የውርስ ኃጢአትና የሙስሊም ኡስታዞች ስህተት – ለአቡ ሐይደር የተሰጠ መልስ

የውርስ ኃጢአትና የሙስሊም ኡስታዞች ስህተት

ለአቡ ሐይደር የተሰጠ መልስ

ሙስሊም ወገኖቻችን አጥብቀው ከሚቃወሟቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች መካከል “የውርስ ኃጢአት” አንዱ ነው፡፡ ይህ አስተምህሮ በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በተፈጥሮ በሚታዩት እውነታዎች ድጋፍ ያለው ቢሆንም ለብዙ ሙስሊሞች የሚዋጥ አልሆነም፡፡ የዚህም ምክንያቱ “የውርስ ኃጢአት” ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አለመገንዘባቸው ነው፡፡ የአስተምህሮውን ምንነት በትክክል ቢገነዘቡና የገዛ መጻሕፍታቸውን ቢያገናዘቡ ኖሮ ትክክለኛውን መረዳት አግኝተው ከክርስትና ጋር በተስማሙ ነበር፡፡ ነገር ግን በርዕሱ ላይ የሚጽፉትና የሚያስተምሩት ብዙዎቹ ኡስታዞች አስተምህሮውን የተረዱና የገዛ መጻሕፍታቸውን ያጠኑ ባለመሆናቸው ምክንያት ሙስሊሙ ማሕበረሰብ በተዛቡ መረጃዎች ላይ በተመሠረቱ ሙግቶች ለስህተት ተዳርጓል፡፡ ያለ በቂ መረዳት በጉዳዩ ላይ ለመጻፍ ብዕራቸውን ካነሱት ኡስታዞች መካከል አቡ ሐይደር (ኡስታዝ ሳዲቅ ሙሐመድ) አንዱ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ እርሱ ያቀረበውን ሙግት የምንፈትሽ ይሆናል፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

አቡ ሐይደር፡-

ከአዳም ለወረሳችሁት ኃጢአት ዕዳውን ማን ከፈለላችሁ?

እናንተ ሙስሊሞች ኢየሱስ ስለ ሰው ልጅ ኃጢአት አልሞተም አልተሰቀለም ካላችሁ ከአዳም ለወረሳችሁት ኃጢአት ዕዳውን ማን ከፈለላችሁ? ማንስ ሞተላችሁ?

እኛ መጀመሪያውኑ የኃጢአት ውርስ አለ ብለን መች አምነን ነው ይህን ጥያቄ የምታቀርቡልን? ደግሞስ ከአደም (ዐለይሂ ሰላም) ኃጢአትን ወርሰናል ማለት ምን የሚሉት ፍልስፍና ነው? ኃጢአት በምንም አይነት መልኩ ሊወረስ ወይንም ከአያት ቅድም አያት ወደ ልጅ ሊተላለፍ አይችልም፡፡ እንዴት? የሚል ጥያቄ ከተነሳም፡ ቀጥሎ ያለውን ማብራሪያ በጥሞና ያንብቡ፡

ኃጢአት በውርስ የማይተላለፍ መሆኑን ለመረዳት፡ ቅድሚያ የኃጢአትን ትርጉምና ፍቺ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

መልስ፡-

ቅድሚያ “የውርስ ኃጢአት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መታወቅ ያለበት የመጀመርያው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የውርስ ኃጢአት” የሚል ቃል አለመኖሩ ነው፡፡ ቃሉ አዳምና ሔዋን የሠሩትን የመጀመርያውን ኃጢአት (Original Sin) ለመግለፅ ሰዎች የተጠቀሙት ቃል ነው፡፡ አንዳንዶች ከዚህ ቃል በመነሳት እንደሚያስቡት መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ራሳቸውን ከማወቃቸው በፊት ኃጢአት እንደሠሩ ወይንም ከተጨባጭ ኃጢአት ጋር እንደተወለዱ አያስተምርም፡፡ በክርስትና “የውርስ ኃጢአት” ማለት ሰው ኃጢአትን ከመሥራት ዝንባሌ ጋር ይወለዳል እንዲሁም የኃጢአት ውጤት ሰለባ ይሆናል ማለት እንጂ ራሱን ከማወቁ በፊት ኃጢአት ሠርቷል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በፍጥረቱ የቁጣ ልጅ ነው፤ ለዚህም ምክንያቱ ከተጨባጭ ኃጢአት (Actual Sin) ጋር መወለዱ ሳይሆን ኃጢአትን ከመሥራት ዝንባሌ ጋር መወለዱ ነው (ኤፌሶን 2፡3)፡፡ ስንወለድ ከተጨባጭ ኃጢአት ጋር አልተወለድንም፡፡ ነገር ግን ኃጢአትን ከመሥራት ዝንባሌ ጋር ስለተወለድን ኃጢአተኞች የመሆናችን ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ አይቻለንም፡፡ ሌላው “የውርስ ኃጢአት” ትርጉም የኃጢአትን ውጤት ከአዳም መውረሳችን ነው፡፡ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የሆነው አዳም ኃጢአትን በመሥራቱ ምክንያት ሁላችንም ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ነን (ሮሜ 5፡12)፡፡ ከገነት በመባረር ለምድር ሥቃይ መዳረጋችን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱን እውነታዎች ያላገናዘበ ሙግት ነጥቡን የሳተ ነው፡፡ አቡ ሐይደር በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሁለቱን የውርስ ኃጢአት ግንዛቤዎች አልጠቀሰም፤ ስለዚህ መልስ የሰጠው ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው አመለካከት ሳይሆን ለዘልማድ አስተሳሰብ ነው፡፡

