እግዚአብሔር በብዙ ቁጥር የተገለጸባቸው ጥቅሶች – አምላካችን ሥላሴ ስለመሆኑ የማይታበሉ ማስረጃዎች

እግዚአብሔር በብዙ ቁጥር የተገለጸባቸው ጥቅሶች

አምላካችን ሥላሴ ስለመሆኑ የማይታበሉ ማስረጃዎች


በክርስትና አስተምሕሮ መሠረት እግዚአብሔር ሥላሴ ነው፡፡ ይህም ማለት አንዱ መለኮት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በተሰኙ ሦስት አካላት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህ አስተምህሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ጠልቆ የተመሠረተ አስደናቂ አስተምህሮ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥሉስ አሓዳዊነት በአዲስ ኪዳን ይበልጥ የተገለጠ ቢሆንም ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ታይቷል፡፡ ከእነዚህ መንገዶች መካከል አንዱ እግዚአብሔር አምላክ በነጠላ ቁጥር ብቻ ሳይሆን በብዙ ቁጥርም ጭምር መገለጹ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተወሰኑ አጋጣሚዎች እነዚህን ጥቅሶች በትክክለኛው መንገድ ቢተረጉሙም (ዘፍ. 1፡26፣ 3፡5፣ 22፣ 11፡7፣ ኢሳ. 6፡8፣ 48፡16) በብዙ አጋጣሚዎች ይህንን ብዝኀነት በትክክለኛው መንገድ ከመተርጎም ይልቅ በነጠላ ቁጥሮች በመተርጎማቸው ሳብያ ከብዙ ወገኖች የተሰወረ ሆኗል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በዋናው የእብራይስጥ ንባብ በብዙ ቁጥር የተነገሩ ሆነው ሳሉ ተርጓሚዎች በነጠላ ቁጥር የተረጎሟቸውን ጥቅሶች እናቀርባለን፡፡ በእግዚአብሔር ሥላሴነት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች መጽሐፍ ቅዱሳችን ለሥላሴ አስተምህሮ የሚሰጠውን የማያወላዳ ምስክርነት በማስተዋል እውነትን ወደ ማወቅ ይመጡ ዘንድ ጸሎታችን ነው፡-

ማሳሰብያ፡- የእብራይስጥ አጻጻፍ እንደ አረብኛ ከቀኝ ወደ ግራ ቢሆንም የኔ ኮምፒውተር ግን የቃላቱን አደራደር ከግራ ወደ ቀኝ አስቀምጧል፡፡

ማሳያ አንድ

ዘፍጥረት 20፡13 “እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት…”

 በዚህ ጥቅስ ውስጥ אֱלֹהִים֮ אֹתִ֗י הִתְע֣וּ כַּאֲשֶׁ֧ר (ካዓሼር ሂትዑ ኦቲ ኤሎሂም) ማለት በአማርኛ እንደተተረጎመው ሳይሆን “ኤሎሂም … ባወጡኝ ጊዜ” ማለት ነው፡፡ הִתְע֣וּ “ሂትዑ” የ תָּעָה (ታህ)  ሦስተኛ መደብ ብዙ ቁጥር ሲሆን “አስኬዱኝ”፣ “አወጡኝ” ወይም “አንከራተቱኝ” (they caused me to wander) ተብሎ በብዙ ቁጥር ይተረጎማል፡፡

ማሳያ ሁለት

ዘፍጥረት 35፡7  “በዚያም መሰውያውን ሠራ፡ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና።”

ይህ ጥቅስ በእብራይስጥ הָֽאֱלֹהִ֔ים אֵלָיו֙ נִגְל֤וּ שָׁ֗ם “ሻም ኒግሉ ኢላው ሀኤሎሂም” ይላል፡፡ נִגְל֤וּ (ኒግሉ) የሚለው ቃል የ גֶּלֶה “ጋላህ” ሦስተኛ መደብ ብዙ ቁጥር ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ “ተገለጡለት” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ጥቅሱ ሲተረጎም “ኤሎሂም በዚያ ተገለጡለት” የሚል ይሆናል።

ማሳያ ሦስት

ዘዳግም 4፡7 “በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?”

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ቅርብ” የሚለው ቃል በእብራይስጥ “ቃሩቢም” קְרֹבִ֣ים የሚል ሲሆን “የቃሮብ” קָרוֹב ብዙ ቁጥር ነው፡፡ ጥቅሱ በቀጥታ ሲተረጎም “ኤሎሂም ለእኛ ቅርብ እንደሆኑ” የሚል ትርጉም ይሰጣል።

ማሳያ አራት

ዘዳግም 10፡16–17 “እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ።”

የእብራይስጡ ንባብ הָאֲדֹנִ֑ים וַאֲדֹנֵ֖י הָֽאֱלֹהִ֔ים אֱלֹהֵ֣י ה֚וּא אֱלֹֽהֵיכֶ֔ם יְהוָ֣ה (ያሕዌ ኤሎሂከም ሁ ኤሎሄይ ሃኤሎሂም ወ አዶኔይ ሃአዶኒም) የሚል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “ያሕዌ አምላኮችህ የአማልክት አምላኮች እና የጌቶች ጌታዎች ነው” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ኤሎሂከም” (አምላኮችህ)፣ “ኤሎሄይ” (አምላኮች)፣ “አዶኔይ” (ጌታዎች) የሚሉት ቃላት ሁሉ ለያሕዌ ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆኑም ብዙ ቁጥር ናቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መሰል ቃላትን በቀጥተኛ ትርጉማቸው ማስቀመጥ ከተለመደው የሰዎች መረዳት አንጻር ወደ መድብለ አማልክትነት የተሳሳተ ድምዳሜ ሊመራ እንደሚችል ስላሰቡ በነጠላ ቢተረጉሟቸውም እውነታው ግን ብዙ ቁጥር አመልካች መሆናቸው ነው፡፡ የሥላሴን ትምህርት ለተረዳ ሰው ግን ጥያቄ የሚፈጥሩ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር በመለኮቱ አንድ ቢሆንም በአካል ግን ሦስት ነው፡፡

ማሳያ አምስት

2ኛ ሳሙኤል7፡23  “ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፡ በአሕዛብና በአምላኮቻቸውም ፊት ከግብጽ በተቤዠው ሕዝብ ፊት ተአምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደ ሄደለት እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ?”

