የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል ስድስት]

የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል ስድስት]

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


ሦስቱ ጨለማዎች?

በእናቶቻችሁ ማኅፀኖች ውስጥ በሦስት ጨለማዎች ውስጥ ከመፍጠር በኋላ ሙሉ መፍጠርን ይፈጠራችኋል። ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ስልጣኑ የእርሱ ብቻ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ታዲያ ወዴት ትዞራላችሁ (ሱራ 39:6)

አንድ በ21ኛው ክፍለዘመን ለሚኖር ሰው ይሄንን የቁርአን ክፍል ቢያነብ ቁም ነገር ከመያዝ ይልቅ ፈገግታን የሚጭርበት ነው። በክፍሉ እንደ ቁርአን ደራሲ ሀሳብ ከሆነ ስለ ፅንስ በጥልቀት በማብራራት ፤ ያብራራውንም አላህ እንዳደረገው ስለዚህም ከአላህ ሌላ አምላክ እንደሌለ ለማስረዳት ይሞክራል። በስነፅንስ ዙርያ ቁርአን ያስቀመጣቸው የተሳሳቱ ጥንታውያን አመለካከቶች የአምላክ ቃል እየተባሉ በአምላክ ስም የተነገሩ ንግግሮች በሚያሳዝን መልኩ በሙሉ ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህንንም የቁርአን ክፍል ቃል በቃል በሙሐመድ ዘመን ሊገኝ ከሚችለው ፍልስፍና ውስጥ እናገኘዋለን

ፆታ መች እና እንዴት ይፈጠራል?

በእስላማዊ ምንጮች የፆታ ልየታ ተብሎ የቀረበው ልክ እንደጥንታውያን ፈላስፎች ሁሉ ከዘመናዊው ጥናት ጋር ለእየቅል ነው።

የሚፈሰስ ከሆነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን? ከዚያም የረጋ ደም ሆነ ፈጠረውም፡፡ አስተካከለውም። ከእርሱም ሁለት ዓይነቶችን ወንድ እና ሴትን አደረገ። (ሱራ 75 ፡37-39)

በዚህ የቁርአን ክፍል ገለፃ የፍህትወት ጠብታ ከሆነ በኋላ የረጋ ደም ይሄናል ከዚያም አላህ ያስተካክልና ወንድ እና ሴት ያደርጋቸዋል። በዘመናዊ ህክምና ሳይንስ ግን ፆታ የሚለየው ገና የወንዴ ዘር እና የሴቴ ዘር እንደተገናኙ ነው። ይሄ የቁርአን ገለፃ በግልፅ እንደሚያሳየው ፅንሱ የረጋ ደም ሆኖ ተስተካክሎ ካበቃ በኋላ ነው። የረጋ ደም የሚባል ደረጃ ባይኖርም!

ነገር ግን ቀጥተኛ እስላማዊ ንግግሮችን በማጠፍ ስራ የበዛባቸው የሙስሊም ሊቃውንት ይሄንንም ፆታ የሚለ’ይ’በት ደረጃ ሳይሆን ፆታን የሚለዩ አካላት የሚስተካከሉበት ነው ብለው ይሞግታሉ። ብዙ ግልፅ ሀዲሶችን ማቅረብ ይቻላል።

አናስ እንዳወራው፦ “የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ “አላህ በማህፀን ላይ መልአክ ይመድባል፤ መልአኩም ይላል፦ ‘ጌታ ሆይ የወንድ ዘር ፈሳሽ ነው! ጌታ ሆይ አሁን ደግሞ የረጋ ደም ነው! ጌታ ሆይ አሁን ደግሞ ቁራጭ ሥጋ ነው።’ ከዚያም አላህ ፍጥረቱን ለመፈጸም ከወደደ መልአኩ ‘ጌታ ሆይ ወንድ ነው ወይስ ሴት ነው የሚሆነው?’ በማለት ይጠይቃል። (ሳሂህ አልቡኻሪ 8፡77፡594)

