ምዕራፍ አምስት የቁርኣን ግጭቶች “የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት” በሚል ርዕስ በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ

ምዕራፍ አምስት

የቁርኣን ግጭቶች

ክፍል 2 [ክፍል 1]

 

  1. ግጭት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር

በቁርኣን መሠረት ብሉይና አዲስ ኪዳናት ከፈጣሪ ዘንድ የመጡ መጻሕፍት ከመሆናቸውም በላይ በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ነበሩ፡፡ እስላማዊ ትውፊቶችም ይህንን እውነታ ያረጋግጣሉ፡፡ በሙሐመድ ዘመን የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዘመን በእጃችን ከሚገኘው ጋር ፍፁም አንድ መሆኑ ሊታበል የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ስለዚህ “መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል” የሚለው የዘመናችን ሙስሊሞች አባባል በእስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በታሪክ ድጋፍ የሌለው አሉባልታ ነው፡፡

ቁርኣን መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ቃለ እግዚአብሔር የመሆኑን ሃቅ ካረጋገጠ በኋላ መልሶ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረሱ ታሪኮችንና ትምህርቶችን በማቅረብ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰጠው ምስክርነት ጋር በመላተሙ ምክንያት ሙስሊም ወገኖች አስቸጋሪ ቅርቃር (Dillema) ውስጥ ገብተዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አለመበረዙን ከተቀበሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩት የቁርኣን ክፍሎች ስህተት መሆናቸውን ለማመን ሊገደዱ ነው፡፡ ተበርዟል የሚሉ ከሆነ ደግሞ እውነተኛነቱን ከሚመሰክሩትና የአላህ ቃል ሊለወጥ እንደማይችል ከሚናገሩት የቁርኣን ክፍሎች ጋር ይላተማሉ፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት የመረጡት መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት የሚናገሩትን የቁርኣን ክፍሎችና እስላማዊ ትውፊቶች ዓይተው እንዳላየ መሆን ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በመጻሕፍታቸው ውስጥ የሚገኙትን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛነት የተሰጡትን ምስክርነቶች በበቂ ሁኔታ ሳያብራሩና የተጠየቁትን ጥያቄ ሳይመልሱ መጽሐፍ ቅዱስ “ተበርዟል” የሚለውን ማስረጃ አልባ አቋማቸውን እውነት ለማስመሰል ሲጣጣሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አቶ ሐሰንም ይህንን አቋማቸውን “በማስረጃ” ለማረጋገጥ በቁርኣንና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል የሚገኙትን አንዳንድ ልዩነቶች በመጥቀስ የቁርአኑ “እውነት” የመጽሐፍ ቅዱሱ ደግሞ “ስህተት” መሆኑን ለማስረዳት ተጣጥረዋል፡፡ የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

  • የአብርሃም አባት ስም ማነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የአብርሃም አባት ስም ታራ ሲሆን (ዘፍ. 11፡31) በቁርኣን ደግሞ አዘር ተብሏል (የቤት እንስሳዎች ምዕራፍ 6፡74)፡፡ አቶ ሐሰን ቁርኣን “ትክክል” መሆኑንና መጽሐፍ ቅዱስ “መሳሳቱን” ለማስረዳት የተጠቀሙት አካሄድ “መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል” የሚለውን የተለመደ ውንጀላቸውን ማቅረብ ነው (ገፅ 163-165)፡፡ የዚህን ውንጀላ ሐሰትነት ቀደም ሲል ስላረጋገጥን ራሳችንን መድገም አያሻንም፡፡

አቶ ሐሰን የአብርሃምን አባት ስም በተመለከተ በሙስሊሞች መካከል ስምምነት አለመኖሩን የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ ስመጥር የሆኑት የሱኒ ሙስሊም ሊቃውንት አዘር የአብርሃም አባት እንደሆነ በቁርኣን መገለጹ የጎሣ አባት ስለሆነ እንጂ ወላጅ አባቱ በመሆኑ ምክንያት እንዳልሆነ የሚናገሩ ሲሆን  የአብርሃም ወላጅ አባት ስም ታራ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢብን ከሢርና አል-ጦበሪን መጥቀስ ይቻላል፡፡[1] የሺኣ ሙስሊሞች ደግሞ አዘር የአብርሃም አባት ወንድም  (የአብርሃም አጎት) ነው ይላሉ፡፡[2] ይህ ልዩነት የተፈጠረው በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ የአብርሃም አባት ስም ታራ መሆኑ በመገለጹ ምክንያት ነው፡፡

ምሑራን የቁርኣን ጸሐፊ “አዘር” የሚለውን ስም ከየት አመጣው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ጥረት አድርገዋል፡፡ ኢዮስቢዮስ የተሰኘ ክርስቲያን ጸሐፊ የአብርሃም አባት ስም “አሠር” እንደሚሰኝ በስህተት ጽፎ የነበረ ሲሆን የእርሱ ጽሑፍ በሙሐመድ ዘመን ከግሪክ ወደ ሢርያክ ተተርጉሞ ነበር፡፡ ሙሐመድ ወደ ሦርያ ለንግድ በሄዱበት ወቅት ይህንን የተሳሳተ አጠራር ከሦርያውያን ክርስቲያኖች በመስማት ወደ አረብኛ ዘዬ ቀይረውት “አዘር” የሚለውን አጠራር ሳይፈጥሩ እንዳልቀረ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡[3]

  • ማርያም የኢምራን ልጅና የአሮን እህት?

በቁርኣን የጌታ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም የኢምራን ልጅና የአሮን እህት መሆኗ የተገለጸ ሲሆን (3፡35-36፣ 60፡12፣ 66፡12፣ 19፡27-28)፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የአባቷ ስም ኤሊ መሆኑ ተገልጿል (ሉቃ 3፡23)፡፡[4]

በብሉይ ኪዳን መሠረት አሮን፣ ሙሴና ነቢይቱ ማርያም የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ የአባታቸው ስም እንበረም ይሰኛል (ዘኁ. 26፡59፣ 1ዜና 6፡3)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የነቢይቱ ማርያምን ቤተሰብና በቁርኣን ውስጥ ስለ ድንግል ማርያም ቤተሰብ የሚናገሩትን ጥቅሶች በማስተያየት ሙሐመድ ሁለቱን በዘመን የማይገናኙ ሰዎች እንዳምታቱ የሚናገሩ ምሑራን አሉ፡፡

ቁርኣን፡- “«የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፡፡ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም» አሏት፡፡” (የማርያም ምዕራፍ 19፡28)
መጽሐፍ ቅዱስ፡- “የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ፡፡” (ዘጸ. 15፡20)
ቁርኣን፡- የዒምራንን ልጅ መርየምንም ያችን ብልቷን የጠበቀችውን (ምሳሌ አደረገ)፡፡ በእርሱም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፍፋን፡፡ በጌታዋ ቃላትና በመጻሕፍቱም አረጋገጠች፡፡ ከታዛዦቹም ነበረች፡፡  (የማርያም ምዕራፍ 19፡28)
መጽሐፍ ቅዱስ፡- “የእንበረምም ልጆች አሮን፥ ሙሴ፥ ማርያም፡፡” (1ዜና 6፡3)
ቁርኣን፡- “የዒምራን ባለቤት (ሐና)[5] «ጌታዬ ሆይ! እኔ በሆዴ ውስጥ ያለውን (ፅንስ ከሥራ) ነጻ የተደረገ ሲኾን ለአንተ ተሳልኩ፡፡” (የኢምራን ቤተሰብ 3፡35)
መጽሐፍ ቅዱስ፡- “የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ፡፡ እርስዋ በግብፅ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት” (ዘኁ 26፡59)

ከላይ የተቀመጡት የሁለቱ መጻሕፍት ዘገባዎች ጎን ለጎን ሲነበቡ የቁርኣን ደራሲ የጌታን እናት ከአሮን እህት ከነቢይቱ ማርያም ጋር እንዳምታታ ለመደምደም እንገደዳለን፡፡ በሁለቱ ስብዕናዎች መካከል ያለው የዘመን ልዩነት ከ1300 ዓመታት በላይ በመሆኑ ይህ ጉዳይ በቁርኣን ተዓማኒነት ላይ ትልቅ ችግር ያስከትላል፡፡

አቶ ሐሰን ይህንን ችግር ለመፍታት ጥያቄውን ለሁለት ከፍለውታል፡፡ መጀመርያ መልስ ለመስጠት የሞከሩት የማርያም አባት ስም ማነው? ለሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ኤሊ መባሉ ስህተት መሆኑንና በቁርኣን ኢምራን መባሉ ትክክል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህ አባባላቸው ምንም ዓይነት አሳማኝ ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

በእርግጥ የተሳሳቱት ከእየሱስ ሞት ከዘመናት በኋላ ወንጌሎችን ያዘጋጁት የወንጌል ጸሐፊዎች ናቸው፡፡ ከጊዜ ብዛት እውነታዎችን በመዘንጋታቸውና የየሱስን ትምህርት በአፈታሪክ እንጅ የመልእክቱ ባለቤት ከሆነው ከእየሱስ በቀጥታ ባለመስማታቸው ከጊዜ ብዛት የተነሳ የስምና የቦታ ስህተት መፈጸማቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ቁርኣን በባህሪው ‹‹ፉርቃን›› (እውነትን ከሐሰት የሚለይ) ነውና ይህንን ስህተታቸውን በማረም የማርያምን አባት እውነተኛ ስም ይፋ አድርጓል፡፡ (ገፅ 165)

