የቁርኣን ግጭቶች – የሙሐመድ ኃላፊነት መልእክቱን ማድረስ ብቻ ወይስ ያልተቀበሉትን በኃይል ማስለም?

የሙሐመድ ኃላፊነት መልእክቱን ማድረስ ብቻ ወይስ ያልተቀበሉትን በኃይል ማስለም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

መልእክቱን ማድረስ ብቻ፡-

ሱራ 3፡20 “ቢከራከሩህም :- ፊቴን ለአላህ ሰጠሁ፤ የተከተሉኝም ሰዎች (እንደዚሁ ለአላህ ሰጡ) በላቸዉ፤ ለእነዚያም መጽሐፍን ለተሰጡት ሰዎችና ለመሀይሞቹ፦ሰለችማሁን? በላቸዉ፤ ቢሰልሙም በእርገጥ ተመሩ እምቢ ቢሉም በአንተ ላይ ያለበህ ማድረስ ብቻ ነዉ:: አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው::”

ያልተቀበሉትን በኃይል ማስለም፦

ሱራ 8፡38-39 “እውከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚሆን ድረስ ተጋደሉዋቸው፤ ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው።”

መልስ

ወደ ኢሥላም በሦስት ምክንያት የሚገባ ሰው እሥልምናው ተቀባይነት የለውም። አንደኛ ለተቃራኒው ጾታ ብሎ፣ ሁለተኛ ለገንዘብ ብሎ፣ ሦስተኛ ተገዶ።

ጅብ ቁርበት አንጥፉልኝ ያለው የማያውቁት አገር ሄዶ ነው እስልምና ግን ውስጠ ምስጢሩን ከንባብ ባለፈ በተግባር በሚያውቁት ሰዎች ፊት ይዋሻል፡፡ ይህ የሽብር ሃይማኖት ለመስፋፋት ሁሉንም አማራጮች ሲጠቀም እያየነው ነው፡፡ ይኸውም ደግሞ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ የታዘዘና ሙሐመድና የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ሲፈፅሙት እንደነበር የማይታበል ሃቅ ነው፡፡

ኢሥላም በግድ እመኑ ብሎ ምንሽርና ዝናር አይታጠቅም፥ በቀረርቶ፣ በሽለላ በፉከራ አያስገድድም፤ ምክንያቱም በሃይማኖት ማስገደድ የለም፤ የፈለገ ያምናል፥ ያልፈለገ ይክዳል፥ በኃላ የትንሳኤ ቀን የሚተሳሰበው አላህ ነው፦

2፥256 በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡

18፥29 «እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ» በላቸው፡፡

10፥99 ጌታህም በሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሰዎች ሁሉም የተሰበሰቡ ሆነው ባመኑ ነበር፡፡ ታዲያ አንተ ሰዎችን አማኞች እንዲኾኑ ታስገድዳለህን?

11፥28 «ሕዝቦቼ ሆይ! ንገሩኝ ከጌታዬ በግልጽ ማስረጃ ላይ ብሆን ከእርሱም ዘንድ የሆነን ችሮታ ነብይነት ቢሰጠኝ እና በእናንተ ላይ ብትደበቅባችሁ እናንተ ለእርሷ ጠይዎች ስትሆኑ እርሷን በመቀበል እናስገድዳችኋለን?» አላቸው፡፡

ነቢያችንም ከጌታቸው ወደ እርሳቸው የወረደውን መልእክት ግልጽ ማድረስ እንጅ ሌላ የለባቸውም፦

17፥15 መልእክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም፡፡

5፥67 አንተ መልክተኛ ሆይ! ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን አድርስ፡፡ ባትሠራም መልክቱን አላደረስክም፡፡

5፥99 በመልእክተኛው ላይ ማድረስ እንጅ ሌላ የለበትም፡፡ አላህም የምትገልጹትን ነገር የምትደብቁትንም ሁሉ ያውቃል፡፡

16፥82 ከኢስላም ቢሸሹም በአንተ ላይ ያለብህ ግልጽ ማድረስ ብቻ ነው፡፡

ባለፈው ምላሻችን እንደገለፅነው እነዚህ ጥቅሶች ቁርኣንን የማያነበውንና የእስልምናን ታሪክና አስተምህሮ በወጉ የማያውቀውን ሕዝብ ለማደናገር ከማገልገል ባለፈ ፋይዳ የላቸውም፡፡ የቁርኣን ሐታቾች እንደሚናገሩት በመካና መዲና ቀደምት ዘመናት የተነገሩት የሰላም ጥቅሶች በኋለኛው ዘመን በመዲና በወረዱት የሰይፍ ጥቅሶች ተሽረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢብን ከሢር ሱራ 2፡256 ላይ ሲያትት የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም፤ ማለትም ሰዎች እምነታቸውን እንዲቀይሩ ማስገደድ አስፈላጊ አለመሆኑን እንደሚናገር ካብራራ በኋላ እንዲህ ይላል፡-