ጥቅሱ אֱלֹהִים הָלְכֽוּ־ (ሐለኩ ኤለሂም) የሚለው የአማርኛ ተርጎሚዎች እንዳስቀመጡት ሳይሆን “ኤሎሂም እንደ ሄዱለት” የሚል ነው ምክንያቱም הָלְכֽוּ־ የ הָלַךְ (ሐለክ) ሦስተኛ መደብ ብዜት ነውና።

ማሳያ ስድስት

ዘጸአት 33፡14-15 “እግዚአብሔርም፦ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን።”

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ” ተብሎ የተተረጎመው በእብራይስጥ יֵלֵ֖כוּ פָּנַ֥י (ፓነይ ይልኩ) የሚል ሲሆን በቀጥታ ሲተረጎም “ኃልዎቴ [ከአንተ ጋር] ይሄዳሉ” የሚል ነው፡፡ “ይልኩ” የሚለው ቃል ነጠላ ሳይሆን ብዙ ቁጥር ነው፡፡ እንዲሁም “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ” የሚለውም הֹלְכִ֔ים פָּנֶ֙יךָ֙ אֵ֤ין אִם־ (ዒም ዒን ፓኔካ ሆለኪም) ተብሎ የሚነበብ ሲሆን “ሆለኪም” የሚለው ቃል ብዙ ቁጥር በመሆኑ “ኃልዎትህ ከኛ ጋር ካልሄዱ” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡

ማሳያ ሰባት

ኢዮብ 35፡10 “ነገር ግን፦ በሌሊት መዝሙርን የሚሰጥ፥ ከምድርም እንስሶች ይልቅ የሚያስተምረን ከሰማይም ወፎች ይልቅ ጥበበኞች የሚያደርገን፤ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም።”

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ፈጣሪዬ እግዚአብሔር” የሚለው በእብራይስጥ עֹשָׂ֑י אֱל֣וֹהַּ (ኤሎሃ ዖሴይ) የሚል ሲሆን “ዖሴይ” የሚለው ቃል ብዙ ቁጥር በመሆኑ ቃል በቃል ሲተረጎም “ኤሎሂም ፈጣሪዎቼ” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡

ማሳያ ስምንት

መዝሙር 58፡11 “ሰውም፦ በእውነት ለጻድቅ ፍሬ አለው፤ በእውነት በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ ይላል።”

መዝሙረኛው ዳዊት שֹׁפְטִ֥ים אֱ֝לֹהִ֗ים “ኤሎሂም ሾፌጢይም” የሚል ብዙ ቁጥር የተጠቀመ ሲሆን ፣ ቃል በቃል ብንተረጉመው “በምድር ላይ የሚፈርዱ ኤሎሂም” ማለት ነው።

ማሳያ ዘጠኝ

ዘዳግም 5፡26 “ከሥጋ ለባሽ ሁሉ እኛ እንደ ሰማን በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሕያው አምላክን ድምፅ ሰምቶ በሕይወቱ የኖረ ማን ነው?”

“የሕያው አምላክን ድምፅ” ተብሎ የተተረጎመው በእብራይስጡ חַיִּ֜ים אֱלֹהִ֨ים קוֹל֩ (ቆል ኤሎሂም ሐይም) የሚል ሲሆን በቀጥታ ሲተረጎም “የሕያዋን ኤሎሂም ድምፅ” የሚል ነው፤  ምክንያቱም  “ሐይም” የሚለው ቅፅል የ חַי (ኸይ) ተባዕታይ ብዙ ቁጥር ነውና፡፡

ማሳያ አሥር

ኢያሱ 24፡19 “ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፡ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም።”

“ቅዱስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል קְדֹשִׁ֖ים  “ቃዶሺም” የሚል ሲሆን “ቅዱሳን” ተብሎ ሊተረጎም የሚችል የብዜት  ቅፅል ነው፡፡ ስለዚህ ምንባቡ “እርሱ ቅዱሳን አምላክ ነው” ተብሎ ቢተረጎም የዕብራይስጡን ሐሳብ ይበልጥ ይገልጻል።

ማጠቃለያ

ከላይ በተመለከትናቸው ጥቅሶች ውስጥ የነጠላና የብዜት ስሞች፣ ቅፅሎች፣ ግሦች፣ ወዘተ. ተሰባጥረው መምጣታቸው እግዚአብሔር በባሕርዩው አንድ ቢሆንም ነገር ግን በአካል ከአንድ በላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስለሆነ የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያጠናክር የማይታበል ማስረጃ ነው። በእርግጥ እነዚህ ጥቅሶች በብዙ ቁጥር ቢናገሩም የቁጥሩን መጠን አይገልጹም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሥላሴነት የሚናገሩ መሆናቸውን ለመረዳት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማገናዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ትምህርተ ሥላሴን የማይቀበሉ ወገኖች በብዙ ቁጥር የተቀመጡትን እነዚህን ቃላት ከእግዚአብሔር አንድነት አኳያ በበቂ ሁኔታ ማብራራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ቃላቱ ከትምሕርተ ሥላሴ ውጪ ሊብራሩ የሚችሉበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡

 

እግዚአብሔር ማነዉ?