ምዕራፍ አራት ቁርኣንና ሳይንስ “የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት” በሚል ርዕስ በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ

ምዕራፍ አራት

ቁርኣንና ሳይንስ

ባለፉት ሦስት ክፍለ ዘመናት በምዕራቡ ዓለም ከተቀጣጠለው የሳይንስ አብዮት የተነሳ የሙስሊሙ ዓለም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ስጋቱ ከአብዮቱ ፖለቲካዊ ምልከታ ባሻገር ሳይንሳዊ ግኝቶች የእስልምና ሃይማኖት መሠረት በሆነው በቁርኣን ውስጥ ስህተቶች መኖራቸውን ይገልጥ ይሆናል የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሳይንሳዊ ግኝቶች ለእስልምና ጥቅም ማዋል የሚቻልበትን መንገድ የቀደደ አንድ መጽሐፍ ለሕትመት በመብቃቱ የሙስሊሙ ዓለም እፎይታን አገኘ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ መውሪስ ቡካይሌ ይሰኛል፡፡ ዶ/ር ቡካይሌ የሳዑዲ አረብያ ንጉሥ የግል ኃኪም የነበረ ሲሆን ሙስሊም አልነበረም፡፡ በ1976 ዓ.ም. መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቁርኣንና ሳይንስ በሚል ርዕስ ባሳተመው ጥራዝ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ “በሳይንሳዊ ስህተቶች የተሞላ” መሆኑንና ቁርኣን ደግሞ በተጻራሪው ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ “ሳይንሳዊ ቅድመ ዕውቀቶችን በውስጡ የያዘ ከስህተት የጸዳ መለኮታዊ መጽሐፍ” መሆኑን ይሞግታል፡፡ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ተጠቅሞ የቁርኣንን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙግት ቡካይሌኢዝም የሚል ስም የተሰጠው ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ከዚህ ሰው ነው፡፡

ሐሰን ታጁ በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ቡካይሌን ጠቅሰውታል፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-

… በዚህ ዘመን በተለያዩ የሳይንስ መስኮች የተገኙ አዳዲስ ግኝቶችን ቁርኣን ከ14 ክፍለ ዘመናት በፊት ቀድሞ ከመናገሩ የበለጠ አምላካዊነቱን መስካሪ ነገር ማግኘት ይቻላልን? በዚህ ረገድ ከተደረጉ ምርምሮች መካከል ፈረንሳዊው የሕክምና ሊቅ ዶክተር ሞሪስ ቡካይ The Bible The Quran and the science በሚል ርዕስ ያሳተመው መጽሐፍ ይገኝበታል፡፡ ጸሐፊው ምርምሩን ለማድረግ ሲነሳ ሙስሊም አልነበረም፡፡ ጥናቱን ካጠናቀቀ በኋላ ግን በደረሰበት አስገራሚ ግኝት በመደነቅ ነቢዩ ሙሐመድ እነዚህን ሳይንሳዊ እውነታዎች ሊያውቁ የሚችሉበት ምንም አይነት መንገድ እንደሌለ ከገለጸ በኋላ የቁርኣን ምንጭ መለኮታዊ መሆኑን በመገንዘብ እስልምናን ተቀብሏል፡፡ (ገፅ 178)

የቡካይሌ መጽሐፍ የእንግሊዘኛ ሙሉ ርዕስ The Bible, The Qur’an, and Science: The Holy Scriptures Examined in the Light of Modern Knowledge የሚል ሲሆን መጀመርያ የተዘጋጀው በፈረንሳይኛ ነበር፡፡ መጽሐፉ ከእንግሊኛ በተጨማሪ ወደ ብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሟል፣ በሙስሊሙ ዓለም ውስጥም በከፍተኛ ሁኔታ ተሽጧል፡፡

ፈጠራ የማይሰለቻቸው አቶ ሐሰን ቡካይሌ “እስልምናን ተቀብሏል” ቢሉም ነገር ግን እስልምናን መቀበሉን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ሰውየው እስልምናን መቀበሉን በመጽሐፉ ውስጥም ሆነ በየትኛውም ቦታ አልገለፀም፡፡ እስላማዊ መጻሕፍትን በማሰራጨት የሚታወቀው Pak Books የተሰኘ ድረ-ገፅ በዶ/ር ቡካይሌ ካታሎግ ስለ ሰውየው ሲገልፅ፡-

“በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን መረጃዎች ማጥናቱ ዶ/ር ቡካይሌ ለቁርኣን ከፍ ያለ አክብሮት እንዲኖረውና በክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ተቃርኖዎች እንዲገነዘብ ረድቶታል፡፡ ይህ በንዲህ እንዳለ ለእስልምና ጥልቅ አክብሮት ቢኖረውም የክርስትና እምነቱን አልቀየረም” በማለት ጽፏል፡፡[1]

ቡካይሌ ክርስቲያን መሆኑን ተናግሮ ባያውቅም ነገር ግን ሙስሊሞች የእስልምናን እውነተኝነት የተገነዘበ ክርስቲያን ሊቅ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ዳሩ ግን ሙስሊሞችን ሁሉ ሊያሳስብ የሚገባው አንድ ጥያቄ አለ፤ ቡካይሌ ቁርኣን የፈጣሪ ቃል መሆኑን ካረጋገጠና ሌሎች ሰዎችም ይህንኑ እንዲያውቁ በሚል መጽሐፍ ከጻፈ ለምን እስልምናን አልተቀበለም? መልሱ ግልፅ ነው፡፡ ቡካይሌ እስልምና እውነት መሆኑን ከልቡ የሚያምን ሰው አልነበረም፡፡ መጽሐፉን የጻፈው ለገንዘብ እንጂ የእውነት ምስክር ለመሆን አልነበረም፡፡ ይህ መጽሐፍ ምድራዊውን ኃብት በአቋራጭ የማጋበስ ዓላማውን በማሳካት በዶላር ኮረብታ ላይ አስቀምጦታል፡፡ እንዲህ ያለ ሰው የእውነት ምስክር የመሆን ብቃት እንዴት ሊኖረው ይችላል?

  1. ሳይንስን ማን አስተማራቸው?

ሳይንስን ማን አስተማራቸው? የሚለው ጥያቄ አቶ ሐሰን “የቁርኣን ደራሲ ከሌሎች ምንጮች ቀድቷል” ለሚለው ሙግት የሰጡት ምላሽ ነው፡፡ የ20ው ክ.ዘ. ግኝቶች የሆኑ በርካታ ሳይንሳዊ እውነታዎች በቁርኣን ውስጥ መገኘታቸውን ከገለጹ በኋላ ሁለት ምሳሌዎችን በመጥቀስ ምላሻቸውን በማስረጃ ለማጠናከር ይሞክራሉ (ገፅ 118)፡፡ ዳሩ ግን የጠቀሷቸው ሁለቱም ምሳሌዎች ቁርኣን ምን ያህል ከሳይንስ የራቀ መሆኑን የሚያሳዩ እንጂ ነጥባቸውን የሚያረጋግጡ ሆነው አላገኘናቸውም፡፡ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡-

  • ሁሉም ነገር የተፈጠረው ጥንድ ሆኖ ነው?

