ሰው ነፃ ፈቃድ አለው ወይስ የለውም?

20. ሰው ነፃ ፈቃድ አለው ወይስ የለውም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

የለውም፡-

ሱራ 10፥100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን ችሎታ የላትም፡፡

አለው፡-

ሱራ 81፥27-18 “እርሱ የዓለማት መገሠጫ እንጂ ሌላ አይደለም። ከእናንተ ቀጥተኛ መሆንን ለሻ ሰው መገሠጫ ነው።”

መልስ

10፥100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን ችሎታ የላትም”፡፡

እዚህ አንቀጽ ላይ፦ “ሰው ነጻ ፈቃፍ የለውም” የሚል ሃይለ-ቃል ይቅርና ሽታው እንኳን የለም። ይህ ባለማወቅ ሳይሆን ሆን ተብሎ የዋህ ክርስቲያኖችን ሲያነቡ አያመዛዝኑም ብሎ መናቅ ነው። የአላህ ፈቃድ ከሰው ነጻ ፈቃድ ጋር በፍጹም አይጋጭም፤ ለሰው ነጻ ፈቃድ የሰጠው አላህ እራሱ ፈቅዶ ነውና።

እኛ ክርስቲያኖች ስህተት የመሰለንን ነገር በቅንነት እንጠይቃለን እንጂ እንደናንተ የዋሐንን የማወናበድ ዓላማ ይዘን አንጽፍም፣ አንናገርም፡፡ ተቂያ (“ቅዱስ” ውሸት) በናንተ እንጂ በኛ ሃይማኖት ውስጥ የለም፡፡ ጥያቄያችንን ቆርጠህ ማቅረብህ በራሱ ምን ያህል ሃቀኝነት የራቀህ ሰው እንደሆንክ ያሳያል፡፡ በድረገፃችን ላይ የሰፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡-

ሰው ነፃ ፈቃድ አለው ወይስ የለውም?

የለውም፡ሱራ 10፡100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን (ችሎታ) የላትም፡፡ (አላህ ለከፊሎቹ እምነትን ይሻል)፡፡ በእነዚያም በማያውቁት ላይ ርክሰትን ያደርጋል፡፡”

ነፃ ፈቃድ አለው፡ ሱራ 81፡27-18 “እርሱ የዓለማት መገሠጫ እንጂ ሌላ አይደለም። ከናንተ ቀጥተኛ መሆንን ለሻ ሰው መገሠጫ ነው።”

It is not except a reminder to the worlds. For whoever wills among you to take a right course.

ሱራ 30፡9 “በምድር ላይ አይኼዱምና የነዚያን ከበፊታቸው የነበሩትን ሰዎች ፍጻሜ እንዴት እንደ ነበረ አይመለከቱምን? በኀይል ከነርሱ ይበልጥ የጠነከሩ ነበሩ፤ ምድርንም አረሱ፤ (እነዚህ) ከአለሟትም የበዛ አለሟት፤ መልክተኞቻቸውም በታምራቶች መጡባቸው፤ (አስተባበሉምና ጠፉ)፤ አላህም የሚበድላቸው አልነበረም፤ ግን ነፍሶቻቸውን ይበድሉ ነበሩ።

የመጀመርያው ጥቅስ ማንም ሰው እንዲያምንም ሆነ እንዳያምን ወሳኙ አላህ መሆኑንና በምርጫው ማመን የሚችል አለመኖሩን ይናገራል፡፡ አክሎም አላህ ሰዎች ዕውቀትን በማጣታቸው ብቻ ርክሰትን እንደሚያደርግባቸው ይናገራል፡፡ በማስከተል የሚገኙት ደግሞ ትክክለኛውን መንገድ ለመምረጥ ውሳኔው በሰዎች ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ነፃ ፈቃድ ማለት በራሳችን ምርጫና ኃላፊነት ግራና ቀኛችንን መምረጥ ማለት ነው፡፡ የመጀመርያውን ጥቅስ አንብበህ የሰዎችን ነፃ ፈቃድ የሚክድ መሆኑን መረዳት አለመቻልህ አስገራሚ ነው፡፡ ያንተን ምላሽ እንስማ፡-

ይህ እሳቤ በቀደር ትምህርት ውስጥ የሚካተት ነው፤ “ቀደር” የተለያየ “መራቲብ” مراتب ማለትም “ደረጃ”Degree” አሉት፥ ከእነርሱ አንዱ “መርተበቱል መሺያህ” ነው።

