ሰባው ሱባዔና የሙስሊም ሰባኪያን የኩረጃ ሙግት
ወሒድ የተሰኘ አንድ አብዱል በዳንኤል ትንቢት የተነገረው “ሰባ ሱባዔ” የመሲሁን መምጣት እንደማያመለክት ሙግት አቅርቧል፡፡ ይህ ሙግት ከረበናተ አይሁድ የተቀዳ ሲሆን ከክርስቲያናዊው ትርጓሜ አኳያ ውኀ የሚያነሳ አይደለም፡፡ አስደናቂው ትንቢት እንዲህ ይነበባል፡-
“ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፡፡ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል ጥፋትም ተቀጥሮአል።” ዳንኤል 9፡24-27
በዚህ ትንቢት መሠረት ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ ስድሳ ዘጠኝ ሱባዔ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሱባዔ (ሸቡአ) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሰባት ዓመታት ናቸው፡፡ በአይሁድ አቆጣጠር መሠረት እነዚህ በአጠቃላይ 483 ዓመታት ናቸው፡፡ የኢየሩሳሌም ቅጥር እንዲጠገን በ444 ዓ.ዓ. ንጉሥ አርጤክስስ ትእዛዝ ካወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተሰቀለበት ዘመን ያመጣናል፡፡
ወሒድ ለዚህ ያቀረበው የማስተባበያ ሙግት ብዙ ስህተቶችን የሸከፈ ነው፡፡ የመጀመርያው ስህተት “ትእዛዙ የወጣበትን ዘመን” ወደ ኤርምያስ ዘመን መውሰዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ” የሚለውን በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን የወጣውን ትእዛዝ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለ ኢየሩሳሌም እንደገና መሠራት ለነቢዩ ኤርምያስ የሰጠውን ቃል እንደሚያመለክት ይነግረናል፡፡ ወሒድ የጠቀሰው የኤርምያስ ትንቢት 29፡10-14 እንዲሁም 30፡18 ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም እንደገና መሠራት የተናገረው ትንቢት ንጉሥ ሴዴቅያስ ገና ሳይማረክ በ593 ዓ.ዓ ገደማ የተነገረ ነው፡፡ ወሒድ ግን “ይመጣል” የተባለው መሢህ ቂሮስ መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲመቸው አርባ ዘጠኝ ዓመታትን የያዙትን ሰባቱን ሱባዔዎች ለብቻቸው ከነጠለ በኋላ ቆጠራውን ሴዴቅያስ ከተማረከበትና የኤርምያስ አገልግሎት ከተገባደደበት ከ586 ዓ.ዓ ጀምሮታል፡፡ “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ቃሉ የመጣው ከተማይቱ በፈረሰችበት በ 586 ቅድመ-ልደት ነው” በማለትም ከእውነት የራቀ ነገር ይናገራል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኤርምያስ ትንቢቱን የተናገረው ሴዴቅያስ ገና ንጉሥ ሳለ ነበር፡፡ ይህ የወሒድን ስሌት የሚያዛባ ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡
ዳንኤል በተናገረው ትንቢት መሠረት ቆጠራው የሚጀምረው “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት” ጊዜ እንጂ ትንቢት ከተነገረበት ጊዜ አይደለም፡፡ ይሁን እንኳ ብንል ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ምርኮና ስለ ኢየሩሳሌም እንደገና መሠራት ከነቢዩ ኤርምያስ በማስቀደም ተናግሮ ሳለ ቆጠራውን ከእርሱ ከመጀመር ይልቅ ከኤርምያስ የምንጀምርበት ምክንያት ግልፅ አልተደረገም (ኢሳ. 