የቁርኣን ግጭቶች – አንዲት ነፍስ የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም ወይስ ትሸከማለች?

13. አንዲት ነፍስ የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም ወይስ ትሸከማለች?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

አትሸከምም፦

35:18 “ኀጢአትን ተሸካሚም ነፍስ የሌላዋን ሸክም አትሸከምም”፤

ትሸከማለች፦

16፥25 ይህንንም የሚሉት በትንሣኤ ቀን ኀጢኣቶቻቸውን በሙሉ ”ከእነዚያም ያለ ዕውቀት ኾነው ከሚያጠሟቸው ሰዎች ኀጢአቶች ከፊሉን ሊሸከሙ ነው”፡፡ ንቁ! የሚሸከሙት ኃጢኣት ምንኛ ከፋ!

መልስ

ከላይ ያለውን አጠያየቅ ከአንሰሪንግ ኢሥላም ላይ በትክክል ስላላስቀመጡት እኔ በትክክል አስቀምጬላቸዋለው።

እያምታታህ ስለሆነ እዚህ ጋ ላስቁምህ፡፡ እኛ የጠየቅነውን ጥያቄ ላንተ በሚቀልህ መንገድ ለውጠህ አቅርበኸዋል፡፡ የኛ ኦሪጅናል ጥያቄ እንዲህ ይላል፡-

አንዱ የሌላውን ኃጢኣት ይሸከማል ወይንስ አይሸከምም?

አይሸከምም:- 35:18 “ኀጢኣትን ተሸካሚም (ነፍስ)፣ የሌላዋን ሸክም አትሸከምም፤ የተከበደችም (ነፍስ) ወደ ሸክሟ ብትጠራ (ተጠሪው) የቅርብ ዝምድና ባለቤት ቢሆንም እንኳ ከርሷ አንዳችን የሚሸከምላት አታገኝም። የምታስጠነቅቀው፣ እነዚያን ጌታቸውን በሩቅ የሚፈሩትን፣ ሦላትንም አስተካክለው ያደረሱትን ብቻ ነው፤ የተጥራራም ሰው፣ የሚጥራራው ለራሱ ብቻ ነው፤ መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው።”

53:37-42 “በዚያም (የታዘዘውን) በፈጸመው በኢብራሂም ጽሑፎች ውስጥ ባለው አልተነገረምን?) (እርሱም ኃጢአት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም። ለሰውም ሁሉ የሠራው እንጅ ሌላ የለውም። ሥራውም ሁሉ ወደፊት ይታያል። ከዚያም ሙሉውን ምንዳ ይመነዳዋል። መጨረሻውም ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡”

ይሸከማል:- ሙሐመድ በእርሱ ዘመን የነበሩትን አይሁድ አባቶቻቸው በሠሯቸው ኃጢኣቶች ሳብያ ሲወቅሳቸው በብዙ የቁርኣን ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ቁርኣን 2:50-52 እንዲህ ይላል:- “በናንተም ምክንያት ባሕሩን በከፈልን ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ ወዲያውም አዳንናችሁ፡፡ የፈርዖንንም ቤተሰቦች እናንተ የምትመለከቱ ኾናችሁ አሰጠምናቸው፡፡ ሙሳንም አርባን ሌሊት በቀጠርነው ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ)፡፡ ከዚያም ከርሱ (መኼድ) በኋላ እናንተ በዳዮች ስትኾኑ ወይፈንን (አምላክ አድርጋችሁ) ያዛችሁ፡፡ ከዚያም ከዚህ በኋላ እናንተ ታመሰግኑ ዘንድ ከናንተ ምሕረት አደረግን፡፡”

የወርቁን ጥጃ ያመለኩት አባቶች ሆነው ሳሉ ነገር ግን ልጆች ተወቃሾች ሆነዋል፡፡ ታድያ አንዱ የሌላውን ኃጢኣት ይሸከመል ወይንስ አይሸከምም? የቱን እንቀበል?

