የቁርኣን ግጭቶች – የአላህ ቃል ይለወጣል ወይስ አይለወጥም?

8. የአላህ ቃል ይለወጣል ወይስ አይለወጥም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ይለወጣል፡–

ሱራ 2፡106 “ከአንቀፅ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ቢጤዋን እናመጣለን፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መሆኑን አታውቅምን?”

አይለወጥም፡-

ሱራ 18፡27 “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም፡፡”

መልስ

የባይብል ሃያሲ በሃያሲያነ-ፅሑፍ”textual criticism” ላይ ባይብልን ሂስ ሲሰጡ ውጤቱ አይን ያስፈጠጠ ጥርስ ያስገጠጠ ግጭትና ፍጭት መሆኑ ብዙዎች ወደ ኢስላም እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል፤ የሚሽነሪ ነውጠኞች ሰዎች ከክርስትና አካውንት ወደ ኢስላም አካውንት ሲጎፉ ሲያዩ በእልህ መሳ ለመሳ ቁርኣን ላይ ግጭት ለማግኘት ያልቆፈረሩት ጉድጓድ ያልፈነቀለሉት ድንጋይ የለም፤ ይህ አልበቃ ሲላቸው የግለሰቦችን ስም ማንጓጠጥ ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፤ በዚህ መሃል ግን ቁርኣን ላይ የሚያነሱት ሂስ ተፋልሶ”Fallacy” ቢሆንም ለጊዜው እንደ እኔ አይነቱ ላይ ብዥታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፤ ይህንን ስሑት ሙግት ገለባ መሆኑን በስሙር ሙግት ማሳየት የሁላችንም ተቀዳሚ አላማ ሊሆን ይገባል፤ ለዚህም የተንሸዋረረ እይታ ምንጨታዊ ሥነ-አመክንዮ”deductive logic” በመጠቀም ሙግቴን እጀምራለው፤ አላህ ቃሉን ይለውጣል ወይስ አይለውጥም የሚለው ሂስ ከመነሻው በቋንቋ ሙግት ድባቅ ይገባል፤ ይህንን ለመረዳት ሁለት የሙግት ነጥቦች”premises” ተጠቅሜአለው፦

የቴክስቹዋል ክሪቲሲዝም ጥናት ዓላማ የእጅ ጽሑፎች ምን ያህል ለመጀመርያዎቹ ጽሑፎች የቀረቡ እንደሆኑ በማጥናት የግልበጣ ግድፈቶችንና ጣልቃ ገብ ጽሑፎችን መለየት እንጂ “ተቃርኖ” “ግጭት” የሚባሉት ሙግቶች መነሻም ግብም አይደሉም፡፡ ስለ ቴክስቹዋል ክሪቲሲዝም ያለህ ዕውቀት ቁንፅል ነው፡፡ ቁርኣንን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ከግልበጣ ግድፈቶችና ከመሳሰሉት ሰብዓዊ ችግሮች የጸዳ አይደለም፡፡ መጻሕፍት በእጅ ሲገለበጡ ምንም ዓይነት የፊደልና የቃል ግድፈት ሊኖር አይችልም ብሎ ማሰብ በራሱ ቂልነት ነው፡፡ በማተምያ ማሽን ዘመን የታተመው የአማርኛ ቁርኣን እንኳ መጀመርያ ለገበያ ሲቀርብ ብዙ የፊደል ግድፈቶችና የተዘለሉ ገፆች ስለነበሩት የማስተካከያ አባሪ አብሮ ማሳተም አስፈላጊ ሆኖ ነበር፡፡ ቋንቋው አረብኛ ሲሆን አንዳች ምትሓታዊ ኃይል ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ “የሰነዓ የእጅ ጽሑፎች” የተሰኙትን የቁርኣን ጽሑፎች ስንመለከት ምሑራን ብዙ የግልበጣ ስህተቶችና እርማቶችን አግኝተውባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች የሚጠበቁ መሆናቸውን አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ የሚስተው አይደለም፡፡ የቁርኣን የእጅ ጽሑፎች ብዙ የግልበጣ ስህተቶችና ጣልቃ ገብ ጽሑፎች ያሉባቸው መሆኑን እንዲሁም በሙሐመድ ዘመን የነበረው ቁርኣን ብዙ የተቀነሱና የተጨመሩ ነገሮች እንዳሉበት እስላማዊ የታሪክ ድርሳናትንም ሆነ የእጅ ጽሑፎችን አጣቅሶ በማስረጃ አስደግፎ መናገር ይቻላል፡፡ በዓለም ላይም ብዙ ልዩነቶች ያሏቸው ቁርአኖች መኖራቸውንና አሁን ሙስሊሞች የሚጓደዱበት የሐፍስ የቁርኣን ቅጂ በ1924 ዓ.ም. በግብፅ የተዘጋጀ መሆኑ እንዲሁም ከእርሱ ቀደም የነበሩትን ብዙ የእጅ ጽሑፎችን ያላገናዘበ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ “ቁርኣን አንድ ነው፣ አንዲት ነጥብ እንኳ አልተጨመረበትም አልተቀነሰም” የሚለው ያልተማሩ ሙስሊሞች ቧልት ጊዜው አልፎበታል፡፡

