የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች? “የብልጥ ዓይን ቀድማ ታለቅሳለች…”

የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች?

“የብልጥ ዓይን ቀድማ ታለቅሳለች…”

ሰሞኑን አንድ ሙስሊም ሰባኪ “የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች” በሚል ርዕስ አጭር ጽሑፍ አስነብቦናል፡፡ ይህ አብዱል እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

የጠፉ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎችየሚለውን አርዕስት ስትመለከቱ ምናልባት ፀሀፊዎቻቸው ስለማይታወቁ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍሎች አስመልክቶ የቀረበ ፁሁፍ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል። በርግጥ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ፀሀፊያቸው የማይታወቅ በርካታ መፅሀፍቶች አሉ። ከሙሴ ኦሪት ጀምሮ አብዛኛው የይዘቱ ክፍል በማን እንደተፃፈ በትክክል አይታወቅም።

“የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች” በሚል ርዕስ ስለጀመርክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የነበሩ ነገር ግን አሁን ስለጠፉ ክፍሎች ልታወራን እንደሆነ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ ይገነዘባል፡፡ ርዕስህ “የጠፉ” እንጂ “ማን እንደጻፋቸው የማይታወቁ” አይልም፤ ስለዚህ ሁለቱ ሐሳቦች የሚምታቱበት አንባቢ ሊኖር ይችላል ብለህ ማሰብህ አስቂኝ ነው፡፡ “ማን እንደጻፋቸው የማይታወቁ…” የምትለዋን ነጥብ የግድ በገደምዳሜ ማንሳት አለብኝ ብለህ ካሰብክ እንዲህ የአንባቢያንህን የመረዳት ችሎታ አሳንሰህ የምትመለከት በሚያስመስልህ ሁኔታ ሳይሆን በሌላ መንገድ ማንሳት ትችል ነበር፡፡ ርዕስህ ሌላ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ጭራሹኑ ባታነሳው ይመረጥ ነበር፡፡ ለማንኛውም “ማን እንደጻፋቸው በትክክል የማይታወቁ” የሚለውን ሙግት በተመለከተ ለሰልማ መጽሐፍ በጻፍነው ምላሽ ውስጥ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተንበታል፡፡

ነገር ግን ዛሬ የምናወራው ከዛም ስለከፋ ነገር ነው። ይኸውም የመጽሀፉ ህልውና በስያሜ ደረጃ ተነግሮ ነገር ግን የተነገረው መፅሀፍ ከነ አካቴው የት እንዳለ ስለማይታወቅ መጽሀፍ ነው። መሠል ንግግሮች መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግመው ተጠቅሰው እናገኛለን። ለአብነት ጥቂቶችን ከታች ለመጥቀስ እሞክራለሁ፦

ምን እያልከን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት መጻሕፍት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ናቸው ያለው ማን ነው? ባንተ ሎጂክ መሠረት ከሄድን በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው ዛሬ ግን ልናገኛው የማንችለው የአብርሃም መጽሐፍ የቁርኣን አካል ነው ማለት ነው? (ሱራ 87:18-19)፡፡ ለምሳሌ አንተ ተውራት፣ ዘቡርና ኢንጂል በዚህ ዘመን ሊገኙ እንደማይችሉ ታምናለህ እንበል፤ ነገር ግን እነዚህ መጻሕፍት በቁርኣን ውስጥ ስለተጠቀሱ ብቻ “የጠፉ የቁርኣን ክፍሎች” ልንላቸው እንችላለን ማለት ነው? እንደርሱ ካልሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት መጻሕፍት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደሆኑ ልታስብ የቻልከው በየትኛው ሎጂክና ማስረጃ ነው? ጎበዝ እያሰብን እንጻፍ እንጂ!

1- የእግዚአብሔር የጦርነት መጽሀፍ

ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ፦ ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥ ዘኍልቁ 21: 14

እግዚአብሔር የጦርነት መጽሀፍ እንደነበረው መስማት አስደናቂ ቢሆንም እንዳለመታደል ሁኖ ግን ይህ መጽሀፍ አሁን ላይ የውሃ ሽታ ሁኗል። መጽሀፉ እንደነበረ ተገለፀልን እንጅ መጽሀፉ የት እንደገባ አይታወቅም..!

መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስ አካል እንደነበረ ወይንም አምላካዊ መገለጥ እንደነበረ ምን ማስረጃ አለህ? ስሙ ስለተጠቀሰ ብቻ “የጠፋ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል” ልትል አትችልም፡፡

2- የሰለሞን ታሪክ

የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 1 ነገሥት 11: 41

ይህ የሰለሞን ታሪክ መፅሀፍ ከወዴት ይገኛል?

