የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል አራት]

የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል አራት]

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


የረጋ ደም

የቁርአን የፅንስ አስተዳደግ ትርክት የሚቀጥለው የወንዱ እና የሴቷ የፍትወት ጠብታዎች ከተቀላቀሉ በኋላ በማህፀን ውስጥ ወደ ረጋ ደምነት ይቀየራሉ በማለት ነው። የረጋ ደም ማለት ሙት ስብስበ ቁስ ማለት ነው። በህክምና ቋንቋ “ደም ረጋ” ከተባለ ደሙ ህይወት የለውም ማለት ነው።የሰው ልጅ በፅንስ ወቅት የረጋ ደም የሚሆንበት ወቅት የለም። ቁርአን እንዲህ ይለናል

የሚፈሰስ ከሆነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን? ከዚያም የረጋ ደም ሆነ፥ ፈጠረውም፡፡አስተካከለውም። ሱራ 75:37-38)

ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)  (ሱራ96:2 )

እርሱ ያ ከአፈር ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ከዚያም ከረጋ ደም የፈጠራችሁ ነው፡፡ ከዚያም ሕጻናት አድርጎ ያወጣችኋል። (ሱራ40:67)

ከዚያም ጠብታዋን የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን። (ሱራ23:14)

ሙሐመድ የቁርአን ፍቺ እንዲሰጠው ወደ አላህ የፀለየለት ኢብን አባስ (ሳሂህ አል-ቡኻሪ፣ መጽሐፍ 96፣ ሐዲስ 3) የረጋ ደም የሚለውን የቁርአንን ክፍል እንዲህ ያብራራዋል፦

(ከዚያም የረጋ ደም ሆነ) የረጋ ደም ሆነ፤ ከዚያም አላህ ህይወት ያለው አድርጎ ቀረፀው። ሁለት እጆች፣ ሁለት እግሮች፣ ሁለት ዓይኖች ሁለት ጆሮዎችን እና ሌሎች አካላትን አበጀለት። ከዚያም በውስጡ መንፈስን አኖረ። (ሱራ 75:37)

በተጨማሪም ሱራ 23: 14 ን እንዲህ ያብራራዋል፦

ከዚያም በእናቱ ማህፀን ውስጥ በመልካም ማረፊያ ቦታ ለአርባ ቀን የዘር ጠብታ ሲሆን ያስቀምጠዋል። (23:14)

ثُمَّ خَلَقْنَا النُّطْفَةَ عَلَقَةً فَخَلَقْنَا الْعَلَقَةَ مُضْغَةً فَخَلَقْنَا الْمُضْغَةَ عِظَامًا فَكَسَوْنَا الْعِظَامَ لَحْمًا ثُمَّ أَنشَأْنَاهُ خَلْقًا آخَرَ ۚ فَتَبَارَكَ اللَّهُ أَحْسَنُ الْخَالِقِينَ

ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን፡፡ የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን፡፡ ቁራጯንም ሥጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን፡፡ አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው፡፡ ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረትን አድርገን አስገኘነው፡፡ ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ፡፡ 

በሚያሳዝን መልኩ የሙስሊም ሰባኪያን እስልምና የሚያስተምረው ትምህርት ፣ የቃላቱ ትክክለኛ ፍቺ ፣ የክፍሉ አውድ እንዲሁም እራሱ የዘመናዊው ሳይንሳዊ ግኝት ግድ ሳይሰጣቸው ሁሉን በአንድ መጨፍለቅ ሳይንሳዊ ተአምር በማለት ያቀርባሉ። ቁርአኑ አሻሚ ሆኖ ቢገኝ እንኳን እውነተኛ ሙስሊም ቢሆኑ፥ በሙሐመድ ነቢይነት ከልባቸው ቢያምኑ ሙሐመድ ወደ አላህ የቁርአን ፍቺ እንዲሰጠው በፀለየለት በኢብን አባስ ፍቺ ይሄዱ ነበር። የቁርአን ክፍሉ ከሳይንስ አልስማማ ብሎ እንጂ እንደምናየው አሻሚ አይደለም።