14፡1-6፣ 48፡17-20፣ 54)፡፡ ምናልባት “ዳንኤል የኤርምያስን መጽሐፍ ሲያነብ ስለነበር” የሚል ምላሽ ይሰጠን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሙግቱ “ትእዛዙ መለኮታዊ ቃል ነው” በሚል እሳቤ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እንዲህ ያለ ምላሽ አያስኬድም፡፡ ትእዛዙ “መለኮታዊ ቃል” ከሆነ ኢሳይያስ መለኮታዊውን ቃል አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ስለዚህ ስሌቱ መጀመር ያለበት ከዚያ ነው፡፡ ሲጀመር ደግሞ መለኮታዊ ቃል በጊዜ ተገድቦ “ከዚህ ዓመት ይጀምራል” ስለማይባል የዳንኤል አነጋገር “የነገሥታትን ትእዛዝ ወይም አዋጅ” የተመለከተ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ወደ ጎን አድርገን በወሒድ መረዳት መሠረት እንሒድ ብንል እንኳ ቆጠራውን መጀመር ያለብን ኤርምያስ ለመጀመርያ ጊዜ ስለ ጉዳዩ ከተናገረበት ጊዜ እንጂ ከኤርምያስ የአገልግሎት ፍጻሜ ዘመን አይደለም፤ ምክንያቱም “…ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ” ተብሎ በግልፅ ተጽፏልና፡፡ ትእዛዙ የኤርምያስ ትንቢት ነው ከተባለ ኤርምያስ ትንቢቱን የተናገረው ሴዴቅያስ ገና ንጉሥ ሳለና ኢየሩሳሌም ከመፍረሷ በፊት በመሆኑ ስሌቱ ከቂሮስ ጋር አይገጥምም፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ ደግሞ የወሒድን ሙግት ውኀ በላው ማለት ነው፡፡
የዳንኤልን ትንቢት በአስተውሎት ስናነበው የሰውየው ሙግት ትርጉም አልባ መሆኑ ይበልጥ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ትንቢቱን ደግመን እናንብበው፡- “…ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፡፡” በትንቢቱ መሠረት መሢህ የሚመጣው ከሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ በኋላ፣ ማለትም ከስድሳ ዘጠኝ ሱባዔ በኋላ ነው (7+62=69)፡፡ ስለዚህ መሲሁ የሚመጣው ከ 483 ዓመታት በኋላ ነው (69×7=483)፡፡ ነገር ግን ወሒድ እንደነገረን መሢሁ ቂሮስ ከሆነና ስሌቱ የሚጀምረው ከ586 ዓ.ዓ ከሆነ ውጤቱ ወደ 103 ዓ.ዓ ያመጣናል (586-483=103)፡፡ በዚህ ጊዜ እንግዲህ ቂሮስ ከሞተ ክፍለ ዘመናት አልፈዋል፡፡
ሁለተኛው ስህተቱ እብራይስጡን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ለገዛ ሙግቱ ችግር መፍጠሩ ነው፡፡ “…እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፡፡ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች” የሚለውን “ከዚያም በስድሳ ሁለት ሱባዔ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ጎዳና እና ከቅጥር ጋር ትሠራለች” በማለት በመተርጎም የኢየሩሳሌምን መሠራት ከአራት ክፍለ ዘመናት በላይ አራዝሟል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኢየሩሳሌም በነህምያ ዘመን በአርጤክስስ ፈቃድ መሠራት ጀምራ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ የተሟላች ከተማ ሆናለች፡፡ የወሒድ ትርጓሜ የእብራይስጡን ሐሳብ የማያንጸባርቅ ከመሆኑም በተጨማሪ የኢየሩሳሌምን መሠራት ከአራት ክፍለ ዘመናት በላይ በማራዘም ከታሪክ ጋር ይጋጫል፡፡ ነገር ግን ዘግይቶ በለቀቀው ጽሑፍ የመጀመርያ ሐሳቡን ረስቶት እንዲህ በማለት ተጻራሪ ሐሳብ ያቀርባል፡-
