የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል ሦስት]
ዶ/ር ሻሎም መኮንን
የፅንስ አጀማመር
የቁርአን እና የስነ-ፅንስ ሳይንስ ተቃርኖ እስካሁን ባየነው አያበቃም። በቁርአን ገለፃ መሰረት ከእርግብግቢት (ተረዒብ) እና ከጀርባ (ሱልብ) መካከል የሚወጣው የወንዱ ተስፈንጣሪ ውሃ ወደ ሴቷ ማህፀን ውስጥ ይገባል ፤ ይህ ወደ ሴቷ ማህፀን የገባው ጠብታ በመቀጠል የረጋ ደም ይሆናል። የኢስልምና ድርሳናት ስለ-ፅንስ አጀማመር ያሉትን በማስቀደም ንፅፅራችንን እንጀምር :-
የሚፈሰስ ከሆነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን? ከዚያም የረጋ ደም ሆነ፥ ፈጠረውም፡፡(ሱራ 75:37-38)
ከደካማ ውሃ አልፈጠርናችሁም ? በተጠበቀ መርጊያ ውስጥም አደረግነው (ሱራ 77:20-21)
ሰውን ከፍህትወት ጠብታ ፈጠረው ( ሱራ 16:4)
ከፍህትወት ጠብታ ፈጠርነው (ሱራ 80:19)
እርሱ ያ ከአፈር፣ ከዚያም ከፍትህወት ጠብታ፣ ከዚያም ከረጋ ደም የፈጠራችሁ ነው። (ሱራ 40:47)
እርሱ ያ ከአፈር ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ፤ ከዚያም ከረጋ ደም የፈጠራችሁ ነው፡፡ ከዚያም ሕጻናት አድርጎ ያወጣችኋል። (ሱራ 40:67)
በእርግጥ ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው። ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ(ማህፀን) ውስጥ የፍህትወት ጠብታ አደረግነው ፤ ከዚያም ጠብታዋን የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን ፤ የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን። (ሱራ 23:12-14)
አናስ እንዳወራው፦ “የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ “አላህ በማህፀን ላይ መልአክ ይመድባል፤ መልአኩም ይላል፦ ‘ጌታ ሆይ የወንድ ዘር ፈሳሽ ነው! ጌታ ሆይ አሁን ደግሞ የረጋ ደም ነው! ጌታ ሆይ አሁን ደግሞ ቁራጭ ሥጋ ነው።’ ከዚያም አላህ ፍጥረቱን ለመፈጸም ከወደደ መልአኩ ‘ጌታ ሆይ ወንድ ነው ወይስ ሴት ነው የሚሆነው?’ በማለት ይጠይቃል። (ሳሂህ አልቡኻሪ 8፡77፡594)
ጠብታው ወደ ማህፀን ከገባ 42 ሌሊት ሲሆነው አላህ ወደ እርሱ መልአክ ይልክና ቅርፁን ያሳምራል። አላህ ለእርሱ ጆሮውን ፣አይን ቆዳ ጡንቻ አጥንት *ይፈጥርለታል። (ሳሂህ ሙስሊም፣ መጽሐፍ 16 ሀዲስ 4)
እስላማዊ ድርሳናት እንዲህ ይበሉ እንጂ በዘመናዊ ስነሀተታ-ፅንስ አስተምህሮ ይህ ሀተታ ባእድ ነው። በአንድ ጊዜ የሚረጨው የፍትህወት ጠብታ ብዛት በአማካኝ ከ 2 እስከ 5 ሚሊ ሊትር ይደርሳል። ከ200 እስከ 300 ሚልየን የሚጠጉ የወንዴ ዘር ህዋሶች በአንድ ጠብታ ውስጥ ሲገኙ ከ2-5% የሚሆነውን የፍትህወት ጠብታ ክፍል ይሸፍናሉ። እንግዲህ ከበርካታ ሚልየን ህዋሶች ልጅ የሚሆነው አንዱ ህዋስ ብቻ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ሴቷ የገባው የፍትወት ጠብታ ወደ ማህፀን አንገት(cervix) እንኳን የሚደርሰው በአማካኝ 30 በመቶ የሚሆነው ፈሳሹ ብቻ ሲሆን የተቀረው ብልት ውስጥ ይቆይና በገባበት በኩል ተመልሶ ይወጣል። ቁርአን ላይ የሰፈረው ይህ የፅንስ አፈጣጠር ትርክት ገና የመጀመርያው ሀተታ ላይ ከዘመናዊ ስነፅንስ ጥናት ጋር በተቃራኒ የቆመ ነው።