ነጥብ አንድ

“ተብዲል”

“ተብዲል” تَبْدِيل ማለት ደግሞ “ማስቀየር” ነው፤ ተብዲል የንግግርን ሃሳብ፣ የውሳኔ ቃል እና የተስፋ ቃል ማስቀየርን ያመለክታል፤ አላህ የተናገረውን የውሳኔ ቃል አሊያም የትንቢትና የተስፋ ቃል ማንም ማስቆም አሊያም ማስቀረት እንደማይችል አላህ በቃሉ ይናገራል፦

6:115 “”የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን “ተፈጸመች”፡፡ ለቃላቱ #ለዋጭ የለም” لَا مُبَدِّلَ፡፡ እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡

10:64 ለእነሱ በቅርቢቱ ሕይወትም በመጨረሻይቱም “ብስራት” አላቸው፤ “”የአላህ ቃላት “#መለወጥ የላትም*لَا تَبْدِيلَ ፤ ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡

6:34 ከበፊትህም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡ “”የአላህንም ንግግሮች *#ለዋጭ የለም*وَلَا مُبَدِّ፡፡

18:27 ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ “ለቃላቶቹ #ለዋጭ የላቸውም” لَا مُبَدِّلَ፤

በተለይ “ተፈጸመች” እና “ብስራት” የሚሉት ቃላት የሚበሰርን እና የሚፈጸም ቃልን እንጂ በቀድሞ መጽሐፍት የተናገረውን መልእክት አያመለክትም፣ ኢማም ጦበራኒ ለሱረቱል አንአም 6፡115 የሰጡት ማብራሪያ እንዲህ ይላል፦

‹‹ለቃላቱ ለዋጭ የለም የሚለው ቃል አላህ በእርሱ መጽሀፍ ውስጥ ጉዳዩ ይከሰታል ብሎ ለመተግበሩ የሰጠው ቃል በጊዜው ከመተግበር ማንም አያግደውም እሱ እነደተናገረው ይፈጸማል ማለት ነው››

ኢማም ቁርጡቢም ተመሳሳይ ሀሳብ ያዘለ ማብራሪያቸውን እንዲህ ሲሉ ይገልጻል፦

‹‹አልራሚኒ እንዳስተላለፉት አቡ ቀታዳ እንዲህ ይላሉ፡- ለኣላህ ፍርድ ምንም ለዋጭ የለውም የመጽሀፉ ሰዎች እንዳደረጉት ቃላቱን አንድ ሰው እንኳ ቢቀይረው የአላህ እውነተኛ ቃል ግን ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም የተለወጠው ቃል የሚፈጸመውን ቃል መለወጥ አይችልም፡፡››

አል-ቁርጡቢ (በትክክል ጠቅሰኸው ከሆነ) “ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም” የሚለውን ቃል ከእስላማዊ የብረዛ አስተምሕሮ ጋር ለማስታረቅ እየጣረ ነው፡፡ ነገር ግን ሱራ 10፡64 ላይ “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” የሚለውን ቃል ከስሌቱ ውጪ ያደረገው ይመስላል፡፡ ይህ ቃል የአላህ ቃል በባሕርዩ የማይለወጥ መኾኑን የሚነግረን ሲሆን ቁርኣን “የአላህ ቃል አይለወጥም” ሲል ማንኛውንም የአላህ ቃል እንጂ ነጥሎ አንዲትን ገፅታ፣ ማለትም የውሳኔና የተስፋ ቃሉ ብቻ ነው የሚል አቋም የለውም፡፡