“…የመቅደሱ ግንባታ የተጠናቀቀው በ 516 ቅድመ-ልደት ነው። ከመጀመሪያው ከቂሮስ አዋጅ ከ 539 እስከ የመቅደሱ ግንባታ መጠንናቀቅ 516 ድረስ 23 ዓመት እንጂ 49 ዓመት አይደለም፥ 539-516= 23 ዓመት ይሆናል።”
አቶ ወሒድ፤ ከራስ ጋር መጋጨት የነቢዩ ሱና በመሆኑ አንፈርድብህም፡፡
“እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች” የሚለውን ደግሞ ከምርኮ ዘመን ጀምሮ ያለውን የጭንቀት ዘመን እንደሚያመለክት ይናገራል፤ የምርኮው ዘመን የጭንቅ ዘመን እንደነበረ የሚናገሩ ጥቅሶችንም ጠቅሷል፡፡ ጥቅሱ “በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች” ስለሚል መሠራትን እንጂ መፍረስን አይጠቅስም፡፡ የምርኮው ዘመን የጭንቀት ዘመን መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ኢየሩሳሌም ዳግመኛ ስትሠራ የነበረው ተቃውሞና ጭንቀት ደግሞ በነህምያ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ተዘግቧል፡፡ “በጭንቀት ዘመን … ትሠራለች” የሚለውን ወደ ኋላ ወስዶ ከመፍረስ ዘመን ጋር ማጣበቅ የወሒድን አንብቦ የመረዳት አቅም ጥያቄ ላይ ይጥላል፡፡ የመፍረስ ዘመን የራሱ የሆነ ጭንቀት እንደነበረበት ሁሉ የመሠራት ዘመንም የራሱ የሆነ ጭንቀት ነበረው፡፡ ጥቅሱ በመሠራት ዘመን ስለነበረው ጭንቀት የሚናገር በመሆኑ “ጭንቀት” የሚል ቃል በሁለቱም ዘመናት ስለተጠቀሰ ብቻ ቆጠራውን ከምርኮ ዘመን መጀመር ትርጉም አይሰጥም፡፡
ሦስተኛው ስህተቱ የጥቅሱን ሰዋሰዋዊ ይዘት የሚያዛባ የዘመን ስሌት መጠቀሙ ነው፡፡ የመሲሁን መገደል በተመለከተ የተነገረውን እንዲህ በማለት ተርጉሞታል፡-
በ 605 ቅድመ-ልደት”BC” ከተማይቱ ተማረከች፥ የጭንቀቱ ዘመኗ ጀመረ። ከ 605 ጀምረን 62 ሱባዔ ስንቆጥር 171 ቅድመ-ልደት”BC” ይሆናል። ቅድሚያ 62 ሱባዔ 434 ዓመት ነው፥ 62×7=434 ይሆናል። እንግዲህ ከምርኮ 605 ጀምሮ 434 ዓመት ስንቆጥር 171 ቅድመ-ልደት”BC” ነው። 605-434=171 ይሆናል። በዚህ ጊዜ የተገደለ መሢሕ አለ፦ ዳንኤል 9፥26 “ከስድሳ ሁለት ጊዜ በኋላ መሢሕ ይገደላል” ፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም።
“ተገደለ” እያለን ያለው “መሢህ” ሊቀ ካህኑ አንያስ ወልደ ስምዖን ነው፡፡ አንጥያኮስ ኤጲፋኔስ በ 170 ዓ.ዓ. ሣልሳዊ አንያስን አስገድሎት ነበር፡፡ ወሒድ የመጀመርያዎቹን ሰባት ሱባዔዎች በተመለከተ ከ 586 ዓ.ዓ ጀምሮ እስከ ቂሮስ ዘመን ማስላቱን እናስታውስ፡፡ በማስከተል የሚመጡትን 62 ሱባዔዎችን በተመለከተ ከተቀራራቢ ዓመት በመነሳት አስልቷል፡፡ ጥቅሱ ግን በግልፅ “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል” በማለት ይናገራል፡፡ ሰባቱና ስድሳ ሁለቱ ሱባዔዎች ተከታትለው የሚመጡ እንጂ ተደራራቢ አይደሉም፡፡ “እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል” ተብሎ የመሢህ መምጫ ከስድሳ ዘጠኝ ሱባዔዎች በኋላ እንደሆነ በግልፅ ተነግሮ ሳለ ስድሳ ሁለቱን ሱባዔዎች በሰባቱ ላይ እንደ መደመር አንዱን አንስቶ በሌላው ላይ መደረብ የጥቅሱን ሰዋሰዋዊ አወቃቀር መናድ ነው፡፡ የጥቅሱን ተፈጥሯዊ ንባብ ተከትለን ከኼድን ትንቢቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት የሚያሳይ እንጂ የሣልሳዊ አንያስን መገደል የሚያመለክት እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ የእብራይስጡን ሰዋሰዋዊ አወቃቀር ለማየት ይህንን ገፅ ይጠቀሙ፡- https://biblehub.com/text/daniel/9-25.htm፡፡ የወሒድን ትርጓሜ የሚደግፍ ምንም ነገር የለም፡፡ የጥቅሱ ሰዋሰዋዊ አወቃቀር የማያፈናፍን መሆኑን የተረዱ ብዙ የአይሁድ ሊቃውንት “መሢህ” የአይሁድ ደጋፊ የነበረውን ንጉሥ አግሪጳን ወይንም በሮማውያን ሥልጣኑን የተቀማውን ሊቀ ካህን ሊያመለክት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህንን አመለካከት ለማፅደቅ “ይገደላል” ተብሎ የተተረጎመውን “ይከሬት” የሚለውን ቃል አሳስተው ይተረጉማሉ፡፡
በማስከተል ደግሞ ይህ አብዱል ከመሢህ መገደል በኋላ ከተማይቱንና መቅደሱን እንደሚያጠፋ የተነገረው አለቃ አንጥያኮስ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አንጥያኮስ በዚህ ትንቢት ውስጥ ቦታ ስለሌለው ከመሢህ መገደል በኋላ የመጣው አለቃ ሮማዊው ጀነራል ቲቶ (ታይተስ) ነው፡፡ በትንቢቱ ውስጥ ይፈጸማሉ የተባሉት ተግባራት በአንጥያኮስ አልተፈፀሙም፡፡ በትንቢቱ መሠረት “የሚመጣው አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ” ተብሎ የተነገረ ቢሆንም አንጥያኮስ መቅደሱን ከማርከስ በዘለለ ከተማይቱንም ሆነ መቅደሱን አላጠፋም፡፡ ሮማዊው ቲቶ ግን ከተማይቱንም መቅደሱንም ሙሉ በሙሉ አጥፍቷል፡፡ የአንጥያኮስ ስደት በጣት ለሚቆጠሩት ዓመታት ብቻ የቆየ በመሆኑ “ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል” ከተባለው ትንቢት ጋር አይጣጣምም፡፡ በሮማዊው የጦር መሪ በቲቶ አማካይነት ኢየሩሳሌምና መቅደሱ የፈረሱበት ሁኔታ በአይሁድ ታሪክ እጅግ የከፋው ውድመት ሲሆን በዚህም ምክንያት የኢየሩሳሌምና የመቅደሱ ባለቤትነት ጥያቄ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የጦርነት ሰበብ እንደሆነ መቀጠሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህም ትንቢቱ አንጥያኮስን ሳይሆን ቲቶን እንደሚያመለክት በግልፅ ያስገነዝባል፡፡
እንደሚገደል የተነገረው መሢህ ሣልሳዊ አንያስ ነው የሚሉ ወገኖች ቁጥር 24 ላይ የተባለውን ልብ ማለት ያስፈልጋቸዋል፡-
“ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል።” (ዳን. 9፡24)
ለግልጽነት ያህል በአዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንብበው፡-
“ዐመፃን ለማቆም፣ ኃጢአትን ለማስወገድ፣ በደልን ለማስተሰረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራዕይንና ትንቢትን ለማተምና እጅግ ቅዱስ የሆነውን ለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔ ታውጇል፡፡”
ስለዚህ ሰባው ሱባዔ ከምርኮ ዘመን ጀምሮ እስከ አንጥያኮስ መምጣትና ሣልሳዊ አንያስ መገደል ያለውን ዘመን የሚመለከት ከሆነ እነዚህ ትንቢቶች እንዴትና መቼ እንደተፈጸሙ ሊያስረዳን የሚችል ሰው ይኖር ይሆን? እነዚህ ትንቢቶች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሥራ የተፈጸሙና በዳግም ምፅዓቱ ወደ ምልዓት የሚመጡ መሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ከሚያውቅ ሰው ኹሉ የተሰወረ አይደለም፡፡
