የዮናስ ምልክት ምንድር ነው?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋው በምድር ላይ በነበረ ሰዓት፥ አይሁዳውያን ምልክትን እንዲያሳያቸው ይጠይቁታል። ሰዎቹ ምልክትን የጠየቁት ላለማመናቸው ማመካኛ እንዲሆን ነበር። ጌታም መልስ ሲሰጣቸው፥ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት እንደማይሰጣቸው ይነግራቸዋል። (ማቴ 12:39-40)
እርሱም፥ ዮናስ በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሶስት ቀንና ሌሊት እንደነበር ሁሉ፥ የሰውም ልጅ ሶስት ቀንና ሌሊት በምድር ውስጥ ይኖራል። እንደ ክርስቶስ አስተምህሮ መሰረት፥ ለአይሁድ የሚሰጣቸው ምልክት ይህ ነው።
የዮናስ ሶስት ቀንና ሌሊት በአሳ ሆድ ውስጥ መሆን ምልክትነቱ እንዴት ነው?
የዮናስ ሶስት ቀንና ሌሊት በአሳ ሆድ ውስጥ መሆን ተአምርነቱ፥ ከአሳው ሆድ ውስጥ ወጥቶ መመለሱ ነው። በአሳው ተውጧል፥ በሆዱ ውስጥም ሶስት ቀንና ሌሊት አሳልፏል። ነገር ግን ከሶስት ቀንና ሌሊት በኋላ ከአሳው ሆድ በመተፋት ተመልሶ መጥቷል። ክስተቱን ተአምር ያደረገው ይህ ነው።
ስለዚህ ክርስቶስም ልክ ነቢዩ ዮናስ ሶስት ቀንና ሌሊት በአሳ ሆድ ውስጥ እንደ ነበር፥ የሰውም ልጅ በምደር ሆድ ውስጥ ይሆናል ሲል እያመለከተ የነበረው ይህንኑ ነው። ልክ ዮናስ ከሶስት ቀን በኋላ ከአሳው ሆድ ውስጥ እንደወጣ ሁሉ፥ የሰውም ልጅ በሶስተኛው ቀን ከመቃብሩ ይወጣል ማለት ነው። ይህ ነው ለአይሁድ የሚሰጣቸው ምልክት።
በሌላ ቋንቋ፥ ለአይሁድ የሚሰጣቸው ታላቁ ምልክት የክርስቶስ ትንሳኤ ነው!
ሙስሊሞች ግን በዚህ አስተምህሮ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። የዮናስ ምስስሎሽ ክርስቶስ ላለመሞቱና ከሞት ላለመነሳቱ ማሳያ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። በተለይ ታዋቂው ዳዒ ዛኪር ናይክ ይህን ሙግት በማቀንቀን ይታወቃል
የሙግታቸው ነጥብ ይህን ይመስላል፦
“ዮናስ ወደ አሳ ነባሪው ሆድ ሲገባ በሕይወት ነበር፥ በአሳ ነባሪው ሆድ ውስጥ ሳለም በሕይወት ነበር፥ ከአሳ ነባሪው ሆድ ሲወጣም በሕይወት ነበር። ክርስቶስ ደግሞ የዮናስ ታሪክ ለእርሱ ምሳሌ መሆኑን ተናግሯል። ስለዚህ ክርስቶስም ወደ መቃብሩ ሲገባ ሕያው ነበር፥ በመቃብሩ ውስጥ ሳለም ሕያው ነበር፥ ከመቃብሩ ሲወጣም ሕያው ነበር ማለት ነው። ስለዚህ በራሱ አስተምህሮ መሰረት፥ ክርስቶስ አልሞተም፥ ከሞትም አልተነሳም”
ይህ ሙግት የዮናስን ታሪክ በትክክል ካለመረዳት የመነጨ እጅግ የተሳሳተ መረዳት ነው። ምክንያቱም የዮናስን ታሪክ በጥንቃቄ ስናጠና፥ ዮናስ በአሳ ነባሪው በተዋጠ ጊዜ እንደሞተ፥ ከዚያም በሶስተኛው ቀን ከሞት እንደተነሳ እንረዳለን
ማስረጃዎቹን አንድ በአንድ እንመልከት፦
“ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ። በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ። (ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ 2:2-3)
በዚህ ስፍራ ዮናስ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ እንመለከታለን። ቁ.2 ግልፅ እንደሚያደርገው፥ ዮናስ ይህን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያደረሰው በአሳው ሆድ ውስጥ እያለ ነው። ይህ እጅግ ሊስተዋል የሚገባው ሀቅ ነው