የእስልምና መዛግብት ምንጮች

የቁርአን ደራሲ ሙሐመድ ለመሆኑ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። የተለያዩ ብጥስጣሽ እና አንባቢ ያለማንም ድጋፍ ቢያነባቸው ምሉእ ትርጉም የማይሰጡ ታሪኮች ውቅር እንደሆነ ሊቃውንትን የሚያስማማ ሀቅ ነው። ሙስሊም ወገኖቻችን እንደሚሉት የቁርአን ደራሲ ሙሐመድ ብቻ ነው ብለን ብንቀበል እንኳን ቁርአን  ከእሱ ሞት በኋላ የተሰበሰበ ሲሆን ምን ያህል ክፍል እንደሚኖረው የቱ እንደሚቀድም እንዲሁም የቱ ምኑ ጋር እንደሚገባ የወሰኑት ሌሎች ሰዎች ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የቁርአንና የኢስልምና መዛግብት ደራሲ ሙሐመድ ነው ብለን አስበን እንመርምር።

1) በቁርአን ላይ የሰፈረው የስነ-ፅንስ ተረክ የቁርአን ደራሲ ከየት አመጣቸው?

ፍንጭ 1

የቁርአን ደራሲ ከእነጋለን ስራዎች ወስዷል የምንለው የሚያቀርቡት ሀተታ ስለተመሳሰለ ብቻ አይደለም። ጋለን ማለት ለረጅም ዘመናት ስሙ የገነነ መምህር ነበር። የእርሱ ስራዎች የሌሎች ፈላስፋዎች ማለትም ፍላጦን፣ አርስጣጣሊስ እንዲሁም የሂፖክራተስ አመለካከት ቅልቅል ናቸውም ይሏቸዋል። [https://www.britannica.com/biography/Galen]  ጋለን በዘመኑ በሮማው ገዢ ማርከስ ኦሪሊየስ “ከሀኪሞች ቀዳሚው ከፈላስፋዎች ልዩ” የሚል ሙገሳንም አግኝቷል። እንዱሁም ሙሐመድ በነበረበት ዘመን የነበረ ገጣሚም የጲስድያው ጊዮርጊስ ጋለንን እንደ “ሁለተኛው ክርስቶስ” አድርጎ ልዕለ ስብዕና አጎናፅፎታል። [https://pmmc.or.id/index.php/en/news-page/aelius-galenus-or-claudius-galenus]

ሙሐመድ በኖረበት ዘመን የነበሩ በሶርያ ይኖሩ የነበሩ ክርስትያኖች የጋለንን ጨምሮ ሌሎች ግሪክ ፍልስፍና ይጠቀሙ ነበር። [Arthur John Brock, Galen. On the Natural Faculties, Introduction, p. XIX, https://ia600504.us.archive.org/30/items/galenonnaturalfa00galeuoft/galenonnaturalfa00galeuoft_bw.pdf] በተጨማሪም ወደ ሶርያ ቋንቋ የጋለንን ስራ በጽሑፍ መልክ በስድስተኛ ክፍለዘመን በረሻይናው ሰርጊየስ ተዘጋጅቶ ነበር። በስድስተኛውና ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀ የሰርጊየስ የእጅ ጽሑፍ እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛል። ምስሉን ከታች ይመልከቱ።  

የጋለን ጽሑፍ የሶርያ ትርጉም ቅድመ እስልምና የተዘጋጀ። የፎቶ ምንጭ፦ https://mizanproject.org/the-syriac-galen-palimpsest/

ሙሐመድ የሶርያ ሰዎች ጋር ከ9-12 አመቱ አንስቶ ይገናኝ ነበር። ሙሐመድ አቡጧሊብ የተባለው አጎቱ ወደ ሶርያ ይወስደው እንደ ነበር በእስላማዊ ምንጮች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ኢብን ይስሐቅ እንደዘገበው፥- ከዚያን ጊዜ በኋላ አቡ ጧሊብ ለንግድ ወደ ሶሪያ አመራ። ዕቃዎቹን እያዘጋጀ ለጉዞው እየተሰናዳ ሳለ ነቢዩ በጥልቀት ይናፍቀው ጀመር።  ከዚያም አቡ ጧሊብ አዘነና “ወላሂ እርሱን ከራሴ ጋር ይዤው እሄዳለሁ፡ ከእንግዲህ መቼም ጥዬው አልሄድም አለ። ከዚያም ነቢዩ ከእርሱ ጋር አብሮት ሄደ። [ሲራ አነበዊያ ኢብን ከቲር ቅፅ 1 ገፅ 174]