የመጨረሻው ሱባዔ ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት መካከል አከራካሪ ርዕስ ነው፡፡ አንዳንዶች በቲቶ ወረራ ዘመን ፍፃሜን እንዳገኘ የሚናገሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ወደፊት በመጨረሻው ዘመን ከክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት ጋር ተያይዞ ይፈፀማል ይላሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዘመነ ፍጻሜ ጋር አያይዞ ትንቢቱን ተርጉሞታል (ማቴ. 24፡15)፡፡ የሆነው ሆኖ ሰባኛው ሱባዔ በስድሳ ዘጠኙ ትርጓሜ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ በስድሳ ዘጠነኛው ሱባኤ ላይ መሢህ እንደሚመጣና እንደሚገደል በግልፅ ተጽፏል፤ እርሱ ደግሞ ከጌታ ኢየሱስ ውጪ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡
የአዋጁን ጅማሬ በተመለከተ ይህ አብዱል በክርስቲያኖች መካከል መግባባት አለመኖሩን ለመግለፅ ሞክሯል፡፡ ኢየሩሳሌምን የተመለከቱ አዋጆች በተለያዩ ዘመናት መውጣታቸው የሚታወቅ ቢሆንም በግልፅ የከተማይቱ ቅጥር እንዲሠራ የፈቀደው በ444 ዓ.ዓ የወጣውና በነህምያ አማካይነት ተፈፃሚ የሆነው የአርጤክስስ አዋጅ በመሆኑ ብዙ ክርስቲያን ሊቃውንት ስድሳ ዘጠኙን ሱባዔዎች ማስላት የሚጀምሩት ከዚያ ነው፡፡ አራቱ አዋጆች የሚከተሉት ናቸው፡-
- የቂሮስ አዋጅ፡- ዕዝራ 1:1-3፣ (538 ዓ.ዓ)፡፡ አዋጁ መቅደሱ እንዲገነባና አይሁድ ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ የሚናገር ነው፡፡
- የዳርዮስ አዋጅ፡- ዕዝራ 6:1-12፣ (521 ዓ.ዓ)፡፡ የዳርዮስ አዋጅ የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንዲቀጥል የቂሮስን አዋጅ የሚያድስ እንጂ አዲስ ግንባታን የሚመለከት አይደለም፡፡
- የመጀመርያው የአርጤክስስ አዋጅ፡- ዕዝራ 7:12-26፣ (457 ዓ.ዓ)፡፡ ይህኛውም አዋጅ ከቤተ መቅደሱ ጋር የተያያዘ እንጂ ኢየሩሳሌምን የሚጠቅስ አይደለም፡፡
- ሁለተኛው የአርጤክስስ አዋጅ፡- ነህምያ 2:1-8 (444 ዓ.ዓ)፡፡ ይህ አዋጅ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መገንባትን የተመለከተ ነው፡፡
የዳንኤል ትንቢት የኢየሩሳሌምን መሠራት የሚመለከት በመሆኑ ከተማይቱ እንድትሠራ የፈቀደው ብቸኛ አዋጅ በነህምያ አማካይነት ተፈፃሚ የሆነው የአርጤክስስ አዋጅ በመሆኑ ቆጠራውን ከዚያ መጀመር ትክክልና አሳማኝ ነው፡፡ ስሌቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የትንቢት ዘመን አቆጣጠር በኛ ዘመን ወዳለው አቆጣጠር በመቀየር ላይ የተመሠረተ ሲሆን በትክክል 33 ዓ.ም ላይ ይመጣል፡፡ ወሒድ ይህንን አቆጣጠር ባለመረዳቱ ምክንያት በፀሐይ የዘመን አቆጣጠር በማስላት “ከ 62 እና 7 በኋላ መሢሕ ይገደላል” የሚለውን ይዘን ከሄድን ከ 38 በኋላ ይገደላል ተብሎ እንደ እነርሱ እምነት ኢየሱስ የተገደለው በ 33 ድኅረ-ልደት ነው፥ ያ ማለት ኢየሱስ ከተገደለ በኋላ ከ5 ዓመት በኃላ መሢሕ ይገደላል ማለት ትንቢቱ ፉርሽ ይሆናል” ሲል በተወናገረ አጻጻፉ ይሟገታል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች ሊቅ የሆኑት ሐሮልድ ዎልተር ሆኤህነር (Harold Walter Hoehner) ትክክለኛውን አቆጣጠር እንዲህ አስቀምጠዋል፡-
