የቁርኣን ግጭቶች – አጋሪ ሴቶችን ማግባት ተፈቅዷል ወይንስ አልተፈቀደም?

የቁርኣን ግጭቶች

ለሙስሊሞች ምላሽ የተሰጠ ምላሽ

እጅ እጅ የሚል ምግብ እንዳለ ሁሉ እጅ እጅ የሚል ጽሑፍም አለ፡፡ እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን በመጻፍ ከሚታወቁ ሙስሊም ሰባኪያን መካከል አንዱ የቁርኣን ግጭቶችን ለሚዘረዝረው ጽሑፋችን ተከታታይ “ምላሾችን” በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡ ከአጻጻፉ እንደተረዳነው ግጭቶቹን የዘረዘርንበትን ዓላማ የተገነዘበ አይመስልም፡፡ በመግቢያው ላይ በግልፅ እንዳሰፈርነው ዓላማችን ሙስሊም ወገኖቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዝሩት ትችት በቁርኣን ላይ ተግባራዊ ሲሆን ምን ውጤት እንደሚኖረው ተረድተው አባይ ሚዛን መጠቀም እንዲደቆሙ፤ እንዲሁም ግጭቶች ናቸው የተባሉትን ነጥቦች የገዛ መጽሐፋቸውን ለማስታረቅ የሚጠቀሙበትን ተመሳሳይ አካሄድ ተጠቅሞ ማስታረቅ እንደሚቻል እንዲረዱ ማስገንዘብ ነው፡፡ እነዚህን ግጭቶች ቁርኣንን ላለመቀበል እንደ ምክንያት እንደማንጠቅስና ቁርኣንን እንደ ፈጣሪ ቃል የማንቀበልባቸው ሌሎች መሠረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን አስረድተናል፡፡ ግጭቶቹን ማስታረቅ ለሙስሊም ወገኖቻችን ቀላል እንደማይሆንላቸው ግምታችንን ብናስቀምጥም “መልስ” እንዳላቸው እንደሚያምኑ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መጽሐፍ ቅዱስም በተመሳሳይ መንገድ ሊብራራ መቻሉን እንዲገነዘቡ ስንል በቅንነት ጠይቀናል፡፡ ዳሩ ግን አንዳንድ ሙስሊም ወገኖች ይህንን ነጥብ በትክክል ባለመረዳት ወይንም ለመረዳት ባለመፈለግ ያልተገቡ ቃላትን በመናገር አጉል ፍልሚያ ውስጥ ለመግባት የወሰኑ ይመስላል፡፡ ስለዚህ በቀና መንፈስ የጀመርነውን ውይይት በቀናነት ከመመለስ ይልቅ ወዳልተፈለገ የክርክር አቅጣጫ ለመውሰድ የሚፈልጉ ከሆነ እስከ ምን ድረስ እንደሚያስኬዳቸው አብረን የምንመለከተው ይሆናል፡፡

መልሶቻችንን በተከታታይ የምናስነብብ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ሙስሊሙ ወገናችን ለመጀመርያው ጥያቄያችን የሰጠውን የተራዘመ ምላሽ እንመለከታለን፡፡

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

1. አጋሪ ሴቶችን ማግባት ተፈቅዷል ወይንስ አልተፈቀደም?

አንድን ሰው፦ “ያምሃልን?” ስትሉት እርሱም፦ “አንተም ያምሃል” ካለ መታመሙን አረጋግጧል ማለት ነው። አንድን ሚሽነሪይ፦ “ባይብል ይጋጫል” ስትሉት እርሱም፦ “ቁርኣንም ይጋጫል” ካለ ባይብል መጋጨቱን አረጋግጧል ማለት ነው። ይህ እከክልኝ ልከክልህ ነገር ነው። አንድ ሚሽነሪይ፦ “ቁርኣን ይጋጫል” ቢለን እኛ፦ “እረ በፍጹም” እስቲ ጥቀሰው እንጂ ባይብልም ይጋጫል አንለውም። ምክንያቱም ባይብል የሰው ንግግር ስለገባበት እና ሥረ-መሠረቱ ሳይኖር ቀርቶ ቅጂ ስለሆነ፥ ገልባጮቹ ስህተት እንደሰሩ የባይብል ለዘብተኛም ጽንፈኛም ምሁራን ይስማማሉ። የቁርኣን ግጭት ተብሎ የቀረበው የዛሬ ስድስት ዓመት አንሰሪንግ ኢሥላም ላይ የቀረቡ እንጂ አዲስ ነገር የለውም። መልሱን በተከታታይ ኢንሻላህ በጽሑፍ እና በድምጽ እንሰጣለን፦