የኢስልምና ሰባኪዎች ለዚህ ምላሽ ብለው የሚሰጡት እንደተለመደው የአረብኛ ቋንቋ ትንተና ውስጥ በመግባት ነው። ሰባኪያኑ በግልፅ ቃል ” የፍህትወት ጠብታ ” በማህፀን ውስጥ እንደሚገባ የሚያስረዱ በርካታ እስላማዊ ሀተታዎችን ወደጎን በመተው አንዷን ክፍል ነጥሎ በማውጣት ፤ ከእሷም ላይ እንደገና የአንዲቷን ቃል ፍቺ ያለ አውዱ በመጠምዘዝ ቁርአን ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ተስማማ እያሉ ነጋሪት ያስመታሉ።
“ሳይንሳዊ ተአምር” ነው የሚሉትን ለመፍጠር ይመቸናል በሚል ካልሆነ ቁርአንም ሆነ የኢስልምና መዛግብት ካስቀመጡት በርካታ ግልፅ ትንተናዎች ውስጥ አንዷ ተነጥላ ሳተነጥ”ሳይንሳዊ ተአምር” የምትሆንበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። ለማምታታት የሚሞክሩበት የቁርአኑ የአረብኛ ክፍል እንዲህ ይነበባል :-
أَلَمْ يَكُ نُطْفَةً مِنْ مَنِيٍّ يُمْنَ
አለም የኩ ኑጥፈተን ሚን መኒይን ዩምነ
“ኑጥፋ” የሚለው የአረብኛ ቃል ትርጉሙ “ትንሽ” ስለሆነ በዚህ ክፍል ላይ የቁርአን ደራሲ “መኒይ” ን ደግሞ አብሮ መጠቀሙ ህዋስ (cell)ን ለማመልከት ነው የሚል ማስተባበያ በሙስሊም ሰባክያን ይሰጣል። ነገር ግን እነሱ እንዲህ ይበሉ እንጂ ቁርአን ሌሎች ቦታዎች ላይ ” ኑጥፋንም ( ሱራ 16:4, ሱራ 18:37, ሱራ 22:5, ሱራ 23:13. .. ) ፥ “መኒይንም (ሱራ 75:37.) ” ፥ “ማዕን ( ሱራ32:8 ፣ሱራ77:20 ፣ሱራ 86:6) ” ነጣጥሎ የፍህትወት ጠብታን ለማመልከት ተጠቅሟቸዋል። የአማርኛው የቁርአን ተርጓሚዎች እንደወረደ ትርጉሙን ቢያስቀምጡም በርካታ የእንግሊዝኛ የቁርአን ትርጉሞች በድፍረት የአላህን ቃል በመቀየር “ህዋስ” ያሉትም አልጠፉም። ቢሆንም ግን የሀገራችን የኢስልምና ሰባክያን ከውጪዎቹ እንደወረደ ሙግታቸውን ስለሚቀዱ “ከአማርኛው ትርጉም” ይልቅ እነሱ የሚሰጡትን ማስተባበያ መከተልን መርጠዋል።
በእርግጥ “ኑጥፋ” ማለት ትንሽ ፈሳሽን ለመግለፅ የሚያገለግል ቃል ነው። የወንዴ ዘር ከሌሎች ፍሳሾች አንፃር ትንሽ ስለሆነ ኑጥፋህ ተብሎ ይጠራል። [www.studyquran.org/LaneLexicon/Volume8/00000288.pdf] ነገር ግን በህዋስ ደረጃ ያለን ለመግለፅ የሚያገለግል አይደለም። የወንዴ ዘርን የሚያመለክተው የአረብኛ ቃል “ሐይዋን መንዊ” حيوان منوي ነው።
በቁርአን ላይ “ኑጥፈተን ሚን መኒይን” የተባለው የወንድ ልጅ የፍህትወት ፈሳሽ ትንሽነት ለማመላከት እንጂ የወንድ ዘር ፈሳሽን ትንሽዬዋን ክፍልን ለማመልከት ፈፅሞ አይደለም። በቦታው ቀጣይ ለመጣው ድርጊት አመላካች የአረብኛ ቃል “ዩምና” ሲሆን ትርጉሙም “የሚፈስ” ማለት ነው። የሚፈስ ትንሽዬ ጠብታ እየተባለ ቃሉን ቃል በቃል ፣ አይን በአይን ለማጠፍ መሞከር አስተዛዛቢ ጉዳይ ነው። ” ዩምና” ለፈሳሽ የሚገባ ድርጊት አመላካች ቃል ነው። “ኑጥፈተን ሚን መኒይን” ማለት ከወንድ የዘር ፈሳሽ ውስጥ ህዋስ ይወጣል ማለት ፈፅሞ አይደለም። ተፍሲር አልጃለላይ ክፍሉን እንዲህ ያብራራዋል :-