ለሙግታቸው መልስ ከመስጠታችን በፊት አንድ ትኩረታችንን የሳበ ነጥብ እግረ መንገዳችንን ጠቅሰን እንለፍ፡፡ አቶ ሐሰን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “ከኢየሱስ ሞት በኋላ…” የሚል ሐረግ በመጠቀም የኢየሱስን ሞት ሲገልጹ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው (ገፅ 43)፡፡ በሌሎች ቦታዎች ላይ ግን የኢየሱስን ስቅለት አጥብቀው ሲቃወሙና ክርስቲያኖችን ሲኮንኑ ይታያሉ (ገፅ 172-173 እንዲሁም ገፅ 158)፡፡ እንዲህ ዓይነት ግጭት መፍጠራቸው ሰውየው በማስተዋል ሆነው ሲጽፉ እንዳልነበር ያሳያል፡፡ ለማንኛውም ወደ ዋናው ነጥባችን እንመለስ፡፡

አቶ ሐሰን ወንጌላት ለምን ሊታመኑ እንደማይገባ ሲገልጹ በጽሑፍ የሰፈሩት “ከኢየሱስ ሞት ከዘመናት በኋላ ስለሆነ ነው” የሚል መከራከርያ አቅርበዋል፡፡ እሳቸው ከተናገሩት በተጻራሪ ወንጌላት በዓይን ምስክሮችና በቅርብ ወዳጆቻቸው እንደተጻፉና ዘገባቸው እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ሊመሰክር በሚችለው “የመስቀሉ ትውልድ” ዘመን ተጽፈው መጠናቀቃቸውን ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡

ኡስታዙ በወንጌላት ላይ የሰነዘሩት ሒስ መሠረተ ቢስ በመሆኑ ምክንያት ከድምዳሜያቸው ጋር ባንስማማም ዳሩ ግን በሙግታቸው ውስጥ ከተንጸባረቀው መርህ ጋር እንስማማለን፡፡ አንድ ዘገባ ከሚያስነብበው ታሪክ ጋር ያለው የዘመን ልዩነት እየሰፋ በሄደ ቁጥር አፈታሪክ በውስጡ ሊቀላቀል መቻሉ እሙን ነው፡፡ ስለዚህ በሙግታቸው ውስጥ ያንጸባረቁትን ይህንን ነጥብ በመያዝ፤ ከቁርኣን ጸሐፊና ከወንጌላት ጸሐፊያን ለኢየሱስ ዘመን የቀረቡት ማንኛቸው ናቸው? ብለን እንጠይቃለን፡፡ መልሱ ግልፅ ነው፡፡

የቁርኣን ጸሐፊ ከኢየሱስ ዘመን በ600 ዓመታት የራቀና የእስራኤልን መልክኣ ምድራዊ አቀማመጥ እንኳ በወጉ የማያውቅ ሰው መሆኑ ሊካድ የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ታድያ ከእርሱ ዘገባና ከወንጌላት ጸሐፍት ዘገባ መታመን ያለበት የማነው? ምናልባት አቶ ሐሰን “ቁርኣንን ለሙሐመድ የገለጠላቸው ጅብሪል ነው” የሚል ምላሽ ይሰጡ ይሆናል፡፡ ሆኖም ለዚህ ጭፍን እምነታቸው ሊያቀርቧቸው የሚችሏቸው “ማስረጃዎች” ሙሐመድ ካለፉ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉ እስላማዊ ትውፊቶች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ በተጠቀሙት ሙግት ውስጥ ባንጸባረቁት መርህ መሠረት ውድቅ ነው፡፡ ለሙሐመድ ቁርኣንን ጂብሪል እንደገለጠላቸው የጻፉት ግለሰቦች ከእሳቸው ሕልፈት ከክፍለ ዘመናት በኋላ የኖሩ በመሆናቸው ዘገባቸው አስተማማኝ ሊሆን አይችልም፡፡ ሙሐመድ ጂብሪል ተገልጦላቸው ቁርኣንን ሲሰጣቸው ያየ ምስክር ስለመኖሩ እነዚህ ትውፊቶች አይናገሩም፡፡ ያዩ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ለሙሐመድ ተገለጠላቸው የተባለው ጂብሪል እውነተኛው የእግዚአብሔር መልአክ ስለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠት አይችሉም፡፡ ለሙሐመድ ነቢይነት ብቸኛው ምስክር ራሳቸው ሙሐመድ ናቸው፡፡ ታድያ “ተገለጠልኝ” ያሉት ቁርኣን እንዴት ሆኖ ነው በመጀመርያው ክፍለዘመን በዓይን ምስክሮችና በወዳጆቻቸው የተጻፉትን ጽሑፎች ሊያርም የሚችለው? ማስረጃዎች ሁሉ የሚያሳዩት የቁርኣን ዘገባ ሐሰት የመጽሐፍ ቅዱስ ግን እውነት መሆኑን ነው!

በሁለተኛው ክፍል ምላሻቸው ማርያም “የአሮን እህት” የመሰኘቷን ሚስጥር ለመፍታት ሞክረዋል (ገፅ 165-166)፡፡ ምላሻቸው በአጭሩ የድንግል ማርያም ወንድም አሮን ሌላ ሰው ነው የሚል ነው፡፡ ይህንን ምላሽ ደግሞ ሙሐመድ የነጅራን ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ጥያቄ ባቀረቡላቸው ጊዜ ከሰጡት ምላሽ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ የሐዲሱን ዘገባ እንዲህ ጽፈውታል፡-

የአላህ መልእክተኛ ወደ ነጅራን ዘንድ ላኩኝ፡፡ ከዝያ ስደርስ፡- ‹‹ቁርአናችሁ መርየምን የሐሩን እህት ይላት የለምን?›› በማለት ጠየቁኝ፡፡ አዎ አልኳቸው፡፡ ‹‹በሙሣና በኢሳ መካከል ይህን ያህል የዘመን ርቀት መኖሩንስ ታውቁ የለምን?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ወደ አላህ መልእክተኛ በመመለስ የጠየቁኝን ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹አይሁዶች ልጆቻቸውን በነብያትና በደጋግ ሰዎች ስም እንደሚጠሩ አትነግራቸውም ነበርን?›› አሉኝ፡፡ (ገፅ 166)

አቶ ሐሰን ሐዲሱን በትክክል አልተረጎሙትም፡፡ ትክክለኛው ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡-

“When I came to Najran, they (the Christians of Najran) asked me:  You read “Sister of Harun”, (i.e. Mary), in the Qur’an, whereas Moses was born well before Jesus. When I came back to Allah’s Messenger I asked him about that, and he said:  “The (people of the old age) used to give names (to their persons) after the names of Apostle and pious persons who had gone before them.””

“ሙጊራ ቢን ሹዐባ እንዳስተላለፈው፡- ወደ ነጅራን በደረስኩ ጊዜ (የነጅራን ክርስቲያኖች) እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረቡለኝ፡- ‹‹ሙሴ ከኢየሱስ በብዙ ዘመናት በመቅደም የተወለደ ሆኖ ሳለ በቁርኣን ውስጥ “የአሮን እህት ሆይ” ብላችሁ ታነብቡ የለምን?›› ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ተመልሼ በሄድኩ ጊዜ ስለ ጉዳዩ ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፡- “(የጥንቶቹ ሕዝቦች ሰዎቻቸውን) ከእነርሱ ቀድመው በኖሩት መልእክተኞችና ደጋግ ሰዎች ይሰይሙ ነበር”፡፡[6]

በዚህ ሐዲስ ውስጥ የተጠቀሰው የሙሐመድ ንግግር አሻሚ በመሆኑ ለተለያዩ ትርጓሜዎች ተጋልጧል፡፡ ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት ማርያም የአሮን እህት የተባለችበትን ምክንያት ሲገልጹ ከአሮን ዘር የተገኘች በመሆኗ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ድንግል ማርያም በሰናይ ምግባሯ የታወቀች በመሆኗ ምክንያት ዘይቤያዊ በሆነ መንገድ “የአሮን እህት” ተብላ መጠራቷን ይናገራሉ፡፡[7] በአይሁድ ልማድ መሠረት ሰዎች ከእነርሱ ቀድመው ከኖሩት ቅዱሳን ሰዎች ወይም የጎሣ አባቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚገለጸው “እህትና ወንድም” በሚል ሳይሆን “አባትና ልጅ” በሚል በመሆኑ እነዚህ ትርጓሜዎች የሚያስኬዱ አይደሉም፡፡

ሌላው የትርጓሜ አማራጭ አቶ ሐሰን ያቀረቡት ነው፡፡ ይህ ትርጓሜ ብዙ እውነታዎችን ችላ በማለት በሙሐመድ ነቢይነት በጭፍን ማመንን የሚጠይቅ ነው፡፡ ትርጓሜውን ልንቀበል የማንችልባቸውን ጥቂት ምክንያቶች ለመጥቀስ ያህል፡-