ሌላው ልናስተውለው የሚገባን ነገር፥ በዮናስ ምዕራፍ 2 ላይ ያለውን ጸሎቱን ስንመለከት በአላፊ ግስ (past tense) እንደሆነ እንረዳለን። ይህ፥ ተከሰቱ ያላቸው ነገሮች በሙሉ ጸሎቱን ከመጸለዩ በፊት የተከሰቱ ነገሮች መሆናቸውን ያሳያል። እነዚያ ነገሮች ቀድመው ተከሰቱ፥ ከዚያም በኋላ ዮናስ በጸሎቱ በአላፊ ግስ ጠቀሳቸው። ይህም እጅግ ሊስተዋል የሚገባው ሌላ ነጥብ ነው
በቁ.3 ላይ ላይ እንደምናነበው፥ ዮናስ በሲኦል ሆድ ውስጥ ነበርኩ ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሰረት፥ ሰዎች ሲኦል የሚገቡት ሲሞቱ ነው።
“ክንዱም ወደ ነበሩት በአሕዛብም መካከል በጥላው ወደ ተቀመጡት፥ በሰይፍ ወደ ተገደሉት ሰዎች ወደ ሲኦል ከእርሱ ጋር ወረዱ።” (ትንቢተ ሕዝቅኤል 31:17)
“የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል።” (ትንቢተ ሕዝቅኤል 32:21)
“ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች።” (ትንቢተ ሆሴዕ 13:14)
“በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?” (መዝሙረ ዳዊት 6:5)
“አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ፤” (መዝሙረ ዳዊት 115:17)
“ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው?” (መዝሙረ ዳዊት 89:48)
“ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም።” (ትንቢተ ኢሳይያስ 38:18)
“ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና።” (መዝሙረ ዳዊት 55:15)
“ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ_ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ።” (የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1622-23)
ይህ ግልፅ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ነው። አንድ ሰው ወደ ሲኦል ወረደ ማለት ሞተ ማለት ነው። ሲኦል የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ያሉበት ቦታ ነው። ለዚያም ነው በመጨረሻው ቀን ሲኦልም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ የሚለው (ራዕ 20:13) ሲኦል የሞቱ ነፍሳት የሚሄዱበት ስፍራ ነውና።
ስለዚህ ዮናስም “በሲኦል ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮህኹ” ሲል፥ ሞቼ ነበር ማለቱ ነው። በሲኦል ሆድ ውስጥ ነበርኩ ማለት ሞቼ ነበር ማለት ነውና። በሲኦል ሳለ ወደ እግዚአብሔር እንደ ጮኸና እግዚአብሔር እንደሰማው የተናገረበት ክፍል ነው። ይህ ዮናስ በአሳው ሆድ ውስጥ እንደሞተ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ነገር ግን ከዮናስ ጸሎት የምንረዳው፥ በአሳ ነባሪው ሲዋጥ መሞቱን ብቻ አይደለም። ነገር ግን ከሞት መነሳቱን ጭምር እንጂ፦
“ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ።” (ትንቢተ ዮናስ 2:7)
በዚህ ስፍራ፥ ቁ.2 ላይ የጀመረውን ጸሎት ሲቀጥለው እንመለከታለን። በቁ.7 ላይ “ሕይወቴን ከጉድጓዱ አወጣህ” ይላል። “ጉድጓድ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ሻኻት/שַׁחַת” ሲሆን ትርጉሙ “መቃብር፥ ጥፋት፥ መበስበስ (corruption)፥ ጉድጓድ” ማለት ነው። ሙት መሆንን የሚያመለክት ቃል ነው
