የጀነት በር ተከፍቷል!
ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ተለይተው ለጥፋት እንደተዳረጉ ያምናሉ፡፡ ትክክለኛ መኖርያችን የነበረው ተድላና ደስታ የተሞላበት ገነት ቢሆንም አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ከገነት ስለተባረርን በሰቆቃ በተሞላው ምድር እንድንኖር ተወስኖብናል፡፡ ነገር ግን ቸርና አዛኝ የሆነው ፈጣሪ አምላካችን ከእርሱ ተለይተን ለዘላለም እንድንጠፋ ስላልወደደ የገነትን በር ድጋሜ ከፍቶታል፤ የመመለሻ መንገዱንም እጅግ አቅልሎልናል፡፡ በቁርአንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችን ስናጠና ፈጣሪ አምላካችን ሩቅ ሆኖ መመርያዎችን ከመላክ ይልቅ ወደ ሰው ልጆች ቀርቦ ከእርሱ ጋር መኖር የሚያስችላቸውን ከእነርሱ የሚጠበቁትን መስፈርቶች ራሱ ባዘጋጀው መንገድ ሲያሟላ እንመለከታለን፡፡
ከተከታዮቹ አምስት ታሪኮች መካከል አራቱ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቁርአን ውስጥ ተመዝግበዋል፡፡ ውዱ ሙስሊም ወዳጄ! እነዚህ ታሪኮች እግዚአብሔር ካንተ የሚጠበቁትን መስፈርቶች አሟልቶልህ ወደ ገነት ሊመልስህ የሠራውን ሥራ የሚያሳዩ ናቸውና እባክህን በጥንቃቄ አጥናቸው፡፡
በኃጢአታቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ራቁትነታቸውን ለመሸፈን እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ልብስ አዘጋጀላቸው፡፡ ለቃኤልና ለአቤል እግዚአብሔር ትክክለኛውን የመሥዋዕት መንገድ አዘጋጀ፡፡ ለአብርሃም ልጁን ለመታደግ ታላቅ መሥዋዕትን አዘጋጀለት፡፡ ለሙሴና ለእስራኤላውያን ለተወሰኑ ኃጢአቶች ስርየት የሚሆን የመሥዋዕት ስርአትን በካህናትና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አማካይነት አቋቋመላቸው፡፡ ለሰው ልጆች በሙሉ ደግሞ የመሥዋዕት ስርአቶችን ወደ ፍጻሜ የሚያመጣ ቤዛ ቅዱስ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጠ፡፡ ያለፉት የእንስሳት መሥዋዕቶች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የኃጢአት ይቅርታንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት ለማደስ የተደረገልንን ቤዛነት ትዕምርታዊ በሆነ መንገድ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ይህንን ወሳኝ እውነታ በመዘንጋት በእግዚአብሔር ማመን፣ መልካም ሥራዎችን መሥራትና መልካም ነገርን መመኘት ብቻ በቂ እንደሆነ የሚያስቡ ወገኖች ለእግዚአብሔርና እርሱ ላዘጋጀው መንገድ ክብርን ባለመስጠታቸው ምክንያት ከስኬት ይጎድላሉ፡፡ ስለዚህ እባክህን ከላይ የተጠቀሱትን አምስቱን ታሪኮች በጥንቃቄ አጥናቸው፡፡
አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ)
አዳምና ሔዋን ኃጢአትን ከሠሩ በኋላ ራቁታቸውን ሆኑ፤ እፍረትና ፍርሃትም ሕይወታቸውን ተቆጣጠረ፡፡ በገዛ ፈጣሪያቸው ላይ ማመጻቸው ለውርደት ዳረጋቸው፡፡ የገዛ ራቁትነታቸውን ለመሸፈን የሞከሩት በቅጠል ነበር፡፡ በኃጢአታቸው ምክንያት የመጣባቸውን ይህንን እፍረትና ውርደት ለመሸፈን ያደረጉት ጥረት በእግዚአብሔር ዕይታ በቂ አልነበረም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ከተከለከሉት ዛፍ ቢበሉ ሞትን እንደሚሞቱ ነግሯቸው ነበር፡፡ ይህ ሞት መንፈሳዊ ሞት ሲሆን ከገነት በመባረራቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የግል ሕብረት በማጣት የሚመጣባቸው ነው፡፡ አካላዊ ሞት ደግሞ እርሱን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ አንድ ሰው የሞት ፍርደኛ ከሆነ አክትሞለታል፤ ሟች ነው! ስለዚህ እግዚአብሔር ጣልቃ በመግባት እፍረታቸውን የሚሸፍኑበትን የእንስሳን ቆዳ ሰጣቸው፡፡ ይህም አጥፊ ለሆነው የኃጢአት ውጤት የሚቀርበውን መሥዋዕት የሚያመለክት ነው፡፡ (ተውራት፣ ዘፍጥረት 3፡7፣ 21)፡፡ በቁርአን ውስጥም አላህ ራቁትነታቸውን የሚሸፍኑበት ልብስ እንደሰጣቸው ተነግሯል (ሱራ 7፡26)፡፡