አቡ ሐይደር፡-

ኃጢአት ማለት፡የጌታችንን አላህ ፈቃድ በሀሳብም ሆነ በተግባር መቃወምና ጥሶ መገኘት ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህ፡አንድን ነገር አድርጉ ብሎ ትእዛዝ አስተላልፎ፡ ያን የታዘዝነውን ነገር ማድረግና መፈጸም እየቻልን ከተውነው፣ ወይንም አንድን ነገር አትቅረቡ በማለት ከልክሎን ሳለ፡ እኛ ደግሞ የተከለከልነውን ነገር መተውና መጠንቀቅ እየቻልን ስንዳፈረውና ስንፈጽመው ተግባራችን ኃጢአት ይሰኛል፡፡ የኃጢአት ፍቺው በአጭሩ ይኸው ነው፡፡

መልስ፡-

የክርስትናና የእስልምና የኃጢአት ትርጓሜ እንዲሁ ከላይ ሲታይ የሚመሳሰል ቢሆንም መሠረታዊ በሆነ ሁኔታ ይለያያል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኃጢአት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ከመተላለፍም ያለፈ ተግባር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ መሆኑን ይናገራል፡- “ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው” (1ዮሐ. 3፡4)፡፡ በእስልምና መሠረት አንድ ሰው ኃጢአትን ሲሠራ ራሱን ብቻ የሚበድል ሲሆን (ሱራ 7፡22)፤ በክርስትና መሠረት ግን ኃጢአትን የሚሠራ ሰው እግዚአብሔርንም ጭምር ይበድላል (መዝ. 51፡4)፡፡ በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ትርጓሜ መሠረት ኃጢአት በሰው ልጆች ሁሉ ልብ ውስጥ ከሚገኝ አመፀኛ አስተሳሰብ የተነሳ መጥፎ ሐሳቦችን በማሰብ ጭምር የሚፈፀም ክፉ ነገር ነው (ዘፍ. 8፡21፣ ያዕ. 1፡14፣ ማቴ. 5፡27-28)፡፡ እስልምና ብዙ ጊዜ ይህንን የኃጢአት ገፅታ እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም፡፡ ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ነጥብ እግዚአብሔር ፍፁም ቅዱስ በመሆኑ ምክንያት ኃጢአት ከእርሱ ዕይታ አኳያ በጣም ከባድ ነገር መሆኑ ነው፡፡ እስልምና ኃጢአትን “ማረኝ ማረኝ” በማለት ብቻ የሚታለፍና በሌላ መልካም ሥራ የሚካካስ ስህተት አድርጎ መተርጎሙ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እጅግ በጣም ስህተት ነው፡፡ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና…” (ሮሜ 6፡23)፡፡ “…ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝቅኤል 18፡4)፡፡

አቡ ሐይደር፡-

በዚህ ፍቺ ከተስማማን፡ በውስጡ አንድ የምናገኘው ቁም ነገር ይኖራል፡፡ እሱም፡ነጻ ፈቃድ የሚባለው ዋናው ቁልፍ!፡፡ ጌታ አላህ ፈጽሙ ብሎ ያዘዘንን ነገር፡ ለመፈጸምም ሆነ ለመተው የሚያስችል ውስን ኃይልና ፈቃድ ሊኖረን ግድ ነው፡፡ በተቃራኒው አታድርጉ በማለት የከለከለንን ነገር፡ ለመተውም ሆነ ለመዳፈር የሚያስችለን ፈቃድና ውስን ኃይል ሊኖረን ይገባል፡፡ ትእዛዝና እቀባ ፈቃድ አልባ ለሆነ አካል ትርጉም የሌሽ ነውና፡፡ ወደ ታች ይጓዝ የነበረውን ወንዝ፡ወደ መጣህበት ተመለስ! ማለት ይቻላልን?