እንስሳት ብቻ ሳይሆኑ እጽዋትም ጭምር ሴቴና ወንዴ ፆታ እንዳላቸው፤ ከዚህም አልፎ ሁሉም ነገር የጥንድ (ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ) ባሕርይ መያዙ በቁርኣን መገለፁን ለማረጋገጥ ገፅ 118 ላይ ተከታዮቹን ጥቅሶች ጠቅሰዋል፡-

“ያ ምድር ከምታበቅለው ከነፍሶቻቸውም ከማያውቁትም ነገር ዓይነቶችን ሁሏንም የፈጠረ (አምላክ) ጥራት ይገባው፡፡” Exalted is He who created all pairs – from what the earth grows and from themselves and from that which they do not know. (ሱራ 36፡36)

“ትገነዘቡም ዘንድ ከነገሩ ሁሉ ሁለት (ተቃራኒ) ዓይነትን ፈጠርን፡፡” And of all things We created two mates; perhaps you will remember. (ሱራ 51፡49)

አብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ሁለተኛውን ጥቅስ ሲያብራሩት እንዲህ ብለዋል፡-

ሁሉም ነገር ጥንድ ነው፤ የእፅዋትና የእንስሳት ፆታ… የማይታዩት የተፈጥሮ ኃይላት፣ ቀንና ሌሊት፣ ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ የኤሌክትሪክ ሞገዶች…

የአማርኛ ቁርኣን የግርጌ ማስታወሻም ጥቅሱን በተመሳሳይ መንገድ ይተረጉመዋል፡፡

እንስሳትና እፅዋት ወንዴና ሴቴ እንዳላቸው ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ በመሆኑ እንዲህ ያለው ንግግር ሳይንሳዊ ቅድመ ዕውቀት ሊባል አይችልም፡፡ ዳሩ ግን የቁርኣን ጸሐፊ ሁሉም ነገር ጥንድ ሆኖ እንደተፈጠረ በመናገር መገለጡ መለኮታዊ አለመሆኑን ይፋ አውጥቷል፡፡ ወንዴና ሴቴ የሌላቸው ብዙ የእፅዋት ዝርያዎች አሉ፡፡ ባክቴርያን የመሳሰሉት ባለ ነጠላ ሴል ፍጡራን ተባዕታይና እንስታይ ፆታ የላቸውም፡፡ ብዙ የፈንገስ ዝርያዎችም ተመሳሳይ ተፈጥሮ አላቸው፡፡[2] ተቃራኒ ፆታ የሌላቸው በዓይን የሚታዩ ብዙ የእንስሳት ዝርያዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በኒው ሜክሲኮ የምትገኝ ዊብቴይል ሊዛርድ የተሰኘች የእንሽላሊት ዝርያ እንስታይ ፆታ ብቻ ያላት ስትሆን የራሷን ምስለኔ (Clone) ዕንቁላል በመጣል ራሷን ትተካለች፡፡[3] የቁርኣን ደራሲ መገለጡ ከሰማይ የመጣለት ቢሆን ኖሮ ይህንን ሐቅ ማወቅ ባልተሳነው ነበር፡፡ አቶ ሐሰን ቁርኣን ሳይንሳዊ ሐቆችን በውስጡ መያዙን ለማሳየት የጠቀሱት አንቀፅ አንድ የሰባተኛው ክፍለ ዘመን አረባዊ ከነበረው ዕውቀት ያልተሻለ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

  • የሽል እድገት

በማስከተል ደግሞ ተከታዩን ጥቅስ ጠቅሰዋል፡-

“…እኛም ከዐፈር ፈጠርናችሁ፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ፣ ከዚያም ከረጋ ደም፣ ከዚያም ከቁራጭ ሥጋ፣ ፍጥረትዋ ሙሉ ከሆነችና ሙሉ ካልሆነች (ችሎታችንን) ለናንተ ልንገልጽላችሁ ፈጠርናችሁ፡፡ የምንሻውንም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በማሕፀን ውስጥ እናረጋዋለን፡፡ ከዚያም ሕፃን ሆናችሁ እናወጣችኋለን፡፡ ከዚያም ሙሉ ጥንካሪያችሁን ትደርሱ ዘንድ (እናሳድጋችኋለን)፡፡” (ሱራ 22፡5)

ይህንን ጥቅስ ሲያብራሩት እንዲህ ብለዋል፡-

በዚህ አንቀፅ ውስጥ የፅንስ ዑደት ከሳይንስ እውነታ ጋር መቶ በመቶ በሚጣጣም መልኩ ተገልጿል፡፡ የሰው ልጅ መጀመርያ የፍትወት ጠብታ ነበር፡፡ ይህ ጠብታ ከሴቷ እንቁላል ጋር ሲዋሃድ እና ሲያዳብረው የረጋ ደም አይነት ባህሪ በመያዝ ከማህጸን ግድግዳ ላይ ይንጠለጠላል፡፡ ‹ዓለቃህ› የመንጠልጠልና የመጣበቅ ባህሪ ስላለው ነው፡፡ በመቀጠልም የተላመጠ ስጋ ይመስላል፡፡ ከነዚህ ሂደቶች በኋላ የተሟላ ቅርጽ ይይዛል፡፡ (ገፅ 119)

ቁርኣን ስለ ፅንስ ዑደት ደረጃዎች የሰጠውን ትንታኔ ሙሉ ምስል ለማግኘት አቶ ሐሰን ያልጠቀሱትን አንድ ጥቅስ እንጨምር፡-

“በእርግጥም ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው፡፡ ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍትወት ጠብታ አደረግነው፡፡ ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን፡፡ የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን፡፡ ቁራጯንም ሥጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን፡፡ አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው፡፡ ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረትን አድርገን አስገኘነው፡፡ ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ፡፡” (ሱራ 23፡12-14)

ስለዚህ በቁርኣን መሠረት ሰው በማህፀን ውስጥ መጀመርያ የፍትወት ጠብታ ነበር (የሴቷ ዕንቁላል አለመጠቀሱን ልብ ይሏል) è ጠብታው የረጋ ደም ይሆናል è የረጋው ደም ቁራጭ ሥጋ ይሆናል è ቁራጭ ሥጋው ወደ አጥንቶች ይለወጣል è አጥንቶቹ እንደገና ሥጋ ይለብሳሉ è ነፍስ በመዝራት ሰው ይሆናል፡፡

ይህንን የሽል ዕድገት ደረጃ በተመለከተ ቀድሞ የእስልምና እምነት ተከታይ የነበሩት ክርስቲያን ዐቃቤ እምነት ዶ/ር ነቢል ቁሬሺ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

የሥነ ሕይወት አጥኚ ይህንን ጥቅስ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አያገኘውም፡፡ ቡካይሌ እንኳ ትንተናውን ሲጀምር ይህንን ሃቅ በመረዳት እንዲህ በማለት ይናዘዛል፡- “ይህ ዘርፉን በሚያጠኑት ሊቃውንት ዘንድ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፡፡”[4] ነገር ግን ችግሩ ቁርኣን በሰባተኛው ክፍለዘመን ለመጠቀም የተገደደው ቃል መሆኑንና “ዩተረስ” የሚለውን የዘመናዊ ሳይንስ ቃል “በተጠበቀ መርጊያ” በሚለው ቦታ ብንተካ ችግሩ እንደሚወገድ ተናግሯል፡፡[5] ቁርኣንን አመቺ በሆነ መንገድ ሁሉ እየተረጎመ እንዳደገ ሙስሊም የቡካይሌን ሐሳብ እጋራለሁ፡፡ እንደ ኅክምና ተማሪ ግን ቃላትን የፈለገ ያህል ብንተካ የዚህ ጥቅስ አንዱ ችግር ፈፅሞ ሊቀረፍ እንደማይችል ተገንዝቤያለሁ፡፡ ጥቅሱ የሽልን የዕድገት ቅደም ተከተል የሚናገር ቢሆንም ቅደም ተከተሉ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ሽል መጀመርያ አጥንት ሆኖ ከዚያ በሥጋ አይሸፈንም፡:፡ ሜሶደርም የተሰኘው የሽል ክፍል ነው በአንድ ጊዜ ሥጋም አጥንትም ወደመሆን የሚያድገው፡፡