በዚህ ክፍልም ላይ በተመሳሳይ የሙስሊም መምህራን የተለመደው የአረብኛ ቋንቋ ትንተና ውስጥ በመግባት ከሳይንሳዊ ግኝት ጋር የማስታረቅ ሙከራ ያደርጋሉ። በክፍሎቹ ላይ የረጋ ደም ተብሎ የተረጎመው የአረብኛ ቃል “አለቅ” ሲሆን ወፍራም ደም፣ የረጋ ደም እንዲሁም ደም የሚመጡ አለቅት እና እንደ አለቅት ያሉ እንስሳትን ለመግለፅ ያገለግላል። [www.studyquran.org/LaneLexicon/Volume5/00000419.pdf]

የእስልምና ሰባኪያን ይህንን ለማስተባበል የሚያቀርቡት ማስተባበያ ወጥ አይደለም። የተወሰኑት “አለቃህ” የሚለው የአረብኛ ቃል “አለቅት” የሚል ተጨማሪ ትርጉም  ስላለው የሰው ልጅ አለቅት የሚመስልበት የፅንስ ደረጃም አለው ይላሉ።  ነገር ግን የእነዚኞቹ አካሄድ የረጋ ደም ተብሎ ከመተርጎሙ በላይ የባሰ ተፋልሶ ውስጥ የሚያስገባቸው ነው።

አለቅት በውሀ እና በየብስ የሚኖሩ ዝርያዎች ሲኖሩት ተጣብቆ ደም የሚመጡ እንስሳት ናቸው። [https://www.britannica.com/animal/leech] ስለዚህ የሰው ልጅ ይሄንን እንስሳ የሚሆንበት የፅንስ ደረጃ የለውም።

የሚገርመው ነገር የሙስሊም ሰባኪያን አለቅት ሰውነት ላይ ተለጥፎ ደም እንደሚመጠው ሁሉ የሰው ፅንስም በማህፀን ግርግዳ ጋር ይለጠፋል ብለው ለመተንተን መሞከራቸው ነው።  በእርግጥ ከወንዴ ዘር ጋር የተዋሀደው ውህድ-ኅዋስ ወደ ማህፀን ግርግዳ ይለጠፋል። ይህ ሂደት ጥባቄ ጽንስ ሲባል የሚከናወነውም ፅንሰት ከተጀመረ በመጀመርያው ሳምንት ገደማ ላይ ነው ፣ ነገር ግን ሙስሊም ወገኖቻችን “የአለቅት አይነት ቅርፅ” ብለው የሚያገናኙት ደግሞ በሶስተኛው ሳምንት ላይ ነው። ጥባቄ-ፅንስ በሚከወንበት ጊዜ ኳሰ -ፅንሱ በቅርፅም፣ በዓይነትም፣  በምንም ነገር ከአለቅት ጋር አይገናኝም።

በዚህኛው ምስል እንደምናየው ኳሰ ፅንሱ ወደ ማህፀን ግርግዳ በሚለጠፍበት ጊዜ የአለቅት አይነት ቅርፅ አይዝም

ዘመነኛ የሙስሊም ዐቃቤያን አዲስ ስነ-አፈታት ሰጥተውት እንጂ “አለቃህ” ከረጋ ደም ውጪ ያለው ትርጉሙ “የአለቅት አይነት ቅርፅ” ወይንም “የሚለጠፍ ነገር” ማለት አይደለም። አለቃህ ከረጋ ደም ውጪ ያለው ትርጉሙ አለቅት እራሱ እንስሳው ወይንም የአለቅት አይነት እንስሳት ናቸው። በዚህ ድረ-ገጽ ላይ ከሚገኘው ፋትዋ እንደምንረዳው ሙስሊም ሊቃውንት ፅንስ የረጋ ደም መሆኑን ህሊናቸው ባይቀበልም የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም “የረጋ ደም” እና “አለቅት” ማለት መሆኑን ተቀብለዋል። [https://www.islamweb.net/en/fatwa/223507/two-meanings-of-alaqah-in-the-quran]