መልስ፡-

በኃጢአት ትርጓሜ ውስጥ ነፃ ፈቃድ ዋናው ቁልፍ ከሆነ የእስልምና “ቀዳ ወል ቀድር” አስተምህሮ ውኀ ሊበላው ነው፡፡ እስልምና ሁሉም ነገር በቅድመ ውሳኔ እንደሚመራ ያስተምራል፡-

ሱራ 10፡100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን (ችሎታ) የላትም፡፡ (አላህ ለከፊሎቹ እምነትን ይሻል)፡፡ በእነዚያም በማያውቁት ላይ ርክሰትን ያደርጋል፡፡”

ሱራ 2:6 “እነዚያ የካዱት (ሰዎች) ብታስፈራራቸውም ባታስፈራራቸውም በነርሱ ላይ እኩል ነው፤ አያምኑም፡፡ አላህ በልቦቻቸው ላይ በመስሚያቸውም ላይ አትሞባቸዋል፤ በዓይኖቻቸውም ላይ መሸፈኛ አልለ፤ ለነሱም ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡”

ሱራ 4:88 “በመናፍቃንም (ነገር) አላህ በስራዎቻቸው ወደ ክሕደት የመለሳቸው ሲሆኑ ሁለት ክፍሎች የሆናችሁት ለናንተ ምን አላችሁ? አላህ ያጠመመውን ልታቀኑ ታስባላችሁን? አላህም ያሳሳተውን ሰው ለርሱ መንገድን ፈጽሞ አታገኝለትም።

ሱራ 5:18 “ይሁዶችና ክርስቲያኖችም እኛ የአላህ ልጆችና ወዳጆቹ ነን አሉ። ታዲያ በኀጢአቶቻችሁ ለምን ያሰቃያችኋል? አይደላችሁም እናንተ ከፈጠራችሁ ሰዎች ናችሁ፣ በላቸው፤ ለሚሻው ሰው ይምራል፤ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፤ የሰማያትና የምድርም በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው። መመለሻም ወደርሱ ብቻ ነው።”

ሱራ 5:40 “የሰማያትና የምድር ንግሥና የሱ ፦ የአላህ – ብቻ መሆኑን አላወቅክምን? የሚሻውን ሰው ይቀጣል፤ ለሚሻውም ሰው ይምራል፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው። አንተ መልክተኛ ሆይ እነዚያ በክሕደት የሚቻኮሉት ከነዚያ ልቦቻቸው ያላመኑ ሲሆኑ በአፎቻቸው አመንን ካሉትና ከነዚያም አይሁድ ከሆኑት ሲሆኑ አያሳዝኑህ፤ (እነርሱ) ውሸትን አዳማጮች ናቸው፤ ንግግሮችን ከቦታቸው ሌላ ያጣምማሉ፤ ይህንን (የተጣመመውን) ብትሰጡ ያዙት፤ ባትሠጡትም ተጠንቀቁ ይላሉ። አላህም መፈተኑን የሚሻበትን ሰው ለርሱ ከአላህ (ለመከላከል) ምንንም አትችልም። እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ማጥራትን ያልሻላቸው ናቸው፤ ለነርሱ በቅርቢቱ ዓለም በውርደት አላቸው፤ ለነርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከባድ ቅጣት አላቸው።”

ሱራ 14:4 “ከመልክተኛ ማንኛውንም፤ ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም፤ አላህም የሚሻውን ያጠማል፤ የሚሻውንም ያቀናል፤ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው።”

ሱራ 7:178 “አላህ የሚያቀናው ሰው ቅን እርሱ ነው፤ የሚያጠመውም ሰው እነዚያ ከሳሪዎቹ እነሱ ናቸው። ከጋኔንም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን፤ ለነርሱ በርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፤ ለነሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሉዋቸው፤ ለነሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሏቸው። እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፤ ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፤ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡”

