አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር! ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት የተሰጠ መልስ

አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!

ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት የተሰጠ መልስ


ክርስቶስ ጌታችን “አማኑኤል” መባሉን በተመለከተ አንድ ሰለምቴ ነኝ ባይ ሙስሊም ሰባኪ ለጻፈው ጽሑፍ ምላሽ እንድንሰጥ አንዳንድ ወገኖች ጠይቀውናል፡፡ ጽሑፉ በሙግትም ሆነ በሥነ ጽሑፍ ረገድ ደካማና ለመልስ የማይመጥን ቢሆንም ብዙ ሙስሊም ወገኖቻችን በማሕበራዊ ሚድያ ላይ ከመቀባበላቸው አኳያ መልስ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ታይቶናል፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

አብዱል

3፥47 ፡-ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል አላት፡፡

አምላካችን አላህ የሩቅ ነገር ሁሉ ዐዋቂ ነው፥ ከነቢያችንበፊት የተከሰተው ክስተት ለነቢያችንይተርክላቸዋል። ከተረከላቸው የሩቅ ወሬ መካከል የዒሣ ከመርየም በድንግልና መወለድ ነው፦

3፥47 ፡-ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል አላት፡፡

መልስ

በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው የክርስቶስ የልደት ታሪክ ከሞላ ጎደል በአፖክሪፋ ወንጌላት ውስጥ የሚገኙ ተረቶች ቅጂ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የቁርኣን ደራሲ መገለጡ ከሰማይ እንዳልመጣለትና ከምድራዊ ምንጮች የተቃረመ መሆኑን ከሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ይህ ሃቅ ነው፡፡ ማስረጃዎቹን በዝርዝር ለማየት እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡

አብዱል

በባይብል ስንሄድ ኢየሱስ በድንግልና እንደተወለደ በተመሳሳይ ይናገራል፥ ነገር ግን ዐበይት ክርስትና፦ “የተወለደው አምላክ ነው” የሚል እምነት አላቸው። እዚህ ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸው “ኢየሱስ በትንቢት አማኑኤል መባሉ ነው” የሚል ሙግት ያቀርባሉ፦

ኢሳይያስ 7፥14 ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። לָכֵן יִתֵּן אֲדֹנָי הוּא, לָכֶם–אוֹת: הִנֵּה הָעַלְמָה, הָרָה וְיֹלֶדֶת בֵּן, וְקָרָאת שְׁמוֹ, עִמָּנוּ אֵל.

“ኢማኑ-ኤል” עִמָּנוּ אֵל የሁለት ቃላት ውቅር ነው፥ “ኢማኑ” עִמָּ֥נוּ ማለት “ከእኛ ጋር” ማለት ሲሆን “ኤል” אֵֽל ማለት ደግሞ “አምላክ” ማለት ነው። በጥቅሉ “አምላክ ከእኛ ጋር” ማለት ነው፥ ልክ እንደ “እስማ-ኤል” “ሳሙ-ኤል” “መላል-ኤል” “ባቱ-ኤል” “እስራ-ኤል” ወዘ ተ..ነው። “አምላክ” የሚለው አጫፋሪ ስም መድረሻ ቅጥያsuffix” ሆኖ የመጣ ነው፥ “አምላክ” አጫፋሪ ስም ሆኖ በመድረሻ ቅጥያ ላይ መግባት አምላክነትን ካሳየማ “እስማ-ኤል” “ሳሙ-ኤል” “መላል-ኤል” “ባቱ-ኤል” “እስራ-ኤል” ወዘተ.. አምላክ ይሆኑ ነበር። ቅሉ ግን “ኤል” አምላካዊ ማዕረግን”theo-phoric” እንጂ አምላክነትን በፍጹም አያሳይም።

