የቁርኣን ግጭቶች – በገሃነም ውስጥ የተጣሉ ሰዎች ምግባቸው አንድ ብቻ ነው ወይንስ ብዙ?

9. በገሃነም ውስጥ የተጣሉ ሰዎች ምግባቸው አንድ ብቻ ነው ወይንስ ብዙ?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ዶሪዕ የሚባል ዛፍ ብቻ፡–

ሱራ 86፡6 “ለነሱ ዶሪዕ ከሚባል (እሾሃም) ዛፍ እንጂ ሌላ ምግብ የላቸውም፡፡”

የዘቁም ዛፍ የሚባል፡–

ሱራ 37፡62-68 “በመስተንግዶ ይህ ይበልጣልን ወይስ የዘቁም ዛፍ?… እርሷ በገሃነም አዘቅት ውስጥ የምትወጣ ዛፍ ናት፡፡ እንቡጧ ልክ የሰይጣናት ራሶች ይመስላል፡፡ እነርሱም ከርሷ በይዎች ናቸው…”

የቁስል እጣቢ ብቻ፡–

ሱራ 69፡36 “ምግብም ከእሳት ሰዎች ቁስል እጣቢ (እዥ) በስተቀር የለውም”

መልስ

ወሒድ ሾርባ እንጂ ሌላ አይበላም ተብሎ ፈይሰል ደግሞ ስጋ እንጂ ሌላ አይበላም ቢባል ይህ ግጭት አይባልም። ምክንያቱም ፈይሰል የሚኖርበት ቤትና ወሒድ የሚኖርበት ቤት ይለያያልና፣ ከመነሻው የዐውዱ ፍሰት የሚናገረው ስለተለያዩ በቅጣት ላይ ስላሉ ሰዎች ነው። እስቲ መጀመሪያ ጀሃነም የተለያየ ደረጃና መኖርያ እንዳለው ከቁርኣን እንረዳ፦

አብረን እንደምንመለከተው ጥቅሶቹ የገሃነም ነዋሪዎችን በአጠቃላይ የሚያሳዩ እንጂ ከገሃነም ነዋሪዎች መካከል ወሒድና ፈይሰል ብለው ለያይተው አያስቀምጡም፡፡ ስለዚህ ያንተ ምሳሌ ፊየል ወዲህ ቁርኣን ወዲያ ዓይነት ነው፡፡

15፤44 «ለእርሷ ሰባት ደጃፎች አሏት፡፡ ለየደጀፉም ሁሉ ከእነሱ የተከፈለ ፋንታ አለ”፡፡

16፥29 «የገሀነምንም ደጃፎች በውስጧ ዘውታሪዎች ስትኾኑ ግቡ» ይባላሉ፡፡ የኩሩዎችም መኖሪያ ገሀነም በእርግጥ ከፋች!

ጀሃነም ደጃፎች እንዳሏት ለየደጀፉም ሁሉ ከእነሱ የተከፈለ ፋንታ እና የተለያየ ደረጃዎች እንዳለ ከተመለከትን አንቀጹ ስለ እነማን እንደሚያወራ በአጽንኦት መመልከት ይቻላል። ፊቶች ተዋራጆች የሆኑ “ካፊሪን” كَافِرِين ማለትም “ከሃድያን” ዶሪዕ ከሚባል እሾሃም ዛፍ እንጅ ሌላ ምግብ የላቸውም፦

 80፥40 “ፊቶችም በዚያ ቀን በላያቸው ላይ ትቢያ አለባቸው”፤

80፥42 እነዚያ እነርሱ ከሓዲዎቹ አመጸኞቹ ናቸው”፡፡

88፥2 “ፊቶች በዚያ ቀን ተዋራጆች ናቸው”፡፡

88፥6 “ለእነርሱ ዶሪዕ ከሚባል እሾሃም ዛፍ እንጅ ሌላ ምግብ የላቸውም”፡፡

“እነርሱ ከሓዲዎቹ ናቸው” ናቸው የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት።

ሱራ 80፡42ን ከሌላ ቦታ አምጥተህ በመደንቀር ከሱራ 88፡6 ጋር ለማገናኘት ሞክረሃል፡፡ በሱራ 80 እና 88 መካከል 8 ምዕራፎች ይገኛሉ፡፡ እንዴት አገናኘኻቸው? በምንም አይገናኙም፡፡ የሱራ 88፡6 አውድ እዚያው ይገኛል፡፡ አጠቃላይ ምዕራፉን ስንመለከት በዕለተ ትንሣኤ ሰዎች ለሁለት እንደሚከፈሉ ይናገራል፤ ከፊሎቹ ወደ ገሃነም ከፊሎቹ ወደ ገነት ይሄዳሉ፡፡ ከነዚህ ሁለት ቡድኖች ውጪ የተጠቀሰ ክፍልፋይ ቡድን በቦታው ላይ የለም፡፡ ወደ ገሃነም የሚሄዱት የፈላ ውኀ እንደሚጠጡና ዶሪዕ የተሰኘ ምግብ ብቻ እንደሚበሉ ይናገራል፡፡ ዶሪዕ ወደ ገሃነም የወረዱ ሰዎች ሁሉ ምግብ ነው፡፡ ስለዚህ ገሃነም የገቡ ሰዎች ከዶሪዕ ውጪ ሌላ ምግብ ከሌላቸው ዘቁምና የቁስል ዕዥ ይበላሉ የሚሉት ጥቅሶች ሐሰት ይሆናሉ፡፡