ሱራ :13 “በሻንም ኑሮ ነፍስን ሁሉ ቅንነቷን (እምነቷንም) በሰጠናት ነበር፤ ግን ገሀነምን አጋንንትና ከሰዎች የተሰባሰቡ ሆነው በእርግጥ እመላለሁ ማለት ቃሉ ከኔ ተረጋግጧል፡፡”

አዳም ራሱ የሠራው ኃጢአት ከመፈጠሩ ከአርባ ዓመታት በፊት እንደተወሰነበት በእስላማዊ ሐዲሳት ውስጥ ተጽፏል፡፡ አል-ቡኻሪ ሙሴ አዳምን “ከገነት እንድንባረር ያደረከን አንተ አባታችን ነህ” በማለት በወቀሰው ጊዜ አዳም መልሶ “አላህ ከመፈጠሬ ከአርባ ዓመታት በፊት ወስኖልኝ ለጻፈብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን?” በማለት እንደመለሰለት ዘግቧል፡፡ (Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 77, Number 611)

ስለዚህ ነፃ ፈቃድ በኃጢአት ትርጓሜ ውስጥ ቁልፍ ጉዳይ ከሆነ ከላይ በተጠቀሱት የቁርአንና የሐዲስ ጥቅሶች መሠረት ኃጢአተኞች ኃጢአትን እንዲሠሩ አስቀድሞ የተወሰነባቸው በመሆኑ የአቡ ሐይደር ትርጓሜ አያስኬድም፡፡ የአቡ ሐይደር የኃጢአት ትርጓሜ ትክክል ከሆነ እነዚህ የቁርአንና የሐዲስ ጥቅሶች ስህተት ይሆናሉ፡፡

አቡ ሐይደር፡-

ሰው በአላህ እገዛ ያንን ውስን ኃይሉንና ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ፡ ጌታው ያዘዘው ቦታ ላይ ሲገኝ፡ ስራው ‹‹ጽድቅ›› ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡ ካልሆነም በሸይጧን ቅስቀሳ የተሰጠውን ውስን ኃይልና ነጻ ፈቃድ ተጠቅሞ፡ አላህ የከለከለው ቦታ ሲገኝ፡ ስራው ‹‹ኩነኔ›› ሆኖ ይቆጠራል፡፡ በጥቅሉ ኸይርና ሸር (ጽድቅና ኩነኔ) ተግባራት የነጻ ፈቃድ ውጤቶች ናቸው፡፡ የመረጠውን መልካም ነገር ለመተግበር ነጻ ፈቃድ የሌለው ሆኖ በግዳጅ የሚፈጽም አካል እንዴት ስራው የተመሰገነ ይሆናል? ደግሞስ የተከለከለውን ነገር ጠልቶ ለመራቅ ፈቃድ የሌለው ሆኖ በግዳጅ የሰራ ሰው እንዴት በስራው ሊኮነን ይችላል? በኢስላም አስተምህሮት መሰረት፡ ሃይማኖታዊ ስርአቶች በጠቅላላ የሚያናግሩት ነጻ ፈቃድ ያለውን አካል ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአትም ሆነ የጽድቅ ተግባር በውርስ የሚተላለፍ ንብረት ወይም ልክፍት ሳይሆን፡ በገዛ ራሳችን ድክመት፡ በዕውቀት ማነስ፡ በኢማን አለመጎልበት፡ በሸይጧን አታላይነትሰበብ የምንፈጽመው ተግባር ነው፡፡

መልስ፡-

ነፃ ፈቃድ ይህን ያህል ቦታ ካለውና ያለ ነፃ ፈቃድ እስልምና ትርጉም አልባ ከሆነ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው የቁርአንና የሐዲስ አንቀፆች ሐሰት ሊሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ከሁለት አንዱን መምረጥ ግድ ይላል፡፡ እስላማዊ መጻሕፍት ቅድመ ውሳኔን አጥብቀው የሚያስተምሩ ሆነው ሳሉ አቡ ሐይደር ሙግቱን በሰው ነፃ ፈቃድ ላይ መመሥረቱ አስገራሚ ነው፡፡

ሰው ከኃጢአት ዝንባሌ ጋር መወለዱና የኃጢአትን ውጤት መውረሱ በክርስቲያናዊም ሆነ በእስላማዊ መጻሕፍት የተረጋገጠ በተፈጥሮም ደግሞ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ ማስተባበል አይቻልም፡፡ የዘመናችን ሙስሊሞች የውርስ ኃጢአትን መካዳቸው በተፈጥሮ ከሚታያው እውነታ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍታቸውም ጭምር ያጋጫቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርአን እንዲህ ይላል፡-