ለዚህ የተሰጡትን ምላሾች መርመሬያለሁ፡፡ ብዙዎቹ ደካማ የሆነ ተቃውሞ መሆኑን ቢናገሩም ሙስሊም እያለሁ እንኳ ምላሹን አልተቀበልኩትም ነበር፡፡ ቡካይሌ በጥቅሱ ውስጥ የሚገኙት ቅደም ተከተሎች ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ ትክክል መሆናቸውን ለማስረዳት ቢሞክርም ቅደም ተከተሉ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ይህ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ቡካይሌ ጥቅሱን በስፋት ለመተንተን ቢሞክርም ነገር ግን ችግሩን አለባብሶ አልፎታል፡፡

ግልፅ በሆነው የጥቅሱ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን ስህተት መረዳት ቀላል ነው፤ ነገር ግን ይህ ብቸኛው ችግር አይደለም፡፡ የጥቅሱ የመጀመርያው ክፍል የአረብኛውን የተሳሳተ ቃል በሳይንሳዊ ቃል እንድንተካ ያስገድደናል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያውን ችግር ብቻ በመፍታት ሁለተኛውን በቸልታ የምናልፈው ከሆነ ሳይንሳዊ ተዓምር ሊባል የሚችል ምን ነገር ይኖራል? ይህ ጥቅስ ቁርኣን ግልጠተ መለኮት መሆኑን እንደማያስረዳ ተገንዝቤያለሁ፡፡[6]

የተጠቀሱት ሁለቱም ጥቅሶች ቁርኣን ከሳይንስ ጋር የተስማማ መጽሐፍ መሆኑን ከማረጋገጥ ይልቅ ተቃራኒውን እንደሚያረጋግጡ ተመልክተናል፡፡ አቶ ሐሰን ጥቅሶቹን ካቀረቡ በኋላ በአሸናፊነት ስሜት እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፡-

እነዚህንና ሌሎችን ሳይንሳዊ እውነታዎች ለነቢዩ ሙሐመድ ማን አስተማራቸው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀዷቸውን? በፍጹም፡፡ ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ እንደ እሳትና ጭድ የማይስማሙ ተጻራሪ ነገሮች ናቸው፡፡ ከአይሁድ አዋልድ መጽሐፍት? ይህም ሊሆን እንደማይችል ሐመሮች ያውቁታል …. ታድያ ሙሐመድ እነዚህን ድንቅ ሳይንሳዊ እውነታዎች ከየት አገኟቸው? ሐመሮች ከጠቀሷቸው ምድራዊ ምንጮች በላይ ከሆነ ሌላ ምንጭ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ (ገፅ 120)

[ቁርኣን ከሳይንስ ጋር “የተስማማ” ሆኖ ሳለ የእስልምናው ዓለም ምንም የረባ ሳይንሳዊ ግኝት ለዓለም አለማበርከቱና አንፀባራቂ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታዮች በሆኑት በክርስቲያኖችና በአይሁድ የተበረከቱ መሆናቸው አስገራሚ ነው፡፡]

የቁርኣን ደራሲ ስለ ሽል ዕድገት የሚያወራውን ኢ-ሳይንሳዊ ሐተታ ከላይ ከተጠቀሱት ከየትኞቹም ምንጮች አላገኘም፡፡ ከሰማይም አልወረደለትም፡፡ ጉዳዩን በጥልቀት ያጠኑት ወገኖች የዚህ ሐተታ ምንጭ ጋለን የተሰኘ ግሪካዊ የሕክምና ሊቅ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ ሰው ቱርክ ውስጥ በምትገኝ የጴርጋሞን (የዛሬዋ ቤርጋማ) ከተማ በ131 ዓ.ም. የተወለደ ሲሆን ፅንስን በተመለከተ የሰጣቸው ትንታኔዎች ለክፍለ ዘመናት አረብያን ጨምሮ በብዙ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው፡፡ ቁርኣን የጠቀሳቸው የሽል ዕድገት ደረጃዎች ያለምንም መዛነፍ በጋለን ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡[7]

  1. ኢ-ሳይንሳዊ “መገለጦች”

አቶ ሐሰን በቁርኣን ውስጥ ይገኛሉ ተብለው በተደጋጋሚ ለሚነሱት ኢ-ሳይንሳዊ አናቅፅ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ በማስከተል መልሶቻቸውን አንድ በአንድ እንፈትሻለን፡፡

  • ጸሐይ በጥቁር ጭቃ ምንጭ ውስጥ?

ቁርኣን ጸሐይ የምትጠልቅበትን ቦታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-

“ወደ ፀሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት፡፡ ባጠገቧም ሕዝቦችን አገኘ፡፡ «ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም (በመግደል) ትቀጣለህ ወይም በእነርሱ መልካም ነገርን (መማረክን) ትሠራለህ» አልነው፡፡” (ሱራ 18፡86)

አቶ ሐሰን ለዚህ ያፈጠጠ ያገጠጠ የቁርኣን ስህተት እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣሉ፡-

ነገሩ እንደዚህ አይደለም፡፡ አንቀጹ ከሳይንስ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለውም፡፡ እንዲያውም የቁርኣንን የገለጻ ምጥቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህውም ዙልቀርነይን የተባለው ሰው ባደረገው ረዥም ጉዞ ከአንድ ውቂያኖስ ወይም ባሕር አጠገብ ደረሰ ወቅቱ የጸሐይ መጥለቂያ ወቅት ነበር፡፡ ጸሐይ ከውቂያኖሱ ባሻገር ስትጠልቅ ተመለከታት፡፡ ለእርሱ እይታ ከውሃው ውስጥ የጠለቀች ይመስል ነበር፡፡ ይህ ዘወትር የምናየው ትእይንት ነው፡፡ ከፊት ለፊታችን ተራራ ካለ ጸሐይዋ ልክ ከተራራው ጀርባ የጠለቀች ይመስለናል፡፡ ባሕር ካለ ወደ ባህሩ ስትጠልቅ እናያለን፡፡ ዙልቀርነይን ያየውን ክስተት ቁርኣን ምስል ሰርቶ ውብ በሆነ ቋንቋ አስቀመጠው እንጅ የጸሐይ መጥለቂያ ምንጭ ወይም ባሕር ነው የሚል ቃል አልወጣውም፡፡ (ገፅ 179)

አቶ ሐሰን የሰጡት ትንታኔ አሳማኝ አይደለም፡፡ ይህንን ትርጉም ለማግኘት “ምንጭ” የሚለውን ወደ ውቂያኖስ ቀይረውታል፤ “አገኛት” የሚለውንም “ተመለከታት” በሚል ቃል ተክተዋል፡፡ ጥቅሱ ዙልቀርነይን የተባለው ሰው ወደ ፀሐይ መግቢያ እንደደረሰ እንጂ ሲሄድ ሳለ እንደመሸበት አይናገርም፡፡ ክስተቱ ሲፈፀም በቦታው እንደተገኘ ነው የሚናገረው፡፡ ይህ ጉዳይ በተከታዩ ጥቅስ ተጠናክሯል፡-

“ከዚያም መንገድን (ወደ ምሥራቅ) ቀጠለ፡፡ ወደ ፀሐይ መውጫ በደረሰም ጊዜ ለእነሱ ከበታችዋ መከለያን ባላደረግንላቸው ሕዝቦች ላይ ስትወጣ አገኛት፡፡” (ሱራ 18፡88-89)

ሰውየው ፀሐይ የምትጠልቅበትን ቦታ ከጎበኘ በኋላ በቀጥታ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በመሄድ ስትወጣ አገኛት፡፡ ከበታቿም ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህንንስ እንዴት ይተረጉሙት ይሆን?