ከካድያን በተቃራኒው አማንያን ሆነው መጥፎ ሥራ ሰርተው ተውበት ካላደረጉ ይቀጣሉ። እነዚህ “ኻጢዑን” خَاطِئُون ማለትም “ኀጢኣተኞች” ይባላሉ፤ እነርሱ ከእሳት ሰዎች በተለየ መልኩ ምግባቸው እዥ በስተቀር የለውም፦

69፥36 “ምግብም ከእሳት ሰዎች እዥ በስተቀር የለውም”፡፡ 

69፥37 “ኀጢኣተኞች እንጅ ሌላ አይበላውም፤ ይባላል”፡፡

ሱራ 88 የሰው ልጆችን “ወደ ገሃነም የሚወርዱና ወደ ገነት የሚገቡ” በማለት ለሁለት ከከፈለ በኋላ 6ው ቁጥር ላይ ወደ ገሃነም የሚገቡት ምግባቸው የዶሪዕ ዛፍ ብቻ እንደሆነ ስለሚናገር “(የኃጢአተኛ ሰው) ምግብም ከእሳት ሰዎች እዥ በስተቀር የለውም” መባሉ አሁንም ግጭት ነው፡፡

ሌላው አንተ እንዳልከው “ኀጢአተኛ” ማለት “መጥፎ ሥራ ሠርቶ ተውበት ያላደረገ አማኝ” ከሆነ እዚያው ምዕራፍ 69፡33 ላይ “እርሱ ታላቅ በሆነው አላህ አያምንም ነበርና” ለምን ተባለ? “ኀጢአተኛ” ማለት በአላህ የማያምን ከሃዲ ወይንስ በአላህ የሚያምን መጥፎ ሥራ ሠርቶ ንስሐ ያልገባ አማኝ? አውዱን ሳታነብ እንዲህ መዘባረቅህና እዚያው ከሚገኝ የቁርኣን ጥቅስ ጋር መላተምህ አሁን ምን ይባላል? ነው ወይንስ አያነቡትም ብለህ አስበሃል?

እዥ የኀጢአተኞች ማለትም በአላህ የሚያምኑ ነገር ግን ከኀጢአታቸው ንስሐ ያልገቡ ሙስሊሞች ምግብ ከሆነ ሌሎች ቦታዎች ላይ የከሃዲያንም ምግብ እንደሆነ ስለሚናገር እንዴት አድርገህ ልታስታርቀው ነው? (ለምሳሌ ሱራ 38፡57፣ 14፡13-17 ተመልከት)፡፡ እዥ የኀጢአተኞችም የከሃዲያንም ምግብ ነው የምትል ከሆነ ቀደም ሲል የከሃዲያን ምግብ ዶሪዕ ብቻ መሆኑን መናገርህን ማስታወስ ያስፈልግሃል፡፡ ከዚህ የግጭት ማጥ ውስጥ ለመውጣት ጸሎት ብትጀምር ጥሩ ነው፡፡

አምልኮ የሚገባው የፈጠረን አላህ ብቻ ነው። በእርሱ ላይ ሌላ ማንነትና ምንነት ማጋራት ታላቅ በደል ነው። ለበደለኞች የዘቁም ዛፍ በይዎች ናቸው፦

37፥62 “በመስተንግዶነት ይህ ይበልጣልን? ወይስ የዘቁም ዛፍ?”

37፥63 “እኛ ለበዳዮች ፈተና አድርገናታል”፡፡

37፥66 እነርሱም ከእርሷ በይዎች ናቸው፤ ሆዶችንም ከእርሷ ሞይዎች ናቸው፡፡

“ዛሊሚን” ظَّالِمِين ማለትም “ሙሽሪኮች” በገሃንም ውስጥ የቅጣት ምግብ ገደብ አልተደረገባቸውም። ስለዚህ ከመነሻው ዐረፍተ-ነገሩን ከዐውዱ አፋቶ መረዳት ሽርክት መረዳት ነው።

ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ዘቁም የኀጢአተኞች ምግብ እንደሆነ ቁርኣን ይነግርሃል፡-

