መሲሑ ይመለካል!

መሲሑ ይመለካል!

ወንድም ሚናስ


ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ሊቃውንትና ባለሥልጣናት ፊት በቀረበበት የፍርድ ሂደት ላይ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የሚከተለውን እናነባለን፦

ማርቆስ 14፥61-62 “ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ የቡሩኩ ልጅ፣ መሲሑ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ።” (አዲሱ መ.ት)

ጌታችን መሲሕ መሆኑን በጠየቁት ጊዜ ለመሲሕነቱ ማረጋገጫ በቀጥታ የጠቀሰው ትንቢተ ዳንኤል 7፥13-14 ያለውን ክፍል ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል፦

ዳንኤል 7፥13-14 “በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ *ይገዙለት*(יִפְלְח֑וּן) ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።”

በክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ ሳይሆኑ በጥንታውያን አይሁድ ሊቃውንት ዘንድም ትንቢተ ዳንኤል ላይ የተጠቀሰው የሰው ልጅ መሲሑ መሆኑን ይታመን ነበር። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፦

“ረቢ እስክንድር እንዲህ አለ፡- “ረቢ የሆሹኣ ቤን ሌዊ እንዳብራራው …. “ጽድቅን ካደረጉ [መሲሁ] በሰማይ ደመና ይመጣል (ዳንኤል 7፡13)፤ ጽድቅን ካላደረጉ ጎስቋላ ሰው ሆኖ በአህያ ይመጣል (ዘካርያስ 9፡9)፡፡”[1]

“አናኒ [ከደመና የሆነው] ወደ ፊት ራሱን የሚገልጠው ንጉሡ መሲህ ነው፡፡” [2]

ይህንን ከተመለከትን ዘንዳ ጥቅሱ (ዳንኤል 7፥13-14) ስለ መሲሑ የሆነስ እንደው መሲሑ እንደሚመለክ የሚያሳየው በምን አግባብ ነው? የሚል ሰው ካለ ምላሽ እንስጥ።  አማርኛ ተርጓሚዎች “ይገዙለታል” ብለው ያስቀመጡት ቃል በአራማይክ ቋንቋ “ይፕላኹን” יִפְלְח֑וּן የሚል ሲሆን የ “ፕላኽ” (פְלַח) ሦስተኛ መደብ፤ ተባዕታይ፤ ብዜት ነው። ቃሉ በብሉይ ኪዳን አሥር ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን የሰው ልጆች እውነተኛ አምላክ ነው ብለው ላመኑበት አካል ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ቃል ነው። ለምሳሌ በዚሁ በዳንኤል ላይ የተወሰነውን ለመመልከት ያህል፦

“ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያመልኩም (פְלַח)፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።”
  — ዳንኤል 3፥12

“ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማምለካችሁ (פְלַח) እውነት ነው?”
  — ዳንኤል 3፥14

“ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው (פְלַח) አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።”
  — ዳንኤል 3፥17 (አዲሱ መ.ት)

“ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶችም ጒድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ሁል ጊዜ የምታመልከው (פְלַח) አምላክህ ያድንህ” አለው።”
  — ዳንኤል 6፥16

“ወደ ጒድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ።”
  — ዳንኤል 6፥20

Brown-Driver-Briggs Hebrew and English Lexicon. የተባለ እጅግ ስመጥር መዝገበ ቃላት ግሱን ምን ብሎ እንዳስቀመጠው ተመልከት፦

                        [ምስል 1]

ከየትኛውም የዕብራይስጥ እና የአረማይክ ሙዳየ ቃላት በፊት በቀዳሚነት የሚጠራው ከላይ ያለው የዕብራይስጥና የአረማይክ መዝገበ ቃላት  פְלַח “ፕላኽ” የሚለው ግስ ትርጉም አምላክን ማገልገል የሚል ፍቺ እንዳለው ለዚህም ማሳያነት ዳንኤል 7፥14ን በማጣቀሻነት እንዳቀረበ ልብ በሉ። “ጥንታዊው ግሪክ” ተብሎ የሚታወቀው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም λατρεύουσα (ላትሬውሳ) በማለት ያስቀመጠ ሲሆን ለአምላክ ብቻ ተገቢ የሆነውን አምልኮ የሚገልጽ ነው፡፡ ይኽ ኹሉ የሚያሳየው በብሉይ ኪዳን መሠረት פְלַח “ፕላኽ”  ለእግዚአብሔር ብቻ መሰጠት እንዳለበት ነው። 

ሌላው በዳንኤል 7፡13 “የሰው ልጅ” ከሰማይ ደመና ጋር እንደሚመጣ ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አገላለጽ ለያህዌ ጥቅም ላይ ውሏል፦

“ስለ ግብፅ የተነገረ ንግር፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።”
  — ኢሳይያስ 19፥1 (አዲሱ መ.ት)

“ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤ በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤ ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣ እጅግ ደስ ይበላችሁ።”
  — መዝሙር 68፥4 (አዲሱ መ.ት)

በተጨማሪም እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፦ (ዘጸአት 13:​21-22፤ 14:​19-24፤ 33:​7-11፤ 40:​34-38፤ ዘኍልቍ 10:​34፤ ዘዳግም 33:​26-27፤ 33-34፤ 104:​2 —3፤ ናሆም 1:3) በዚህ ምክንያት የአይሁድ ተንታኞች እንኳን ይህ የሰው ልጅ እንደ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ብቻ መሆኑን ለመደምደም ሲቸገሩና ሲያመነቱ እንመለከታለን። [3]

በእውነትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምልኮ የተገባው አምላክ ነው!


[1] Targum to I Chronicles 3.24

[2] Pirque Mashiah, Bhm 3.70

[3] Michael L. Brown, Answering Jewish Objections to Jesus: Vol. 1, (Grand Rapids, MI, 2000), pp.  247-48


መሲሁ ኢየሱስ