ኢየሱስና የኒቅያ ጉባኤ – ለሙስሊም ሰባኪያን የተሰጠ መልስ – ክፍል አንድ

ኢየሱስና የኒቅያ ጉባኤ

ለሙስሊም ሰባኪያን የተሰጠ መልስ

ክፍል አንድ

ተቃዋሚዎች ክርስትናን ለመተቸት በተዛባ መንገድ ከሚያቀርቧቸው ታሪካዊ ክስተቶች መካከል የኒቅያ ጉባኤ ዋነኛው ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና የጉባዔው አጀንዳ ባልነበረበትና ርዕሱ እንኳ ባልተነሳበት ሁኔታ በጉባዔው ላይ በድምፅ ብልጫ ተወስኗል የሚለውን የፈጠራ ታሪክ ጨምሮ መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮዎች በሙሉ በጉባዔው ላይ በጳጳሳት የድምፅ ብልጫና በቆስጠንጢኖስ አስገዳጅነት የተወሰነ በማስመሰል መናገር የተለመደ ነው፡፡ በተለይም ሙስሊም ሰባኪያን ስለ ጉባዔው ሲጽፉም ሆነ ሲናገሩ ለታሪክ ሃቀኝነት ምንም ዓይነት ታማኝነትና ጥንቃቄ ሳያሳዩ በድፍረትና በራስ መተማመን የግል ተረቶቻቸውን ይናገራሉ፤ ተከታዮቻቸውም አሜን ብለው ይቀበሏቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ጉባዔውን በተመለከተ በአንድ ሙስሊም ሰባኪ ተጽፎ በኢንተርኔት ላይ በሰፊው እየተዘዋወረ የሚገኝን አንድ ጽሑፍ እንቃኛለን፤ እውነተኛውንም ታሪክ ከተረት ለይተን እናሳያለን፡፡ ሙስሊሙ ጸሐፊ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

ኢየሱስና የኒቅያ ጉባኤ ክፍል አንድ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

መግቢያ

የክርስትና ታሪካዊ ስነ-መለኮት ስንዳስስ በተለይ የኒቅያ ጉባኤ የማይረሳ ታሪክ ነው፣ በኒቅያ ጉባኤ ውስጥ ሁለት አቀንቃኝና ተቀናቃኝ ኤጲስ ቆጶሳት አሉ አንዱ አርዮስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አትናቲዎስ ናቸው፣ ሁለቱም የአንድ መምህር ተማሪዎች ናቸው፣ ሁለቱም ያልተግባቡበት የሙግት ነጥብ አላቸው፣ አርዮስ አብና ወልድ ሄትሮ-ኦሲያ ማለትም የተለያዩ ህላዌዎች ናቸው ሲል አትናቴዎስ ግን አብና ወልድ ሆሞ-ኦሲያ ማለትም በህላዌ ተመሳሳይ ናቸው ብሎ አለ፣ ይህን ሙግት ለመፍታት ከተለያየ ቦታ 118 ኤጲስ ቆጶሳት ኒቅያ በሚባል ቦታ ተሰበሰቡ፣ ጉባኤውን የጠራውና በሊቀ-መንበርነት ሲመራ የነበረው በመንግሥቱ መከፋፈል የፈራው ቆስጦንጢኖስ የሚባል የሮሙ ንጉሥ ነው፡፡