“ስድሳ ዘጠኙን ሱባዔዎች እያንዳንዳቸውን በሰባት ዓመታት እና እያንዳንዱን ዓመት በ360 ቀናት ብናባዛ 173,880 ቀናትን እናገኛለን፡፡ በዚህ መሠረት በ444 ዓ.ዓ. እና በ33 ዓ.ም. መካከል ያለው ልዩነት 476 የፀሐይ ዓመታት ናቸው፡፡ 476ን በ365 ቀናት፣ 5 ሰዓታት፣ 48 ደቂቃዎች፣ 45.975 ሴኮንዶች ብናባዛ [በአንድ ዓመት ውስጥ 365 1/4 ቀናት ናቸው ያሉት] የምናገኘው ውጤት 173,855 ቀናት፣ 6 ሰዓታት፣ 52 ደቂቃዎች፣ 44ሴኮንዶች፣ ወይንም 173,855 ቀናት ይሆናሉ፡፡ ይህ በ444 ዓ.ዓ. እና በ33 ዓ.ም. መካከል መቆጠር የነበረባቸውን 25 ቀናት ብቻ የሚያስቀር ይሆናል፡፡ ሃያ አምስቱን ቀናት በመጋቢት 5 (444 ዓ.ዓ.) ላይ ብንደምር ኒሳን 10/ 33 ዓ.ም. ወደ ሆነው ወደ መጋቢት 30 (33 ዓ.ም.) እንመጣለን፡፡ ይህም ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ነው፡፡”
የምሑሩን ጽሑፍ ዋቢ አድርገው የጻፉት ዕውቁ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነት ጆሽ ማክዱዌል በዚህ ላይ አክለው እንዲህ ይላሉ፡-
በነቢዩ ዳንኤል ትንቢት መሠረት ኢየሩሳሌምን ለመጠገንና ለመሥራት አዋጅ ከወጣበት ጊዜ፤ ማለትም ከኒሳን 1/444 ዓ.ዓ. ጀምሮ መሲሁ ወደ ኢየሩሳሌም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ 483 ዓመታት (69×7) ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ዓመት 360 ቀናት ካሉት የአይሁድ (ትንቢታዊ) ዓመት ጋር እኩል ነው፡፡ (ይህም በአጠቃላይ 173,880 ቀናት ይሆናል፡፡) … ስድሳ ዘጠኙ ሱባኤ ከመደምደሙ በፊትና ሰባኛው ሱባኤ ከመግባቱ በፊት ሁለት ክስተቶች መታየት አለባቸው፡- የመሲሁ ሞት (ዳንኤል 9፡26) እና የኢየሩሳሌምና የቤተመቅደሱ (በሮማዊው) ልዑል (ታይተስ ወይም ቲቶ) በ70 ዓ.ም. ላይ መደምሰስ ነው፡፡ ስሌቶቹ በሙሉና የአዋጁ በ444 ዓ.ዓ. መውጣት ትክክል ከሆነ ክርስቶስ የተሰቀለው ወደ ኢየሩሳሌም በክብር መግባቱን ተከትሎ ሚያዝያ 3/33 ዓ.ም. ነው የሚሆነው፡፡ (Josh McDowell, Evidence That Demands a Verdict, pp. 197-201)
ረበናተ አይሁድ ይህንን ሃቅ ቢቀበሉ የኢየሱስን መሢህነት መቀበል ግዴታ ስለሚሆንባቸው ይህ አብዱል የተጠቀመውን የመሳሰሉ የተለያዩ ደካማ ሙግቶችን በማቅረብ ትንቢቱ አዳኛችን ኢየሱስን የተመለከተ መሆኑን ለመካድ ይሞክራሉ፡፡ ሙስሊም ወገኖችም ትንቢቱ “ክርስቶስ አልተሰቀለም” የሚለውን ከታሪክ ጋር የተኳረፈ መሠረተ ቢስ እምነታቸውን ውድቅ የሚያደርግና የመጽሐፍ ቅዱስን መለኮታዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ በመሆኑ ከእውነት ለመሸሽ የረበናተ አይሁድን ትርጓሜዎች ያቀነቅናሉ፡፡
ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ከሙታን ተነስቷል፡፡ ይህ በቅዱሳን ነቢያት አስቀድሞ የተተነበየና በሐዋርያት ምስክርነት የጸና የታሪክ እውነታ ነው፡፡ በስሙ ያመነ የዘላለምን ሕይወት ያገኛል፡፡ የጥፋትን መንገድ የመረጠ ግን ከላይ ያየነውን በመሳሰሉት ከንቱ ሙግቶች ውስጥ በመደበቅ ዘመኑን ይፈጃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሙስሊም ወገኖቻችንን የልብ ዓይኖች በመክፈት ወደ ክርስቶስ ብርሃን ይመራቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