የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት [ክፍል ሦስት]
በወንድም ሚናስ
የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የመሲሑን አምላክነት በተመለከተ ምን እንደሚል በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብን እንገኛለን። ካቆምንበት እንቀጥላለን።
“አንቺ ግን፣ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤ ከይሁዳ ነገዶች መካከል ትንሿ ብትሆኚም፣ አመጣጡ ከጥንት፣ ከዘላለም የሆነ፣ የእስራኤል ገዥ፣ ከአንቺ ይወጣልኛል።” — ሚክያስ 5፥2 (አዲሱ መ.ት)
וְאַתָּה בֵּית-לֶחֶם אֶפְרָתָה, צָעִיר לִהְיוֹת בְּאַלְפֵי יְהוּדָה–מִמְּךָ לִי יֵצֵא, לִהְיוֹת מוֹשֵׁל בְּיִשְׂרָאֵל; וּמוֹצָאֹתָיו מִקֶּדֶם, מִימֵי עוֹלָם.
እንደ አዲስ ኪዳን ሁሉ (ማቴ. 2:5-6) የአይሁድ ሊቃውንትም ትንቢቱ ስለ መሲሑ መሆኑን ተናግረዋል[1]። ቀጣዩ ሊመረመር የሚገባው ነገር፣ ነቢዩ የገዢውን አመጣጥን ሲገልጽ ከ “ጥንት” (קֶדֶם) ይኸውም ከ “ዘላለም” (עוֹלָם) መሆኑን ይናገራል። ይህ በግልጽ የመሲሑን ቅድመ ህልውና አመልካች ነው። קֶּ֖דֶם “ቄዴም” የሚለው ቃል ዘላለማዊ የሚል ሐሳብ ሊኖረው የሚችልባቸው ምሳሌዎች እዚህ አሉ።
“ዘላለማዊ (קֶּ֖דֶם) አምላክ መኖርያህ ነው፤ የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው።” — ዘዳግም 33፥27 (አዲሱ መ.ት)
“እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዘላለም (קֶּ֖דֶם) ጀምሮ ያለህ አይደለህምን?” — ዕንባቆም 1፥12 (አዲሱ መ.ት)
ከላይ እንዳየነው קֶּ֖דֶם “ቄዴም” በተለያዩ ሁኔታዎች በተለያዩ መንገዶች ለያሕዌ ጥቅም ላይ ውሏል።
እንዲሁም עוֹלָם “ዖላም” የሚለው ቃል መሲሑንም ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ ይህንን ቃል የሚጠቀሙ የተወሰኑ ምንባባትን እናቀርባለን፦
“አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለም (עוֹלָם) አምላክን ስም ጠራ።” — ዘፍጥረት 21፥33 (አዲሱ መ.ት)
“አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም (עוֹלָם) አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።” — ኢሳይያስ 40፥28 (አዲሱ መ.ት)
“እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም (עוֹלָם) ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።” — ኤርምያስ 10፥10 (አዲሱ መ.ት)
በሚክያስ 5፥2 ላይ በዕብራይስጡ ንባብ ውስጥ “ከጥንት” ተብሎ የተተረጎመው “ሚቄዴም” מִקֶּ֖דֶם የሚለው ቃል ሲሆን የበኵረ ጽሑፉ ቃል የሁለት ቃላት ውቅር ነው፤ ይኸውም מ (“ሚ”) “ከ” ከሚል ቅድመ ቅጥያ መስዋድድ (Prefixed preposition) እና קֶּ֖דֶם “ቄዴም” ማለትም “ምስራቅ” ወይም ከፀሐይ መውጣት ጋር በተያያዘ መልኩ ሊጠቀስ የሚችል ቃለ ነው [2]። የ “ሚቄዴም” ትርጉም ላይ ተጨማሪ ግንዛቤን ከአይሁዳውያን ታልሙድ ማግኘት ይቻላል፦
“የኤደን ገነት የተፈጠረችው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነው እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ (ሚቄዴም)፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ ዘፍ2፥8፤” በምሥራቅ ተብሎ የተተረጎመው [ሚቄዴም]” የሚል ነው። ሚቄዴም፣ ማለትም ዓለም ሳይፈጠር በፊት ማለት ነው።”[3]