ከላይ በሚገኙት ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ከዓረፍተ ነገሮቹ የበዙ ስህተቶች ይገኛሉ፡፡ አንደኛ፤ በወቅቱ አትናቴዎስ ዲያቆን፣ አርዮስ ደግሞ ቄስ እንጂ ኤጲስ ቆጶሳት አልነበሩም፡፡ ሁለተኛ፤ በቦታው የተገኙት ጳጳሳት ቁጥር በየትኛውም ቆጠራ 118 አልነበረም፤ የመጣጥፉ ጸሐፊ ራሱ በጠቀሰው በማርክ ኤ ኖል መሠረት 230 ነበሩ (Mark A Noll. Turning Points: Decisive Moments in the History of Christianity; 1997, p. 52)፡፡ በብዙ ሊቃውንት መሠረት የጳጳሳቱ ቁጥር ከ250-325 መካከል ነው  (Paul Pavao. In the Beginning was the Logos; 2011, p. 47)፡፡  ሦስተኛ፤ ሁለቱ የአንድ መምህር ተማሪዎች አልነበሩም፡፡ አትናቴዎስ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ የእስክንድር ተማሪ የነበረ ሲሆን አርዮስ ደግሞ የአንፆኪያው የሰማዕቱ ሉቂያኖስ ተማሪ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አራተኛ፤ የአትናቴዎስ አቋም አብና ወልድ በሕላዌ ተመሳሳይ ናቸው የሚል አልነበረም፡፡ የአትናቴዎስ አቋም አብና ወልድ በባሕርይ/ሕላዌ አንድ ወይም የተካከሉ (homoousios) ናቸው የሚል ሲሆን በባሕርይ/ሕላዌ ተመሳሳይ (Homoiousios) ናቸው የሚለው አባባል የክርስቶስን አምላክነት ጥብቅ በሆነ ሁኔታ የማይገልጽ በመሆኑ የተተወ የተለያዩ አቋሞች በነበሯቸው ወገኖች ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ አገላለጽ ነው (J.F. Bethune-Baker. The Meaning of Homoousios in the ‘Constantinopolitan’ Creed; 2004, p. 2)፡፡ አርዮስ አብና ኢየሱስ ፈጣሪና ፍጡር ናቸው የሚል አቋም እንደነበረው ቢታወቅም በሕላዌ/ ባሕርይ የተለያዩ (Heteroousios) ናቸው የሚለው አባባል Anomoeanism የተሰኘ ኋላ ላይ የተነሳ አርዮሳዊ ቡድን የቃል ምርጫ ነው፡፡

ሙስሊሙ ጸሐፊ ይህንን ሁሉ የስህተት ናዳ ካዘነበ በኋላ በማስከተል እንዲህ በማለት ምናባዊ ትረካውን ያስነብበናል፡-

አርዮስ የሙግቱ ነጥብ አስቀመጠ ኢየሱስ ከሁሉ በፊት የተፈጠረ ነው መረጃዬ ይኧው፦

ምሳሌ 8.22

Greek Septuagint-

κύριος ἔκτισέν με ἀρχὴν ὁδῶν αὐτοῦ εἰς ἔργα αὐτοῦ

International Standard Version

“The LORD made me as he began his planning,

1980 አዲስ ትርጉም

እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ፈጠረኝ፥ ከጥንት ጀምሮ የሥራው ተቀዳሚ አደረገኝ።

አትናቴዎስ ቀበል አረገና፦ ፈጠረኝ ተብሎ በግሪኩ ሰፕቱአጀንት የተቀመጠው የዕብራይስጡ ቃል ቃናህ ሲሆን ወደ ግሪክ ሲተረጎም መሆን የነበረበት ክታኦማይ ነው ትርጉሙ *ገንዘቡ አደረገኝ* የሚል ፍቺ አለው፣ በመቀጠል አርዮስ ግሪኩ የተተረጎመበት ዕብራይስጡ የለም፣ የብሉይ ኪዳን ቀዳማይ እደ-ክታብ ሰፕቱአጀንት ነው ከሰፕቱአጀንት በፊት ምንም አይነት የዕብራይስጥ እደክታብ ቅሪት የለም፣ ሁሉም የዕብራይስጥ እደክታብ ከሰፕቱአጀንት ወዲህ የተዘጋጁ ናቸው፣ ኢየሱስ ከሁሉ በፊት የተፈጠረ ነው መረጃዬ ይኧው፦ ኪትዞ ἔκτισέν ፈጠረኝ የሚለው ነው፣ ሰፕቱአጀንት ተሳስቷል ካልክ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ነበር የውይይቱ ነጥብ፡፡ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ ምሳሌ 8.22 ስለ ኢየሱስ ነው የሚያወራው ሲሉ ዘመነኞቹ ፕሮቴስታንት ግን ይህ ለኢየሱስ አይደለም ይላሉ፡፡