መልስ

መጽሐፍ ቅዱሳቸውን የሚያውቁ ክርስቲያኖች Theophoric ስሞች በሙሉ አምላክነትን ያሳያሉ የሚል ሙግት አያቀርቡም፡፡ ነገር ግን ስሞቹ ጥቅም ላይ የዋሉበት መንገድ ታይቶ አምላክነትን የሚያሳዩ መሆን አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡ በሒደቱም ሁለት ከግምት ውስጥ መግባት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው የተጠሪው ማንነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተጠራበት አውድ ነው፡፡

ከተጠሪው ማንነት አንፃር ስንመለከት “አማኑኤል” የሚለው ስም አምላክነትን እንዲያሳይ ምክንያት የሆነው ለመሲሁ መዋሉ ነው፡፡ መሲሁ “አማኑኤል” (አምላክ ከእኛ ጋር) ተብሎ ሲጠራ እውነትም አምላክ በመሆኑ መጠርያው አምላክነቱን ለማሳየት የታለመ ነው፤ ምክንያቱም መሲሁ መለኮት መሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በስፋት ተገልጿልና፡፡

የተጠራበትን አውድ ስንመለከት ደግሞ ትንቢቱ ለክርስቶስ መሆኑን የነገረን ማቴዎስ “አማኑኤል” የሚለውን መጠርያ እንዴት ባለ አውድ እንዳስቀመጠው ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የአንድን መጽሐፍ ጭብጥ ለማወቅ መግቢያውንና መደምደሚያውን ማየት አስፈላጊ መሆኑ ምሑራን ሁሉ የሚስማሙበት መርህ ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረት ከሄድን በመግቢያው ላይ ክርስቶስ አማኑኤል (እግዚአብሔር ከኛ ጋር) መሆኑን በመግለፅ የጀመረው ማቴዎስ በመደምደሚያው ላይ ይህንን ነጥብ ሲደግም እንደመለከታለን፡-

“ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28፡18-20)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከአማኞች ጋር መሆን የሚችለው በስፍራና በጊዜ ያልተወሰነ መለኮት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማኑኤል መሆኑን ሲነግረን በዚህ መረዳት ልክ እንጂ ስያሜው ባሕርዩን የማይገልፅ መጠርያ ብቻ ነው በሚል አይደለም፡፡ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አማኑኤል” የመሆኑን እውነታ በመጽሐፉ መዝጊያ ላይ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፉ መካከልም ነግሮናል፡-

“ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፡፡ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና፡፡” (ማቴዎስ 18፡19-20)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማኞች በተሰበሰቡበት ቦታ ሁሉ በመካከላቸው መገኘት መቻሉን የተናገረው ጊዜና ቦታ የማይገድቡት መለኮት ስለሆነ ነው፡፡ በጊዜና በቦታ ሳይገደብ በሁሉም ቦታ መገኘት የሚችል ፍጡር የለም፡፡ ስለዚህ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማኑኤል መሆኑን በመግለፅ ጀምሮ በመጽሐፉ መካከልና መደምደሚያ ላይ በጊዜና በቦታ ሳይገደብ ከአማኞች ጋር እንደሚሆን አፅንዖት መስጠቱ “አማኑኤል” መጠርያው ብቻ ሳይሆን ማንነቱንም የሚገልፅ ስያሜ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ የሙስሊሙ ጸሐፊ ሙግት ውኀ የሚቋጥር አይደለም፡፡

