሱ ያ ከሰማይ የመጣው ቃል ነው! አንድ ክርስቲያን ጸሐፊ እንደተናገረው፡-
ኢየሱስ የአምላክ ቃል ነው፣ ይህም ሙስሊሞች እንደሚሉት በመለኮታዊ ትእዛዝ በአምላክ ቃል በመፈጠሩ ሳይሆን እርሱ የአምላክን ሐሳብና ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ለሰው ዘር የሚያሳውቅ በመሆኑ ነው፡፡ በኢየሱስ አማካኝነት አምላክ ተናገረ በልዩ መንገድም ፈቃዱን አከናወነ፡፡[8]
ሌላም ጸሐፊ እንዲህ ይላል፡-
አላህ ራሱ ኢየሱስን “የአላህ ቃል” እያለ እስከጠራው ድረስ እርሱ ብቸኛና ትክክለኛ የአምላክ የፈቃዱ መገለጫና የአምላክም ብቸኛ መገለጥ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡[9]
ቁርአን ስለ አዳም “አደምም የጌታውን ቃል ተቀበለ” ከሚለው ውጪ ብዙ አይናገርም (ሱረቱል 2፡37)፡፡ ከጌታው ዘንድ (ሚረቢ)ከሊማት የወረደለት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን እርሱ ራሱ ከሊማቱላህ (የአላህ ቃል) ተባለ፡፡
እንግዲህ የስያሜው ትርጉም ቁርአን ውስጥ ባለመኖሩ ምክንያት ለአል-መሲህ እንዳደረግነው ለዚህም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በመምጣት ትክክለኛውን ትርጉም ማየት ግድ ይለናል፡፡
ስያሜው የኢየሱስን መለኮታዊነት አመልካች ነው
“ቃል” የሚለው ስያሜ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰው የመጣ መገለጥ መሆኑን እንደሚያመለክት ተመልክተናል፡፡ እርሱ ትክክለኛው የአምላክ ለሰው ልጆች መገለጥ ነው፡፡ እርሱን ማወቅ አምላክን ማወቅ ነው፡፡ ከዮሐንስ ወንጌል የቃሉን ትርጉም እናገኛለን፡-
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ዮሐ 1:1-2
በዚህ ክፍል ኢየሱስ ቀድሞ አምላክ ፍጥረትን ሊፈጥር ሲጀምር በቃልነት ይኖር የነበረ እንደሆነ፣ በፍጡርነት ሳይሆን ሙሉ መለኮትነትን በመላበስ የነበረ እንደሆነ እናያለን፡፡ ወደእርሱ ቃል አልተላከም፤ ያ ቃል ራሱ ነው ሥጋ የሆነው፡-
ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፡፡ ዮሐ 1፡14
ቁርአን ግልፅ በሆኑ ኹኔታ ኢየሱስን የአምላክ ቃልና ከአምላክ የኾነ ቃል ይለዋል፡፡ ታድያ በዚያ ቃል ውስጥ የመለኮት ማንነትን ብናይ አመክንዮአዊ አይደለምን? በሚገርም ሁኔታ ቀደምት ክርስቲያኖችም ይህን የኢየሱስን ልዩ የሆነ ስያሜ በቁርአን መገኘቱ ለመለኮትነቱ ፍንጭ እንዳለው አስተውለዋል፡፡ መሐመድ ክርስቶስን ለማመልከት “ቃል” የሚለውን በመጠቀሙ ሳያስተውል ነገር ግን በውስጠ አዋቂነት የክርስቶስ የአዳኛችንን መለኮትነት አምኗል፡፡[10]
አንድ ጸሐፊ ይህን ሐሳብ ሲያጠቃልል እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“የጌታ የኢየሱስ ስያሜ ሊታወቅ የሚችለው በወንጌሉ ማጣቀሻነት ብቻ ሲሆን ወንጌሉ ደግሞ እርሱን የእግዚአብሔር ቃል ሲለው መለኮትነቱንና ከመወለዱ በፊት ቀድሞ ከአባቱ ጋር የነበረ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡”[11]
አንድ ሙስሊም ጸሐፊም ስያሜው ሰማያዊ የሆነ ማንነትን በውስጡ የያዘ መሆኑን ዕውቅና በመስጠት እንዲህ ብሏል፡-
በተፈጥሮ ሩሁላህ (የአላህ መንፈስ) እና ከሊማቱላህ (የአላህ ቃል) በሚለው ስያሜ የተጠራውና ከገብርኤል እፉታ የተፈጠረው ከሰማይ ሰማያዊ ሲሆን ሌሎች አብዱላህ (የአላህ ባርያ) ተብለው የተጠሩት ከመሬት መሬታውያን መሆናቸውን ያሳያል፡፡[12]
ጸሐፊው ኢየሱስ የአምላክ ቃልና መንፈስ በመሆኑና ሙሐመድ የአላህ ባርያ ብቻ በመሆኑ መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ ያነጻጽረዋል፡፡ ለኢየሱስ ልዩ የሆነ ስያሜ መሰጠቱ እርሱ ሰማያዊ መሆኑንና ወደ ሰማይ ከመወሰዱ ጋር ትልቅ ግንኙነት እንዳለው ሲያረጋግጥ ሙሐመድ ግን እንደ ሌሎቹ ተራ ባርያ በመሆኑ ወደመጣበት መሬት ተመልሶ ሞቷል፡፡ (ሙስሊሞች ሙሐመድ እንደ ኢየሱስ ልዩ የሆነ ማንነት አለው ብለው ሊናገሩ አይችሉም፤ ምክንያቱም ሙሐመድ አንድም ቦታ የአላህ ቃልና መንፈስ አልተባለምና፡፡ ምንም እንኳን ኢየሱስ እንደ ሙሐመድ በሱራ 19፡30 ላይ አብዱላህ (የአላህ ባርያ) ቢባልም ሙሐመድ ግን እንደ ኢየሱስ የአላህ ቃልና መንፈስ አንድም ቦታ አልተባለም፡፡)