ፍንጭ 2

የሙሐመድና የግሪኮች ፍልስፍናን የሚጠቀሙ በሶርያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ግንኙነታቸው አንዴ ብቻ ሳይሆን ሙሐመድ ከመጀመርያ ሚስቱ ከዲጃ ጋር በሚሠራበት ጊዜም እንደቀጠለ መረዳት ይቻላል። ሙሐመድ በነበረበት ዘመን የነጅራን ንስጥሮሳውያን መነሻቸው ሶርያ ሲሆን በአረብ ባህረ ሰላጤ በስፋት ይገኙ ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ ሙሐመድ ኸዲጃን ወክሎ በሃላፊነት ተልእኮውን በሚወጣበት ጊዜ ከሶርያ ሰዎች ጋር አይገናኝም ማለት አይቻልም።

ፍንጭ 3

ነቢይ ከሆነ በኋላ እሱ በኖረበት የአረብ ምድር ስለ ግሪክ ተናጋሪው ዓለም በስፋት ይታወቅ ነበር። ሙሐመድ የቁርአን 30ኛው ሱራ ወረደልኝ ያለው የቤዛንታይን ግሪኮች ከፋርሶች ባደረጉት ውጊያ ሲሸነፉ ነበር። ስለግሪኮች በመካ ዙርያ መነገር አዲስ ስላልነበረ የሙሐመድ ተከታዮች የቤዛንታይን ግሪኮች በተሸነፉ ሰአት ተሸብረው ነበር።  ይህ የሚያሳየው የአረቡ ዓለም ከግሪኩ ዓለም ጋር ትውውቅና ቅርርብ እንደነበረው ሲሆን የዕውቀት መወራረስም በዚያው መጠን ሊኖር መቻሉ አጠያያቂ አይደለም።

ፍንጭ 4

የጋለንና የሌሎች ግሪክ ፈላስፎችን እሳቤ በእስልምና መዛግብት ውስጥ ከተነገሩት የሽል እድገት ደረጃዎች ጋር ስናነጻጽር ሙሐመድ ከግሪኮች የመውሰዱን እውነታ ፈጽሞ መካድ አይቻልም።

የቀደመው የሰውነት ክፍል የእስልምና መዛግብት የጋለን ፍልስፍና የአርስጣጣሊስ ፍልስፍና የሂፖክራተስ ፍልስፍና
የወንዴ ዘር ጠብታ(ኑጥፋ) የወንዴ ዘር ፈሳሽ የወንዴ ዘር ፈሳሽ የወንዴ ዘር ፈሳሽ
ቅልቅል ፈሳሾች (ኑጥፈቲን አምሻጂን) ቅልቅል ፈሳሽ ቅልቅል ፈሳሽ ቅልቅል ፈሳሽ
ቁራጭ ሥጋ (ሙድጋ) ቅርፅ አልባ ሥጋ ሥጋ ሥጋ
አጥንት (ኢዛም) አጥንት አጥንት አጥንት
አጥንቱ ሥጋ ይለብሳል አጥንቱ ሥጋ ይለብሳል አጥንቱ ሥጋ ይለብሳል አጥንቱ ሥጋ ይለብሳል

ከላይ በሰንጠረዡ ለማሳየት እንደተሞከረው ቁርአን ከየት እንደቀዳ በጣም ግልፅ ነው። ዘመነኛ የሙስሊም መምህራን ቀጥተኛ ንግግሮቹን የማይመስል የቃላት ትንተና ውስጥ በመግባት ሽምጥጥ ቢያደርጉም የስነ-ፅንስ ጥናት ያልደረሳቸው ሙስሊሞች ከግሪኮች ፍልስፍና ጋር እንደሚጣጣም ሲያምኑበት የኖረ ነው። ለምሳሌ ኢብን ሲና በእስልምና ወርቃማው  ዘመን የሚባለው ላይ የተነሳ ሊቅ ሲሆን  ከግሪክ ስራዎች ጋር እያነፃፀረ ሲያቀርብ ነበር።

የእስልምና መዛግብት የባቢሎን ታልሙድ
“…የአላህ መል እክተኛ እንዲህ አሉ፦ የዘር ፈሳሽ በማህፀን ውስጥ ለአርባ ሌሊት ይቆያል; ከዚያም መልአክ ቅርጽ ይሰጠዋል…” (Sahih Muslim Book 33, number 6395) ካላረገዘች ከቶ አልጸነሰችምና; እርጉዝ ሆና ከተገኘችም የወንድ የዘር ፈሳሽ እስከ አርባኛው ቀን ድረስ ፈሳሽ ብቻ ነው። (Babylonian Talmud Sanhedrin 72b)
ሁዛይፋ ቢን ዑሰኢድ እንደዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

