መግቢያ
ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ለክፍለ ዘመናት አብረው የኖሩ የሃይማኖት ማሕበረሰቦች ናቸው፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሁለቱ እምነቶች ተከታይ በመሆኑ በነዚህ የሃይማኖት ማሕበረሰቦች መካከል የሚኖር ሰላምም ሆነ አለመግባባት በዓለም ሰላም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ አለው፡፡ አንዳንድ ወገኖች አብሮ በሰላምና በመከባበር ለመኖር ልዩነቶቻችንን ችላ ማለትና በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮር መፍትሔ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ክርስትናና እስልምና በየፊናቸው ብቸኛ ትክክለኛ ወደ ፈጣሪ የመድረሻ መንገዶች እንደኾኑ የሚያስተምሩ (Exclusivist) ሃይማኖታት በመኾናቸው ልዩነቶቻችንን በቸልታ ማለፍ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አብሮ በሰላም ለመኖር ዘላቂ መፍትሔ አይመስልም፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት ለልዩነቶች ስሜቱ ስስ የኾነን ማሕበረሰብ በመፍጠር ልዩነቶች በተነሱ ቁጥር ቁጣና አመፅን እንደመፍትሄ ወደመቁጠር የማምራት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ አንዳችን የሌላችንን ስብዕና ሳናጎድፍ በሐሳብ ልዩነቶቻችን ላይ ብቻ በማተኮር በሰለጠነ መንገድ መወያየት በመግባባት አብሮ በሰላም ለመኖር ትክክለኛው ፍኖት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይበል የሚያሰኙ ሥራዎችን የሠሩ የሃይማኖት መምህራን ቢኖሩም አንዳንዶች ግን ማሕበረሰቡን የማቀራረብና መቻቻልን የማስተማር ዝግጅት ጎድሏቸው ታይተዋል፡፡ በእስልምናው ወገን የሚገኙ አንዳንድ ጸሐፍት እንዲያውም በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚገኘውን የመቻቻል ወርቃማ ባሕል ለማፍረስ ታጥቀው የተነሱ እስኪመስሉ ድረስ በግዴለሽነት ብዙ ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ የሚኾነን “የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት” በሚል ርዕስ ኡስታዝ ሐሰን ታጁ የጻፉት መጽሐፍ ነው፡፡
ኡስታዝ ሐሰን ታጁ የተሻለ እውቀት እንዳላቸው ከማስባቸው ሙስሊም ጸሐፊያን መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ በአካል አይቻቸው ባላውቅም ስለ እሳቸው ከሚያውቁት ወገኖች ያገኘሁት መረጃ ሰውየው የተረጋጉ፣ ለመናገር የማይቸኩሉና አስተውሎት ያላቸው ሰው እንደሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይኸኛውን መጽሐፋቸውን ሳነብ ያንን የተወራለትን ሰናይ ባሕርይ ማየት አልቻልኩም፡፡ የዕውቀታቸውም ልክ ከዚህ ቀደም የገመትኩትን ያህል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
መጽሐፉ በብዙ የሐሰት መረጃዎች፣ ከተጭበረበሩ ምንጮች በተቀዱ ሐሳቦችና በአንካሳ ሙግቶች የተሞላ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጸሐፊው ከአንድ የሃይማኖት አስተማሪ የሚጠበቀውን የሌላውን ሰው እምነትና ስብዕና በማክበር መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ ብቻ አተኩሮ መልስ የመስጠትና ጥያቄ የመጠየቅ ትዕግስት በእጅጉ እንደሚጎድላቸውም አስተውያለሁ፡፡ ክርስቲያኖችን ከፈለጉ ይሳደባሉ፣ ሲያሻቸው ደግሞ በቅፅል ስሞች ይጠራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በስላቅ መጽሐፍ “ቅዱስ” በማለት ይጠራሉ፤ እዚህ ቦታ መልሶ ለመጻፍ በማይመጥኑ ከአንድ የሃይማኖት መምህር በማይጠበቁ ኃላፊነት በጎደላቸው ቃላት ይወርፋሉ፡፡ ዓላማቸው እውነትን ማስተማር አለመሆኑና የአንባቢያንን አስተሳሰብ መመረዝ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከክርስቲያን ጎረቤቶቹ ጋር ተከባብሮና ተቻችሎ የኖረውን ሕዝበ ሙስሊሙን ከክርስቲያን ወገኖቹ ጋር የማቃቃር ዓላማ ያነገቡ ነው የሚመስሉት፡፡ በቁርኣን ላይ የተነሱትን ጥያቄዎች ምሑራዊ ሙግቶችን በማቅረብ መርታት አስቸጋሪ መሆኑን ስለተገነዘቡ እነዚህን የዘለፋ ቃላት ሙግታቸውን ለማጠናከር እንደ አማራጭ ወስደው ይሆን?