“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡ አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡ «ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡” (ሱራ 2፡36-38)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው “ሁላችሁም” የሚለው በአረብኛ ከሁለት በላይ ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ፍርዱ በአዳምና በሔዋን ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ያሳያል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir, Abridged: part 1, Surah Al-Fatiah Surah Al-Baqarah, ayat 1 to 141, pp. 109-110) አላህ የአዳምን ንስሐ እንደተቀበለ ተነግሯል ነገር ግን ከገነት መባረሩ አላህ ኃጢአቱን ይቅር እንዳላለ ያሳያል፡፡ ኃጢአቱን ይቅር ቢለው ኖሮ ለምን ወደ ገነት አልመለሰውም ነበር? ፀፀቱን ተቀብሎ ኃጢአቱን ይቅር ከማለት ይልቅ ፀፀቱን ተቀብሎ ወደ ፊት ለዘሮቹ የሚሆን መመርያን ለመስጠትና ይህንን መመርያ የተከተለውን ሰው ብቻ ለመማር እንደወሰነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡ ይህ የቁርአን ጥቅስ የሰው ልጆች የአዳምን የኃጢአት ውጤት መውረሳቸውን በማረጋገጥ ክርስቲያናዊውን “የውርስ ኃጢአት” እሳቤ ይደግፋል፡፡ ሳሂህ ሙስሊም “ከገነት ያስባረራችሁ የአባታችሁ የአደም ኃጢአት ነው” በማለት ይህንኑ ሐሳብ ያጸናል፡፡ (Sahih Muslim, Book 001, Number 0380)

ቲርሚዚ ሐዲስ የአዳም ክፉ ባሕርይ ወደ ዘሮቹ ሁሉ መዛመቱን እንዲህ በማለት ይገልፃል፡-

“አደም ስለ ካደ ዘሮቹ ሁሉ ካዱ፡፡ አደም ዝንጉ በመሆን የተለከለከለውን ዛፍ ስለበላ ዘሮቹም ዝንጉዎች ሆኑ፡፡ አደም ስለተሳሳተ ዘሮቹ ሁሉ ስህተት ፈፀሙ፡፡” (Al-Tirmidhi Hadith, Number 37; (ALIM CD ROM Version))

አል-ቡኻሪ ደግሞ ሙሴ አዳምን “ከገነት እንድንባረር ያደረከን አንተ አባታችን ነህ” በማለት በወቀሰው ጊዜ አዳም መልሶ “አላህ ከመፈጠሬ ከአርባ ዓመታት በፊት ወስኖልኝ ለጻፈብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን?” በማለት እንደመለሰለት ዘግቧል፡፡ (Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 77, Number 611)

ሳሂህ ሙስሊም “ከገነት ያስባረራችሁ የአባታችሁ የአደም ኃጢአት ነው” ይላል፡፡ (Sahih Muslim, Book 001, Number 0380)

እስላማዊ ምንጮች ከዚህም አልፈው ሴቶች “እስከዛሬ ድረስ ለሚያሳዩት ጸባይ” ሔዋንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡-

“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- በእስራኤል ልጆች ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሥጋ ባልበሰበሰ ነበር፡፡ በሐዋ ምክንያት ባይሆን ኖሮ የትኛዋም ሴት ባሏን ባልከዳች ነበር፡፡” (Sahih al-Bukhari, Volume 4, Book 55, Number 611. Sahih Muslim Book 008, Number 3472)

በተጨማሪም አል-ጠበሪ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ጸሐፊ ሴቶች የወር አበባ የሚፈስሳቸውና “በአስተሳሰብ ደካማ የሆኑት” በሔዋን ምክንያት እንደሆነ ጽፏል፡፡ (ክርስትና እንደ እስልምና ሴቶች በአስተሳሰብ ደካሞች መሆናቸውን አያስተምርም፡፡) (The History of Al-Tabari: General Introduction from the Creation to the Flood, Translated by Franz Rosenthal, SUNY press, Albany, 1998, Volume 1, pp. 280-281)

እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት እስላማዊ መጻሕፍት ስለ ውርስ ኃጢአት ከመጽሐፍ ቅዱስ ባልተናነሰ ሁኔታ ያስተምራሉ፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን የገዛ መጻሕፍታቸውን ማጥናት ያስፈልጋቸዋል፡፡