  1. በቁርኣን መሠረት ድንግል ማርያም የአሮን እህት መሆኗ ብቻ ሳይሆን “የኢምራን ልጅ” መሆኗም ጭምር ተገልጿል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የአሮን፣ የሙሴና የነቢይቱ ማርያም አባት ስም እንበረም ይሰኛል፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ ሙሴን ሙሳ፣ አሮንን ሐሩን እንዳላቸው ሁሉ እንበረምን ኢምራን ብሎታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው ማስረጃ በተጨማሪ እስላማዊ ትውፊቶች ሙሴን “ሙሳ ኢብን ኢምራን” በማለት ይጠሩታል፡፡[8] ይህ ደግሞ ድንግል ማርያም በቁርኣን “የአሮን እህት”ና “የኢምራን ልጅ” መባሏ በአጋጣሚ አለመሆኑን በማስረዳት በቸልታ እንዳናልፈው ያስገድደናል፡፡ አቶ ሐሰን ይህንን በመገንዘባቸው የድንግል ማርያም አባት ስም ማነው? የሚለውን ጥያቄ ለብቻው ነጥለው “ምላሽ” በመስጠት የአንባቢያንን ትኩረት ለመበተን ሞክረዋል፡፡
  2. የጌታ እናት ማርያም አሮን የተሰኘ ወንድም እንዳላትና የአባቷ ስም “ኢምራን” መባሉን የሚገልፅ ከቁርኣን ውጪ የሚገኝ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ለቁርኣን ታሪኮች ዋና ምንጮች በሆኑት የአፖክሪፋ ወንጌላት ውስጥ እንኳ አልተገለፀም፡፡
  3. በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ጥንታውያን በሆኑት የአይሁድ ድርሳናት መሠረት እንበረም (ኢምራን) የሚባል አባትና አሮን (ሀሩን) የሚባል ወንድም እንደነበራት የተነገረላት ብቸኛ ሴት ነቢይቱ ማርያም ናት፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ አንድ ሰው በመምጣት “የእንበረም ልጅና የአሮን እህት” ስለሆነችው ማርያም ቢናገር የጠቀሳት ማርያም በነዚህ ምንጮች ውስጥ ከተጠቀሰችው የተለየች እንደሆነች ማሰብ እንዴት ይቻላል?
  4. የቁርኣን ጸሐፊ የግለሰቦችን ማንነት ሲያምታታና በቦታና በዘመን የማይገናኙትን ታሪኮች ሲያገናኝ የመጀመርያ ጊዜው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-
  • ሱራ 40፡36-37 ላይ በሙሴ ዘመን የነበረውን ፈርዖንን፣ በአስቴር ዘመን የኖረውን ሐማንና የረጅሙን ግንብ ታሪክ አንድ ላይ በመስፋት አቅርቧቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እነዚህ ሦስት ታሪኮች በጊዜና በቦታ የማይገኙ ናቸው፡፡ የፈርኦን ታሪክ በዘጸአት 7-9፣ ሐማ በአስቴር 3፣ የግንቡ ታሪክ ደግሞ በዘፍጥረት 11 ላይ ይገኛሉ፡፡
  • ሱራ 2፡249 ላይ የጌድዎንን ታሪክ የሳዖል በማስመሰል አቅርቧል፡፡
  • ሱራ 17፡1 ላይ ሙሐመድ ወደ “ሩቁ መስጊድ” (በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው መስጅድ አል አቅሳ) እንደሄዱ ይናገራል፡፡ እስላማዊ ትውፊቶች ሙሐመድ ወደ መስጊዱ በመግባት ሰላት እንደሰገዱ ይናገራሉ፡፡[9] ነገር ግን በሙሐመድ ዘመን መስጊድም ሆነ ቤተ መቅደስ በቦታው ላይ አልነበረም፡፡

ብዙ ተመሳሳይ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የቁርኣን ጸሐፊ እንዲህ ዓይነቶቹን ታሪካዊ ስህተቶች የመሥራት ዕድሉ የሰፋ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያምን በተመለከተ ስህተት አለመሥራቱን ለማመን የሚያበቃ ምን ዋስትና አለን?

የነጅራን ክርስቲያኖች ይህንን ስህተት ነቅሰው በማውጣት ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ ሙሐመድ የመለሱት ምላሽ ቀደም ሲል የፈጠሩትን ስህተት ለመሸፈን የተፈጠረ ፈጣን ምላሽ (Ad hoc) መሆኑን ከላይ ከጠቀስናቸው ነጥቦች መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎች ችላ በማለት የሙሐመድን ምላሽ ለማመን ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ መሆናቸውንና አለመዋሸታቸውን አስቀድሞ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ነቢይ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ ካለመኖሩም በላይ በተፃራሪው እንድናምን የሚያስገድዱ ብዙ ምክንያቶች ስላሉ ሙሐመድ ተሳስተዋል ደግሞም ስህተታቸው ሲጋለጥ እውነታውን አድበስብሰዋል እንላለን፡፡

  • የዘካርያስ ስዕለትና ምልክት

ካህኑ ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ መልአኩ ሲያበስረው ምልክት እንደጠየቀና ለሦስት ቀናት ያህል ዲዳ ሆኖ እንደቆየ ቁርኣን ይናገራል (የኢምራን ቤተሰብ 3፡41)፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ዘካሪያስ ዲዳ የሆነው ለምልክት ሳይሆን የመልአኩን ብስራት ባለማመኑ ነበር፡፡ ጊዜውም ሦስት ቀናት ሳይሆን ለዘጠኝ ወራት ያህል ነበር (ሉቃ 1፡5-76)፡፡ አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

የመጽሐፍ ‹‹ቅዱስ›› ጸሐፊዎች ዘከርያ የአላህን መላአክ በመጠራጠራቸው መላእኩ ቁጣ እንዳወረደባቸው ይገልጻል፡፡ ‹‹ነብይ የአላህን መላእክ ተጠራጠረ›› መባሉ ስህተት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ግና መጽሐፍ ‹‹ቅዱስ›› ለነብያት ክብር የለውም… (ገፅ 170)

አቶ ሐሰን መጽሐፍ ቅዱስን በማብጠልጠል ብዙ ያልተገቡ ነገሮችን የተናገሩ ቢሆንም ዋናው ነጥባቸው “ነቢይ መልአክን ሊጠራጠር አይችልም” የሚል ነው፡፡ ለዚህ ሦስት ምላሾች አሉን፡-

  1. የመጥምቁ ዮሐንስ አባት ዘካርያስ ካህን እንጂ ነቢይ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተገለጸም (ሉቃ. 1፡9)፡፡ አቶ ሐሰን እስላማዊ አስተሳሰባቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው፡፡
  2. መጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ኃጢአት ሊሠሩ እንደማይችሉ አይናገርም፡፡ ይልቁኑ እንደ እኛው የእግዚአብሔር ምሕረት የሚያሻቸው ሥጋ ለባሾች እንደሆኑ ይናገራል፡፡
  3. “ነቢይ መልአክን ሊጠራጠር አይችልም” የሚለው አባባላቸው ትክክል ከሆነ ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ ላይሆኑ ነው! መጀመርያ ጂብሪል በሒራ ዋሻ ውስጥ ባገኛቸው ጊዜ “መልአክ ሳይሆን ሰይጣን ይዞኛል” የሚል ፍርሃት አድሮባቸው ነበር፡፡[10] ዘካርያስ የተጠራጠረው የመልአኩን ቃል ሲሆን ሙሐመድ ግን “የመልአኩን” ማንነት ነበር የተጠራጠሩት፡፡ የፈጣሪን መልአክ “ሰይጣን ነው” ብሎ ከመጠራጠር የበለጠ ምን ኃጢአት አለ?

የቁርኣን ትረካ ትክክል ሊሆን የማይችልባቸውን ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል በቁርኣን መሠረት ዮሐንስ “የሕያ” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የእብራይስጡ አጠራር “ዮሐናን” ሲሆን በአረብኛ መጽሐፍ ቅዱስ “ዩሐና” ተብሏል፡፡ ስሞች ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላው ሲሸጋገሩ ለቋንቋዎቹ ተናጋሪዎች ሊመች በሚችል መንገድ ለውጥ እንደሚደረግባቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጡ ከዋናው ቋንቋ መሠረታዊ በሆነ መንገድ ከራቀ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ “የሕያ” የሚለው የቁርኣን አጠራር “ዮሐናን” ከሚለው የእብራይስጥ አጠራር በጣም የተለየና ትርጉም አልባ በመሆኑ ትክክል አይደለም፡፡ ሌላው ስህተት ቁርኣን ከዮሐንስ በፊት በስሙ የተጠራ ሌላ ሰው አለመኖሩን መናገሩ ነው፡፡

«ዘከሪያ ሆይ! እኛ በወንድ ልጅ ስሙ የሕያ በኾነ ከዚህ በፊት ሞክሼን ባላደረግንለት እናበስርሃለን» (አለው)፡፡ (የማርያም ምዕራፍ 19፡7)

አልጀለላይን የተሰኙ ሁለት ዕውቅ የቁርኣን ተንታኞች ይህንን ጥቅስ ሲያብራሩት “ከእርሱ በፊት በዚህ ስም የተጠራ ሰው የለም ማለት ነው” ብለዋል፡፡[11] ኢብን አባስ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ሊቅ ይህንን ሐሳብ ይጋራል፡፡[12] ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ (2ነገ. 25፡23፣ 1ና 3፡15፣ 24፣ 6-9፣ ዕዝራ 8፡12)፣ በብሉይ ኪዳን አፖክሪፋና (1መቃብያን 2፡1-2፣ 16፡19) በሌሎች መጻሕፍት ውስጥ ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት በዚህ ስም የተጠሩ ብዙ ሰዎች ተጠቅሰዋል፡፡[13]

እንዲህ ያሉ ታሪካዊ ግድፈቶች የሚታዩበትን የቁርአኑን ትረካ ትክክል ነው ብሎ መቀበል እንዴት ይቻላል?

