የአቡበክር ብልጠትና የቁርኣን ሐሰተኛነት

የአቡበክር ብልጠትና የቁርኣን ሐሰተኛነት


በኸይበር ወረራ ወቅት አንዲት አይሁዳዊት ሴት ባበላችው መርዝ ምክንያት ሲሠቃይ ከቆየ በኋላ ሙሐመድ ለህልፈት መዳረጉ በወቅቱ በነበሩት ሙስሊሞች ዘንድ ድብልቅ ስሜት ፈጥሮ ነበር። ነቢይነቱን ከልባቸው የተቀበሉት ሙስሊሞች የተደናገጡ ሲሆን ነቢይነቱን ከልባቸው ሳይቀበሉ በሰይፍ ተገድደው በአንደበታቸው ብቻ ማመናቸውን የገለጹ በርካታ አረቦች አጋጣሚውን በመጠቀም እስልምናን ለቀው ወጥተው ነበር፤ ለእስላማዊው መንግሥት የሚከፈለውንም ግዴታ ምጽዋት መክፈል አቁመው ነበር። የሙሐመድን ሞት ተከትሎ በችኮላ ሥልጣን የተረከበው የአይሻ አባት አዛውንቱ አቡበክር ሲዲቅ እነዚህን ወገኖች በማስገደድ እንደገና ወደ እስልምና ለመመለስ ሑሩብ አር-ሪዳህ (የክህደት ጦርነቶች) የተሰኙ ተከታታይ ዘመቻዎችን አወጀ። ሙስሊሞቹና ከእስልምና የወጡት ወገኖች የማማ በተባለ ቦታ ውጊያ ገጠሙ። ጦርነቱ የተጠናቀቀው በሙስሊሞቹ አሸናፊነት ቢሆንም ኪሳራው ቀላል አልነበረም። በተለይም ቁርኣንን በቃላቸው የሸመደዱ በርካታ አነብናቢዎች በጦርነቱ ላይ በመሞታቸው ሳብያ በርካታ የቁርኣን ክፍሎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። እስከ ወዲያኛውም ጠፍተው የቀሩ ክፍሎች ነበሩ። በዚህ ሳብያ በዑመር አስታዋሽነት ቁርኣን በአንድ ጥራዝ ይሰበሰብ ዘንድ አቡበክር አዋጅ አወጀ። ይህ ቁርኣንን የማሰባሰብ ሂደት ጥርጣሬን በሚያጭሩ ሁነቶች የተከበበ መሆኑን ለማየት ተከታዩን ጽሑፍ ያንበቡ https://ewnetlehulu.net/abubakr-quran-compilation/

አቡበክር ቁርኣንን በቃላቸው ያጠኑ ሰዎችን ለቁርኣን ጥበቃ ሲል ከመንከባከብ ይልቅ በጦርነት ላይ እንዲሳተፉና እንዲሞቱ ለምን አደረገ? የሚለውን ጥያቄ ሳውጠነጥን አንድ ሐሳብ ተከሰተልኝ። ጉዳዩ የአቡበክርን ብልጠት የሚያሳይ ነው። አላህ በቁርኣኑ እንደተናገረው የቁርኣን ጠባቂ እርሱ ራሱ በመሆኑ ምክንያት ቁርኣንን ማጥፋት አይቻልም (ሱራ 15:9)። በእኔ እሳቤ በአቡበክር አእምሮ ውስጥ የነበረው ሎጂክ ቁርኣንን በቃላቸው ያጠኑት ወገኖች ከሞቱ ቁርኣን ስለሚጠፋ አላህ ለቁርኣኑ ጥበቃ ሲል ቁርኣንን በቃላቸው የሸመደዱ ወገኖችን ከሞት ይታደጋል። እናም አቡበክር እነዚህን ወገኖች ለጦርነቱ ሲመለምል መሞት የማይችሉ ወታደሮችን መመልመሉ ነበር። ነገር ግን ከወታደሮቹ መካከል ብዙዎቹ በጦርነቱ ላይ ስለሞቱ ቁርኣን የመጥፋት አደጋ ተጋረጠበት። በዚህ ሳብያ በአንድ ጥራዝ ይሰብሰብ የሚለውን አጣዳፊ አዋጅ ማውጣት  አስፈለገ። ሆኖም ቁርኣን በሁሉም አነብናቢዎች እኩል በሆነ ሁኔታ ስላልተሸመደደ በርካታ የቁርኣን ክፍሎች በየማማ ጦርነት ላይ ከሞቱት ወገኖች ጋር ሞተው ቀርተዋል። ይህንን በተመለከተ ኢብን አቢ ዳውድ እንዲህ ሲል ጽፏል፦