 “…በትክክል ስላላስቀመጡት እኔ በትክክል አስቀምጬላቸዋለው” በሚል ሰበብ ያልጠየቅነውን መመለስ ጥያቄያችንን ደካማ አስመስሎ የማቅረብ ስልት ነው፡፡ ለማንኛውም እስኪ የምታወራውን እንስማ፡፡

በቁርኣን እስተምህሮት ውስጥ እንደ ክርስትናው “ጥንተ-ተአብሶ” Original sin ማለትም እንደ ስኳርና ሳይነስ ለትውልድ በዘር የሚተላለፍ ኃጢአት የለም፤ ኃጢአት ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም፤ አምላካችን አላህ ብዙ አንቀጾቹ ላይ፦ “ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም” እያለ ይነግረናል፦

ሳይነስ በኢንፌክሽን የሚመጣ ሲሆን በዘር ከማይተላለፉ በሽታዎች መካከል ይመደባል፡፡ የስኳር በሽታም ቢሆን Type 2 የተሰኘው በዘር ሊመጣ እንደሚችል ግምት ቢኖርም በአጠቃላይ ግን የስኳር በሽታ ከአኗኗር ዘይቤያችን የተነሳ የሚመጣ መሆኑን የሕክምና ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ሥነመለኮቱን በአቦ ሰጡኝ ማማሰልህ ሳያንስህ ወደ ኅክምናውም ገባህ፡፡ ይገርማል፡፡ መሳሳት የማይሰለችህ ሰውዬ፡፡

17፥15 የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ የተሳሳተም ሰው የሚሳሳተው ጉዳቱ በእርሷ ላይ ነው፡፡ ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ኃጢኣት አትሸከምም፡፡

እዚህ ድረስ ከተግባባን የሚቀጥለውን አንቀፅ እንዲህ መረዳት ይቻላል፦

በፍፁም አልተግባባንም፡፡ እስልምና ስለ ውርስ ኃጢአት አሳምሮ ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡ አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡ «ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡” (ሱራ 2፡36-38)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው “ሁላችሁም” የሚለው በአረብኛ ከሁለት በላይ ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ፍርዱ በአዳምና በሔዋን ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ያሳያል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir, Abridged: part 1, Surah Al-Fatiah Surah Al-Baqarah, ayat 1 to 141, pp. 109-110)፡፡ አላህ የአዳምን ንስሐ እንደተቀበለ ተነግሯል ነገር ግን ከገነት መባረሩ አላህ ኃጢአቱን ይቅር እንዳላለ ያሳያል፡፡ ኃጢአቱን ይቅር ቢለው ኖሮ ለምን ወደ ገነት አልመለሰውም ነበር? ፀፀቱን ተቀብሎ ኃጢአቱን ይቅር ከማለት ይልቅ ፀፀቱን ተቀብሎ ወደ ፊት ለዘሮቹ የሚሆን መመርያን ለመስጠትና ይህንን መመርያ የተከተለውን ሰው ብቻ ለመማር እንደወሰነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡

ቲርሚዚ ሐዲስ አዳም የሠራው ኃጢአት ወደ ዘሮቹ ሁሉ መተላለፉን እንዲህ በማለት ይገልፃል፡-

“አደም ስለ ካደ ዘሮቹ ሁሉ ካዱ፡፡ አደም ዝንጉ በመሆን የተለከለከለውን ዛፍ ስለበላ ዘሮቹም ዝንጉዎች ሆኑ፡፡ አደም ስለተሳሳተ ዘሮቹ ሁሉ ስህተት ፈፀሙ፡፡” (Al-Tirmidhi Hadith, Number 37; (ALIM CD ROM Version)

አልቡኻሪ ደግሞ ሙሴ አዳምን “ከገነት እንድንባረር ያደረከን አንተ አባታችን ነህ” በማለት በወቀሰው ጊዜ አዳም መልሶ “አላህ ከመፈጠሬ ከአርባ ዓመታት በፊት ወስኖልኝ ለጻፈብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን?” በማለት እንደመለሰለት ዘግቧል፡፡ (Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 77, Number 611)

ሳሂህ ሙስሊም “ከገነት ያስባረራችሁ የአባታችሁ የአደም ኃጢአት ነው” ይላል፡፡ (Sahih Muslim, Book 001, Number 0380)

እስላማዊ ምንጮች ከዚህም አልፈው ሴቶች “እስከዛሬ ድረስ ለሚያሳዩት ጸባይ” ሔዋንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡-