“ሻአ” شَآءَ ማለት “ፈቃድ” ማለት ሲሆን አምላካችን አላህ በፍጥረተ-ዓለማት ውስጥ የሚሻውን ይፈጥራል፦

24፥45 አላህ የሚሻውን ሁሉ ይፈጥራል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡

86፥16 የሚሻውን ሁሉ ሠሪ ነው፡፡

5፥17 የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

3፥47 አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል አላት፡፡

የአላህ ፈቃድ በሁለት መልክ ለፍጡራን ተቀድሯል፤ አንዱ ያለፈቃዳቸው ሲሆን ሁለተኛው በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ ላይ ነው። የመጀመሪያው ፍጥረት ሲፈጠር ያለፈቃዱ በአላህ ፈቃድ የተፈጠረ ነው። ሰው በመወለድ፣ በሞት፣ በመተኛት፣ በማስነጠስ ምርጫ የለውም፤ ልጅ እንኳን ሲወልድ ወንድ ወይም ሴት እወልዳለው ብሎ ምርጫ የለውም፤ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ ለሚሻው ሰው ሴቶችን ይሰጣል፤ ለሚሻውም ሰው ወንዶችን ይሰጣል። ለሚሻው መንታ ያደርጋል፤ የሚሻውን መካን ያደርገዋል። ለፍጡራን ምርጫ የላቸውም፦

42፥49 የሰማያትና የምድር ንግሥና የአላህ ነው፡፡ የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ ለሚሻው ሰው ሴቶችን ይሰጣል፡፡ ለሚሻውም ሰው ወንዶችን ይሰጣል፡፡

42፥50 ወይም ወንዶችና ሴቶች አድርጎ ያጠናዳቸዋል፡፡ የሚሻውንም ሰው መካን ያደርገዋል፡፡ እርሱ ዐዋቂ ቻይ ነውና፡፡

28፥68 ጌታህም የሚሻውን ይፈጥራል፤ ይመርጣልም፡፡ ለእነርሱ ለፍጡራን ምርጫ የላቸውም፡፡

በዚህ ምርጫ በሌለው ነገር ፍጥረት አይጠየቅበትም፤ አይቀጣበትም፣ አይሸለምበትም።

ሰዎች በፈጣሪ ፈቃድ ከተወደለዱና ለአቅመ ምርጫ ከደረሱ በኋላ አንተ በጠቀስካቸው ጉዳዮች ሁሉ ላይ መምረጥ እንደሚችሉ የታወቀ ነው፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ መምረጥ መቻል አለመቻላቸው እኔ ባነሳሁት ጥያቄ ትክክለኛነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ባይኖርም ለአቋምህ የማይሆኑ ነጥችን መጥቀስህን እያየሁ ማለፍ አልፈለኩም፡፡ ሰዎች መሞት ከፈለጉ መሞት ይችላሉ፣ የእንቅልፍ ሰዓታቸውን መምረጥ ይችላሉ፣ የእንቅልፍ ወይንም እንቅልፍ የሚነሳ መድኃኒት መውሰድ ይችላሉ፣ እንጥሽታቸውን መቆጣጠር ይችላሉ፣ የሰው ልጆች በቴክኖሎጂ የሚወልዷቸውን ልጆች ፆታና መጠን መወሰን እየቻሉ ነው (In vitro fertilization (IVF) ብሎ በይነ መረብ ላይ ፍለጋ ማድረግ ይቻላል)፣ መውለድ የማይችሉ መካኖችም ሲወልዱ፣ መውለድ የሚችሉ ራሳቸውን ሲያመክኑ እያየን ነው፡፡ ሕይወትና ሞትን በተመለከተም ሰዎች ሌሎችንም ሆነ ራሳቸውን መግደል ይችላሉ፡፡ አንተ የጠቀስካቸው ነገሮች ሰዎች ነፃ ምርጫ እንደሌላቸው ለማሳየት ጥሩ ምሳሌዎች አይመስሉኝም፡፡ ናቸው የምትል ከሆነ አልከራከርህም፡፡ በኔ ነጥብ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለምና፡፡

ሁለተኛው ፍጥረት በተሰጠው ነጻ ፈቃድና ምርጫ ይጠየቃሉ፦

21፥23 ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ ፍጥረቶቹ ግን ይጠየቃሉ፡፡

አላህ በሚሰራው ሥራ አይጠየቅም፤ ምክንያቱም አላህ ለዓለማት በደልን የሚሻ አይደለም፤ አላህ ሰዎችን ምንም አይበድልም፤ ግን ሰዎች እራሳቸውን ይበድላሉ፦