“አገኛት” የሚለው ቃል በአረብኛ “ወጀደሃ” ሲሆን በቁርኣን ውስጥ በተለያየ መልክ 107 ጊዜ ተጠቅሷል፤ ነገር ግን “ማየት” ወይም “አየ” የሚል ትርጉም የለውም፡፡ ፀሐይ ስትወጣና ስትገባ ስለማየት መናገር ከፈለግን “ረዐ” የሚለውን ቃል ነው የምንጠቀመው፡፡ ለምሳሌ ሱራ 6፡78 እንዲህ ይላል፡-

“ፀሐይንም ጮራዋን ዘርግታ ባየ (ረዐ) ጊዜ፡- «ይህ ጌታዬ ነው፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ነው» አለ፡፡”

የዘመናችን ሙስሊሞች ይህንን ያፈጠጠ ያገጠጠ ሳይንሳዊ ስህተት አለባብሶ ለማለፍና መጽሐፋቸውን ከስህተቱ ለማዳን ጥረት ቢያደርጉም የቀደሙት እስላማዊ ምንጮች የእነርሱን ትርጓሜ ውድቅ በማድረግ ስህተቱን ያፀናሉ፡፡ አል-ዘመቅሻሪ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ሙሐመድ ይህንን ጥቅስ የተረጎሙበትን መንገድ እንዲህ ይነግሩናል፡-

“አቡ ዘር (ከሙሐመድ ወዳጆች መካከል አንዱ) በፀሐይ መግቢያ ሰዓት ከነቢዩ ሙሐመድ ጋር በመስጊድ ውስጥ ነበር፡፡

ነቢዩ ሙሐመድ እንዲህ ብለው ጠየቁት፡- “አቡ ዘር ሆይ የት እንደምትጠልቅ ታውቃለህን? እርሱም ‹አላህና መልእክተኛው የበለጠ ያውቃሉ› በማለት መለሰ፡፡ ነቢዩም ‹በድፍርስ ውሃ ውስጥ ነው› አሉ፡፡”[8]

አል-በይደዊ የተሰኙ ሌላ ሊቅ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡-

“ፀሐይ የምትጠልቀው በድፍርስ ምንጭ ውስጥ፣ ማለትም ጭቃ ያለበት ምንጭ ውስጥ ነው፡፡ አንዳንድ የቁርኣን አንባቢዎች ‹… ሞቃት ውሃ› በማለት ያነቡታል፡፡ ይህ ማለት ውሃው ሁለቱም ባሕርያት አሉት ማለት ነው፡፡ ኢብን አባስ ሙአዊያ ‹ሞቃት› ብሎ ሲያነብ እንዳገኘው ይነገራል፡፡ እርሱም ‹ጭቃማ ነው› ብሎ ነገረው፡፡ ሙአዊያም ወደ ካዕብ አል-አሕባር ‹ፀሐይ የት ነው የምትጠልቀው› የሚል ጥያቄ ላከ፡፡ ጥቂት ሰዎች በሚገኙበት ውሃና ጭቃ ውስጥ ነው በማለት መለሰ፡፡ ስለዚህ እርሱም ከኢብን አል-አባስ ሐሳብ ጋር ተስማማ፡፡”[9]

አቶ ሐሰንና በማስረጃነት የጠቀሷቸው ዘመንኛ ሙስሊም መምህራን ከሙሐመድና ከጥንታውያኑ ሙስሊም ሊቃውንት በላይ ያውቁ እንደሆን ይንገሩን፡፡

  • ጋራዎች ምድር እንዳታረገርግ ይጠብቃሉ?

ቁርኣን ጋራዎች የተፈጠሩበትን ምክንያት ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-

“ሰማያትን ያለምታዩዋት አዕማድ (ምሰሶዎች) ፈጠረ፡፡ በምድርም ውስጥ በእናንተ እንዳታረገርግ ተራራዎችን ጣለ፡፡ በእርሷም ላይ ከተንቀሳቃሽ ሁሉ በተነ…” (ሱራ 31፡10)

“በምድርም ውስጥ በእናንተ እንዳታረገርግ ተራራዎችን ጣለባት፡፡ ጂረቶችንም፣ መንገዶችንም ትመሩ ዘንድ (አደረገ)፡፡” (ሱራ 16፡15)

“በምድርም ውስጥ በእነሱ እንዳታረገርግ ጋራዎችን አደረግን፡፡ ይመሩም ዘንድ በእርሷ ውስጥ ሰፋፊ መንገዶችን አደረግን፡፡” (ሱራ 21፡31)

አቶ ሐሰን ማብራርያ ሲሰጡ እንዲህ ይላሉ፡-

… ምድር ብዙ እንቅስቃሴዎችን እንደምታደርግ በሳይንስ ይታወቃል፡፡ በዛብያዋ አማካይነት በሰአት 1000 ማይሎችን እንደ እንዝርት ትሾራለች፡፡ በምህዋሯ አማካይነት ደግሞ በጸሐይ ዙርያ በሰአት 65000 ማይሎችን ትሽከረከራለች፡፡ እርሷና ሌሎች የከዋክብት ስብስቦችም በሰአት 20000 ማይሎችን ወደ መዳረሻቸው ይቀዝፋሉ፡፡ ምድር ይህን ሁሉ እንቅስቃሴ እያደረገች ግን አታረገርግም፡፡ ለሰው ልጅ ሕይወት ምቹ ናት፡፡ ይህ እንዲሆን ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች መካከል የጋራዎች መኖር አንድ ምክንያት እንደሆነ አንቀጹ ያስረዳል፡፡ ይህ ነገር ሳይንሳዊ ነው፡፡ የዘመኑ የሳይንስ ሊቃውንት አረጋግጠውታል፡፡ ለአብነት የዶክተር ሞሪሳ ቡካይን <<The Bible the Quran and the science>> የተሰኘ መጽሐፍ ማንበብ ይቻላል፡፡ ታዋቂው የስነ ፈለክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዘጉል ነጃር ይህንኑ አጀንዳ የሚመለከት ጥናት አዛጅተዋል፡፡ (ገፅ 182)

ጸሐፊው በዘርፉ ሊቃውንት የተጻፈ ምንም ዓይነት የተጨበጠ ማስረጃ እንዳልሰጡ ልብ በሉ፡፡ ማውሪስ ቡካይሌ በመጽሐፉ ውስጥ እነዚህን ጥቅሶች በመጥቀስ ሳይንሳዊ ለማስመሰል ቢሞክርም የሕክምና ባለሙያ እንጂ የስነፈለክ ተመራማሪ ባለመሆኑ ከራሱ ግምት በመነሳት የሰጠው ሐተታ ኡስታዝ ሐሰን ታጁ ከሰጡት የበለጠ ዋጋ ያለው አይደለም፡፡

ዘጎሎል ኧል-ነጋር ኡስታዝ እንዳሉት የሥነ-ፈለክ ተመራማሪ ሳይሆኑ ጂኦሎጂስት ናቸው፡፡[10] በዚህ ጉዳይ ላይ ትንታኔዎችን የመስጠት አቅም ሊኖራቸው ቢችልም ከምሑርነት ወደ ሙስሊም ዐቃቤ እምነት ያደሉ በመሆናቸው ሚዛኑን የጠበቀ ሐቀኛ መረጃ ከእሳቸው አንጠብቅም፡፡ ለምሳሌ ያህል እኚህ ሰው በአንድ ወቅት የግመል ሽንት መጠጣት “ለጤና ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ” ለማስረዳት ሲሞክሩ በግብፅ ቴሌዢዥን ታይተዋል፡፡[11] ይህንን ያደረጉት ነቢዩ ሙሐመድ የሰጡትን ትዕዛዝ ሳይንሳዊ ለማስመሰል ነበር፡፡[12]