እዚህ ክፍል ላይም የበፊት ሙስሊሞች እንዲሁም ሙፈሲሮች “አለቅ” የሚለውን ቃል የተረዱበት መንገድ “የረጋ ደም” ብለው ነው [https://quranx.com/tafsirs/23.14]። ይህንን ግን የሳይንስ መሠረት ላይ ቆመው ቁርአኑን እንደፈለጉ የሚለጥጡት ሙስሊሞች መቀበል ቸግሯቸዋል። አሁን የተነሱ የእስልምና መምህራን እንጂ ቁርአንም ሆነ የእስልምና ምንጮች “የረጋ ደም የሚመስል” አልያ “የአለቅት አይነት ቅርፅ ያለው አላሉም። የኢስልምና መዛግብት ” የሚፈስ የፍህትወት ጠብታ ነበር፤  ከዚያም የረጋ ደም ሆነ፤ ከዚያም ቀጥሎ ቁራጭ ስጋ ይሆናል ” ብለው በቀጥታ የስነ-ፅንስ እድገት ነው ያሉትን አስቀምጠዋል።  ” ይመስላል ፥ የመሰለ ነገር ፥መሰለ ” የሚለው ትንታኔ በእዚህ ዘመን ላይ የተገኙ የእስልምና ሰባክያን ማስተባበያ እንጂ የኢስልምና መዛግብት ላይ የሰፈረው ሀተታ አይደለም።

 በትንታኔያቸው መሰረት እንሂድ ቢባል እንኳን ቁርአን “የፍህትወት ጠብታ ነበር” ሲልም “የፍህትወት ጠብታ ይመስላል” ወይንም “የፍህትወት ጠብታ አይነት ቅርፅ ይዞ ነበር ” እያልን መፍታት ይኖርብናል። እውነት ከልቡ የአምላክ ቃል ነው ብሎ ለቁርአን ክብር ያለው ሰው ቁርአን ይሆናል ካለ “ይሆናል” ብሎ ነው መረዳት የሚገባው። ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ከሙስሊም መምህራን ይልቅ እኛ ቁርአኑ የሚለውን ብሏል ለማለት ታማኝ ነን። የእስልምና መዛግብት ያሉትን ሳናጣምም እንዲህ ብለዋል እንላለን። እግረ መንገዳችንንም ሙስሊም መምህራን መፅሀፋቸው ያለውን ነገር ብሏል ብለው የእኛን ያህል እንኳን ” እንዲታመኑለት ” እንመክራለን።

ከላይ የተሰመረበት የአረብኛው ቃል “ሱማ ካነ ዓላቃተን” ሲሆን ምንም በማያምታታ መልኩ “የረጋ ደም መምሰልን” ሳይሆን “የረጋ ደም መሆንን” የሚያመላክት ገለፃ ነው። የረጋ ደም ሆነ ማለት ደግሞ በሳይንሳዊ ቋንቋ ህይወት አልባ ሆነ ማለት ነው። ይህ ገለፃ ምንም ማስተባበያ የማያሻው ስህተት ነው።

 