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ይህ ቃል ሙታን መሆንን ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው
“ነፍሱ ወደ ጕድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች።” (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 33:22)
“ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል። (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 33:18)
“ይህም ነፍሱን ከጕድጓድ ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው።” (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 33)
“ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥” (መዝሙረ ዳዊት 103:4)
“ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል፤ አይሞትም ወደ ጕድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም።” (ትንቢተ ኢሳይያስ 51:14)
“ለዘላለም እንዲኖር፥ ጥፋትንም እንዳያይ፤ የነፍሳቸው ለውጥ ከብሮአልና፥ ለዘላለምም ቀርቶአልና።” (መዝሙረ ዳዊት 49:8-9)
“ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን?” (መዝሙረ ዳዊት 30:9)
ይኸው “ሻኻት/שַׁחַת” የሚለው ቃል በሌላ አገባብ በዘጽ 12:23 ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፦
“እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም።” (ኦሪት ዘጸአት 12:23)
በዚህ ስፍራ፥ “አጥፊው” የሚለው ቃል በዮናስ 2:7 ላይ “ጥፋት” የሚለው ቃል ነው። ገዳይ፥ አውዳሚ፥ አጥፊ የሚል ትርጉም ይሰጣል። አጥፊው፥ አጥፊ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት የበኩር ልጆችን ለመግደል ስለተላከ ነው። የግብፅ የበኩር ልጆችን ገድሏል፥ የእስራኤልንም የበኩር ልጆች እንዳይገድል እግዚአብሔር በመቃናቸው ላይ ደም እንዲቀቡ አዘዘ። ያልገደላቸው ሊዚያ ነው
“አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ።” (ወደ ዕብራውያን 11:28)
ይህ በግልፅ አጥፊው እንደሚገድል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። አጥፊው የተባለው ስለሚገድል ነው። ስለዚህ ጥፋት (ሻኻት) ሞትን የሚያመለክት ቃል ነው ማለት ነው። አጥፊው፥ በዚህ ስም የተጠራው ለዚያ ነውና።
ከላይ በተጠቀሱት ክስተቶች በሙሉ “ጉድጓድ፥ ጥፋት/שַׁחַת” የሚለው ቃል ሞትን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ዮናስ ሕይወቴን ከጉድጓዱ መለስክ ሲል፥ ከሞት አስነሳኸኝ፥ መልሰህ ሕያው አደረከኝ ማለት ነው። ይህ ዮናስ ከሞት እንደተነሳ የሚያሳይ ግልፅ ማስረጃ ነው።
ልክ በ1 ነገሥት 17 እና በ2 ነገሥት 4 ላይ ነቢዩ ኤልሳዕ እንዳስነሳቸው ልጆች፥ ልክ በሉቃ 8 ላይ ጌታ እንዳስነሳት የመምህሩ ልጅ፥ ልክ እንደ አልዓዛር፥ ልክ በሐዋርያት ስራ 9 ላይ ሐዋሪያው ጴጥሮስ እንዳስነሳት ጣቢታ፥ ዮናስም ከሞት ተነስቷል። ለዚህ ነው ሕይወቴን ከጉድጓድ አወጣህ ያለው።