እኔ የመጀመርያ ዲግሪዬን በጂኦግራፊ ነው የሠራሁት፡፡ ብዙ የጂኦግራፊ መጻሕፍትን አንብቤያለሁ፤ ከተራሮች ጋር የተያያዙ ብዙ መረጃዎች አሉኝ፡፡ ነገር ግን ተራሮች በምድር ውስጥ በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ምክንያት መፈጠራቸውን እንጂ እንቅስቃሴ እንዳይኖራት መከልከላቸውን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መረጃ አላየሁም፡፡ አቶ ሐሰን ከላይ ላቀረቡት “ሳይንሳዊ” ድምዳሜ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ፡፡ ይህንን ድምዳሜ ያገኙት ከየትኛው የሳይንስ መማርያ መጽሐፍ ወይም ጆርናል ነው? የመጽሐፉን ስም፣ ገጹንና የታተመበትን ዓመተ ምህረት እንዲጠቅሱልን እንፈልጋለን፡፡ የሁለት ግለሰቦችን ስም ጠቅሶ ማለፍ በምንም መስፈርት ይህንን ለመሰለ ግዙፍ አባባል ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡  በዚህ አጋጣሚ ከሙስሊም ወገኖች ጋር መሰል ውይይቶችን የምታደርጉ ክርስቲያን ወገኖች ሙስሊም ሰባኪያን ብዙ ጊዜ ማስረጃ የሌላቸውን መሰል አባባሎች ስለሚጠቀሙ ተጨባጭ ማስረጃ እንዲሰጧችሁ አጥብቃችሁ እንድትጠይቁ እንመክራችኋለን፡፡

አቶ ሐሰን ከተናገሩት በተጻራሪ እነዚህ ጥቅሶች ተራሮች ከላይ ወደ ታች የተጣሉ ለብቻቸው የተፈጠሩ አካላት በማስመሰል መናገራቸው ተራሮች በከርሰ ምድር እንቅስቃሴዎች ምክንያት ከምድር ውስጥ የወጡ የመሆናቸውን ሳይንሳዊ እውነታ ስለሚጣረስ ትክክል አይደለም፡፡

  • ከዋክብት የሰይጣን ማባረርያ ሚሳኤሎች?

ቁርኣን ከዋክብት የተፈጠሩበትን ምክንያት ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-

“ቅርቢቱን ሰማይም በእርግጥ በመብራቶች (በከዋክብት) አጌጥናት፡፡ ለሰይጣናትም መቀጥቀጫዎች አደረግናት፡፡ ለእነርሱም (ለሰይጣኖች) የእሳትን ቅጣት አዘጋጀን፡፡” And We have (from of old), adorned the lowest heaven with lamps, and we have made such (Lamps as) missiles to drive away Satans, … (Y. Ali) (ሱራ 67፡5)

“እኛ ቅርቢቱን ሰማይ በከዋክብት ጌጥ አጌጥናት፡፡ አመጸኛም ከሆነ ሰይጣን ሁሉ መጠበቅን ጠበቅናት፡፡ ወደላይኛው ሰራዊት አያዳምጡም፡፡ ከየወገኑም ሁሉ ችቦ ይጣልባቸዋል፡፡ የሚባረሩ ሲሆኑ (ይጣልባቸዋል)፡፡ ለእነሱም ዘውታሪ ቅጣት አላቸው፡፡ ንጥቂያን የነጠቀ ወዲያውም አብሪ ኮከብ የተከተለው ሲቀር፤ (እርሱ ይሰማዋል)፡፡” (ሱራ 37፡6-8)

“በሰማይም ላይ ቡርጆችን በእርግጥ አድርገናል፡፡ ለተመልካቾችም (በከዋክብት) አጊጠናታል፡፡ ከተባረረ ሰይጣንም ሁሉ ጠብቀናታል፡፡ ግን (ወሬ) መስማትን የሚሰርቅ ወዲየውኑ አብሪ ችቦ ይከተለዋል፡፡ (ያቃጥለዋል)፡፡” (ሱራ 15፡16-18)

አቶ ሐሰን እነዚህን ጥቅሶች ሲተረጉሙ እንዲህ ብለዋል፡-

የሰይጣናት መምቻዎች ናቸው ማለት እነዚህ ግዙፍ አካላት ከወዲያ ወዲህ እየተወነጨፉ በዩኒቨርስ ውስጥ ትርምስ ይፈጥራሉ ማለት አይደለም … ሰማያትን ከሰይጣናት እንዲጠብቁ የታዘዙት መላእክት ከከዋክብት ላይ በሚቀጣጠሉ ችቦዎች (እሳት) አማካይነት ሰይጣናትን ወደ ላይ እንዳይዘልቁ ያሳድዳሉ ማለት ነው፡፡ ወደ ሰይጣናት የሚወረወሩት ግዙፉ ከዋክብቶች ሳይሆኑ ከነርሱ የሚቀጣጠሉ ችቦዎች ናቸው፡፡ ችቦዎችን የሚወረውሩትም የመጀመርያውን ሰማይ የሚጠብቁ መላእክት ናቸው፡፡ (ገፅ 183)

አቶ ሐሰን ከጻፉት በተጻራሪ አቡ ቀታዳ የተሰኘ ጥንታዊ የሐዲስ ዘጋቢ እንዲህ ማለቱ ተነግሯል፡-

“የከዋክብት መፈጠር ለሦስት ዓላማ ነው፤ (ቅርቢቱን) ሰማይ ለማስጌጥ፣ እየተወረወሩ ሰይጣናትን እንዲመቱና ተጓዦችን እንዲመሩ…”[13]

የአቶ ሐሰን ትርጓሜ ከዚህ ጥንታዊ ሙስሊም የተለየ ቢሆንም ዋናው ችግር እርሱ አይደለም፡፡ ዋናቸው ችግር ከዋክብትም ሆኑ ከእነርሱ “የሚቀጣጠሉት ችቦዎች” ቁስ መሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ሰይጣንና አጋንንቱ መናፍስት እንጂ ቁስ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ቁስ አካል እንዴት መናፍስትን ሊመታ ይችላል? የሚል ነው፡፡

  • ፀሐይ ትጓዛለች?

ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“ፀሐይም ለእርሷ ወደ ሆነው መርጊያ ትሮጣለች፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው፡፡” (ሱራ 36፡38)

ሐሰን ታጁ ይህንን ጥቅስ በሚከተለው መንገድ ይፈቱታል፡-

በእርግጥ ይህ እጅግ አስደናቂ ከሆኑት የቁርኣን ሳይንሳዊ ተአምራት መካከል አንዱ ነው፡፡ የጥንት ሰዎች ጸሐይ ትንቀሳቀሳለች ምድር ግን ባለችበት የቆመች ናት የሚል እምነት ነበራቸው… ግና የሰው ልጅ ከምእተ ዓመታት ምርምር በኋላ ምድር እንደምትንቀሳቀስ ደረሰበት፡፡ ጸሐይ ግን ባለችበት የቆመች ነገር እንደሆነች አድርጎ ገመተ፡፡ ይህ መላ ምት ግን በዚያው አልቆመም፡፡ የሰው ልጅ ምርምር ቀጠለና ቁርኣን ከ1400 ዓመታት በፊት የገለጸውን እውነታ ደረሰበት፡፡ ይህም እውነታ ጸሐይ የምትንቀሳቀስ መሆኗ ነው፡፡ ለዚያውም በሰአት 20000 ማይሎች በሚሆን ፍጥነት፡፡

