የኢየሱስና የአብ አንድነት የዓላማ ብቻ ወይንስ የባሕርይም ጭምር?
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 10:30 ላይ “እኔ እና አብ አንድ ነን” በማለት ተናግሯል፡፡ ማናችንም እንደምናውቀው በሰው ልጆች ታሪክ እንዲህ ብሎ የተናገረ ነቢይ የለም፡፡ ሙስሊሞች እንደ መጨረሻው ነቢይ የሚቆጥሩት ሙሐመድ አንድም ጊዜ “እኔና አላህ አንድ ነን” ብሎ ተናግሮ አያውቅም፡፡ እንዲህ ያለው ንግግር አንድ አካል አምላክነቱን እያወጀ ስለመሆኑ ግልፅ ማስረጃ ነው፡፡ ታድያ ሙስሊም ወገኖቻችን ይንን ግልፅ የኢየሱስ ንግግር ለማስተባበል የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ በመደበኛነት የሚጠቀሙት ሙግት ኢየሱስ ስለ ዓላማ አንድነት እንጂ ስለ ባሕርይ አንድነት እየተናገረ አይደለም የሚል ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ኦሪጅናሉን የግሪክ ንባብ በማጣቀስ ይህንን ማስረጃ ለማጣጣል ጥረት ያደረገውን የአንድ ሙስሊም ሰባኪ ሙግት የምንመለከት ይሆናል፡፡ ይህ አብዱል የተለያዩ ኑፋቄ ቡድኖችን ሙግቶች በመቅዳት የሚታወቅ ሲሆን የሙግቶቹን ምንጭ ባለመጥቀስ የገዛ ራሱ ሙግት በማስመሰል ያቀርባል፡፡ ምንም ዓይነት የግሪክ ቋንቋ ዕውቀት ሳይኖረው ልክ ግሪክ እንደሚችል ሰው በራስ በመተማመን ትንታኔዎችን ይሰጣል፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
መንደርደርያ
አንድ ጊዜ አንዱን ሰው፦ ”ኢየሱስ እኔ አምላክ ነኝ አምልኩኝ” ያለበትን ጥቅስ አሳየን ብዬ ስጠይቀው፣ አንተም፦ ኢየሱስ ”እኔ አምላክ አይደለሁም አታምልኩኝ” ያለበትን ጥቅስ አሳየን ብሎ አረፈው። እኔም በመቀጠል፦ ኢየሱስ እኔ አምላክ አይደለሁም አታምልኩኝ ያለበትን ጥቅስ ባይገኝ ኢየሱስ አምላክ መሆኑንና መመለኩን ያሳያልን? ብዬ ጠየኩት፣ እርሱም አዎ አለ፣ እኔም በመቀጠል፦ ስለዚህ የእምነት አባት አብርሐም ”እኔ አምላክ አይደለሁም አታምልኩኝ” አላለም፣ አለማለቱ ግን አምላክ ለመሆንና ለመመለክ መስፈርት አይደለም፣ ይህ ከስነ–ኣመክኖ ኣንፃር ፉርሽ የሆነ ሙግት ነው።
ከሥነ አመክንዮ አንጻር ፉርሽ የሆነው ያንተ ጥያቄ እንጂ የእርሱ ምላሽ አይደለም፡፡ አንድ አካል አምላክ የሚሆነው የአምላክ ባሕርያት ካሉት ብቻ እንጂ አምላክ ነኝ ስላለ አምላክ አይሆንም፡፡ ከግብፅ ፈርዖኖችና ከሮማውያን ነገሥታት ጀምሮ እስከ ዘመናችን ሐሰተኛ ክርስቶሶች ድረስ “አምላክ ነን” ያሉ ብዙ ሰዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ ነገር ግን እንደርሱ ማለታቸው አምላክ አላደረጋቸውም፡፡ አምላክ መሆናቸውን በማወጅ ያጭበረበሩ ሰዎች በሰው ልጆች ታሪክ በተደጋጋሚ ከመታየታቸው አንፃር እንዲህ ያለው ንግግር ለአምላክነት መስፈርት ሊውል አይገባውም፡፡ ትክክለኛው መስፈርት አንድ አካል አምላካዊ ባሕርያትን አንጸባርቋል ወይ? የሚል እንጂ አምላክ ነኝ ብሏል ወይ? የሚል አይደለም፡፡
በአንፃሩ ኢየሱስ አምላክ አለመሆኑን አለመናገሩ የአምላክነቱ ማረጋገጫ በመሆኑ አምላክ አይደለሁም ያለበትን ቦታ እንድታሳየው መጠየቁም ትክክል ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ለሰዎች ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ክብር ሲሰጡ ሰው እንጂ አምላክ አለመሆናቸውን ሲገልፁ እንመለከታለን (ሐዋ. 14፡11-18)፡፡ ኢየሱስ ግን ሰዎች ሥራውን ተመልክተው ሲሰግዱለት፣ ሲያመሰግኑትና “አምላኬ” ብለው ሲጠሩት ተቃውሞ ከማሰማት ይልቅ ተግባራቸውንና ንግግራቸውን ሲያጸድቅ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ አምላክ አለመሆኑን አለመናገሩ የአምላክነቱ ማረጋገጫ ነው፡፡