“የዘቁም ዛፍ የኀጥአተኛው ምግብ ነው።” (ሱራ 44:43-44)

ቀደም ሲል “የኀጢአተኛ ምግብ ዕዥ ብቻ” እንደሆነ እንደነገርከን አስታውስ፡፡ ስለዚህ የኀጢአተኛ ምግብ እዥብቻ ወይንስ የዘቁም ዛፍም ጭምር? ከዚህ የግጭት ትርምስ አላህና መልእክተኛውም ሊያወጡህ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡

ሲቀጥል “ኢላ” إِلَّا የሚለው አፍራሽ ቃል “ኢስቲስናዕ” اِسْتِثْنَاء‏ ማለትም “ግድባዊት”Exceptional” ሆኖ የመጣ ነው፥ በአንጻራዊና በፍጹማዊ አገባብ ይመጣል። በፍጹማዊ ግድብነት “Absolute Exception” ሲመጣ “ሙጥለቅ” مطلق ይባላል፤ በአንጻራዊ ግድብነት“Relative Exception” ሲመጣ ቀሪብ” قريب ይባላል። ይህንን ለመረዳት አንድ ጥቅስ ማየት ይበቃል፦

እንዲህ ያለ አገባብ እንዳለው ከአውዱ ማሳየት ሳትችል ወደ ሌላ ጥቅስ መዝለል ማንንም አያሳምንም፡፡

21፥25 ከአንተ በፊትም እነሆ “ከእኔ ሌላ አምላክ የለም” እና አምልኩኝ በማለት ወደ እርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡

“ኢላ” إِلَّا እዚህ ዐውድ ላይ አንጻራዊ ሆኖ መጥቷል። ወደ መልእክተኞቹ “ከእኔ ሌላ አምላክ የለም” ማለትን ብቻ ነው የሚያወርደው? አይ ወደ እነርሱ መልካም ሥራዎችን መሥራትን፣ ሶላትንም መስገድን፣ ዘካንም መስጠትን አውርዳል፦

21፥73 ”ወደ እነርሱም መልካም ሥራዎችን መሥራትን፣ ሶላትንም መስገድን፣ ዘካንም መስጠትን አወረድን”፡፡

ታዲያ ለምን “ከእኔ ሌላ አምላክ የለም” ማለት ብቻ ሆነ ስንል ከዐቂዳህ ጭብጥ አንጻር ነው እንጂ በጥቅሉ ሙጥለቅን አያመለክትም ከተባለ እንግዲያውስ የጀሃነም ምግብ “በስተቀር” የሚለው ከጀነት አስደሳች ምግቦች አንጻር እንጂ ሌላ አይደለም።

አንዱ ቦታ ላይ “ከእኔ ሌላ አምላክ የለም” ማለትን ብቻ እንዳወረደ ተናግሮ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ መልእክቶችንም እንዳወረደ ከተናገረ ሌላ ግጭት ነው፡፡ ስለዚህ ግጭቱን ከመፍታት ይልቅ ተጨማሪ ግጭት ነው ያሳየኸን፡፡ እናም እንጠይቅሃለን፤ አላህ ወደ ነቢያቱ ሲያወርድ የነበረው “ከእኔ ሌላ አምላክ የለም” ማለትን ብቻ ወይንስ ሌሎች መልእክቶችንም ጭምር? የቱ ነው ትክክል? እዚህ ቦታ ላይ በአንጻራዊ ግድባዊነት እየተናገረ እንዳለ ምንም ማስረጃ የለህም፡፡ ለነቢያት የወረደውን መልእክት ከምን ጋር አነጻጽሮ ነው በግድባዊ አንጻራዊነት የገለጸው? እንዲህ ያለ ንግግርስ እዚህ ቦታ ላይ አስፈላጊነቱ ምንድነው? የገሃነም ምግብስ ቢሆን በግድባዊ አገላለጹ ስለመገለጹ ከጥቅሶቹ አውድ ምን ማስረጃ አለህ? “ቁርኣን ሊሳሳት አይችልም” ከሚለው ከንቱ ቅድመ ግንዛቤህ የመነጨውን ሐሳብ በጭፍን እንድንቀበል የምትፈልግ ይመስላል፡፡ ቁርኣን አንዱ ጥቅስ ላይ የገሃነም ሰዎች ከዶሪዕ ውጪ ሌላ ምግብ እንደሌላቸው ከተናገረ በኋላ እዥ ብቻ እንደሆነ በመናገር ይህንን ሐሳብ ያፈርሳል፡፡ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ የዘቁም ዛፍ የሚባል እንዳለም በመግለፅ ከሁለቱም ጋር የሚጋጭ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ ለዚህ ግልፅ ግጭት አሳማኝ መፍትሄ ማቅረብ ተስኖሃል፡፡

 

የቁርኣን ግጭቶች