የወንድ ዘር ጠብታ በማህፀን ውስጥ አርባ ወይም አርባ አምስት ሌሊት በቆየ ጊዜ መልአኩ መጣና፡- ጌታዬ ሆይ መልካም ነው ወይስ ክፉ? ከዚያም እነዚህ ሁለቱም ነገሮች ይጻፋሉ። ከዚያም መልአኩ፡- ጌታዬ ወንድ ወይስ ሴት? ከዚያም እነዚህ ሁለቱም ነገሮች ይጻፋሉ። ተግባራቱ እና ሥራዎቹ፣ ሞቱ፣ መተዳደሪያው፣ እነዚህም ይመዘገባሉ። ከዚያም የርሱ የዕጣ ፈንታ ሰነድ ስለሚጠቀለል ምንም ተጨማሪ እና ቅናሽ የለም… (Sahih Muslim, Book 33, number 6392)

“በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ውስጥ አንድ ሰው ዘሩ እንዳይበሰብስ ይጸልይ፤ ከሦስተኛው እስከ አርባኛው ቀን ልጁ ወንድ እንዲሆን ይጸልይ።” (Babylonian Talmud, Berakoth 60a)

 

ሙሐመድ የሽል እድገት ደረጃዎችን ከግሪክ ፍልስፍናዎች በተጨማሪ ከሌሎች በዙርያው ከነበሩት ማሕበረሰቦች መቅዳቱ ግልጽ ነው። ታድያ ይህ ከሰማይ የወረደ መገለጥ እንዴት ሊባል ይችላል?


ማጠቃለያ

ሙስሊም ወገኖቻችን አዲስ የቋንቋ ፍቺ ትንታኔ ውስጥ ገብተው አዲስ የሽል አስተዳደግ ደረጃ ፈልስፈው ካልሆነ በቀር ቀጥታ በቀጥታ እንደወረደ ቁርአንም ሆነ የእስልምና መዛግብት  ቢነበቡ ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር እንደማይስማሙ ግልፅ ነገር ነው። ይህ የሙስሊም መምህራንንም የሚያስማማ ነገር ነው።

የእስልምና ታላላቅ ሙፈሲሮች የእስልምና መዛግብት ላይ በቀጥታ የሰፈሩትን ተረኮች ያስረዱትበት መንገድ፣ እንዲሁም ህዝበ ሙስሊሙ ለዘመናት ሲረዳው የኖረው በግልፅ ትርጓሜው ነው። በዚህ ዘመን ያሉ የሙስሊም መምህራን በእስልምናው አለም በማይታወቅ አዲስ ትንታኔ እስልምናን ከዘመናዊ ግኝት ጥናቶች ጋር አብሮ ለማስኬድ ቢጥሩም እስካሁን እንደተመለከትነው ከስህተት አልታደጉትም። ከስነ ፅንስ ጥናት ግኝት ጋር ብቻም ሳይሆን በሁሉም ሳይንሳዊ ዘርፎች ዙርያ ቁርአን ላይ የሰፈሩትን ስህተቶች ለማረም ሰፊ ዘመቻ የተጀመረው ከፈረንሳዊው ቀዶጠጋኝ ማውሪስ ቡካይሌ ወዲህ ነው።ሳይንሳዊ ግኝቶችን ተጠቅሞ የቁርአንን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙግት ቡካይሌኢዝም የሚል ስም የተሰጠው ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ከዚሁ ሰው ነው፡፡ ከእነዚህ ዘመቻዎች ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑ ሳይንቲስቶች ስለቁርአን ሳይንሳዊነት መሰከሩ የሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ይገኝበታል። እንኳን ሳይንቲስት ቀርቶ በጭፍን እምነት እምነት ያልተሸበበ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የቁርአንን ስህተት አንድ ባንድ ማስረዳት ይችላል።

አንድ ሙስሊም ሰባኪ በቁርአን ውስጥ ስለተጠቀሰው የስነ-ፅንስ ተረክ ማውራት ከጀመረ የቁርአን ክፍል ይመስል ሳይጠቅሰው የማያልፈው ሰው ኪይት ሙር ነው። ኪይት ሙር ከ ሼይክ አብዱል መጅድ ዚንዳኒ ጋር በመሆንም The Developing Human: Clinically Oriented Emryology with Islamic Additions የሚል እስልምናን የሚደግፍ መጽሐፍ አሳትሟል።