ሌላው የጥያቄው ችግር ለክርክር እንጂ እውነትን ለማወቅ የተጠየቀ አለመሆኑ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ “እኔ አምላክ ነኝ” ያለበት ቦታ ቢኖር የእውነት ትቀበላለህ ወይንስ “መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል” ትላለህ? ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስለመኾኑ፣ ስለስቅለቱ፣ ስለሞቱና ስለትንሣኤው የተናገረባቸው በርካታ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን እውነታዎች አለመቀበልህ “አምላክ ነኝ” ብሎ የተናገረበትን ቦታ ብናሳይህ ላለመቀበልህ ማረጋገጫ አይደለምን? ስለዚህ ጥያቄው ሲጀመር በቅንነት የተጠየቀ ሳይሆን ፍሬ ለሌላው ክርክር የተጠየቀ በመሆኑ የጥያቄውን ከንቱነት በሚያሳይ ሌላ ጥያቄ ሊመለስ እንጂ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡
ፈጣሪማ “እኔ አምላክ ነኝ አምልኩኝ” ይላል፦ ዘዳ.32:39፤ “አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤”
ቁርአን 21:92 “እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ።”
ዘመነ ብሉይና ዘመነ ሐዲስ ልዩነት ስላላቸው እግዚአብሔር በኹሉም ዘመናት በተመሳሳይ መንገድና ኹኔታ ራሱን መግለጥ የግድ አያስፈልገውም፡፡ ጥያቄያችን ሊሆን የሚገባው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በምን ዓይነት መንገድ ነው የገለጠው? የሚል እንጂ እኛ በምንፈልገው መንገድ ስላልተናገረ አምላክ አይደለም ብሎ ማለት ትክክል አይደለም፡፡
በቁርአን ውስጥ አላህ “እኔ አምላክ ነኝና አምልኩኝ” ብሎ የተናገረበትን ጥቅስ አላሳየኸንም፡፡ የምድር ንጉሥ እንኳ “እኔ ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ” ብሎ ሊናገር ይችላል፡፡
ኢየሱስ ግን አንድም ጊዜ “ኢየሱስ እኔ አምላክ ነኝ አምልኩኝ” አላለም፣ ስለው ልጁ ቀጠል አረገና፦ ዮሐ10:30 ጠቀሰልኝ፣ ደስ የሚለው ነገር ክርስቲኣኖች ለኢየሱስ ኣምላክነት ብለው የሚጠቅሳቸው ጥቅሶች ለእኔ ኢየሱስ ኣምላክ አለመሆን የሚያሳዩ ናቸው፦
ዮሐ.10:30 እኔ እና አብ አንድ ነን።
የጥቅሱ አውድ ኢየሱስ በትክክል አምላክ መሆኑን እየተናገረ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይህንንም ከአፍታ በኋላ የምናየው ይሆናል፡፡
ነጥብ አንድ እኔ እና አብ እኔ *i* የሚለው ባለቤት ተውላጠ–ስምና አብ*father* የሚለው የማእረግ ስም እና*and* በሚል አያያዝ መስተጻምር* coplative conjuction* እንደተለየ አስተውል። በስነ–ሰዋሰው ጥናት ከማእረግ ስም በፊት *the* የሚል ጠቃሽ አመልካች መስተኣምር*definite article* ካለና ተውላጠ–ስሙ በመስተጻምር ከተለየ ሁለት የተለያየ ማንነቶችን*persons* ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ታዲያ ይህ ጥቅስ ኢየሱስ አብ አሊያም አምላክ ሊሆን ይቅርና ከአብ አሊያም ከአምላክ የተለየ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
