የቁርኣን ግጭቶች – ማርያም የተገለጡላት ስንት መላእክት ነበሩ?

11. ማርያም የተገለጡላት ስንት መላእክት ነበሩ?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ብዙ መላእክት፡–

3፥42 “መላእክትም ያሉትን አስታውስ፡- መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ አነጻሽም በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሸ”

አንድ መልአክ:-

19፥17 “ከእነሱም መጋረጃን አደረገች መንፈሳችንንም ወደ እርሷ ላክን ለርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት፡፡

መልስ

ወደ መርየም የመጡት መላእክት ብዙ ሲሆን እነዚህን ሹማምንት ወክሎ ሲያናግር የነበረው የልኡካኑ አለቃ ግን ጂብሪል ነው፦

3፥42 “መላእክትም ያሉትን አስታውስ”፡፡ «መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ፡፡ አነጻሽም፡፡ በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሽ፡፡»

እዚሁ ዐውድ ላይ ነጠላ መልአክ ያናግራት እንደነበረ ለመግለጽ በነጠላ “ቃለ” قَالَ ማለትም “አለ” የሚል ሃይለ-ቃል አለ፦

3፥47 ፡-ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል አላት፡፡

ስለዚህ ሱረቱል አለ-ዒምራን ላይ “ብዙ” መላእክት “ብቻ” እንጂ “አንድ” ብቻ አላናገራትም የሚል እና ሱረቱል መርየም ላይ አንድ መልአክ ብቻ እንጂ ብዙ መላእክት አላናገሯትም የሚል የለም። ይህ የመጨረሻ የወረደ ስሁት ሙግት ነው።

ጥያቄያችንን ቆርጠኸዋል፡፡ በኦሪጅናል ጽሑፋችን እንዲህ ብለን ነበር፡-

በሱራ 3፡42 እና 45 መሠረት መላእክቱ በብዙ ቁጥር ነው የተገለጹት፤ ማለትም በአረብኛ ቋንቋ የብዙ ቁጥር አተረጓጎም ከሦስት ያላነሱ መላእክት እንደነበሩ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በአረብኛ አካሄድ አራት መላእክት ወይንም ሺ ወይንም ሚሊዮንም ማለትም እንኳን ሊሆን ይችላል፡፡ በ19፡18 ላይ እንደተገጸው ደግሞ ማርያም ከአንድ መልአክ ጋር ብቻ ነው የተነጋገረችው፡፡ አንዱን መልአክ ብቻ መፍራቷም የታያት አንድ መልአክ ስለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው፡፡

ስለዚህ በሱራ 3፡42-45 ላይ ወደ ማርያም የመጡት ብዙ መላእክት ከነበሩ ሱራ 19፡18 ላይ ሁሉንም መፍራት ሲገባትና ከሁሉም መጠበቅ ሲገባት ለምን እርሱን ብቻ ፈራች? ለምንስ እርሱን ብቻ “አንተ” እያለች አናገረች?  “እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ፤ ጌታህን ፈሪ እንደ ኾንክ፣ (አትቅረበኝ) አለች።” ነገር ግን ሱራ 3፡42 ላይ ያነጋገሯት ብዙ መላእክት መሆናቸው እንዲህ ተነግሮናል፡- “መላእክትም ያሉትን አስታውስ፡- መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ አነጻሽም በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሸ፡፡” ስለዚህ እንደርሱ ከሆነ ማርያም መፍራትም ማነጋገርም የነበረባት ሁሉንም እንጂ አንዱን ብቻ አልነበረም፡፡

ሌላው “ወደ መርየም የመጡት መላእክት ብዙ ሲሆን እነዚህን ሹማምንት ወክሎ ሲያናግር የነበረው የልኡካኑ አለቃ ግን ጂብሪል ነው” ብለሃል፡፡ “ጂብሪል ነው” የሚል እስኪ “ሁሉንም ነገር አሟልቶ ከያዘው” ቁርኣንህ አሳየን? ቁርኣን ወደ ማርያም የመጣው ጂብሪል ነው አይልም፤ ይልቁኑ የአላህ መንፈስ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የአላህ መንፈስ የተባለው ደግሞ ጂብሪል ስለመሆኑ በቁርኣን ውስጥ በአንድም ቦታ አልተጻፈም፡፡ ያለ ውጪያዊ መጻሕፍት እገዛ ራሱን ችሎ መቆም የማይችል መጽሐፍ ቢኖር ቁርኣን ነው፡፡

ይህ በቁርኣን ውስጥ የተለመደ አገላለጽ ነው። ለምሳሌ ሩሕን በማውጣት የሚወስዱት መላእክት ብዙ መሆናቸው አንድ ቦታ ላይ ሲናገር ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ አንድ መልአክ መለኩል መውት ተጠቅሷል፦

47:27 መላእክትም ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን የሚመቱ ሲሆኑ በገደሉዋቸው ጊዜ ሁኔታቸው እንዴት ይሆናል?