ይህ መፅሀፍ ብዙ አስገራሚ ገፅታዎች አሉት።  ሙስሊም ወገኖቻችን እዚህ ጋር አንድ ነገር ማስተዋል እንዳለባቸው እንመክራለን። ኪይት ሙር አረብኛ አያውቅም ፣ የሙስሊም ሰባኪያን ደግሞ የፅንስ አስተዳደግ ተረክ ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ተስማማ የሚሉት ደግሞ የአረብኛዎቹ ስርወ ቃል ውስጥ በመግባት የተለየ አዲስ ትንታኔ በመስጠት ነው። ይህ ሰው ሌላው ቀርቶ ትንታኔ የሚሰጥባቸውን የአረብኛ ቃላትን በሚገባ እንኳን አስተካክሎ መጥራት አይችልም [99]  እራሱም በግልፅ አረብኛ ትርጓሜዎቹ ትክክል ናቸው በማለት እንዳላረጋገጠ በቀጥታ ገልጿል [793] ይህ ሳይንቲስት ቁርአንን ትክክል ነው የሚለን በእራሱ አንብቦ ፣ እና ተረድቶት ሳይሆን ሳይሆን በ1980 (እኤአ) በንጉስ አብዱላዚዝ ዩኒቨርስቲ ታስተምራለህ በሚል ስም ተጠርቶ ነው።  በመፅሀፉ መግቢያ ላይ ለሶስት አመታት ያህል የዩኒቨርሲቲው የስነ-ፅንስ ኮሚቴዎችን በቁርአን ላይ ያሉ ተረኮችን ወደ ዘመናዊው ሳይንስ በማጠጋጋት (በእሱ አባባል በመተርጎም) እንዳገዛቸው ይናገራል። እውነት ቁርአን እንዲህ አይነት ነገር ብሎ ከሆነ ተጨንቆ እና ተጠቦ ሳይንቲስት በመጥራት ሳይሆን በግልፅ የሚታይ ነገር ይሆን ነበር። የመጽሐፉ መግቢያ እንዲህ ይላል:-

ኪይት ሙርን ስለ ዘመናዊ ስነፅንስ አስተምህሮ አያውቅም የማለቱ ድፍረት የለኝም። ነገር ግን ከሼክ አብዱል መጅድ ዚንዳኒ ጋር በድርድር እንዲህ የማይመስል ነገር ማለት እንደጀመረ በግልፅ የሚታይ እውነት ነው።

ይህ የየመን ሰው በአብዱላዚዝ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ፅንስ ኮሚቴ መሪ የነበረ ሲሆን በ1984 Commission on Scientific Signs in the Quran and Sunnah የሚባል ተቋም አቋቁሞ በቁርአን ያሉ ስሁት ተረኮችን በቃላት ማምታታት ለማረም በሰፊው ደክሟል። ሙርን እንዳግባባው ሁሉ ሌሎች ምዕራባውያን ሳይንቲስቶች የቁርአንን ልከኝነት እንዲመሰክሩ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በማግባባት ብሎም ረጅም ርቀት በመሄድ ንግግራቸውን እየቆራረጠ ያላሉትን እንዳሉ በማድረግ አቅርቧል። [222]  ንግግራቸው ተቆርጦ ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ በማቅረቡ ብዙ ሳይንቲስቶችን ያስቆጣ ሲሆን  ለምሳሌ በስነፅንስ ተረክ ዙርያ ፕሮፌሰር ሊይ ሲምሰን ከአውዱ ውጪ ወጥቶ የቀረበ የማይረባ እና አሳፋሪ “ብሎ ኮንኖታል። [11]  በዚህ ሰው አማካኝነት በሌሎች ዘርፍም ባሉ ሳይንቲስቶች ንግግራችው አለአግባብ እንደ[@@]

በየመን መንግስት ድጋፍም ኢማን የሚባል የትምህርት ተቋም ከፍቷል። በዚህ የትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን ጨርሰው የሚወጡ ሰዎች በብዛት አሸባሪ እና አክራሪ መሆናቸው በብዛት እያጠያየቀ ይገኛል።