ይህ ሰው ገና በመጀመርያው አረፍተ ነገር ግልፅ እንዳደረገው የዚህ ሙግት ቀስቃሾች ሙስሊሞች ናቸው፡፡ እነርሱ ግጭቶች ናቸው በማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላነሷቸው ተቃውሞዎች በሙሉ በቃልም በጽሑፍም መልስ ስንሰጥ ነበር፤ ወደፊትም እንሰጣለን፡፡ ነገር ግን እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት የተጠቀሙበትን የሙግት አካሄድ በገዛ መጽሐፋቸው ላይ ተግባራዊ በማድረግ ውጤቱን እንዲያዩት አደረግን እንጂ እርሱ እንዳለው እከክልኝ ልከክልህ የሚል የህፃናት ጨዋታ ውስጥ አልገባንም፡፡ ይህንን በገጻችን ላይ በግልፅ አስፍረናል፤ ወደፊትም አቋማችን ይህ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ሲተቹና ሲያብጠለጥሉ የኖሩት ሙስሊም ወገኖቻችን የገዛ ሙግታቸውን በቁርኣን ላይ ተግባራዊ ማድረግ ስንጀምር መደንበራቸው፣ መቆጣታቸውና ዘለፋ መጀመራቸው አስገራሚ ነው፡፡ “እኔ ብቻ ልናገርህ፤ አንተ ለምን ትናገረኛለህ፤ እኔ ያንተን መጽሐፍ መተቸት እችላለሁ፤ የኔ ግን አይነኬ ነው” የሚል አጉል ትዕቢት በዚህ በሰለጠነ ዘመን ከኛ የሚጠበቅ አይደለም፤ አያዋጣምም፡፡

ይህ ሙስሊም ወገናችን እንደ ብዙዎቹ የአገራችን ሙስሊም ሰባኪያን ሁሉ በእስልምና ላይ ሒስ የሚያቀርቡትን ሰዎች “ሚሽነሪ” በማለት ይጠራል፡፡ አንድን ቃል ስንጠቀም ትርጉሙንና የማሕበረሰቡን አውድ በማገናዘብ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ትርጉም አልባ የሞኝ ንግግር ይሆናል፡፡ እስልምና በመካከለኛው ምስራቅ በአውሮፓውያን ሚስዮናውያን ከፍተኛ ኪሣራ ስለደረሰበት አረቦች “ሚሽነሪ” የሚል ቃል ሲሰሙ የመቆጣትና የመጸየፍ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ በአገራችን ግን አንድን ሰው “ሚሽነሪ” ብሎ መጥራት በዚህ መንገድ አይታሰብም፤ የወንጌል አገልጋዮችንም “ሚሽነሪ” ብሎ መጥራት እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በሚሽን ትምሕርትቤቶች ስለተማሩ ቃሉን በበጎ መንገድ ይመለከቱታል፡፡ የአገራችን ሙስሊም ሰባኪያን ግን ጥያቄያቸውም ሆነ ምላሻቸው ከውጪ አገራት ሙስሊም ሰባኪያን የተኮረጀ በመሆኑ ለአገሬው ትርጉም አልባ የሆኑ ቃላትን በጽሑፎቻቸው ውስጥ ይደጋግማሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስንም በአማርኛ ጽሑፎቻቸው ውስጥ “ባይብል” ይሉታል፡፡ ከኮረጁ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ!

ከላይ በሚገኘው አንቀጽ ውስጥ የሚገኘውን ሌላውን አሉባልታ እንለፈውና በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ እንግባ፡፡ ይህ ሰው አሳማኝ ምላሽ አቅርቦ ይሆን?

ጥያቄ 1

 አጋሪ ሴቶችን ማግባት ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?