  • የኢየሱስ የመጀመርያው ተዓምር

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የኢየሱስ የመጀመርያው ተዓምር ውሃን ወደ ወይንጠጅ መለወጥ ሲሆን (ዮሐ. 2፡1-11) በቁርኣን መሠረት በአንቀልባ ውስጥ ሆኖ መናገሩ ነው (ሱራ መርየም 19፡30-31)፡፡ አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

… የኢሣ ከአንቀልባ ሳይወርድ የመናገር ተአምር የወንጌል ጸሐፊዎች ከዘነጓቸው ወይም ካላወቋቸው እውነታዎች መካከል ሲሆን ቁርኣን ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ አድርጎታል፡፡ የወይንጠጅ ተአምር እውነት ስላልሆነ ቁርኣን አንጓሎ ትቶታል፡፡ ደግሞስ እየሱስን የሚያህል ታላቅ የአላህ ነቢይ እርም የሆነውን የአስካሪ መጠጥ ጠምቆ (ተአምር ሰርቶ) ታዳሚዎችን ማሳከሩ ተገቢ ነውን?… (ገፅ 172)

የኢሣን ከአንቀልባ ሳይወርድ የመናገር “ተዓምር” ለመጥቀስ የቁርኣን ጸሐፊ የመጀመርያው ሰው እንደሆነ በመናገራቸው አቶ ሐሰን ቅጥፈት ፈጽመዋል፡፡ ይህ “ተዓምር” በሙሐመድ ዘመን በምድረ አረብ ውስጥ በታወቀ “የህፃንነቱ ወንጌል” በተሰኘ የተረታ ተረት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡[14] “ተዓምሩ” ተረት እንጂ እውነት ባለመሆኑ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ አለመጠቀሱ ትክክልና ተገቢ ነው፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሚገኘው የኢየሱስ የመጀመርያው ተዓምር የዓይን ምስክር በነበረው በሐዋርያው ዮሐንስ የተጻፈ እንጂ እንደ ቁርኣን ከተረት መጽሐፍ ላይ የተገለበጠ አይደለም (ዮሐ. 21፡24)፡፡

በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወይን በአይሁድ ዘንድ ትልቅ ቦታ ነበረው፡፡ ሠርግ ላይ የወይን ጠጅ ቢያልቅ የሚያስከትለው ሐፍረት “ወጥ አለቀ” ቢባል ከሚያስከትለው ሐፍረት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ጌታችን መለኮታዊ ኃይሉን በመጠቀም ያንን ቤተሰብ ከሐፍረት ታድጓል፡፡ በተፈጥሮ ላይ መለኮታዊ ስልጣን ያለው መሆኑንም አሳይቷል፡፡

የሚገርመው ነገር የቁርአኑ አላህ በምድር ላይ የከለከለውን ወይን በሰማይ መፍቀዱ ነው (ሱራ 47፡15፣ 83፡22-25)፡፡ ሙስሊም ወንዶች ወይን እየጠጡ ከደናግላን ሴቶች ጋር እንደሚተኙ ቁርኣን ይናገራል (ሱራ 55፡70-74፣ 78፡33)፡፡ አቶ ሐሰን በጀነት ውስጥ የሚገኘው ወይን አስካሪ እንዳልሆነ ይነግሩን ይሆናል፡፡ ታድያ ጌታችን በተዓምራዊ ኃይሉ ወደ ወይን የለወጠው ውሃ አስካሪ ስለመሆኑ ምን ማስረጃ ይሰጡናል?

  • የኢየሱስ ስቅለት

በመጽሐፍ ቅዱስና በቁርኣን መካከል ከሚገኙት ዋና ዋና ግጭቶች መካከል አንዱ የኢየሱስን ስቅለት በተመለከተ በሁለቱ መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩት ሐሳቦች ናቸው፡፡ አቶ ሐሰን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

… የስቅለት ጽንሰ ሐሳብ ያለ ጥርጥር በ4ኛው ክፍለ ዘመን ወደ እየሱስ ታሪክ የተቀላቀለ ሐሰት ነው፡፡ ምክንያት አልባ ሆኖም እናገኘዋለን፡፡ አሐዳውያን ክርስቲያኖች ሲቃወሙት ኖረዋል፡፡ በዚህ የተነሳም በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ተጨፍጭፈዋል፡፡ (ገፅ 172)

ኡስታዙ ለዚህ አባባላቸው ዋቢ የሚሆን ምንም ዓይነት ማስረጃ አልጠቀሱም፤ ሊጠቅሱም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም አባባሉ የግል ፈጠራቸው እንጂ ማስረጃ ያለው አይደለምና፡፡

የኢየሱስን ስቅለት በተመለከተ ከአራቱ ወንጌላት በተጨማሪ በዘመኑ በነበሩት የታሪክ ምሑራን የተጻፉ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

  1. ሮማዊው ጸሐፌ ታሪክ ቆርኖሌዎስ ታሲተስ የኢየሱስን ስቅለት ጽፏል፡፡[15]
  2. አይሁዳዊው ጸሐፌ ታሪክ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን የኢየሱስን ስቅለት በማያሻማ ቃል ጽፏል፡፡[16]
  3. የባቢሎናውያን ታልሙድ ኢየሱስ በፋሲካ ዋዜማ መሰቀሉን ይናገራል፡፡[17]
  4. ኢስጦኢክ ፈላስፋ የነበረው ማራ በር ሰራፒዮን ለልጁ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ የኢየሱስን ሞት ጠቅሷል፡፡[18]
  5. ሉሺያን የተሰኘ ግሪካዊ ጸሐፊ ኢየሱስ መገደሉን ጽፏል፡፡[19]
  6. ፍሌጎን የተሰኘ ሮማዊ ጸሐፊ ስለ ኢየሱስ መሰቀል ብቻ ሳይሆን በስቅለቱ ወቅት በምድር ላይ ስለወደቀው ጨለማና ስለ ምድር መናወጥ እንዲሁም ስለ ትንሣኤው ጽፏል፡፡[20]

ከነዚህ በተጨማሪ ከአዲስ ኪዳን ውጪ የኢየሱስ ሞት ተዘግቦ የምናገኘው በጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች ውስጥ ነው፡፡ የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ የክርስቶስን ሞት ደጋግሞ የጻፈ ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከጽሑፎቹ መካከል በአንዱ ውስጥ “ስለ ኃጢአታችን እስከ ሞት ድረስ መከራን የተቀበለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ…” በማለት አስፍሯል፡፡ የፖሊካርፕ ወዳጅ የነበረው የእስክንድርያው ኢግናጢዎስ በበኩሉ “በእውነት መከራን ተቀብሎ ከሞተ በኋላ ተነስቷል… ጌታችንን የሰቀሉት ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው ሰዎች ነበሩ” በማለት ጽፏል፡፡[21] የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያን ጸሐፊ የነበረው ዮስቶኒዮስ ሰማዕትም ትሪፎ ለተሰኘ አይሁዳዊ በሰጠው ምላሽ በእርሱ ዘመን የነበሩት አይሁድ ኢየሱስን “የተሰቀለ ገሊላዊ” በማለት ይጠሩት እንደነበር ጽፏል፡፡[22]

እነዚህ ሁሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች በአንደኛው ክፍለመንና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ከመወለዱ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት ስለ ስቅለቱ ቅዱሳን ነቢያት ተንብየዋል (ኢሳ. 53፡1-12፣ ዳን. 9፡24-25፣ መዝ. 22፡12-18)፡፡ ታድያ አቶ ሐሰን “የስቅለት ጽንሰ ሐሳብ ያለ ጥርጥር በ4ው ክፍለ ዘመን ወደ ኢየሱስ ታሪክ የተቀላቀለ ሐሰት ነው” ብለው በድፍረት የተናገሩት በምን ማስረጃ ነው? በማስረጃ ያልተደገፉ ባዶ ቃላትን በድፍረት በመናገር እውነትን ሐሰት፣ ሐሰትን ደግሞ እውነት ማድረግ የሚቻል መስሏቸው ይሆን?