ምንም እንኳን ሙስሊም ባይሆንም የቁርአንን ትርክት እውነተኛነት ለማስረዳት የተጠቀመው ኪይት ሙር ነው። በእውነቱ ከሆነ ይህ ምስል እስልምናን ለመደገፍ የሄደበትን ርቀት ቢያመለክት እንጂ የማይገናኝ ነገርን ለማቀራረብ እየጣረ እንደሆነ የአለቅት ምስልን የሚያውቅ ሰው በቀላሉ ይገነዘበዋል። በምስሉ ላይ አለቅት ነች ተብላ የተቀናበረችው ምስል ከወደ ጭንቅላቷ ወፈር ብላ እንድትታይ አንገቷን ሰበር አድርጋዋለች፤ ወገቧ ቀጠን ብሎ እንዲታይላት ደግሞ ወደ ውስጥ አጠፍ አድርጋዋለች፤ ጭራዋ ወፈር እንዲል ደግሞ ወደላይ አጥፋዋለች። ለተመለከተው ሰው አሳማኝ ሊሆን ቀርቶ በጣም አስቂኝ ነው። እንደሚሉት ከሆነ ምስሉ የተወሰደው ከአንድ የድሮ የzoology መፅሀፍ ነው። ምስሉን የሚጠቀሙት ሰዎች ከሰው ፅንስ ጋር ሊመሳሰልልን ይችላል ብለው እንጂ ብዙ የአለቅት ምስሎች አሉ። የአለቅትን ፎቶ ማሳየት እየተቻለ የድሮ መፅሀፍ ላይ ያለ ስዕል ማሳየት ለማጭበርበር እንደሆነ ግልፅ ነው።

እውነት ለመናገር አለቅት ብለው ያቀረቡት “አለቅት” እንደሆነ ባይነግሩን እኔን ጨምሮ ብዙሀኑ ሰው የዛፍ ቅጠል እንደሆነ አድርጎ የሚረዳው ይመስለኛል። በአይን ማንም ሰው ሊያየው የሚችልን ነገር እንዲህ መለወጥ ከደፈሩ የፅንስ ምስል ብለው የሚያቀርቡትን ምስል ምን ያህል አለቅት ለማስመሰል እንደለወጡት ማወቅ አይከብድም።

በዚህ ምስል ላይ ሰውየው እንደአንበሳ አይነት ቁመና እንዲኖረው ተደርጓል አንበሳው ደግሞ ሰው እንዲመስል ተደርጎ ተስሏል። አለቅትን እና የሰው ፅንስን ያነፃፀሩበት ፎቶ የእዚህ አይነት ስላቅ የሚመስል ንፅፅር ነው።

 

የ22 ቀን ገደማ ያለ ፅንስ ሲሆን አምስት የሚደርሱ እምብዛም ጉልህ ያልሆኑ አፅቀፅንሶች አሉት።

ሶስተኛው ሳምንት አጥቢያ ላይ ፅንሱ ሱ ከ4-12 አፅቀ ፅንሶች ሲኖሩት ጉልህ የሆነ ምልክት ይኖራቸዋል። ከላይ የሚታየው ምስል ባለ 8 አፅቀ ፅንስ ሲሆን የ23 ቀን ፅንስ ነው። በአፅቀ ፅንሶቹ መሀል ነርቫዊ ቱቦ ሲኖር በፅንሱ ጫፍ እና ጫፉ ላይ የሚገኙት ሮስታል እና ከውዳል ኒውሮፖሮች ክፍት ናቸው። 

ምስሉ የተወሰደው ከscience direct ድረገፅ ሲሆን ሙስሊሞች ሳይመስል አለቅት ይመስላል የሚሉት የፅንስ ደረጃን ያሳያል።

 

መገለጫ አለቅት የሶስት ሳምንት ፅንስ
ቀለም ብዙ ጊዜ ጥቁር ወይንም ደማቅ አረንጓዴ ናቸው። ነጠብጣብ ምልክት ወይንም ዥንጉርጉር አለባቸው።      X
ውጫዊ መለያ በጭንቅላታቸው በተቃራኒ መምጠጫ አካል ሲኖራቸው ቀጥ ያለ ሰውነት አላቸው። ጫፍና ጫፋቸውም ክፍት አይደለም።      X
ውስጣዊ መለያ 32 አይምሮ አላቸው

300 ጥርስ አላቸው።

 