የውቅያኖስ ሳይንቲስቱ ዊሊያም ይ። በተመሳሳይ ያልተገኘ የኤችኣይቪ በሽታ መድሀኒት ከጥቁር አዝሙድ ተገኘ እያለ በባዶ ሜዳ ሽብር ሲፈጥር የቆየ ሰው ነው።

ሙር ቢሆንም ኪይት ሙር ለትምህርት አላማ ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን THE DEVELOPING HUMAN CLINICALLY ORIENTED EMBRYOLOGY በሚለው መፅሀፍ ላይ ጥንታውያን ፈላስፎች ያቀረቡትን መላምት እንዲህ አስቀምጧል

ሙር የኒውተንን አባባል በማስቀደም የስነ-ፅንስ ጥናትን ታሪካዊ ዳራ ማስቀመጥ ይጀምራል “If I’ve seen further ,Its by standing on the shoulder of giants” ግርድፍ ትርጉሙ የተሻለ መመልከት ከቻልኩኝ ታላላቆች ትከሻ ላይ በመሆን ነው ማለት ነው። ነገር ግን ለቁርአን ብቻ ይህንን አባባል እንዳልተጠቀመበት አልገባኝም። በቁርአን ላይ የተጠቀሰው የፅንስ እድገት አስቀድሞ ሲነገር የነበረ ነው። ስለዚህ ለቁርአን እውቅና ከመሰጠቱ በፊት ከቁርአን አስቀድመው ለነበሩት ሀተታዎች እውቅና መሰጠት አለበት። ስለቁርአን ይቀጥላል…

በመካከለኛው ዘመን የስነ-ፅንስ ሳይንስ እንደቀዘዘ በመጥቀስ በቁርአን የተገለፀውን ፅንስ ” ከቅልቅል የወንድ እና የሴት ፈሳሾች (mixture of secretion)” እንደተፈጠረ ያስታውሳል። በተጨማሪም እንደቁርአን ተረክ” ፅንሱ ከተጀመረ በስድስተኛው ቀን አለቅት የሚመስል ቅርፅ ይይዛል በመቀጠልም የታኘከ ነገር እንደሚሆን” ቁርአን ንደሚናገር ያስረዳል። ኪይት ሙር ይቀጥላል…

ሙር ቅልቅል ፈሳሾች (የወርአበባ ደም እና የዘር ፈሳሽ) ልጅ ይፈጥራሉ ብሎ አርስጣጣሊስ ማስተማሩን ከገለፀ በኋላ እርሱን  በመዝለል ከእርሱ ተመሳሳይ የሆነውን የቁርአንን ገለፃ ለምን ትክክል እንዳደረገ ግልፅ አይደለም።  ሙር “ቁርአን ከወንድ እና ከሴት የሚወጡ ቅልቅል ፈሳሾች ( mixture of secrrtions) ልጅ ይፈጥራሉ ” ይላል ባለበት ብዕሩ  እዛው ገፅ ላይ 13 መስመር ከፍ ብሎ መፃፉን ዘንግቶት ነው ወይንስ ምሁራዊ አድርባይነት ?

ሙር በመቀጠል በወቅቱ የዕውቀት እጥረት እንደነበር ገልፆ ከአርስጣጣሊስ አስተምህሮ በመነሳት የረጋ ደም ልጅ ሲሆን የሚያሳይ ስህተት የሆነ ምስል በ1554 (እኤአ) በያዕቆብ ሩኢፍ የተሳለ ምስል ያሳያል። በመቀጠልም የረጋ ደም የሚባል የፅንስ እድገት እስከ18ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ እንደቆየ ከምስሉ ስር በተቀመጠው ማብራርያ ያስቀምጣል።የእኛ ጥያቄ ቁርአንስ ከዚህ ውጪ ምንድን ነው ያለው ? የሚል ነው።

ኪይት ሙር ያለውን ለሰማ ሰው አንድ ጥያቄ በውስጡ ያጭርበታል። ኪይት ሙር የዘመናዊ ስነ-ፅንስ ግኝት በሰባተኛው ክፍለዘመን በተከተቡት የእስልምና መዛግብት ላይ ስለተገኘ ቁርአን መለኮታዊ ራዕይ ነው የሚል ለሰሚው አስቂኝ የሆነ ሙግት ያነሳል። ኪይት ሙር እውነት ከልቡ እስልምና መለኮታዊ ሀይማኖት ነው ብሎ ካመነ ለምን እስልምናን አይቀበልም? ለሙስሊም ወገኖቻችን ቁርአን ግልጠተ መለኮት ነው ቢልም እርሱ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ አልተቀበለም። ይሄ በግልፅ የሚያሳየው የሙስሊሙን ማኅበረሰብ (ተጽፎ በተሰጠው) በማይመስል ታሪክ ከማፅናናት ባለፈ እስልምናን እንዲቀበል የሚያደርገውን ጠንካራ ምክንያት አላገኝም።  በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች ባሉበት ፕላኔት ላይ እንደሙስሊም ሰባኪያን አጠቃቀስ ግን እዚህ ምድር ላይ ያለ ብቸኛ ሳይንቲስት ኪይት ሙር ይመስላል።

ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ የተከበራችሁ ሙስሊሞች! እስላማዊ መዛግብት እንዲህ ስህተት ሆነው ሳለ ቀርቶ ቃል በቃል ተመሳሳይ ቢሆኑ እንኳ ለቁርአን የአምላክ ቃልነት ማረጋገጫ አይሆኑም። በእርግጥ እውነተኛ ሀይማኖት በተጨባጭ ምርምር ከተረጋገጠ ግኝት ጋር መጋጨት ባይኖሩባቸውም ነገር ግን ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለአምላክ ቃልነት መፈተሻ መውሰድ አግባብ አይደለም። ከላይ እንዳየነው የሙስሊም መምህራን እያደረጉት ያለው ተአምር ፈጠራ ነው። በቁርአን ውስጥ ቀጥታ የተነገሩ በእስልምናው አለም ሲታመንባቸው የኖሩትን ነገሮች ለንጥል ቃላቶቻቸው አዲስ ፍቺ በማፈላለግ ከክፍል በማይገጥም ግን ደግሞ ለተረጋገጠው ሳይንሳዊ እውነት ይገጥማል ባሉት መንገድ እየተረጎሙ ይገኛሉ። ቁርአን ውስጥ ያሉት ነገሮች በዘመኑ ያልታወቁ ነገሮች ቢሆኑ የተለየ መረዳት በሙስሊሙ ዘንድ ይኖር ነበር። በሙስሊም ሰባክያን አካሄድ የጋለንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን አስተምህሮ ትክክል ነው ብሎ በጭፍኑ መሞገት ይቻላል።

  • ጋለን እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው!
  • ጋለን የተጠቀመበት የግሪኩ ቃል ድርብ ትርጉም ስላለው በድርቡ ትርጉም ውስጥ ያለውን ነገር ይመስላል ማለቱ ነው፤  ቀጥታ ሲተረጎም የኖረው ከበፊት ፈላስፎች አስተምህሮ ጋር የሚገጥመው ትርጉም የጋለንን አስተምህሮ አይገልፅም።
  •  ጋለን ትክክል ሆኖ 1400 ዓመት ሙሉ የተከተሉት ተከታዮቹ  ምን እንዳለ አልተረዱትም።
  • ጋለን በወቅቱ የተናገረበት ቀጥተኛ ንግግር በወቅቱ ከነበሩት አስተሳሰቦች ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ዘመናዊ ግኝቶች ላይ ቆመን ለንግግሮቹ የተጠቀመባቸውን ቃላት እየነጣጠልን፤ ወደምንፈልገው አመለካከት እስኪቀርቡልን ስንለጥጣቸው ትክክል ይሆናል። ወዘተ …

የተወደዳችሁ ሙስሊም አንባብያን እስልምናን እንሰብካለን የሚሉ በተናገሩት መልኩ ለቁርአንም ገለፃ ለሳይንሱም ገለፃ ግድ ሳይሰጣቸው እንዲሁም የህዝበ ሙስሊሙን እና ሙስሊም ያልሆነውን ማህበረሰብ ይሉኝታን ባለመፍራት በእየአደባባዩ አይን ያወጣ ውሸት ያስተላልፋሉ። ሁለቱንም አጣጥፈው ገጠመ እያሉ አዋጅ ያስነግራሉ። ህዝበ ሙስሊሙ ለገንዘብ ያደሩ ህሊናቸውን የሸፈኑ ሰዎች ስብከት ሳይደናበር እውነታን በንፁህ ልቡ እንዲፈልግ እና ሀቀኛ የሆነ ንፅፅር እንዲያደርግ እመክራለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንንም ይርዳን!


ቁርኣንና ሳይንስ?

ቁርኣን