የሚፈስ የዘር ፈሳሽ (Semen) አልነበረምን? በእርግጥ ነበር። ዩምና ወይም ቱምና በማህፀን ውስጥ ይቀመጣል።
በርካታ የቁርአን እና የሀዲስ ሀተታዎች እንዳላየ ተሆነው ተዘለው በአንዲቷ የቁርአን ክፍል ላይ የተደረገውን ግልፅ የቁርአን እርማት እንቀበል ቢባል እንኳን ከግንኙነት በኋላ ወደ ሴቷ የገባው ፈሳሽ ሲወጣ በአይን የሚታይ በመሆኑ ይህንን ለመረዳት ግልጠተ መለኮት ወይንም የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ያለው መሳርያ እርዳታ አያስፈልግም። ቁርአን ያላለውን ወደሚፈልጉት ጠምዝዘው ለእስልምና ተአምራዊ ሀይማኖትነት እንደማስረጃ የሚያቀርቡትን ከእስልምና አስቀድሞ የነበሩ ፅሁፎች ላይ ከሚሉት ጠመዝማዛ መንገድ ይልቅ በቀጥታ የወንዴ ዘር ሙሉ በሙሉ ማህፀን ገብቶ እርግዝና የማይፈጥር መሆኑን ተዘግቦ እናገኛለን። የአይሁዶች ታልሙድ እንዲህ ይላል
የተጣራው ክፍሉ ብቻ እንጂ ሰው ከሁሉም የወንዴ ዘር ጠብታ የተገኘ አይደለም። [halakhah.com/niddah/niddah_31.html]
የሴቷ እንቁላል
በስነፅንስ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ጥንታውያን አጥኚዎች ሙሉ በሙሉ ስለ ሴቷ እንቁላል ማወቅ ባለመቻላቸው ምክንያት ከለመጥቀሳቸው ባሻገር በእርሱ ፈንታ የወር አበባ ደም ፣ የፍህትወት ፈሳሽ በሚል ትንተና ሰተዋል። ነገር ግን አንድም ሰው የስለ ሴቷ እንቀላል ምንነት ትንፍሽ ያለ የለም።በተመሳሳይ መልኩ በሙስሊም ወገኖቻችን “የአምላክ ቃል ነው” ተብሎ የሚቀርበው ቁርአንም ስለ ሴቷ እንቁላል አስፈላጊነት የሚለው አንዳች ነገር የለም። በሚያስገርም መልኩ ልክ እንደ-ጥንታውያኑ አጥኚዎች ቅልቅል ፈሳሾች በማለት አስቀምጧል (ሱራ76:2)እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ መጠየቅ አግባብ ሆኖ ስላገኘሁት ጥያቄዬን ላስቀድም። እውነት ፈጣሪ ስለ ስነፅንስ ሲያብራራ መሰረታዊ የሆነውን የሴቷን እንቁላል አስፈላጊነት ዘንግቶት ነው ? አላህ ይዘነጋል ካላልን በወቅቱ በነበረው ጥናት ስላልተደረሰበት በአምላክ ስም እየተናገረ ያለው ሰው ሳይጠቅሰው ቀርቶ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም። የሴቷ እንቁላል ለፅንሱ መገኘት መሰረታዊ ስለሆነ ስለ ስነፅንስ ያውቃል በተባለው አካል መጠቀስ አለበት።
ችግሩ የኢስልምና መዛግብት ስለሴቷ የእንቁላል ባለመጥቀሳቸው አያበቃም። ልጅ የሚወለደው ቅልቅሎች ከሆኑ የፍህትወት ጠብታዎች ነው ብለው ያክላሉ።
እኛ ሰዉን በሕግ ግዳጅ የምንፈትነው ስንሆን ቅልቅሎች ከሆኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነዉ ሰሚ ተመልካችም አደረግነዉ። (ሱራ 76:2)
የሴት ልጅ የፍትህወት ጠብታ በጭራሽ ከፅንስ ጋር ግንኙነት የለውም። በእርግጥ የቁርአን ደራሲ ይህንን አመለካከት የወሰደው በዘመናዊ የስነ-ጽንስ ጥናት ተፈትኖ ከወደቀው የፈላስፎች መላምት መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።