     X
ፆታ ሁሉም አለቅቶች ድርብ ፆታ አላቸው።      X

ከ22 -28 ቀን ያሉ ሽሎችን የሚያሳይ ምስላዊ መግለጫ THE DEVELOPING HUMAN CLINICALLY ORIENTED EMBRYOLOGY  ገጽ 71

ሙር ገፅ 73 ያስቀመጠው የ24-25 ቀን ፅንስ

እስካሁን እንዳየነው የሙስሊም ሰባክያን የቃሉን ትርጉም ወዳሻቸው ቢተረጉሙት እንኳን አለቅት የሚመስልበት የፅንስ ደረጃ የለም። በፅንስ እድገት ውስጥ የረጋ ደም የሚሆንበት ደረጃ አለው በማለት የእስልምና መዛግብት በዘመናዊው ጥናት ግኝት ሲታይ ወንጀል ነው ለማለት እስኪያስደፍር ሰርተዋል። በእርግጥ አንድ በመሀከለኛው ዘመን የነበረ ሰው በዚህ መልኩ ቢረዳው አይፈረድበትም። የሰው ልጅ የረጋ ደም የሚሆንበት የፅንስ ደረጃ አለው ተብሎ እስልምና የተጀመረበትን ጨምሮ ለረጅም ዘመን ይታመን ነበር። ቁርአንም ሆነ የኢስልምና ምንጮች ለምን ተሳሳቱ የሚል ሀሳብ የለኝም፤ የተሳሳቱበት ምክንያት በወቅቱ በነበረው ዕውቀት ደረጃ ስላልታወቀ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።ቁርአንም ሆነ የኢስልምና መዛግብት የተሳሳቱት ግልጠተ መለኮት ሳይሆኑ በወቅቱ የነበረው ፍልስፍናን እየቀዱ እንደ ግልጠተ መልኮት ስለሚያስቀምጡ ነው።

ቁርአን በግልፅ ያስቀመጠውን ሀተታ የአሁን ዘመን ሰባኪያን የተዋጠላቸው አይመስልም።በእርግጥ እውነት አላቸው። የዚህ ዘመን ሰው በቁርአን የቀረበው የስነ-ፅንስ ሀተታ ፍፁም ስህተት እንደሆኑ በቀላሉ ይረዳል። እነዚህ ሰባክያን የሳይንስ መሰረት ላይ ቆመው የቁርአኑን ቃላት እየበጣጠሱም ቢሆን ወደ እራሳቸው ይጎትቱታል። እውነተኛ ግልጠተ መለኮት ከሆነ እርሱን ወደ እኛ ሳይሆን እኛ ነን ወደእርሱ መሳ’ብ ያለብን። ቁርአን ራዕየ መለኮት ከሆነ ቃላቶቹን የተለየ ፍቺ እየሰጠን በሳይንሳዊ ግኝት እንድናስተካክለው አይሻም። ትክክል ከሆነ ትክክል ነው ፤ ስህተት ከሆነ የአምላክ ቃል አይደለም።

እንግዲህ የረጋ ደም የሚለውን የቁርአንን ገለፃ ከሚያስተባብሉት ሰባኪያን ውስጥ “አሊቅ” የሚለው የአረብኛ ቃል መለጠፍ፣ ስለሆነ ” አለቅ ” የተባለው የክፍሉ የአረብኛ ቃል “የረጋ ደም” ተብሎ ሳይሆን “የሚለጠፍ ነገር” ተብሎ ነው የሚል ማስተባበያ የሚሰጡ አሉ። በተጨማሪም የፅንሱን ሁኔታ ሳይሆን ጥባቄ ፅንስ የሚከናወንበት ጊዜን የሚያመለክት ክፍል ነው በማለትም ያክሉበታል። የእነዚኞቹም ሰባኪያን ትንተና እንደሌሎቹ ሁሉ ሩቅ መንገድ የሚያስኬዳቸው አይመስልም። ” አለቃ” የሚለጠፍ ነገር የሚል ፍቺ ባይኖረውም መንገዳቸውን ተከትለን ብንሄድ ያለ አውዱ በመተርጎማቸው እነዚህ ዝግ መንገዶች ይጠብቁናል :-