አብዱል

ሲቀጥል ይህ ስም የወጣው በወቅቱ ለተወለደ ሕጻን ነው፦

ኢሳይያስ 8፥3 ”ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች”።

ኢሳይያስ 8፥8 አማኑኤል ሆይ፥ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።

ኢሳይያስ 8፥10 አምላክ ከእኛ ጋር ነውና።

“ነቢይቱ” የተባለችው ሴት ማርያም እንዳልሆነች ቅቡል ነው፥ ያ የተወለውን ሕጻን በሁለተኛ መደብ “አማኑኤል ሆይ” በማለት ያናግረዋል። በወቅቱ የተወለደውን የአማኑኤልን አገር የአሦር መንግስት ሞልቶቷም። በዚህ ጊዜ ምልክቱ አምላክ ከእነርሱ ጋር ነው፥ “አምላክ ከእኛ ጋር ነውና” ተብሎ የተቀመጠው የዕብራይስጥ ቃል “ኢማኑ-ኤል” עִמָּנוּ אֵל መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። ይህ ሕጻን አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ለመሆኑ ምልክት ስለሆነ ስሙ “አማኑኤል” ነው። በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ሲመጡ፥ አምላክ ከሶርያ ጋር የተባበሩትን የኤፍሬምን ነገድ በ 65 ዓመት ውስጥ እንደሚሰባብር ምልክት ይሆን ዘንድ አምላክ አካዝን እንዲጠይቅ ተጠይቆ ለዛ ምልክት ምላሽ “ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች” የሚል ነው፦

ኢሳይያስ 7፥16 ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች።

ኢሳይያስ 8፥4 ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና”።

ይህ ሕጻን አባት ስላለው “አባቱንና እናቱን” የሚል ኃይለ-ቃል እናነባለን።

መልስ

ኢሳይያስ 7-9 ላይ የተጠቀሱት ልጆች ሦስት ሲሆኑ ስማቸውም ያሱብ (7፡3፣) አማኑኤል (7፡14፣ 8፡8)፣ እና ማሔር-ሻላል-ሐሽ-ባዝ (8፡1) ናቸው፡፡ ሙስሊሙ ጸሐፊ አማኑኤልንና ማሔር-ሻላል-ሐሽ-ባዝን እያምታታ ነው፡፡ ኢሳይያስ 8፡1-4 የሚናገረው ነቢዩ ኢሳይያስ ስለወለደው ልጅ ሲሆን የአሦር ንጉሥ በደማስቆና በሰማርያ ላይ የሚፈፅመውን ወረራ ለማመልከት ስሙ ማሔር-ሻላል-ሐሽ-ባዝ (ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ) ተብሎ እንዲጠራ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኢሳይያስ ትዕዛዝ ሰጥቶታል፡፡  ስለዚህ ኢሳይያስ 8፡4 አማኑኤልን የተመለከተ አይደለም፡፡ ያሱብና ማሔር-ሻላል-ሐሽ-ባዝ የኢሳይያስ ልጆች መሆናቸው በግልፅ የተጻፈ ቢሆንም አማኑኤል የኢሳይያስ ልጅ ስለመሆኑ ማስረጃ የሚሆን ነገር በሁለቱ ምዕራፎች ውስጥ አይገኝም፡፡

አብዱል

 “ድንግል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “አልማ” הָעַלְמָ֗ה ሲሆን “ልጃገረድ” “ወጣት ሴት” “ኮረዳ” “ቆንጂት” “ድንግል” “ብላቴናይት” ማለት ነው፦

ዘፍጥረት 24፥43 እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ הָֽעַלְמָה֙ ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ፡ ስላት፥

ዘጸአት 2፥8 የፈርዖንም ልጅ፦ ሂጂ አለቻት፤ ብላቴናይቱም הָֽעַלְמָ֔ה ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች።

ስለዚህ ወጣት ሴት ወይም ድንግል ሴት አሊያም ብላቴናይት ልጅ የምትወልደው አግብታ ነው። ነቢይቱም አማኑኤልን በወቅቱ ወልዳዋለች፥ ልጇ “አማኑኤል” መባሉ አምላክ መሆኑን ወይም አምላክ መወለዱን በፍጹም አያሳያም። ስለዚህ ከመነሻው የኢሳይያስን 7፥14 ዐውደ-ንባብ በወቅቱ ለተወለደ ሕጻን ነው፥ የማቴዎስ ጸሐፊ ይህንን ትንቢት ለኢየሱስ ነው ይለናል፦

ማቴዎስ 1፥22-23 በነቢይ ከጌታ ዘንድ፦ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።

መልስ

“ዐልማህ” የሚለውን የእብራይስጥ ቃል ከዚህ ቀደም ማብራርያ ስለሰጠንበት እንደገና መጻፍ አያስፈልገንም፡፡ ፍላጎቱ ያለው አንባቢ እዚህ ጋ ጠቅ በማድረግ ማንበብ ይችላል፡፡