የሙስሊም መምህራን ለእዚህ በተቃርኖ የቆመ ሀተታ የሚሰጡት ማስተባበያ ለማንም የማይዋጥ ነው። በዚህ የቁርአን ክፍል የተገለፀው የፍህትወት ጠብታ የሴቷ እንቁላል ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ (cytoplasm) ነው በማለት ያብራራሉ። እኛም “እና እሱ እውነት የፍትህወት ጠብታ ነውን? ” ብለን እንጠይቃለን። የሴቴ እንቁላል ከፍህትወት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን ፍህትወት ተፈፀመም አልተፈፀመም የእራሱን ሂደት ጠብቆ የሚመረት ትልቁ ህዋስ ነው።
የሙስሊም መምህራን እያሉት ያለውን የማይዋጥ ነገር ተቀበልናቸው ቢባል እንኳን ቁርአን ጠቅሶታል የሚሉት የእንቁላሉ ቤተ ኅዋስ (Cytoplasm) ከወንዴ ዘር ጋር በመገናኘቱ ፅንስ አይፈጠርም። ቤተኅዋሱ (cytoplasm) ለፅንሱ የሚያስፈልገው ንጥረ ነገር የያዘ የሴቴ እንቁላል ህዋስ ክፍል ነው። በፅንሰት ጊዜ የወንዴ ዘር ፍሬ ህዋሱ እንዲያድግም በተጨማሪ ያደርጋል ነገር ግን ፅንስ የሚፈጠረው የሴቴ እንቁላል ውስጥ የሚገኘው ፍሬኅዋስ ከወንዴ ዘር ፍሬኅዋስ ጋር ሲቀላቀል ነው። ስለዚህ ፅንሱን የሚፈጥረው የእንቁላሉ ክፍል ፍሬኅዋሱ (nucleus) እንጂ ቤተኅዋሱ (cytoplasm) አይደለም። በክፍሉ ግልፅ የተደረገን ንግግር በማጣመም እዚም እዚያም ቢረግጡ፤ የፈለገውን ያክል በቃላት ትንተና ቢራቀቁ ቁርአንን ፈፅሞ ከስህተት ሊያድኑት አይችሉም።
እስላማዊ ምንጮች በቀጥታ የሚያስቀምጡትን ገለፃ አጣምሞ የመተርጎሙ ሙከራ ብዙም የሚያዛልቅ አይመስልም። ምክንያቱም በደንብ የተብራራባቸው በርካታ እስላማዊ ድርሳናት ስላሉ አንዲት ብቻ ቃል ውስጥ ተገብቶ ፍቺውን በማብዛት የንግግሩን ይዘት ለማጠፍ መሞከር ሀሳቡን የመቀየር እድል አይሰጥም።
አናስ እንደተረከው፦ የአላህ መልእክተኛም እንዲህ አሉ፦ የልጆች እና የወላጆቻቸው መመሳሰል እንዲህ ነው ወንዱ ከሴቷ ጋር ግንኙነት በፈፀመ ጊዜ የእርሱ ፈሳሽ ከቀደመ እርሱን ይመስላል፣ የእርሷ ፈሳሽ ከቀደመ ደግሞ እርሷን ይመስላል። (ሳሂህ አልቡክኻሪ መጽሐፍ 60 ቁጥር 4)
ይህ ክፍል ማብራራትም የሚያስፈልገው አይደለም። በሙሐመድ ንግግር መሰረት “የሴቷ ፈሳሽ እና የወንዱ ፈሳሽ ቅልቅል ፅንስ እንደሚፈጥር” ፣ ከዚያም አልፎ የሴቷ ፈሳሽ ከቀደመ ፅንሱ እናቱን እንደሚመስል፤ የወንዱ ፈሳሽ ከቀደመ ደግሞ አባቱን እንደሚመስል በግልፅ ተቀምጧል። ይህንን እስላማዊ መረዳት በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርቶ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን እየተከታተለ የሚገኝ ተማሪ እንኳን ስህተት እንደሆነ ለደቂቃ አይስተውም። ልጅ አባቱን ወይንም እናቱን የሚመስለው በበራሂ አማካኝነት እንጂ በፈሳሽ መሽቀዳደም አይደለም። የሴት ፈሳሽ የሚባል ነገር ፅንስ ባይፈጥርም፣ መመሳሰልን የሚፈጥረው የወላጆች በራሂ እንጂ የሴት እና የወንድ ፈሳሽ መስቀዳደም አይደለም።
ከእስላማዊ ሐዲስ አንድ መረጃ እንጨምር።
አቡ ሰላማ እንደተረከው ሰላማ እንዲህ አለች ” ኦ! የአላህ መልእክተኛ አላህ እውነት ከመናገር አይከለከልም። ሴት ልጅ ህልመ ሌሊት ካየች መታጠብ ግዴታዋ ነው? ሙሐመድም :- አዎ ፈሳሹ መፍሰሱን ካወቀች። ሰላማም ፈገግ በማለት ሴት ልጅ ፈሳሽ አላት እንዴ? ነቢዩም መለሱ ታድያ እናቱን ለምን ልጅ ይመስላል? (ሳሂህ አልቡክኻሪ፣ ቅፅ 55፣ ቁጥር 545)
ይህንን የሚደግፍ ሳይንስም ሆነ ይህንን የሚቀበል የሥነ ፅንስ ምሑር የለም!