[coplative conjuction ያለው copulative conjunction ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ አጻጻፉ ግድፈት አለበት ለማለት ያህል ነው፡፡] ይህ ሰው ገና ከጅምሩ Straw man fallacy የተሰኘውን የሥነ አመክንዮ ተፋልሶ ፈፅሟል፡፡ ይህ ተፋልሶ ሞጋቻችሁ ያልተናገረውን ደካማ ሙግት በመፍጠር ማፈራረስ ማለት ነው፡፡ በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአካል ልዩ ሲሆኑ አንድነታቸው በመለኮት ነው፡፡ ስለዚህ አብና ወልድ ሁለት ማንነቶች ናቸው ነገር ግን በምንነት አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያናዊው አስተምህሮ ከጥቅሱ ጋር የሚስማማ ሆኖ ሳለ ክርስቲያናዊውን አስተምህሮ የሚጻረር ነጥብ ያገኘ ማስመሰሉ ግራ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ደግሞስ ኢየሱስ አምላክ ለመሆን “አብ” መሆን አለበት ብሎ የሚያምን ሥላሴያዊ ክርስቲያን የለም፡፡ በትምህርተ ሥላሴ መሠረት ሦስቱም የሥሉስ ቅዱስ አካላት የአንዱ መለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች በመሆናቸው አንድነታቸው በመለኮት (በምንነት) እንጂ በአካል (በማንነት) አይደለም፡፡ ይህ አብዱል ወይ የሥላሴን አስተምህሮ አልተረዳም አለበለዚያም ለሙግት እንዲያመቸው ሲል ትክክለኛውን ነጥብ እያጣመመ ነው፡፡
ነጥብ ሁለት ነን በመቀጠል ነን*are* የሚል የብዜት አያያዝ ግስ*linking verb* ተጠቀመ እንጂ ነኝ *am* አሊያም ነው *is* የሚል አልተጠቀመም ይህም በስነ–ሰዋሰው ጥናት ሁለት የተለያየ ማንነቶችን *persons* መሆናቸውን ቁልጭ ኣድርጎ ያሳያል።
አሁንም ጸሐፊው የቀደመውን ተፋልሶ ደግሞታል፡፡ ክርስቲያኖች አብና ወልድ ሁለት አካላት እንደሆኑ እንጂ አንድ አካል እንደሆኑ አያምኑም፡፡
ነጥብ ሶስት አንድ እዚህ ጋር የሚነሳ ትልቁ ነጥብ አብና ወልድ የምን አንድነት ነው ያላቸው? የአላማ? የማንነት? የህላዌ ? ይህን ለማወቅ አንድ የሚለውን ቃል በስነ–ቋንቋ ሙግት ይፈታል፦ A.የማንነት አንድነት *heis* የማንነት አንድነት ማለት የአንድ ቅዋሜ–ማንነት*person* የግሪኩ የሚጠቀምበት ሄእስ εἷς ሲሆን በስነ–ሰዋስው ተባታይ ጾታ ነው ይህንን ለአንድ ቅዋሜ–ማንነት*person* ብቻ ነው፦
ማር 12:29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ εἷς ነው፤
ማር 12:32 አንድ εἷς ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤
1ቆሮ 8:4 ከአንዱም εἷς በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
1ቆሮ 8:6 ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ εἷς አምላክ አብ አለን፥
ኤፌ 4:6 ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ εἷς አምላክ የሁሉም አባት አለ።
1ጢሞ 2:5 አንድ εἷς እግዚአብሔር አለና፥ ገላ 3:20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ εἷς ነው።
ያዕ 4:12 ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ εἷς ነው፤
ማር 10:18 ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ εἷς ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።
ያዕ2:19 እግዚአብሔር አንድ εἷς እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል።
ስለዚህ ኣንዱ አምላክ አንድ ቅዋሜ–ማንነት*person* ነው ማለት ነው፣ ምክንያቱም የሚጠቀምበት አያያዥ ግስ ነው*is* እንጂ ናቸው*are* አይደለም።