የሚገርም ፈጠራ ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ አርዮስ እንደ ተናጋሪ በጉባዔው ላይ ስላልተገኘ ከአትናቴዎስ ጋር እንዲህ ያለ ክርክር አልገጠመም፡፡ ሁለቱ የተወሰነ ሙግት አድርገዋል ቢባል እንኳ ከላይ ሙስሊሙ ጸሐፊ የጠቀሳቸውን ንግግሮች ስለመለዋወጣቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም። ከገዛ ምናቡ የፈጠረውን ንግግር እያስነበበን ነው። የአርዮስ ደጋፊ የነበረው የኒቆሜድያው ጳጳስ አውሳቢዮስ በጉባዔው ላይ ከአትናቴዎስ ጋር የተወሰነ እንደተሟገቱ መረጃ አለ (Pavao፡ 48-49)፡፡ ሌላው ቅጥፈት በክርስቶስ ማንነት ዙርያ በቤተክርስቲያን ውስጥ ውዝግብ በተነሳባቸው በነዚያ ዘመናት ምሳሌ 8፡22 አንዱ አወዛጋቢ ጥቅስ ቢሆንም የግሪኩን ትርጉም መሠረት ያደረገ ክርክር እንጂ ዕብራይስጡን ጠቅሶ ሙግት ያቀረበ ሰው ስለመኖሩ ማስረጃ የለም፡፡ ዕብራይስጡን መሠረት ያደረገ ሙግት ካልተደረገ ደግሞ አርዮስ ስለ ዕብራይስጥ ቀዳሚያን ጽሑፎች አንስቶ የሚከራከርበት ምክንያት የለም፡፡ ጸሐፊው እያስነበበን ያለው ሁሉ ከገዛ ልቡ የፈለቀ እንጂ እውነተኛ ታሪክ ባለመሆኑ ለዚህ ፈጠራው ቅንጣት ታክል ማስረጃ መጥቀስ አይችልም፡፡ በጽሑፉ መጨረሻ ላይ ባስቀመጣቸው ምንጮች ውስጥም ከላይ የተናገረውን የሚደግፍ ምንም ነገር የለም፡፡

ጸሐፊው የግሪክ ቋንቋ ዕውቀት እንደሌለውና ፊደላቱን እንኳ ለይቶ እንደማያውቅ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህም ነው  ἔκτισέν (ኤክቲሴን) የሚለውን “ኪትዞ” ብሎ ያነበበው፡፡ ሥላሴያውያኑ አበው ይህንን ቃል ኢየሱስ በዘላለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘ መሆኑን እንደሚያመለክትና ኢየሱስ ፍጡር ነው የሚለውን ኑፋቄ እንደማይደግፍ በመግለፅ በዘመኑ የነበሩትን የሐሰት መምህራን ዝም አሰኝተዋል፡፡ የእግዚአብሔር ጥበብ ፍጡር ነው ከተባለ እግዚአብሔር ጥበብ አልባ የነበረበት ጊዜ ነበረ ማለት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሐሰት ነው፡፡ ስለዚህ አርዮሳውያን ቃሉን የተረዱበት መንገድ ስህተት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚያው ምዕራፍ ቁጥር 23-25 ላይ ጥበብ የተወለደችና ዘላለማዊት መሆኗ ተገልጿል፡-

ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፡፡”

በምዕራፉ መሠረት ጥበብ ዘላለማዊትና የተወለደች ናት፡፡ ይህም ኢየሱስ በዘላለማዊ መገኘት (Eternal Generation) ከአብ የተገኘ ነው የሚለውን የአበው አቋም የሚደግፍና የአርዮሳውያንን ሙግት ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡

ለግሪኩ ሰብቱጀንት የትርጉም መሠረት የሆነውን ዕብራይስጡን ስንመለከት ደግሞ ቃሉ አስቀድሞ የነበረን ነገር ገንዘብ ማድረግን የሚያመለክት በመሆኑ የአርዮሳውያን አረዳድ ስህተትነቱ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል፡፡ ጸሐፊው የብሉይ ኪዳን ቀዳማይ የእጅ ጽሑፍ ሰፕቱጀንት መሆኑንና ከሰፕቱጀንት በፊት ምንም አይነት የዕብራይስጥ የእጅ ጽሑፍ ቅሪት እንደሌለ የተናገረው ቅጥፈት ነው፡፡ በ1947 በቁምራን ዋሻዎች ውስጥ የተገኙ ብዙ የብሉይ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች አሁን በእጃችን ከሚገኙት ጥንታውያን የሰብቱጀንት የእጅ ጽሑፎች ይቀድማሉ፡፡ የኢሳይያስ ጥቅልልና ብዙ ቁርጥራጮች ሰብቱጀንት ለተተረጎመበት ዘመን በእጅጉ የቀረቡና እንዲያውም ሊቀድሙ የሚችሉ ናቸው፡፡

ሙስሊሙ ጸሐፊ ዲስኩሩን ይቀጥላል፡-

በመቀጠል በድምጽ ብልጫ የአትናቴዎስ እሳቤ ተቀባይነት አገኘ፣ ተመልከቱ የአንበሳው አርዮስን ሙግት ያስተናገደ አንድም ውሃ የሚቋጥር ምላሽ አልነበረም፣ የአርዮስ ሙግት እስከ ዛሬ ተግዳሮትና ማነቆ፣ ሸፍጥና ጋሬጣ ነው፣ በመቀጠል የአትናቴዎስ አንቀጸ-እምነት በጉባኤው ታወጀ ያም አንቀጸ-እምነት ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፣ ከአብ ጋር በህላዌ የተስተካከለ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ የአንድ አብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፣ እርሱም ከአምላክ የተገኘ አምላክ ብሎ ሲያነብ በጉባኤው ከነበሩት መካከል አምስቱ ተቃወሙ፣ እነርሱም አንድ አምላክ አብ ከሆነ ከአንዱ አምላክ አምላክ ከተገኘ አምላክ ሁለት ይሆናል ብለው ተቃወሙ፣ ነገር ግን ጉባኤው ሆነ በመንግሥቱ መከፋፈል የማይፈልገው ቆስጦንጢኖስ በግድ ይህን አንቀጸ-እምነት እንዲቀበሉ ተገደዱ ይህ ነበር የኒቅያ ጉባኤ፣ እግዚአብሔር ወልድ የሚለውም ስያሜ አገልግሎት ላይ የዋለው በዚህ ጉባኤ ነው፣ ኢንሻላህ በሚቀጥለው ክፍል ይህን አንቀጸ-እምነት ተከትለን የተለያየ ነጥቦችን እንዳስሳለን።

አርዮስን “አንበሳ” ብሎ ከሚጠራ ሙስሊም በላይ አስቂኝ ፍጥረት የለም፡፡ አርዮስ ፈጣሪ አምላክ ኢየሱስ የሚባል ሌላ አምላክ ከፈጠረ በኋላ በእርሱ አማካይነት ደግሞ ሌሎች ፍጥረታትን ፈጠረ ብሎ ነበር ያስተማረው፡፡ በአርዮስ መሠረት አንድ ዘላለማዊ አምላክና ሌላ በጊዜ ውስጥ የተፈጠረና ሁሉን የፈጠረ አነስተኛ አምላክ አለ፡፡ በእርሱ እሳቤ ኢየሱስ አምላክና ፈጣሪ ነው ነገር ግን በጊዜ የተገደበ አምላክና የተፈጠረ ፈጣሪ ነው፡፡ ይህ ዓይን ያወጣ ጣዖታዊነት ነው፡፡ እስልምና እንዲህ ያለውን እሳቤ አጥብቆ ይቃወማል፡፡ የሥላሴን አስተምህሮ ስለካደ ብቻ የትምህርቱን አንድምታ ሳያገናዝቡ ማሞገስ ራስን ማቄል ነው፡፡

በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት የአብ ቃልና ጥበብ የሆነው ኢየሱስ በመለኮት ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ አብ ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ ከሆነና ኢየሱስ ደግሞ  አብ ሁሉን የፈጠረበት ጥበብና ቃል ከሆነ ከአንዱ አብ የተነጠለ ሌላ አምላክ ሳይሆን የአብ መለኮታዊ ባሕርይ ተካፋ ነው ማለት ነው፡፡ አብ አንድ አምላክ መሆኑን በመሰከርንበር ቅፅበት ኢየሱስም አንድ አምላክ መሆኑን ተቀብለናል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጠርጡሊያኖስ ሲናገር እንዲህ ያለው፡- “እግዚአብሔርና ቃሉ – አባትና ልጅ – ደግሞም ሁለት ናቸው ብዬ እመሰክራለሁ፡፡ ስርና ዛፍ ሁለት ልዩ ነገሮች ናቸው ነገር ግን የማይነጣጠሉ ናቸው፤ ምንጭና ወንዝ ሁለት ገፅ ናቸው ነገር ግን የማይነጣጠሉ ናቸው …  ከአንድ ነገር የተገኘ ሌላ ነገር የግድ ከመገኛው ሁለት ተብሎ መቆጠር አለበት፡፡ በተመሳሳይ ሥላሴ በተጣመረና በተያያዘ ደረጃ ከአብ የሚመነጭ መሆኑ አሓዳዊ አገዛዙን አይፃረርም፡፡” (Pavao: 38-39)፡፡

አርዮሳዊነት የእግዚአብሔር  ቃልና ጥበብ የሆነውን ኢየሱስን ከአብ በመነጠል ፍጡር ያደርጋል፡፡ እስልምና ደግሞ የእግዚአብሔር ቃልና ጥበብ ፍጡራን አለመሆናቸውን እንዲሁም የማንነቱ አካል መሆናቸውን ያምናል ነገር ግን ኢየሱስ በቅዱሳት መጻሕፍት “የእግዚአብሔር ቃልና ጥበብ” ተብሎ ተጠርቶ ሳለ መለኮትነቱን በመካድ “ፍጡር ነው” በማለት በድርቅና ይከራከራል፡፡ አርዮሳዊነትም ሆነ እስልምና ሐሰት መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም አስተምሕሯቸው እሳትና ጭድ ነው፡፡

በኒቅያ ጉባዔ እስከ መጨረሻው አርዮስን በመደገፍ ከስብሰባው የተሰናበቱ ወገኖች መኖራቸው የታሪክ ሃቅ ነው ነገር ግን የሥላሴያውያኑ አቋም እንደ ፖለቲካ አቋም በዘፈቀደ በድምፅ ብልጫ ተቀባይነት እንዳገኘ ማስመሰል ፈፅሞ የተሳሳተ ነው፡፡ አቋሙ በአብላጫው ጉባዔያተኛ ድጋፍ ያገኘውና አርዮስ የተወገዘው በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ እንጂ በግለሰቦች ውዴታ አይደለም፡፡ በግለሰቦች ውዴታማ ቢሆን ኖሮ ከቆስጠንጢኖስ በኋላ የነገሡት አራት የሮም ነገሥታት አርዮሳውያን በመሆናቸውና አትናቴዎስን ጨምሮ የሥላሴ አማኞችን ሲያሳድዱ ስለነበር አርዮሳዊነት አሸናፊ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን መሠረቱ ሐሰት ስለሆነ የነገሥታት ድጋፍ እንኳ በሁለት እግሮቹ ሊያቆመው አልቻለም፡፡ ከአርዮስ በፊት ከኖሩት አበው መካከል ቅዱሳት መጻሕፍት ወልድ ፍጡር እንደሆነ ያስተምራሉ ብሎ የተረጎመ፣ ያስተማረም ሆነ የጻፈ አንድም የቤተክርስቲያን አባት የለም!

ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር ክፍል ሁለት ምላሻችን ይቀጥላል፡፡

የመጀመርያው ፍጡር ወይንስ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ?

የአዲስ ኪዳን ቀኖና አመጣጥ – እውነታውና የሙስሊም ሰባኪያን ተረት

መሲሁ ኢየሱስ