ተውራት፣ ዘቡርና ኢንጂል “ኃጢአት” የሚለውን ቃል በስህተት መጥፎ ሥራን ከመሥራት የዘለለ ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በሰው ልጆች ሁሉ ልብ ውስጥ ከሚገኝ አመፀኛ አስተሳሰብ የተነሳ መጥፎ ሐሳቦችን በማሰብ ጭምር የሚፈፀም ክፉ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍፁም ቅዱስ በመሆኑ ምክንያት ኃጢአት ከእርሱ ዕይታ አኳያ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ፍርድ ይገባቸዋል (ሱራ 16፡1)፡፡
እፍረት የኃጢአት ውጤት ነው፡፡ በልብ የታሰበ ኃጢአት በሌለበት ቦታ እፍረት የለም፡፡ ለዚህ ነው ህፃናት ራቁታቸውን ቢሆኑ የማያፍሩት፡፡ በክርስትና የውርስ ኃጢአት ማለት ሰው ኃጢአትን ከመሥራት ዝንባሌ ጋር ይወለዳል ማለት እንጂ ራሱን ከማወቁ በፊት ኃጢአት ሠርቷል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በፍጥረቱ የቁጣ ልጅ ነው፤ ለዚህም ምክንያቱ ከተጨባጭ ኃጢአት ጋር መወለዱ ሳይሆን ኃጢአትን ከመሥራት ዝንባሌ ጋር በመወለዱ ነው (ኤፌሶን 2፡3)፡፡ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የሆነው አዳም ኃጢአትን በመሥራቱ ምክንያት ሁላችንም ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ነን (ሮሜ 5፡12)፡፡ ስንወለድ ከተጨባጭ ኃጢአት ጋር አልተወለድንም፡፡ ነገር ግን ኃጢአትን ከመሥራት ዝንባሌ ጋር ስለተወለድን ኃጢአተኞች የመሆናችን ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ አይቻለንም፡፡
ቃኤልና አቤል (ቃቢልና ሀቢል)
ስለ ቃኤልና አቤል መሥዋዕት በቁርአን ውስጥ በዝርዝር አልተነገረም (ሱራ 5፡27)፡፡ ተውራትና ኢንጂል እንደሚነግሩን ከምድር ዘር የነበረውን የቃኤልን መሥዋዕት እግዚአብሔር ያልተቀበለ ሲሆን የእንስሳ መሥዋዕት የሆነውን የአቤልን መሥዋዕት ተቀብሏል (ዘፍጥረት 4፡3-7)፡፡ ደግሞም አቤል መሥዋዕቱን በእምነት ስላቀረበ ተቀባይነትን እንዳገኘ ተነግሯል (ዕብራውያን 11፡4)፡፡ አቤል ለምንድን ነበር የእንስሳን መሥዋዕት ማቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ ያመነው? አዳምና ሔዋን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ከእፍረት እንዲተርፉ የእንስሳን ቆዳ በማልበሱ ምክንያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ ፈልጎ ይሆንን? የሙሴን ታሪክ ስንመለከት ይህ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል፡፡
አብረሃም (ኢብራሂም)
አብረሃም ልጁን እንዲሠዋ ከታዘዘ በኋላ በልጁ ፈንታ የሚቀርብን የበግ መሥዋዕት እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጀ (ሱራ 37፡107፣ ተውራት ዘፍጥረት 22)፡፡ ያ የእንስሳ መሥዋዕት እንደ ቀላል የአምልኮ ተግባር ብቻ የሚቆጠር አይደለም፤ ምክንያቱም ቁርአን ክብደቱን ሲገልፅ “በታላቅ እርድ (መሥዋዕትም) ተቤዠነው” ይላልና፡፡ ልጅ ከእንስሳ እጅግ የላቀ ዋጋ አለው፡፡ እንስሳው “ታላቅ” የተባለው ሌላ ፍፁም የሆነን መፃዒ መሥዋዕት ትዕምርታዊ በሆነ መንገድ ስለሚያሳይ ይሆን?
