ኢየሱስ አምልኮ የተገባው አምላክ ነው!
በዳንኤል ላይ የተጠቀሰውን “የሰው ልጅ” በተመለከተ ለሙስሊም ሰባኪያን የተሳሳተ ትርጓሜ የተሰጠ እርማት
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምልኮ የተገባው አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቦታዎች ላይ ይናገራል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በትንቢተ ዳንኤል 7፡13-14 ላይ የሚገኝ ሲሆን ለሐሰት አስተማሪዎች የራስ ምታት ከሆኑት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ይህ ጥቅስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ መገኘቱና ከመሲሁ መምጣት በፊት የተነገረ መሆኑ የኢየሱስ አምላክነት ከእርገቱ በኋላ የተፈጠረ አስተምህሮ ሳይሆን የነቢያት አስተምህሮ መሆኑን በማረጋገጥ እስልምናን የሚያሸማቅቅ በመሆኑ ሙስሊም ሰባኪያን ለጥቅሱ የተለየ ትርጉም ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ከረበናተ አይሁድና ከተለያዩ የኑፋቄ ቡድኖች የተቀዱ አሮጌ ሙግቶችን ከማቅረብ በዘለለ ቀደም ሲል ክርስቲያኖች መልስ ያልሰጡበትን አዲስ ሐሳብ አቅርበው አያውቁም፡፡ በዚህ ጽሑፍ አንድ አብዱል ከዚያም ከዚህም የቃረማቸውን ሙግቶች ያቀረበበትን ጽሑፍ እንፈትሻለን፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምልኮ የተገባው ዘላለማዊ ንጉሥ መሆኑን በመረዳት ተገቢውን ክብር እንዲሰጡት መንፈስ ቅዱስ ይህንን ጽሑፍ ይጠቀም ዘንድ ጸሎታችን ነው፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
ኢየሱስ ይመለካልን?
“ዒባዳ” عبادة የሚለው ቃል “ዓበደ” عَبَدَ “አመለከ” ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን “አምልኮ” ማለት ነው፤ አምልኮ የሚገባው አንዱ አምላክ አላህ ብቻ ነው፤ አላህ ዒሳን በል ብሎ ያዘዘው ቃል፦ “ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን አምልኩ” ማለትን ነው፦
5፥117 «በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል፦ *ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን አምልኩ* ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡
ይህ ንግግር ከክርስቶስ እርገት ከ600 ዓመታት በኋላ በሙሐመድ የተፈበረከ ፈጠራ እንጂ ከጌታችን አንደበት የወጣ አይደለም፡፡ አቀራረቡም ታሪካዊ ሳይሆን ዒሳ በዘመነ ፍጻሜ ይናገረዋል ተብሎ የተተነበየ ንግግር ነው፡፡ ሙሐመድ አንድም የተፈጸመ ትንቢት ስለሌለው ይህኛውም ይፈፀማል ብለን እንድንጠብቅ የሚያስችል ምክንያት የለንም፡፡
ነገር ግን በተቃራኒው ክርስቲያኖች ኢየሱስን በቀጥታ ያመልካሉ፤ “አምልኮ” የሚለው ቃል በእብራይስጥ “አባድ” עָבַד ሲሆን በግሪክ ደግሞ “ላትሬኦ” λατρεύω ነው፤ ይህም ለአንዱ አምላክ ብቻ በሙሉ ሁለንተና የሚቀርብ ልመና፣ ስእለት፣ ማጎብደድ፣ መተናነስ፣ ስግደት፣ መገዛት ፣ አገልግሎት Adoration ነው። ኢየሱስ፦ አምልኩኝ ያለበት፣ ሀዋርያት እና ነብያት፦ ኢየሱስን አምልኩ ያለበት እና ሰዎች ኢየሱስን ያመለኩበት አንድ አንቀጽ የለም። ነገር ግን ኢየሱስ የሚመለክ መሆኑን የሚጠቁሙ ጥቅሶች አሉ ይላሉ፡-
የእምነታችን መሠረት የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቶስን አምላክነት ይመሰክራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ የኢየሱስን አምላክነት የሚክድ ሰው በእኩለ ቀን የጠራ ሰማይ ስር ቆሞ ፀሐይ አይታየኝም እንደሚል የታወረ ሰው ነው፡፡ የኢየሱስን አምላክነት የተመለከቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን እንዲሁም በቅዱሳኑ ስለመመለኩና አምልኮን ስለመቀበሉ በስፋት የዳሰስንበትን ጽሑፍ እዚህ ገፅ ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡
እውን ይህ ጥቅስ ኢየሱስ ይመለካል ይላልን? እስቲ ጥቅሱን እንየው፦
ዳንኤል 7፥13-14 በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ “የሰው ልጅ የሚመስል” ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ “ይገዙለት” δουλεύσουσιν ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም “ተሰጠው”፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።
