እውን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ተሳስቷልን?
በወንድም ሚናስ
በዐዲስ ኪዳን ላይ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ክሶች መኻከል ጸሓፊያኑ የብሉይ ኪዳንን ምንባባት በሚጠቅሱበት ጊዜ በተደጋጋሚ ይሳሳታሉ የሚል ነው። የተለመደው ምሳሌ በ ሉቃስ 4፥18 ላይ የሚገኝ ሲኾን ሉቃስ የኢሳይያስ 61፥1 ጥቅስ ከራሱ ጨምሮ ተርጕሞአል የሚል ነው። የኢሳይያስ ትንቢትን በማስቀደም እንጀምር ፦
“የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛል። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል” ኢሳ.61፥1
ኾኖም ግን የሉቃስ ወንጌል 4፥18 በምናነብበት ጊዜ “ለታወሩት ማየትን” የሚል ይገኝበታል።
ጽርዕ፦ πνεῦμα κυρίου ἐπ’ ἐμὲ οὗ εἵνεκεν ἔχρισεν με εὐαγγελίσασθαι πτωχοῖς, ἀπέσταλκεν με, κηρύξαι αἰχμαλώτοις ἄφεσιν καὶ τυφλοῖς ἀνάβλεψιν ἀποστεῖλαι
τεθραυσμένους ἐν ἀφέσει
የዐማርኛ ትርጕም፦
“የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም መጽሐፍ በተረተረው ጊዜ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ክፍል አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣” ሉቃ. 4፥18
የግእዙ ትርጕም፦
“መንፈስ እግዚአብሔር ላዕሌየ በዘእንቲአሁ ቀበአኒ እዜንዎሙ ለነዳያን ፈነወንኒ እስብክ ሎሙ ግዕዛነ ለፂዉዋን ወይርአዮ ዕዉራን ወአንግፎሙ ለግፉዓን ወእስብክ ዐመተ እግዚአብሔር ኅሪተ” ሉቃ. 4፥18-19
እንደምንመለከተው ፣ “ለታወሩትም ማየትን” የሚለው ቃል አስቀድመን ባነበብነው የኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ አይገኝም። ታዲያ ሉቃስ ይህ ጥቅስ ዕውራን እንደሚያዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ ተናግሯል፤ ኢየሱስም ይህንን ክፍል አንብቧል፤ የሚለውን ዐሳብ ከወዴት አመጣው? ምላሹ አስተማሪ ነውና ይከታተላሉ።
1. እንደሚታወቀው ኻያ ሰባቱም የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የብሉይን ምንባባት በሚጠቅሱበት ጊዜ ከጥንታዊው የጽርዕ የብሉይ ኪዳን ትርጕም ከኾነውና በዘመኑም በአይሁዳውያን ምኵራብ ጭምር ይነበብ ከነበረው ከሰባ ሊቃናት ትርጕም መኾኑ ይታወቃል። የኢሳይያስ 6፥11 ክፍልም በዚኹ ጥንታዊ ትርጕም እንዲኽ ይነበባል፦
“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ልባቸውን የተሰበረውን እዘግን ዘንድ፣ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለታወሩት ማየትን እሰብክ ዘንድ ልኮኛል”
Πνεῦμα Κυρίου ἐπ᾽ ἐμέ, οὗ εἵνεκεν ἔχρισέν με· εὐαγγελίσασθαι πτωχοῖς ἀπέσταλκέν με, ἰάσασθαι τοὺς συντετριμμένους τὴν καρδίαν, κηρῦξαι αἰχμαλώτοις ἄφεσιν καὶ τυφλοῖς ἀνάβλεψιν.
ከላይ ባነበብነው ጥንታዊ የጽርዕ ቅጂ ውስጥ “ለታወሩት ማየትን” የሚለው ማጣቀሻ እንዳለ ልብ ይሏል። ስለዚኽም ወንጌላዊው ሉቃስ ስቷል ሊያስብለው የሚችል አንዳችም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነበረው ስመጥር የአይሁድ መዛግብት መካከል አንዱ በኾነው የኢሳይያስ ቅጂ ውስጥ የተካተተ ሐረግ ነውና።
2. በ1947 ዓ.ም በተገኘው የሙት ባሕር ጥቅልሎች በርካታ የኢሳይያስ ቅጂዎችን የተገኘ ሲኾን ከእነርሱም መኻከል “ዐይን ማየት” የሚል የዕብራይስጥ ቅጂ ተገኝቷል። የዃለኛው የአረማይክ ታርጕምም በተመሳሳይ “የታሰሩትም ብርሃንን ያያሉ” ብሎ አስፍሯል፤ ይህም የዕብራይስጥ ምንባብ የሰባ ሊቃናት ተርጓሚዎች የዕውራን ብርሃንን እንደ ሚያገኙ ከገለጹበት ጋር ይስማማል። በተጨማሪም ይህ ትርጓሜ በኢሳይያስ 61 እና ኢሳይያስ 42 መኻከል ባለው መመሳሰል የጸና ጭምር ነው ። ኢሳይያስ 61:1ን በምናነብበት ጊዜ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛል” ሲል እንደሚጀምረው በምዕራፍ 42 ተመሣሣይ ነገር እናነባለን፦
“ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ ምርጤ ይህ ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ ደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል።”
— ኢሳይያስ 42፥1 (አዲሱ መ.ት)
ከተወሰኑ ቍጥሮች በዃላም፦
“የዕውሮችን ዓይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ።”
— ኢሳይያስ 42፥7 (አዲሱ መ.ት)
ስለዚህ በጣም ተመሳሳይ በኾነ ዐውድ ውስጥ የዕውራን ዐይን መብራት ከእስረኞች ነፃ መውጣት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ይህ ትይዩ የኢሳይያስ 61ን የጥንት የአይሁዶች ንባብ የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አልተሳሳተም።