አልቁርጡቢ በዋቢነት በጠቀሰው በአቡ ቀታዳ መሠረት በጽሑፍ ያለው የአላህ ቃል በሰዎች መለወጥ እንደሚችል ከተነገረን ይህ ሐሳብ ከሌሎች ሙስሊሞች አቋም ጋር ይጣረሳልና የቱን እንቀበል? ለምሳሌ ያህል ኢብን ከሢር እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“… አል ቡኻሪ እንደዘገበው ኢብን አባስ እንዲህ ብሏል፤ ‹የዚህ አያ ትርጉም የሚከተለው ነው፡- … ከአላህ ፍጥረታት መካከል ማንም የአላህን ቃላት ከመጻሕፍቱ ውስጥ ማስወገድ አይችልም፡፡ ግልፅ ትርጉማቸውን ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡› ወሃብ ኢብን ሙነቢህ እንዲህ አለ “ተውራት እና ኢንጂል ልክ አላህ በገለጣቸው ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ከውስጣቸው አንድም ፊደል አልተወገደም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ተሞርኩዘው በመጨመርና ውሸት በሆነ አተረጓጎም ሌሎችን ያሳስታሉ፡፡” … “የአላህ መጻሕፍት ግን እስከ አሁን ተጠብቀው ይገኛሉ፤ ሊለወጡም አይችሉም፡፡” (Tafsir Ibn Kathir – Abridged, Volume 2, Parts 3, 4 & 5, Surat Al-Baqarah, Verse 253, to Surat An-Nisa, verse 147, First Edition: 2000, p. 196)

ታድያ ከሁለቱ የቱ ነው ትክክለኛው አቋም?

ግራም ነፈሰ ቀኝ ሲጀመር “መለወጥ” የሚለው ቃል ተመሳሳይ ቃል ቢኖረው እንኳን ተመሳሳይ ሀሳብና ትርጉም አለው ማለት አይደለም፤ የአንድን ቃል አማራጭ ትርጒም የሚወስነው ቃሉ የሚገኝበት ዐረፍተ ነገር ወይም ዐውድ እንደ ሆነ ቅቡል ነው፤ ቃሉ ሳይሆን ቃሉ የወከለው ሐሳብ መታየት ያለበት።

ሲቀጥል “መለወጥ” የሚለው ንግግርን ማስቀየር “ተብዲል” መሆኑን እንጂ “ነሥኽ” እንዳልሆነ አይተናል።

“መለወጥ” የሚለው ቃል ብዙ ገፅታዎች ያሉት ጥቅል ቃል ሲሆን ሽረት ወይም “ነስኽ” ከመለወጥ ገፅታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ “መለወጥ ይላል እንጂ ሽረት አይልም” ብሎ ማለት የመለወጥን ትርጉም ያለማወቅ ነው፡፡

ሲሰልስ ” መለወጥ” “ነሥኽ” ነው ተብሎ ቢባል እንኳን አላህ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ቃሉን በሌላ ቃል መለወጥ ይችላል፤ ፍጡሮቹ ግን ወደ ነብያችን የወረደውን ቃል መለወጥ አይችሉም፤ ምክንያቱም “ሙበዲል” مُبَدِّل “ለዋጭ” የሚለው ቃል ከአላህ ውጪ የሆኑትን ማንነቶች እና ምንነቶች የሚያሳይ ስለሆነ፤ እንደዛ ከሆነ የሚቀጥለውን የሙግት ነጥብ እንመልከት፦

ቁርኣን የአላህ ቃል ለዋጭ እንደሌለው ብቻ ሳይሆን እንደማይለወጥም ጭምር ይናገራል፡፡ ለዋጭ የለውም ሲባል ከአላህ ውጪ ያሉትን ብቻ ያመለክታል የሚለውን ብንቀበል እንኳ “አይለወጥም” ሲል ትኩረቱ በለዋጩ ማንነት ላይ ሳይሆን በቃሉ ባሕርይ ላይ በመሆኑ አላህ ቃሉን መለዋወጡ ግጭትን ይፈጥራል፡፡ ቃሉ አይለወጥም ተብሎ የቃሉ ባሕርይ ከተነገረን በኋላ አላህ ለውጦት ቢገኝ “አይለወጥም” ተብሎ የተነገረን ባሕርዩ ሐሰት ነው ማለት ነው፡፡ ቃሉን መለወጥ አለመለወጥ ደግሞ ፈጣሪ በቃሉ ላይ ካለው አቋምና ከቃሉ ባሕርይ ጋር የሚያያዝ እንጂ የሁሉን ቻይነቱ ጉዳይ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በባሕርዩ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን እንደተፈፀመው ይፈፀማል እንጂ አይሻርም አይለወጥም፡፡ የሚሻርና የሚለወጥ የፍጡር ቃል እንጂ የፈጣሪ ቃል አይደለም፡፡