ነጥብ አንድ
“የሰው ልጅ የሚመስል”
ዳንልኤ በራእይ አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ሲወጡ አየ፤ እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው፤ በራእይ ያየው “የሰው ልጅ የሚመስል” ደግሞ “የልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ” ነው፦
ዳንኤል 7፥27 መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት *”ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ”* ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ “ይገዙለታል* δουλεύσουσι ይታዘዙለትማል።
ዳንኤል 7፥18 ነገር ግን *”የልዑሉ ቅዱሳን”* መንግሥቱን ይወስዳሉ፥ እስከ ዘላለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ።
ዳንኤል 7፥22 *”በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ፍርድም ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪሰጥ ድረስ”*፥ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወስዱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ አሸነፋቸውም።
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው የልዑሉ ቅዱሳን እንደሆኑ የተነገረው የቱ ጋር ነው? የሰው ልጅ መሲሁ ነው፡፡ መሲሁ ተመልሶ ሲመጣ ቅዱሳን የምድርን መንግሥት ሁሉ ይወስዳሉ፡፡ መሲሁ ንጉሣቸው፤ እነርሱ ደግሞ ሕዝቡ ይሆናሉ (ራዕይ ም. 19-22)፡፡ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር እንደሚመጣ በነጠላ የተነገረውን “ቅዱሳን ናቸው” ብለህ ለመተርጎም የሚያስችል አውዳዊም ሆነ ሰዋሰዋዊ አግባብ የለም፡፡ ከደመና ጋር የሚመጣው መሲሁ ስለመሆኑ በአዲስ ኪዳን በግልፅ ተነግሮናል፡- “እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን። ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።” (ራዕይ 1፡7-8)
የአይሁድ ኮሜንቴርይ አንዳቸውም “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ዐውዱ ላይ መሲሁ ነው ብሎ የሰጡበት ማብራሪያ የለም። ዐውዱ ላይ የሰው ልጅ የሚመስል የልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ መሆኑን ፍትንው አርጎ ከዘጋ በኃላ ሌላ ትርጉም እንዳንሰጥ “የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው” በማለት ይቋጫል፦ ዳንኤል 7፥28 የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው።
“አንዳቸውም “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ዐውዱ ላይ መሲሁ ነው ብሎ የሰጡበት ማብራሪያ የለም” የሚለው አባባልህ ሐሰት ነው፡፡ የተለያዩ የአይሁድ ሐተታዎች በሰማይ ደመና የሚመጣው የሰው ልጅ መሲሁ መሆኑን ጽፈዋል፡፡ ጥቂቶቹን ልጥቀስልህ፡-
“R. Alexandr said: “R. Y’hoshu’a ben Levi explained:..’If they will be righteous, [the Messiah will come] on the clouds of heaven (Daniel 7.13); if they will not be righteous, [he will come] as a poor man riding upon an ass (Zech 9.9)'” [B. Sanh 98a]
“ረቢ እስክንድር እንዲህ አለ፡- “ረቢ የሆሹኣ ቤን ሌዊ እንዳብራራው …. “ጽድቅን ካደረጉ [መሲሁ] በሰማይ ደመና ይመጣል (ዳንኤል 7፡13)፤ ጽድቅን ካላደረጉ ጎስቋላ ሰው ሆኖ በአህያ ይመጣል (ዘካርያስ 9፡9)፡፡”
“Anani [“He of the clouds”] is King Messiah, who will in the future reveal himself” [Targum to I Chronicles 3.24]
አናኒ [ከደመና የሆነው] ወደ ፊት ራሱን የሚገልጠው ንጉሡ መሲህ ነው፡፡