አልተፈቀደም:-

ሱራ 2፡221 “በአላህ አጋሪ የሆኑ ሴቶችን እስኪያምኑ ድረስ አታግቧቸው፡፡

ተፈቅዷል:-

ሱራ 5፡5 “ከነዚያ ከናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም ዘማዊዎችና የሚስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትሆኑ ጥብቆች ሆናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ ልታገቧቸው የተፈቀዱ ናቸው።

መልስ

5፥5 ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለእናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ ያረዱት ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለእነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡

አምላካችን አላህ በእርሱ ላይ ሌሎች ማንነትንና ምንነትን የሚያጋሩ ሙሽሪኮችን እንዳናገባ እና ከእርሱ ስም ውጪ በሌላ ፍጡር ስም ተባርኮ የታረደን እርድ እንዳንበላ ከልክሏል፦

2፥221 አጋሪ የሆኑ ሴቶች እስከሚያምኑ ድረስ አታግቡዋቸው፡፡ ከአጋሪይቱ ምንም ብትደንቃችሁም እንኳ ያመነችው ባሪያ በእርግጥ በላጭ ናት፡፡ ለአጋሪዎቹም እስከሚያምኑ ድረስ አትዳሩላቸው፡፡ ከአጋሪው ጌታ ምንም ቢደንቃችሁ ምእምኑ ባሪያ በላጭ ነው፡፡ እነዚያ አጋሪዎች ወደ እሳት ይጣራሉ፡፡ አላህም በፈቃዱ ወደ ገነትና ወደ ምሕረት ይጠራል፡፡ ሕግጋቱንም ለሰዎች ይገልጻል እነርሱ ሊገሰጹ ይከጀላልና፡፡

6፥121 በእርሱም ላይ የአላህ ስም ካልተጠራበት ነገር አትብሉ፡፡ እርሱም በእርግጥ አመጽ ነው፡፡ ሰይጣናትም ወደ ወዳጆቻቸው በክትን በመብላት ይከራከሯችሁ ዘንድ ያሾከሹካሉ፡፡ ብትታዘዙዋቸውም እናንተ በእርግጥ አጋሪዎች ናችሁ፡፡

ያልተጠየከውን ጉዳይ በማምጣት ነገር ብታንዛዛም ሌላ ግጭት ፈጠርክ እንጂ ለቀደመው ግጭት ምላሽ አልሰጠህም፡፡ የመጀመርያው ጥቅስ የመጽሐፉ ሰዎች (አይሁድና ክርስቲያኖች) ያረዱትን ብሉ ይላል፡፡ ሁለተኛው ጥቅስ ግን ከአላህ ስም ሌላ የተጠራበትን አትብሉ ይላል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች እንስሳን ሲባርኩ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ስለሚሉ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ከአላህ ሌላ ስም የተጠራበትን አትብሉ ያለው ቁርኣን ክርስቲያኖች በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የባረኩትን ብሉ በማለት እርስ በርሱ ተላትሟል፡፡ ለመሆኑ እርስ በርሱ የማይጋጭ የቁርኣን አንቀፅ ይኖር ይሆን?

“ሺርክ” شِرْك የሚለው ቃል “አሽረከ” أَشْرَكَ ማለትም “አጋራ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን “ማጋራት” ማለት ነው፤ የሚያጋራው ሰው ደግሞ “ሙሽሪክ” مُشْرِك ማለትም “አጋሪ” ይባላል፤ እንዲሁ በአላህ ላይ የሚያጋሩት ማንነትና ምንነት “ሸሪክ” شَرِيك ማለትም “ተጋሪ” ይባላሉ፤ ከአህለል ኪታብ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ከነሳራዎች አበይት የሚባሉት ሙሽሪኪን ናቸው፦

የቋንቋ ዕውቀትህን ልታሳየን እየጣርክ ያለህ ይመስላል፡፡ ጥያቄው ግልፅና ቀላል ነው፡፡ ያልተገባ ትንታኔ ውስጥ በመግባት አታወሳስብ፡፡ ለማንኛውም እንቀጥል፡፡

5፤72 እነዚያ «አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ አልመሲህም አለ፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፡፡» እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡

እነዚያ «አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ እነሆ ይህ ንግግራቸው ማጋራት ነውና አላህ በእርሱ ላይ የሚያጋራ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ይህ ጥቅላዊ መልእክት “ሙጅመል” مجمل ወይም “ዓም” عام ይባላል፤ ነገር ግን አላህ ከሙሽሪኪን አህለል ኪታቦችን በተናጥል “ሙፈሰል” مُفَصَّل ወይም “ኻስ” خاص በማድረግ ለያቸው፤ ይህም ሙሽሪኪን እና አህለል ኪታብ በሚሉ ቃላት መካከል “ወ” وَ ማለትም “እና” የሚል መስተጻምር አስቀምጧል፦