ስለዚህ በሚክያስ 5፥2 קֶּ֖דֶם “ቄዴም” የሚለው ቃል፣ מ “ሚ” ቅድመ-ቅጥያ መስተዋድድ ጋር ስለተዋቀረ “ከፀሐይ በፊት” ወይም “ዓለማት ከመፈጠራቸው አስቀደሞ ነበር” የሚል ትርጉም ይኖረዋል።
ይልቁንም ደግሞ “ጥንት” (קֶדֶם “ቄዴም”) እና “ዘላለም” (עוֹלָם “ዖላም”) የሚሉት ቃላት ሁለቱ ቃላት በጥምር ሆነው ኑባሬን ለመግለጽ ከያሕዌ እና ከመሲሑ ውጪ ለየትኛውም ፍጥረት ግልጋሎት ላይ ውለው አያውቁም። ቃላቱ ህላዌን ለመግለጽ በሚገቡበት ጊዜ ያልተፈጠረ ቅድመ-ህልውናን ያሳዩልና።
አይሁዳዊው ሊቅ ዶክተር ሚካኤል ራይደልኒክ ይህንን በተሻለ ሁኔታ ገልጾታል፦
❝መዝ 90፡2 “ገና ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ በፊት፣ አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ” ይላል። ልብ በሉ፤ ቄዴም እና ዖላም አንድ ላይ ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ ሁልጊዜም ዘላለማዊነትን ያመለክታሉ (ምሳሌ 8፡22-23፤ ዘዳ. 33፡27 ይመልከቱ)። በሚክያስ 5፥2 ውስጥ፣ እነዚህ ቃላቶች ጥንድ ሆነው መቀመጣቸው መሲሑ ከቤተልሔም በፊት ቅድመ-ዓለም መኖሩን ያሳያል።❞[4]
ከላይ በዳሰስነው ሐቲት መሠረት ሚክያስ 5፥2 የጌታችንን ቅድመ-ህልውና እንደሚያመለክት በቂ ማሳያ ነው። እኛም በቅድስና ሕይወቱ እጅግ ምስጉን የሆነው የነገረ መለኮት ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በሚክያስ ላይ የሰጠውን አንድምታ በማቅረብ ይህንን ክፍል እናጋባድዳለን፦
“እግዚአብሔርን መምሰልን እንደተረዳችሁ እንዲሁ በዘላለማዊ ህላዌ ከእርሱ የነበረውን አንድያ ልጁን ማወቅም ይበጠበቅባችኋል። በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ሳይሆን ከዘመናት በፊት የነበረ ነውና። ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ ብሏልና፦ “አንቺ ቤተ ልሔም ሆይ፥ የኤፍራታ ቤት ሆይ፥ ከይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኛለሽ። ከአንቺ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ አለቃ ወደ እኔ ይወጣል፤ አወጣጡም ከጥንት ጀምሮ ከዘላለም ዘመን ጀምሮ ነው።” እንግዲህ አሁን ከቤተልሔም መምጣቱን ብቻ አትመልከቱ፤ ነገር ግን ከዘላለም ፊት ከአብ በመወለዱም አምልኩት። ማንም ወልድ በጊዜ መጥቷል ጅማሬ አለው እንዲላችሁ አትፍቀዱ፤ ነገር ግን ጊዜ የማይሽረው ጅማሬ የሌለውን አብን አስተውሉ። ወልድም እንዲሁ ጊዜ የማይሽረው የማይመረመርም መጀመሪያ የሌለው ነው።” [5]
ማጣቀሻዎች
[1] Targum Jonathan on Micah
[2]G. Johannes Botterweck, Theological Dictionary of the Old Testament; Vol I (Volume 1) p. 506
[3] Babylonian Talmud, Nedarim 39b
[4]Rydelnik, The Messianic Hope: Is The Hebrew Bible Really Messianic? [B&H Publishing Group, Nashville, TN 2010] 7. Decoding the Hebrew Bible: How the New Testament Reads the Old, p. 98.
[5] Cyril of Jerusalem, Catechetical Lectures 11