“… ነገር ግን ይህ ጥቅስ በውጊያ ጥቅሶች ተሽሯል ስለዚህ ሁሉም የዓለም ህዝቦች ወደ እስልምና እንዲመጡ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ማናቸውም ሰዎች ያንን ለማድረግ ፍቃደኛ የማይሆኑ ከሆነ ወይም ጂዝያን ለመክፈል እምቢ የሚሉ ከሆነ እስኪገደሉ ድረስ ውጊያ ሊደረግባቸው ይገባል…” (Tafsir of Ibn Kathir, Al-Firdous Ltd., London, 1999: First Edition, Part 3, pp. 37-38)፡፡

ቁርኣን የሰዎችን ሃይማኖት በኃይል ማስለጥ አስፈላጊ መሆኑን እንዲህ ሲል ይናገራል፡-

“ሁከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሏቸው፡፡ ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡” (የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ 8፡39)

“የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡5)

በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ የሚከተለው ዘገባ ሰፍሮ እናገኛለን፡

“ኢብን ዑመር እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤ ሰዎች ከአላህ በስተቀር ሊመለክ የሚገባው እንደሌለና ሙሐመድም ደግሞ መልእክተኛው መሆኑን እስኪመሰክሩ ድረስ እንዲሁም ሶላትን ደንቡን ጠብቀው እስኪሰግዱ ድረስና ዘካትን እስኪሰጡ ድረስ እንድዋጋቸው (በአላህ) ታዝዣለሁ፡፡ ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ በእስልምና ሕግ ከተደነገገው በስተቀር ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ከእኔ ይታደጋሉ፤ ድርሻቸውም በአላህ ይታሰብላቸዋል፡፡” (Sahih Al-Bukhari; Vol. 1 Book 2, Number 24)

“ነቢዩ ‹ማንኛውንም እስልምናን ለቆ የሚወጣ ሰው ግደሉት› ብለዋል፡፡” (Sahih al-Bukhari, 52:260; 83:37; 84:57; 89:271; 84:58; Abu Dawud, 4346)

ሙሐመድና የእስላም ሊቃውንት እንዲህ የሚሉ ከሆነ አንተ ተቂያ እየፈፀምክ ነው ማለት ነው፡፡ እስላማዊ ምንጮች “በሃይማኖት ማስገደድ የለም” የሚለውን ቃል በማፍረስ “በኃይል አስልሙ፤ ከሃይማኖቱ የሚወጡትን ግደሉ” ይላሉ፡፡ አንተ ግን “ኧረ በጭራሽ እንዲህ ያለ ነገር የለም” ብለህ ትዋሻለህ፡፡

ነገር ግን ከሃድያን ወሰን አልፈው ሊገሉን ሲመጡ እጅና እግራችንን አጣጥፈን መቀመጥ ሳይሆን በአላህ መንገድ መጋደል ነው፦

2፥190 እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን በአላህ መንገድ ተጋደሉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎን አይወድምና፡፡

2፥193 ሁከት እስከማይገኝ እና ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሉዋቸው፡፡ ቢከለክሉም ወሰንን ማለፍ በበዳዮች ላይ እንጂ የለም ወሰን አትለፉባቸው፡፡

2፥194 “በእናንተም ላይ ወሰን ያለፈባችሁን ሰው በእናንተ ላይ ወሰን ባለፈው ብጤ በእርሱ ላይ ወሰን እለፉበት”፡፡ አላህንም ፍሩ አላህ ከሚፈሩት ጋር መኾኑንም ዕወቁ፡፡

“ወሰን አትለፉ” የሚለው ይሰመርበት። ወሰን ያለፈብንስ? “በእናንተም ላይ ወሰን ያለፈባችሁን ሰው በእርሱ ላይ ወሰን እለፉበት” በተባለው መሠረት እንጋደለዋለን። ይህ የሚሆነው ሰላም ሆኖ ሁከት እስከሚጠፋ ድረስ እና ሃይማኖት ለአላህ እስከሚሆን ድረስ ነው፤ “ዲን” دِين ማለት ደግሞ “ሃይማኖት” “ፍትህ” “ፍርድ” “ሕግ” “መርህ” ማለት ነው፤ ይህ ዲን ለአላህ የሚሆነው የዲኑ ቀን ነው፤ አላህ የዲኑ ቀን ባለቤት ነው፦