ሙሴ (ሙሳ)
ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ኃጢአት ማስተሰርያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የተፈጠሩትን እንስሳት እንዲሠዋ ታዘዘ (ተውራት ዘኁልቁ 19፡1-10፣ ሌሎችም ብዙ ጥቅሶች)፡፡
እንደ ዩሱፍ አሊና መውዱዲ ያሉ ሙስሊም ሐታቾች ሱራ አል-በቀራ 2፡67-74 ላይ የሚገኘው ይህንን አስደናቂ ታሪክ የሚያስታውስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የአይሁድ ካህናትና ቤተ መቅደሱም ሱራ 17፡1-7፣ 5፡44 ላይ ተጠቅሰዋል፡፡ ለኃጢአት ሥርየት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚቀርቡት የእንስሳት መሥዋዕቶች የተውራት ማዕከላዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የአዳምና የሔዋን እፍረት እንደተሸፈነላቸው ሁሉ ያለ ደም መሥዋዕት የሚሸፈን እፍረት የለም፡፡ ተውራት ሌዋውያን 17፡11 ላይ እንዲህ ይላል፡-
“የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት።”
መሲሁ ኢየሱስ
ብዙ መሥዋዕቶች በተደጋጋሚ ቢቀርቡም ለሰው ልጆች የኃጢአት ችግር ግን ዘላቂ መፍትሄ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ችግሩ ደግሞ እንስሳት የሰው ልጆችን ሰብዓዊ ዋጋ የሚመጥኑ አለመሆናቸው ነው፡፡ ፍፁምና ኃጢአት አልባ የሆነውን መፃዒ መሥዋዕት የሚያመለክቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ልክ እንደ ባንክ ቼክ ዓይነት ናቸው፡፡ የባንክ ቼክ ለገንዘብ እንደ መያዣ ያገለግላል ነገር ግን አንዴ ገንዘቡ እጃችሁ ከገባ ቼኩ አያስፈልጋችሁም፡፡
የእንስሳት መሥዋዕት የላቀውን መሥዋዕት አመላካች ነው፡፡ ያ መሥዋዕት አንዴ ከተፈፀመ የእንስሳት መሥዋዕት አያስፈልጋችሁም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ (የሕያ) ኢየሱስን “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ሲል ነበር የጠራው (ኢንጂል ዮሐንስ 1፡29)፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት፣ እፍረት፣ ፍርሃትና ወቀሳ ለማስወገድ በሰልጆች ምትክ ሆኖ የሞትን ፅዋ ተቀብሏል (ኢንጂል ማርቆስ 10፡45)፡፡
ኢንጂል ሉቃስ 24፡44-47 እንዲህ ይላል፡-
እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።
እግዚአብሔር ኢየሱስን በሦስተኛው ቀን ከሙታን በማስነሣትና በአርባኛው ቀን ወደ ራሱ በማንሳት ለሥራው መስክሯል (ኢንጂል፣ የሐዋርያት ሥራ 1፡3፣ 1ቆሮንቶስ 15)፡፡ ይህ ፍፁማዊ ይቅርታን የማግኛ መንገድ ከገዛ መንገዳቸው ተመልሰው እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን መንገድ ለመቀበል ፈቃደኛ ለሆኑት ሰዎች ሁሉ የተዘጋጀ መሆኑን ተውራት፣ ዘቡርና ኢንጂል ይናገራሉ፡፡ ቁርአንም ሙስሊሞች በነዚህ መጻሕፍት ማመን እንደሚገባቸው ይናገራል (ሱራ 5፡46-48)፡፡
ከእግዚአብሔር ዕይታ አኳያ እኛ በኃጢአታችን ምክንያት የተራቆትንና እፍረት ውስጥ ያለን ነን፡፡ ነገር ግን በፈሰሰልን በልጁ ቅዱስ ደም አማካይነት ጽድቅን መጎናጸፍ እንችላለን፡፡ ይህ የምሥራች ከአዳም ዘመን ጀምሮ ተገልጧል፡፡ በመሲሁ ኢየሱስ በኩል ደግሞ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ለሰው ልጆች ሁሉ ዝግጁ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ከዚህ ተሽሎ ሊሽረው የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ብቸኛው ለሰው ልጆች ሁሉ በቂ፣ አስተማማኝና ፍፁም የሆነ የመዳኛ መንገድ ነው፡፡
—————
እንዲያው ይሁን እንኳ ብንል የሚከተሉትን በረከቶች ሊተካ የሚችል ምን የተሻለ መንገድ ይገኛል?
