የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት [ክፍል አራት]

የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት [ክፍል አራት]

ወንድም ሚናስ

ብሉይ ኪዳን ያሕዌ አቻ እንደ ሌለውና ማንኛውም ፍጥረት (በሰማይም ሆነ በምድር ላይ) እንደ እርሱ እንዳልሆነ የነቢያት ጽሑፎች አበክረው ይናገራሉ፦

““ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር እኩል ታደርጉኛላችሁ? እንመሳሰልስ ዘንድ ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ?” — ኢሳይያስ 46፥5 (አዲሱ መ.ት)

“ቅዱሱ፣ “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።” — ኢሳይያስ 40፥25 (አዲሱ መ.ት)

እነዚህ ጥቅሶች የትኛውም የተፈጠረ ማንነት ከያሕዌ ጋር ሊተካከል እንደማይችል በአጽንኦት ይናገራሉ፣ ይህም ወደ ቀጣዩ ነጥቤ ይመራኛል።

ትንቢተ ዘካሪያስ ላይ ያሕዌ ከራሱ ጋር አስተካክሎ የሚጠራው አንድ የተለየ ሰው እንዳለ ተገልጿል። ነቢዩ ዘካርያስ እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ በደል የሚታረድ እረኛ እንደሚነሳ እስራኤልም  የሚበተንበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል፦

“ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ (עָמִית) በሆነው ሰው (גֶּבֶר) በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ።” — ዘካርያስ 13፥7

[የዚህ ትንቢት ፍጻሜ በማቴዎስ 26፥31 እና በማርቆስ 14፥27 ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ተጠቅሷል።]

ስለዚህ የዘካርያስ 13፥7 ቁልፍ ሃሳብ ለመረዳት עָמִית “ዓሚቲ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ማወቅ አስፈላጊ ነው። ቅጽሉ “ጓደኛዬ/ባልንጀራዬ” ወዘተ. የሚል ትርጕም ያለው ነው። ትንቢተ ዘካርያስን ጨምሮ  አሥር ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን በዘሌዋውያን 9 ላይ ተመሳሳይ ቃል ጥቅም ላይ ውሏል። በእነኚህ ቦታዎች ውስጥ ለወንድም ወይም ለደም ዘመድ አሊያም  እጅግ ቅርብ ለሆነ አካል  የሚጠቀስ ቃል ሆኖ  ነው የመጣው።

“ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጒዳት ቢያደርስ የዚያው ዐይነት ጒዳት ይፈጸምበት፤” — ዘሌዋውያን 24፥19 (አዲሱ መ.ት)

ዘሌዋውያን 19፥11፣15፣17፦ ❝አትስረቁ፤ “ ‘አትዋሹ፤ “ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን (בַּעֲמִיתוֹ) አያታል። …ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን *ለባልንጀራህ* (עֲמִיתֶֽךָ) በትክክል ፍረድ።…ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን *ባልንጀራህን*( עֲמִיתֶ֔ךָ) በግልጽ ገሥጸው።❞ (አዲሱ መ.ት)

“ዓሚቲ”(עָמִית) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል אָח “ኣሕ” (“ወንድም”) ከሚለው ጋር በተለዋዋጭነት ይመጣል፦

ወንድምህን (אָחִ֖יךָ) በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን (עֲמִיתֶ֔ךָ) በግልጽ ገሥጸው።” — ዘሌዋውያን 19፥17 (አዲሱ መ.ት)

በተጨማሪም እነዚህን ጥቅሶች ይመልከቱ፦(ዘሌዋውያን 6፥2፣ 18:20፣ 25:14-15፣ 17)

በአጭሩ፣ ቃሉ አንድ ዓይነት ማንነት ያለውን ተመሣሣይ ኑባሬን (Essence) ለተላበሰ አካል የሚያገለግል ነው። በሚያስደንቅ ሁኔታ ይህ ጥቅስ አንዳንድ የአይሁድ ረቢዎችን ግራ ቢያጋባቸውም እንኳ የያሕዌ እረኛ ከያሕዌ ጋር እኩል ነው የሚለውን ክርስቲያናዊ ትርጓሜ ደግፈዋል፦