1፥4 የፍርዱ ቀን ባለቤት ለኾነው፡፡

26፥82 ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለእኔ ሊምር የምከጅለው ነው፡፡

37፥20 «ዋ ጥፋታችን! ይህ የፍርዱ ቀን ነው» ይላሉም፡፡

እስልምና የተዋጉትን ብቻ እንደሚዋጋ የምትናገሩት ተረት ሐሰት መሆኑን ልቦናችሁ ያውቀዋል፡፡ ሙሐመድ መላውን አረብያ ያሰለመው በሰይፉ እንጂ በሰላማዊ ስብከት አልነበረም፡፡ ተከታዮቹም ከእስፔን እስከ ቻይና የሚገኘውን ምድር የወረሩት በጦር ኃይል እንጂ ከረሜላ በማደል አልነበረም፡፡ ቁርኣን ሰዎችን በኃይል ማስለም እንደሚያስፈልግ እንዲህ ይናገራል፡-

“የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡5)

ሙስሊሞች በአቅራቢያቸው የሚገኙትን ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች እንዲዋጉና እንዲገድሉ ያዛል፡-

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በአቅራቢያችሁ ያሉትን ከሓዲዎች ተዋጉ፡፡ ከእናንተም ብርታትን ያግኙ፡፡ አላህም ከሚጠነቀቁት ጋር መኾኑን ዕወቁ፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡123)

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡73)

ሙሐመድ እምነቱን ያልተከተሉትን ወገኖች በኃይል ለማስለም እንደተላከ በሐዲስ ተናግሯል፡-

“…ሰዎች ከአላህ በስተቀር ሊመለክ የሚገባው እንደሌለና ሙሐመድም ደግሞ መልእክተኛው መሆኑን እስኪመሰክሩ ድረስ እንዲሁም ሶላትን ደንቡን ጠብቀው እስኪሰግዱ ድረስና ዘካትን እስኪሰጡ ድረስ እንድዋጋቸው (በአላህ) ታዝዣለሁ፡፡ ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ በእስልምና ሕግ ከተደነገገው በስተቀር ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ከእኔ ይታደጋሉ…” (Sahih Al-Bukhari; Vol. 1 Book 2, Number 24)

ሙሐመድ ሰዎችን በኃይል ለማስለም እንደተላከ እንዲህ በግልፅ ተናግሮ ሳለ ተጻራሪውን ልትነግረን አንተ ምን ሥልጣንና ዕውቀት አለህ? ራስህን ከአላህና ከመልእክተኛው በላይ ልታስቀምጥ ተመኘህ? እውነቱ ግልፅ ነው፡፡ እስልምና የተዋጉትንም ያልተዋጉትንም መዋጋትን ያዛል፡፡ “ወሰን አትለፉ” የተባለው ሰዎቹ ከሰለሙ በኋላ ስላለው ሁኔታ እንጂ ከዚያ በመለስ ስላለው ሁኔታ አይደለም፡፡

“እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን በአላህ መንገድ ተጋደሉ” እስከ መቼ? “ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ” መቼ ነው ዲን ለአላህ የሚሆነው? የዲኑ ቀን በተባለው በትንሣኤ ቀን፤ እስከዛ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ወሰን አልፎ በሚመጣው ላይ ለእነዚያ ለሚገደሉት ምእመናን እነርሱ የተበደሉ በመኾናቸው መጋደል ተፈቀደላቸው፦

22፥39 ለእነዚያ ለሚገደሉት ምእመናን እነርሱ የተበደሉ በመኾናቸው መጋደል ተፈቀደላቸው፡፡

ሁለት የተለያየ አውድ ያላቸውን ጥቅሶች ነው ያገናኘኸው፡፡ ሱራ 22፡39 ሙሐመድ ከመካ ኮብልሎ ገና ወደ መዲና ሲገባ የተነገረ ሲሆን መዋጋትን ለማዘዝ የመጀመርያው ጥቅስ መሆኑን ኢብን ከሢር በተፍሲሩ ገልጿል http://www.recitequran.com/en/tafsir/en.ibn-kathir/22:39 ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስልምና አሸባሪነቱ እየጨመረ በመምጣት በመጨረሻም ፍጹም አሸባሪ ሆኗል፡፡ ሙሐመድ ገና ነቢይነቱን ሲያውጅ ሰላማዊ ሰባኪ ነበር፣ ወደ መዲና ሲገባ አካባቢ ተከላካይ ሆነ፣ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ ወራሪና በማስገደድ የሚያሰልም ሆነ፡፡ ከዚህ የተነሳ እስልምና ሰላምንና ጦርነትን በተመለከተ እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተምሕሮ ያለው ሃይማኖት ለመሆን በቅቷል፡፡ የሰይፍ ጥቅሶች ሰላማዊ ጥቅሶችን ሽረዋል ብሎ ማለት አንድ ነገር ነው፤ የእስልምናን አሸባሪነት ክዶ ሰላማዊ መሆኑን መስበክ ግን እፍረት አልባ ቅጥፈት ነው፡፡ ትዝብት ላይ ይጥልሃል፡፡

የቁርኣን ግጭቶች