አብዱል

የማቴዎስ ጸሐፊ እራሱ ማቴዎስ አይደለም። ይህ ሌላ አርስት ነው፥ ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ ከኢሳይያስ 7፥14 “የቀጥታ ጥቅስ”metaphrase quotation” ሲያስቀምጥ በትክክል አላስቀመጠም። ኢሳይያስ “ብላ ትጠራዋለች” የሚለውን አዛብቶ “ይሉታል” ብሎ አስቀምጦታል፥ “ትለዋለች” የሚለውን ለውጦ “ይሉታል” የሚለውን ከየት አምጥቶ ነው? ምን አለ ኮፒ ሲደረግ በትክክል ኮፒ ቢደረግ? ማን ነው የተሳሳተው መንፈስ ቅዱስ ወይስ ጸሐፊው? መንፈስ ቅዱስ ስለማይሳሳት ጸሐፊው ወይም ከጊዜ በኃላ እደ-ክታባትን ያዘጋጁት ተሳስተዋል።

መልስ

የማቴዎስ ጸሐፊ ራሱ ማቴዎስ መሆኑ በጥንት አበው ምስክርነትና በእጅ ጽሑፎች ማስረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ዕውቅ የአዲስ ኪዳን ምሑር የሆኑት ዶ/ር  ቴኒ እንዲህ ይላሉ፡-

“በወንጌሉ ውስጥ ማቴዎስ ጸሐፊው እንደሆነ አልተናገረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ማቴዎስ እንደጻፈው ግን አረጋግጠዋል፡፡ … የመጀመርያውን ወንጌል መነሻ በተመለከተ ከእነኚህ ጥንታዊ ገለፃዎች ብዙ ማጠቃለያ አሳቦች ማግኘት ይቻላል፡፡ አንደኛ የማቴዎስ ጸሐፊነት የሚያከራክር አይደለም፤…” (ሜሪል ሲ. ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217-218)

ሙስሊም ሰባኪያን ከአምላክ የለሽ የክርስትና ተቃዋሚዎች የሰሟቸውን በደመነፍስ ከመድገም የዘለለ በማስረጃ ሲናገሩ አይታዩም፡፡ ይህ ዕውቀት አጠርነታቸውን የሚገልጥ ነው፡፡

ማቴዎስ ጥቅሱን ከኢሳይያስ ሲወስድ “ትለዋለች” የሚለውን ቃል “ይሉታል” በሚል ለምን ለወጠው? ለሚለው ጥያቄ ምሑራን የተለያዩ ምላሾችን ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶች ወንጌላዊው ማቴዎስ ሲጽፍ የነበረው በግሪክ ቋንቋ ስለነበር በዘመኑ ተቀባይነት የነበረውን ሰብቱጀንት የግሪክ ትርጉም እንደተጠቀመ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሚታወቀው የሰብቱጀንት ቅጂ καλέσεις (ትለዋለህ) የሚል ቢሆንም በእርሱ እጅ የነበረው የእጅ ጽሑፍ καλέσουσιν (ይሉታል) የሚል ቃል የያዘ ሊሆን ስለሚችል እርሱን ተጠቅሞ ሊሆን ይችለላል ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከማሶሬቱ ቅጂ በፊት የነበረው የዕብራይስጥ ጽሑፍ አናባቢ ስላልነበረውና 1QIsaa በመባል የሚታወቅ የእጅ ጽሑፍ ארקו የሚል ቃል ይዞ በመገኘቱ καλέσουσιν (ይሉታል) ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ (Novum Testamentum Vol. 43, Fasc. 2 (Apr., 2001), pp. 144-160)፡፡ ዋናው ነጥብ የህፃኑ ልደትና ማንነት በመሆኑ ጥቅሱ በነዚህ መንገዶች ቢተረጎምም የመልእክት ለውጥ እንደማያስከትል መረዳት አስፈለጊ ነው፡፡ ጠሪዋ እናቱ ትሁን ሌሎች ሰዎች የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ እናቱ ከጠራችው ሌሎችም ይጠሩታል፡፡ “አማኑኤል” (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) የሚለው የብዙ ቁጥር አመላካች መሆኑ በራሱ ቅድመ ማሶሬቲክ የነበረውን ጽሑፍ ማቴዎስ “ይሉታል” በሚል መተርጎሙ ከአውዱ ጋር በትክክል ስለሚገጥም ይበልጥ ትክክል አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

