የቁርኣን ግጭቶች – ሙስሊሞች ስንት እናቶች ናቸው ያሏቸው?

25. ሙስሊሞች ስንት እናቶች ናቸው ያሏቸው?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

አንዲት እናት ብቻ፡-

ሱራ 58:2 “እነዚያ ከናንተ ውስጥ ከሚስቶቻቸው እንደናቶቻቻን ጀርባዎች ይሁኑብን በማለት የሚምሉ እነሱ እናቶቻቸው አይደሉም፤ እናቶቻቸው አሊያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም በዚህ ቃል ከንግግር የተጠላንና ውሸትን በእርግጥ ይናገራሉ፤ አላህም ለሚጸጸት ይቅርባይ መሃሪ ነው።”

ብዙ እናቶች፡-

ሱራ 33:6 “ነቢዩ፣ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፤ የዝምድና ባለ ቤቶችም ከፊላቸው በከፊሉ (ውርስ) በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ከምእምናንና ከስደተኞቹ ይልቅ የተገባቸው ናቸው፤ ግን ወደ ወዳጆቻችሁ (በኑዛዜ) መልካምን ብትሰሩ (ይፈቀዳል)፤ ይህ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ነው።”

መልስ

58፥2 “እነዚያ ከእናንተ ውስጥ ከሚስቶቻቸው እንደ እናቶቻቻን ጀርባዎች ይሁኑብን በማለት የሚምሉ እነርሱ እናቶቻቸው አይደሉም፤ እናቶቻቸው እነዚያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም በዚህ ቃል ከንግግር የተጠላንና ውሸትን በእርግጥ ይናገራሉ”፤ አላህም ለሚጸጸት ይቅርባይ መሓሪ ነው።

እዚህ ዐውድ ላይ ወንዶች ሚስቶቻቸውን፦ “እንደ እናቶቻቻን ጀርባዎች ይሁኑብን” በማለት ይምላሉ። አላህ ሚስትን ለባል እናት አላደረገም። እናት የሚባሉት ሚስት ሳትሆን የወለደች ናት፦

33፥4 አላህ ለአንድ ሰው በሆዱ ውስጥ ሁለትን ልቦች አላደረገም፡፡ “ሚስቶቻችሁንም እነዚያን ከእነርሱ እንደናቶቻችሁ ጀርባዎች ይሁኑብን የምትሏቸውን እናቶቻችሁ አላደረገም”፡፡ ልጅ በማድረግ የምታስጠጓቸውንም ልጆቻችሁ አላደረገም፡፡ ይህ በአፎቻችሁ የምትሉት ነው፡፡ አላህም እውነቱን ይናገራል፡፡ እርሱም ትክክለኛውን መንገድ ይመራል፡፡

“እናቶቻቸው እነዚያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው” የሚለው ይሰመርበት። “ብቻ” ብሎ የገባው ገላጭ ቅጽል “ኢነማ” إِنَّمَا ሲሆን ብዙ ቦታ በአንጻራዊት ደረጃ የሚገባበት ጊዜ አለ፥ ለምሳሌ፦

64፥15 “ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁ ለእናንተ መፈተኛ ብቻ ናቸው”፤ አላህም እርሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ አልለ፡፡

“ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁ ለእናንተ መፈተኛ ብቻ ናቸው” ናቸው ማለት ከፈተና ሌላ መደሰቻ አይደሉም ማለት እንዳልሆነ ዐውዱ ላይ እናት የሚባሉት ወላጅ እናት ብቻ ነው የሚለው ሚስትን በተመለከተ ብቻ ነው። ሚስት ለባል በፍጹም እናት አይደለችም፥ እናትም ለልጇ ሚስት አይደለችም፥ ሁለቱም የተለያየ ደረጃ አላቸው።

ግጭቱን ከመፍታት ይልቅ ሌላ ግጭት ነው ያሳየኸን፡፡ የቁርኣን ደራሲ እንዲህ የቃላትን ትክክለኛ ትርጉም የሚለውጥ አነጋገር ከሚጠቀም በግልፅ መናገር ይችል ነበር፡፡ ሱራ 33፡4 የማደጎ ልጅን “ልጅ” ብሎ መጥራትንና የልጅነት መብት መስጠትን የሚከለክለውን እስላማዊ ሕግ የሚያጠነክር ነው፡፡ ሚስቶችንም “እናት” ብሎ መጥራት የተከለከለው በዚያው አውድ ነው፡፡ ስለዚህ ያልወለድናቸው ልጆቻችን አይደሉም፤ ያልወለዱን ሴቶችም እናቶቻችን አይደሉም ማለት ነው፡፡

የነቢያችን ባልተቤቶች ለምዕመናን የሃይማኖት እናቶች ናቸው፦

 33፥6 “ነቢዩ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው”፡፡

እዚህ ዐውድ ላይ እናት የተባሉት ቃል በቃል እማሬአዊ ሳይሆን ፍካሬአዊ ነው። ለምሳሌ በባይብል እግዚአብሔር አንድ አባት ተብሏል፦

ሚልክያስ 2፥10 “ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን?” አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? “የአባቶቻችንን” ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?