አቶ ሐሰን ለኢየሱስ አለመሰቀል ሊያቀርቡ የሚችሉት ትልቁ “ማስረጃ” በቁርኣን ውስጥ በሱራ አል-ኒሳ 4፡157-158 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ስለ ክርስቶስ አለመሰቀል በቀጥታ እንደሚናገር የሚታመን የቁርኣን ብቸኛ ጥቅስ ሲሆን እንዲህ ይነበባል፡-

“እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (ረገምናቸው) ፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ነገር ግን ለነሱ (የተሰቀለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዝያ በሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡”

ሙስሊሞች በሙሉ ልብ የተቀበሉት ይህ ብቸኛ ዘገባ የተገኘው ከታሪካዊ ክስተቱ በጊዜም ሆነ በቦታ እጅግ ከራቀ ከአንድ ሰው ነው፡፡ ይህ ክስተት ከተፈፀመ ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኖረና ታሪኩ ከተከሰተበት ቦታ ቢያንስ በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ የኖረ የቦታውን መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ እንኳ በወጉ የማያውቀውን ሰው ሀሳብ ያለምንም ማስረጃ መቀበል ጭፍን እምነት አይሆንምን?

አቶ ሐሰን በዚህ ቦታ ላይ የውርስ ኃጢአትና በመስዋዕት የመቤዠትን አስተምህሮ በመቃወም ጽፈዋል፡፡ እነዚህ ሁለቱ አስተምህሮዎች “ሐሰት” መሆናቸውን በከረረ ንግግር ገልጸዋል (ገፅ 172-173)፡፡ አቶ ሐሰን ያላስተዋሉት አንድ ነገር ቢኖር የሰው ልጆች የአዳምን ኃጢአት መውረሳቸው በጥንታዊያን ሙስሊሞች ይታመን የነበረ መሆኑን ነው፡፡ የዘመናችን ሙስሊሞች የውርስ ኃጢአትን መካዳቸው በተፈጥሮ ከሚታያው እውነታ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍታቸውም ጭምር እንዲጣሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡ አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡ «ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡” (ሱራ 2፡36-38)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው “ሁላችሁም” የሚለው በአረብኛ ከሁለት በላይ ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ፍርዱ በአዳምና በሔዋን ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ያሳያል፡፡[23] አላህ የአዳምን ንስሐ እንደተቀበለ ተነግሯል ነገር ግን ከገነት መባረሩ አላህ ኃጢአቱን ይቅር እንዳላለ ያሳያል፡፡ ኃጢአቱን ይቅር ቢለው ኖሮ ለምን ወደ ገነት አልመለሰውም ነበር? ፀፀቱን ተቀብሎ ኃጢአቱን ይቅር ከማለት ይልቅ ፀፀቱን ተቀብሎ ወደ ፊት ለዘሮቹ የሚሆን መመርያን ለመስጠትና ይህንን መመርያ የተከተለውን ሰው ብቻ ለመማር እንደወሰነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡

ቲርሚዚ ሐዲስ አዳም የሠራው ኃጢአት ወደ ዘሮቹ ሁሉ መተላለፉን እንዲህ በማለት ይገልፃል፡-

“አደም ስለ ካደ ዘሮቹ ሁሉ ካዱ፡፡ አደም ዝንጉ በመሆን የተለከለከለውን ዛፍ ስለበላ ዘሮቹም ዝንጉዎች ሆኑ፡፡ አደም ስለተሳሳተ ዘሮቹ ሁሉ ስህተት ፈፀሙ፡፡”[24]

አልቡኻሪ ደግሞ ሙሴ አዳምን “ከገነት እንድንባረር ያደረከን አንተ አባታችን ነህ” በማለት በወቀሰው ጊዜ አዳም መልሶ “አላህ ከመፈጠሬ ከአርባ ዓመታት በፊት ወስኖልኝ ለጻፈብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን?” በማለት እንደመለሰለት ዘግቧል፡፡[25]

ሳሂህ ሙስሊም “ከገነት ያስባረራችሁ የአባታችሁ የአደም ኃጢአት ነው” ይላል፡፡[26]

እስላማዊ ምንጮች ከዚህም አልፈው ሴቶች “እስከዛሬ ድረስ ለሚያሳዩት ጸባይ” ሔዋንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡-

“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- በእስራኤል ልጆች ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሥጋ ባልበሰበሰ ነበር፡፡ በሐዋ ምክንያት ባይሆን ኖሮ የትኛዋም ሴት ባሏን ባልከዳች ነበር፡፡”[27]

በተጨማሪም አል-ጠበሪ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ጸሐፊ ሴቶች የወር አበባ የሚፈስሳቸውና “በአስተሳሰብ ደካማ የሆኑት”[28] በሔዋን ምክንያት እንደሆነ ጽፏል፡፡[29]

አቶ ሐሰን የውርስን ኃጢአት ለመካድ ተከታዩን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሰዋል፡-

“አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል፡፡” (ዘዳ. 24፡16)

ይህ ጥቅስ የወንጀለኛ መቅጫን የሚደነግግ እንጂ ከውርስ ኃጢአት ጋር የሚገናኝ ነገር የለውም፡፡ እስራኤላውያን አባቶች ለሠሩት ወንጀል ልጆቻቸውን እንዳይገድሉ የሚናገር ነው፡፡ አቶ ሐሰን ይህ ጥቅስ ከአዳም ስለወረስነው ኃጢአት እንደሚናገር የሚያምኑ ከሆነ አላህ አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ዘሮቹ ሁሉ ከገነት ውጪ ሆነው ለመከራና ለሥቃይ እንዲጋለጡ ማድረጉን እንዴት ያዩታል?

እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ፡-

አምላክ የሰውን ልጅ ሐጢአት ለመማር የሆሊውድ ፊልም ወደሚመስል ተውኔት ሂደት ውስጥ ማለፉን ለምን መረጠ? ይቅር ብያችኋለሁ ማለቱ በቂ አይደለምን? (ገፅ 173)

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የኃጢአት ውጤቱ ሞት ነው (ምሳሌ 10፡16፣ ሮሜ 6፡23)፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የፍቅር አምላክ የሆነውን ያህል የፍትህም አምላክ ነው (ኢሳይያስ 28፡17፣ 61፡8፣ ምሳሌ 24፡12፣ ሮሜ 1፡18-32፣ 2፡5)፡፡ የፍትህ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ያለ ቅጣት ኃጢአተኛን ማሰናበት ከባሕርዩ ጋር ይጣረሳል፡፡ ነገር ግን የፍቅር አምላክ በመሆኑ ምክንያት ደግሞ የሰው ልጆች ለዘለዓለም ከእርሱ ተለይተው እንዲጠፉ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍትህ ባለዕዳዎች የሆንነውን እኛን እዳችንን በመክፈል ነፃ የሚያወጣንን ቤዛ በማዘጋጀት ፍትሃዊ ባሕርዩን ሳይጣረስ ፍቅሩን ገለጠልን፡፡ ኢየሱስ መሰቀሉ የእግዚአብሔር ፍትህ ከፍቅሩ ጋር ሳይጣረስ ይቅር እንዲለን አስችሎታል፡፡ እስልምናን ጨምሮ ከክርስትና ውጪ የሚገኝ የትኛውም ሃይማኖት የፈጣሪ ምህረት ፍትሃዊ ባሕርዩን ሳይጣረስ ለሰው ልጆች የኃጢአት ይቅርታ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ማቅረብ አይችልም፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ስላዘነልን እንዳንጠፋ ሲል አንድያ ልጁ በቅዱስ ደሙ ይዋጀን ዘንድ ላከልን (ሮሜ 5፡6-8)፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአትን ያለ ቅጣት ዝም ብሎ ይቅር ማለት አለበት የሚለው አመለካከት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነትና ምህረት እንጂ ፍትሃዊ ባሕርዩንና ለኃጢአት ያለውን አመለካከት ያገናዘበ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡

  • ለመስዋዕት የተመረጠው ይስሐቅ ወይስ እስማኤል?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አብርሃም እንዲሰዋው የታዘዘው ልጅ ይስሐቅ ሲሆን በቁርኣን ግን የልጁ ማንነት አልተጠቀሰም፡፡ አቶ ሐሰን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኢልን እንዲያርዱ በአላህ መታዘዛቸው በቁርኣን ተተርኳል (ገፅ 173)

ይህንን ብለው ሱራ 37፡100-107 ላይ የሚገኘውን ተከታዩን የቁርኣን ክፍል ጠቅሰዋል፡፡

“ጌታዬ ሆይ! ከመልካሞቹ የሆነን (ልጅ) ስጠኝ፡፡ ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም አበሰርነው፡፡ ከእርሱ ጋርም ለሥራ በደረሰ ጊዜ «ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ እኔ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ «አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ሥራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ» አለ፡፡ ሁለቱም ትዕዛዙን በተቀበሉና በግንባሩም ጎን ላይ በጣለው ጊዜ (የሆነው ሆነ)፡፡ ጠራነውም፤ (አልነው) «ኢብራሂም ሆይ! ራእይቱን በእውነት አረጋገጥክ፡፡» እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡”

አቶ ሐሰን ከተናገሩት በተጻራሪ ይህ የቁርኣን ክፍል ለመስዋዕት የቀረበውን ልጅ ማንነት በግልፅ አይናገርም፡፡ ነገር ግን በውስጠ አዋቂነት ለመስዋዕት የቀረበው ልጅ ይስሐቅ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ቁርኣን በተከታዮቹ ጥቅሶች ላይ ይስሐቅን በተመለከተ አብርሃም መበሰሩን ይናገራል፡-

“መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን (በልጅ) ብስራት በእርግጥ መጡት፡፡ ሰላም አሉት፡፡ ሰላም አላቸው፡፡ ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ፡፡ እጆቻቸውም ወደ እርሱ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው፡፡ ከነሱም ፍርሃት ተሰማው፡፡ «አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና» አሉት፡፡ ሚስቱም የቆመች ስትኾን (አትፍራ አሉት) ሳቀችም፡፡ በኢስሐቅም አበሰርናት፡፡ ከኢስሐቅም በኋላ (በልጁ) በያዕቁብ (አበሰርናት)፡፡” (11፡69-73)

በኢስሐቅም አበሰርነው፡፡ ከመልካሞቹ የሆነ ነቢይ ሲሆን፡፡” (37፡112)

በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ተመሳሳይ ታሪክ እናገኛለን፡-

“እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ፡፡ እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርስዋ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ፡፡” (ዘፍ. 17፡15-16)

ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት ለመስዋዕት በቀረበው ልጅ ማንነት ዙርያ ስምምነት የላቸውም፡፡ ከኋለኞቹ ሊቃውንት መካከል አብዛኞቹ እስማኤል መሆኑን ቢናገሩም ከጥንት ሊቃውንት መካከል ብዙዎቹ ይስሐቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡[30] የኢስላም ኢንሳይክሎፒድያ ውስጥ ተከታዩ ተጽፏል፡-

“የተጠቀሰው የቁርኣን አንቀፅ ለመስዋዕት የቀረበው ልጅ ማን እንደሆነ አይናገርም፡፡ ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት ለመስዋዕት የታሰበው እስማኤል መሆኑን ይናገራሉ … ነገር ግን አል-ታላቢ የተሰኘው ቀደምት ትውፊት በአፅንዖት እንደሚገልጸው አስሃባ እና ታቢዑን፣ ማለትም የነቢዩ ወዳጆችና ከዑመር ኢብን ኸጧብ ጀምሮ እስከ ከዕብ አል-አሕባር ድረስ የሚገኙት ወገኖች ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አቋም አልነበራቸውም፡፡[31]

ኢብን አባስ የተሰኘ የሙሐመድ ወዳጅ የነበረ ሙስሊም ጸሐፊ ለመስዋዕት የቀረበው ልጅ እስማኤል ይሁን ይስሐቅ እርግጠኛ ባልሆነ አነጋገር ሁለቱንም በመጥቀስ ጽፏል፡፡[32] ሁለቱ ጃለሎችም ሙስሊም ሊቃውንት ለመስዋዕት በቀረበው ልጅ ማንነት ዙርያ አንድ ዓይነት አቋም እንደሌላቸው ጽፈዋል፡፡[33]

አል ጠበሪ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ሊቅ ሱራ 37፡100-107 ላይ የተገለጸው የመስዋዕቱ ልጅ ይስሐቅ መሆኑን ጽፏል፡፡[34] ዘገባውም የተላለፈው ከነቢዩ ሙሐመድ መሆኑን በመግለጽ የዘገባ አስተላላፊዎቹን ስም ዘርዝሯል፡፡[35] ሙስናድ አሕመድ ኢብን ሐንበል ሐዲስ ውስጥ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡-

“አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ለመሰዋት ሲዘጋጅ ልጁ እንዲህ አለው፣ ‹አባቴ ሆይ እንዳልፈራና የኔ ደም በአንተ ላይ እንዳይረጭ እሰረኝ…›”[36]

ሚሽካት አል-መሳቢህ በተሰኘ የሐዲስ ስብስብ ውስጥ እንዲህ ተጽፏል፡-

“ሙሐመድ ኢብን አል-ሙንተሸር እንዳስተላለፈው አላህ ከጠላቶቹ ቢታደገው ራሱን ለመሰዋት ስዕለት የተሳለ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ኢብን አባስን ለምክር በጠየቀው ጊዜ መስሩቅን እንዲያማክረው ነገረው፡፡ እርሱን ባማከረ ጊዜ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠው፡- ‹‹ራስህን አትሰዋ ምክንያቱም አማኝ ከሆንክ አማኝ ነፍስ ትገድላለህና ከሃዲ ከሆንክ ደግሞ ወደ ገሃነም ትፈጥናለህና፤ ነገር ግን በግ በመግዛት ለድኾች ስትል መስዋዕት አድርግ ምክንያቱም ይስሐቅ ካንተ የተሻለ ሆኖ ሳለ በበግ ተዋጅቷልና፡፡›› ጉዳዩን ለኢብን አባስ ባወጋው ጊዜ ‹‹እኔም ልነግርህ የፈለኩት ውሳኔ ይኸው ነበር›› በማለት መለሰለት፡፡”[37]

መጽሐፍ ቅዱሳችን የመስዋዕቱ ልጅ ይስሐቅ መሆኑን በግልፅ ስለሚናገር በድንግዝግዝ የተሞላውን የሰባተኛ ክፍለ ዘመን መጽሐፍ የምንቀበልበት ምንም ዓይነት ምክያት የለም፡፡ ሙስሊም ወገኖች የመስዋዕቱ ልጅ እስማኤል መሆኑን እንድናምንላቸው ጥረት ከማድረጋቸው በፊት በጉዳዩ ዙርያ በገዛ ሊቃውንታቸው መካከል የሚገኙትን ልዩነቶች ማስታረቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡

አቶ ሐሰን ዘፍጥረት 22፡9 ላይ ይስሐቅ የአብርሃም አንድያ ልጅ መሆኑ እንደተነገረ በመግለጽ ተከታዩን ሙግት ያቀርባሉ፡-

እስማኤል የኢስሐቅ ታላቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንዲያርድ የታዘዘው ኢስሐቅን ቢሆን ኖሮ አንድዬ ልጅ የሚለው ትርጉም ያጣል፡፡ ምክያቱም ሁለት ልጆች ነበሩትና፡፡ ኢብራሂም አንድዬ ልጅ ሊኖረው የሚችለው ኢስሐቅ ከመወለዱ በፊት ነው፡፡ እርሱም እስማኤል ነው፡፡ (ገፅ 174)

ይስሐቅ የአብርሃም አንድ ልጅ መሆኑ የተገለጸው በተከታዮቹ ምክንያቶች ነው፡-

  1. ይስሐቅ ብቸኛው የቃልኪዳን ልጅ ነው (ዘፍ. 17:15-21)፡፡ ይህንን ሐቅ ቁርኣን እንኳ በግልፅ ይመሰክራል (ሱራ 11:69-73፣ 37:112-113፣ 51:24-30)፡፡
  2. ይስሐቅ በዕድሜና በመካንነት ምክንያት መውለድ ከማትችለው ከሣራ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ የተወለደ ልጅ ነው፡፡ እስማኤል ግን በተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደ ነው (17፡15-17፣ 18፡9-15፣ 21፡1-7፣ ገላትያ 4፡28-29)፡፡ ቁርኣንም ከዚህ ሐቅ ጋር ይስማማል (ሱራ 11፡69-73 51፡24-30)፡፡
  3. ከነዓንን እንደሚወርስ እግዚአብሔር ቃል ኪዳን የሰጠው በይስሐቅ በኩል ላለው የአብርሃም ዘር እንጂ በእስማኤል በኩል ለሚመጣው አይደለም (ዘፍ. 13፡14-18፡ 15፡18-21፣ 28፡13-14)፡፡
  4. እስማኤል ከእናቱ ጋር ስለተሰደደ በወቅቱ በቤት ውስጥ የነበረው ብቸኛው ልጅ ይስሐቅ ነበር (ዘፍ. 21፡9-21)፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን እንኳንስ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው የመስዋዕቱ ልጅ እስማኤል መሆኑን ሊያረጋግጡልን ይቅርና በገዛ ቁርአናቸው እንኳ ያንን ማድረግ አይችሉም፡፡ ስለዚህ የማያዋጣቸውን ክርክር በመተው እውነቱን ቢቀበሉ መልካም ይመስለናል፡፡

አቶ ሐሰን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

ክርስትያኖች የእስማኤልን ልጅነት አይቀበሉም፡፡ ለምን? ሲባሉ ከባርያይቱ ከሐጋር ስለተወለደ ይላሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ሐጋር እነርሱ እንደሚሉት እንኳ አገልጋይ አልነበረችም፡፡ ልክ እንደ ሳራ የኢብራሂም ሚስት እንጅ፡፡ ይህን እውነታ የታሪክ ምሑራን አረጋግጠዋል፡፡ (ገፅ 174-175)