“ብዙ የወረዱ የቁርኣን ጥቅሶች በየማማ ጦርነት ላይ በሞቱት ብዙ ሰዎች ይታወቁ ነበር … ከጦርነቱ በተረፉት ሰዎች ግን አይታወቁም ነበር እንዲሁም በጽሑፍ አልሠፈሩም ነበር፡፡ ቁርኣን ሲሰበሰብ አቡበክር፣ ዑመርም ሆነ ኡሥማን አያውቋቸውም ነበር፡፡ ከእነርሱ በኋላ በነበረ አንድም ሰው ጋ ማግኘት አልተቻለም፡፡” (Ibn Abi Dawud, Kitab al-Masahif, p. 23)

ሌላ እስላማዊ ምንጭ ስለዚሁ ጉዳይ እንዲህ ሲል ይናገራል፦

“ዑመር አልኸጧብ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኝ አንድ ጥቅስ ጥያቄ ጠየቀ፤ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ «በየማማ ጦርነት ዕለት የተገደለ ሰው ዘንድ ነበር።» …” (Kanz ul Ummal, Volume 2, p. 574)

ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን በርካታ እስላማዊ ምንጮች መጥቀስ ይቻላል።

የአቡበክር ብልጠት አልሠራም። አላህም ለቃሉ ታማኝ ሆኖ አልተገኘም። ቁርኣን ሰው ሠራሽ መጽሐፍ ነው የምንለው በምክንያት ነው።



የሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈትና የቁርኣን ሐሰተኛነት


ሰሞኑን ለጻፍኩት አንድ ጽሑፍ የተወሰኑ አብዱሎች የሰጡትን መልስ እያነበብኩ በጣም ስገረም ነበር። የዳንኤል ቅጥፈት ብለው ጀመሩና የኢብን አቢ ዳውድ ሐዲስ ቅጥፈት ነው ብለው ደመደሙ። የኢብን አቢ ዳውድ ሐዲስ ቅጥፈት ነው ከተባለ መወቀስ ያለበት በገዛ ራሱ ላይ የቀጠፈው እስልምና እንጂ ሌላ ሰው እንዴት ሊሆን ይችላል? ሐዲሶቻችሁ የቅጥፈት ጥርቅም ከሆኑ እያሳታማችሁ ከትውልድ ትውልድ እያስተላለፋችሁ እዚህ ማድርስ ለምን አስፈለጋችሁ? ክርስቲያኖች ሲጠቅሷቸውና ሕዝባችሁን ግራ ሲያጋቡ ጠብቃችሁ “ቅጥፈት ነው!” ብላችሁ ለመጮህ? የአብዱሎች ነገር! ለማንኛውም ጥቂት ሐሳብ ልስጥ።

ኢብን አቢ ዳውድ በእስልምና ታሪክ በዕውቀት እጅግ የመጠቁ ከሚባሉት ሊቃውንት መካከል አንዱ ነበር። ለዚህ ምስክርነታቸውን የሰጡትን በርካታ ሙስሊም ሊቃውንት መጥቀስ ይቻላል።  እርሱ የጻፈውን ሐዲስ ሰበብ ፈልጎ ማጣጣል በጊዜያዊነት ከቅርቃር ለመውጣት ብቸኛ አማራጭ ቢሆንም የሰውየውን ማንነት ከግምት ውስጥ ስናስገባ በቀላሉ የሚታለፍ አይሆንም።