3፥108 አላህም ለዓለማት በደልን የሚሻ አይደለም፡፡

10፥44 አላህ ሰዎችን ምንም አይበድልም፤ ግን ሰዎች እራሳቸውን ይበድላሉ፡፡

ሰዎች የሚፈጽሙ እውነትና ውሸት፣ ትክክልና ስህተት፣ መልካሙና ክፉ፣ አላህ የሚወደውና የሚጠላው ሃራምና ሃላል በሙሉ አላህ ስለፈቀደ ነው የሚከናወኑት፤ ያለ አላህ ፈቃድ ምንም የሚሆን ነገር የለም፣ አላህ ፈቀደ ማለት ግን ጉዳዩን ወዶታል አሊያም ተስማምቶበታል ማለት አይደለም፣ አላህ ስለፈቀደ ነው ሰው ነጻ ፈቃድ ያለው፣ አላህ ሳይፈቅድ ሰው ነጻ ፈቃድ አይኖረውም ነበር፦

ጥያቄው እርሱ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በሉኣላዊ ምርጫው ለሰዎች የመምረጥን ችሎታ እንደሰጠ የካደ ማንም የለም፡፡ በምድር ላይ የሚከናወኑ ጉዳዮችም ያለ እርሱ ፈቃድ ይፈፀማሉ አልተባለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ወዶና ፈቅዶ ለሰው ነፃ ፈቃድ በሰጠባቸው ጉዳዮች፣ በተለይም በማመንና ባለማመን ጉዳይ ሰዎች በገዛ ምርጫቸው ሳይሆን በቅድመ ውሳኔ ብቻ እንደሚያምኑና እንደማያምኑ በቁርኣን መነገሩ ነው፡፡ በሌሎች ቦታዎች ግን ሰዎች ማመንም ሆነ አለማመን የግል ምርጫቸው መሆኑን በመናገር ይህንን ሐሳብ ያፈርሳል፡፡

81፥29 የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡

76፥30 አላህም ካልሻ በስተቀር አትሹም፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡

አላህ ለሰዎች ነጻ ፈቃድ እንዲኖራቸው ፈቅዷል፤ ነገር ግን አላህ የሚወደው ብናመሰግነው እንጂ ብንክደው አይደለም፤ አላህ ለሰው ይህ የሚያስክድ መንገድ ነው፤ ይህ የሚያስመሰግን መንገድ ነው ብሎ ሁለቱንም መንገድ በቅዱስ ቃሉ ተናግሯል፦

14፥7 ጌታችሁም «ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ ብትክዱም እቀጣችኋለሁ፤ ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና» በማለት ባስታወቀ ጊዜ አስታውሱ፡፡

39፥7 ብትክዱ አላህ ከእናንተ የተብቃቃ ነው፡፡ ለባሪያዎቹም ከህደትን አይወድም፡፡ ብታመሰግኑም፤ እርሱን ይወድላችኋል፡፡

90፥10 ሁለትን መንገዶችም አልመራነውምን?

76፥3 እኛ ወይ አመስጋኝ ወይም ከሓዲ ሲኾን መንገዱን መራነው፤ ገለጽንለት፡፡

አንተ በጠቀስካቸው ጥቅሶች መሠረት እንኳ ብንሄድ አመስጋኝም ከሃዲም እንዲሆን መንገዱን የመራው አላህ ከሆነ አላህ ሰዎችን ወደ መልካምም ወደ ክፉም ይመራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ስለ ክፉ ሥራቸው ለምን ይጠየቃሉ? ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት መንገዱን የመራው አላህ ነው፡፡

2፥256 በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡

በሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ “ግደሉ፣ በኃይል አስልሙ” ወዘተ. ይላል፡፡ ይህንን ከአፍታ በኋላ በስፋት እንመለከታለን፡፡

ሰው የራሱ ነፃ ፈቃድ ባይኖረው ኖሮ ተጠያቂነት፣ ቅጣትና ሽልማት፣ ጀነትና ጀሃነም፣ ትክክል እና ስህተት ትርጉም አይኖራቸውም ነበር፤ ለዛ ነው አላህ፦ “የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ” ያለው፤ ለዛ ነው በምድር ላይ ከሓዲ እና አማኝ ያለው፦

18፥29 «እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ» በላቸው፡፡

64፥2 እርሱ ያ የፈጠራችሁ ነው፡፡ ከእናንተም ከሓዲ አለ፡፡ ከእናንተም አማኝ አለ፡፡ አላህም በምትሠሩት ሁሉ ተመልካች ነው፡፡

በሌሎች የቁርኣን ጥቅሶች መሠረት አላህ መጀመርያውኑ የሚያምነውንና የማያምነውን ራሱ ወስኖ ከፈጠረ ሰዎች እንዴት በገዛ ፈቃዳቸው ማመንም አለማመንም ይችላሉ?