- ፍፁም የሆነ የኃጢአት ይቅርታ
- ከእፍረት ወደ ክብር መመለስ
- ከፍርሃትና የኅሊና ክስ ነፃ መሆን
- የተሟላ ሕይወት
- እንደ እግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ ለመመላለስ የሚያስችል የመንፈስ ቅዱስ ኃይል
—————
ኢየሱስ ነቢያት አስቀድመው የተነበዩለት የዓለም አዳኝ ነው፤ ይህንን የማድረግ ብቃት ያለው እርሱ ብቻ ነው (ኢንጂል ማርቆስ 2፡6፣ ሉቃስ 24፡44-47፣ ዮሐንስ 11፡25-26)፡፡ የእርሱ መልእክት የተለየ ነው፡፡ በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡- እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፣ እኛን ይወደናል – ሁለችንም ኃጢአተኞች በመሆናችን ከእርሱ ተለይተን ጠፍተናል – ሃይማኖታት አቅጣጫቸውን ስተዋል፣ መልካም ሥራዎቻችንም እኛን ለማዳን በቂ አይደሉም – ብቃት ያለውና ለችግራችን መፍትሄው ኢየሱስ ብቻ ነው! እርሱ ቅጣታችንን ተቀብሎልናል – ንስሐ ግቡ – እርሱን ተከተሉ! ውዱ ወዳጄ፣ እውነተኛና ፍፁም የሆነውን መሥዋዕት፣ ዘላለማዊና ሕያው የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን ኢየሱስን ልትታመነው ትሻለህን? ምላሽህ አዎንታዊ ከሆነ ተከታዩን ጸሎት ከልብህ ሆነህ በመጸለይ አዲስ ሕብረት ከፈጣሪህ ጋር መጀመር ትችላለህ፡-
“ሁሉን ቻዩ አምላኬ ሆይ በቅዱስ ቃልህ ውስጥ የተገለጸውን ያንተ መንገድ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመከተል ከመንገድህ ስቼ ጠፍቻለሁ፡፡ አቤቱ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለላክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ የኃጢአት ዕዳዬን ከፍሎታል፡፡ ከሙታን ተነሥቶ ለዘላለም ሕያው መሆኑን አምናለሁ፡፡ ከአሮጌው መንገዴ ተመልሼ እንደ ፈቃድህ መኖር እችል ዘንድ ቅዱሱን መንፈስህን ስጠኝ፡፡ ስለወደድከኝና በልጅህ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ከአንተ ጋር አዲስ ሕብረት እንዲኖረኝ መልካም ፈቃድህ ስለሆነ አመሰግንሃለሁ፤ አሜን!”
እንኳን ደስ ያለህ! በእምነትህ ለማደግ እባክህን መጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፣ ዕለት ዕለትም ጸልይ፡፡ እግዚአብሔር የሰጠህን ይህንን አዲስ ሕይወት መኖር ትችል ዘንድ ሊያግዙህ የሚችሉትን የኢየሱስ ተከታዮች ሕብረት ተቀላቀል፡፡ ጥያቄ ወይንም አስተያየት ካለህ ወይንም እገዛም የሚያሻህ ከሆነ በተከታዩ አድራሻ ብታገኘኝ ልረዳህ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ ewnet4hulu@gmail.com