አቢ ዳውድም ሆነ እርሱ ለዘገባው ዋቢ ያደረጋቸው አስተላላፊዎች እምነታቸውን የሚያከብሩ ሙስሊሞች ናቸው። እምነታቸው እውነት እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ እንጂ ለእምነታቸው አደጋ ሊፈጥር የሚችል እንዲህ ያለ አስደንጋጭ ጉዳይ ከራሳቸው ፈጥረው ወይም እውነተኛነቱን ሳያጣሩ ያስተላልፋሉ ማለት ዘበት ነው። ዘመንኛ ሙስሊሞች ምንም ያህል ሰበብ እየፈጠሩ ቢያጣጥሉ ዘገባው “የሐፍረት መሥፈርት” ስለሚያሟላ ሚዛናዊ አእምሮ ያላቸው ወገኖች ሁሉ የሚቀበሉት ነው። አንድ ሰው በጣም ስለሚወደውና ስለሚያከብረው ሃይማኖቱ በተቻለው መጠን መልካም ነገሮችን ይናገራል እንጂ ሃይማኖቱን ሐሰት ሊያሰኝ የሚችል የሐሰት ዘገባ ፈጥሮ ወይም በበቂ ሁኔታ ሳያጣራ አይጽፍም። በሐሰተኛነት መጠርጠር ካለብን ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ የሌለ ይመስል ጥሩ ጥሩውን ብቻ መርጠው የጻፉትን እንጂ ለህሊናቸው ሃቀኛ በመሆን እነርሱ ራሳቸው የሚሸማቀቁበትን እውነት የነገሩንን አይደለም። በምሑራን ዓለም የመረጃ ትክክለኛነት የሚለካው በዚህ መንገድ ነው። እስልምና ግን ሁሉ ነገሩ ግራ ነው።

ሌላው መታወስ ያለበት የሱኒ ሙስሊሞች ተዓማኒ አድርገው በመደቧቸው ምንጮች መሠረት እንኳ አሁን ያለው የኡሥማን ቅጂ በዘመኑ ከነበሩት ሌሎች የቁርኣን ቅጂዎች አንጻር ብዙ ልዩነቶችን እንደሚያሳይ ያደባባይ ምስጢር ነው። ከቃላት ጀምሮ እስከ ምዕራፎች ድርስ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከውስጡ መጉደላቸው በብዙ እስላማዊ ድርሳናት ተዘግቧል። ገሚሶቹ ተሽረዋል በሚል ሰበብ ገሚሶቹ ደግሞ በቂ ሰበብ ሳይገኝላቸው ከኡሥማን ቅጂ ተሰርዘዋል። የኡሥማን ቅጂ ተፎካካሪ እንዳይኖረው ቀደምት ቅጂዎች ሁሉ እንዲቃጠሉ ተደርገዋል። በሙሐመድ ዘመን ተጽፈዋል ከተባሉት የቁርኣ ጽሑፎች መካከል አንዳቸውም በዚህ ዘመን የሉም። “ኦሪጅናል” ሊባል የሚችለው በሐፍሷ ቤት የነበረው የአቡበክር ጥራዝ እንኳ እንዲቃጠል ተደርጓል። ይህ ቁርኣን ከኡሥማን የተለየ ይዘት እንደነበረው ማስረጃ አለ። ጥንታውያን ሺኣዎች ኡሥማንና ተባባሪዎቹ ከ500 የሚልቁ ጥቅሶችን ከቁርኣን ውስጥ ሰርዘዋል የሚል ክስ አቅርበዋል። ለዚህ ሁሉ ማስረጃ ወደ ተከታዩ ገጽ በመሄድ የጻፍናቸውን በርካታ ጽሑፎች ማንበብ ይቻላል። https://ewnetlehulu.net/quran/