በመጽሔቱ ላይ ለተነሱት ሐሳቦች መልስ ከመስጠታቸው በፊት በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ማሕበሩ የተጻፈ ጽሑፍ በመገልበጥ የአንባቢያንን ጊዜ ማባከናቸው ስለ እውነተኛ ሙግት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመጽሐፋቸው መቅድም ላይ የጠቀሷቸው ስለ ማሕበሩ የተወሩት ጉዳዮች እውነት ቢሆኑ እንኳ ክርስትናን ስህተት እስልምናን ደግሞ እውነት ሊያሰኝ የሚችል ሙግት መፍጠር አይችሉም፡፡ “ጥሩ” የተባሉ ሰዎች ውሸትን ሊናገሩ እንደሚችሉት ሁሉ “ጥሩ ያልሆኑ” የተባሉትም ሰዎች እውነትን ሊናገሩ ስለሚችሉ ብስለት ያላቸው አንባቢያን አንድን ሙግት ከተናጋሪው ማንነት ነጥለው ማየት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ፡፡ ሐሰን ታጁ ይህንን ማድረግ አለመቻላቸውና የሙግት አቅራቢዎቹን ማንነት በመተቸት (Ad hominem) የሥነ አመክንዮን ሕግ መጣሳቸው ምሑራዊ ሙግት የማድረግ ዝግጅት እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡ ይህንን መሠረታዊ ምሑራዊ አካሄድ ባልጠበቁበት ሁኔታ በማሕበሩ ድረ-ገፅ ላይ እንደሚገኝ ከሦስተኛ ወገን መስማታቸውን የገለፁትንና ምንጭ ያልጠቀሱለትን አንድ “የፈውስ” ታሪክ፣ ከኦርቶዶክስ ድርሳናት እንደተጠቀሰ የገለጹትን ሌላ ታሪክና ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ በማከል መሰል ታሪኮችን ከሚቀበሉ ወገኖች ጋር ምሑራዊ ውይይት ማድረግ “የዳገት ሩጫ” እንደሆነ መናገራቸው ምሑራዊ ውይይት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሚያውቁት ወገኖች ዘንድ ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል (ገፅ 10)፡፡
የተዘበራረቀውንና ሥርዓት አልባ የሆነውን የምንጭ አጠቃቀሳቸውን የተመለከተ አስተዋይ አንባቢ ሌሎች ወገኖችን ለምሑራዊ ውይይት የማይመጥኑ በማስመሰል የሚያንጓጥጡት የተከበሩት ኡስታዝ ራሳቸው ምን ያህል ለምሑራዊ ውይይት የበቁ ናቸው? ብሎ መጠየቁ የማይቀር ነው፡፡ ማንነታቸው በውል የማይታወቁ ጸሐፊያንን በተደጋጋሚ የጠቀሱ ሲሆን ብዙ መረጃዎቻቸው ምንጭ አልባ በመሆናቸው መልስ እንኳ የሚያሻቸው አይደሉም፡፡ ይህንን መጽሐፍ ብዙ ሙስሊም ወገኖቻችን እንደ ጥሩ የሙግት ምንጭ በመቁጠር ትልቅ ቦታ ስለሰጡት ጊዜያችንን በመሰዋት መልስ ለመስጠት ወስነናል፡፡
የኡስታዙ መጽሐፍ የዘመናችን ሙስሊም ዳዒዎች የሚጠቀሟቸውን የሙግት ዘዴዎች ሁሉ የሚወክሉ እንደ ሥነ አመክንዮ ተፋልሶዎች፣ ምንጮችን ከአውድ ውጪ መጥቀስ፣ ቃላትን በተሳሳተ መንገድ መተርጎም፣ መረጃዎችን መካድ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ስሁት አካሄዶችን ሁሉ የሸከፈ በመሆኑ ይህንን ምላሽ ያነበቡ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጽሑፎች ቢያጋጥሟቸው አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ሙስሊም ወገኖች ደግሞ ሳባኪዎቻቸው እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚያታልሏቸው ስለሚገለጥላቸው መንገዳቸውን በመመርመር ትክክለኛውን ውሳኔ መወሰን ይችሉ ዘንድ ይረዳቸዋል፡፡ አንባቢያን ጥሩ ዕውቀት መቅሰም ይችሉ ዘንድ ኡስታዙ ከጻፉበት ደረጃ ከፍ በማድረግ በማስረጃና ርቱዕ አመክንዮ የተዋዙ መልሶችን አቅርበናል፡፡
ይህንን መጽሐፍ ስታነቡ ሳላችሁ የሰማዩ አምላካችን ይባርካችሁና ያንፃችሁ ዘንድ ምኞትና ጸሎቴ ነው፡፡ ተከታዩን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህ በልባችሁ በመያዝ ከኔ ጋር ወደ ዋናው ይዘት ትዘልቁ ዘንድ በአክብሮት ተጋብዛችኋል፡፡
“ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ፡፡ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” (ሮሜ 12፡17-18)፡፡
በክርስቶስ የናንተው፦ ዳንኤል እውነትለሁሉ