እስማኤል የአብርሃም ልጅ መሆኑን የሚክድ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ አላጋጠመኝም፡፡ አቶ ሐሰን እንዲህ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ከየት እንዳመጡ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ፡፡ እኛ ክርስቲያኖች እስማኤል የቃልኪዳኑ ልጅ እንዳልሆነ እንጂ የአብርሃም ዘር ወይም ልጅ እንዳልሆነ አንናገርም፡፡[38] የቃልኪዳኑ ዘር እርሱ እንዳልሆ የምንናገርበት ምክንያት እንደ ተስፋው ቃል ስላልተወለደና እግዚአብሔር የአብርሃምን ቃል ኪዳን በእርሱ በኩል ስላላቆመ ነው፡፡ ይልቁኑ ለዚህ የተመረጠው እንደተስፋው ቃል ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ የተወለደው ይስሐቅ ነው (ዘፍ 17፡18-21፣ 21፡1-5)፡፡

ስለ አብርሃምና ስለ አጋር ማንነት የሚናገረው ዕድሜ ጠገብ የታሪክ ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ ማስረጃ አጋር የሣራ ባርያ መሆኗን እንጂ የአብርሃም ሚስት እንደነበረች አይናገርም፡፡ አቶ ሐሰን አጋር የአብርሃም “ሚስት” መሆኗን የታሪክ ምሑራን የትኛውን የጽሑፍና የአርኪዎሎጂ ማስረጃ ጠቅሰው እንዳረጋገጡ እንዲያስረዱን እንፈልጋለን፡፡

አንዳንድ ሙስሊሞች አጋር የአብርሃም ሚስት መሆኗን የሚያረጋግጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ፤ ማስረጃ ይሆናቸውም ዘንድ ተከታዩን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡-

“የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባሪያም ነበረቻት። ሦራም አብራምን፦ እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ምናልባት ከእርስዋ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርስዋ ግባ አለችው። አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር አሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች። ሦራም አብራምን፦ መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው። አብራምም ሦራን፦ እነሆ ባሪያሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦራም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች። የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው። እርሱም፦ የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም፦ እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች። የእግዚአብሔር መልአክም፦ ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት።” (ዘፍ. 16፡1-9)

“… ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው” የሚለው ቃል አጋር የአብርሃም ሕጋዊ ሚስት መሆኗን የሚገልፅ ሳይሆን በዚያች ምሽት ከአብርሃም ጋር በመተኛቷ ምክንያት በጨዋ አነጋገር የተነገረ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን የሚያመለክት ዘይቤያዊ ንግግር ነው፡፡ አጋር ከአብርሃም ጋር በመተኛቷ ምክንያት ደረጃዋ እንዳልተለወጠ ከአውዱ መረዳት ይቻላል፡፡ የዘፍጥረት ጸሐፊ አጋር ከአብርሃም ጋር ከተኛች በኋላም እንኳ ሣራ እመቤቷ መሆኗን ገልጿል፡፡ ሣራም “ባርያዬ” ብላ ጠርታታለች፡፡ አብርሃምም አጋር የሣራ ባርያ መሆኗን ገልጿል፡፡ ስትኮበልል ያገኛት መልአክም “የሦራ ባርያ” ብሎ ጠርቷታል፡፡ አጋርም ብትሆን ሣራን “እመቤቴ” ብላ ስትጠራት እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ የአጋር ደረጃ ከባርነት ወደ ሚስትነት ከፍ አላለም፡፡

ሙስሊም ወገኖች አጋር የአብርሃም ሚስት መሆኗን በተደጋጋሚና በአፅንዖት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን የሚናገር ሐሳብ በቁርኣንና በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ይኖር እንደሆን ለማወቅ ፍለጋ ብናደርግም ማግኘት አልቻልንም፡፡ ምናልባት ሙስሊም ሊቃውንት ያውቁ እንደሆን ቢያሳዩን ደስ ይለናል፡፡

በማስከተል አቶ ሐሰን አንድ አስገራሚ ነገር ጽፈዋል፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-

ሰዎችን ባርያና ጨዋ ብሎ መከፋፈልና ‹‹ባርያ›› ያሉትን ወገን ሕልውና መካድ አስከፊ ዘረኝነት አይደለምን? ይህ ዘረኝነት የቆዳ ቀለም መሠረት አድርጎ መንጸባረቁ ደግሞ ያሳዝናል፡፡ በክርስትያን የሐይማኖት ስእሎች የምናየው የሰይጣን ስእል ጥቁር (አፍሪካዊ) ሲሆን የመላእክትና የአምላክ ስእሎች ደግሞ ነጭ (አውሮፓዊ) ናቸው፡፡ እየሱስ የፍልስጥኤም ሰው ስለሆነ ቆዳው ቀይ ነው እንበል፡፡ መላእክት አውሮፓዊ መልክ እንዲይዙ መደረጉ ለምን ተፈለገ? ሌላው ቀርቶ ቤተ አምልኮዎቻቸው እንኳ የጥቁር፣ የነጭ ተብለው የተከፋፈሉበትን ሁኔታ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ ክርስትና ከሰው ልጅ እኩልነት ይልቅ ዘረኝነትን እና አድሎን መስበኩ አያሳዝንም? (ገፅ 175)

አቶ ሐሰን የሚጽፉት ነገር ያለቀባቸው ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል እንደተባለው እስማኤል የአብርሃም ልጅ መሆኑን የሚክድ ክርስቲያን የለም፡፡ የአብርሃም ዘር ነው፣ ከእርሱ ተወልዷል፣ ልጁ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ይስሐቅ የቃልኪዳን ዘር አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ነቢያት ሁሉ ከይስሐቅ ዘር የሆኑት፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ ያመነ ክርስቲያን ሁሉ በዘር፣ በቀለምና በፆታ ሳይለያይ እኩል መሆኑን አውጇል፡-

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡” (ገላ. 3፡28)

ይህንን መለኮታዊ አዋጅ በመተላለፍ ሰዎች መከፋፈልና መናናቅ ቢጀምሩ፣ አንዳቸው ለሌላቸው ደረጃ ቢመድቡ፣ ቤተ አምልኳቸውን ቢነጣጥሉ ከክርስትና መርህ በመውጣት የተሳሳቱት ሰዎቹ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን አመለካከቱና ምግባሩ የክርስትና መመርያ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ይለካል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በእርሱ አይለካም፡፡

በጥቁር አፍሪካዊውም ሆነ በነጭ አውሮፓዊው ባሕል መሠረት ጥቁር ቀለም ኀዘንና መጥፎ አጋጣሚን ነጭ ቀለም ደግሞ ደስታንና መልካም አጋጣሚን እንደሚወክል ይታወቃል፡፡ ይህ እንግዲህ በብርሃንና በጨለማ ምክንያት በሰው ልጆች አእምሮ ውስጥ በተፈጥሮ የተሳለ ምስል ነው፡፡ ይህ ነጩም ሆነ ጥቁሩ የሚስማማበት በመሆኑ ከዘረኝነት ጋር ምንም የሚያያዝ ነገር የለውም፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ታላላቅ አሕጉራት፣ ማለትም ኢስያን አፍሪካንና አውሮፓን በሚያገናኝ ቦታ በምድረ እስራኤል በመወለዱ ምክንያት ነጭም ጥቁርም አይደለም፡፡ (አቶ ሐሰን “ፍልስጥኤም” የሚባል አገር ባልነበረበት ዘመን የተወለደውን አይሁዳዊውን ኢየሱስን ፍልስጥኤማዊ ማድረጋቸው አስገራሚ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአይሁድ ሕዝብ ያላቸውን የመረረ ጥላቻና በልባቸው ውስጥ የሰረፀውን የዘረኝነት መንፈስ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡) የጥንቶቹ አይሁዳውያን የቆዳ ቀለም ነጭም ሆነ ጥቁር ሊባል እንደማይችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ኢየሱስን ነጭ አውሮፓዊ አስመስሎ መሳል በመካከለኛው ዘመን የተጀመረ ሲሆን ከዚያ ቀደም የተሳሉትን ምስሎች ስንመለከት ቡናማ ዓይነት ቀለም ያላቸው መሆኑን እናስተውላለን፡፡

ሰይጣንም ሆነ መላእክት መንፈሳዊያን ፍጥረታት በመሆናቸው የቆዳ ቀለም የላቸውም፡፡ በዘመናችን ተስለው የምናያቸው ምስሎች በሰው ሐሳብ የተፈጠሩ እንጂ የቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት እንደሌላቸው ማንኛውም ሃይማኖቱን የሚያውቅ ክርስቲያን ይገነዘባል፡፡ ሰይጣንን በጥቁር ሰው መመሰል በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ የተገለፀ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን እንደዚያ የሚል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን አቶ ሐሰን እንደ እውነተኛ ነቢይ ተቀብለው የሚሟገቱላቸው ሙሐመድ እንዲህ በማለት ሰይጣንና ጥቁር ሰው አመሳስለዋል፡-

“ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ሰይጣንን ማየት የሚፈልግ ሰው ነብጣል ኢብን አል-ሐሪሥን ይመልከተው!›› ጥቁር ሰው ሲሆን የተንጨባረረ ረጅም ፀጉርና ጥቁር መንጋጋዎች አሉት፡፡”[39]

የጥንት ሙስሊሞች ሙሐመድ ጥቁር መሆናቸውን የሚናገር ሰው ይገድሉ ነበር፡-

“የሰህኑን ወዳጅ የነበረው አሕመድ ኢብን አቢ ሱለይመን እንዲህ አለ፡- ‹‹ማንኛውም ነቢዩ ጥቁር እንደሆኑ የሚናገር ሰው ይገደላል፡፡ ነቢዩ ጥቁር አልነበሩም››፡፡”[40]