ይህ ጸሐፊ አስተምህሮተ ሥላሴንም ሆነ ሥነ አመክንዮን አያውቅም፡፡ በሥላሴ አስተምህሮት መሠረት እግዚአብሔር በሦስት አካላት የሚኖር አንድ መለኮት ነው፡፡ ሦስቱም የሥላሴ አካላት የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት እንጂ ሦስት የተለያዩ አማልክት ስላልሆኑ በተናጠል “አንድ አምላክ” “አንድ ጌታ” “አንድ ፈጣሪ” ወዘተ. ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አብን “አንድ አምላክ” ባለበት በዚያው ቦታ ወልድን “አንድ ጌታ” ብሎ የጠራው፡- “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” (1ቆሮ. 8፡6)፡፡ በዚህ ቦታ ሐዋርያው የተጠቀመው “ኩሪዮስ” የሚለው የግሪክ ቃል ሰብዓ ሊቃናት ብሉይ ኪዳንን ከእብራይስጥ ወደ ግሪክ ሲተረጉሙ ስመ እግዚአብሔርን እንዲወክል የመረጡት ቃል ነው፡፡ በርግጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ክፍል የብሉይ ኪዳንን የአይሁድ “ሼማ” እያብራራ ነው፡- “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው” (ማር. 12፡29)፡፡ ሐዋርያው በአይሁድ ሼማ ውስጥ አንድ አምላክ ለሚለው አብን የጠቀሰ ሲሆን አንድ ጌታ ለሚለው ደግሞ ኢየሱስን ጠቅሷል፡፡ ይህም በተለያዩ ሁለት ቃላት አብም ኢየሱስም መለኮት መሆናቸውን የገለጸበት መንገድ ነው፡፡ ሐዋርያው ይሁዳም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶን “ብቻውን ያለ ጌታ” በማለት ይጠራዋል፡- “ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ” (ይሁዳ 4)፡፡ እንዲህ ያሉ የተናጠል አገላለፆች ከሥላሴ አስተምህሮ መሠረታዊ ግንዛቤ ጋር የሚስማሙ እንጂ የሚጣረሱ አይደሉም፡፡
ሌላው የጸሐፊው ችግር የአዲስ ኪዳንን ግሪክ አለማወቁ ነው፡፡ በርግጥ አንድ ሰው አዲስ ኪዳንን ለመረዳት የግድ ግሪክ ማወቅ አለበት የሚል ሕግ የለም፡፡ ነገር ግን ሌሎችን ለማስተማር እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን የሚጽፍ ሰው ቋንቋውን የሚያውቁትን መጠየቅ አለበለዚያም በዘርፉ ምሑራን የተጻፉ መጻሕፍትን ማንበብ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ጸሐፊ እንዳደረገው ዝም ብሎ ከራሱ እየፈለሰፈ ቢጽፍ ለራሱም ተሳስቶ ሌሎችንም ያሳስታል፡፡
ግሪኩ የአንድ ቅዋሜ-ማንነትን (person) ለማመልከት εἷς (ሄይስ) የሚል ቃል እንደሚጠቀምና ይህንንም ቃል ለአንድ ቅዋሜ-ማንነት ብቻ እንደሚጠቀም ገልጿል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ቃሉ ነጠላ አንድነትንም ሆነ ብዝሃ አንድነትን ለማመልከት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል፡- “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ (ሄይስ) ሰው ናችሁና” (ገላ. 3፡28)፡፡ ይህ ማለት አማኞች በክርስቶስ ባላቸው ሕብረት አንድ ይሆናሉ ማለት እንጂ ተጨፍልቀው ነጠላ አንድነት ይኖራቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ “ሄይስ” የሚለው ቃል የማንነት አንድነትን እንደሚገልፀው ሁሉ የሕብረት አንድነትንም ይገልፃል፡፡ እናም ከዚህ ቃል በመነሳት እግዚአብሔር በአካል ነጠላ እንደሆነ መናገር አይቻልም፡፡
የህላዌ አንድነት*mia* የህላዌ አንድነት ማለት የአንድ ተፈጥሮ *essence* የግሪኩ የሚጠቀምበት ሚአ μίαν ሲሆን በስነ ሰዋስው ኣንስታይ ጾታ ነው ይህንን ለተፈጥሮ አንድነት ነው፦ ማቴ 19:5 አለም፡– ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ μίαν ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?