አብዱል

ሲቀጥል ኢሳይያስ የጠቀሳት ሴት ልጇን ስሙንም አማኑኤል ብላ እንደምትጠራው ይናገራል፥ ማርያም ግን ልጇን የምትጠራው “አማኑኤል” ብላ ሳይሆን “ኢየሱስ” ብላ ነው፦

ሉቃስ 1፥31 ”እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።

ሉቃስ 2፥21 ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።

ስለዚህ አማኑኤል ብላ ካልጠራችው ኢሳይያስ የጠቀሳት ሴት ማርያም ሳትሆን በወቅቱ የነበረችው ነብይቱ ናት።

መልስ

ይህ “ከዝምታ በመነሳት የመሞገት” ተፋልሶ (Argument from silence) ነው፡፡ ማርያም ኢየሱስን አማኑኤል ብላ እንዳልጠራችው በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንጉሥ ሰለሞን “ይዲድያ” የሚል ሌላ ስም ቢኖረውም ሰዎች በዚህ ስም እንደጠሩት አልተዘገበም፡- “ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው” (2ሳሙኤል 12፡25)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላልተዘገበ ብቻ ማንም በዚያ ስም ጠርቶት አያውቅም ሊባል አይችልም፡፡ ሙሐመድ “አሕመድ” በሚል ሌላ ስም እንደተጠራ ከአንድ ጥቅስም በመነሳት በሙስሊሞች ቢታመንም ማንም ሙሐመድን በዚህ ስም ሲጠራው በቁርኣን ውስጥ አይታይም (ሱራ 61፡6)፡፡ ስላልተዘገበ ማንም በዚህ ስም ጠርቶት አያውቅም ሊባል ይችላልን? ከዝምታ በመነሳት ድምዳሜ ላይ መድረስ የሥነ አመክንዮ ተፋልሶ ነው፡፡

አብዱል

ዋናው የመጣጥፉ ነጥብ ኢሳይያስ 7፥14 “አምላክ ይወለዳል” የሚለው የተንሸዋረረ መረዳት በፍጹም አያሳይም ነው። ፈጣሪ መውለድ እና መወለድ የሚባሉ የፍጡራን ባሕርይ የለውም፦

112፥3 ”አልወለደም አልተወለደምም”። لَمْ يَلِدْ وَلَمْ يُولَدْ

መልስ

ክርስቲያኖች “አምላክ ተወደለ” ስንል ምን ማለታችን ነው? ቀደም ሲል የነበረው መለኮት ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር መጣ ማለታችን እንጂ ልደት የህልውናው መነሻ ነበር ማለታችን አይደለም፡-

“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። … ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 14)

“እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።” (1ጢሞቴዎስ 3፡16)

አምላካችንና ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከዘላለም ጥፋት ለማዳን ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር መጥቷል፡፡ እርሱ ግን ጅማሬና ፍጻሜ የሌለው ዘላለማዊ መለኮት ነው፡፡

አማልክት እንደ ሰው እንደሚዋለዱ በሚያምን አረማዊ ማሕበረሰብ ውስጥ የተወለደ እስልምናን የመሰለ ሰው ሠራሽ ሃይማኖት የአምላክን ዘላለማዊነት ከክርስትና ተምሮ ካበቃ በኋላ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን በማጣመም ክርስቲያኖች አምላክ ጅማሬ እንዳለው የሚያምኑ በማስመሰል መክሰሱ አስገራሚ ነው፡፡

 

መሲሁ ኢየሱስ