መጽሐፍ ቅዱስ የሰለሞን የታሪክ መጽሐፍ ሳይሆን ለሰው ልጆች ትምህርት ሊሆኑ የሚችሉ የተመረጡ ታሪኮችን ያካተተ አምላካዊ መጽሐፍ ነው፤ ስለዚህ ከሰለሞን ጥንካሬና ስህተቶች መማር እንድንችል አስፈላጊ የሆኑ ታሪኮቹን ብቻ ማካተቱ በቂ ነው፡፡ ሁሉንም ለምን አላካተተም? ወይንም ስለ ሰለሞን የተጻፉት የታሪክ መጻሕፍት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለምን አልሆኑም? ብሎ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስን ምንነትና ዓላማ አለማወቅ ነው፡፡

3- የያሻር መጽሀፍ

ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም። ኢያሱ 10: 13

በተጨማሪም

የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል።2 ሳሙኤል 1: 18

የያሻር መጽሀፍ አሁን ታዲያ መገኛው ወዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለመሆኑ ማስረጃህ ምንድነው? ይህ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለመካተቱስ ቀርቶብናል ብለህ የምታስበው የሕይወት መርህ ወይንም ነገረ መለኮታዊ ዕውቀት ምን ሊሆን ይችላል ብለህ ታስባለህ?

4- የጠፉ የሰለሞን ምሳሌዎችና መኃልዬች

እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። 1 ነገሥት 4: 32

እነዚህ መፅሀፍት ወዴት ይሆን የሚገኙት?

3000 ምሳሌዎችንና 1500 መዝሙሮችን ለማካተት ሌላ ብሉይ ኪዳንን የሚያክል መጽሐፍ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለሰለሞን ከሰጠው ጥበብ የሚያስፈልገን ያህል ተጽፎልናል፡፡ ሁሉም ስላልተካተተ የቀረብን ነገር አለ ብለህ የምታስብ ከሆነ የቁርኣን ደራሲ ስለ ሰለሞን ተረት መሳይ ታሪኮችን ከሚጽፍ እነዚህን ምሳሌዎች ለምን እንዳልጻፈ ብትጠይቅ ጥሩ ነው፡፡

5- የነብዩ ናታን ታሪክና የባለራእዩ የአዶ ራእይ

የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በኦሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ የተጻፈ አይደለምን? 2 ዜና 9: 29

የነብዩ ናታን ታሪክና የባለራእዩ የአዶ ራእይስ ከወዴት ይገኛል?

በነቢያት የታዩትን ራዕዮች ሁሉና የተጻፉትን መጻሕፍት ሁሉ የሚያካትት መጽሐፍ አንድ ላይብረሪ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ መንፈስ ቅዱስ የመረጣቸው መጻሕፍት በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እናንተስ ቁራጭ የምታክል መጽሐፍ ይዛችሁ አምላካዊ መገለጦች በሙሉ በዚያ ውስጥ እንደተካተቱ እየነገራችሁንም አይደል?

6- የነብዩ ሸማያና የአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሀፍ

የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። 2 ዜና 12: 15

የነብዩ ሸማያና የአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሀፍ አሁን ከወዴት ይገኛል?

የታሪክ መጽሐፍ ሁሉ ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተካተተም ከተባለማ በአይሁድ የተጻፉት የታሪክ መጻሕፍት ሁሉ መካተት ነበረባቸው ልትለን ነው፡፡

7- የነብዩ ኢሳያስ ድርሳን

የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል። 2 ዜና 26: 22

ነብዩ ኢሳያስ የቀረውን የዖዝያንን ነገር የጻፈበት ድርሳኑስ ከወዴት ይገኛል?

በዘመኑ የነበረው ሕዝበ እግዚአብሔር ታሪኩን ለማወቅ ተጠቅሞበታል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ለትምሕርታችን በቂ ነው፡፡

8- የሳሙኤል፣ የናታንና የጋድ ታሪክ

የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል።1 ዜና 29: 29

የሳሙኤል፣የናታንና የጋድ ታሪክ አሁን ላይ ከወዴት ይገኛሉ?