በርሷ ዙሪያ ያሉ ከዋክብት እና ምድርም አብረዋት በሕዋው ውስጥ ይቀዝፋሉ፡፡ ወደ የት ትጓዛለች? ቁርኣን ወደ ምርጊያዋ እንደምትቀዝፍ ይነግረናል፡፡ ስለዚህም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እዚያ ደርሳ ልትቆም ትችላለች፡፡ ያኔ ምን አልባትም የዓለማችን ፍጻሜ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ጊዜ የሚያውቀው አላህ ብቻ ነው፡፡ (ገፅ 185-186)

ጸሐይ በዙርያዋ የሚገኙትን ፕላኔቶች ይዛ በሚልኪዌይ ጋላክሲ ውስጥ እንደምትንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ቁርኣን እያለ ያለው እንቅስቃሴ ይህ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ ሌላ ነው፡፡ ቁርኣን በሌሎች ቦታዎች ላይ የፀሐይና የጨረቃን ምሕዋር በማነጻጸር ያቀርባል፡፡

“እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው፡፡ ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ፡፡” (ሱራ 21፡33)

“ፀሐይም ለእርሷ ወደ ሆነው መርጊያ ትሮጣለች፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው፡፡ ጨረቃንም የመስፈሪያዎች ባለቤት ሲኾን እንደ ዘንባባ አሮጌ ቀንዘል እስኪኾን ድረስ (መኼዱን) ለካነው፡፡ ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም፡፡ ሌሊትም ቀንን (ያለ ጊዜው) ቀዳሚ አይኾንም፡፡ ሁሉም በመዞሪያቸው ውስጥ ይዋኛሉ፡፡” (ሱራ 36፡40)

“በፀሐይና በብርሃኗ እምላለሁ፡፡ በጨረቃም በተከተላት ጊዜ፤ በቀኑም (ፀሐይን) በገለጻት ጊዜ…” (ሱራ 91፡1-3)

የፀሐይና የጨረቃ ምሕዋሮች በንጽጽር መቅረባቸው የቁርኣን ደራሲ የሁለቱም ምሕዋሮች ተመሳሳይ መሆናቸውን ማመኑን ያመለክታል፡፡ በተለይም ሱራ 36፡40 ላይ “ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም” ብሎ መናገሩ እነዚህ ሰማያዊ አካላት በተመሳሳይ ምሕዋር ተከታትለው መሄዳቸውን ማመኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ የቁርኣን ደራሲ የፀሐይን በሚልኪዌይ ጋላክሲ ውስጥ መንቀሳቀስ ተገንዝቦ ቢሆን ኖሮ፤ ይህ ዓይነቱ አነጋገር አቶ ሐሰን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በእግራቸው ቢንሸራሸሩና ጓደኛቸው ደግሞ በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ቢንሸራሸር ሊጋጩ አለመቻላቸውን በአግራሞት የመግለፅ ያህል የቂላቂልነት ንግግር ስለሚሆንበት በንፅፅር ባላቀረባቸው ነበር፡፡ ንግግሩ ትርጉም የሚሰጠው ፀሐይ እንደ ጨረቃ ሁሉ ምድርን እንደምትዞር ካመነ ብቻ ነው፡፡

ነቢዩ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው በዘመኑ እንደ ነበሩት ሌሎች አረቦች ሁሉ ፀሐይ በምድር ዙርያ እንደምትዞር ያምኑ እንደነበርና ከላይ ያሉትንም ጥቅሶች በዚያው ሁኔታ ይተረጉሙ እንደነበር ተከታዩ ሐዲስ ያስረዳናል፡-

አቡ ዘር እንደዘገበው፡- ነቢዩ በፀሐይ መግቢያ ሰዓት እንዲህ ብለው ጠየቁኝ፣ ‹ፀሐይ (ከጠለቀች በኋላ) የት እንደምትሄድ ታውቃለህን?› እኔም፣ ‹አላህና መልእክተኛው የበለጠ ያውቃሉ› ብዬ መለስኩ፡፡ እንዲህ አሉ፣ ‹በዙፋኑ ስር እስክትሰግድ ድረስ ትጓዛለች፣ ዳግመኛም እንድትወጣ ፍቃድ ትጠይቃለች፣ ይፈቀድላታልም፡፡ ስግደቷ ተቀባይነት የማያገኝበት ጊዜ ይመጣል፣ እንደገና ለመሄድ ፍቃድ ትጠይቃለች፣ ፍቃድም አይሰጣትም፡፡ ነገር ግን ወደ መጣችበት እንድትመለስ ትታዘዛለች ከዚያም በስተ ምዕራብ በኩል ትወጣለች፡፡ ይህ ደግሞ አላህ እንዲህ ብሎ የተናገረው ቃል ትርጉም ነው ‘ፀሐይም ለእርሷ ወደ ሆነው መርጊያ ትሮጣለች፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው፡፡’›[14]

ነቢዩ ሙሐመድ “የፀሐይ መርጊያ” የሚለውን የተረጎሙት ፀሐይ በየዕለቱ “የምትጠልቅበትን ቦታ” እንጂ በሚልኪዌይ ጋላክሲ ውስጥ የምታደርገውን ጉዞ አይደለም፡፡ በሚልኪዌይ ጋላክሲ ውስጥ የምታደርገው ጉዞ አቶ ሐሰን እንዳሉት ወደ አንድ ያልታወቀ ቦታ የሚደረግ ሳይሆን በሚልኪዌይ እምብርት ዙርያ የሚደረግ የሁለት ሚሊዮን ክፍለ ዘመናት ዙረት ነው፡፡[15] ይህም ልክ እንደ ፕላኔቶች ምሕዋር ሁሉ ማለቂያ የሌለው የሚደጋገም የክብ ቅርፅ እንጂ ቀጥ ያለ መስመር አይደለም፡፡ ስለዚህ የሰጡት ትንታኔ ከቁርኣን አውድ አንፃር፣ ሙሐመድ ለጥቅሱ ከሰጡት ፍቺ አንፃርም ሆነ ከሳይንስ አንፃር ውድቅ ነው፡፡ ቁርኣን እየተናገረ ያለው ስለ ፀሐይ በመሬት ዙርያ መዞር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል አለመሆኑ በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡

  • ምድር ዝርግ ናት?

የምድርን ቅርፅ በተመለከተ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“(እርሱ) ያ ለናንተ ምድርን ምንጣፍ ሰማይንም ጣራ ያደረገ ነው፤ ከሰማይም (ከደመና) ውሃን ያወረደ በርሱም ከፍሬዎች ለናንተ ሲሳይን ያወጣ ነው፡፡” (ሱራ 2፡22)

“እርሱም ያ ምድርን የዘረጋ በሷም ተራራዎችንና ወንዞችን ያደረገ በውስጧም ከፍሬዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ዓይነቶችን ያደረገ ነው፡፡ ሌሊትን በቀን ይሸፍናል፡፡” (ሱራ 13፡3)

ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በውስጧም ኮረብታዎችን ጣልናባት፡፡ በውስጧም (የተለካን) በቃይ ሁሉ አበቀልንባት፡፡” (ሱራ 15፡19)

“(እርሱ) ያ ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ ያደረገላችሁ፣ በእርሷም ውስጥ ለእናንተ መንገድን ያገራላችሁ” (ሱራ 20፡53)

ወደ ምድርም እንዴ እንደተዘረጋች (አይመለከቱምን?)” (ሱራ 88፡20)