98፥1 እነዚያ ከመጽሐፉ ባለቤቶች እና ከአጋሪዎቹም የካዱት ግልጹ አስረጅ እስከ መጣላቸው ድረስ ተወጋጆች አልነበሩም፡፡

 “በእርሱም ላይ የአላህ ስም ካልተጠራበት ነገር አትብሉ” የሚለው “ዓም” عام ሆኖ ከመጣ በኃላ “የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ ያረዱት ለእናንተ የተፈቀደ ነው” “ኻስ” خاص ሆኖ እንደመጣ ኢብኑ ዐባሥ”ረ.ዐ” ተናግሯል፦

መጀመርያ በጠቀስከው ሱራ 5፡72 ላይ የመጽሐፉ ሰዎች “አጋሪዎች” ተብለዋል፡፡ ስለዚህ በቁርኣን መሠረት የመጽሐፉ ሰዎች “አጋሪዎች” ናቸው፡፡ ሁለተኛ ላይ የቁርኣን ጸሐፊ “የመጽሐፉ ሰዎች” እና “አጋሪዎች” በማለት ለሁለት በመክፈል የመጽሐፉ ሰዎች አጋሪዎች አለመሆናቸውን መጠቆሙ ቀደም ሲል የመጽሐፉ ሰዎችን በአጋሪነት ከፈረጀበት ክፍል ጋር የሚጋጭ እንጂ የመጀመርያውን ግጭት ለማስታረቅ የሚረዳ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ጥቅሶች በመጥቀስ ሌላ ግጭት ፈጠርክ እንጂ ግጭቱን ለመቅረፍ የሚያስችል ሐሳብ አላቀረብክም፡፡ በመጀመርያው ጥቅስ መሠረት የመጽሐፉ ሰዎች አጋሪዎች ናቸው፤ በሁለተኛው መሠረት ግን አይደሉም፡፡ የቱ ነው ትክክል?

ሱነን አቢ ዳውድ :መጽሐፍ 16, ሐዲስ 30

ኢብኑ ዐባሥ”ረ.ዐ” እንደተናገረው፦ 6፥118 “የአላህ ስም በእርሱ ላይ ከተወሳበት እንስሳ ብሉ” የሚለው አንቀጽ እና 6፥116 “በእርሱም ላይ የአላህ ስም ካልተጠራበት ነገር አትብሉ” የሚለው አንቀጽ ኢስቲስናዕ በመሆን “የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ ያረዱት ለእናንተ የተፈቀደ ነው” በሚለው ተነሥኻል”

አቡ ዳውድ እንዳንተ ሁሉ ግልፁን ግጭት ለማስታረቅ እየሞከረ ነው፡፡ እርሱ ግን “አንዱ ሌላውን ሽሯል” በሚል መንገድ እንጂ ሁለቱም በአንድ ጊዜ ትክክል ናቸው የሚል ቅድመ ግንዛቤን በመያዘ ለማስታረቅ አልሞከረም፡፡ ምክንያቱም በነዚህ ጥቅሶች መካከል የሚገኘውን ግጭት ተገንዝቧልና፡፡ ለማንኛውም የተጠየከው ስለ ምግብ ሳይሆን ስለ ጋብቻ መሰለኝ፡፡ በጠቀስከው ቦታ ላይ አቡ ዳውድ ስለ ምግብ እንጂ ስለ ጋብቻ እየተናገረ አይደለም፡፡

ይህንን ሪዋያህ ሼኹል አልባኒ ሐሠን ነው ብለውቷል፤ “ወኢሥተስና” وَاسْتَثْنَى የሚለው ይሰመርበት፤ “ኢሥቲስናዕ” اِسْتِثْنَاء‏ ማለት “ግድባዊ ቃል”Exceptional word” ነው፤ ከዚህ ሐዲስ የምረዳው አምላካችን አላህ ከጥቅላዊ መልእክት ተናጥሏዊ መልእክት ይህንን አንቀጽ ማውረዱ ነው፦

5፥5 ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለእናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ ያረዱት ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለእነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡

በአቡ ዳውድ ሐዲስ ውስጥ فَنُسِخَ “ፈኑሲኻ” የምትለዋን ቃል የት አደረካት? በአቡ ዳውድ መሠረት አኽለል ኪታብ ያረዱት ሥጋ የተፈቀደው “አትብሉ” የሚለው “ብሉ” በሚለው ስለተሻረ (ፈኑሲኻ) ነው፡፡ “ሙሽሪኮች ያረዱትን አትብሉ” የሚለው ተሽሮ የአኽለል ኪታብ የተለየ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ “ተሽሯል” የሚለው አባባል ቁርኣን ግጭት እንዳለበት የመናገርያ ተዘዋዋሪ መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ልታድበሰብሰው የሞከርከው፡፡

አላህ ተናገረ የተባለውን እስኪ ደግመን እናንብበው፡- 6፥121 “በእርሱም ላይ የአላህ ስም ካልተጠራበት ነገር አትብሉ፡፡ እርሱም በእርግጥ አመጽ ነው፡፡ ሰይጣናትም ወደ ወዳጆቻቸው በክትን በመብላት ይከራከሯችሁ ዘንድ ያሾከሹካሉ፡፡ ብትታዘዙዋቸውም እናንተ በእርግጥ አጋሪዎች ናችሁ፡፡”

“አትብሉ፡፡ አመጽ ነው፡፡ እንድትበሉ የሚያነሳሳችሁ ሰይጣን ነው፡፡ ከበላችሁ አጋሪዎች ናችሁ፡፡” ካለ በኋላ መልሶ ደግሞ “ግድባዊ (Exceptional) በማድረግ “ብሉ” የሚል አምላክ ምን ዓይነት ነው? አንድ ነገር ወይ አመፅ ነው ወይም አይደለም፤ ወይ የሰይጣን ሐሳብ ነው ወይም የፈጣሪ ነው፤ ወይ አማኒነት ነው ወይም ኢ-አማኒነት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ አመፅም መታዘዝም፣ ከሰይጣንም ከፈጣሪም፣ አለማመንም ማመንም ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ክፉና መልካሙን የሚያምታታ እንደ እስልምና ያለ ሃይማኖት ከቶ የት ይገኝ ይሆን?

አላህ ለሙስሊም ወንድ ከአህለል ኪታብ ሴትን የፈቀደበት ሂክማ ሴት በቀጥታ ሙስሊም ቤት ስለምትገባ ነው፤ በተቃራኒው ሴት ሙስሊም ወንድ ካፊርን ማግባት ያልፈቀደበት ሴቷ ሙስሊም ሙሽሪክ ቤት ስለምትገባ ነው። በማን ስም እንደታረደ ካልታወቀ ደግሞ ቢሥሚላህ ተብሎ መብላት እንደሚቻይ ይህ ሐዲስ ያሳያል፦

ለምን የተጠየከውን በአጭሩ አትመልስም? ለማንኛውም ይህ የሚያሳየው እስልምና ለወንዶች የሰጠውን ያልተገደበ ፈቃድ ነው፡፡ ሙስሊም ወንድ እስከ አራት ማግባት ይችላል፣ የወሲብ ባርያዎች ሊኖሩት ይችላሉ፣ የሌላ ሃይማኖት ሴት ማግባት ይችላል፣ በገነትም ብዙ ሚስቶች ይጠብቁታል፣ ወዘተ.፡፡ ሙስሊም ሴት ግን ማግባት የምትችለው ሙስሊም ወንድ ብቻ ሲሆን የጋብቻ መብቷ የሙስሊሙን ወንድ ሩብ ያህል እንኳ አይሆንም፡፡ ሙስሊም ወንድ የወደዳትን ክርስቲያን ሴት ማግባት ይችላል፤ ሙስሊም ሴት ግን የወደደችውን ክርስቲያን ወንድ ማግባት አትችልም፡፡ ይህ የሚያሳየው የእስልምናን ኢ-ፍትሃዊነትና ምድራዊ ፖለቲካነት ነው፡፡ የውድቀት ውጤት ከሆነው የሰው አእምሮ የመነጨ ሃይማኖት ቢኖር እስልምና ነው፡፡

ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 34, ሐዲስ 11

ዓኢሻህ”ረ.ዐ.” እንደተረከችው፦ ”ሕዝቦች፦ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ስጋ በሕዝቦች ለእኛ ቀርቦልናል፤ የአላህ ስም ይወሳበት አይወሳበት እርግጠኛ አይደለንም” አሉ፤ የአላህ መልእክተኛም አሉ፦ “የአላህን ስም አውሱበት ከዚያ ብሉት”።

የሙሥሊም ስጋ ቤት ካለ አንድ ሙሥሊም ምርጫው መሆን ያለበት የሙሥሊም ስጋ ቤት ነው፤ የሙሥሊም ስጋ ቤት ከሌለ ግን የእነርሱን ስጋ ቤት መጠቀም ሙባህ ነው፦

ወዳጃችን ስለ ምግብ እስላማዊ ፋትዋ ስጠን ብሎ የጠየቀህ የለም፡፡ የተጠየከው ስለ ጋብቻ ነው፡፡ ለምን እርሱን አትመልስም?

ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 21, ሐዲስ 17

አቡ ሰለባህ ሲናገር እንደሰማሁት፦ “ወደ አላህ መልእክተኛ ሄጄ፦ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በአህለል ኪታብ አገር ውስጥ ነው የምንኖረው፤ የእነርሱን ምግብ እንበላለን” አልኩኝ፤ እርሳቸውም፦ “ከእነርሱ ሌላ(የሙሥሊም) ካገኘህ ከእነርሱ አትብላ፤ ከእነርሱ ሌላ ካላገኘህ አጥበህ ከእነርሱ ብላ”። አቡ ዒሣ እንዳለው ይህ ሐዲስ ሐሠን ሰሒሕም ነው።

የተጠየከው ስለ ጋብቻ አንተ ግን የምታወራው ስለ ምግብ፡፡ አቅጣጫ ለማስለወጥ ያደረከው ሙከራ አልተሳካልምህም፡፡ ቀጥተኛ መልስ መስጠት ለምን ጨነቀህ?

ከላይ የተዘረዘረው ግንዛቤ የዐሊሞቻችን አንዱ ረእይ ማለትም እይታ”dimension” ነው።  በሙሽሪክ እና በአህለል ኪታብ “ኢሥቲስናዕ” اِسْتِثْنَاء‏ ማለት “ግድባዊ ቃል”Exceptional word” በመሆን ስለ “ዓም” عام ማለትም “ጥቅላዊ መልእክት” እና ስለ “ኻስ” خاص ማለትም “ተናጥሏዊ መልእክት” አይተን ነበር፤ ይህ አንደኛው የዐሊሞቻችን እይታ”dimension” ነው፤ ስለ አህለል ኪታብ ሁለተኛው የዐሊሞቻችን እይታ” ደግሞ “ሢያቅ” سیاق ማለትም “አውዳዊ መልእክት”context” ነው። ይህም ከሙሳ እና ዒሳ ተከታዮች ብዙዎቹ አመጸኞች ናቸው፤ ነገር ግን አላህ ከእነርሱም ለእነዚያ ላመኑት ምንዳቸውን ሰጣቸው፤ በእነርሱ ላይ ቁርኣን በሚነበብላቸውም ጊዜ «በእርሱ አምነናል፡፡ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፤ እኛ ከእርሱ በፊት ሙስሊሞች ነበርን» ይላሉ፦

28፥52 እነዚያ ከእርሱ በፊት መጽሐፍን የሰጠናቸው እነርሱ በእርሱ ያምናሉ፡፡

28፥53 በእነርሱ ላይ በሚነበብላቸውም ጊዜ «በእርሱ አምነናል፡፡ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ እኛ ከእርሱ በፊት ሙስሊሞች ነበርን» ይላሉ፡፡

እዚህ ጥቅስ ላይ ልብ አድርግ “እኛ ከእርሱ ማለትም ከቁርኣን መውረድ በፊት ሙስሊም ነበርን” ማለታቸው ምክንያታዊ ነው። ሙስሊም” مُسْلِم ትርጉሙ “አቢድ” عَابِدُ ማለትም “አምላኪ” አሊያም “ቃኒት” قَانِتِ ማለትም “ታዛዥ” ማለት ነው። እንደሚታወቀው ከመጽሐፉ ሰዎች ብዙዎቹ አመጸኞች ናቸው፤ አይሁዳውያን አላህ የተቆጣባቸው ሲሆኑ ክርስቲያኖች ደግሞ የተሳቱተት ናቸው፦

ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 47, ሐዲስ 3212

ዐዲይ ኢብኑ ሓቲም እንደተረከው ነብዩም አሉ፦ አይሁዳውያን የተቆጣባቸው ናቸው፤ ክርስቲያኖች የተሳቱተት ናቸው።

“ግድባዊ” ያልከው ምግብን በተመለከተ ነው ወይንስ ጋብቻን? ጋብቻን በተመለከተ ስለመሆኑ ማስረጃ አላቀረብክም፡፡ እስከ አሁን ያወራኸው በሙሉ የሚበላ ሥጋን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ የሀተታህ ነጥብ ግልፅ አይደለም፡፡ “ያው ሥጋ ሥጋ ነውና…” ብለህ የሰው ሥጋና የእንስሳትን ሥጋ ልታጠጋጋ ባልሆነ!  ቁርኣን ሙሽሪኮችን አታግቡ ይላል፤ ክርስቲያኖችና አይሁድን ሙሽሪክ ይላቸዋል፤ በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ክርስቲያኖችና አይሁድን አግቡ ይላል፡፡ ይህንን ግልፅ ጉዳይ በአጭሩ ማብራራት ሲገባህ ነገሮችን በማወሳሰብ አንባቢን ለማምታታት እየሞከርክ ነው፡፡ የተጨበጠ መልስ አልሰጠህም፡፡ እስኪ እንቀጥል፡፡

ነገር ግን ከአይሁዳውያን ጥቂት ያልተቆጣቸው፤ እንዲሁ ከክርስቲያኖች ጥቂት ያልተሳሳቱ ነበሩ፤ እኛም ከመንገዱ እንዳንስት የእነዚያን በእነርሱ ላይ በጎ የዋለላቸውን መንገድ ምራን ብለን እንቀራለን፦

1፥7 የእነዚያን በእነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን፣ በእነርሱ ላይ ”ያልተቆጣህባቸውን እና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ ምራን”፤ በሉ።

ኢማም ቡኻርይ : መጽሐፍ 65, ሐዲስ 4475

አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው የአላህ መልእክተኛ አሉ፦ “ኢማሙ፦ “ያልተቆጣህባቸውን እና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ ምራን” ባለ ጊዜ አሚን በሉ፤

ስለዚህ ከመጽሐፉ ሰዎች በተውሒድ ያሉትን የኢስራኢል ልጆች እና ነሳራዎች ያረዱትን መብላትን እና በሃላል ሴቶቻቸውን ማግባት ተፈቅዷል፦

5፥5 ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለእናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ ያረዱት ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለእነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው፡፡

እኮ መፈቀዱ ግጭት ነው እያልን ነው፡፡ አንዱ ቦታ ላይ ከአላህ ሌላ ስም የተጠራበትን አትብሉ፤ መብላት መጥፎ ነው፤ ከሰይጣን ነው፤ ከሃዲነት ነው ብሎ ሌላ ቦታ ላይ ክርስቲያኖች ያረዱትን ብሉ ይላል፡፡ አንዱ ቦታ ላይ አጋሪዎችን አታግቡ፤ ክርስቲያኖች አጋሪዎች ናቸው ብሎ ሌላ ቦታ ላይ አግቡ፤ ተፈቅዷል ይላል፡፡ ያንተ ምላሽ “አዎ ተፈቅዷል” ብሎ ሃቁን ማመን እንጂ “አልተፈቀደም” ከሚለው ጋር የተፈጠረውን ግጭት የሚያስታርቅ አይደለም፡፡ እስከ አሁን ነገርህ ሁሉ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንደሚለው አባባል ነው፡፡ ስለ ጋብቻ ተጠይቀህ ስለሐላል ሥጋ በማውራት ጊዜያችንን በከንቱ አባክነሃል፡፡ እስኪ የመቋጫ ሐሳብህ ተስፋ ያለው እንደሆን እንይ፡፡

“መጽሐፍን የተሰጡት” በሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ “ሚን” مِنَ ማለትም “ከ” የሚል መስተዋድድ አለ፤ ያ የሚያሳየው ከአህለል ኪታብ መካከል ያሉትን ያላሻረኩ፣ የፍጡር ስም ሳይሆን የአላህን ስም ብቻ የሚጠሩ እና ከዝሙት ብልቶቻቸውን ጥብቆች የሆኑ ሴቶች ማግባት ሙባህ ነው። ይህ ሁለተኛው እይታ ነው። ሁለቱም እይታዎች ቁርኣናዊ ናቸው፤ መርጦ መቀበል የግል ምርጫ ነው።