የሳሙኤል መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኙ አለማወቅህ ይገርማል፡፡ ሌሎቹም ተመሳሳይ ታሪክ መዘገባቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስለ ዳዊት ሕይወት በቂ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል፡፡ ጥያቄው ትርፍ ለምን አልኖረንም? የሚል ካልሆነ በስተቀር፡፡

ሲጠቃለል

ይህ ብዙ ትንተና ሳያስፈልገው በግልጽ ቋንቋ የነኝህ ሰዎችና ነብያት ራዕይና ድርሳን ጠፍቷል፡፡ የነብያት ጹሁፍና ራእያቸው አይጠፋም እያሉ የሚከራከሩን ክርስቲያኖች እነዚህ ስያሜያቸው ብቻ ለታሪክ የቀሩ መጽሀፍቶች እንዴት ከምድረ ገፅ ሊጠፉ እንደቻሉ ሊነግሩን ይችላሉ?

የነቢያት ራዕይና የታሪክ መጻሕፍት ሊጠፉ አይችሉም ብሎ የተናገረ ክርስቲያን አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የላካቸው ትውልድ ተሻጋሪ መገለጦችና ትምህርቶች ጠፍተው እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር ይተዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ ሙስሊሞች እንደሚሉትም መጽሐፍቱ ተበርዘው ከተጻፉለት ዓላማ ውጪ የሰው ልጆችን እንዲያስቱ እግዚአብሔር ይፈቅዳል ብለን አናምንም፡፡ ለዚህ ደግሞ ማረጋገጫው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ብዙ ሃያላን ነገሥታት መጽሐፍ ቅዱስን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ቢሞክሩም እነርሱ ጠፍተው መጽሐፉ ድል ነስቶ ዛሬ በስርጭት፣ በተነባቢነትና በተተርጓሚነት የዓለም ቁጥር አንድ መጽሐፍ ሆኗል፡፡ ብዙ የኑፋቄ ቡድኖችና እስልምናን የመሳሰሉት የፓጋኒዝም መሠረት ያላቸው ሃይማኖታት መጽሐፍ ቅዱስን በፈለጉት መንገድ ጠምዝዘው አንዳንዴም “የበርናባስ ወንጌል” እና “ወንጌል በእስልምና መሠረት” የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከእስልምና ፈጠራዎች ጋር የቀየጡ መጻሕፍትን በመጻፍ መጽሐፉን ለመበረዝ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የላካቸው ታላላቅ ነቢያትና መገለጦቻቸው እንዲሁም ስለ ሕዝበ እግዚአብሔር የጻፏቸው ታሪኮች እነዚህን ሁሉ የማጥፋትና የመበረዝ ዘመቻዎች በመቋቋም እስከ ዛሬ ድረስ በእጃችን ይገኛሉ፡፡

ዛሬ በእጃችን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በታሪክ ሁሉ ለሰው ልጆች የሰጣቸውን መልእክቶች በዝርዝርም ሆነ ሐሳባቸውን በመጭመቅ ያካተተ መጽሐፍ እንደሆነ እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች መናገር ከፈለጋቸው መልእክታት ቀርቷል የምንለው የለንም፡፡ እንዲያውም ከአንድ በላይ በሆኑ ምስክሮች መረጋገጥ የሚገባቸው በተለይም ታሪካዊ ክስተቶችን የተመለከቱ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ተዘግበዋል፡፡ ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ አራት የወንጌል ዘገባዎች የተላለፉልን በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ግን ፈጣሪ ለሰው ልጆች የላካቸው መገለጦች ከፊሉ ደብዛው ጠፍቶ ከፊሉ ተበርዞ ትክክለኛ ይዘታቸውን እንኳ ማወቅ እስከማይቻል ድረስ ተበላሽተዋል የሚለች አቋም አላቸው፡፡ ይህ አመለካከት ከታሪክ፣ ከገዛ ቁርአናቸውና ከእውነተኛው አምላክ ባሕርይ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ አለመበረዙን ያረጋግጣል፡፡ በእጃችን የሚገኙት ጥንታዊያን ጽሑፎችና የቅዱሳን አባቶቻችን ትምህርቶች እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ የጠቀሷቸው ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመርያው ይዘቱ ስለመገኘቱ እማኝ ናቸው፡፡ ቁርኣንም በሙሐመድ ዘመን ቶራህ፣ መዝሙርና ኢንጂል በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ እንደነበሩ በማመልከት፣ ለሰው ልጆች ትክክለኛ መመርያ እንደሚሰጡ በመመስከርና አማኞች እንዲታዘዟቸው በማበረታታት እንዲሁም የፈጣሪ ቃል የሚለወጥ አለመሆኑን በማረጋገጥ ይህንን የታሪክ እውነታ ያፀናል፡፡ ዳሩ ግን የቁርኣን ደራሲ የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ባለመሆኑ ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረስ ትምህርት በማስተማር ሐሰተኝነቱን ግልፅ አድርጓል፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የላካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ትውልድ ተሻጋሪ መገለጦች በክፉዎች ተንኮል ተበርዘው እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክርነት በመተው ለቢሊዮኖች መጥፋት ሰበብ የሚሆን ታሪካዊ ስህተት ይፈጽማል ብሎ ማለት ከእውነተኛነቱ፣ ከክብሩና ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡

ማጠቃለያ

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ “የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች” በሚል ርዕስ ጀምሮ ነገር ግን በማስረጃነት የጠቀሳቸው ጽሑፎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው ከመጠቀሱ ውጪ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መሆናቸውን የሚገልፅ ማስረጃ አላቀረበልንም፡፡ አንድ ውጪያዊ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በየትኛውም መጽሐፍ ውስጥ ስለተጠቀሰ ብቻ የመጽሐፉ አካል አይሆንም፡፡ ተውራት፣ ዘቡርና ኢንጂል በቁርኣን ውስጥ ተጠቅሰዋል ነገር ግን የቁርኣን አካል እንደሆኑ የሚያምን ሙስሊም የለም፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ መጻሕፍት ሁሉ “የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች” ተብለው የሚገለጹት በምን ስሌት ነው? ይልቅ የተወሰነ ክፍሉ የጠፋው ቁርኣን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፡፡ የአንድ መጽሐፍ ክፍል “ጠፋ” የሚባለው ምን ሲሆን እንደሆነ ለማወቅ ተከታዩን እስላማዊ ሐዲስ ማንበብ ጥሩ ነው፡-

“አቡ ሀርብ ቢን አቡ አል-አስዋድ አባታቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት አቡ ሙሳ አል-ሸዐሪ የበስራ ቁርኣን አነብናቢዎችን አስጠሯቸው፡፡ ቁጥራቸው ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑቱ መጡ፡፡ ቁርኣንን አነበነቡት፤ እርሳቸውም እንዲህ አሏቸው ‹‹እናንተ አነብናቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን ከበስራ ነዋሪዎች ሁሉ ምርጦች ናችሁ፡፡ ማነብነባችሁን ቀጥሉ፡፡ (ነገር ግን) ለረጅም ጊዜ ማነብነባችሁ ከናንተ በፊት የነበሩትን ሰዎች ልቦች እንዳደነደነ ልቦቻችሁን እንዳያደነድን ተጠንቀቁ፡፡ በርዝመትና በጥንካሬ ከሱራ በረዓት ጋር የሚነፃፀር ሱራ እናነበንብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹የአደም ልጅ በኃብት የተሞሉ ሁለት ሸለቆዎች ቢኖሩት ሦስተኛውን ይመኛል፡፡ ከአፈር ውጪ የአደምን ልጅ ሆድ የሚሞላ ምንም ነገር የለም፡፡›› ከሱረት ሙሰቢሃት መካከል ከአንዱ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ሱራም እናነበንብ ነበር ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የማትፈፅሙትን ነገር ስለምን ትናገራላችሁ? እርሱም በናንተ ላይ ምስክር እንዲሆንባችሁ በአንገቶቻችሁ ላይ ተጽፏል፤ በዕለተ ትንሣኤም ከእርሱ ትጠየቃላችሁ፡፡››” Sahih Muslim 5:2286; Jalal al Din `Abdul Rahman b. abi Bakr al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; Halabi, Cairo, 1935/1354, part 2, p. 25

በዚህ ሐዲስ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለቱ “መገለጦች” በዛሬው ቁርኣን ውስጥ አይገኙም፡፡ ሱራ በረዓት (አት-ተውባ) 129 አንቀፆች ያሉት ሲሆን ይህን ያህል ርዝመት ያለው አንድ ሙሉ ምዕራፍና ሌላ ርዝመቱ ምን ያህል እንደሆነ ያልተገለፀ፤ ነገርግን ‹ሙሰቢሃት› በመባል ከሚታወቁት በቁርኣን ውስጥ ከሚገኙ ሱራዎች ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሱራ መረሳቱ ተነግሯል፡፡ የአንድ መጽሐፍ ክፍል “ጠፋ” የሚባለው ከላይ ያየነው ሁኔታ ሲፈጠር እንጂ ይህ አብዱል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳቀረበው ውንጀላ በመጽሐፉ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰ ውጪያዊ መጽሐፍ መጥፋቱ አይደለም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ቁርኣን እንዲህ ያለ አስደንጋጭ ታሪክ እንዳለው ስለሚያውቁ የገዛ ጉዳቸውን ለመሸፈን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጣታቸውን ይቀሥራሉ፤ “የብልጥ ዓይን ቀድማ ታለቅሳለች” እንዲሉ!

መጽሐፍ ቅዱስ