“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- በእስራኤል ልጆች ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሥጋ ባልበሰበሰ ነበር፡፡ በሐዋ ምክንያት ባይሆን ኖሮ የትኛዋም ሴት ባሏን ባልከዳች ነበር፡፡” (Sahih al-Bukhari, Volume 4, Book 55, Number 611. Sahih Muslim Book 008, Number 3472)

በተጨማሪም አል-ጠበሪ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ጸሐፊ ሴቶች የወር አበባ የሚፈስሳቸውና “በአስተሳሰብ ደካማ የሆኑት” በሔዋን ምክንያት እንደሆነ ጽፏል፡፡ (The History of Al-Tabari: General Introduction from the Creation to the Flood, Translated by Franz Rosenthal, SUNY press, Albany, 1998, Volume 1, pp. 280-281)

ኃጢአትና ውጤቱ በዘር የማይተላለፉ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሁሉ እስላማዊ አስተምሕሮዎች ስህተትና ትርጉም አልባ ይሆናሉ፡፡ አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት በእነርሱ ላይ ብቻ ቢሆን ኖሮ ከገነት መባረራቸው እኛንም ከገነት ውጪ እንድንሆን ባላደረገንና ልክ ስንወለድ ወደ ገነት በተመለስን ነበር፡፡ ሙስሊሞች ጥንተ አብሶን ወይንም የመጀመርያውን ኃጢአት መካዳቸው ከእውነታ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍታቸውም ጋር እንዲላተሙ ያደርጋቸዋል፡፡

16፥25 ይህንንም የሚሉት በትንሣኤ ቀን ኀጢኣቶቻቸውን በሙሉ ”ከእነዚያም ያለ ዕውቀት ኾነው ከሚያጠሟቸው ሰዎች ኀጢአቶች ከፊሉን ሊሸከሙ ነው”፡፡ ንቁ! የሚሸከሙት ኃጢኣት ምንኛ ከፋ!

አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሲያሳስት አሳሳቹ በማሳሳቱ ምክንያት የተሳሳተው ሰው የሚያገኘውን ቅጣት ከሚሳሳተው ላይ ቅጣቱ ሳይቀነስ ሳይጨመር የተሳሳተውን ሰው ቅጣት አሳሳቹ ይቀበላል፤ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ከመራ መሪው በመምራቱ ምክንያት የተመራው ሰው የሚያገኘውን አጅር ከሚመራው ላይ አጅሩ ሳይቀነስ ሳይጨመር የተመራውን ሰው አጅር መሪው ይቀበላል፤ ከላይ ያለው መልክእት ይህ ነው፤

ኢብኑ ከሲር ይህንን አንቀፅ በሐዲስ እንዲህ ይፈስረዋል፦

ሱነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 210

አነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተረከው፤ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ፦ “ማንም ጠሪ ሰዎችን ወደ ጥመት የሚጣራ የተከተሉት ሰዎች የሚሸከሙትን ኀጢአት ከእነርሱ ላይ ሳይጓደል ይሸከማል፤ ማንም ጠሪ ሰዎችን ወደ ምሪት የሚጣራ የተከተሉት ሰዎች የሚያገኙትን ምንዳ ከእነርሱ ላይ ሳይጓደል ያገኛል”።

ነፍስ የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም ማለት ለምሳሌ መቶ ኪሎ ጤፍ ተሸክሜ ከነበረ ሌላ ሰው ለእኔ ጤፉን ከተሸከመልኝ እኔ ላይ መቶ ኪሎ ጤፍ የለም ማለት ነው፤ ግን አጥማሚ የጠመመውን ሰው በእርሱ ምክንያት ነውና ከእርሱ ቅጣት ሳይጓደል ይቀጣል፤ ለምሳሌ ቃየል የአደም ልጆች መግደልን ያስተማረ ነው፤ ሰዎች ሰው በገደሉ ቁጥር ገዳዩ ሊቀጣበት ያለውን ቅጣት ቃየልም ይቀጣል፤ ያ ማለት ገዳዩ ቅጣቱ ይቀልለታል ማለት አይደለም፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 28, ሐዲስ 38

ዐብደላህ እንደተረከው፤ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ፦ “በግፍ ገዳይ አንድም ሰው የለም፥ የእርሱ ወንጀል ድርሻ በመጀመሪያው የአደም ልጅ ላይ ቢሆን እንጂ፤ ምክንያቱም እርሱ ግድያን በማስተዋወቅ የመጀመሪያ ነበር”።