ሌላው በጣም ያሳቀኝ ነገር መልስ ለመስጠት የሞከሩት አብዱሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነሱት ትችት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ልዩነቶችን በተመለከተ ለዘብተኛ ምሑራን አንዳቸውም እርስ በርሳቸው እንደማይስማሙ በማጋነን የሚናገሩትን ሐሳብ ጠቅሰዋል። የጥንት ብራናዎች በእጅ ይገለበጡ ስለነበር የፊደል ግድፈቶችና የመሳሰሉት ያጋጥማሉ። በጥንት ዘመን የጽሕፈትና የኮፒ ማሽኖች ስላልነበሩ መጻሕፍት ይገለበጡ የነበሩት ልዩ ክህሎት በነበራቸው የጽሑፍ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በሚገለብጡበት ሰዓት ፊደላትን መግደፍ፣ ቃላትን መዝለል፣ ቦታ ማቀያየርና የመሳሰሉትን ስህተቶች ይሠራሉ፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ከንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የፀዳ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ሥልጣን ከርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ የላቀ በመሆኑ የግልበጣ ስህተቶች ተዓማኒነቱን አጠራጣሪ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአንዱ ብራና ውስጥ የተዘለለ ወይንም ደግሞ የተገደፈ ክፍል ቢኖር በሌሎች ብራናዎች ውስጥ ተስተካክሎ ይገኛል ወይንም ደግሞ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመነሳት ትክክለኛውን አጻጻፍ ማወቅ ይቻላል፡፡ ቴክስቹዋል ክሪቲሲዝም የተሰኘው የጥናት ዘርፍ ያስፈለገው ለዚሁ ነው። የቁርኣን ማኑስክሪፕቶች ራሳቸው በርካታ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንደተገኙባቸው ሙስሊም ሊቃውንት አምነው በተቀበሉበት ዘመን እንዲህ ያለ ክስ ማንሳት የተቺዎቹን አላዋቂነትና ጥራዝ ነጠቅነት ያሳያል። በቅርቡ ዶ/ር ዳን ብሩቤከር ለጻፈው የቁርኣን እርማቶችና ስርዝ ድልዞች መልስ ለመስጠት የሞከሩት የሀገራችን ሙስሊሞች ሳይቀሩ ይህንን እውነታ አልካዱም። በግልበጣ ስህተቶች ምክንያት በቁርኣን ማኑስክሪፕቶች መካከል ያሉት ልዩነቶ ስፍር ቁጥር የላቸውም። “የቂርኣት ልዩነቶች” ተብለው ዕውቅና የተሰጣቸው ከአናባቢ እስከ ተነባቢ የፊደል ልዩነቶችን እንዲሁም የትርጉም ልዩነቶችን የሚያሳዩ ከሠላሳ የሚልቁ የቁርኣን ቅጂዎች በዓለም ዙርያ ይገኛሉ። በዚህ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፤ ዷኢፍ ወይም ደካማ ተብለው የተወገዙ ቢያንስ አራት ቁርኣኖችም ይገኛሉ። ይህንን ሁሉ ጉድ ታቅፎ መጽሐፍ ቅዱስን መተቸት በእውነቱ አሳፋሪ ነው።

በመጨረሻም ለኔ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ላሉት ወገኖች እውነት በምትናገሩት ነገር የምትተማመኑ ከሆነና ቁርኣን በትክክል ተጠብቆ ለዚህ ዘመን መብቃቱን በማስረጃ ማረጋገጥ እንችላለን የምትሉ ከሆነ “ቁርኣን በትክክል ተጠብቋልን?” በሚል ርዕስ በድምፅ የቀጥታ ውይይት እንድናደርግ በአደባባይ በድጋሜ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ። ሰበብ ፈጥራችሁ እንደማትሸሹ ተስፋ አደርጋለሁ።

 

ቁርኣን