① ቁርአን የፍህትወት ጠብታ በማህፀን ገብቶ አለቃ ይሆናል ስለሚል ትርጉሙን ብንቀይረውም ከስህተት ሊወጣልን አይችልም። የፍህትወት ጠብታ የሚለጠፍ ነገር አይሆንም።

የፍህትወት ጠብታ አድርገን ፈጠርን ፤ከዚያም የፍህትወት ጠብታውን የረጋ ደም (የሚለጠፍ ነገር) አድርገን ፈጠርን። (ሱራ 23:13-14)

② የሚለጠፈው ፅንሱ ሳይሆን የእንግዴ ልጁ (placenta) ነው። ስለዚህ የሰውን ልጅ ከሚለጠፍ ነገር ፈጠርን ቢባልም ክፍሉ ከስህተት አይድንም።

☞ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም) ሱራ 96:2

☞እርሱ ያ ከአፈር ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ከዚያም ከረጋ ደም(ከሚለጠፍ ነገር) የፈጠራችሁ ነው፡፡ ከዚያም ሕጻናት አድርጎ ያወጣችኋል። (ሱራ40:67)

③ ቁርአን የሚለጠፈው ነገር (አለቃ) ወደ ቁራጭ ስጋነት (ሙድጋ) እንደሚቀየር ያትታል። ነገር ግን የሚለጠፈው ነገር ጊዜያዊ ሳይሆን እስከ ውልደት ድረስ የሚቀጥል ነው።

ከዚያም የረጋውንም ደም(የሚለጠፈውንም ነገር) ቁራጭ ስጋ አድርገን ፈጠርን።

ቁራጯንም ስጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን (ሱራ 23:14)

በእርግጥ እነዚህ መምህራን እንደሚሉት “አሊቅ” ማለት መጣበቅ ፣ መለጠፍ ማለት ነው። ነገር ግን “አለቅ “ማለት የሚጣበቅ ነገር የሚል ትርጉም የለውም። ለዚህ አዲስ ትርጉማቸው ከጥንታዊ አረብኛ  መዝገበ ቃላት እንዲሁም ከቀደምት ፅሁፎች ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። እንደሚሉን ይሁን ብለን እንቀበል ቢባል እንኳን ቀደምት አረቦች ነፍሰጡርን ሴትን ለመግለፅ አሉቅ ፣ አለቅ የሚል ቃል ይጠቀሙ ነበር። ስለዚህ የሙስሊም መምህራን ግልጠተ መለኮትነት ለቁርአን ማዕረግ ከመስጠታቸው በፊት ለአረቦችም ማካፈል አለባቸው።

በስነፅንስ ዙርያ አስተያየታቸውን የሰጡ ፈላስፋዎች \ምሁራን የፅንስ ሁኔታን ሊያውቁበት የሚችሉበት መሳርያ ስለሌላቸው ከዶሮ ፣ ከጨነገፈ ፅንስ እንዲሁም ከተለያዩ የእንስስሳት ፅንስ አስተዳደግ እየተነሱ መላምት ሲያስቀምጡ ነበር። የወንዴ ዘር በሴት ማህፀን ውስጥ ገብቶ ወደ ረጋ ደምነት ይቀየራል ብሎ ለመናገር ግልጠተ መለኮት አልያ የተለየ ዕውቀት አያስፈልገውም። ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ ሩቅ እንኳን ሳንሄድ ቤተሰቦቻችን የሰው እርግዝና ሲቋረጥ “አገሊትን እኮ ደም መታት” ይላሉ። በመጀመርያው የፅንስ ክፍለ-ጊዜ ውርጃ ከተፈፀመ የሚወጣው የረጋ ደም ነው። ይህ እንዲህ ቢሆንም የቁርአን ደራሲ በእራሱ ያመነጨው አዲስ ዕውቀት ሳይሆን አስቀድሞ የነበረ ነገር ነው።