ማቴ 19:6 ስለዚህ አንድ μίαν ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።
“ሚኣን” የሚለው የግሪክ ቃል ጸሐፊው በጠቀሳቸው ጥቅሶች ውስጥ የህላዌ አንድነትን ለማሳየት የዋለ ቢሆንም በሌሎች ብዙ ቦታዎች የቁጥርና የዓላማ አንድነትን ለማመልከት ስለዋለ ጸሐፊው ቃሉን በዚህ መወሰኑ ጥናት አለማድረጉን ያመለክታል፡፡ ጥቂት ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፡-
ነጠላ ቁጥርን ለማመልከት፡- “ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን (ሚኣን) ለአንተ አንዱንም (ሚኣን) ለሙሴ አንዱንም (ሚኣን) ለኤልያስ እንሥራ አለ።” (ማቴ. 17፡4)
አንድ ማንነትን ለማመልከት፡- “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት (ሚኣስ μιᾶς) ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ” (1ጢሞ. 3፡2)፡፡ “ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ (ሚኣ μία) ትወሰዳለች አንዲቱም (ሚኣ μία) ትቀራለች።” (ማቴ. 24፡41)
የዓላማ አንድነትን ለማመልከት፡- “እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም (ሚኣን) አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና።” (ራዕይ 17፡17)
የሕብረት አንድነትን ለማመልከት፡- “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ (ሚኣን ፖይሜን) ይሆናሉ እረኛውም አንድ (ሄይስ)” (ዮሐ. 10፡16)፡፡
የአላማ አንድነት*hen* የአላማ አንድነት የግሪኩ የሚጠቀምበት ሄን ሲሆን በስነ–ሰዋስው ግዑዝ ጾታ ነው ይህንን ለአላማ የሚጠቀምበት አንድነት ነው፦
1ቆሮ 3:6 እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ 1ቆሮ 3:8 የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ἕν ናቸው፥
በተመሳሳይ “ሄን” የሚለው ቃል ነጠላ ቁጥርን፣ የዓላማ አንድነትንም ሆነ የሕብረት አንድነትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
ነጠላ ቁጥር፡- “እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ (ሄን ἕν) በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?” (ማቴ. 12፡11)
አንድ ማንነት፡- “እንደዚህም ያለውን አንድ (ሄን ἕν) ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል” (ማቴ. 18፡5)፡፡ “አካልም አንድ (ሄን) እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ (ሄን) አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው” (1ቆሮ. 12፡12)
አንድ ሕብረትን፡- “እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ (ሄን ἕν) አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።” (ሮሜ 12፡5)
ታዲያ የአብና የወልድ የምን አንድነት ነው የሚጠቀምበት? ስንል ሄን የሚለውን ነው፤ ይህም የአላማ አንድነት እንጂ ሥላሴአውያን እንደሚሉት የህላዌ አሊያም አፖስተሊኮች እንደሚሉት የአካል አይደለም፡፡
በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድነትን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋሉት ሁሉም ቃላት የተለያዩ ትርጉሞች እንዳላቸው ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ የቃላቱን ትርጉም የሚወስነው የተጠቀሱበት አውድ እንጂ ወጥ የሆነ ትርጉም ኖሯቸው እንዲህ ብቻ ነው ብለን የምናስቀምጠው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በዮሐንስ 10፡30 ላይ ምን እያለ እንደሆነ አውዱን በመመልከት መረዳት ይኖርብናል፡፡ ጥቅሱን በአውድ ውስጥ እናንብበው፡-
