“ሰይጣናዊ ጥቅሶች”: ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ አለመሆናቸውን የሚገልጥ ጥንታዊ ታሪክ

“ሰይጣናዊ ጥቅሶች”

ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ አለመሆናቸውን የሚገልጥ ጥንታዊ ታሪክ

ተመሳሳይ ርዕስ ካለው በሰልማን ሩሽዲ ከተጻፈውና ዓለም አቀፋዊ የሙስሊሞች ቁጣና ተቃውሞን ካስነሳው የልበወለድ መጽሐፍ የተነሳ በዓለም ዙርያ የሚገኙ ብዙ ሕዝቦች ከዚህ ታሪክ ጋር ተዋውቀዋል፡፡ ይህ ታሪክ ቀዳሚያን በሆኑት እስላማዊ ምንጮች ውስጥ በስፋት የተዘገበ ሲሆን[1] የሙሐመድን እውነተኛ ነቢይነት ጥርጣሬ ላይ ስለሚጥል ብዙ ሙስሊሞች ሊቀበሉት አይወዱም፡፡ ታሪኩ በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ወቅቱ ሙሐመድ ስደትና መገለል ስለበረታባቸው የመካ ነዋሪዎችን ለማስደሰት መልዕክታቸውን ማመቻመች የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ አንድ ቀን ካዕባ በተባለው የመካ አምልኮተ ጣዖታት ቦታ ሳሉ የተለያዩ የአረብ ጎሣ መሪዎችን አንድ ላይ ተሰብስበው ተመለከቱ፡፡ የእነዚህን ሰዎች ልብ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉና ከራሳቸው ወገን ማሰለፍ እንደሚችሉ ካወጡና ካወረዱ በኋላ አንድ ሐሳብ ተከሰተላቸው፡፡ በአረብያ ይመለኩ ከነበሩት ጣዖታት መካከል ታዋቂ የሆኑት ሦስቱ ጣዖታት፤ ማለትም አል-ላት፣ መናትና ኡዛ ከፍተኛ ክብር እንዳላቸውና ከአላህ የማማለድ ሥልጣን እንዳላቸው ተናገሩ፡፡ ይህ ደግሞ ቁረይሾችን አስፈነደቀ፡፡ እርሳቸው ሲሰግዱ ሁሉም አብረዋቸው ሰገዱ፡፡ የመካ ነዋሪዎች እስልምናን መቀበላቸውን በተመለከተ እስከ አክሱም ድረስ የተወራው ወሬ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ሱራ 53፡19-20 ላይ የሚገኘው “አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን (አያችሁን? የምትግገዟቸው ኃይል አላቸውን?)”[2] የሚለው ጥቅስ መጀመርያ እንዲህ አልነበረም፡፡ “እነዚህ ከፍ ያሉ በራሪዎች ናቸው፡፡ ምልጃቸውም ተስፋ ይደረጋል” የሚል ተጨማሪ ንባብ ነበረው፡፡

ቀደም ሲል ሲነቅፏቸው የነበሩትን ጣዖታት ማሞጋገሣቸውና የተቃወሙትን አምልኮተ ጣዖት የሚያጸድቅ “መገለጥ” መናገራቸው ተከታዮቻቸውን ማስቆጣቱና ጥርጣሬ ላይ መጣሉ አልቀረም፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሐመድ ተከታዮቻቸውን ላለማጣትና ከገቡበት አጣብቂኝ ለመውጣት ሌላ መላ ዘየዱ፡፡ ይህም “መገለጡ” ከሰይጣን መሆኑን መናገር ነበር፡፡ ይህ ውዥንብር ከተከታዮቻቸው መካከል የተወሰኑትን ጥርጣሬ ላይ የጣለና የቁረይሾች ስደት እንዲበረታባቸው ያደረገ ቢሆንም ቅሉ በአጎታቸው በአቡጧሊብና በባለቤታቸው በከዲጃ ድጋፍ አስቸጋሪውን ጊዜ ለማለፍ ችለዋል፡፡ ስህተቱም ያልተለመደና በሌሎች ነቢያት ላይ ያልደረሰ አለመሆኑን ለማስረዳት ሌሎች “መገለጦችን” ሲያመጡ እንመለከታለን፡-

“ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አላክንም ባነበበ (እና ዝም ባለ) ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ (ማጥመሚያን ቃል) የሚጥል ቢሆን እንጅ፡፡ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል፡፡ ከዚያም አላህ አንቀጾቹን ያጠነክራል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡ ሰይጣን የሚጥለውን ነገር ለእነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ላለባቸው ልቦቻቸውም ደረቆች ለሆኑት ፈተና ሊያደርግ (ይጥላል)፡፡ በዳዮችም ከእውነት በራቀ ጭቅጭቅ ውስጥ ናቸው፡፡” (የሐጅ ምዕራፍ 22፡52-53)

የጉዳዩን ታሪካዊነት በተመለከተ ሻቢር አኽታር የተሰኙ ሙስሊም ጸሐፊ የሚከተለውን ብለዋል፡- “ይህ በጣም ሐቀኛ በሆነ እስላማዊ ትውፊት የተዘገበው አውዳሚ የሆነ ክስተት ሰይጣን በነቢዩ የመገለጥ ንባብ አቀባበል ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል አሳይቷል … ሩሽዲ በሱራ 53 ላይ የሚገኘውን ሙሉ ተቀባይነት ያለውንና ሳይከለስ የተጠበቀውን ተያያዥ አንቀፅ ጠቅሶ በማጣመም በመጀመርያው መገለጥ ውስጥ የነበረውን ሰይጣን ያስገባውን ተክቷል፡፡”[3]

“ሰይጣናዊ ጥቅሶች” የሚለውን ሐሳብ ያመነጨው ሰልማን ሩሽዲ ወይም ሌላ ሰው አይደለም፡፡ ታሪኩ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ የተዘገበና ለክፍለ ዘመናት የኖረ ነው፡፡ ይህ “የሰይጣናዊ ጥቅሶች” ክስተት ሙሐመድ መገለጥን በመገለጥ የመሻር አስተምህሮን እንዲያስተዋውቁ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡[4]

ማጠቃለያ

ሙስሊም ወገኖቻችን ብዙ ጊዜ ስለ ሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተተነበየ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል ደግሞ ዘዳግም 18፡18 ላይ የሚገኘው አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡-

“እግዚአብሔርም አለኝ፦ የተናገሩት መልካም ነው፤ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ፡፡”

ሙስሊም ወገኖቻችን “ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ” የሚለው ሙሐመድን እንደሚያመለክት ይናገራሉ፡፡ የዚህን ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም በሌላ ጽሑፍ የምንዳስስ በመሆኑ ለጊዜው አስተያየት ከመስጠት እንቆጠባለን፡፡ አሁን ትኩረታችንን ማድረግ የምንፈልገው በጥቅሱ ቀጣይ ክፍል ላይ ይሆናል፡፡ ሙስሊሞች ሳያነቡ የሚያልፉት የጥቅሱ ቀጣይ ክፍል እንዲህ ይላል፡-

ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል፡፡ (ቁ. ቀ9)

ሙሐመድ አል-ላት፣ መናትና ኡዛ በተሰኙት የአረብ ጣዖታት ስም ትንቢት መናገራቸውን ጥንታውያን እስላማዊ ምንጮች በግልፅ አስፍረዋል፡፡ ነቢዩ ሙሴ ሙሐመድን ቢያገኛቸው ኖሮ ያለምንም ጥርጥር በድንጋይ ተወግረው እንዲሞቱ ያደርጋቸው ነበር! እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ በሙሐመድ ላይ በታየው ሁኔታ በሰይጣን ሊታለል አይችልም፡፡ ስለዚህ ነቢዩ ሙሐመድ እውነተኛ የፈጣሪ ነቢይ አይደሉም፡፡


[1] Al-Tabari, The History of al-Tabari (Ta’rikh al-rusul wa’l-muluk), Vol. VI: Muhammad at Mecca; Translated by W. M. Watt and M.V. McDonald, pp. 107-112. Guillaume. The Life of Muhammad; pp. 165-167

[2] በአማርኛ የቁርኣን ትርጉም በቅንፍ የተቀመጡት በአረብኛው አይገኙም፡፡

[3] Shabbir Akhtar. Be Careful With Muhammad; 1992, p. 114

[4] ሳም ሰለሞንና ኢ-አልመቅዲሲ፡፡ አል-ሂጅራ፣ ገፅ 60