ስለዚህ አላህ በሰው ቀኝና ግራ ባሉት መላእክት የሚከትበው ሰዎች የሰሩትን መልካምና ክፉ ስራ ብቻ ሳይሆን “ፈለጎቻቸውንም” ማለትም ያጠመሙትን ወይም የመሩትን ስራ ጭምር ነው፤ አንድ ሰው በመመሳቱ ብቻ ሳይሆን በማሳሳቱም ይጠየቃል፦

36፥12 እኛ ሙታንን እኛ በእርግጥ ሕያው እናደርጋለን፡፡ ”ያስቀደሙትንም ሥራ እና ፈለጎቻቸውንም እንጽፋለን”፡፡

ሊቃውንቶቻችሁ የቁርኣንን ግጭት ለማስታረቅ ኢ-አመክንዮአዊ ነገር ተናግረዋል፡፡ ሱራ 16፡25 “ከእነዚያም ያለ ዕውቀት ኾነው ከሚያጠሟቸው ሰዎች ኀጢአቶች ከፊሉን ሊሸከሙ ነው” በማለት በግልፅ ይናገራል፡፡ አጥማሚዎቹ ያጠመሟቸውን ሰዎች ከፊሉን ኃጢአት ሲሸከሙ ከዚያኛው ወገን ሸክም የማይቀንስ ከሆነ “ከሚያጠሟቸው ሰዎች ኀጢአቶች ከፊሉን ሊሸከሙ ነው” መባሉ ትርጉም አይሰጥም፡፡ መባል የነበረበት “ከሚያጠሟቸው ሰዎች የኃጢአት ሸክም ጋር የሚመጣጠን ተጨማሪ ሸክም” እንጂ “ከሚያጠሟቸው ሰዎች ኀጢአቶች ከፊሉን” አይደለም፤ ምክንያቱም ከኃጢአታቸው የተሸከሙት ምንም የለምና፡፡ ተመሳሳይ ወይንም ተመጣጣኝ ሸክም መሸከምና ሌላ ሰው የፈፀመውን ኃጢአት ከፊሉን መሸከም የተለያዩ ናቸው፡፡ ቁርኣን የሚናገረው አጥማሚዎች የሚያጠሟቸውን ሰዎች ኃጢአት ከፊሉን እንደሚሸከሙ እንጂ ተመሳሳይ የኃጢአት ሸክም እንደሚሸከሙ አይደለም፡፡ ስለዚህ “ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ኃጢኣት አትሸከምም” ከሚለው ጥቅስ ጋር ይጋጫል፡፡

ሒደቱም ፈጣሪን ኢ-ፍትሃዊ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ያህል የስርቆት ቅጣት ዋጋ 100 ነው ብንልና ስርቆት አስተማሪውም ስርቆት ተማሪውም በየፊናቸው 100 ቢቀጡ፤ ስርቆት አስተማሪው ተጨማሪ 50 ቢቀጣና ቅጣቱ 150 ቢሆን የስርቆት ተማሪው ቅጣት የማይቀንስ ከሆነ ለስርቆት ቅጣት መከፈል ከነበረበት በላይ 50 ቅጣት ዋጋ ተከፍሏል፡፡ ስለዚህ በፈጣሪ የፍትህ ዓለም ውስጥ የጥፋትና የቅጣት አለመመጣጠን አለ ማለት ይሆናል፡፡ ፈጣሪ ደግሞ ኢ-ፍትሃዊ አይደለም፡፡

ቀጥሎ ያለውን ውዥንብር ተመልከቱ፦ “አላህ በሙሐመድ ዘመን የነበሩትን አይሁድ አባቶቻቸው በሠሯቸው ኃጢኣቶች ሳብያ ሲወቅሳቸው እንመለከታለን፦

2፥51 ሙሳንም አርባን ሌሊት በቀጠርነው ጊዜ የኾነውን አስታውሱ፡፡ ከዚያም ከእርሱ መኼድ በኋላ ”እናንተ በዳዮች ስትኾኑ ወይፈንን አምላክ አድርጋችሁ ያዛችሁ”፡፡