“And now let us speak in praise of King Messiah who will come in the future with the clouds of heaven and two Seraphim to his right and to his left, as it is written, Behond, with the clouds of heaven came one like unto a son of man (Dan 7.13) [Pirque Mashiah, Bhm 3.70]
ወደ ፊት በሰማይ ደመና በቀኝና በግራው ደግሞ ከሁለት ሱራፌል ጋር ስለሚመጣው ስለ መሲሁ የምስጋና ቃል እንናገር፤ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- “እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ” (ዳንኤል 7፡13፡፡
ከዚህ በላይ ማስረጃ ካስፈለገ ልንጨምርልህ እንችላለን፡፡ በቂ ዕውቀት ሳይዙ ከፒኪፒድያ ያገኙትን የተዛባ መረጃ ይዞ አጉል አስተማሪ መሆኑ ለእንዲህ ላለ ስህተት ይዳርጋል፡፡
መረጃህ ሐሰት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አይሁድ “የሰው ልጅ” የተባለው መሲሁ እንደሆነ አለመቀበላቸው “የሰው ልጅ” መሲሁ አለመሆኑን የሚያረጋግጣው በየትኛው አመክንዮ መሠረት ነው? “አይሁድ እንደዚያ ስላላሉ እንደዚያ ሊሆን አይችልም” የሚለው ሙግት Appeal to Authority የተሰኘ የሥነ አመክንዮ ተፋልሶ ነው፡፡ ከአፍታ በኋላ እንደምንመለከተው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ ራሱን “የሰው ልጅ” በማለት ጠርቷል፤ ከደመና ጋር የሚመጣውም እርሱ መሆኑን ነግሮናል፤ ሐዋርያቱም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ የአይሁድን ዝምታ ከእነርሱ ንግግር ይልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባን ለምንድነው? ለትክክለኛ የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ የአይሁድ ምልከታ መሠረታችን ሊሆን ከተገባው ሲጀመር ጌታችን ኢየሱስና ሐዋርያቱስ አይሁድ አይደሉም እንዴ? የሌሎቹን አይሁድ ትርጓሜ ተቀብለን የእነርሱን የማንቀበልበት ምክንያት ምንድነው? ሙግትህ ትርጉም አልባ ነው፡፡
ነጥብ ሁለት
“ተሰጠው”
ሙግቱን ጠበብ አድርገነው ዳንኤል ላይ “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ኢየሱስ ነው ቢባል እንኳን አሁንም ፍጡር ከመሆን የዘለለ ማንነት የለውም። ምክንያቱም በሃረጉ ውስጥ “ተሰጠው” የሚል ሃይለ–ቃል አለ፤ ሰጪው ደግሞ “በዘመናት የሸመገለው” አብ ነው፤ አንዱ አምላክ ለኢየሱስ የአባቱን ዙፋን ሰጥቶታል፦
ማቴዎስ 28፥18 ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ *ሥልጣን ሁሉ* በሰማይና በምድር *ተሰጠኝ*።
ሉቃስ 10፥22 *ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል*፥
ሉቃስ 1፥32 እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ *ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል*፤
መሲሁ በሰብዓዊነቱ የዳዊት ዘር በመሆኑ የዳዊት ዙፋን ወራሽ ነው፡፡ ነገር ግን አምላክ በመሆኑ የዳዊት ጌታ ነው፡-
“ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ፦ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ ዳዊት፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው።” (ማቴ. 22፡41-45)
ጌታችን ሥልጣንን ከአብ መቀበሉ ክብሩን ጥሎ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ አኳያ ሊታይ ይገባዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-
“እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2፡6-11)
ከትንሣኤው በኋላ ቀደም ሲል ጥሎት የመጣውን ሥልጣኑን መልሶ ከአባቱ ተቀብሏል፡፡ ይህ ሥልጣን የእርሱ የነበረ እንጂ አዲስ ሥልጣን አይደለም፡፡ ኢየሱስ ፍጡር ቢሆን ኖሮ እንዴት አብ መለኮታዊ ሥልጣን ይሰጠዋል? እንዴትስ የሰው ልጆች ሁሉ ያመልኩታል? ኢየሱስ የሥላሴ አካልና አምልኮ የተገባው አምላክ ነው፡፡
ሰው እና የሰው ልጅ የተባለው ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ፍጡር ነው፤ ታዲያ ይልቁንስ *ብስብስ የሆነ ሰው፥ ትልም የሆነ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ፊት ምንኛ ያንስ?