ነጥብ ሁለት

“ነሥኽ”

“ነሥኽ” نسخ ማለት “ሽረት”abrogation” ማለት ሲሆን ይህም ሽረት በሁለት እሳቤዎች አቅፏል፤ እነርሱም፦

1ኛ. “ናሢኽ” الناسخ ማለትም “ሻሪ”Abrogator” ሲሆን ይህ አንቀፅ ሻሪ አንቀፅ ይባላል።

2ኛ. “መንሡኽ” المنسوخ “ተሻሪ”Abrogated” ነው፤ ይህ አንቀጽ ተሻሪ አንቀፅ ይባላል።

“ሽረት” ህጉን ታሳቢና ዋቢ ያረደገ ሲሆን የማህበረሰቡትን ዕድገትና የአስተሳሰብ ደረጃ፣ የጊዜውን ቅድመ-ተከተል እና ዘመነ-መግቦት”dispensation” ያማከለ ነው፣ ይህም “ተከታታይ ግህደተ-መለኮት”progressive revelation” እሴትና ግብአት ነው፦

2:106 ከአንቀጽ ብንለውጥ نَنْسَخْ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ብጤዋን እናመጣለን፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አታውቅምን?፡፡

16:101 በአንቀጽም ስፍራ አንቀጽን በለውጥን ጊዜ፣ አላህም የሚያወርደውን ነገር አዋቂ ነው፤ አንተ ቀጣፊ እንጂ ሌላ አይደለህም ይላሉ፤ በእውነቱ አብዛኞቻቸው አያውቁም።

አላህ የቃሉን ባሕርይ ሲነግረን እንደማይለወጥ አስቀድሞ ስላስታወቀን በሽረትም ሆነ በማንኛውም መንገድ ቢለወጥ አለመለወጥ የቃሉ ባሕርይ እንደሆነ የነገረን የቁርኣን ጥቅስ ሐሰት ሊሆን ነው፡፡ “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” (10፡64)፡፡ ስለዚህ የምታወራው ነገር ምንም አያሳምንም፡፡ እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያረጋግጡት ሙሐመድ “ወረዱልኝ” ያላቸውን መገለጦች ይረሳ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በነቢይነቱ ላይ ጥርጣሬን እንዳያጭር መገለጦቹን የሚያስረሳው አላህ ራሱ መሆኑን ተናገረ፡፡ አላህ ያወረደውን መገለጥ በማስረሳት አዲስ ሥራ ከሚፈጥር መጀመርያውኑ እነዚህን መገለጦች ባያወርድ አይሻልም ነበርን?

አላህ የሕጉን አንቀጽ በሌላ የህግ አንቀጽ የመሻሩ ሂደት በሁለት ይከፈላል፤ እርሱም፦

1ኛ. “ሁክሙ” ማለትም “ህጉ” ተነሥኾ ነገር ግን “መትኑ” ማለትም “የህጉ ጥሬ ቃል” የማይነሠኸው ሲሆን የተነሠኸው እና የነሠኸው አያህ ቁርኣን ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል።

2ኛ. ሁክሙ ተነሥኾ በተጨማሪም መትኑ ተነሥኾ፤ የነሠኸው አያህ ቁርኣን ውስጥ ሰፍሮ፤ ነገር ግን የተነሠኸው አያህ ሁክሙና መትኑ የማይገኝ ሲሆን የተነሠኸው አያህ በማስረሳት በሌላ አያህ መተካት ነው፦

87:6-7 ቁርኣንን በእርግጥ እናስነብብሃለን፤ አትረሳምም፤ አላህ ከሻዉ በስተቀር።

2:106 ከአንቀጽ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከእርሷ የሚበልጥን ወይም ብጤዋን እናመጣለን፤