አንዳንዶቹ ይህን ሀሳብ ለመቃወም፥ ዮናስ ሕይወቴን ከጉድጓድ አወጣህ ሲል ከአሳ ነባሪው ሆድ መተፋቱን ለማመልከት ነው ይላሉ። ይህ ስህተት ነው። ምክንያቱም ዮናስ ይህን የተናገረው ከአሳው ሆድ ከመተፋቱ በፊት ነው። ቁ.2 ግልፅ እንደሚያደርገው፥ ጸሎቱን የጸለየው በአሳው ሆድ ውስጥ ሳለ ነው። ስለዚህ ሕይወቴን ከጉድጓዱ አወጣህ ያለው በአሳው ሆድ እያለ ነው። አሳው ዮናስን የተፋው ጸሎቱን ከጨረሰ በኋላ ነው። ስለዚህ ሕይወቴን አወጣህ ሲል መተፋቱን እያመለከተ አልነበረም። ከሞት መነሳቱን እንጂ
“እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፥ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው።” (ትንቢተ ዮናስ 2:11)
በተጨማሪም ከላይ ለማመልከት እንደሞከርነው፥ በዮናስ 2 ላይ የምንመለከተው ጸሎት በአላፊ ግስ (past tense) ነው። ይህ ማለት ሞቶ ከተነሳ በኋላ የጸለየው ጸሎት ነው ማለት ነው። በአሳው ሲዋጥ ሞተ፥ ስጋውም በአሳው ሆድ ውስጥ ሶስት ቀንና ሌሊት ቆየ
“እግዚአብሔርም ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ነበረ።” (ትንቢተ ዮናስ 2:1)
ነፍሱ ደግሞ በሲኦል ውስጥ ነበረች (ዮና 2:3) ከዛም በሶስተኛው ቀን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሳው (ዮና 2:7) ከተነሳ በኋላም ጸሎቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረበ። ለዚህ ነው ክስተቶቹን በሙሉ ያለፉ ክስተቶች መሆናቸውን የገለጸው።
በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር ላደረገለት ነገር ምስጋናን አቀረበለት። ሕይወቱን ከጉድጓድ መልሶታልና፦
“እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ” (ትንቢተ ዮናስ 2:10)
አስተውሉ! ዮናስ ምስጋናን እያቀረበ ያለው ከአሳው ሆድ ከመተፋቱ በፊት ነው። በአሳው ሆድ ውስጥ ሳለ እንኳ ምስጋናን ማቅረቡ፥ የምርም ሞቶ እንደተነሳ የሚያመለክት ነው። ቅድም ለመግለጽ እንደሞከርነው፥ ምስጋናውን ያቀረበው ከአሳው ሆድ ስለተተፋ አይደለም። ሳይተፋ ነው ያመሰገነው። ምስጋናውን ያቀረበው ከሞት ስለተነሳ ነውና።
ይህ ከክርስቶስ አንጻር እንዴት ይታያል?
ዮናስ በአሳው ሆድ ውስጥ ሞቶ ሶስት ቀንና ሌሊት እንደ ቆየው ሁሉ፥ ክርስቶስም ነፍሱ ከስጋው ተለይታ በምድር ልብ (በመቃብር) ሶስት ቀንና ሌሊት ቆይቶ ነበር (ዮሐ 20:1) ልክ የዮናስ ነፍስ በሲኦል እንደነበረች ሁሉ፥ የክርስቶስም ነፍስ እንዲሁ ወደ ሲኦል ወርዳ ነበር (ሐዋ 2:31) ልክ ዮናስ ከሞት እንደተነሳው ሁሉ፥ ክርስቶስም እንዲሁ ከሞት ተነስቷል (ሉቃ 24:5) ልክ ዮናስ ከአሳው ሆድ እንደ ወጣው ሁሉ፥ ክርስቶስም ከሞት በተነሳ ማንነት ከመቃብር ወጥቷል፥ በዚያ የለም (ማቴ 28:6)።
የዮናስ ምሳሌ ክርስቶስ አለመሞቱን እና ከሞት አለመነሳቱን የሚያሳይ አይደለም። ይልቁንም መሞቱን እና ከሞት መነሳቱን የሚያሳይ እንጂ። ክርስቶስ የዮናስን ታሪክ ለራሱ ጥላ መሆኑን መናገሩ፥ ፍጹም ትክክል ነው። ዮናስ ለመሲሁ ሞትና ትንሣኤ ምሳሌ ነውና። ስለዚህ የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ ለመቃወም የሚውለው ይህ ሙግት፥ ውድቅ ነው ማለት ነው።
- እስልምናና የመሲሁ ስቅለት
- ክርስቶስ ተሰቅሏልን? በአሕመድ ዲዳት እና ጆሽ ማክዱዌል መካከል የተደረገ ሙግት፡፡
- ኢየሱስ “አለመሰቀሉን” የሚያመለክቱ ጥንታውያን መዛግብት ይገኙ ይኾንን?
- የክርስቶስ ትንሣኤና የከፊል ሞት እሳቤ
- ስንት ሰዓት ተሰቀለ? በስንተኛው ቀንስ ተነሳ?