2ኛ ቆሮንቶስ 3 እና የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት
በወንድም ሚናስ
በዚህ መጣጥፍ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 ውስጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ አካላዊነትና መለኮትነት ላይ መጠነኛ ትንታኔ እናቀርባለን። በዚህም “መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም”፤ “ከአብ የሚወጣ ኃይል ብቻ ነው” የሚለው አስተምህሮ የተሳሳተ መሆኑን እናስገነዝባለን።
ቍጥር 6፦
“…. መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።”
…τὸ δὲ πνεῦμα ζῳοποιεῖ.
ζωοποιέω “ዞፖይኦ” የሚለው ግስ “ሕያው ማድረግ፣ ሕይወትን መስጠት” የሚል አንድምታ አለው። በመዝሙረ ዳዊት 36፥9 ላይ ስለ ሁሉን ቻይ አምላክ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህም ብርሃንን እናያለን” ሲል፣ ቅዱስ ጳውሎስም “ለሁሉም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር ፊት አዝሃለሁ” በማለት ፈጣሪነት የመለኮት ግብር መሆኑን ይነግረናል። ከ2ኛ ቆሮንቶስ 3፥6 በተጨማሪ ብሉይ ኪዳንም በተመሣሣይ ስለ መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪነት የሚንገረን አለው፦ “የእግዚአብሔር መንፈስ (רוּחַ־אֵל) ፈጠረኝ (עָשָׂתְנִי) ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ።” (ኢዮብ 33፥4)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ የዕብራይስጡ አወቃቀር አስገራሚ ነው። ይኸውም፣ “ሩሓ-ኤል” רוּחַ־אֵל (የእግዚአብሔር መንፈስ) ካለ በኋላ “ዓሳቴኒይ” עָשָׂתְנִי የሚል ሲሆን “ፈጠረኝ” ተብሎ ተተርጉሟል። የዕብራይስጡ ቃል አንስታይ፣ ነጠላ ቁጥር ነው። ቃል በቃል “እሷ ፈጠረችኝ” የሚል ይሆናል። ምክንያቱም “መንፈስ” רוּח “ሩሓ” ሰዋሰዋዊ ጾታው አንስታይ ነውና። ስለዚህ “ፈጠረኝ” የሚለው ቃል የመንፈስን ግብር እየገለጠ ከመንፈስ (“ሩሓ” רוּח ) ጋር ስሙሙ ለመሆን በአንስታይ ጾታ ተቀምጧል። ይኸውም መንፈሱ የሌላ አካል ማንነት ሳይሆን ራሱን የቻለ አካል መሆኑ በዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ሆኖ መዋቀሩ ምስክር ነው። የሰብዓ ሊቃናት ትርጕምም ይህንን ጥቅስ “መለኮታዊው መንፈስ ፈጠረኝ (πνεῦμα θεῖον τὸ ποιῆσάν με)” ብሎ የተረጎመው በዚህ አግባብ ነው።
ቍጥር 17፦
“ጌታ መንፈስ ነው፤…..”
ὁ δὲ κύριος τὸ πνεῦμα ἐστιν·
ከላይ የሚገኘው የአማርኛ ቅጂ የትርጕም ህፀፅ አለበት። ይኸውም በሚከተለው ሰዋስዋዊ አወቃቀር ምክንያት ነው፦ κύριος “ኩሪዮስ” የሚለው ቃል ሙያዊ ባለቤት (Predicate Nominative) ሲሆን፤ πνεῦμα “ፕኒውማ” የሚለው ደግሞ ስማዊ ባለቤት (Subjective Nominative) ነው። ይኽንንም የምናውቀው፣ πνεῦμα “ፕኒውማ” ከሚለው ቅጽል ፊት τὸ “ቶ” የምትል መስተኣምር በመኖሯ ነው። ስለዚህ አረፍተ ነገሩ በቀጥታ ሲተረጎም “መንፈስ ጌታ ነው” የሚል ይሆናል። ይኽውም ማንነቱ መንፈስ ምንነቱ ደግሞ ጌትነት ይሆናል ማለት ነው። ቀለል ባለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ሓሳቡን ግልጽ ለማድረግ ልሞክር፦ ዮሐ 4፥24 “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” (πνεῦμα ὁ θεὸς) በዚህ ጥቅስ ውስጥ “እግዚአብሔር” (በግሪኩ θεὸς) የሚለው ὁ የምትል መስተኣምር ስትኖር πνεῦμα የምትለዋ ላይ ግን የለችም። ስለዚህ የጥቅሱ ዋናው ንሑስ ስም “እግዚአብሔር” ሲሆን ምንነቱ ደግሞ መንፈስ (πνεῦμα) ነው። በተመሳሳይ 2ቆሮንቶስ 3፥17 የክፍሉ ዋናው ባለቤት (Subjective Nominative) መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ጌታ የሚለው ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ባሕርይ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ያለ መለኮታዊ ማንነት ነው።
ይህንን ጥቅስ አስመልክቶ የተለያዩ የቤተክርስቲያን አባቶች የግሪኩን ሰዋሰው ዋቢ በማድረግ ጥቅሱ የመንፈስ ቅዱስን ጌትነት በሚያመለክት መልኩ አስቀምጠውታል። ለምሳሌ ዮሐንስ አፈወርቅ “በቍጥር 17 መንፈስም ጌታ ነው፤ ይላል። ስለ ጰራቅሊጦስም እንደ ተናገረ ዕወቁ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ ይላልና።” (2 Corinthians 3 Homilies of Chrysostom)
ስናጠቃልል መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና እንደ ወልድ ሁሉ ማንነት ያለው በክብሩ ጌታ እና በግብሩ ፈጣሪ እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት ኃይል ብቻ አይደለም።