እነዚህ ጥቅሶች ምድር ዝርግ መሆኗን በማያሻማ ቃል ይናገራሉ፡፡ አቶ ሐሰን ለዚህ ጥያቄ እንዲህ በማለት መልስ ሰጥተዋል፡-

በዚህ አንቀጽ ምድር ዝርግ (ጠፍጣፋ) መባሏ ከሳይንስ እውነታ ጋር ይጋጫልን? በእርግጥ አይጋጭም፡፡ ቁርኣን ሁለቱንም አገላለጽ ተጠቅሟል፡፡ (ገፅ 186)

ምድር ክብና እንቁላል ቅርጽ መሆኗን በተከታዩ አንቀጽ ይገልጻል፡-

وَالْأَرْضَ بَعْدَ ذَٰلِكَ دَحَاهَا

“ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት፡፡” (አል ናዚአት፣ 30)

‹‹ደሃ›› የሚለው የአረብኛ ቃል ሙሉ ክብ ያልሆነ፣ በአንድ ወገኑ የረዘመ (ልክ እንቁላል ቅርጽ) ክብ ማለት ነው፡፡ በአማርኛው የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ‹ዘረጋ› ተብሎ መተርጎሙ የቃሉን መንታ መልእክት መያዝ ያመለክታል፡፡

በእርግጥም እውነተኛው የመሬት ቅርጽም እንቁላል መሳይ ነው፡፡ ይህ ግን ሳይንስን ለተረዱ ሰዎች የሚገባ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ግን በአይኑ ሲያያት ዝርግ ትመስላለች፡፡ ቁርኣን ይህንንም አልዘነጋም፡፡ የሚያናግረው የሳይንስ ምሁራንን ወይም የ20ኛው ክፍለ ዘማን ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዘመንና ቦታ የሚኖሩ የሰው ልጆችን ነው፡፡ እናም ‹‹ምድርን በመዘርጋት ለኑሮ እንድትመች እንዳደረግና አስተውሉ›› አለ፡፡ ማንም ሰው ሊገባው በሚችል ቋንቋ፡፡ እግረ መንገዱን ግን ክብነቷን በመናገር ሳይንሳዊ ተአምር ቋጠረ፡፡ ተከታዩን አንቀጽ እንመልከት፡-

يُكَوِّرُ اللَّيْلَ عَلَى النَّهَارِ وَيُكَوِّرُ النَّهَارَ عَلَى اللَّيْلِ وَسَخَّرَ الشَّمْسَ وَالْقَمَرَ

“ሌሊትን በቀን ላይ ይጠቀልላል፡፡ ቀንንም በሌሊት ላይ ይጠቀልላል፡፡” (አል ዙመር 5)

‹መጠቅለል› (ተክዊር) የሚለው ቃል ክብ ለሆነ ነገር እንጅ ለዝርግ ነገር አይደለም፡፡ ይህም አንቀጽ የመሬትን ክብነት ይገልጻል፡፡ (ገፅ 186-187)

እስቲ ይህንን ሐተታ ጠጋ ብለን እንመልከት፡፡ እውን ኡስታዙ እንዳሉት ቁርኣን የመሬትን ክብ መሆን ይናገር ይሆን?

የምድር ቅርፅ ከዕንቁላል ይልቅ ወደ ኳስ ቅርፅ የቀረበ መሆኑን ማንኛውም የጂኦግራፊ ተማሪ ያውቃል፡፡ የምድር ቅርፅ እንደ ዕንቁላል ሞላላ አይደለም፡፡ ሁለቱ ዋልታዎች የጠፍጣፋነት መልክ ሲኖራቸው በስፋት ረገድ ከምድር ወገብ ጋር ያላቸው ልዩነት በጣም ኢምንት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ትርጓሜ ከሳይንስ አንጻር ስንመዝነው ተቀባይነት የለውም፡፡

‹ደሃሃ› የሚለው የአረብኛ ቃል ትርጉም፡

ሱራ 79፡30

وَالْأَرْضَ بَعْدَ ذَٰلِكَ دَحَاهَا ‹‹ወል ዐርደ በዐዳ ዛሊከ ደሃሃ››

በአማርኛ ቁርኣን “ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ብዙ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችም ምድር ዝርግ መሆኗን በሚያመለክት ሁኔታ ተርጉመውታል፡፡ ለምሳሌ፡-

  • And after that He spread the earth. (Sahih International)
  • And the earth, moreover, hath He extended (to a wide expanse); (Yusuf Ali)
  • And afterwards stretched forth the earth, (J M Rodwell)
  • And after that He spread the earth, (Pickthall)
  • And the earth – after that He spread it out, (Arberry)
  • And the earth, He expanded it after that. (Shakir)

አንዳንድ ሙስሊሞች ‹ደሃ› የሚለው ቃል ‹ዕንቁላል› የሚል ትርጉም ካለው ‹ዱሂያ› ከሚለው ቃል ጋር ስለሚመሳሰል ‹የዕንቁላል ቅርፅ› ተብሎ መተርጎም እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ትክክለኛው ትርጉም ‹መዘርጋት› የሚል ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ሙስሊም ሊቃውንት ቃሉን በዚሁ መንገድ ሲተረጉሙት ኖረዋል፡፡ የቃሉ ትክክለኛ ትርጉም አቶ ሐሰን እንዳሉት ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሙስሊም ሊቃውንት ሳይንሳዊ የሆነውን የቃሉን ትክክለኛ ትርጉም በመተው ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ስለምን ይተረጉሙት ነበር?

ጀለላይን የተሰኙ ሁለት ሙስሊም ሊቃውንት ይህንን ጥቅስ ሲያብራሩት እንዲህ ብለዋል፡-

“ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት” ማለት ዝርግ አደረጋት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የተፈጠረችው ከሰማይ በፊት ነበር፣ ነገር ግን አልተዘረጋችም ነበር፡፡[16]

የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ምድር ዝርግ ሆና ‹ኑን› በተባለ ዓሣ ነባሪ ጀርባ ላይ እንደተቀመጠች ያምኑ ነበር፡፡ ይህንን በተመለከተ ኢብን ከሢር የተሰኘ ሙስሊም ሊቅ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

…ኢብን አባስ እንዳስተላለፈው […] ከዚያም አላህ ‹ኑን› የተባለውን ከፈጠረ በኋላ ሰማይ የተፈጠረበት ጭስ እንዲወጣ አደረገ፡፡ ከዚያም ምድር በኑን ጀርባ ላይ ተዘረጋች፡፡ ከዚያም ኑን ስለደነበረ ምድር ማረግረግ ጀመረች፤ ነገር ግን (አላህ) ምድርን እንዳትንቀሳቀስ አድርጎ በተራሮች ቸከላት…

ኢብን አቡ ኑጃኢህ እንደተናገረው ኢብን አቡ በኪር በሙጃሂድ እንዲህ ተብሎ ተነግሮት ነበር፣ “ኑን ከሰባቱ መሬቶች በታች የሚገኝ ታላቁ አሣ እንደሆነ ይነገራል፡፡” በተጨማሪም አል ባግሃዊ (አላህ ነፍሱን ያሳርፋትና) እንዲሁም ሌሎች ሐታቾች እንደተናገሩት በዚህ ዓሣ ጀርባ ላይ ውፍረቱ ከሰማይና ከምድር የሚበልጥ ትልቅ ዓለት አለ፡፡ ከዚህ ዓለት በላይ ደግሞ አርባ ሺህ ቀንዶች ያሉት ኮርማ ቆሟል፡፡ በዚህ ኮርማ ላይ ሰባቱ መሬቶችና በውስጣቸው የሚገኙት ሁሉ ተቀምጠዋል፡፡[17]