ሙሐመድ ጥቁር ባርያዎች እንደነበሯቸው በብዙ እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡[41] ጥቁር ባርያዎችንም በስጦታ ይቀበሉ እንደነበር ተነግሯል፡፡[42]

በአንድ ወቅት አንድ ባርያ በሁለት ጥቁር ባርያዎች እንደለወጡ እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ተጽፏል፡-

“ጃቢር ኢብን አብዱላህ እንዳስተላለፈው፡- አንድ ባርያ ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በመምጣት ቃል ኪዳን ያዘ፡፡ ነቢዩም ባርያ መሆኑን አላወቁም ነበር፡፡ አሳዳሪው በመምጣት ባርያው እንዲመለስለት በጠየቀ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ‹‹ሽጥልኝ›› አሉት? በሁለት ጥቁር ባርያዎችም ገዙት፡፡”[43]

አቶ ሐሰን በእስልምና ውስጥ ስለሚገኝ እኩልነት አጥብቀው ቢናገሩም እውነቱ እንደርሱ አይደለም፡፡ ጥቁር አፍሪካውያን በአረብ ሙስሊሞች ዘንድ እንዴት እንደሚታዩ ይታወቃል፡፡ ቁርኣን የሰው ልጆችን እኩልነት በሚክዱ መልእክቶች የተሞላ ነው፡፡ ስለ ሴቶች ከሚናገራቸው መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፡-

  • ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ ብልጫ አላቸው፡- 2፡88 “… ለነርሱም (ሴቶች) የዚያ በነሱ ላይ ያለባቸው (ግዳጅ) ብጤ በመልካም አኗኗር (በባሎቻቸው ላይ መብት) አላቸው፡፡ ለወንዶችም (ጣጣቸውን ስለሚሸከሙ) በነሱ ላይ ብልጫ አላቸው፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡”
  • ሴቶች ለባሎቻቸው እርሻ ስለሆኑ በፈለጉበት ሁኔታ “ሊደርሷቸው” ይችላሉ፡- 2፡223 “ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው፡፡ እርሻችሁን በፈለጋችሁት ሁኔታ ድረሱ”
  • ባሎች ሚስቶቻቸውን በመምታት መቅጣት ይችላሉ፡- 4፡34 “እነዚያም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገስፁዋቸው በመኝታዎችም ተለዩዋቸው (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም፡፡ ቢታዘዟችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ አላህ የበላይ ታላቅ ነውና፡፡”
  • የአንድ ወንድ ምስክርነት ከሁለት ሴቶች ምስክርነት ጋር እኩል ነው፡- 2፡282 “ከወንዶቻችሁም ሁለትን ምስክሮች አስመስክሩ፡፡ ሁለትም ወንዶች ባይሆኑ ከምስክሮች ሲሆኑ ከምትወዷቸው የሆኑን አንድ ወንድና አንድኛዋ ስትረሳ አንደኛዋን ታስታስውሳት ዘንድ ሁለት ሴቶች (ይመስክሩ)፡፡”

ድንቄም የሰው ልጅ እኩልነት!

ማጣቀሻዎች


[1] Ibn Katheer. Al-Bidaya wan Nahaya; Vol. 1, p. 139;

Al-Tabari. The History of al-Tabari; Vol. 1, p. 119 http://www.islamawareness.net/Prophets/ibrahim.html

[2] ለምሳሌ ያህል ተከታዩን ድረ-ገፅ በመጎብኘት ይህንን የቁርኣን ትርጉም ይመልከቱ http://www.alahazrat.net/alquran/Quran/006/006_074_081.html

[3] The Qur’an Dilemma; p. 254

[4] የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት በማቴዎስ ወንጌል ላይ የሚገኘው የኢየሱስ የዘር ሐረግ በዮሴፍ በኩል እንደሆነና በሉቃስ ወንጌል ላይ የሚገኘው ደግሞ በማርያም በኩል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የማርያም አባት ስም ኤሊ ነው የሚለው የሊቃውንት አቋም ጥንታውያን በሆኑት የአይሁድ ጽሑፎችም ጭምር ድጋፍ ያለው ነው፡፡

[5] በቅንፍ የተቀመጠው (ሐና) የሚለው በተርጓሚዎቹ የተጨመረ እንጂ የአረብኛው ቁርኣን ውስጥ አይገኝም፡፡ “የያዕቆብ ወንጌል” በተሰኘ ከቁርኣን በፊት በተጻፈ የአፖክሪፋ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

[6] Sahih Muslim; Book 25, Number 5326

[7] Arabic commentary of Al-Tabari on Sura 19:28, online edition፡ http://quran.al-islam.com/Tafseer/DispTafsser.asp?l=arb&taf=

TABARY&nType=1&nSora=19&nAya=28

[8] Sahih Muslim; Book 1, Number 0317

[9] Sahih Muslim; Book 001, Number 0309

[10] Ibn Ishaq, The Life of Muhammad, tr. Guillaume, 1967, p. 107

[11] https://quranx.com/tafsirs/19.7

[12] https://quranx.com/tafsirs/19.7

[13] ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረ ሌላ “ዮሐንስ” ጠቅሷል፤ Jewish War, 2.125

[14] Rev. W. ST Clair Tisdall. The Sources of Islam; p. 58

[15] Josh McDowell, Evidence that Demands a Verdict, New and Revised, 1999, pp. 122-123

[16] Ibid., p. 125

[17] Ibid., pp. 123-124

[18] Ibid., p. 123

[19] Norman L. Geislere, Encyclopedia of Christian Apologetics, 1999, p. 128

[20] Ibid.

[21] Ibid.

[22] Ibid.

[23] Tafsir Ibn Kathir, Abridged: part 1, Surah Al-Fatiah Surah Al-Baqarah, ayat 1 to 141, pp. 109-110

[24] Al-Tirmidhi Hadith, Number 37; (ALIM CD ROM Version)

[25] Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 77, Number 611

[26] Sahih Muslim, Book 001, Number 0380

[27] Sahih al-Bukhari, Volume 4, Book 55, Number 611. Sahih Muslim Book 008, Number 3472

[28] ክርስትና ሴቶች በአስተሳሰብ ደካሞች መሆናቸውን አያስተምርም፡፡

[29] The History of Al-Tabari: General Introduction from the Creation to the Flood, Translated by Franz Rosenthal, SUNY press, Albany, 1998, Volume 1, pp. 280-281

[30] Muhammad H. Haykal. The Life of Muhammad; trans. Isma’il Raji al-Faruqi [Islamic Book Trust Kuala Lumpur/American Trust Publishers, 1976], pp. 24-25

[31] Gibb and Kramers. A Shorter Encyclopaedia of Islam; p. 175

[32] anwîr al-Miqbâs min Tafsîr Ibn ‘Abbâs; Online Edition:

http://altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=73&tSoraNo=37&tAyahNo=102&tDisplay=yes&UserProfile=0

[33] Tafsir al-Jalalayn; Online Edition:

http://altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=74&tSoraNo=37&tAyahNo=107&tDisplay=yes&UserProfile=0

[34] Al-Tabari. The History of al-Tabari, Vol. II, Prophets and Patriarchs, trans. William M. Brenner [State University of New York Press, Albany 1987], p. 89)

[35] Ibid., pp. 82-83

[36] Musnad Ahmad, Number 2658

[37] Mishkat Al-Masabih English Translation With Explanatory Notes by Dr. James Robson, Volume I [Sh. Muhammad Ahsraf Publishers, Booksellers & Exporters, Lahore-Pakistan, Reprint 1990], p. 733

[38] ከያዕቆብ ልጆች መካከል አራቱ፣ ማለትም ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድና አሴር ከባርዎች የተወለዱ ቢሆኑም ከአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች መካከል ተቆጥረዋል፡፡ ዔሳውና ያዕቆብ ከርብቃ የተወለዱ መንትያ የይስሐቅ ልጆች ቢሆኑም የተስፋው ቃል በዔሳው በኩል ሳይሆን በያዕቆብ በኩል ቀጥሏል፡፡ ይህ የሚያመለክተን እስማኤል የቃል ኪዳን ዘር ያለመሆኑ ጉዳይ የእግዚአብሔር ሉኣላቂ ምርጫ እንጂ ከባርያ ከመወለዱ ጋር የተያያዘ አለመሆኑ ነው፡፡

[39] Ibn Ishaq, Sirat Rasulallah, translated as, The Life of Muhammad by A. Guillaume, page 243

[40] Qadi ‘Iyad Musa al-Yahsubi, Muhammad Messenger of Allah (Ash-Shifa of Qadi ‘Iyad), translated by Aisha Abdarrahman Bewley [Madinah Press, Inverness, Scotland, U.K. 1991; third reprint, paperback], p. 375 & 387

[41] Sahih Bukhari, Volume 9, Book 91, Number 368

[42] Malik’s Muwatta, Book 21, Number 21.13.25

[43] Sahih Muslim, Book 10, Number 3901

ለሐሰን ታጁ ምላሽ ዋናው ማውጫ