“Smite the shepherd.”–The wicked prince. But the wise man, R. Abraham Ibn Ezra, has interpreted this prophecy of the great wars which shall be in all the world in the days of the Messiah, the son of Joseph. And the meaning of “my shepherd” is, *Every king of the Gentiles whom God has caused to rule over the earth, and he thinks himself to be as God, therefore he says, “Against the man my fellow;” i.e., who thinks of himself that he is my fellow.*

ትርጕም ፦ “እረኛውን ምታ” – ክፉው ልዑል። ነገር ግን ጠቢቡ ረቢ አብርሃም ቤን ዕዝራ በዮሴፍ ልጅ በመሲሕ ዘመን በዓለም ሁሉ ስለሚደረጉት ታላላቅ ጦርነቶች ትንቢት ተርጉሞታል። እረኛዬም ማለት  እግዚአብሔር በምድር ላይ እንዲነግሥ ያደረገው የአሕዛብ ንጉሥ  ራሱን እንደ እግዚአብሔር አድርጎ ስለሚቆጥር፣ “በሰውዬው ላይ ባልንጀራዬ” ይላል። ማለትም እሱ (ያሕዌ) የእኔ ባልንጀራ ነው ብሎ ራሱን የሚያስብ ነው።

ምንም እንኳን እነሱ አማልክት ነን ብለው የሚያምኑትን ክፉ የአሕዛብ ገዥዎችን እንደሚያመለክት በመናገር ለማስረዳት ቢሞክሩም “ዓሚቲ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል እረኛው ከያሕዌ ጋር የሚተካከል ሰው እንደሆነ የሚገልጽ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

ስመጥሩ የብሉይ ኪዳን ሊቅ ዋልተር ኬይሰር “መሲሑ በብሉይ ኪዳን” በሚለው መጽሐፋቸው ይህንን ብለዋል፦

❝ይህ እረኛ ማን ነው? በርግጠኝነት እርሱ ተራ የበጎችና የፍየሎች እረኛ አይደለም፣ ምክንያቱም በጌታ ‘እረኛዬ’ ተብሎ ተጠርቷል (ቁ. 7)። ከዚህም በላይ “ባልንጀራዬ የሆነ ሰው” ተብሏል። ይህ ትልቅ ውዳሴ ነው፣ ምክንያቱም በዘሌዋውያን ‘ባልንጀራዬ ‘ ወይም ‘የቅርብ ወዳጄ’ የሚለው ቃል የቅርብ ዘመድን ያመለክታልና። ስለዚህ እረኛው ከያሕዌ ጋር እኩል መሆኑን ያሳያል።❞

ታዋቂው ፀረ-ክርስትያን የሆነው ረቢ ቶቪያ ሲንገር (Rabbi tovia singer) ለክርስትና ምላሽ ባለ 2 ጥራዝ መጽሐፉ ውስጥ ዘካርያስ 13፥1-6 እና ዘካርያስ 8፥9ን ሲጠቅስ ዘካርያስ 13፡7ን ፈጽሞ አለመናገሩ አስገራሚ እውነታ ነው።

በአጠቃላይ እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎች በአንድ ላይ በማጤን ዘካርያስ 13፥7 መሲሐዊ ትንቢትና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ማረጋገጫ ስለመሆኑ ጠንከር ያለ ማስረጃ ያቀርባል።


[1] Rabbi David Kimchi. Commentary Upon The Prophecies Of Zechariah Translated From the Hebrew With Notes And Observations On The Passages Relating To The Messiah. pp. 167-168 [2] Walter C. Kaiser. The Messiah in the Old Testament. pp. 226-227


መሲሁ ኢየሱስ