 እግዚአብሔር አንድ አባት ከሆነ እዛው አንቀጽ ላይ “አባቶቻችን” የተባሉት ምንድን ናቸው? አይ! እግዚአብሔር አባት የተባለበት እና አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ አባት የተባሉበት የተለያየ አጠቃቀም ነው ከተባለ እንግዲያውስ ከላይ ወላጅ እናት የተባለችበት እና የነቢያችን ባልተቤቶች እናት የተባሉበት ለየቅ የሆነ ሁለት የተለያየ አጠቃቀም ነው።

የመጽሐፍ ቅዱሱን ራስህ በትክክል መልሰኸዋል፡፡ የቁርአኑን ግን በዚያ መንገድ መረዳት ፈፅሞ አይቻልም፡፡ የመጀመርያው ጥቅስ ሙስሊሞች አንዲት እናት ብቻ እንዳለቻቸውና ሌሎች ሴቶችን በተምሳሌታዊ መንገድ “እናቶች” ብለው መጥራታቸው ውሸትና በአላህ ዘንድ የተጠላ ንግግር እንደሆነ ይገልፃል፡-

ሱራ 58:2 “እነዚያ ከናንተ ውስጥ ከሚስቶቻቸው እንደናቶቻቻን ጀርባዎች ይሁኑብን በማለት የሚምሉ እነሱ እናቶቻቸው አይደሉም፤ እናቶቻቸው አሊያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም (በዚህ ቃል) ከንግግር የተጠላንና ውሸትን በእርግጥ ይናገራሉ፤ አላህም (ለሚጸጸት) ይቅርባይ መሃሪ ነው።”

ቁርኣን በዚህ ቦታ እየተቃወመ የሚገኘው ከወለዱን እናቶች ውጪ የሚገኙትን ሴቶች በምንም መንገድ “እናት” ብሎ መጥራት እንደማይቻል ነው፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ የተጠቀሱት ሙስሊሞች ሚስቶቻቸውን በተምሳሌታዊ መንገድ “እናቶች” ብለው እየጠሩ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን የቁርኣን ደራሲ በዚህ አስታኮ ከወለዷቸው እናቶች ውጪ የትኞቹንም ሴቶች “እናቶች” ብለው መጥራት እንደማይችሉ ይገልጿል፡፡ “እናቶቻቸው አሊያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው” የሚለው የትኛዋንም ሴት ያጠቃልላል፡፡

ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ የሙሐመድ ሚስቶች ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የሙስሊሞች እናቶች እንደሆኑ ይናገራል፡-

ሱራ 33:6 “ነቢዩ፣ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፤ የዝምድና ባለ ቤቶችም ከፊላቸው በከፊሉ (ውርስ) በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ከምእምናንና ከስደተኞቹ ይልቅ የተገባቸው ናቸው፤ ግን ወደ ወዳጆቻችሁ (በኑዛዜ) መልካምን ብትሰሩ (ይፈቀዳል)፤ ይህ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ነው።”

ጡት ያጠቡን ሴቶችም ባይወልዱንም እናቶቻችን መሆናቸውን የሚናገር ሌላ ጥቅስ አለ፡-

4:23 “እናቶቻችሁ፣ ሴት ልጆቻችሁም፣ እኅቶቻችሁም፣ አክስቶቻችሁም፣ የሹሜዎቻችሁም፣ የወንድም ሴቶች ልጆችም፣ የእኅት ሴቶች ልጆችም፣ እነዚያም ያጠቡዋችሁ እናቶቻችሁ…”

የቁርኣን ደራሲ “እናቶቻቸው አሊያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው” በማለት ከዘጋ በኋላ የሙሐመድ ሚስቶችና ያጠቡ ሴቶች የሙስሊሞች እናቶች መሆናቸውን መናገሩ ግፅ ግጭት ነው፡፡ ይህንን ማስታረቅ የሚችል የቋንቋ ሕግ የለም፡፡

የቁርኣን ግጭቶች