ከነዚህ ሊቃውንት በተጨማሪ አል-ጠበሪና አል-ቁርጡቢን የመሳሰሉት ሌሎች ሙስሊም ሊቃውንት ተመሳሳይ ዘገባዎችን አስተላልፈዋል፡፡ በዘመናች የሚገኙ የቁርኣንን ሐሳብ በሚገባ የተገነዘቡ ሙስሊም ሊቃውንት ምድር ዝርግ መሆኗን በአፅንዖት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሳዑዲ አረብያ ዋና ሙስሊም ሊቅ ሼኽ አብደል-አዚዝ ኢብን ባዝ እንዲህ ማለታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡-

“ምድር ዝርግ ናት፡፡ ክብ መሆኗን የሚናገር ማንኛውም ሰው ቅጣት የሚገባው አምላክ-የለሽ ነው፡፡”[18]

ከላይ የሰጠናቸው ማስረጃዎች እንዳሉ ሆነው ቁርኣን ምድር ክብ መሆኗን በመናገር ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ተስማምቶ ቢገኝ እንኳ ተዓምራዊ ሊሆን የማይችልበት አንድ ትልቅ ምክንያት አለ፡፡ እርሱም ምድር ዝርግ አለመሆኗና ክብ መሆኗ ሙሐመድ ከመወለዳቸው ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የታወቀ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ፓይታጎረስ የተሰኘው ግሪካዊ የሒሳብ ሊቅ (ሕይወቱ ያለፈው 497 ዓ.ዓ. ነው) መሬት፣ ጨረቃና ሌሎች የሕዋ አካላት ክብ መሆናቸውን ያምን ነበር፡፡ ከርሱ ቀጥሎ በነበረው ክፍለ ዘመን የኖረው ፊሎላውስ የተሰኘ ሌላ ግሪካዊ ሊቅ ተመሳሳይ እምነት ነበረው፡፡ በተጨማሪም አርስጣጣሊስ (አርስቶትል) የተሰኘው ዝነኛ ግሪካዊ ፈላስፋ (384-322 ዓ.ዓ.) ምድር ክብ መሆኗን በማስረጃዎች አስደግፎ አስተምሮ ነበር፡፡[19] ይህ እንግዲህ ሙሐመድ ከመወለዳቸው ቢያንስ ከ900 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ የሚቀድም የምድርን ክብ መሆን የሚናገር ሌላ ምንጭ አለ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው…” (በኢሳይያስ 40፡22)

“ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ…” (ምሳሌ 8፡27)

“ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል፡፡” (ኢዮብ 26፡7)

የተጠቀሱት ሦስቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግሪካውያኑ ፈላስፎች ከኖሩበት ዘመን የቀደሙ ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

ክርስቲያኖችና አይሁድ መጽሐፋቸው ከሳይንስ ጋር እንደማይጣረስ ቢያውቁም ነገር ግን ፍፁም ያልሆነው የሰው አእምሮ ያመነጫቸው ሳይንሳዊ እሳቤዎች ፍፁም በሆነው ቃለ እግዚአብሔር ላይ የበላይና ደረጃ መዳቢ እንዲሆን አይፈቅዱም፡፡ ሙስሊሞች ግን ሳይንስን የቁርአናቸው አረጋጋጭ አድርገው በማቅረብ ከፍ ያለ ሥልጣን አጎናፅፈውታል፡፡ ስለዚህ ሳይንስ የቁርኣንን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ከቻለ ውድቅ የማያደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡

ብዙ የዓለም ሃይማኖቶች ቅዱሳት መጻሕፍታቸው ከሳይንስ ጋር የተስማሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሙከራዎችን ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን የዘመናችን ሙስሊሞች ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ይህንን ዘርፍ ለሃይማኖታቸው ትክክለኛነት እንደ ዋና ማረጋገጫ አድርገው ይዘውታል፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ሳይንሳዊ ሐቆች በአንድ መጽሐፍ ውስጥ መገኘታቸው ከመቅፅበት መጽሐፉን መለኮታዊ ሊያደርጉ እንደማይችሉ ማወቅና መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ እንደርሱ ቢሆን ኖሮ ትላንት የማይታመኑ የነበሩትን ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳቦች በልበወለድ መልክ አቅርበው የነበሩና ዛሬ ግን ትንቢያዎቻቸው እውን ሆነው የምናያቸው መጻሕፍት መለኮታዊ በሆኑ ነበር፡፡

ሌላው መረሳት የሌለበት ነጥብ ሰይጣንና መላእክቱ ከሰው ልጆች በላይ ዕድሜን ያስቆጠሩና እኛ የማናያቸውን የተፈጥሮ ገፅታዎችና ሕግጋት ከኛ በላይ ማወቅ የመቻላቸው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ የተፈጥሮ እውነታዎችን ለአገልጋዮቻቸው ማቀበል የማይችሉበት ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም አንድ መጽሐፍ ሳይንሳዊ ሐቆችን በውስጡ መያዙ መለኮታዊ መጽሐፍ መሆኑን ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ አያረጋግጥም፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ቁርኣን መለኮታዊ መጽሐፍ መሆኑን ሊያሳዩ የሚችሉ የተሻሉ ማስረጃዎችን እንዲያመጡ እንጠይቃቸዋለን፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] http://www.j51.com/~alicamp/auth.htm#b

[2] http://en.wikipedia.org/wiki/Asexual_reproduction

[3] http://en.wikipedia.org/wiki/Cnemidophorus_neomexicanus

[4] Maurice Bucaille. The Bible, The Qur’an, and Science: The Holy Scriptures Examined in the Light of Modern Knowledge; p. 214

[5] Ibid., 215

[6] Nabil Qureshi. Seeking Allah Finding Jesus; p.

[7] 19.Corpus Medicorum Graecorum: Galeni de Semine (Galen: On Semen) (Greek text with English trans. Phillip de Lacy, Akademie Verlag, 1992) section I:9:1-10 pp. 92-95, 101

[8] Al-Zamakhshari. Al-Kash-shaf; 3rd Edition, Volume 2, p. 743, 1987

[9] Al-Baidawi. The Lights of Revelation; (p. 399).

[10] www.elnaggarzr.com/en/aboutus.php

[11] http://www.clarionproject.org/blog/sharia-medicine-debate-about-benefits-drinking-camel-urine https://www.youtube.com/watch?v=r5nv292dN4c

[12] Sahih Al-Bukhari; 7:71:623; 5:59:505; 1:4:234; 4:52:261; Sahih Muslim; 16:4131; 16:4130; 16:4132; 16:4134; Abu Dawud; 38:4356; 36:4357

[13] Dr. Muhammad Taq-i-ud-Din Al-Hillai & Dr. Muhammad Muhsin Khan. Interpretation of the Meaning of the Noble Quran;  pp. 214, 394-395

[14] Sahih al-Bukhari, Vol. 4, Number 421

[15] Dr. Henry Morris. Science and The Bible [Moody Press, Chicago 1986], p. 13

[16] Tafseer Ibn Katheer; Online Edition: http://altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=74&tSoraNo=79&tAyahNo=30&tDisplay=yes&UserProfile=0

[17] Tafseer Ibn Katheer; Online Edition: http://quran.al-islam.com/Tafseer/DispTafsser.asp?l=arb&taf=KATHEER&nType=1&nSora=68&nAya=1

[18] Yousef M. Ibrahim, “Muslim Edicts take on New Force”, The New York Times, February 12, 1995, p. A-14.

[19] George O. Abell. Exploration of the Universe, 4th edition, New York: Holt, Rinehart and Winston, pp. 16-18

ለሐሰን ታጁ ምላሽ ዋናው ማውጫ