ስለዚህ ሁለት የተለያዩ ነጥቦችን አምጥቶ ይጋጫሉ ማለት የሥነ-አመክንዮ ተፋልሶ ነው።

ሌሎች የረሳኻቸው (ምናልባትም ልትነግረን ያልፈለካቸው) የሽረት ዓይነቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው የሽረት ዓይነት የተሻረው አንቀፅ ቁርኣን ውስጥ ሆኖ የሻረው አንቀፅ ግን በሐዲስ ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዘማውያንን በድንጋይ ወግሮ ስለመግደል የተነገረው አንቀፅ በቁርኣን ውስጥ ያልተካተተ ቢሆንም ጉዳዩን በተመለከተ የመጨረሻው የአላህ ትዕዛዝ ነው (Sahih Muslim, 17:4194)፡፡ የአይሻ ፊየል (ሰላም በሷ ላይ ይሁንና) ባትበላው ኖሮ በቁርኣን ውስጥ በተካተተ ነበር፡፡ ይህ ሕግ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙትን በግርፋት መቅጣትና የዕድሜ ልክ እስራትን ሽሯል፤ እናም የተሻሩት ጥቅሶች በቁርኣን ውስጥ ተካትተው ሻሪው ጥቅስ ከቁርኣን ውጪ መገኘቱ አስገራሚ ነው (ሱራ 24:2)፡፡

ሌላው ደግሞ የሚሽሩም የሚሻሩም ሳይሆኑ በሰዎች በመረሳታቸው ምክንያት ብቻ በቁርኣን ውስጥ ያልተካተቱ አናቅፅ ናቸው፡፡ ለዚህም በማሳያነት ተከታዩን ሐዲስ እንጠቅሳለን፡-

“አቡ ሀርብ ቢን አቡ አል-አስዋድ አባታቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት አቡ ሙሳ አል-ሸዐሪ የበስራ ቁርኣን አነብናቢዎችን አስጠሯቸው፡፡ ቁጥራቸው ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑቱ መጡ፡፡ ቁርኣንን አነበነቡት፤ እርሳቸውም እንዲህ አሏቸው ‹‹እናንተ አነብናቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን ከበስራ ነዋሪዎች ሁሉ ምርጦች ናችሁ፡፡ ማነብነባችሁን ቀጥሉ፡፡ (ነገር ግን) ለረጅም ጊዜ ማነብነባችሁ ከናንተ በፊት የነበሩትን ሰዎች ልቦች እንዳደነደነ ልቦቻችሁን እንዳያደነድን ተጠንቀቁ፡፡ በርዝመትና በጥንካሬ ከሱራ በረዓት ጋር የሚነፃፀር ሱራ እናነበንብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹የአደም ልጅ በኃብት የተሞሉ ሁለት ሸለቆዎች ቢኖሩት ሦስተኛውን ይመኛል፡፡ ከአፈር ውጪ የአደምን ልጅ ሆድ የሚሞላ ምንም ነገር የለም፡፡›› ከሱረት ሙሰቢሃት መካከል ከአንዱ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ሱራም እናነበንብ ነበር ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የማትፈፅሙትን ነገር ስለምን ትናገራላችሁ? እርሱም በናንተ ላይ ምስክር እንዲሆንባችሁ በአንገቶቻችሁ ላይ ተጽፏል፤ በዕለተ ትንሣኤም ከእርሱ ትጠየቃላችሁ፡፡››” Sahih Muslim 5:2286; Jalal al Din `Abdul Rahman b. abi Bakr al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; Halabi, Cairo, 1935/1354, part 2, p. 25

በዚህ ሐዲስ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለቱ “መገለጦች” በዛሬው ቁርኣን ውስጥ አይገኙም፡፡ ሱራ በረዓት (አት-ተውባ) 129 አንቀፆች ያሉት ሲሆን ይህን ያህል ርዝመት ያለው አንድ ሙሉ ምዕራፍና ሌላ ርዝመቱ ምን ያህል እንደሆነ ያልተገለፀ፤ ነገርግን ‹ሙሰቢሃት› በመባል ከሚታወቁት በቁርኣን ውስጥ ከሚገኙ ሱራዎች ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሱራ መረሳቱ ተነግሯል፡፡

እንዲህ ያሉ ቁርኣን በቀድሞ ይዘቱ አለመገኘቱን የሚያመለክቱ ትረካዎች የአላህ ቃል እንደማይለወጥ ከሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች ጋር ይጣረሳሉ፤ ስለዚህ ጉዳዩ አንተ አቅልለህ ለማሳየት የሞከርከውን ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ግጭቱንም ማስታረቅ አልቻልክም፡፡

 

የቁርኣን ግጭቶች