ዮሐንስ 13:31 ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ። *አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚእብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ*፤
ኢዮብ 25፥6 ይልቁንስ *ብስብስ የሆነ ሰው፥ ትልም የሆነ የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ*!
“የሰው ልጅ” የሚል ሐረግ በሁለቱም ቦታ ስላገኘህ ብቻ ሁለቱን አንድ ማድረግህ ስህተት ነው፡፡ ኢየሱስ መበስበስ የማያውቀው መለኮት ሲሆን ስለ እኛ ሲል ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል፡፡ ሰው የሆነው ባሕርዩ እንኳ መበስበስን ሳያይ ከሙታን ተነስቷል፡-
“ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና፦ ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ። ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፡፡” (ሐዋ. 2፡25-32)
መጽሐፈ ኢዮብ እየተናገረ ያለው ስለ እኔና ስለ አንተ እንጂ ስለ ኢየሱስ አይደለም፡፡
የሰው ልጅ የሚመስል የሚባለው ኢየሱስ ነው ብንል እንኳን ኢየሱስ የሚመስለው አለ የሰው ልጅ የሚመስል ተብሏልና፤ ሰውን ይመስላል፤ ነገር ግን ነገር ግን ያ የሚመለከው አንዱ አምላክ የሚመስለው አለን? የለም፦
ኢዮብ 23:13 *እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው?*
እግዚአብሔርን የሚመስለው የለም ስንል በፍፁማዊ መንገድ (Absolute Sense) ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአብርሃም ሲገለጥለት በሰው መልክ ነበር (ዘፍ. 18)፡፡ አጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ሳያገናዝቡ ጥቅሶችን ነጥሎ መጥቀስ ለስህተት ይዳርጋል፡፡
ነጥብ ሶስት
“ይገዙለት”
“ይገዙለት” ተብሎ በግሪክ ሰፕቱጀንት”LXX” ላይ የሰፈረው ቃል “ዱልኦስ” δοῦλος ነው፦
ዳንኤል 7፥14 ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ “ይገዙለት” δουλεύσουσιν ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም “ተሰጠው”፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።
“ይገዙለት” ተብሎ መገዛት የተገባው የሰው ልጅ የሚስመለው የልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ እንደሆነ ዐውዱ ላይ ፍንትውና ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፦
ዳንኤል 7፥27 መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት “ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ” ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ “ይገዙለታል* δουλεύσουσι ይታዘዙለትማል።