ሰው በፈቃዱ በሚያምነት እምነት አላህ የሚሻውን ያንን ያመነውን ሰው ይምራል፤ ሰው በፈቃዱ በሚክደው ክህደት አላህ የሚሻውን ያንን የካደውን ሰው መቅጣት ይችላል፤ አማንያንን እና ከሃድያንን በቅጣትና በሽልማት እኩል አይመነዳም፦

5፥40 የሰማያትና የምድር ንግሥና የእርሱ ብቻ መኾኑን አላወቅክምን የሚሻውን ሰው ይቀጣል፡፡ ለሚሻውም ሰው ይምራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

3፥129 በሰማያት ያለው በምድርም ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ ለሚሻው ሰው ይምራል፤ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

38፥28 በእውነቱ እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችን የሠሩትን በምድር ውስጥ እንደሚያጠፉት እናደርጋለን? ወይስ አላህን ፊረዎቹን እንደ ከሓዲዎቹ እናደርጋለን?

ስለዚህ ሰው በነጻ ፈቃዱ ለማመን ወይም ለመካድ የፈቀደለት አላህ ነው። ያለ አላህ ፈቃድ ማንኛይቱም ነፍስ ልታምን ወይም ልትክድ አትችልም።

በሌሎች የቁርኣን ጥቅሶች መሠረት አላህ የሚያምኑትንና የማያምኑትን አስቀድሞ ወስኖ ፈጥሯል፡፡ ለማመንና ላለማመን ማንም ሰው ነፃ ምርጫ የለውም፡፡ አስቀድሞ ወስኖ የፈጠረው ራሱ አላህ በመሆኑ ለማመንም ሆነ ላለማመን ሰው ምርጫ የለውም፡-

ሱራ 10፡100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን (ችሎታ) የላትም፡፡ (አላህ ለከፊሎቹ እምነትን ይሻል)፡፡ በእነዚያም በማያውቁት ላይ ርክሰትን ያደርጋል፡፡”

ሱራ 9፡51 “አላህ ለኛ የጻፈልን (ጥቅም) እንጂ ሌላ አይነካንም እርሱ ረዳታችን ነው በአላህ ላይም ምእምናን ይመኩ በላቸዉ።

ሱራ 2:6 “እነዚያ የካዱት (ሰዎች) ብታስፈራራቸውም ባታስፈራራቸውም በነርሱ ላይ እኩል ነው፤ አያምኑም፡፡ አላህ በልቦቻቸው ላይ በመስሚያቸውም ላይ አትሞባቸዋል፤ በዓይኖቻቸውም ላይ መሸፈኛ አልለ፤ ለነሱም ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡”

ሱራ 4:88 “በመናፍቃንም (ነገር) አላህ በስራዎቻቸው ወደ ክሕደት የመለሳቸው ሲሆኑ ሁለት ክፍሎች የሆናችሁት ለናንተ ምን አላችሁ? አላህ ያጠመመውን ልታቀኑ ታስባላችሁን? አላህም ያሳሳተውን ሰው ለርሱ መንገድን ፈጽሞ አታገኝለትም።

ሱራ 5:18 “ይሁዶችና ክርስቲያኖችም እኛ የአላህ ልጆችና ወዳጆቹ ነን አሉ። ታዲያ በኀጢአቶቻችሁ ለምን ያሰቃያችኋል? አይደላችሁም እናንተ ከፈጠራችሁ ሰዎች ናችሁ፣ በላቸው፤ ለሚሻው ሰው ይምራል፤ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፤ የሰማያትና የምድርም በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው። መመለሻም ወደርሱ ብቻ ነው።”