“ከ” ወይም በአረብኛ “ሚን” የሚለው ከክርስቲያኖችና ከአይሁድ ሴቶች መካከል ከእስልምና ጋር የሚስማማ እምነት የሚከተሉትን አግቡ የሚል ሐተታ ፈፅሞ የለውም፡፡ ከየት አመጣኸው? በቦታው ላይ የሌለ ፈጠራ እያስነበብከን ነው፡፡ “ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች” ሲል ክርስቲያንና አይሁድ ከሆኑት ሴቶች ለማለት እንጂ አይሁድ ወይንም ክርስቲያን ሆነው የተለየ እምነት ያላቸውን የሚል ነገር አልተጻፈም፡፡

“ሁለቱም ዕይታዎች ቁርአናዊ ናቸው” ስትል ምን ለማለት ፈልገህ ነው? እንዲህ ባለ ከባድ ጉዳይ ላይ ሁለት ዕይታ ለምን ይኖራል? የመጀመርያው ዕይታ ሁሉንም ክርስቲያን ሴቶች ማግባት ይቻላል የሚል ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ አይ ያላሻረኩትን ብቻ ነው ማግባት የሚቻለው የሚል ነው፡፡ ሁለቱም በአንድ ጊዜ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ጉዳዩን ለግለሰብ ምርጫ ማቅረብህ በነፍሳቸው ላይ የሚያመጣውን ዘላለማዊ ጥፋት ልብ አላልክም፡፡ ለምሳሌ ያህል ትክክለኛው የአላህ ሐሳብ ከአህለል ኪታብ ሴቶች መካከል ያላሻረኩትን ብቻ መርጦ ማግባት ቢሆንና አንድ ሙስሊም ግን የመጀመርያውን አመለካከት ይዞ የምታሻርክ ሴት ቢያገባ የአላህን ትዕዛዝ ጥሷል ማለት ነው፡፡ የአላህን ትዕዛዝ የጣሰ ሰው ደግሞ በነፍሱ እንደሚከፍል ታስተምራላችሁ፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ የሚጋጩ ዕይታዎች መካከል አንዱን መያዝ እንዲህ ነፍስን ለጥፋት የሚዳርግ ከሆነ ለግለሰብ ምርጫ የሚቀርብ መሆን የለበትም፡፡ የፈጣሪ መጽሐፍ የተባለው ቁርኣን በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ መሆን ነበረበት፡፡

እንዲህ እርስ በርሱ የማይጣጣም ዕይታ ሌላ ግጭት እንጂ ግጭት መፍቻ እንዴት ሊሆን ይችላል? ግጭት በግጭት ሊፈታ ይችላል እንዴ? ጥያቄያችንን እናስታውስ! ቁርኣን ክርስቲያንና አይሁድን በአጋሪነት ይፈርጃል፤ አጋሪ ሴቶችንም አታግቡ ይላል፤ ሌላ ቦታ ላይ ግን ቀደም ሲል አጋሪ ያላቸውን ክርስቲያንና አይሁድ ሴቶችን አግቡ ይላል፡፡ ጥያቄያችን ይህንን ግጭት ፍቱልን የሚል ነበር፡፡ አንተ ግን “አግቧቸው የተባለው ልዩ በሆነ መንገድ ከአጋሪዎች እነርሱን በመነጠል” እንደሆነ ከነገርከን በኋላ “ከመካከላቸው አጋሪ ያልሆኑትን ብቻ ነው እንድናገባ የተፈቀደው” የሚል ዕይታ እንዳለም ነገርከን፡፡ ሁለቱም ዕይታዎች ደግሞ ቁርአናዊ መሆናቸውን አስገነዘብከን፡፡ ስለዚህ ቁርኣን በአንድ ወገን ሙሽሪክ የሆኑ የአህለል ኪታብ ሴቶችን በሙሉ ማግባት ይፈቅዳል በሌላ ወገን ደግሞ ከመካከላቸው ያላሻረኩትን ብቻ ነው ማግባት የሚፈቅደው፡፡ እናም ውድ ወገናችን ራስህ የፈጠርከውን አዲሱን ግጭት መፍታት ሊኖርብህ ነው፡፡ ሙሽሪክ የሆኑ የአህለል ኪታብ ሴቶችን ማግባት ተፈቅዷል ወይንስ አልተፈቀደም? ያንተ ምላሽ እርስ በርሱ ይጋጫል፡፡ የቱን እንቀበል? በዕውቀት ሳይሆን በስሜት መጻፍ ውጤቱ ይህ ነው፡፡

 

 

የቁርኣን ግጭቶች