“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘለዓለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የሰጠኝ አባቴ ከኹሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፡፡ እኔና አብ አንድ ነን፡፡ አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ፡፡” (ዮሐ. 10፡27-31)፡፡
በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ የሚከተሉትን ነጥቦች ግልፅ አድርጓል፡-
- የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣል (ቁ. 28)
- በጎቹን (ምዕመናንን) ማንም ከእጁ መንጠቅ አይችልም (ቁ. 28)
- እነርሱን የሰጠው አባቱ ከነጣቂዎቹ ኹሉ ይበልጣል፤ እርሱና አብ ደግሞ አንድ በመሆናቸው ከአብ እጅ መንጠቅ እንደማይችሉት ሁሉ ከእርሱም እጅ መንጠቅ አይችሉም (ቁ. 29 እና 30)
ከእርሱም ሆነ ከአብ እጅ በጎቹን ማንም መንጠቅ እንደማይችል ከተናገረ በኋላ እርሱና አብ አንድ እንደሆኑ በማሳወቅ በባሕርይ የተካከሉ መሆናቸውን ግልፅ አድርጓል (ዮሐ. 10፡30)፡፡ ይህ አንድነት የኃይል አንድነትን የሚገልፅ ነው፡፡ አብና ኢየሱስ በኃይል አንድ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ማንም በጎቹን ከአብ እጅ መንጠቅ እንደማይችል ኹሉ ከኢየሱስም እጅ መንጠቅ የማይችለው፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ቦታ ላይ ለበጎቹ የዘለዓለምን ሕይወት እንደሚሰጥ በመናገር አምላክነቱን የበለጠ ግልፅ አድርጓል (ቁ.28)፡፡ ከአምላክ በስተቀር የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት የሚችል አለን? ከዚህ ንግግር በኋላ አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ ያነሱት ኢየሱስ አምላክ መኾኑን እየተናገረ መኾኑ ስለገባቸው ነበር፡-
“አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት” (ቁ.31-33)፡፡
ስለዚህ ከአውዱ ግልፅ ሆኖ እንደሚታየው የአብና የኢየሱስ አንድነት የመለኮት ነው፡፡
ዮሐ 17:11 ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ ἕν እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ዮሐ 17:22-23 እኛም አንድ*hen* እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤
ሃዋርያት ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ መልኩ ያላቸው ኣንድነት እንደ ኣብና ወልድ የአላማ ኣንድነት ነው *እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ* የሚል መመሳሰል ኢየሱስ ይጠቀማል።
ኢየሱስ ዮሐንስ 10፡30 ላይ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ የተናገረው ስለ ኃይል አንድነት እንጂ ስለ ዓላማ አንድነት እየተናገረ ባለመኾኑ በዮሐንስ 17 ላይ ለሐዋርያቱ ከተነገረው አንድነት ጋር ማመሳሰል ትክክለኛውን የሥነ ፍታቴ ሥርኣት የጠበቀ አይደለም፡፡ የሁለቱ አውድ ለየቅል ናቸው፡፡
መደምደሚያ ሰውና አምላክ ሁለት የተለያዩ ህልውናዎች እና ማንነቶች ናቸው። ኢየሱስና እግዚአብሔር ደግሞ የህላዌ ሆነ የማንነት ልዩነት እንዳላቸው ከኢየሱስና ከመፅሐፉ ኣንደበት ይደመጣል፦ ዮሐ 7:16-17 ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ*myself* አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ*myself* የምናገር ብሆን ያውቃል።
ጌታችን ኢየሱስ መለኮታዊ ክብሩን በመተው ሰው ሆኖ ወደ ምድር እንደመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ በማንነቱ አምላክ ቢሆንም ነገር ግን ሰብዓዊ ባሕርይን በመላበስ ወደ ምድር መጥቷል፡፡ ስለዚህ ይህንን ጥቅስ ኢየሱስ መለኮታዊ ክብሩን በመተው ራሱን ባዶ አድርጎ የባርያን መልክ ይዞ መምጣቱን በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት አውድ መረዳት አስፈላጊ ነው (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ ኢየሱስ ራሱን ለማክበርና ከፍ ከፍ ለማድረግ ስላልመጣ በአምላካዊ ባሕርዩ ሳይኾን በሰብዓዊነቱ በሰዎች ፊት ለመታየትና ለማገልገል በመወሰኑ ምክንያት ፍጹም ሰው ኾኖ ተመላልሷል፡፡ ይህንንም በቀጣዩ ቁጥር ላይ አስታውቋል፡-
“ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም፡፡” (ቁ.18)፡፡
ኢየሱስ የራሱን ክብር ለመፈለግ አለመምጣቱን ከአብ የሰማውን ብቻ በመናገር አሳይቷል፡፡ ይህ አምላክነቱን ለማስተባበል የሚበቃ ሙግት አይደለም፡፡
ዮሐ 14:1 ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ አውዱ ካላመለከተ በስተቀር “እግዚአብሔር” ከተባለ የተጠቀሰው የሥላሴ አካል አብ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ቦታ ላይ ኢየሱስ ሐዋርያቱ በእርሱና በአብ እንዲያምኑ መጠየቁ አምላክነቱን የሚያሳይ እንጂ የሚፃረር አይደለም፡፡
ዮሐ 5:31-32 እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ*myself* ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም*HE* ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ።
በአይሁድ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ብቻውን ስለ ራሱ መመስከር አይችልም፡፡ እውነተኛነቱን ለማረጋገጥ ሁለተኛ ወገን ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን የተናገረው ከአይሁድ ሕግ አኳያ ነው እንጂ ዮሐንስ 8፡18 ላይ ስለ ራሱ መመስከር እንደሚችል ተናግሯል፡፡ አብ በተለያዩ መንገዶች ስለ ማንነቱ ስለመሰከረለት የኢየሱስ ምስክርነት የአይሁድን ሕግ ያሟላል፡፡ እናም በዘመኑ የነበሩት አይሁድ የኢየሱስ ምስክር ራሱ ኢየሱስ ብቻ ነው የሚል ማመካኛ የላቸውም፡፡ የሆነው ሆኖ አብ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር ለመጣው አንድያ ልጁ መመስከሩ ልጁን ከአምላክነት ደረጃ ዝቅ አያደርገውም፡፡
ዮሐ 8:18 ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።
አብና ኢየሱስ በአካል ልዩ በመለኮት ግን አንድ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ለአብ መመስከሩና አብም ለኢየሱስ መመስከሩ የአብና የኢየሱስን ማንነት የሚደባልቁ የኑፋቄ አስተምህሮዎችን ውድቅ የሚያደርግና የሥላሴን አስተምህሮ የሚያጸና እንጂ የኢየሱስን አምላክነት የሚጻረር አይደለም፡፡
ስለዚህ መደምደሚያችን ይህ ከሆነ ዮሐ 10:30 እኔና አብ አንድ ነን። የሚለው ንግግር የኢየሱስ ኣምላክነት አሊያም አብ መሆን የሚያሳይ ኣይደለም በቂ መረጃ ይዛችሁ ኑ።
መጽሐፍ ቅዱሳቸውን የሚያውቁ አማኞች ኢየሱስ አብ ነው አይሉም፡፡ አንተ እንዳደረከው ጥቅሶችን ከአውድ ነጥሎ በማውጣትና ትርጉም አልባ የቃላት ስንጠቃ ውስጥ በመግባትም የኢየሱስን አምላክነት አይክዱም፡፡ የኢየሱስን አምላክነት በማወጅ ከሚጀምረውና ከሚደመድመው ወንጌል ውስጥ አምላክነቱን የሚጻረር ሐሳብ መፈለግህ በራሱ ምን ያህል ግራ እንደገባህ አመላካች ነው፡፡ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ሐሳቦች መገንዘብ ያለብን በመግቢያውና ማጠቃለያው ላይ በተገለጸው ጭብጥ መሠረት እንጂ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ዮሐንስ የኢየሱስን አምላክነት በማወጅ ይጀምራል፡-
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐ. 1፡1-2)
መቋጫውንም ያደረገው አምላክነቱን በማረጋገጥ ነው፡-
“ቶማስም ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት፡፡ ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡” (ዮሐ. 20፡28-29)፡፡
ሙስሊሙ ወገኔ ዛሬ አምላክነቱን ለመካድ ራስህን የምታደክመው ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪህና የእስትንፋስህ ምንጭ ቢሆንስ? ዛሬ አምላኬ አይደለም ብለህ የካድከው ኢየሱስ ለፍርድ ተመልሶ ቢመጣና በፊቱ ብትቆምስ?
“እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” (ራዕይ 22፡12-13)
ሙስሊሙ ወገኔ እስኪ ላንድ አፍታ ቆም በልና እውነቱን እንዲገልጥልህ በትህትና ጠይቀው፡፡ ግድ የለም “ፈጣሪዬ ከሆንክ የልብ ዓይኔን አብራልኝና ልወቅህ” ብለህ ጠይቀው፡፡