ክርስቲያኖች ይህንን ልዩ ስያሜ ትርጉም አጽንኦት ሰጥተው ሊመረምሩ ይገባል፡፡ ሙስሊሞች ደግሞ ይህ ስም ለኢየሱስ ብቻ እንደሚገባው ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚስማሙ ሊያስተውሉ ይገባል፡፡
ሌላው አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ነገር የስያሜው መለኮታዊነት ነው፡፡ በአጭሩ መገንዘብ ያለብን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና መለኮት መሆኑን ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ጸሐፊ ስለ ስያሜው ምንነት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
“የእግዚአብሔር ልጅ” እና “የእግዚአብሔር ቃል” የሚሉት ሁለቱም በአዲስ ኪዳን በተመሳሳይ ትርጉም ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ሁለቱም የክርስቶስን መለኮትነትና ከአባቱ ጋር ያለውን አንድነት ይገልጻሉ (ዮሐ 10፡30)፡፡[13]
የእግዚአብሔር ልጅ የሚለው መጠርያ የልጁን ለአባቱ መገዛት እንደሚያሳይ ሊታሰብ ይችላል፤ የእግዚአብሔር ቃል ከሚለው መጠርያ አኳያ ግን እንዲህ ዓይነት መበላለጥ ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስሙ በራሱ ግልጽ በሆነ ሁኔታ የሚያሳየው ተሰያሚው የማይታየው አምላክ ማንነት መገለጫ መሆኑን ነውና፡፡ የሚገርመው ቁርአን ክርስቲያኖች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመናችንን ይኮንናል፤ ራሱ ግን በተመሳሳይ አገላለጽ ኢየሱስን የአላህ ቃል በማለት መለኮታዊ የእግዚእሔር ልጅ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በስሞቹ መካከል ግን የትርጉም ልዩነት አለመኖሩን መረዳት ይኖርብናል፡፡
በዮሐንስ ወንጌል መሠረት “የእግዚአብሔር ቃል” መለኮት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ “ከእርሱ የኾነ ቃል” በሚለው አገላለጽ ከእርሱ (ሚን) የሚለው ቃል በስሙና በተውላጠ ስሙ መካከል ያለውን ጥብቅ ዝምድና ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ትርጉሙ “ቃሉ” (the Word) ከእርሱ (ሁ) ከአምላክ ጋር ተመሳሳይ መለኮት ነው፡፡[14]
ሱራ 4፡171 ቁርአን ምን ለማለት እንደፈለገ ሰፊ ማብራርያ ባይሰጥም ከጥቅሱ የተገኙት ሁለት ስያሜዎች (አል-መሲህ እና የአላህ ቃል) ኢየሱስ ከተራ ነቢይነት ያለፈ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ለሙስሊሞች እውነትን የምንናገርበት፣ ሕይወት ወደ ሆነው ወደ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ የምንጠራበት በቂ አመክንዮ አለን፡፡
ኢየሱስ እንደ ሌሎች ነቢያት መልእክተኛ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ዓለምን ሊያድን የመጣ መሲህ፤ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ የእግዚአብሔር ሕያውና ዘላለማዊ ቃል ነው፡፡
[1] Yusuf Ali, The Holy Qur’an, p. 132
[2] Goldsack, Christ in Islam, p. 14
[3] Ahmad, Jesus in Heaven on Earth, p. 164
[4] Sale, Koran, p. 48, n.4
[5] Abdul-Haqq, Sharing Your Faith with a Muslim, p. 84
[6] ሳሂህ ሙስሊም መጽሐፍ 001 ቁጥር 0380
[7] Goldsack, Christ in Islam, p. 15
[8] Chapman, You Go and Do the Same, p. 81
[9] Zwemer, The Muslim Christ, p. 37
[10] O’Shaughnessy, The Koranic Concept of the Word of God, p. 56
[11] Goldsack, Christ in Islam, p. 14
[12] Alam, Nuzul-e-Esa: Descension of Jesus Christ, p. 86
[13] Pfander, The Mizanu’l Haqq (Balance of Truth), p. 165
[14] Abdul-Haqq, Sharing Your Faith with a Muslim, p. 68