ሙስሊም ሊቃውንት ቁርአንን ከስህተት ለማዳን “አለቅት” የሚል ሌላ ትርጉም ፣ እንዲሁም የተለየ የማይታወቅ እስላማዊ መረዳት ለማምጣት ወደ ቅጠልነት ያመዘነ የአለቅት ምስል ፣ ወደ ፀጉር ማስያዣነት ያዘነበለ የሽል ምስል ቢያቀርቡም እንዲሁም የቃላቱን ትርጉሙን በመቀየር ከፍሎቹን እውነት ለማድረግ ብዙ የበመቀየቢደክሙም አሁንም በርካታ ማይታለፉ እንቅፋቶች አሉ።

በክፍሎቹ አላህ እያስረዳ ነው የተባለው የሰው ፅንስ የረጋ ደም የሚሆንበት ደረጃ አለው ተብሎ የሚታመንበት ዘመን ላይ ነው። ቃላቶቹ እንኳን እንዲህ ግልፅ ሆነው ቀርቶ በሚያሻማ መልኩ ቢል እራሱ ቁርአን ከስህተት አያመልጥም። የረጋ ደም ነው ተብሎ በሚታመንበት ዘመን ላይ የረጋ ደም ተብሎ ሊተረጎም በሚችል ቃል ማስቀመጡ በእራሱ ስህተት ያደርገዋል።ዛሬ ላይ የሰው ፅንስ የረጋ ደም የሚሆንበት ደረጃ እንደሌለው ታውቆ ቁርአንን ሰዎች በተለየ መንገድ ሲረዱት እንደኖረ እርግጠኛ ብንሆን እንኳን አላህ ይህንን ዕውቀት አልገለጠም። ሙስሊሞችም ሳይንሳዊ ዕውቀት ይዘው ካልሆነ አላህ የተናገረውን የሚረዱት የበፊት ፈላስፋዎች በተናገሩበት መልኩ ነው። ስለዚህ አላህ የፅንስን ዕውቀት በቁርአን ገልጧል ለማለት አያስደፍርም።

አርስጣጣሊስ “የአላህ ነቢይ ነው ራዕየ-መለኮት ወርዶለታል” የሚልለት ሰው አጣ እንጂ የፅንስ ጥናቱንም እያካሄደ የነበረው በዶሮ እንቁላል ላይ ነበር። በተመሳሳይም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 3000 አመት በፊት የነበሩ ግብፃውያን በወፍ እንቁላል ላይ ጥናት እና ምርምር ያደርጉ ነበር። [https://blogs.lt.vt.edu/chickens/2013/05/06/the-chicken-egg-as-an-embryo-the-avian-flu-and-other-reasons-why-the-chicken-is-significant-to-the-development-of-a-human-culture/]  

ምስሉን የወሰድኩት  integrated principles of zoology 17ኛ እትም ከገፅ 176 ሲሆን የወፍ ጫጩት እና የሰው ፅንስ ጅማሮ ተቀራራቢነትን ያሳያል ።

እስከዚህ ድረስ የተመለከትናቸው የቁርአን ደራሲ ያቀረበው የፅንስ ደረጃዎች በዘመናዊ ሳይንስ ከተረጋገጠው እውነታ ጋር ፈጽሞ እንደማይገጥሙ እንዲሁም የዘመንኛ ሙስሊም ዐቃቤያን ማስተባበያዎች እንደማያስኬዱ በበቂ ማስረጃዎች አረጋግጠናል። በቀጣይ “ሙድጋ” የተሰኘውን ደረጃ የምንመለከት ይሆናል።


 

ቁርኣን