ሱራ 5:40 “የሰማያትና የምድር ንግሥና የሱ ፦ የአላህ – ብቻ መሆኑን አላወቅክምን? የሚሻውን ሰው ይቀጣል፤ ለሚሻውም ሰው ይምራል፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው። አንተ መልክተኛ ሆይ እነዚያ በክሕደት የሚቻኮሉት ከነዚያ ልቦቻቸው ያላመኑ ሲሆኑ በአፎቻቸው አመንን ካሉትና ከነዚያም አይሁድ ከሆኑት ሲሆኑ አያሳዝኑህ፤ (እነርሱ) ውሸትን አዳማጮች ናቸው፤ ንግግሮችን ከቦታቸው ሌላ ያጣምማሉ፤ ይህንን (የተጣመመውን) ብትሰጡ ያዙት፤ ባትሠጡትም ተጠንቀቁ ይላሉ። አላህም መፈተኑን የሚሻበትን ሰው ለርሱ ከአላህ (ለመከላከል) ምንንም አትችልም። እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ማጥራትን ያልሻላቸው ናቸው፤ ለነርሱ በቅርቢቱ ዓለም በውርደት አላቸው፤ ለነርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከባድ ቅጣት አላቸው።”

ሱራ 14:4 “ከመልክተኛ ማንኛውንም፤ ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም፤ አላህም የሚሻውን ያጠማል፤ የሚሻውንም ያቀናል፤ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው።”

ሱራ 7:178 “አላህ የሚያቀናው ሰው ቅን እርሱ ነው፤ የሚያጠመውም ሰው እነዚያ ከሳሪዎቹ እነሱ ናቸው። ከጋኔንም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን፤ ለነርሱ በርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፤ ለነሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሉዋቸው፤ ለነሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሏቸው። እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፤ ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፤ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡”

ሱራ :13 “በሻንም ኑሮ ነፍስን ሁሉ ቅንነቷን (እምነቷንም) በሰጠናት ነበር፤ ግን ገሀነምን አጋንንትና ከሰዎች የተሰባሰቡ ሆነው በእርግጥ እመላለሁ ማለት ቃሉ ከኔ ተረጋግጧል፡፡”

ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ጥቅሶች ከቁርኣንና ከሐዲስ መጻሕፍት ላይ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በነዚህ ጥቅሶች መሠረት ሰዎች ለማመንም ሆነ ላለማመን ገነት ለመግባትም ሆነ ገሃነም ምንም ዓይነት ምርጫ አልተሰጣቸውም፡፡ አላህ ራሱ አስቀድሞ ወስኗል፡፡ አማኙን የሚያሳምነውም ሆነ ከሃዲውን የሚያስክደው አላህ ነው፡፡ የሰው ነፃ ምርጫ ከስሌቱ ውጪ ነው፡፡ ነገር ግን በሌሎች ቦታዎች ላይ ማመንም ሆነ አለማመን የሰዎች የግል ምርጫ መሆኑን በመናገር ይህንን ሐሳብ ያፈርሳል፡-

ሱራ 81፡27-18 “እርሱ የዓለማት መገሠጫ እንጂ ሌላ አይደለም። ከናንተ ቀጥተኛ መሆንን ለሻ ሰው መገሠጫ ነው።”

ሱራ 18:29 “እውነቱም፥ ከጌታችሁ ነው፤ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ፣ በላቸው፤ እኛ ለበደለኞች አጥርዋ በነሱ የከበበ የሆነችውን እሳት አዘጋጅተናል፤ (ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ፥ ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ፥ ይረዳሉ፤ መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቲም ምንኛ አስከፋች!”

ሱራ 53:38-41 “(እርሱም ኃጢአት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም። ለሰውም ሁሉ የሠራው እንጅ ሌላ የለውም። ሥራውም ሁሉ ወደፊት ይታያል። ከዚያም ሙሉውን ምንዳ ይመነዳዋል።”

በነዚህና በሌሎች በርካታ ቦታዎች ላይ ቁርኣን ለማመንም ሆነ ላለማመን ገነት ለመግባትም ሆነ ገሃነም ምርጫው የእነርሱ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ አማኙ የሚያምነውም ሆነ ከሃዲው የሚክደው በገዛ ምርጨው ነው፡፡ የአላህ ፍርድም በግብታዊ ምርጫ ሳይሆን በሰዎች ሥራ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ተነግሮናል፡፡ ይህ ግልፅ ግጭት ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው የሚመስሉ ጥቅሶችን ቢጠቅሱም ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስና የቁርኣን ሐሳብ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ ይህንን በመጠኑ ለማየት ለግጭት ቁጥር 3 የተሰጠውን ምላሽ ተመልከት፡፡

የቁርኣን ግጭቶች