በመጀመርያ ደረጃ የሰብቱጀንት ትርጉም ውስጥ ዳንኤል 7፡14 δουλεύσουσιν ተብሎ አልተተረጎመም፡፡ አንተ የጠቀስከው በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ቴዎዶሺያን የተሰኘ አይሁዳዊ ሊቅ የሰብቱጀንት ትርጉምን በመከለስ ያዘጋጀውን ትርጓሜ እንጂ ቀዳሚውን ሰብቱጀንት አይደለም፡፡ “ጥንታዊው ግሪክ” ተብሎ የሚታወቀው የሰብቱጀንት ትርጉም δουλεύσουσιν (ዶውሌውሶውሲን) በማለት ሳይሆን λατρεύουσα (ላትሬውሳ) በማለት ያስቀመጠ ሲሆን ለአምላክ ብቻ ተገቢ የሆነውን አምልኮ የሚገልጽ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ይህ ክፍል መጀመርያ የተጻፈው በአራማይክ እንጂ በግሪክ አይደለም፤ ስለዚህ የግሪኩን ትርጉም መጥቀስህ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ በአራማይክ ቋንቋ “ይፕላኹን” יִפְלְח֑וּן ይላል፡፡ “ፕላኽ” የሚለው ቃል ለፈጣሪ ብቻ የተገባውን አምልኮ የሚያሳይ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሥር ጊዜ ያህል የተጠቀሰ ሲሆን ሰዎች አምላክ እንደሆነ ላመኑት አካል ብቻና ብቻ ሲጠቀሙት እናያለን፡- (ዕዝራ 7:24፣ ዳንኤል 3:12፣ 3:14፣ 3:17፣ 3:18፣ 3:28፣ 6:16፣ 6:20፣ 7:14፣ 7:27)፡፡ ከዚህ አንፃር የግሪኩን ትርጉም መሠረት አድርገህ የጠቀስካቸው ተከታዮቹ ጥቅሶች ዳንኤል 7፡13-14 ላይ የተጠቀሰው “የሰው ልጅ” ለፈጣሪ ብቻ የሚገባውን አምልኮ አለመቀበሉን አያረጋግጡልህም፡፡
አይ የሰው ልጅ የሚመስል የተባለው ኢየሱስ ነው፤ “ይገዙለት” ማለት “ያመልኩት” ዘንድ ማለት ነው ብላችሁ ከፈሰራችሁት የማትወጡት ገደል ውስጥ ትገባላችሁ፤ እንግዲያውስ የሚመለኩ አበዛዛቸው፦
ገደል የገባውማ ማን እንደሆነ ታውቋል፡፡ አሁን ገደል ውስጥ ሆነህ እያወራህ እንደሆነ ሁሉም ሰው እያየ ነው፡፡
ኢየሩሳሌም፦
ኢሳይያስ 60:12 ለአንቺም “የማይገዛ” δουλεύσουσί ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ።
ያዕቆብ፦
ዘፍጥረት 25፥23 እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ “ይገዛል” δουλεύσει ።
ዘፍጥረት 27፥29 አሕዛብ “ይገዙልህ” δουλευσάτωσάν ሕዝብም ይስገዱልህ፤
ሮሜ 8፥12 ለእርስዋ፦ ታላቁ ለታናሹ “ይገዛል” δουλεύσει ተባለላት።
“እርስ በእርስ”፦
ገላትያ 5፥13 ነገር ግን በፍቅር እርስ በእርሳችሁ “አገልግሉ” δουλεύετε ። KJV
ልብ አድርጉ ሁሉም ጋር መገዛት ተብሎ በግሪኩ ኮይኔ የቀረቡት ቃላት አንድ አይነት ነው።
ዳንኤል ላይ የሚገኘው ጥቅስ የሰብቱጀንት ትርጉም አንተ ከጠቀስከው የተለየ ከመሆኑም በላይ የተጻፈው በአራማይክ እንጂ በግሪክ ባለመሆኑ ያንተ ሙግት ፊየል ወዲህ ቁርአን ወዲያ ዓይነት ነው፡፡ በአራማይክ “ፕላኽ” የሚለው ቃል ለፈጣሪ ብቻ የተገባውን አምልኮ የሚያሳይ ነው፡፡ በግሪክ ምንም ተብሎ ቢተረጎም ኦሪጅናሉን ሐሳብ አይለውጥም፡፡
ማጠቃለያ
በትንቢተ ዳንኤል 7፡13 ላይ የተጠቀሰው “የሰው ልጅ” መሲሁ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ራሱን “የሰው ልጅ” በማለት መጥራቱና በዳንኤል የተነገረው ከደመና ጋር የሚመጣው የሰው ልጅ እርሱ መሆኑን መናገሩ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በስፋት ተዘግቧል፡-
“የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።” (ማቴ. 16፡27-28)
“ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።” (ማቴ. 19፡28)
“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” (ማቴ. 25፡31-34)
“በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።” (ማር. 13፡26-27)
“ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ፦ አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና፦ የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፦ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ፦ ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።” (ማር. 14:60-64)
ከሰማይ ደመና ጋር የሚመጣው፣ አሕዛብ ሁሉ ለአምላክ ብቻ ተገቢ በሆነ መገዛት የሚገዙለት፣ የማያልፍ ዘላለማዊ ግዛት ያለው በዳንኤል ትንቢት የተነገረለት የሰው ልጅ እርሱ መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ከአምላክ በስተቀር ሕዝቦች ሁሉ ሊገዙት የሚገባና ዘለዓለማዊ ግዛትና መንግሥት ሊኖረው የሚችል ማነው? ይህንን ሃቅ የሚክድና የኢየሱስን አምላክነት ለማስተባበል የሚሞክር ሰው በቃላት በማይነገር ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መኖሩ ግልፅ ነው፡፡
ውድ አንባቢያን፤ ሙስሊሙ ጸሐፊ ምላሻችንን ካነበበ በኋላ የመጀመርያውን ጽሑፍ ኤዲት አድርጎ መልሶ ለጥፎታል፡፡ በዚህ ጊዜ በጥቅሱ ትርጓሜ ዙርያ የአይሁድ ሊቃውንት ያላቸውን አቋም በተመለከተ የፈፀመውን አሳፋሪ ቅጥፈት በመሰረዝ ለማስተካከል ሞክሯል፡፡ በመጀመርያው ጽሑፉ ውስጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “የአይሁድ ኮሜንቴርይ አንዳቸውም “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ዐውዱ ላይ መሲሁ ነው ብሎ የሰጡበት ማብራሪያ የለም።”
ይህ አባባሉ ቅጥፈት መሆኑን ማስረጃዎችን በማጣቀስ ስላጋለጥነው በሁለተኛው ጽሑፉ ውስጥ ይህንን ሐሳብ በመሰረዝ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
“የአይሁድ ኮሜንተርይ፡- “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ዐውዱ ላይ የእስራኤል ሕዝብ ነው” ብለው የፈሰሩት፡፡”
ከአጻጻፉ እንደሚስተዋለው ይህ ሰው ጽሑፋችንን ሲያነብና አሸማቃቂ ስህተቱን ሲያስተውል ተርበትብቶ ኖሮ ኤዲት ሲያደርግ የአማርኛውን ሰዋሰው እንኳ አስተካክሎ መጻፍ አልቻለም፡፡ በቀደመው ጽሑፉ “የሰው ልጅ የሚመስል” የሚለውን አንዳቸውም መሲሁ እንደሆነ እንዳልተናገሩ የገለጸ ሲሆን በሁለተኛው ጽሑፉ ደግሞ ይህንን ግልፅ ቅጥፈቱን በማሻሻል “የእስራኤል ሕዝብ ነው” ብለው መተርጎማቸውን ይነግረናል፡፡ ትክክለኛው መረጃ ግን “የአይሁድ ሕዝብ ነው” በማለት የተረጎሙ በተለይም አንዳንድ ዘመንኛ የአይሁድ ሊቃውንት ቢኖሩም ከጥንት የነበረው አቋም “መሲሁ ነው” የሚል መሆኑ ነው፡፡ የሙስሊሙ ጸሐፊ አገላለፅ ከመጀመርያው የተሻለ ቢሆንም አሁንም እውነታን የሚያንጸባርቅና ሃቀኛ አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ከቀደመው ቅጥፈቱ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን ስንት ዘመን ሙሉ የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍ አንባቢን ሲያስቱ ከኖሩ በኋላ እንዲህ ድምጽ አጥፍቶ ኤዲት በማድረግ ለማረም መሞከር ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ አብዱል ሃቀኛ መምህር ነኝ የሚል ከሆነ ስህተት መፈፀሙን በግልፅ አምኖ ያሳሳታቸውን ተከታዮቹን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ በጽሑፎቹ ውስጥ የሚገኙ ቀደም ሲል ያጋለጥናቸውን ሌሎች በርካታ የመረጃ ስህተቶችንም በዚሁ መንገድ ማረም ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ለዚህ የሚበቃ ስብዕና ያለው አይመስልም፡፡