32፥11 «በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ”ይወስዳችኃል”፡፡ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ» በላቸው፡፡

7፥37 የሞት መልክተኞቻችንም ”የሚወስዷቸው ኾነው በመጡባቸው ጊዜ” «ከአላህ ሌላ የምትጠሯቸው የነበራችሁት የት አሉ» ይሏቸዋል፡፡ «ከእኛ ተሰወሩን» ይላሉ፡፡ እነርሱም ከሃዲያን እንደነበሩ በነፍሶቻቸው ላይ ይመሰክራሉ፡፡

8፥50 እነዚያንም የካዱትን “መላእክት ፊቶቻቸውንና ጀርባዎቻቸውን እየመቱ «የቃጠሎንም ስቃይ ቅመሱ» እያሉ በሚወስዷቸው ጊዜ ብታይ ኖሮ አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር”፡፡

ይህንን ለማስረዳት ከራሳችሁ ባይብል ናሙና ላቅርብ። በሳምንቱ የፊተኛው ቀን ወደ መቃብር የመጣው አንድ መልአክ ነው፦

ማርቆስ 16፥5 ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ”።

ማቴዎስ 28፥2 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ” ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ።

በሳምንቱ የፊተኛው ቀን ወደ መቃብር የመጡት ሁለት መላእክት ናቸው፦

ሉቃስ 24፥4 እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ “ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ”፤

ዮሐንስ 20፥12 “ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው” የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።

በሳምንቱ የፊተኛው ቀን ወደ መቃብር የመጡት መላእክት ብዛት ስንት ነው አንድ ወይስ ሁለት? መልሱ አንድ “ብቻ” ቢል ኖሮ እና ሌላ ቦታ ሁለት ቢል ኖሮ ግጭት ይሆን ነበር። ግን “ብቻ” የሚለው ገላጭ በዐረፍተ-ነገር ውስጥ እስከሌለ ድረስ አንዱ ያልተረከውን ሌላው አብራራው በሚል ስሌት ከተቀመጠ እንግዲያውስ ከላይ ያለው የቁርኣን አናቅጽ ላይ “ብቻ” የሚል ስለሌለ በዚህ ስሌትና ቀመር መረዳት ይቻላል።

ከላይ የሚገኘውን ጥያቄ በቁርኣን ላይ ያነሳነው በክርስቶስ ትንሣኤ ወቅት የተገለጡትን መላእክት ቁጥር በተመለከተ በተደጋጋሚ ስለምትጠይቁና ግጭት ነው ብላችሁ ስለፈረጃችሁ ነው፡፡ በሙስሊሞች የተዘጋጁ ስለ ግጭት ከሚያወሩ ጽሑፎች ውስጥ ይህ ጥያቄ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ የቁርአኑን ለማስታረቅ በሞከርከው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱሱን ለመረዳት መሞከርህ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ ላይ ጥያቄ ስታነሳ ከርመህ ነገሩ ወደ ቁርኣን ሲዞር ሁለቱንም በተመሳሳይ ሚዛን ለመመዘን ፈቃደኛ መሆንህ ለኛ ድል ነው፡፡ በሙግቱ ተረትተሃል፡፡ ዳሩ ግን ቅንነት የጎደለው አካሄድ እንዳለህ ስለምናውቅ ይህንን ኑዛዜህን አጥፈህ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያንኑ ሙግት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስትጠቀም ልናይህ እንችላለን፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በኛ ወገን የመጽሐፍ ቅዱሱ ግጭት አይደለም የቁርአኑ ግን ግጭት ነው የምንልባቸው በቂ ምክንያቶች አሉን፡-

አንተ በትክክል እንዳስቀመጥከው ማቴዎስና ማርቆስ ላይ “አንድ መልአክ ብቻ” የሚል ስለሌለ ከሁለቱ ስለ አንዱ ነው የተናገሩት፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ ዘገባዎች በመነሳት አንድ መልአክ ብቻ ነው ልንል አንችልም፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ግጭት የለም፡፡

ወንጌላት በአራት የተለያዩ ሰዎች የተጻፉ የዐይን እማኞች ዘገባዎች ስለሆኑ ደግሞ በአዘጋገባቸው ላይ መጠነኛ ልዩነት መኖሩ የሚጠበቅ ነው፤ ስለዚህ “አንድ ብቻ” ወይንም “ሌላ መልአክ አብሮት አልነበረም” የሚለውን የመሳሰሉ ግልፅ ተቃርኖን የሚፈጥሩ ልዩነቶች እስከሌሉ ድረስ ልዩነቶቹን በግጭትነት መፈረጅ ትክክል አይሆንም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ ሴቶቹ መላእክቱን አላነጋገሩም፤ ነገር ግን መሪ መልአኩ ተናግሯቸዋል፡፡ የማቴዎስና የማርቆስም ትኩረት በእርሱ ላይ ነው፡፡

የቁርአኑን ዘገባ ስንመለከት ግን አንዱ ቦታ ላይ ብዙ መልአክት እንደተገለጡና እንዳበሰሯት የሚናገር ሲሆን ሌላ ቦታ ላይ ግን አንዱን መልአክ በመጥቀስ መልአኩ እንዳነጋገራትና እርሷም እንዳነጋገረችው ይናገራል፡፡ የፈራችውና መጋረጃን ያደረገችውም ከአንዱ መልአክ እንደሆነ ተጽፏል፡፡ ቁርኣን ደግሞ በአንድ ሰው በኩል የተነገረና በቀጥታ ከፈጣሪ ዘንድ የመጣ መገለጥ እንደሆነ ስለተነገረለት እንዲህ ያለ ልዩነት አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ የቁርአኑ ግጭት ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱሱ ግን ግጭት ሳይሆን ተሰባጣሪ ዘገባ ነው፡፡

የቁርኣን ግጭቶች