አቡ ሐይደር፡-

ጽድቅ ተግባር ደግሞ፡በአላህ አጋዥነት (ተውፊቅ) በቁርኣን አመላካችነት፡ በዑለሞች አስተማሪነት፡ በወንድምና እህቶች አስታዋሽነት፡ በገዛ ፈቃዳችን አሳቢነት የምንተገብረው የምርጫችን ውጤት ነው፡፡

መልስ፡-

መልካም ሥራም ሆነ ኃጢአት የነፃ ፈቃድ ውጤቶች መሆናቸውን እናምናለን፡፡ ነገር ግን እስልምና የቅድመ ውሳኔ ትምህርትን በማስተማር ከዚህ እውነታ ጋር የሚጋጭና በውጤቱም እርስ በርሱ የሚጋጭ አስተምህሮ ያለው ሃይማኖት ለመሆን በቅቷል፡፡

አቡ ሐይደር፡-

ብዙም ሩቅ ሳንሄድ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ታሪክ ማየቱ በራሱ ትልቅ አስረጂ ነው፡፡ አደምና ሐዋእ (ዐለይሂማሰላም) ከነበሩበት የድሎት ዓለም (ጀነት) የወጡት በሸይጧን አሳሳችነት የተከለከሉትን ነገር በመዳፈራቸው ምክንያት ነው (አልበቀራህ 35 አልአዕራፍ 19-24 ጣሀ 117-123)፡፡

ታዲያ በወቅቱ አደምና ሐዋእ አትቅረቡ! ተብለው የተከለከሉትን ዛፍ በሸይጧን አሳሳችነት ሲዳፈሩ፡ ምርጫ አልነበራቸውም እንዴ? ሸይጧን በግድ አፋቸውን ይዞ ነው እንዴ ያጎረሳቸው? ከሆነማ፡ ስለነሱም ጭምር የሚጠየቀው ራሱ ሸይጧን ሊሆን ነዋ! አይ ፈቃድ ነበራቸው፡፡ በገዛ ፈቃዳቸው ነው የተሳሳቱት ከተባለ ደግሞ፡ ታዲያ ዘሮቻቸውስ ኃጢአትን የሚፈጽሙት ልክ እንደ ወላጆቻቸው በገዛ ፈቃዳቸው ነው እንጂ ከነርሱ ወርሰው ወይም ሌላ ኃይል አስገድዷቸው ነው ለምን ይባላል? እኛ ልጆቻቸው ከነሱ የወረስነው ኃጢአት ካለና፡ ያንን ኃጢአት ከመፈጸም ውጪ፡ እንዳንፈጽመው ለመቋቋም አቅሙና ፈቃዱ ከሌለን እንደምን በኃጢአተኝነት እንከሰሳለን? ልጁ ከአባቱ በወረሰው በሽታ (እንደ አስምና መሰል ተላላፊ በሽታዎች) ለምን ታመምክ ተብሎ ይወገዛል እንዴ? እኛ ከአባታችን አደም የወረስነው ከሰዋዊነት ጋር የሚያያዙ ተፍጥሮአዊ ባሕሪን እንጂ በፈቃደኝነት የሚተገበሩ ኃጢአትን አይደለም፡፡

መልስ፡-

ቀደም ሲል እንዳየነው ሳሒህ በተባሉት እስላማዊ ሐዲሳት መሠረት አዳምና ሔዋን የተሳሳቱት አላህ አስቀድሞ ስለወሰነባቸው እንጂ ፈቅደውና ወደው አይደለም፡፡ ቁርአንም አላህ ሰዎችን ገሃነም የመክተት ዓላማ ይዞ እንደፈጠራቸው ይናገራል፡-

ሱራ 11፡119፡- “ጌታህ ያዘነለት ብቻ ሲቀር፤ ከመለያየት አይወገዱም፤ ለዚሁም ፈጠራቸው፤ የጌታህም ቃል፣ ገሀነምን ከአጋንንትና ከሰዎች ከሁሉም በእርግጥ እሞላታለሁ በማለት ተፈጸመች። መጨረሻው ይህ ኾነ።”

በተጨማሪም ቁርአን ለሰይጠን ጥመት አላህን ተጠያቂ በማድረግ በተዘዋዋሪ ለአዳምና ለሔዋን ስህተት ምንጩ አላህ መሆኑን ያረጋግጣል፡-

ሱራ 7:16-18 ፦ “ስለአጠመምከኝም ለእነርሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ በእርግጥ እቀመጥባቸዋለሁ አለ።”