ይህ ከውርስ ኃጢኣት ጋር አንዳች ግንኙነት የውም። ይህ ጥቅላዊ አይሁዳውነትን የሚያሳይ እንጂ በተናጥል የአበውን ወንጀል ወደ ልጆች መሸከምን አያመለክትም። አላህ ደመናን ያጠለለውና መናን እና ድርጭትን ያወረደው በሙሳ ዘመን ቢሆንም በነቢያችን ዘመን ወደነበሩት አይሁድ፦ “በእናንተም ላይ ደመናን አጠለልን፡፡ በእናተም ላይ መናን እና ድርጭትን አወረድን” እያለ ይናገራል፦

2፥57 ”በእናንተም ላይ” ደመናን አጠለልን፡፡ ”በእናተም ላይ” መናን እና ድርጭትን አወረድን፡፡

 “እናንተ” የሚለው ጥቅላዊ አነጋገር እንጂ በነቢያችን ዘመን የነበሩት አይሁድ ደመናም አልጠለለላቸውም፥ እንዲሁ መናን እና ድርጭትን አልወረደላቸውም። አላህ ወደ ነብያት ያወረደው በነቢያችን ዘመን ወደነበሩት አይሁድ እና ክርስቲያን “ወደ እናንተ አወረድን” ማለቱንም አስተውሉ፦

29፥46 የመጽሐፉን ባለቤቶችም በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ፡፡ ከእነርሱ እነዚያን የበደሉትን ሲቀር፡፡ በሉም፦ «በዚያ ወደ እኛ በተወረደው ወደ እናንተም በተወረደው አመንን”፡፡ አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው፡፡ እኛም ለእርሱ ታዛዦች ነን፡፡»

ስለዚህ “እናንተ” የሚለው ሃይለ-ቃል ጥቅላዊ መልእክት እንጂ በተናጥል የአበውን ወንጀል ለልጆች መተላለፉን በፍጹም አያሳይም። አበው ጥጃ በማምለካቸው ልጆችን እየወቀሰ ነው ማለት ነው ብሎ መሞገት ለአበው ደመናን አጠለልን፥ መናን እና ድርጭትን አወረድን የሚለውን ለልጆች ምን አደረገ ብሎ መረዳት ይቻላል? ይህ የቂል እንጉልፏቶ አስተሳሰብ ነው።

ይህንን የተናገረው የቁርኣን ደራሲ እንጂ እኛ ባለመሆናችን ስድቡ አስፈላጊ መስሎ ከታየህ ተገቢነቱ ለቁርኣን ደራሲና የእርሱ ተከታይ ለሆንከው ለአንተ ነው፡፡ ሙሐመድ ሲናገር የነበረው በእርሱ ዘመን ለነበሩት አይሁድ እንደነበር የሚያከራክር አይደለም፡፡ ስለዚህ በወርቁ ጥጃ አምልኮ ምክንያት እየወቀሰ የሚገኘው በእርሱ ዘመን የነበሩትን አይሁድ ነው፡፡ ኢብን ከሢር ራሱ ይህንኑ ያረጋግጣል (Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 1, pp. 296-298)፡፡ እግዚአብሔር ለአይሁድ ሕዝብ ያደረጋቸው መልካም ነገሮች ቢያንስ ዘራቸውን ለማስቀጠልና ያሉበት ቦታ ላይ ለመገኘት ለሁሉም ትውልዶች ተዘዋዋሪ ጥቅም እንዳለው እሙን ነው፡፡ ስለዚህ ለአበው የተደረገው መልካም ነገር ለሁሉም የአይሁድ ትውልድ የሚጠቅም በመሆኑ ለሁሉም እንደተደረገ መልካም ነገር መነገሩ ያስማማናል፡፡ ነገር ግን እስልምና እንደሚያስተምረው የአበው ኃጢአት በልጆች ላይ ምንም ተፅዕኖ ከሌለውና ሁሉም ሰው ራሱ በሠራው ኃጢአት ብቻ የሚወቀስና ቅጣትን የሚቀበል ከሆነ አይሁድ አባቶቻቸው በሠሩት ኃጢአት ምክንያት በጥቅል እንደ ሕዝብም ሆነ በተናጠል እንደ ግለሰብ መወቀስም መጠየቅም የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ አይሁድን አባቶቻቸው በሠሩት ኃጢአት ምክንያት መውቀሱ ከእስልምና አስተምሕሮ ጋር ይጋጫል፡፡

የቁርኣን ግጭቶች