ሱራ 15:39 “ኢብሊስ አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔን በማጥመምህ ይኹንብኝ ለነርሱ በምድር ላይ እሸልምላቸዋለሁ፡፡”

ባጠቃላይ በእስልምና የቅድመ ውሳኔ አስተምህሮ መሠረት ሰው ወዶና ፈቅዶ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም፡፡ ሁሉም በአላህ አስቀድሞ የተወሰነ ነው፡፡ ስለዚህ በቁርአን መሠረት አሳቹ ሰይጣን ማሳሳቱም ሆነ ተሳሳቾቹ አዳምና ሔዋን መሳሳታቸው በአላህ ቅድመ ውሳኔ በመሆኑ የሁሉም ጥፋቶች ዋናው ኃላፊነት የአላህ ነው፡፡ ለማሳሳትም ሆነ ለመሳሳት ምርጫ የሌላቸው ፍጡራን ለጥፋታቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ የለም፡፡

አቡ ሐይደር፡-

ቅዱስ ቁርኣን የኃጢአት ውርስ እንደሌለ፡ የአንዱን ኃጢአት ሌላው እንደማይሸከም፡ ስለ አንዱ ኃጢአት ሌላው እንደማይቀጣ በቀጣዮቹ አንቀጾች እንዲህ በተብራራ መልኩ ያስተምረናል፡

በላቸው «እርሱ (አላህ) የሁሉ ጌታ ሲኾን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ (ክፉን) አትሠራም፡፡ ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላይቱን ሸክም (ኃጢአት) አትሸከምም፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደ ጌታችሁ ነው፡፡ ወዲያውም በእርሱ ትለያዩበት የነበራችሁትን ሁሉ ይነገራችኋል፡፡»” (ሱረቱል አንዓም 164)፡፡

የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፤ የተሳሳተም ሰው፣ የሚሳሳተው (ጉዳቱ) በርሷ ላይ ነው፤ ተሸካሚም (ነፍስ፣) የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም፤ መልክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም።” (ሱረቱል ኢስራእ 15)፡፡

ኀጢአትን ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላዋን ሸክም አትሸከምም፤ የተከበደችም (ነፍስ) (1) ወደ ሸክሟ ብትጠራ (ተጠሪው) የቅርብ ዝምድና ባለቤት ቢሆንም እንኳ ከርሷ አንዳችን የሚሸከምላት አታገኝም…” (ሱረቱ ፋጢር 18)፡፡

ብትክዱ አላህ ከናንተ የተብቃቃ ነው። ለባሪያዎቹም ክህደትን አይወድም፤ ብታመሰግኑም፤ እርሱን ይወድላችኋል፤ ማንኛይቱም ኀጢአትን ተሸካሚ ነፍስ፣ የሌላይቱን ኃጢያት አትሸከምም፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደ ጌታችሁ ነው፤ ትሠሩት የነበራችሁትንም ይነግራችኋል፤ እርሱ በልቦች ውስጥ ያሉትን ዐዋቂ ነውና።” (ሱረቱዙመር 7)፡፡

ይልቁኑ ቅዱስ ቁርኣን የሚያስተምረው፡ሰው የሚጠየቀው በገዛ ስራው ብቻ ነው በማለት ነው፡፡ አንዱ በሰራው ጽድቅ ተግባር ሌላው ነገ በቂያም ቀን ተጠቃሚ እንደማይሆን ሁሉ በአንዱ ኃጢአትም ሌላው የሚኮነንበት እና የሚወቀስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሁሉም የሚያጭደው የዘራውን ብቻ ነው በማለት ነው ቁርኣን የሚሰብከው፡፡ ቀጣዮቹ አንቀጾች ይህንን ያስረዳሉ፡

ይህች (የተወሳችው) በእርግጥ ያለፈች ሕዝብ ናት፡፡ ለርሷ የሠራችው (ምንዳ) አላት፡፡ ለናንተም የሠራችሁት (ምንዳ) አላችሁ፡፡ ይሠሩትም ከነበሩት አትጠየቁም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 134.141)፡፡

ይልቁንም በዚያ በሙሳ ጽሁፎች ውስጥ ባለው ነገር አልተነገረምን? በዚያም (የታዘዘውን) በፈጸመው በኢብራሂም ጽሁፎች ውስጥ ባለው አልተነገረምን?) (እርሱም ኃጢአት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም። ለሰውም ሁሉ የሠራው እንጅ ሌላ የለውም። ሥራውም ሁሉ ወደፊት ይታያል። ከዚያም ሙሉውን ምንዳ ይመነዳዋል።” (ሱረቱነጅም 36-41)፡፡

እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም እምነት የተከተልቻቸው፣ ዝርያቸውን በነሱ እናስጠጋለን፤ ከሥራቸውም ምንም አናጎድልባቸውም፤ ሰው ሁሉ በሰራው ሥራ ተያዢ ነው።” (ሱረቱጡር 21)፡፡

ነፍስ ሁሉ በሰራችው ስራ ተያዥ ናት።” (ሱረቱል ሙደሢር 38)፡፡

መልስ፡-

እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች እውነት ከሆኑ ሌሎች ውሸት የሚሆኑ የቁርአን ጥቅሶች አሉ፡፡ የአንዱ ቅጣት ለሌላው የማይተርፍ ከሆነ  በቁርአን መሠረት በሎጥና በኖኅ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች በሠሩት ኃጢአት ህፃናት ስለምን አብረው ጠፉ? (ሱራ 7፡64፣ 10፡73፣ 11፡40-44፣ 25፡37፣ 29፡14፣ 120፣ 54፡9፣ 11-12፣ 54፡34)፡፡ በተጨማሪም ቁርአን ኣድ እና ሠሙድ የተባሉ ሕዝቦች የጅምላ ጥፋት እንደደረሰባቸው ይናገራል (ሱራ 69፡6፣ 54፡18-21፣ 51፡41፣ 41፡13፣ 7፡78፣ 11፡67፣ 26፡158፣ 41፡17፣ 54፡31፣ 91፡14)፡፡ ህፃናቱ ከአዋቂዎች ጋር ያለቁት ምን አጥፍተው ነው? አባቶች በሠሩት ኃጢአት ምክንያትስ ሌሎች የእስራኤላውያን ትውልዶች ስለምን ተወቃሾች ሆኑ? (ሱራ 2:50-52)፡፡

አቡ ሐይደር፡-

ይሄ ነው እውነቱ! ኃጢአት ይወረሳል የምትሉ ወገኖች ሆይ! ጽድቅስ ይወረሳል? አይወረስም ካላችሁ ለምን?

መልስ፡-

አዎ ጽድቅ ይወረሳል፡፡ ክፉ የሠሩ አባቶች የክፋታቸው ውጤት ትውልዳቸውን እንደሚጎዳ ሁሉ መልካም የሠሩ አባቶች ለብዙ ትውልድ የሚተርፍ መልካም ፍሬ እንደሚኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (ዘጸአት 34፡6-7)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ ያመኑት ሁሉ የክርስቶስን ጽድቅ እንደሚወርሱ፤ በእርሱ ሞት ከዘላለም ሞት እንደሚተርፉ ይናገራል፡-

“በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” (ሮሜ 5፡17-19)

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐ. 3፡16)

“እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።” (2ቆሮ. 5፡21)

“ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።” (1ቆሮ. 1፡30-31)

“ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።” (ራዕይ 1፡5-6)

ጌታችን ኢየሱስ መለኮት በመሆኑ ምክንያት የእርሱን ጽድቅ እንድንወርስ ሊያደርገን አይችልም ብሎ ማለት መለኮታዊ ልዕልናን መቃወም ነው፡፡

ውድ ሙስሊሙ ወገኔ! ትክክለኛ መኖርያችን የነበረው ተድላና ደስታ የተሞላበት ገነት ቢሆንም አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ከገነት ስለተባረርን በሰቆቃ በተሞላው ምድር እንድንኖር ተወስኖብናል፡፡ ነገር ግን ቸርና አዛኝ የሆነው ፈጣሪ አምላካችን ከእርሱ ተለይተን ለዘላለም እንድንጠፋ ስላልወደደ የገነትን በር ድጋሜ ከፍቶታል፤ የመመለሻ መንገዱንም እጅግ አቅልሎልናል፡፡ ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

“ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።” (ሮሜ 10፡9-10)

የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ ሰው ሆኖ በመካከላችን ኖሮ የኛን የኃጢአት ቅጣት በመስቀል ላይ በመቀጣት የእርሱን ጽድቅና ቅድስና ሰጥቶናል፡፡ ታድያ ምን ትጠብቃለህ?

“…በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ…” (ሐዋ. 16፡17)

የጀነት በር ተከፍቷል!

የመዳን መንገድ